ዊሊያም ሼክስፒር 450 ዓመት ሆነው

Wednesday, 30 April 2014 13:54

በድንበሩ ስዩም

 

በዓለም የቲአትር ታሪክ ውስጥ ለ400 ዓመታት ተደጋግሞ የሚነገር ጥቅስ አለ። ይህ ጥቅስ የታላቁ ፀሐፌ -ተውኔት የዊሊያም ሼክስፒር ነው። ሼክስፒር ሲፅፍ እንዲህ አለ፡- ዓለም መድረክ ናት። በውስጧ ያሉት ሰዎችም ተዋናዮች ናቸው። በየጊዜው ወደ መድረክ ይመጣሉ ሕይወትን ተውነው ያልፋሉ” ብሎ ፅፏል። ይህን አባባል አያሌ የፍልስፍና፣ የሥነ-ፅሁፍና የታሪክ ምሁራን በጥናቶቻቸው ውስጥ ሲያሰፍሩት ኖረዋል።

ዊሊያም ሼክስፒር ከሀገሩ እንግሊዝ አልፎ የመላው ዓለም ልጅ ሆኗል። ምክንያቱም ስራዎቹ ያልተተረጎሙበት ሀገር የለም። አለምን በጥበብ ያስተሳሰረ ድንበር አልባ ፀሐፊ ነው። እ.ኤ.አ ኤፕሪል 23/1564 እንግሊዝ ውስጥ ስትራትፎርድ አፕኦን -አቮን ውስጥ የተወለደው ሼክስፒር አሁን ወደ እዚህች አለም ከመጣ 450 ዓመታት ሆነውታል። ይህም የልደት በአሉን ልዩ ልዩ ሀገሮች እያከበሩለትም ይገኛሉ። ምክንያቱም ሼክስፒር በቴአትሮቹ የሰው ዘርን ሁሉ አሳውቋል አስተምሯል፤ አፈላስፏልና ነው።

ሼክስፒር የቴአትር ሰው ቢሆንም ግን ቴአትሮቹ ከማህበራዊ ህይወት መገለጫነት ሁሉ አልፈው የሳይንስና የህክምና መመራመሪያዎች ሁሉ ለመሆን በቅተዋል። ለምሳሌ በአለም ላይ በሳይኮሎጂና በሳይካትሪ ምርምሩ በእጅጉ የሚታወቀው ሲግመንድ ፍሮይድ የሰውን ስነ-ልቦናዊ አስተሳሰብ ሲመራመር የሼክስፒር ሥራ የሆነውን ሐምሌት የተሰኘውን ቴአትር መሰረት አድርጎ ነበር። ከዚህ አልፎ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ፍልስፍናዎችን የሚያቀነቅኑ ሰዎች ሳይቀሩ የሼክስፒርን ገለፃዎች እየተዋሱ ለእንቅስቃሴያቸው ማራመጃ ተጠቅመውበታል።

የሼክስፒር ቴአትሮች በምድር እንግሊዝ ብቻ ታጥረው የሚቆዩ ባለመሆናቸው የሰው ዘር ሁሉ ለፍልስፍና፣ ለኪነ-ጥበብ፣ ለማህበራዊ ኑሮ፣ ለፖለቲካ እና ለመሳሰሉት አስተሳሰቦች ማራመጃ ተጠቅሞበታል እየተጠቀመበትም ይገኛል።

ዛሬ በአለም ላይ ናኝቶ የሚገኘው እንግሊዝኛ ቋንቋ አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ የሼክስፒር አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነው። በድርሰቶቹ አማካይነት ሰዎች የእንግሊዝኛን ቋንቋ ለማወቅ ለዘመናት ጥረት ሲያደርጉ ኖረዋል። ከዛሬ 400 አመት በፊት ይጠቀምበት የነበረው እንግሊዝኛ በአሁኑ ወቅት “ሼክስፒሪያን ኢንግሊሽ” /የሼክስፒር እንግሊዝኛ/ በመባል ይታወቃል። አሁን በስራ ላይ ካለው የእንግሊዝኛ ቋንቋ የሼክስፒር እንግሊዝኛ ይለያል። በዚህም የተነሳ የሼክስፒር ኢንግሊሽ እየተባለ ትምህርት ይሰጣል። በሼክስፒር እንግሊሽ ተምረው የሚመረቁ ሁሉ አሉ። የሼክስፒርን እንግሊዝኛ ማወቅ በራሱ በእጅጉ የሚያስከብር ሙያ ሆኖ እስከ ዛሬ ቀጥሏል።

ከኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ የሼክስፒርን እንግሊዝኛ በማወቅ እና በመተርጎምም ሁለት ሰዎችን በዋናነት ማንሳት እንችላለን። የሼክስፒር ስራ ወደ አማርኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የተተረጎመው ከዛሬ 70 ዓመታት በፊት ነበር። ተርጓሚዋ ደግሞ ሴት ኢትዮጵያዊት ነበረች። ሳራ ወርቅነህ ትባላለች። ሳራ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዶክተር የሀኪም ወርቅነህ እሼቱ ልጅ ናት። የተወለደችውና ያደገችው በእንግሊዞች ቋንቋ እና ባህል በመሆኑ የሼክስፒርን ኢንግሊሽ በስርዓት የምታውቅ ናት። በ1920ዎቹ አጋማሽ ላይ ማዕበል በሚል ርዕስ የሼክስፒርን ቴአትር ተርጉማለች። ቴአትሩ በእንግሊዝኛ The Tempest የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን በአማርኛ ቋንቋ የቴአትር ትርጉም የመጀመሪያው የሼክስፒር ሥራ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ሣራ ወርቅነህ በኢትዮጵያ የቴአትር ትርጉም አለም ውስጥ ፋና ወጊ ስትሆን ነገር ግን ስለ እሷ ስራዎችና አበርክቶዎች እምብዛም አይነገርም።

የሼክስፒርን እንግሊዝኛ በራሱ ጥረት እና ትጋት ተምሮ ያወቀው ኢትዮጵያዊ ባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ነው። ፀጋዬ ገ/መድህን እጅግ በጠለቀ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ምርምሩ እና እውቀቱ የሼክስፒርን ታላላቅ ስራዎች ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ያበረከተው ውለታ በእጅጉ ግዙፍ ነው። ፀጋዬ ሼክስፒርን ከኢትዮጵያኖች ጋር አንድ አድርጎት ኢትዮጵያዊ ደራሲም አድርጎታል።

ፀጋዬ ገና ወጣት ፀሐፌ -ተውኔት በነበረበት ወቅት ማለትም በ1950ዎቹ አጋማሽ ላይ ኦቴሎ እና ሐምሌት የተሰኙትን የሼክስፒርን ታላላቅ ትራጄዲ ቴአትሮችን በመተርጎም ታዋቂነትን አተረፈ። ሁለቱም ቴአትሮች ወደ ኢትዮጵያ የመድረክ አለም ሲመጡ አብዮተኛ ቴአትሮች ሆነው ነበር። አብዮተኝነታቸው ደግሞ በኪነ-ጥበቡ እና በስነ-ቋንቋው ዘርፍ ነበር።

ለምሳሌ ኦቴሎ የተሰኘው ቴአትር የተመልካችን ቀልብና ስሜት በመሳብ ወደር ያልተሰገኘለት ትራጄዲ ሆነ። ተመልካቾች በቴአትሩ ውስጥ የእኩይ ባህሪ ተሰጥቶት በሚሰራው ኢያጎ እና የዋህና ምስኪን በሆነችው ዴዝዴሙና መሀል በሚፈጠሩ ስሜት ኮርኳሪ ጉዳዮች እየተበሳጨ ወደ ሀይል እርምጃ ሁሉ የሚገባበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ በተጨማሪም ኦቴሎ ቴአትር በመድረክ ዝግጅትና በትወና ብቃትም ባለሙያዎቹ ያደጉበትና የጎለመሱበት ሲሆን በቴአትር ታሪካችን ውስጥም ሰፊ ድርሻ ያለውስራ ሆኖ ተመዝግቧል።

የሼክስፒር ማንነት በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላለማዊ እንዲሆን ካደረጉት ጉዳዮች ዋነኛው ደግሞ ሃምሌት የተሰኘው ትራጄዲ ቴአትሩ ነው። ሃምሌትን የተረጎመው ፀጋዬ ገ/መድህን ብዙ ጉዳዮችን ያሳየበት ስራው ነው። የመጀመሪያውና ዋነኛው ተብሎ የሚጠራው የአማርኛ ቋንቋን የገለፃ ጥበብ ያሳደገበት ትርጉም ነው። አማርኛ ቋንቋ በአለም ላይ ያሉ ታላላቅ ሃሳቦችን፣ ፍልስፍናዎችን፣ መግለፅ እንደሚችል ይህ ቴአትር ያሳያል። የቋንቋ ተመራማሪዎች ፀጋዬ በውብ አማርኛ ሼክስፒርን ወደ ኢትዮጵያ አመጣው የሚሉም አሉ። በትርጉም ላይ የተሰሩ የጥናትና ምርምር ወረቀቶችም እንደሚያመለክቱት ከሆነ ሃምሌት የተሰኘው ቴአትር በፀጋዬ ገ/መድህን አማካይነት ፍፁም ውበት በተላበሰ መልኩ ወደ አማርኛ ተመልሷል። ይህን ቴአትር ቀደም ባሉት ዘመናት እነ ተስፋየ ገሠሠ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ኃይሌ ገሪማ፣ ሰለሞን ደሬሳ፣ ስብሀት ገ/እግዚአብሔና ሌሎችም ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን ተውነውበታል። በኛ ዘመን ላይ ደግሞ ሙሉአለም ታደሰ ወፌ ይላን ሆና በተዋጣላት ሁኔታ ተውነዋለች። አሁን በቅርቡ ደግሞ ሙሉአለምና ግሩም ዘነበ ከዚሁ ከሃምሌት ቴአትር ላይ አንዱን ክፍል በራስ ሆቴል አዳራሽ ፖየቲክ ጃዝ ተብሎ በሚታወቀው የሥነ-ግጥም መድረክ ላይ ተጫውተውታል።

ዊሊያም ሼክስፒር ወደ ኢትዮጵያ የቴአትር ትርጉም ውስጥ በሰፊው የተዋወቀው ሰው ነው። ለምሳሌ ጁሊየስ ቄሳር በሚል ርዕስ ሌላኛው ቴአትር ተተርጉሟል። ከዚህ ሌላ ንጉስ ሊር እና ማክቤዝ የተሰኙትም ቴአትሮቹ ወደ ኢትዮጵያ ተተርጉመዋል። The mid summer night የተሰኘው ቴአትሩም በአማርኛ ተተርጉሞ ቀርቧል።

ታላቁ ባለቅኔ ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤልም በ1940ዎቹ ውስጥ ሮሚዮና ጁሌት ብለው የሼክስፒርን ስራ ተርጉመው ለኢትዮጵያ ህዝብ አቅርበዋል።

ሮሚዮ ሮሚዮ የልቤ ወለላ

አለውጠውም ፍቅርህን በሌላ

እያለች ጂለየት ለሮሚዮ የምታቀነቅንለት የፍቅር ድምፅ ነው። የቴአትርን ፍቅር በኢትዮጵያ ውስጥ የዘራ ትርጉም እንደሆነም አንዳንድ ሰነዶች ያመለክታሉ።

    የሼክስፒር ታላላቅ ቴአትሮች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በአማርኛ ብቻም አልተተረጎሙም። በትግርኛ ቋንቋም ተተርጉመዋል። ለምሳሌ ኪዳኔ ወ/እየሱስ የተባሉ ሰው ሮሚዮና ጁሌትን በትግርኛ ተርጉመውታል። ከዚህ ሌላ እኚው ሰው ጁሊየስ ቄሳር የተሰኘውን የሼክስፒርን ስራ በትግርኛ ተርጉመዋል። ዶ/ር ሚካኤል ገ/ህይወት የተባሉ ሰው እንዲሁ ኦቴሎን በትግርኛ ቋንቋ ተርጉመውታል። ባጠቃላይ ሲታይ የዛሬ 450 ዓመት እንግሊዝ ውስጥ የተወለደው ዊልያም ሼክስፒር ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለም ላይ ሁሉ ያሉ ሀገሮች ተርጉመውታል።

ይምረጡ
(25 ሰዎች መርጠዋል)
14832 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us