በአለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ የሆኑት ኢትዮጵያዊት እናት

Wednesday, 14 May 2014 13:48

  

በጥበቡ በለጠ

 

በአሜሪካን ሀገር ፔንስልቬኒያ ውስጥ በአንድ ሆስፒታል በፅዳት ሠራተኝነት ተቀጥረው የሚሰሩት ወ/ሮ አልማዝ ገብረመድህን በ2011 ዓ.ም የአመቱ ምርጥ እናት ተብለው ተሸላሚ ሆነዋል።

 

እኚህ ኢትዮጵያዊት የአመቱ ምርጥ እናት ተብለው በአሜሪካ ውስጥ ያስመረጣቸው ምክንያት በልዩ ልዩ ሰዎች ዘንድ በተሰጣቸው ድምፅ ነው። በተለይም በሆስፒታሉ ውስጥ የሚሰሩት ነርሶችና ዶክተሮች የወ/ሮ አልማዝን ሰዋዊ ጥንካሬ እና ማንነት በተመለከተ በሰጡት አስተያየት የተነሳ ወ/ሮ አልማዝ ተመራጭ እናት ሆነዋል። በአሜሪካ ውስጥ ታዋቂ የሆነው ABC የተሰኘውም ቴሌቭዥን ጣቢያ ስለ ወ/ሮ አልማዝ ሽልማት በወቅቱ ሙሉ የአየር ሽፋን ሰጥቶታል።

 

ሽልማቱን ለወ/ሮ አልማዝ የተሰጣቸው መ/ቤታቸው ገብተው የእለት ስራቸውን በሚያከናውነበት ወቅት ነው። እርሳቸው አገር ሰላም ነው ብለው እለታዊ ተገባራቸውን በሚያከናውኑት ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ተሰብስበው ወ/ሮ አልማዝ እንኳን ደስ አልዎት፤ እርስዎ የአመቱ ምርጥ እናት ተብለው ተመርጠዋል አሏቸው። ወ/ሮ አልማዝ ከፊታቸው ባለው ጠረጴዛ ላይ ፊታቸውን በእጃቸው ሸፍነው ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፤ አነቡ። የወ/ሮ አልማዝ ለቅሶ ምናልባት በህይወት ዘመናቸው ያሳለፉት ውጣ ውረድ እፊታቸው ተደቅኖ እየታያቸው ይሆናል።

 

የፕሮግራሙ መሪ “አልማዝ እርስዎ የአመቷ ምርጥ እናት ነዎት” ሲላቸው ህዝቡ ከያለበት በጭብጨባና በሆታ ድምፁን አስተጋባ። እርስዎ የተመረጡት ሀኪሞቹና ነርሶቹ በሙሉ ምርጥ እናት ብለው ድምፃቸውን ስለሰጥዎት ነው አላቸው። እርስዎ በጣም በጣም የሚደንቁ እናት ነዎት ሲልም ለABC ቴሌቭዥን ተናገረ።

 

የሆስፒታሉ ሀኪሞች ስለ ወ/ሮ አልማዝ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። አንዲት ታዋቂ ሀኪም ስትናገር “አልማዝ ሁሉንም ነገር ናት” ብላለች። ሌላኛው ሀኪም ሲናገር ደግሞ አልማዝ ሁሌም ስራ ላይ ናት አለ።

 

ወ/ሮ አልማዝ እ.ኤ.አ. በ1993 ዓ.ም ከባለቤታቸውና ስድስት ልጆቻቸው ጋር ሆነው ወደ አሜሪካ መጡ። በተለይ ደግሞ ፔንስልቬኒያ ግዛት። ባለቤታቸው ደግሞ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወ/ሮ አልማዝን ከአምስት ልጆቻቸው ጋር ጥለዋቸው ኮበለሉ። ልጆችን ማሳደግና ማስተማር ወ/ሮ አልማዝ ላይ ጫናው ወደቀ። በሆስፒታል ውስጥ እና በሌሎች ሁለት ቦታዎች በፅዳት ሰራተኝነት ተቀጥረውም በቀን 16 ሰዓታት እየሰሩ ልጆቻቸውን ማስተማር ጀመሩ። የአሜሪካን ሀገር ዜግነት ቢያገኙም ተአምረኛ ሴት በመባልም ስማቸው ይጠራል።

 

በሽልማት ስነ-ሥርዓቱ ላይ ወ/ሮ አልማዝ ልጆችም ከያሉበት ተጠርተው ተጋብዘዋል። ልጆቹ ሁሉም ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በከፍተኛ ውጤት ተመርቀዋል።

 

ከወ/ሮ አልማዝ ልጆች አንደኛዋ ስትናገር “እናቴ ያላትን ችግርና ፅናት፣ ያሳለፈችውን ውጣ ውረድ ማንም አያውቅላትም” ብለዋል።

 

ትልቁ ልጃቸው ሲናገር ደግሞ “እናቴ አንዳንድ ጊዜ ለምትመግበን ምግብ ገንዘብ አታገኝም። ባዶዋን ትሆናለች። ነገር ግን ፊቷ ላይ ምንም አይነት ጭንቀት እንዳናይ ሁሉም ጥሩ ፈገግታ ታሳየናለች እያለም ተናግሯል” ከእናታችን ፍቅርን፣ ጥንካሬን፣ ተስፋ አለመቁረጥን ተምረናል ብሏል የወ/ሮ አልማዝ ልጅ።

 

ሌላኛዋ የወ/ሮ አልማዝ ልጅ ስትገር እናቴ እንደ ስሟ አልማዝ ናት። ውድና ድንቅ ናት ብላለች።

 

እናቴ በጣም ድንቅ እናት ነች እያለም ልጃቸው በሽልማት ስነ-ሥርዓቱ ላይ ተናግሯል። እናቴ የተሻለ ሰው እንድሆን፣ እነዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ ስላደረግሽልኝ አመሰግንሻለሁ” ብሏል ልጃቸው።

 

ወ/ሮ አልማዝ ለልጆቻቸው ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈላቸው በአሜሪካ ውስጥ ምርጥ እናት ተብለው ትልቅ ሽልማት አግኝተዋል። ኢትዮጵያዊት እናት እንዲህ ናት

 


ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
16693 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us