ታሪክን በማስተላለፍ ኢሕአፓ በደርግ ተበልጧል

Wednesday, 30 April 2014 13:56

በድንበሩ ስዩም

ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ትውልድ ነበር። ይህ ትውልድ በ1960ዎቹ ውስጥ ብቅ ያለ ነበር። ብቅ ሲል ታዲያ የለውጥ አቀንቃኝ ሆኖ

“ፋኖ ተሠማራ

ፋኖ ተሠማራ

እንደ ሆቺ ሚኒ

እንደ ቼኩ ቬራ”

እያለ በማቀንቀን የመጣ ትውልድ ነው። “ያ ትውልድ” ሆቺ ሚኒን እና ቼኩ ቬራን ነው ለህዝብ መቀስቀሻ የተጠቀመው። ሆቺ ሚኒም ሆነ ቼኩ ቬራ ኢትዮጵያዊያን አይደሉም። ከኢትዮጵያዊያን ጋር ማዕድ ቆርሰው፣ አብረው አድገውና ጎልምሰው የሚታወቁ አይደሉም። የባሕር ማዶ ሰዎች ናቸው። እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያን እነዚህ ሰዎች እነማን እንደሆኑ አያውቋቸውም። ስለዚህ እንደ ሆቺ ሚኒ እና እንደ ቼኩ ቬራ ፋኖ ሆኖ ሊሠማራ አልቻም። ያ ትውልድ ፋኖ ሊያሠማራ ፈልጎ ምሳሌ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ጀግና ያጣ ይመስላል። እነ አፄ ቴዎድሮስን፣ እነ አፄ ዮሐንስን እና እነ አፄ ምኒልክን እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ ጀግኖችን በምሣሌነት “ያ ትውልድ” አልተጠቀመም። ከጥቁር አለም ውስጥ ቅኝ አገዛዝን አሽቀንጥረው የጣሉትን የአድዋ ጀግኖችን እንደ ምሳሌ ከመውሰድ ይልቅ ባሕር አቋርጦ ሆቺ ሚኒ እና ቼኩ ቬራ ዘንድ የተጓዘ ትውልድ መጥቶ አልፏል።

ይህን ከላይ ያሰፈርኩትን ነገር እንደ መንደርደሪያ አቀረብኩት እንጂ ጉዳዬስ ሌላ ነው። ዛሬ ትንሽ ቆርቆር ብሎኝ ይህችን መጣጥፍ እንድፅፍ ያስገደደኝ ምክንያት “ያ ትውልድ” ውስጥ የነበሩ ሰዎች የሚፅፏቸውንና የሚያሳትሟቸውን መፅሐፍት እያነበብኩ አንድ ስሜት ብዕሬን ስለቀሰቀሰው ነው። በነገራችን ላይ “ያ ትውልድ” የምለው የኢሕአፓውን መስራችና ከፍተኛ አመራር የነበረውን የክፍሉ ታደሰን አጠራር ተውሼ ነው። ክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” ሲል በ1960ዎቹ የመጣውን የኢሕአፓን ትውልድ እና በዘመኑ የነበሩትን ሌሎቹንም ትውልዶች መጥራቱ ነው። ከዚያ ትውልድ ውስጥ አንዱ ደግሞ ደርግ ነው።

በዚያ ትውልድ ውስጥ ኢሕአፓን እና መኢሶንን እምሽክ አድርጎ ከጨረሰ በኋላ ጡንቻውን አጠንክሮ በትረሙሴውን የጨበጠው ደርግ ነው። የኢሕአፓም ሆነ የመኢሶን አባላት ሞቱ፣ ለአካልና ለህሊና ጉዳት ተዳረጉ፣ ገሚሶቹ ነፍጥ ይዘው ጫካ ወረዱ። ሌሎቹ ደግሞ በተለያዩ ዓለማት ተሰደዱ። የተለያዩ አቋሞችንም ይዘው የአሰላለፍ ለውጥ ያደረጉም አሉ።

ነገሮች ሁሉ አልፈው የነበረው እንዳልነበረ ሲሆን አንድ ነገር መምጣት ጀመረ። ያለፈውን ታሪክ የሚፅፉ ሰዎች ብቅ አሉ። በ1980ዎቹ መግቢያ ላይ ዋነኛ ማጠንጠኛውን ኢሕአፓ ላይ ያደረገ አንድ መፅሐፍ ታተመ። መፅሐፉ የተፃፈው ኢሕአፓን ከመሰረቱት ጥቂት ወጣቶች መካከል አንዱ በሆነው እና በፓርቲው ውስጥ ከፍተኛ አመራር በሆነው በክፍሉ ታደሰ ነው። ክፍሉ ታደሰ በሕይወት ከተረፉት የፓርቲው መስራቾች ምናልባትም ከአራቱ አንዱ ነው። ክፍሉ የራሱን ትውልድ የዘከረበት መፅሀፍ “ያ ትውልድ” የሚሰኝ ሲሆን በሶስት ተከታታይ ቅፆች የታተመ ሲሆን በእንግሊዝኛ ደግሞ The Generation ብሎ ይህንኑ መፅሐፍ አሳተመ። መፅሐፉ በከፍተኛ ስርጭትና ሽያጭ ገበያውን ያጥለቀለቀ ነበር። ምክንያቱም “ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ” በሚባለው ብሒል መሰረት ክፍሉ ታደሰ መፅሀፉን ማዘጋጀቱ ተነባቢነቱን ጨመረለት። ከዚህ ሌላ የክፍሉ አፃፃፍ ቀላል እና ተነባቢ ከመሆኑም በላይ የቋንቋ ችሎታውም የላቀ በመሆኑ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ ያለን አንባቢ ሊያረካው ችሏል።

ከክፍሉ በኋላ ደግሞ የመኢሶን ታሪክን የያዘው የአንዳርጋቸው መሳይ መፅሐፍ ታተመ። ርዕሱ በጣም ማራኪ ነው። “በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ” ይላል። በውስጡም ያለው ታሪክ መሳጭና አሳዛኝ ነው። የዚያን ትውልድ ታሪክ ሌሎችም በተለያዩ መፅሀፍት መፅሔቶች ጋዜጦች ፃፉ። ከዚያም ስለዚያ ትውልድ የሚፃፉ ነገሮች እየተዳከሙ መጡ። ታሪክ የሚፅፍ ሰው ጠፋ።

ከ1990ዎቹ ጀምሮ ደግሞ የደርግ ወታደሮች፣ ታላላቅ መኮንኖች እና አመራሮች ከተለያየ ቦታ ሆነው የደርግን አብዮት በመፅሀፍ መልክ እያሳተሙ ብቅ አሉ። የደርግ ሰዎች ባለፉት 15 ዓመታት ሃያ የሚሆኑ መፃህፍትን አሳትመዋል። በመፅህፍቶቻቸውም የሚገልፁት ነገር ቢኖር ደርግ ብዙ ስህተቶችን እንዳልሰራ ነው። ጥፋተኞቹ እነ ኢሕአፓ እና መኢሶን መሆናቸውን የሚገልፁ መፅሃፍት እያበረከቱ ነው። እነዚህ መፅሃፍት ለሚቀጥለው ትውልድ የታሪክ ማስረጃዎቹ እየሆኑ ሊቀመጡ ነው።

ደርግን ይመሩ ከነበሩ ትልልቅ ባለስልጣናት መካከል ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እና ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ ሳይቀሩ “ትግላችን” እንዲሁም “እኛ እና አብዮቱ” እያሉ ትልልቅ መፅሐፍትን አሳትመዋል። ስለዚህ የታሪክ አፃፃፉ ሚዛን ወደ ደርግ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው። የደርግ ሰዎች ከኢሕአፓ እና ከመኢሶን ሰዎች በፅሀፍት በልጠዋል። የደርግ ሰዎች ድሮ በጉልበትና በሐይል ኢሕፓንና መኢሶንን በልጠዋል። ዛሬ ደግሞ በታሪክ ፅሁፍና በማስረጃዎች ድርደራ ካለምንም ተከራካሪ መድረኩን እየሞሉት ነው።

ለነገሩ የደርግ ብዙ ወታደራዊ መኮንኖች እና ጀነራሎች ሳይቀሩ ስለ ደርግ ጦር እንቅስቃሴና ዓላማ ከኢሕአዴግ አባላት በላቀ ሁኔታ መፃህፍት እያሳተሙ ነው። የደርግ ሰዎች በመፃህፍት ህትመት ከኢሕአዴግም እየበለጡ ነው። አንባቢው ሚዛናዊ ነገሮችን እንዲያገኝ ከደርግ ጋር ይቀናቀኑ የነበሩ ወገኖች ሁሉ ታሪክን በስርዓት መፃፍና ማሳተም አለባቸው። ካለበለዚያ መድረኩን በሙሉ የደርግ ታሪክ እየተቆጣጠረው ነው።

በተለይ “ያ ትውልድ” በሚል ርዕስ ሶስት ተከታታይ መፃሕፍትን ያሳተመው ክፍሉ ታደሰ ዛሬም በህይወት እንዳለ ስለሚነገር ያላለቀውን የኢሕአፓ ታሪክን ማሳተም ይጠበቅበታል።

ከአጠገቡ የረገፉ ጓደኞቹን ታሪክ እና የዚያን ዘመን ታሪክ በሙሉ እንዳልጨረሰው ክፍሉ በሶስቱም ተከታታይ መፅሐፍቶቹ ገልጿል። ግን ቀሪዎቹን ታሪኮች እስከ አሁን አላሳተመም። ሌሎችም የኢሕአፓ አባላት የራሳቸውን እና የትውልዳቸውን ታሪክ ማስተላለፍ አለባቸው። የታሪክ ፋይሉን በዝምታ እያለፈው ያለው መኢሶንም ለሁለተኛ ጊዜ ተሸናፊ እንዳይሆን ታሪኩን መፃፍ አለበት።

     በአጠቃላይ ሲታይ ብዙ ፀሐፊዎችና ደራሲያን አሉበት ተብሎ የሚነገርለት ኢሕአፓ ዛሬ ዛሬ ከታሪክ አደባባይ እና ከመፃህፍት ህትመት ቦታ ላይ ጠፍቷል። በምትኩ ተቀናቃኙ የነበረው የደርግ ስርዓት አባላትና አመራሮች የራሳቸውን ታሪክ እየፃፉ ለትውልድ እያቃበሉ ነው። የዚህም ዘመን ትውልዶች ካለምንም አማራጭ የነ ፍቅረስላሴን መፅሃፍት እያነበቡ ነው።

ይምረጡ
(10 ሰዎች መርጠዋል)
12763 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us