‘ደቦ’ አዲስ መጽሐፍ በስልሳ ደራስያን

Wednesday, 20 June 2018 12:53

 

                

አርታኢ፡-     እንዳለጌታ ከበደ።

አሳታሚ፡-    ፋንታሁን አቤ።

አከፋፋይ፡-    ሀሁ መጻሕፍት መደብር

…..

እነሆ ‘የደቦ’ መግቢያ!

….

መግቢያ

የዚህ መጽሐፍ አርታኢ፣ እንደዚህ ዓይነት መድበል ለማዘጋጀት ካሳበ ቆየ። ተግባር ላይ ሳያውለው የቀረው በትጋት ሳይሞክር ቀርቶ አልነበረም። ሌሎች ደራስያንና አሳታሚዎችም በርካታ ጸሐፍት የተሳተፉበት ተከታታይ መድበል ለማዘጋጀትና ለአንባብያኑ ለማድረስ በብዙ ሲመኙና ሲደክሙም አይቷል። ፍሬውን ማየት ቢያጓጓም ፈተናው ብዙ ነው - ድርሰቶቹን መሰብሰቡ፣ ስንዴውን ከገለባ ለይቶ ማስቀመጡ፣ የየድርሰቶቹን ባለቤት፣ ወይም ወራሽ፣ ወይም ሕጋዊ ተወካይ ማግኘቱ፣ ከሚመለከተው አካል ጋር መስማማቱ፣ አርትኦት ማድረጉ፣ አሳታሚና አከፋፋይ ማግኘቱ…ኧረ ምኑ ቅጡ! መንፈስን፣ ጉልበትን፣ ገንዘብን፣ ዕውቀትንም ይወስዳል፤ ይቆጣጠራልም።

እርግጥ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአስር በላይ የሆኑ የደራስያን ሥራዎች አሰባስቦ በአንድ ቅጽ ማሳተም ከተጀመረ ሰባ አምስት ዓመታት አልፎታል። ይልማ ደሬሳ፣ በ1933 ዓ.ም. ‘የአዲስ ዘመን መዝሙር ለነጻነት ክብር’ (እነ ከበደ ሚካኤል፣ ስንዱ ገብሩና ሌሎችም የተሳተፉበት) የሚል መድበል አዘጋጅተው ካሳተሙ በኋላ፣ (አልፎ አልፎም ቢሆን) አታሚዎችና አሳታሚዎች፣ የድርሰት ማኅበራት፣ ተቋማት፣ የሥነጽሑፍ ክበባትና ግለሰቦች በጋርዮሽ የተለያዩ መድበሎችን ለአንባብያን ሲያበረክቱ ተስተውሏል።

ይኸኛው ግን የተለየ ነው። ከ1990ዎቹ በፊት የተለያዩ ግጥሞችን ወይም አጫጭር ልብወለዶችን መርጦና ለይቶ የሚያሳትም እንጂ፣ ከየዘርፉ በየዓይነቱ አሰናድቶ መድበል ማሳተም የሚዘወተር አልነበረም። ወጎችን፣ መጣጥፎችንና (የጉዞ ማስታወሻው፣ ቃለ መጠይቁ፣ የምርምር ውጤቱ….) ግጥሞችን….አዳብሎ ማውጣት እምብዛም የተለመደ አልነበረም። እንደዚህ መድበል አዘጋጅና አርታኢ ንባብ፣ እንዲህ ዓይነቱን መንገድ የከፈተው፣ ጥርጊያ መንገዱን የዘረጋውና ስኬታማም የሆነው ተስፋዬ ገብረአብ ነው።

ተስፋዬ ‘እፍታ’ በሚል ርዕስ፣ በሁለት ዓመታት ውስጥ (ከ1992-93ዓ.ም) ብቻ በተከታታይ አምስት ዕትሞችን አወጣ፤ ነባርና ጀማሪ ደራስያንና ጋዜጠኞችን በአንድ ማዕድ እንዲቀርቡ አደረገ፤ ለደራስያኑ ብርታት ለአንባብያኑም አዲስ ቅመማ አዘጋጀ፤ ሥራውም ተወደደ፤ በየመገናኛ ብዙኃኑ ይተረክ፣ በሌሎች ጸሐፍትም ማጣቀሻ ይሆን ገባ። ግና ብዙዎቹ በተነቃቁበትና በተነቃነቁበት ጊዜ፣ ሲያገለግለው ከነበረ የኢሕአዴግ መንግሥት ጋር ተጋጨ። ከሀገርም ወጣ፤ እሱ ሲወጣ የተጀመረው በእንጭጩ ቀረ፤ ሊወጣ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ‘እፍታ ቅጽ አምስት’ን ለማስመረቅ በሚል ሰበብ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ባዘጋጀው የስንብት ፕሮግራም ላይ፣ ‘እኔ ይህን ነገር እስከ አምስት ቅጽ አድርሸዋለሁ፤ እናንተ ደግሞ ቀጥሉበት!’ አለና አደራ መሰል ኑዛዜ አስተላለፈ። ‘አደራ!’ ያላቸው የሚመለከታቸው አካላትም፣ ‘አንተው እንደጀመርክ…፤ ፈረሱም ሜዳውም አንተ እጅ ነው ያለው!’ አሉት እንጂ ርእዩን ለመቀበል ደግሞም ለመቀጠል ዝግጁነት ሳያሳዩ ቀሩ። ‘እፍታ’ እንደተጀመረ ቢቀጥል ኖሮ፣ ዛሬ ስንትና ስንቱን ቅጽ ባነበብነው፤ ባስነበብነው፤ በየቦታው ተበታትነው የነበሩ ጽሑፎችና ተራርቀው የነበሩ ደራስያንም ምንኛ በመንፈስ በተቀራረቡ!

እኛ ሀገር ሁሉንም ነገር እንደ አዲስ ከዜሮ መጀመር እንጂ በነበረው ላይ የመቀጠል ልማድ እንደሌለን በተደጋጋሚ እንተቻለንና፣ ‘ከበሽታው የለንበትም!’ ለማለት፣ ይሄኛው ዕትም ‘እፍታ’ ቅጽ ስድስት ልንለው ነበረ፤ ግና ‘ከሕግ አንጻር ያስጠይቃል’ የሚል በዛ። ከፈቃጁም ሆነ ከከልካዩ ጋር መነካካቱን፣ ጥላ መለካካቱን አልወደድነውም። እናም ‘እፍታ’ የሚለው ስያሜ ተተወና ሀገርኛ ሥያሜ ወጣለት። ‘ደቦ’ ተባለ!

እነሆ! በጋራ የበቀልንበት የሥነጽሑፍ እርሻ፤ በአብሮነት የጠነሰስነው የጥበብ ጠላ፤ ብሔርን፣ ጾታን፣ ሐይማኖትን መስፈርያ ሳያደርግ በኅብር የተዘመረ ኪናዊ ጭፈራ፤ በአንድነት የምንታደምበት፣ የምንደመምበት፣ ሣቅና ሀዘን፣ እሴትና ሀሴት የምንለዋወጥበት፣ ሰውን ከነሃሳቡ የምንመረምርበት ጎጆ!

ይህ ‘ደቦ’ በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ዕትም ቅጽ አንድ ብሎ አይቆምም የሚል ተስፋ አለኝ፤ ቢያንስ በዓመት አንድ ቅጽ ቢወጣ እንኳን ለደራስያኑም ሆነ ለአንባብያኑ የማይናቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ።

የሆነስ ሆነና፣ መድበሉን ለማዘጋጀት ለምን ተነሳሳን? ገፊ የሆኑ ምክንያቶቻችን በአጭሩ መግለጽ ተገቢ ነው።

አንደኛ/ ዘመን ተሻግረው ጥበቡን፣ ዘመኑንና የጸሐፊውን መንፈስ መግልጽ የሚችሉ አንዳንድ ድርሰቶች እንደ ዘበት ተበታትነው እንዳይቀሩ የመዘንጋት ዕጣም እንዳይገጥማቸው ለመታደግ፣ (ድርሰቶቹ ከዚህ ቀደም በጋዜጣ ወይም መጽሔት የተነበቡም ሆኑ በየትኛውም መገናኛ ብዙኃን ያልቀረቡ ሊሆኑ ይችላሉ) ሁለተኛ/ ከዚህ ቀደም በልጨኛ ሥራዎቻቸው የሚታወቁም ሆነ በተቃራኒው ደግሞ ከአንባብያን ጋር በቅጡ ያልተዋወቁ ጸሐፍት በአንድ መድበል ተካትትው እርስ በርስ እንዲናበቡና እንዲነበቡ ለማድረግ፣ ሦስተኛ/ አንባቢው በድርሰት አማካይነት የተለያዩ የሃሳብ ዓለማትን ብቻ ሳይሆን ልዩ ልዩ የአጻጻፍ መንገዶችን እንዲመለከት፣ እንዲያውቅ፣ እንዲጠይቅና እንዲዝናና ለማገዝ ነው።

በተረፈ ሁለተኛው ‘ደቦ’ም በከፊል ተዘጋጅቷል። ሁለተኛው ወይም ቀጣዮቹ ቅጾች ይህን፣ የመጀመርያውን ቢተካከሉት ምናልባትም ቢበልጡት እንጂ አያንሱትም ብለን እናምናለን። ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉም ይሄኛው ለአሁን፣ ያኛው ለሁለተኛው፣ ያኛው ደግሞ እግዜር ከፈቀደ ለሦስተኛው ቅጽ ይሆናሉ ብለን ያስቀመጥናቸው በርካታ ድርሰቶች በእጃችን አሉ። በዚህኛው ቅጽ ያላገኛችኋቸው አንዳንድ ተወዳጅ ነባርና አዳዲስ ደራስያን በቀጣዮቹ ‘ደቦ’ ይጠብቋችኋል።

በነገራችን ላይ፣ በዚህ መድበል የተካተቱ ስብስቦች የተጻፉበት ዘመን የመቶ ዓመታት ዕድሜን ይሸፍናል። ማለትም ድርሰቶቹ ከ1910 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ባሉ ዓመታት ውስጥ የተጻፉ ናቸው። ድርሰቶቹ በእነዚህ ዓመታት ለንባብ ይብቁ እንጂ የሚተርኩት ዘመን ግን ሰፊ ነው። አንዳንዶቹ ወደኋላ ይመለሳሉ፤ አንዳንዶቹ የነበሩበትን ዘመን ይገልጻሉ፤ አንዳንዶቹ የወደፊቱንም ለመተንበይ ይሞክራሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ መቼም የትም ዘመን አይሽራቸውም። ይኼ ድምዳሜ ወደ ውስጥ ስትገቡ የምታዩት ይሆናል። የተሳታፊዎቹ የዕድሜ ክልልም - በሕይወት ካሉት - ከ20ዎቹ አጋማሽ እስከ 80ዎቹ መጀመርያ ያሉ ናቸው።

አንባቢው ሊረዳቸው የሚገቡ አንድ ሁለት ነጥቦች አሉ። የየድርሰቱ ባለቤቶች፣ ወይም ሕጋዊ ወራሾች፣ ወይም የተወካዮቻቸው ፍቃድ ሳይታከልበት በዚህ መድበል የተካተተ አንድም ጽሑፍ እንዳይኖር ጥረት አድርገናል። በዚሁ አጋጣሚ ያለ አንዳች ድጋፍ ሰጪ አካል (በሃሳብም ሆነ በሂሳብ የሚረዳ አጋዥ ተቁዋም ሳይኖር) ይህንን መድበል አሌፍ ብለን ለማዘጋጀት ስንነሳሳ የእናንተ መልካም ፍቃድ ስለታከበት ነውና ምስጋና ይገባችኋል። ሌላው ነጥብ በተከታታይ የሚወጡ እነዚህን ቅጾች በሕይወት ላለ ጀግናችን መታወሻ እንዲሆን አድርገናል። በሕይወት የሌሉትን መዘከር ተገቢ እንደሆነ እናምናለን፤ ሆኖም ግን አላፊውን ለመዘከር ቋሚን ከምስጋና ማዕድ ማራቅ ተገቢ አይደለም ብለን ደግሞ አጥብቀን እናምናለን። ምስጋናችንን የምንገልጽበት አንዱ መንገድ ታሪካቸውና ሕይወታቸው ተጋርዶ እንዳይቀር ለሌሎች ፍንጭ መስጠት ነው።

ስለሆነም፣ ማስታወሻ እንዲሆነው ብለን በመድበሉ ላይ ስሙን የምናሰፍርለት ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ወይም ለኢትዮጵያ በመትጋት የሚታወቅ የውጭ ሀገር ሰው ስሙን መጥቀስ ብቻ በቂ እንዳይደለ ስላመንንበት፣ ስለተበረከተለት ግለሰብ የሚያስተዋውቅ ቃለ መጠይቅ እንዲካተት አድርገናል። ለምሳሌ ይህን መድበል ለገጣሚ ሰሎሞን ደሬሳ ስንሰጥ፣ ሰሎሞንን በጨረፍታም ቢሆን ለመረዳት ያግዝ ዘንድ ከሱራፌል ወንድሙ ጋር ያደረገውን ውብ ቃለ መጠይቅ አትመነዋል።

ያም ሆኖ አንድ ግለሰብ በዚህ ተከታታይ እንደሚሆን ተስፋ በምንጥልበት መድበላችን ለመታወስ የግድ የኪነጥበብ ሰው መሆን የለበትም።

ሲጠቃለል

እስከቻልነው ወደፊት እንገፋለን፤ ካልሆነም እችላለሁ ብሎ ቆርጦ ለተነሳና ሕልማችንን ሕልሙ ላደረገ/ ለነበረ አሳልፈን ሰጥተን ‘ራዕያችንን እናስቀጥላለን።’

ሥራው የተሳካ የሚሆነው ሁላችንም በደቦ ስንረባረብ ነው። ጻፉልን፤ ጽሑፉ በእኛ መመዘኛ መሰረት ይመጥናል ወይስ አይመጥንም ብለን እንናበበው እንደሆነ እንጂ ጸሐፊው ታዋቂ ነው ወይስ አይደለም ብለን የጸሐፊውን የጀርባ ታሪክ አናጠናም። እናም፣ ኑ! አውድማችን አውድማችሁ ይሁን፤ ተያይዘን ተጋግዘን በጥበብ መስክ እንሰማራ፤ በሕይወት በሌሉትም ሆነ ባሉት የብዕር ሰዎች መሃል ራሳችንን እንየው፤ ለአንባቢውም እንታየው!!!

                                         /እንዳለጌታ ከበደ/¾

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1660 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 932 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us