የአማርኛ ቋንቋ በእንግሊዝኛ መበረዝና የፖለቲካ አንደምታው

Wednesday, 18 July 2018 16:00

 

በፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ

 

መግቢያ


ቋንቋ የሰው ወይም የአንድ ህብረተሰብ የመግባቢያ ስልት ብቻ ሳይሆን የማንነት መገለጫም ነው። ስለዚህ ቋንቋን እንዳይጠቀሙበት በልዩ ልዩ ዘዴ መገደብ ወይም ቋንቋው አላድግ ብሎ ከከሰመ የቋንቋው ተጠቃሚ ህብረተሰብ ባዶ ቀፎ ይሆናል። የማንነት ቀውስ ውስጥም ይገባል።


ቅኝ ገዥዎች የቅኝ ግዛታዎቻቸው አገሮች ቋንቋዎች እንዲሞቱ፣ በቋንቋዎች መናገርና ባህላዊ እሴቶቻቸውን መከተል ህገወጥ መሆኑን አስረግጠው ነበር። ምክንያቱም የተገዥው ክፍል ቋንቋ መጠቀም ለምሳሌ: (የአፍሪካውያኖች) ኋላቀርነትን አመላካች ሲሆን የአውሮፓዊያኖችን ቋንቋ መማር የሥልጣኔ ምልክት አድርገውት ነበር። ስለዚህም የአውሮፓውያን ቋንቋ በአፍሪካውያኖች ላይ ተጭኖባቸው ነበር። የቋንቋ ቅኝ አገዛዝ (lingustic Imperialism) ይባላል። የአፍሪካ አገሮች ነፃ ወጥተው ሰንደቅ ዓላማቸውን ቢያውለበልቡና በአገራቸው ሰዎች ቢተዳደሩም ቋንቋቸው ግን ከኢትዮጵያ በስተቀር የቅኝ ገዥዎችን ወርሰው የእንግሊዝኛ፣ የፈረንሳይኛና የፖርቹጊዝ ቋንቋ ተናጋሪ አፍሪካኖች ተብለው ይጠራሉ። ስለሆነም አፍሪካዊ የእናት ወይም አፍ መፍቻ ቋንቋዎች ተዳክመዋል። አሁን የአፍሪካ የትምህርትና የምርምር ተቋማት የአፍ መፍቻ ቋንቋ መዳከምና የአውሮፓውያንን ቋንቋ መጠቀም በመማርና በማስተማር ሂደት ላይ ያመጣውን አሉታዊ አስተዋጽኦ እያጠኑ ነው።

 

የአፍ መፍቻ ቋንቋ እውቅና ማግኘትና ጠቀሜታው


የእናት ወይም የአፍ መፍቻ ቋንቋ አወንታዊ አስተዋጽኦን በመገንዘብና ቅርስ መሆኑ ታምኖበት የተባበሩት የዓለም መንግሥታት ድርጅት በየዓመቱ የካቲት (Februray 21) ዓለም አቀፍ የእናት ቋንቋ ቀን ብሎ ደንግጓል። እንዲሁም ዓለም አቀፍ የቋንቋ ዓመት ታውጇል። ይህ ሁሉ የአንድ አገር ቋንቋ መዘከር፣ መከበርና እውቅና ማግኘቱ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ያመለክታል። ቁም ነገሩ ግን ለራሳቸው ቋንቋ ክብር የሚሰጡ፣ የሚኮሩበትና ከፍ ከፍ የሚያደርጉት የቋንቋው ተናጋሪና ባለቤቶች እራሳቸው መሆን አለባቸው። የጋራ ቋንቋ (ዎች) ተመርጦ(ው) የወል ወይም ብሔራዊ ቋንቋ(ዎች) መኖሩም አስፈላጊ ነው። ይህ ህዝቡን ያቀራርባል። እንዲሁም ያስተሳስራል። እንደ ቋንቋው ተነጋሪ ቁጥርና ትስስር ታይቶም ከአንድ የበለጡ ቋንቋዎች ብሔራዊ ቋንቋ ይሆናሉ። ይህ ሁኔታ እንደ ኢትዮጵያ ላሉት አገሮች የፖለቲካ አንድምታ ብቻ ሳይሆን ባህላዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ትስስርን ያጎለብታል። በታሪካችንም ኩታ ገጠም የሆኑና ራቅ ያሉትም የኢትዮጵያውያን ቋንቋዎች እየተወራረሱና እየዳበሩ ኖረዋል። ይህም ይቀጥላል።


አፍሪካ በአሁኑ ጊዜ አንድ ቢሊዮን ህዝብ ሲኖራት ሁለት ሺህ አንድ መቶ የሚሆኑ ቋንቋዎች ያላት አህጉር ነች። እያንዳንዱ የአፍሪካ አገር ከአሥር ያላነሰ ቋንቋ አለው። አገራችን ኢትዮጵያ ከዘጠና በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት አገር ነች። ለዚህም ነው አንዳንዶች ብዙኃነ ቋንቋ (MULTI-LINGUAL) ተናጋሪዎች ሆነው በማደጋቸው (ለምሳሌ አማርኛና አፋን ኦሮሞ ወይም ትግርኛ) አፍ መፍቻ ቋንቋ አንዱን መምረጥ (እኔንም ጨምሮ) የሚያስቸግራቸው። ይህ ታላቅ ፀጋ ነው። ኢትዮጵያን ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ልዩ የሚያደርጋትና የሚያኮራትም የእራሷ ሥነ ጽሑፍ ያላትና አገር በቀል ቋንቋ አማርኛ የምትጠቀም ነች። ወደፊትም አፋን ኦሮሞና ሌሎችም አገራዊና መንግሥታዊ ቋንቋ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህንን ቅርስ (አገር በቀል ቋንቋ) መያዙና ማቆየቱ የውጪ አገር ቋንቋዎችን ለመማር ለምሳሌ እንግሊዝኛን ለመማር የቁልቁለት ጉዞ ያደርገዋል። ስለዚህ የእናት ወይም የአፍ መፍቻ ቋንቋ ጠቀሜታው ብዙ ነው።


አውሮፓውያን ለምሳሌ በአፍ መፍቻ፣ በእናትና በአገራዊ ቋንቋቸው ይኮሩበታል። በሌላ ቋንቋ እንዳይበረዝም በጣም ይጥራሉ። ፈረንሳዮች ቋንቋቸው በሌላ ቋንቋ ለምሣሌ በእንግሊዝኛ እንዳይበረዝ ከአገራዊ ልዑላዊነት እኩል ለቋንቋቸው ዘብ ይቆማሉ። ለነገሩ ቋንቋ ለአንድ አገር ልዑላዊነት መግለጫና የማንነት ማረጋገጫ ነው። በ1635 ዓ.ም. የተቋቋመው የፈረንሳይ የቋንቋ ማዕከል (አካዳሚ) እስካሁን ድረስ የአገሪቱን የቋንቋ ጥራትና ጥንካሬን ይከታተላል፤ ዘብ ይቆማል። አዲስ የሥራ ውጤቶች በእንግሊዝኛ ሲሠየሙ (ሲጠሩ) ፈረንሳዮች ግን ቋንቋቸውን በእንግሊዝኛ ላለመበረዝ ብለው በፈረንሳኛ ሥያሜ ያወጡለታል። በኢትዮጵያ በደርግ ዘመን እንዲሁ ከግዕዝ በመነሳት አንዳንድ አዳዲስ ቃላት ወደ አማርኛ ተተረጎመ ነበር። ስለዚህ አማርኛ በተለይ አሁን ከእንግሊዝኛ ቃላት ጋር ሳይዳቀል ወይም ሳይበረዝ በእራሱ የሚቆምና ሊዳብር የሚችል ቋንቋ ነው።

 

የአማርኛ ቋንቋ በእንግሊዝኛ ቃላት መበረዝ አሳሳቢነት


ከላይ እንደ መንደርደሪያ ሃሣብ ያቀረብኩት በአገራዊ ቋንቋ ዙሪያ ያሉትን አመለካከትና ታሪካዊ ይዘት ለማስጨበጥ ነበር። የዚህ የጽሑፌ መነሻ የሆነው ግን የአማርኛ ቋንቋ ጉራማይሌ እየሆነ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ለማመላከት ነው። እኔ የቋንቋ ወይም የሥነጽሑፍ ምሁር አይደለሁም። ነገር ግን በተካንኩበት የፖለቲካ ሳይንስ ጥናት በመነሳት ይህ አማርኛንና እንግሊዝኛ ቃላትን ቀላቅሎ (አንዳንዴም ግማሽ በግማሽ) መነገሩ ወደኋላ የሚያስከትለው የፖለቲካ አንድምታ እና አሉታዊ አስተዋጽኦ ስለአሳሰበኝ ነው። አምናለሁ፤ ብዙ ሰዎች ስለዚህ ሁኔታ ሳያስቡ የቀሩ አይመስለኝም። የቋንቋ መምህሮቻችንም አሁን የተበረዘ ቋንቋ ያስተምራሉ ብዬ አላምንም።


ቀደም ብዬ በመንደርደሪያው ላይ እንዳስቀመጥኩት ዲቃላ ወይም ጉራማይሌ በተለይ ራቅ ካለ አገር በመጣ ቋንቋ ታሪካዊ ሂደቱም ለየት ካለ ቋንቋ (እንግሊዘኛ) እስኪሰለች ድረስ ማሰባጠሩ ማንነታችንን ክፉኛ ይፈታተናል ብዬ አምናለሁ። ከጊዜ በኋላ ብሔራዊ ቋንቋችን አማርግሊዝ (አማርኛና እንግሊዝኛ ቅይጥ) እንዳይሆን እሰጋለሁ። ለምሳሌ የዚንባብዌ ህዝብ አብዛኛው የሾና ቋንቋ ተናጋሪ ነው። በዚንባብዌ ዩኒቨርስቲ የሚማሩት የሾና ቋንቋ ተናጋሪዎች ሾና እንግሊዝ (SHONA- ENGLISH) ቋንቋ ፈጥረው የሾና ተማሪዎች የወፍ ቋንቋ ሆኗል። መደበኛ ቋንቋ ሳይሆን የተማሪዎቹ መግባቢያ ቋንቋ ነው። የዩኒቨርሲቲው መደበኛ ቋንቋ እንግሊዝኛ ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናት ከእንግሊዚኛ በስተቀር የእናት ቋንቋቸውን አይቀላቀሉም ምክንያትም እንግሊዚኛ (የቅኝ ገዢ ቋንቋን) ተቀብለው ብሔራዊ ቋንቋ አድርገውታል።


ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት የገዢዎቻቸው ቋንቋ በግድ ተጭኖባቸዋል። የአፍሪካ ቋንቋቸው ኋላ ቀር ተብሎ እንዲያፍሩበት ተደርጓል። የአውሮፓ ቋንቋ መናገር መሠልጠን መስሏል። ስለዚህ ማንነትንና ነፃነትን ከሚፈታተን ሁኔታ ለመላቀቅና አፍሪካዊ የእናት ቋንቋ ማሳደግ የአቀበት ጉዞ ሆኖባቸዋል።


በአገራችን በኢትዮጵያ ከዘመናት በኋላ ቋንቋችን መላው ጠፍቶ የማንነት ቀውስ ውስጥ እንዳንገባ በተለይ ምሁራን፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የባህል አባቶችና ዜጎች በዚህ ጉዳይ ላይ አብይ ትኩረት መስጠት ያለባቸው ይመስለኛል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴራችን በቅርቡ ለጦር ኃይል አባላት ያደረጉት ጉራማይሌ ቋንቋ ብዙዎችን ሳያሳስብ የቀረ አይመስለኝም። የአገር መሪ ማለት አገር ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን የአገሩን ባህል፣ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ወዘተ በምሳሌነት መምራት ይጠበቅበታል።


ነገርግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብፅን ሲጎበኙ በአገራቸው ቋንቋ ጥርት ባለና በእንግሊዝኛ ባልተበረዘ አማርኛ መናገራቸው ራሳቸውንና አገራቸውን አስከብረዋል። በቅርቡ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስተር ናሬንድራ ሞዲ እንግሊዝኛውን ወደ ጎን ብለው ከፕሬዘደንት ትራምፕ ጎን ቆመው በሂንዲ መናገራቸው ህንዶችን አስደስቷል። ጃንሆይ አፄ ኃለሥላሴም ለአገራቸው ክብር ሲሉ በውጪ አገሮች በአማርኛ ይናገሩ ነበር። የአፍሪካ ህብረት (OAU) ሲመሠረት የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ በፈረንሳይኛ ይናገራሉ ተብለው ሲጠበቁ በአማርኛ ንግግራቸውን ሲጀምሩ አስተርጓሚዎቻቸው ግራ ተጋቡ ይባላል። በቅርቡ በሞት የተለየው ታዋቂው የአፍሪካ ጥናት ምሁር አሊ መዝሩኢ የጃንሆይን ምሳሌ በመከተል እንግሊዝኛውን ወደ ጎን ትቶ በአፍ መፍቻው ቋንቋ ጥርት ባለ በኪስዋሂሊ ስብሰባው ላይ እንደተናገር ገልጿል።


የአማርኛና የእንግሊዝኛ ጉራማይሌ ቅልቅል በተመለከተ አንዳንዴ ህዝባዊ መገናኛ አውታሮች ቃለምልልስ ሲያካሂዱ እንግዶቻቸው በአማርኛው ውስጥ እንግሊዝኛ ሲቀላቅሉባቸው ጋዜጠኞቹ “እንዲህ ማለቶ ነው ወይ?” እያሉ በአማርኛ ሲተረጉሙ ይደመጣል። የአማርኛው በእንግሊዝኛ መበረዝ በቅርቡ ጎልቶ ስለሚሰማ በተለይ ወጣቶች በጣም ሊያስቡበት ይገባል። ይህ የአዋቂነትና የሥልጣኔ ምልክት ሳይሆን ጥራዝ ነጠቅነት የማንነት ቀውስ ነው። ለነገሩ ቃል እንዳልታጣለት “ማዘር”ና “ፋዘር” ስንል ነው የተበላሸው። እማማና አባባ ማለት በልዩ ልዩ መልኩ በዓለም ሁሉ የህፃናት አፍ መፍቻ ዓለምአቀፋዊ ቋንቋ ናቸው።

 

መደምደሚያ


ለማጠቃለል ይህ የአማርኛ ቋንቋ በእንግሊዘኛ መበረዝ የፖለቲካ እንድምታው የአገሪቱንና የህዝቧን የማንነት ቀውስ (IDENTITIY CRISIS) ውስጥ ይጥላታል። ስለሆነም መታሰብ ያለበት ነው። በረዥም ጊዜ ታሪካችን፣ በሥነ ጽሑፍና በቋንቋችን መዳበር ላይ ጥላሸት አንቀባ። ወጣቱም ለሚከተለው ትውልድ ምን እንደሚያወርስ ማሰብ የግድ ይላል። የታሪክ ባለአደራነትም አለበት። ከአርባ ዓመታት በላይ ተሰዶ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ቋንቋውንና ማንነቱን አስጠብቆ ሲኖር በአዲሲቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ትውልድ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ። የቋንቋ ምሁራንና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዚህ ርዕስ ላይ እንዲወያዩበትና አቅጣጫ እንዲያስይዙ ይጠበቃል። የዓለምአቀፋዊነት (GLOBALIZATION) የአሉታዊ ገጹ ሰለባ እንዳንሆን መጠንቀቅም አለብን። አገሩ ቅኝ አልተገዛችም ብሎ በኩራት የሚናገረው ኢትዮጵያዊ ባህሉ ቅኝ ሲገዛ ምን ሊል ነው?

 

ምንጭ፤ ኢትዮ-ሚዲያ 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1104 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1018 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us