ስለ ቴአትር እንጨዋወት

Wednesday, 14 May 2014 13:54

በጥበቡ በለጠ

ጊዜው አለም በመጀመሪያው እና በሁለተኛ የአለም ጦርነት የተናጠችበት ሲሆን ከ60 እስከ 100 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱበት፣ የቆሰሉበት፣ አካለ ጉዳተኛ የሆኑበት፣ ቤት እና ሀገር ያጡበት፣ ወላጆች ያለልጅ ልጆችም ያለ ወላጅ የቀሩበት ነው። ከዚህ ጦርነት አስቀድሞ የነበረው ሰው ይህ አለም በፈጣሪ የተፈጠረ እና ለሰው ልጅ ሁሉ እንዲጠቅም ትርጉም በሚሰጥ መልኩ የተዋቀረ ነው በሚለው የሃይማኖት አስተምህሮቶች የሚያምን ነበር። እንደውም እነዚህን አስተምህሮቶች በተለያዬ ባህላዊ እና ማኀበራዊ አስተሳሰብ ውስጥ በማስገባት የሞራላዊ እና የስነ ልቦናዊ ብቃት መለኪያ አድርጎ ይገለገልባቸውም ነበር።

ይህ አለም ትርጉም አለው የሚለው ሰው ከየትኛውም ክፉ እና አስቸጋሪ ከሆኑ ውጣ ውረዶች የሚጠብቀው አካል እንዳለ ያምን እና ያም አካል የአለም ፈጣሪ እንደሆነ ያስባል። ስለዚህም ጥበቃውን ለፈጣሪ ሰጥቶ በእለት ኑሮ ውስጥ ደፋ ቀና ይል ነበር።

አጠቃላይ እድሜያቸው አስር ዓመት የወሰዱት የመጀመሪያው እና የሁለተኛው የአለም ጦርነቶች ያስከተሉትን መከራ በአይኑ እያየ በአካሉ እየዳሰሰ ተሰቃይቶ ህይወቱን ያተረፈው ሰው የፈጣሪውን ህልውና፣ ጠባቂነቱን እና ሩህሩህነቱን መጠየቅ ያዘ። በአንድ ትልቅ የድብርት መንፈስ ውስጥም ወደቀ። ይህ የድብርት መንፈስም የሰው ልጅ በሚፈፅማቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኀበረሰባዊ ወዘተ ዘርፎች ላይ መዳከምን ፈጠረ። አለምም ወደ አንድ የዝምታ አዘቅት ውስጥ ወደቀች።

ታዲያ የሰው ልጅ በአለም ዝምታ ውስጥ ሆኖ ከጦርነቱ በፊት የነበሩት ይህ አለም በፈጣሪ የተፈጠረ በመሆኑ ፈጣሪ ይጠብቀዋል እና በአለም ውስጥ የተፈጠረው ነገር ሁሉ ትርጉም አለው የሚለውን አስተሳሰቡን መመርመር ጀመረ። በመልሱም ይህ አለም ፈጣሪም ትርጉምም የለውም ወደሚል ድምዳሜ ላይ ደረሰ።

በእርግጥ የሰው ልጅ ህይወት ፈጣሪ እና ትርጉም የሌለው ነው ብሎ ለማመን በሁለቱ ጦርነቶች ውስጥ የተከሰቱትን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ብቻ እንደምክንያት አላቀረበም። ይልቁንም በኑሮ መስመሩ ውስጥ ለማግኘት እየፈለገ ማግኘት አለመቻሉን፣ አንድ ዓይነት ቋንቋ እያወራ ወደ ግጭት የሚያመራ መሆኑን ፈትሾ ከደረሰባቸው በኋላ ህይወት ትርጉም የሌላት ናት የሚለውን ሀሳቡን አጠናከረ።

ከሁለተኛው አለም ጦርነት በኋላ ሰዎች ህይወት ወለፈንዲ ወይም ትርጉም አልባ ነች ብለው ያምኑ ነበር ሲባል ግን ሁሉም ሰዎች የዚህ አስተሳሰብ አቀንቃኝ ሆነው ነበር ማለት አይደለም። ከጦርነቱ በኋላም አለም ትርጉም ያላት ናት የሚለው አስተሳሰብ፤ አለም ትርጉም የላትም ወይም ወለፈንዲ ናት የሚለውን አስተሳሰብ እየተቃወመ ቆይቷል።

እንዲያውም እንደ ህልውናዊነት (existentialism) የመሳሰሉትን ፅንሰ ሀሳብ የሚያቀንቅኑ ሰዎች ግለሰብ የነገሮች ሁሉ መለኪያ ነው ከሚለው ሀሳባቸው ተነስተው የወለፈንዲ አቀንቃኞች ህይወት ትርጉም እንዳይኖራት አድርጎዋል ብለው የሚያስቀምጧቸውን ሞት፣ መለያየት፣ አለመግባባትን ወዘተ ለህይወት ትርጉም የሚሰጡ ናቸው ብለው ያስቀምጣሉ።

ህይወት ትርጉም የላትም የሚሉት ሰዎችም የራሳቸውን ምክንያት እየደረደሩ እምነታቸውን ያብራራሉ። የወለፈንዲ ኀሳብ አቀንቃኞች የሚሉትን ከኢትዮጵያዊነታችን ውስጥ ምሳሌ እየጠቀስን እንረዳ።

የወለፈንዲ ኀሳብ አቀንቃኞች የመጀመሪያ ፍልስፍና ቋንቋ አያግባባንም የሚለው ነው። እነዚህ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆኑ ቋንቋ አያግባባንም የሚለውን ፍልስፍናቸውን ለማሳየት የኢትዮጵያን እና የኤርትራን ጦርነት ያነሳሉ። ለምሳሌ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ጦርነቱ ከመካሄዱ አስቀድሞ ሁለቱም ሀገራት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና ውይይት ያደረጉ ሲሆን እነዚህ ውይይቶች ግን ሁለቱን ሀገራት ሊያስማሟቸው አልቻሉም። ምክንያቱ ደግሞ የሁለቱም ሀገር መሪዎች የሚያወሩት ቋንቋ አንድ ዓይነት ቢሆንም ቋንቋ በራሱ የሚገልፀው ሀሳብ እና ስሜት አለ። ይህ ሀሳቡ እና ስሜት ደግሞ የተናጋሪውን የአሁን ሁኔታ እና ያለፈ ማንነት የሚይዝ ነው። ተናጋሪው እና አድማጩ ደግሞ አንድ ዓይነት ፍላጎት፣ ማንነት እና የአሁን ስሜት አይኖራቸውም። ይህ ደግሞ በቋንቋው ተጠቃሚዎች መሀል መቼም መግባባት እንዳይኖር ያደርጋል ብለው ምክንያታቸውን ያስረዳሉ።

“ቋንቋ አያግባባም” ከሚለው አመለካከታቸው በተጨማሪም ህይወት ትርጉም የሌላት ናት የሚለው ፍልስፍናቸው ተጠቃሽ ነው። ታዲያ የህይወት ትርጉም አልባነትን የሚያስረዱንም በፍላጎት እና በአቅርቦት፣ አለመጣጣም ነው። ለምሳሌ ሁላችንም ልናገኛቸው የምንፈልጋቸው ነገሮች አሉን። አብረውን ሁሌም እንዲሆኑ ወይም እንዲኖሩ የምንመኛቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ እኛ ኢትዮጵያውያን ሁላችን የተሻለ ኑሮን፣ ክብርንና ዝናን እንፈልጋለን። ነገር ግን ብዙዎች በኑሮ አዘቅት፣ በችግር እና በውርደት ውስጥ እንኖራለን። ብዙዎቻችን ኢትዮጵያችን በአለም የምትታወቅ የምትከበር እና ሀያል አድርገን እናስባታለን። ነገር ግን በአለም ህዝብ ውስጥ ያለው እውነታ እኛ ከምናምነው እና ከምናውቀው ተቃራኒ የሆነ ነው።

ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ህፃናት፣ ወጣት እና አዛውንቶች እራበን እያሉ በየመንገዱ ሲጮሁ ይታያል። ብዙ ሰዎች የሚለብሱት የሚያድሩበት የሌላቸው በመሆናቸው ፍፁም በወዳደቁ ቤቶች ውስጥ ወይም በጎዳና ላይ ይኖራሉ። ይህ ሁሉ ህይወትን ትርጉም አልባ የሚያደርግ ነው ይላሉ።

ይህ አስተሳሰቡ እራሱን ችሎ ረዥም እድሜ የቆየ ባይሆንም አለም ትርጉም ያላት ናት ቋንቋም ያግባባናል ብሎ የሚያምነው እና ከመጀመሪያው አለም ጦርነት በፊት ያለው ሰው ህይወቱን ትርጉም አልባ የሚያደርጉና የማያግባቡ ነገሮች ሲገጥመው በውዥንብር ውስጥ የሚወድቀውን የሰው ፍጡር ነፃ ያወጣ ነው። የሰው ልጅ በህይወት መስመሩ ውስጥ ትርጉም የሚሰጡ እና ትርጉም የማይሰጡ፣ የሚያግባቡ እና የማያግባቡ ነገሮች ያሉት ሲሆን ትርጉም የማይሰጡት የትኞቹ እንደሆኑ ማሳየት ችሏል።

ይህንን ሀሳብ “ካምብሪጅ ጋይድ ቱ ዘ ቴአትር” የተሰኘው መፅሐፍ ወለፈንዲያዊነት ህይወት ትርጉም እንዳለው በሚናገረው የሃይማኖት አስተምህሮት ተሸፍኖ የነበረውን የሰውን ልጅ ትርጉም አልባ ገፅታ ያጋለጠ ነው ብሎ ከላይ ያለውን ሀሳቡን አጠናክሮት ይገኛል።

ወላፈንዲያዊነት በእንግሊዝኛ አጠራሩ “አብዘርዲዝም” (Absurdisem) የሚለውን ስያሜ የሰጠው የዚህ ፍልስፍና ፍፁም ተቃዋሚ ወይም ተቃራኒ የነበረው እና የህልዊያዊነት (Existentialism) አባት ተብሎ የሚጠራው አልበርት ካሙ ሲሆን ቴአትር ኦፍ ዘ አብዘርድ ብሎ በመጠቀም ሀያሲው ማርቲን ኢስሊን (Martin Esslin) ተጠቃሽ ነው።

የኪነ ጥበብ ሰዎችም ይህንን ሀሳብ በኪነ-ጥበብ ስራቸው ውስጥ ማንፀባረቅ ጀመሩ። ከኪነ-ጥበብ ዘርፎች አንዱ በሆነው የቴአትር ጥበብ ውስጥ እንደ ሳሙኤል ቤኬት (Samuel Beckett) ኢዩጌኔ አዮንስኮ (Eugene lonesco) ጂአን ጌኔት (Jean Genet) ሃሮልድ ፒተር (Harold Pinter)፣ ኤድዋርድ አልቤ (Edward Albee) የመሳሰሉት ሰዎች ይጠቀሙበት ጀመር።

ይህን ፍልስፍና ወደ ቴአትር ያመጡት እና ሁለተኛውን የአለም ጦርነት ተከትሎ የመጣው ድብርት ከመታቸው ሰዎች መሀል ተጠቃሹ ሰው አብርሃም ቤኬት ነው። የአብርሃም ቢኬት ስራ የሆነው ዎይቲንግ ፎር ጎዶት (Whetting for Godot) የተሰኘው ፅህፈተ-ተውኔት የፍልስፍናው የምንጊዜም ድንቅ ስራ ተደርጎ የሚነሳ ነው።

በቤኬት እና በሌሎች የፍልስፍናው አቀንቃኞች የቴአትር ስራ ውስጥ የህይወት ወለፈንዲያዊ ገፅታ የሚታይበት የራሱ መገለጫ አለው። ከመድረክ ገፅ ብንጀምር የወለፈንዲ የመድረክ ገፅ የተመልካቹን ስሜት እማይመስጥ እና ትርጉም በማይሰጡ ቁሳቁሶች የተሞላ ወይም ባዶ የሆነ ነው። የገፀ-ባህሪያቱ አለባበስ ከሚወክሏቸው የማኀበረሰብ ክፍል የተለየ ሲሆን ይህም ማለት ንጉስ ሆኖ የአንድን የእብድ አይነት ልብስ ወይም የተቀዳደደ አይነት ልብስ ሊለብስ ይችላል። ሜካፕ አጠቃቀማቸው የድብርትን መንፈስ እንዲፈጥር ተደርጎ የሚቀርብ ነው።

የመድረክ እንቅስቃሴያቸውን ስናይ ዘፈቀዳዊ ከመሆኑ ባሻገር ከገፀ-ባህሪው ንግግር ጋር የሚጣረስ ነው። ለምሳሌ መድረክ ላይ ቁጭ ብሎ እየታየ እየሮጥኩ ነው ወይም መድረክ ላይ የለሁም ሊል ይችላል። አንድ ፍልስፍናው ያልገባው ሰው ገፀ-ባህሪውን ቢያየው አንድን ወፈፌ ሰው ወክሎ እየሰራ ነው ብሎ ሊል ይችላል። ገፀ-ባህሪያቱ የራሳቸውን እቅድ አላማ እና ግቡ ይዘው የሚነሱ ቢሆኑም ብዙ ጊዜ ይረሷቸዋል። ምን አልባት አስታውሰው እስከ ተውኔቱ ፍፃሜ ይዘዋቸው ቢቆዩ እንኳን አይሳኩላቸውም የትኛውም ነገር ባይሳካላቸውም ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ሆነው ኑሯቸውን ይቀጥላሉ።

በቴአትሩ ውስጥ እውቅያ፣ ትውስብ፣ ጡዘት እና ልቀት የሚባሉ ነገሮች የሚታሰቡ አይደሉም። አንዳንዴ መሀል ላይ የጀመረ ቴአትር እንደሚመስል ሁሉ አንዳንዴ መሀል ላይ ያለቀ ይመስላል። ገፀ-ባህሪያቱ መሀል ግጭት ለመፍጠር ምክንያት አያስፈልገውም። የግጭቱ ውጤትም አይታሰቡም። በሆነ ጊዜ ያለምንም መንስኤ ግጭት ሊፈጠር ይችላል። ግጭቱም ያለምንም ምክንያት መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል።

ከላይ ስለበሃሪው በተወሰነ መንገድ ያነሳነው እና መጀመሪያው እና የሁለተኛው አለም ጦርነት በሰው ውስጥ የፈጠሩትን ተስፋ መቁረጥ ተከትሎ የተፈጠረው ወለፈንዲያዊ ቴአትር የኮሜዲ ታሪካዊ ባህሪ (Historical type of comedy) ነው ሲል ‘‘ዊኪፒዲያ’’ የተሰኘው የመረጃ መረብ ያስቀምጠዋል። ምክንያቱ ደግሞ ተመልካቹ ቴአትሩን በሚያዩበት ወቅት በሳቅ ስለሚፍነከነኩ በማኀበራዊ አስተሳሰቦች ላይ ስለሚያሾፉ ነው።

ከ1945 እስከ 1960 ዓ.ም ድረስ ከላይ ባነሳነው መልኩ የቆየው የወለፈንዲ ቴአትር ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ በእውናዊ (realism) ፅንሰ ሀሳብ ውስጥ በመግባት እየተሰራበት ይገኛል። ይህም ማለት የእውናዊ እና ሌሎች የቴአትር ፍልስፍናዎች ህይወትን ቀፅለው በሚያሳዩበት ጊዜ በህይወት ውስጥ ያለውን ትርጉም አልባነትም አብረው ያሳያሉ። ዛሬ በሀገራችን የሚታዩ እና አውናዊ ተብለው በሚሰሩት ቴአትሮች ውስጥ የወለፈንዲያዊ ቴአትር ፍልስፍናን በደማቁ ሲንፀባረቅ ይስተዋላል። 

 

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
10557 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us