የክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” እንደገና

Wednesday, 28 May 2014 13:42

በድንበሩ ስዩም

 

ክፍሉ ታደሰ የኢትዮጵያን ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲን /ኢሕአፓ/ን በግንባር ቀደምትነት ከመሠረቱት የያኔው ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። ፓርቲውን ከመመስረት ባለፈ ደግሞ በከፍተኛ አመራር ውስጥ ሆኖ የ1960ዎቹን አብዮት ከመሩት መካከል የፊተኛው ረድፍ ውስጥ የሚቀመጥ የለውጥ አቀንቃኝ ነው። ኢሕአፓ ስትፀነስ፣ ስትወለድ፣ ስታድግ፣ ስትዛመት፣ መሣሪያ አንስታ ስትዋጋ፣ አባላቶቿ የሞት አዋጅ ታውጆባቸው ደማቸው በየጎዳናው ሲፈስ፣ የታሰበው ሁሉ እንዳልታሰበ ሆኖ መና ሲቀር፣ ኢሕአፓ የሕልውና አጣብቂኝ ውስጥ ስትገባ፣ በአንጃ ተከፋፍላ ኃይሏ እና ጥንካሬዋ ሲላላ፣ ትውልድ እንደ ጉም በኖ የትም ሲቀር እና የታሰበችው ረጅሟ ሕልም ቀስ በቀስ ደብዝዛ፣ ደብዝዛ እየራቀች ስትሔድ ክፍሉ ታደሰ አይቷል። ሂደቶችን ሁሉ በውስጣቸው አልፏል። የለውጥ አቀንቃኙ ትውልድ ያሰበውና ያለመው ሳይሆን ድንገቴ ደራሹ የሆነው ነፍጥ አንጋቢው ደርግ ብቅ ብሎበት ወርቃማ ህልሙ ሳይታይ ቀሪውን አጀንዳ ለታሪክ አስረክቦ በየአቅጣጫው ነጎደ። ክፍሉ ታደሰ የዚህ ሁሉ አብዮት እና ምስቅልቅል ህይወት ውስጥ በዋናነት ተሳታፊ ነው። የትውልዱ ህልምና ጉዞ ተደነቃቅፎ ቀሪውን ለታሪክ ሲያስረክብ ክፍሉ ታደሰ እዚህጋም አልቆመም። ህይወትን ቀጠላት። ታሪክም አድርጎ ፃፋት። ትውልዱን በሙሉ “ያ ትውልድ” እያለ በተከታታይ መፃህፍት ዘከረው። ዛሬ የምንቋደሰው ይህን ዝክር ነው።

የክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” የሚሰኘው መፅሐፍ ሶስት ቅፆች ያሉት የ1960ዎቹ እና የ1970ዎቹ የኢትዮጵያ የለውጥ አቀንቃኝ ትውልዶች ታሪክ ነው። እነዚህ ሶስቱ ተከታታይ መፃህፍት ከመታተማቸው በፊት ደራሲው ክፍሉ ታደሰ The Generation በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ አንድ ዳጎስ ያለ መፅሀፍ አሳትሟል። ይህም መፅሀፍ ቢሆን ይዘቱ ከአማርኛው ጋር ተመሳሳይ ሆኖ የዚያን ትውልድ ውጣ ውረድ የሚዘክር ነው።

ከሰሞኑ ደግሞ ክፍሉ ታደሰ ተወዳጅ የሆኑትን “ያ ትውልድ” የተሰኙትን እነዚህን ባለ ሶስት ቅፅ መፃህፍት ከ15 ዓመታት በኋላ እንደገና አሳትሟቸው አንባብያን ዘንድ እየደረሱ ነው። የክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ መፅሀፍ በሐገራችን ውስጥ በውድ ዋጋ ከሚሸጡ መፃኅፍት መካከል ዋነኛው ነው። ከገበያ ውስጥ በመጥፋቱ የተነሳ ሶስቱን ቅፆች እስከ ሶስት ሺ ብር ዋጋ የሚጠሩ መፅሀፍ ሻጮች አያሌ ነበሩ። ይህ የሚያሳየው መፅሃፉ የትውልድን ታሪክ ሰብስቦ የያዘ በመሆኑ ለብዙ ጉዳዮች ማጣቀሻ ሆኖ ስለሚያገለግል ነው። ይህን ክፍተት የተረዱት አሳታሚዎቹ መፅሃፉን በ120 ብር የሽያጭ ዋጋ ወደ አንባቢያን በማምጣት የተከሰተውን ክፍተት ሞልተውታል።

“ክፍተት” ያልኩት፣ “ያ ትውልድ” መፅሃፍ ከገበያ በመጥፋቱ የተነሳ የሽያጭ ዋጋውን መናር ብቻ አይደለም። የክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ ከታሪክም ከአንባቢም እየራቀ በመጣ ቁጥር የሌሎች ታሪኮች እየጎሉ እየዳበሩ መጡ። ለምሳሌ የኢሕፓን ትውልድ ቤት ለቤት እያሰሰ ሲረሽን የነበረው ደርግ፣ መሪው ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም ሳይቀሩ እርምጃችን ልክ ነበር እያሉ መፃህፍት አሳትመዋል፤ ታትሞላቸዋልም።

ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም፣ ወ/ሮ ገነት አየለ “የኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች” ብላ በሁለት ቅፆች ባሳተመቻቸው መፃህፍት ውስጥ በኢሕፓ ወጣቶች ግድያ ላይ የተፈፀመው እርምጃ ልክ እንደነበር የተለያዩ ምክንያቶችን እየጠቃቀሱ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም እርሳቸው ራሳቸው ባሳተሙት ትግላችን በተሰኘው መፅሃፍ ውስጥም ደርግ በኢሕአፓ ወጣቶች ላይ የፈፀመው እርምጃ ትክክል እንደነበር ፅፈዋል። እንደ እርሳቸው አባባል መጀመሪያ የተኮሰችብን ኢሕአፓ ነች፤ ስለዚህ እኛ ወደ እርምጃው የገባነው ኢሕአፓአነሳስታን ነው ወደሚል አንደምታ ያዘነበለ ገለፃ ሰጥተዋል።

ከዚያም በኋላ የተለያዩ የደርግ አባላት መፃህፍት አሳትመዋል። አብዛኛዎቹም ስህተትን የመናዘዝ ባህል ባለማዳበራቸው ግድያው ልክ ነው እያሉ ፅፈዋል። የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ተከታይ በመሆን የደርግን መንግስት ከመሩት ሰዎች ዋነኛው የሆኑት ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ ባሳተሙት “እኛ እና አብዮቱ” በተሰኘው መፅሃፍ ደርግ ትክክል መሆኑን በስፋት ፅፈዋል። እነዚህ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚወረወሩት ሃሳቦች ማጠንጠኛቸው ደርግ አልተሳሳተም ወደሚል ትርጓሜ አንባቢን እየወሰዱት መምጣታቸው አይቀሬ ነው። ምክንያቱም አንባቢያን ሌሎች አማራጭ መፃህፍትን ከገበያ ውስጥ ባለማግኘታቸው ስንዴውን እና እንክርዳዱን ለመለየት እያዳገታቸው መጥቶ ነበር።

የኢሕአፓ አባላት በየሀገሩ የተበተኑት በርካቶች ቢሆኑም ያሳለፉትን የሕይወት ውጣ ውረድና ታሪክ ግን የሚፅፉት እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው። በመፅሐፍ መልክ ለንባብ ያበቁት እዚህ ግባ የሚባል ቁጥር የላቸውም። ነገር ግን ክፍሉ ታደሰ በሶስት ተከታታይ መፃኅፍት ከለውጥ ማቀንቀን ጀምሮ እስከ ኢሕአፓ መበታተን ድረስ ያለውን የታሪክ ሂደት ፅፎታል። ስለዚህ መፅሀፍቱ አንባቢው ከአንድ ወገን ብቻ የሚፃፉትን ሃሳቦች ይዞ እንዳይጓዝ ሚዛናዊ እይታ እንዲኖው ያግዙታል።

ለመሆኑ ክፍሉ ታደሰ የፃፈው “ያ ትውልድ” የተሰኘው መፅሃፍ በዋናነት ርዕሰ ጉዳዩ ምንድን ነው? ምንስ ነገሮችን ተሳሳተ? የሚሉትን ሃሳቦች በጥቂቱ አነሳሳቸዋለሁ።

ኢትዮጵያ አንድ ትውልድ ነበራት። ያ ትውልድ በጎ ህልም አለው። ህልሙን እውን ለማድረግ ከያለበት ተጠራራ። ፓርቲም መሰረተ።

ፋኖ ተሰማራ

ፋኖ ተሰማራ

እንደ ሆቺ ሚኒ እንደቼኩ ቬራ

እያለ በየጎዳናው አዜመ። ይህን መነሻ ታሪክ ብዙዎች ፅፈውታል። ክፍሉ ታደሰ ደግሞ ከሃሳብ ፅንስ ይነሳል። ለውጥን ለማምጣት ለምን ታሰበ? ለውጥን መጀመሪያ ያሰበው ማን ነው? ማንስ ተከተለው? የመጀመሪያዎቹ የለውጥ አቀንቃኞች እነማን ናቸው? ምን ሃሳብ ይዘው ተነሱ? የመጀመሪያ እርምጃቸው ምንድን ነው? እንዴት ተደራጁ?እንዴት ተስፋፉ? የሚሉትን እና ሌሎችንም ሃሳቦች አንስቶ ከፅንሳቸውና ከውልደታቸው ጀምሮ እስከ ፍፃሚያቸው ይተርካል።

የክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ የሚጀምረው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ውስጥ ለውጥ የተጫበረትን ቦታ አንስቶ ነው። ከዚያም ያንን ፋና ይዞ ይጓዛል። በንጉሡ ዘመን የነበሩ ምሁራን፣ የላብ አደሩ እንቅስቃሴን፣ የነጋዴውን ክፍል፣ የአርሶ አደሩን፣ የጦር ኃይሉን የሌሎችንም እንቅስቃሴ መሰረት አድርጎ የቀውሱ ዋዜማ በሚል ርዕስ የዚያን ትውልድ ፍጥረት መተረክ ይጀምራል። የቀውስ ዋዜማ ውስጥ ክፍሉና ጓደኞቹ ግንባር ቀደም ሆነው አብዮት ለማቀጣጠል ብቅ ይላሉ። ክብሪቷ የምትጫረው እዚህ ቦታ ላይ ነው።  

ክፍሉ ታደሰ የከፍተኛ ትምህርቱን በኢትዮጵያ እና በውጭ ሀገራት የተከታተለ ሲሆን፣ የ1960ዎቹን ትውልዶች ለመምራት ብቅ ካሉት ወጣት የወቅቱ ምሁራን አንዱ ነው። በውጭ ሀገራት በአውሮፓና በሌሎችም አለማት ያሉትን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ከማስተባበር ባለፈ የለውጥና የአብዮት መንፈስን በመዝራት ትግሉን ይጀምራል።

ዘመኑ ደግሞ አዳዲስ አመለካከቶችና አብዮቶች በልዩ ልዩ ሀገራት የታዩበት ነበር። አያሌ የኢትዮጵያ ተማሪዎችም በአውሮፓ፣ በሩሲያ፣ በአሜሪካ እየተዘዋወሩ ትምህርታቸውን የሚማሩበት ዘመን ነበር። ክፍሉ ታደሰም በንጉሱ ዘመን ወደ ውጭ ሀገር ሔደው ከተማሩት ወጣቶች መካል አንዱ ነው። የልዩ ልዩ ሃገራትን ለውጥና አብዮት በማሽተት እና በማንበብ ጥንታዊቷን ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊ አስተዳደርና አስተሳሰብ መቀየር አለብን ብለው በነክፍሉ ታደሰ አስተባባሪነት የዚያ ትውልድ አባላት ተነሱ፤ ተመሙ። አብዮት ተቀጣጠለ። ሠራተኛው፣ ገበሬም፣ ምሁሩ፣ ተማሪው. . .የለውጥ መዘውር ይዞ ከየአቅጣጫው ድምፁ መሰማት ጀመረ። የዚህን ድምፅ ግለት እና ፍላጎት የተገነዘቡ የደርግ አባላት መሳሪያቸውን ተጠቅመው ንጉሡን ከመንበረ ስልጣቸው አውርደው፣ ኢትዮጵያ ትቅደም ብለው ድንገት የለውጡ ፊታውራሪ ሆነው ብቅ አሉ።

የለውጥ አቀንቃኞቹ ወጣቶች ባላሰቡት ፍጥነት ጩኸታቸው በጦር ሠራዊት ተቀማ። የያዙትን “የመሬት ላራሹ”ን ጥያቄም ደርግ ወስዶት ያቀነቅነው ጀመር። ጥያቄዎች ተለውጠው “ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም” ማለት ተጀመረ። ኢሕአፓ በከተማ ውስጥ በህቡዕ መንቀሳቀስ ጀመረ። ድንገት አንዲት የጠመንጃ ምላጭ ተሳበች። ምላጯን የሳበው ኢሕአፓ ነው ተብሎ ምክንያት ተሰጠና ትውልድ በየጎዳናው ደሙ ፈሰሰ። አስክሬኖች የትም ተጣሉ። ኢትዮጵያ በታሪኳ የሐዘን ማቅ የለበሰችበትን ታሪክ ፈፀመች።

ክፍሉ ታደሰ የዚያን ትውልድ ውጣ ውረድ ደረጃ በደረጃ ስለፃፈው በአሁኑ ወቅት በርካታ ታሪክ ፀሐፊዎች ይህን መፅሃፉን ዋነኛው የታሪክ ምንጭ አድርገው ይጠቀሙበታል። ክፍሉ ታደሰ በተቻለው መጠን በዚያን ዘመን የነበረውን የታሪክ ሒደት መዝግቦታል። አፃፃፉ ደግሞ የተወሳሰበውን ታሪክ ቀለል ባለ መልኩ እና ለሁሉም አንባቢ ግልጽ በሆነ አቀራረብ ስለሰነደው የተወዳጅነቱም ምስጢር ይሄው ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ወቅት ብቅ ብሎ ድንገት ደግሞ ህይወቱን በየጎዳናው ገብሮ ብን በማለት የጠፋው ወጣት ያ ትውልድ ተብሎ መፅሃፍ ታትሞለታል። ያንን ትውልድ የሚዘክሩ ቋሚ ሀውልቶች፣ ጎዳናዎች፣ ቴአትር ቤቶች፣ ሆስፒታሎች ወዘተ የሉንም። መስቀል አደባባይ ላይ የቆመው የሰማዕታት መታሰቢያም በውስጡ ገና ብዙ ነገሮችን ማሰባሰብ ይቀረዋል። ስለዚያ ትውልድ ኪነ-ጥበባችንም ገና አልዘከረውም። መች ፃፍንለት? መች ቴአትር ሰራንለት? መች ፊልም ሰራንለት? በነገራችን ላይ ስለፊልም ስናነሳም ስለዚያ ትውልድ ውጣ ውረድ ፊቸር ፊልም የሰራለት ይሔው ክፍሉ ታደሰ ነው። የፊልሙ ርዕስ ያልደረቀ ዕንባ ሲሰኝ ለእይታ የበቃውም በ1997 ዓ.ም ላይ ነበር።

ጊዜው አሁንም አልረፈደም። በተለይ የኪነ-ጥበብ ሰዎች በዚህ ዙሪያ በርካታ ጉዳዮችን ሊያበረክቱልን ይችላሉ። የክፍሉ ታደሰን ያ ትውልድን በማንበብ ብዙ የፈጠራና የእውነተኛ ታሪኮችን የሚዘክሩ የጥበብ ትሩፋቶችን ማመንጨት ይቻላል። ዛሬ በህይወት የሌለው ገጣሚውና ሰዓሊው ገብረክርስቶስ ደስታ እንዳለው፡-

“ደግሞ ማወቅ ማለት. . .

ከውጭ ያለውን ሔዶ ከመፈለግ

ከውስጥ የበራውን፣ እንዲወጣ ማድረግ. . .”

ብሎ እንደፃፈው ሁሉ፣ የክፍሉ ታደሰ የዚያ ትውልድ ታሪክ ከውስጥ የበራ ብርሃን ነው። ያን ብርሃን ለማየት ከሞከርን ብዙ ባለራዕይ ትውልዶችን ልንፈጥር እንችላለን።

እርግጥ ነው መፅሃፍ ማዘጋጀት ከባድ ስራ ነው። የዚያ ትውልድ አባላት እምብዛም ስለ ታሪካቸው አልፃፉም። ክፍሉ ታደሰ ያንን ሁሉ ትውልድ ወክሎ እስከ አሁን ድረስ የኢሕአፓን ታሪክ እየዘከረ ይገኛል። ኢሕአፓን ከመሰረቱትና ከመሩት ከዚያን ጊዜ ወጣቶች መካከል ዛሬ በህይወት የተረፉት ከአራትና አምስት አይበልጡም። ከተአምር ከተረፉት ውስጥ ዛሬም ድረስ በህይወት ያለው ክፍሉ ታደሰ ነው። ምናልባት ፈጣሪ በሕይወት ያቆየው የጓደኞቸን የዚያን ዘመን ታሪክ እንዲፅፍ ይመስላል። የዚያን ትውልድ ታሪክ ለመፃፍ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ ዘጠኝ አመታት ሙሉ ቤቱን ዘግቶ ያዘጋጃቸው መፃህፍት እንደገና የህትመት ብርሃን አግኝተዋል። ‘ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ’ እንደሚባለው ሁሉ የዚያ ትውልድ አብዮት ጠንሳሽና አመራር አባል የሆነው ክፍሉ ታደሰ፣ የኖረበትን የትውልድ ጅረት መፅሀፍ አድርጎት ሀውልት ሰርቶለታል። ያ ትውልድ ከየቤቱ ወጥቶ ሕይወቱን ሰጥቶ ህልም አሳይቶ አልፏል። ለሀገሩ የሰጠውን ህይወት እንዘክረው ዘንድ ቢያንስ ታሪኩን ማንበብ ግድ ይለናል። የክፍሉ ታደሰን ያ ትውልድ፣ እድልና ገጠመኝ ብኩን ቢያደርገውም ታሪኩ ግን ሕያው ነው።

ይምረጡ
(22 ሰዎች መርጠዋል)
17617 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us