ፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው አሜሪካዊ ሆኖ ለኢትዮጵያ የሠራ የቋንቋ ሊቅ!

Wednesday, 21 May 2014 12:59

በጥበቡ በለጠ

ዛሬ የሕይወት ታሪኩን የምንዳስስለት ሰው አስገራሚ የሆነ ታሪክ አለው። ይህ ሰው ገና በህፃንነቱ በሳንባ ህመም ይጠቃል። ሀኪሞችና በቅርቡ ያሉ ሠዎች ልጁ በሕይወት የመቆየቱ ነገር እምብዛም ተስፋ የማይሰጥ እንደሆነ ይገመታሉ። ከበሽታው ሌላ ደግሞ ችግርም በረታበት። እናቱ በዚሁ በሳንባ ህመም ምክንያት ይህችን አለም በሞት ተሰናበተች። አባቱም እንዲሁ ባለቤቱን ተከትሎ አሸለበ። ታዲያ ዛሬ የማወጋችሁ ባለታሪክ ገና የ10 ዓመት ልጅ ሳለ እናትና አባቱን በሞት ተነጠቀ። መከራ እላዩ ላይ በረከተ። ይሁን እንጂ ይህ በሳንባ ህመም የሚሰቃየውና ወላጆቹንም በለጋ እድሜው የተነጠቀው ልጅ በኋላ አድጎና ጎልምሶ፣ ቀጥሎም በትምህርት ደረጃውም ከአለማችን ምርጥ የቋንቋ ምሁራን አንዱ ሆኖ፣ በዚህችም አለም ላይ አንድ መቶ አመት ከአራት ቀን ኖሮ የእድሜ ባለፀጋም ሆኖ ያለፈ የቋንቋ ፈላስፋ ነው።

ይህ ሰው ፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው ይባላል። ሰውየው በትውልድ የፖላንድ ሀገር ተወላጅ ሲሆን በዜግነት ደግሞ አሜሪካዊ ነው። ፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው በአለም ገናና ሰው ካደረጉት ነገሮች አንዱ ወደ ኢትዮጵያ ከዛሬ 60 ዓመታት በፊት መጥቶ ታሪኳን፣ የብሔረሰቦቿን ቋንቋና ባህል አጥንቶ አያሌ መፃሕፍትን ለትውልድ በማሳተሙ እና በኢትዮጵያ ላይ በአደረገው ጥናትና ምርምር ምክንያት የክፍለ ዘመኑ ሊቅ ነበር እያሉ የፃፉለት ተቋማት አሉ። “He was truly a man of the century” እያሉም የህይወት ታሪኩ ውስጥ በተደጋጋሚ ገልጸውለታል።

ፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው ኢትዮጵያ ላይ ላለፉት 60 ዓመታት ጥናትና ምርምር ከማድረጉም በተጨማሪ አንድ ለየት ያለ ድርጊትም ፈፅሞ ያለፈ ሰው ነው። በሕይወት ዘመኑ 50 መፃህፍትን ከማሳተሙም በላይ እጅግ በርካታ የጥናትና የምርምር ወረቀቶችን አቅርቧል። የሚገርመው ነገር ደግሞ በ98 ዓመቱም መፅሐፍ አሳትሟል። ታዲያ ይህ በ98 ዓመት ዘመኑ ላይ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2004 ዓ.ም ያሳተመው መፅሐፍ የመጨረሻ መፅሐፉ ሲሆን፣ የመፅሐፉ ታሪክም ስለ ኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ብሔረሰቦች ነበር። ርዕሱም The Verb in masqan as Compared with Garage Dialects. ይሰኛል። በዚህ መፅሐፍ ውስጥ የጉራጌን ብሔረሰብ መሠረት አድርጎ ስለ መስቃን ህዝቦች የቋንቋ ዘዬ ምን እንደሚመስል ያጠናበት ሰነዱ ነው። መፅሐፉ ለቋንቋ እና ለባህል ተመራማሪዎች ትልቅ ፋይዳ ያለው እንደሆነም አጥኚዎች ይገልጻሉ።

ዎልፍ ሌስላው የውጭ ሀገር ዜጋ ሆነው ኢትዮጵያን በመውደድ እና ለዚህችም ሀገር ቁም ነገር ያለው ነገር በማበርከት ስማቸው ከሚጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ከሚኖርበት አሜሪካ ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ምሁራን መካከል አንዱ እርሱ ነው። እንደመጣም ያደረገው ነገር ቢኖር በልዩ ልዩ ቦታዎች በመጓዝ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ስብጥር ብዛታቸውን እና ቋንቋቸውን ማጥናት ጀመረ። ምንም አይነት የመጓጓዣ መኪና በሌለባቸው ቦታዎች ውሃ ሲያጋጥመው በታንኳ እና በዋና እያቋረጠ፣ በእንስሳት እና በእግሩ እየዞረ ኢትዮጵያን ሲያጠናት ኖረ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተነገሩ ድንቅዬ ባህሎች፣ ታሪኮች፣ አስተሳሰቦች መኖራቸውን አረጋገጠ። በዞረ ቁጥር ታይተውም ሆነ ተሰምተው የማይታወቁ አጓጊ ታሪኮችን ሌስላው አገኘ።

እናም ግኝቶቹን ሰብሰብ አደረጋቸውና ዳጎስ ያለ መፅሐፍ አሳተመ። ይህ መፅሐፍ ርዕሱ። Ethiopia speak ወይም ኢትዮጵያ ትናገር በሚል ርዕስ በአለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ከተተው። አለምም የኢትዮጵያን ድምፅ መስማት ጀመረ። ታሪኳ፣ ወጓ፣ ማንነቷ በመፅሐፉ ውስጥ ይነገራል።

ፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው ኢትዮጵያን በአለም ላይ አናግሮ ብቻም አላቆመም። በውስጧም ሆነ አንድ ትልቅ የትውልዶች ሁሉ ማህደር የሚሆን ሰነድ ማዘጋጀት ጀመረ። ይህም የእንግሊዝኛ እና የአማርኛን ቋንቋዎች የያዘ መዝገበ ቃላት ወይም ግዙፍ ድክሽነሪ ነበር። ወጣት የኢትዮጵያን ምሁራንን በማስተባበር ትልቁን ድክሽነሪ ከ1ሺ5 መቶ ሶስት ገፆች ጋር ለኢትዮጵያ ህዝብ አሳተመ። ይህ መዝገበ ቃላት በግዙፍነቱ በሀገራችን ውስጥ ከታተሙት ሁሉ የሚልቅ ነው። ላለፉት አርባ ዓመታት ትውልድ ሁሉ ሲማርበት ሲመራመርበት የነበረው ይህ መዝገበ ቃላት ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ህትመቶች መካከል አንዱ ነው። ምክንያቱም እስከ አሁን ድረስ የሚታተሙት መዝገበ ቃላት መነሻቸው የፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው ስራ ስለሆነ ነው።

ግንቦት 27 ቀን 1939 ዓ.ም ታትሞ የወጣው “ሰንደቅ አላማችን” የተሰኘው ጋዜጣም ስለ ዎልፍ ሌስላው ማንነት በመፃፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ጋዜጣ ነው። ስለፕሮፌሰሩ ማንነት ሲገልጽም እንዲህ ብሏል። “ሌስላው ይህን ሁሉ ድካም ያደረጉት አንዳችም ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን ጥበብን በጥበብነቷ ለማግኘት ብቻ ነው። እንዲህ ያሉት የጥበብ ወዳጆች ከእውነተኛው ጥበብ በቀር በፊታቸው ሌላ የሚያስታውሱት ነገር ስለሌላቸው ሃሳባቸው በቅንነት የተሞላ ነው” በማለት ፅፎለታል።

ሌላስላው ኢትዮጵያን ያለማቋረጥ ከ1939 ዓ.ም እስከ 1965 ዓ.ም ለ29 ዓመታት በሚገባ ሲመረምራት ቆይቷል። በዚህም ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ስለነበረውና ዛሬ ከምድራችን ላይ ከጠፉት ቋንቋዎች መካከል አንዱ የሆነውን የጋፋት ቋንቋ ያጠና ምሁርም ነው። ጋፋትኛ ተናጋሪዎች ተመናምነው አስር የሚሆኑ ሰዎች ብቻ በቀሩበት በዚያን በሩቁ ዘመን ላይ ደርሶ የቋንቋውን ታሪክ፣ ቃላት፣ ባህል፣ የአረፍተ ነገር አሰራር እና በአጠቃላይ የቋንቋውን ተፈጥሮ መዝግቦ ያኖረ ትልቅ ተመራማሪ ነው። ዛሬ ጋፋትኛ ቋንቋ ባይኖም ነገር ግን በፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው ዶክመንት ውስጥ በስርዓት ተቀምጦ ይገኛል። ይህን የጋፋት ቋንቋ እንደገና እናንሳው ተብሎ ቢታሰብ ከዶክመንት ውስጥ እያወጡ ማጥናትም ይቻላል ማለት ነው።

ለምሳሌ ዛሬ የአለም የጥናትና የምርምር ቋንቋ የሆነው የእስራኤሉ ኢብራይስጥ ቋንቋ ከምድር ላይ ከጠፉ ቋንቋዎች መካከል አንዱ ነበር። እስራኤል እንደ ሀገር እንደገና ስትመሰረት የሞተውንም የእብራይስጥ ቋንቋ ነብስ ዘርተውበታል። ከሞት ወደ ሕይወት የመጣ ቋንቋ ነው ኢብይስጥኛ። እናም ለእብራይስጡ ቋንቋ እንደገና መምጣትና መጎልበት ምክንያት ከሆኑት ሰዎች መካከልም ዎልፍ ሌስላው አንዱ ሆኖ ስሙ ይጠራል። እናም የእብራይስጥን ቋንቋ መነሻ ልምድ አድርጎ የኢትዮጵያን ጋፋትኛ ቋንቋ መዝግቦ ያለፈ ባለውለታም ነው።

ፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሠራቸው በርካታ ተግባራት መካከል ወደ ምስራቅ ተጉዞ በሐረር ከተማ እና በሐረሪ ቋንቋ እና ባህል ላይ ያደረገው ጥናት ነው። የምስራቋ ጀንበር እየተባለች በተመራማሪዎች የምትጠራውን ጥናታዊቷን ሐረር እና በውስጧ ያለውን ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ቋንቋ እና አስተሳሰቦችንም አካቶ ሐረር ትናገር Harrari speak ብሎ መፅሐፍ ያሳተመላት ባለውለታ ነው።

ፕሮፌሰር ሌስላው የኢትዮጵያን ቋንቋዎች ልዩ ልዩ ባህሪያት እየሰበሰበ የሚያጠና እና በቋንቋ ውስጥ ያሉትን አያሌ የባህል፣ የማንነት እና የአስተሳሰብ መገለጫዎችን የሚተነትን ምሁር ነበር። በ1940 ዎቹ አጋማሽ ላይም ለኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙት ቤተ እስራኤላውያን ባህልና ታሪክም መፅሐፍ አሳትሟል።

በኢትዮጵያ እና በደቡብ አርቢያ ሀገራት ውስጥ ያሉትን ታሪካዊና ባህላዊ ትስስሮቹን ሁሉ በሚገባ በማጥናት መፅሐፍትን ያሳተመ ተመራማሪ ነው። Ethiopic and South Arabic Contributions to the Hebrew Lexcon የሚልም መፅሐፍ በማሳተም ረገድ ዝናን አትርፏል። ይህ መፅሐፍ ኢትዮጵያ እና የደቡብ አረቢያ ሀገራት የሂብሩው ቋንቋን ለማሳደግ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ የሚያሳይ ነው።

ፕሮፌሰር ሌላስላው በአሜሪካን ኦሬንታል ሶሳይቲ (ማህበረሰብ) አሳታሚነት ስለ ትግርኛ ቋንቋ ስዋሰው መፅሐፍ አሳትሟል። መፅሐፉ Short Grammar of Tigre ስትሰኝ የታተመችውም እ.ኤ.አ በ1945 ዓ.ም ላይ ነበር።

ሌስላው በግዕዝ ቋንቋ ላይ ጥናትና ምርምር ካደረጉ ሰዎችም መካከል አንዱ ነው። የግዕዝ ቋንቋ በአለም ላይ ከነበሩ ጥንታዊ የፅሑፍ ቋንቋዎች መካከል አንዱ በመሆኑ በውስጡ አያሌ ቁምነገሮችን እንደያዘ እየተነተነ በማስረዳት ረገድ ሌስላው ያበረከተው አስተዋፅኦ ሰፊ ነው።

ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ቋንቋን እና ባህልን ብሎም ታሪክን የሚያጠኑ ተመራማሪዎች እንደ ማጣቀሻ በሰፊው ከሚጠቀሙባቸው ምሁራን መካል አንዱ ፕ/ር ዎልፍ ሌስላው ነው።

በእነዚህና በሌሎችም ስራዎቹ ኢትዮጵያ ሐገራችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስተዋወቀ የዚህች ሀገር ባለውለታ ነው። ይህን አስተዋፆውን ምክንያት በማድረግ ዋሽንግተን ውስጥ በዋይት ሐውስ በተደረገ የእራት ግብዣ ላይ የውጭ ሀገር ዜጋ ሆኖ ኢትዮጵያን በመውደድ እና በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮችን በማበርከት ተመራጭ በመሆኑ ቀዳዊ ኃይለስላሴ የወርቅ ሜዳሊያ ሸልመውታል።

ዎልፍ ሌስላው ከኢትዮጵያ ውጭም አሜሪካ ውስጥ ካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ከማስተማሩም በተጨማሪ የምስራቅና የአፍሪካ ቋንቋዎች ዲፓርትመት ሊቀመንበርም ሆኖ አገልግሏል። እዚያው አሜሪካ ውስጥ የጥንታዊ ቋንቋዎች ሊቅ እየተባለም ይጠራ ነበር። American Oriental Society የሚባውን ተቋምም በፕሬዝዳንትነት አገልግሏል።

ፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው እ.ኤ.አ ህዳር 18 ቀን 2006 ዓ.ም አንድ መቶ አመት ከአራት ቀን በዚህች አለም ላይ ኖሮ እና ተመራምሮ አልፏል። ስራዎቹ ዛሬም ሆነ ነገ የበርካታ ተመራማሪዎች ትኩረት እንደሆኑ ይኖራሉ።

የፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው ሕትመቶች በጥቂቱ

 • English – Amharic Context Dictionary
 • Amharic Text book
 • Reference Grammar of Amharic
 • Introductory Grammar of Amharic
 • Concise Amharic Dictionary

   Amharic – English

   English – Amharic

 • Concise dictionary of Ge’ze

(Classical Ethiopia)

 • Comparative Dictionary of Ge’ze

(Classical Ethiopia)

 • Gurage studies collected Articles
 • Etymological Dictionary of Gurage
 • Arabic Loanwords in Ethiopian Semitic
 • The Verb in masqan as compared with other Gurage Dialects
 • Hebrew Cognetes in Amharic
 • The verb in Harari
 • The Scientific investigation of the Ethiopian languages
 • Short Grammer of Tigre
 • ZWay Ethiopic Documents

Grammar & Dictionary

 • Ethiopians speak studies in cultural background
 • Bibliography of the semitic language of Ethiopia
 • The Bete Israel in Ethiopia & Israel

እና ሌሎችንም ጥናቶች በኢትዮጵያ ላይ ሠርቷል።

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
12235 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us