ራስታዎች፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እና ቀሪው ዓለም

Wednesday, 04 June 2014 12:42

በጥበቡ በለጠ

ጀማይካ የምትባለው ሀገር በተጠራች ቁጥር የኢትዮጵያ ስም አብሮ ብቅ ይላል። ኢትዮጵያ እና ጀማይካ እጅግ የተሳሰረ ዝምድና እና ቁርኝት ከፈጠሩ ቆዩ። በተለይ ደግሞ ጀማይካዊያን ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር በቃላት ከመግለፅ አልፎ መንፈሳዊም ሆኗል።

በርካታ የጀማይካ ዜጎች ኢትዮጵያን ቅድስቲቱ ምድር እያሉ ይጠሯታል። አንዳንዶቹ ደግሞ ኢትዮጵያ ቅድስት ምድር ስለሆነች በጫማችን አንረግጣትም ብለው በባዶ እግራቸው የሚሔዱባትም አሉ።

ታዲያ የዚህ ሁሉ ፍቅር መንስኤውና መነሻው ምንድን ነው ብለን ስንነሳ አንድ ሰው ከፊታችን ድቅን ይላሉ። ይህ ሰው ጀማይካዊው ማርክስ ጋርቬይ ነው።

ጋርቬይ የተወለደው እ.ኤ.አ. ነሐሴ 17 ቀን 1887 ዓ.ም ሲሆን ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በሳል እየሆነ መጣ። ምክንያቱ ደግሞ አባቱ መፃህፍት አንባቢ እና ተመራማሪ በመሆኑ የአባቱን ፈለግ እየተከተለ ገና በልጅነቱ አያሌ መፃህፍትን አነበበ። በዚህም ጊዜ በአለም ላይ ያለውን ፍትሃዊነት እኩልነት፣ እና ታሪክን ሁሉ ማወቅ ጀመረ። በወቅቱ ደግሞ ጥቁር የሆኑ ህዝቦች እንደ ሰው ልጅ ፍጡር አይታዩም ነበር። እጅግ ተጨቁነው በባርነት ሰንሰለት ተሳስረው መከራ የሚያዩበት ወቅት ነበር። በንባብና በትምህርት እየዳበረ የመጣው ማርክስ ጋርቬይ ይህን አስከፊ ህይወት ለመቀየር ተነሳ።

በ19መቶ 12 ጀምሮ በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተዘዋወረ ጥቁሮችን ማደራጀት እና ለእኩልነታቸውም እንዲታገሉ መቀስቀስ ጀመረ። የቅስቀሳውንም መጠሪያ እየቀያየረ እና ማደራጀት በሚያስችለው መንገድ ሁሉ ይሰይም ነበር። ለምሳሌ Black nationalism (ጥቁር ብሔርተኛ) ወይም Pan Africanism (የአፍሪካ ጥምረት፣ ታላቅነት) እያለ ይጠራ ነበር።

ታዲያ ለነፃነትም ምሳሌ ያስፈልጋልና የነፃነት ተምሳሌት ሆና በወቅቱ ለነበሩ ጥቁሮች የምትቀርበው ኢትዮጵያ ነበረች። ጥቁር ሁሉ በባርነት ስር በወደቀበት ወቅት ለትግል ማነሳሻ ታገለግል የነበረችው ኢትዮጵያ መሆኗ በታሪክ ውስጥ ተፅፎ ይገኛል። በተለይ ደግሞ አድዋ ላይ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን በቅኝ ገዢዎች ላይ ያሳረፉት በትር ጭቆናን እና ባርነትን አሽቀንጥሮ መጣያ ምሳሌ ተደርጎ በጥቁሮች አንደበት ተደጋግሞ ተነሳ። እነ ማርክስ ጋርቬይም ይህን ጉዳይ መቀስቀሻ አድርገው ሲጠቀሙበት ቆዩ። ኢትዮጵያም የመላው ጥቁር ህዝቦች የትኩረት አቅጣጫ ሆነች።

እንዲህ ምሳሌ ሆኖ ታገለግል የነበረችው ኢትዮጵያ ተመልሳ በኢጣሊያኖች ወረራ ሥር በ1928 ዓ.ም ገባች። የፋሽስት ኢጣሊያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ተቆጣጠረ። ንጉሡ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከስልጣናቸው ተነስተው ተሰደዱ። አርበኞች ቅኝ ገዢዎችን ለመፋለም በዱር በገደሉ ተሰማሩ።

ታዲያ በዚያን ወቅት ማርክስ ጋርቬይ የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ስደት የማይደግፍ ቢሆንም ተስፋው የነበረችው ኢትዮጵያ በመወረሯ የተቃውሞ ድምፁን በሰፊው ሲያሰማ ኖሯል።

ጥቁሮች ተስፋ ያደረጉባት የነፃነት ምድሪቱ ኢትዮጵያ ዳግም ስትወረር የሞራል መነካት አስከትሎባቸው ነበር። ነገር ግን በአምስት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ አርበኞች በተስፋፊዎችና በቅኝ ገዢዎች ላይ ድልን ተጎናፅፈው ነፃነታቸውን መልሰው ሲቀበሉ የጥቁሮችም የነፃነት ትግል ተሟሟቀ።

ባጠቃላይ ሲታይ ማርክስ ጋርቬይ የጥቁር ህዝቦችን አንድነትና ለነፃነታቸው የሚደረገውን ትግል በመምራት በእጅጉ የታወቀ ሰው ነው። Negro Improvement Association and pan African Communities League ወይም የጥቁሮች ብልጽግና ማህበርና የአፍሪካ ማህበረሰብ የጥምረት ሊግ እያለ ትግሉን አፋፋመ።

የተስፋይቱ ምድር እየተባለች የምትጠራው ኢትዮጵያም በዚያን ጊዜ ስዕለ ገፅታዋ በእውን የታየበት እና ጎልታም የወጣችበት ነበር። ነገ እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2006 ዓ.ም በብሔራዊ ሙዚየም የሚከፈተው ኤግዚብሽንም ይህ ማርክስ ጋርቬይ የተባለ ጀማይካዊ ለመላው ጥቁሮች ያበረከተው የድል ብስራትና ውጣ ውረዱ ሁሉ እንደሚዘከር ለመረዳት ችለናል። በነገራችን ላይ ማርክስ ጋርቬይ ይህችን አለም በሞት የተሰናበተው እ.ኤ.አ ሰኔ 10 ቀን 1940 ዓ.ም በስትሮክ ህመም ምክንያት በ52 ዓመቱ ለንደን ውስጥ ነበር። አስክሬኑም ለቀብር ሳይበቃ በሳጥን ውስጥ ተቀምጦ ለሀያ አመታት ቆየ። በኋላ ጀማይካዊያን ወደ ሀገራቸው ወስደውት ቁጥር አንድ የጀግኖች ተምሳሌት አድርገው ስርዓተ ቀብሩን ፈፀሙ።

ሌላው የጀማይካዊያንና የመላው ጥቁር ህዝቦች ተወዳጅ ከያኒ የሆነው ቦብ ማርሊም ነገ በሰፊው ይዘከራል። ቦብ ማርሊ በሙዚቃው ንዝረት እና መልዕክት ዓለምን ጉድ ያሰኘ ከያኒ ነበር።

ቦብ ማርሊ ኢትዮጵያ እና ጀማይካ በደምና በአጥንት የተሳሰረ ዝምድና እንዲኖራቸው ያደረገ ብርቅ ሙዚቀኛ ነበር። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን መለያው አድርጎ የኖረ እና ለዚህችም ሀገር እውቅና ብዙ የሰራ የጥበብ ሰው ነው።

በአንድ ወቅት ወደ ኢትዮጵያም መጥቶ ሀገሪቱን የጎበኘ እና ሻሸመኔ ድረስም ሄዶ ተጫውቶ ተደስቶ ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ሻሸመኔ ሳይቀር ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እየተጠራ ሲዘፍን ኖሮ ያለፈ ባለውለተኛችን ነው።

በቅርቡ በብሔራዊ ሙዚየም የተከፈተው ኤግዚቭሽን ይህን የሙዚቃ ሊቅም በሰፊው እየዘከረው ይገኛል።

ከዚህ ሌላ የጋናው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ክዋሜ ንክሩህ ማህ እና የኢትዮጵያው የቀድሞው ንጉሠ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴም በተለይ ጀማይካን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙበትም ጊዜ የኤግዚቢሽኑ አካል ይሆናል።

ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጀማይካን በጎበኙት ወቅት እጅግ ብዙ ህዝብ ኪንግ ስተን ውስጥ ወጥቶ ተቀብሏቸዋል። በወቅቱ የተሰራው ዶክመንተሪ ፊልም እንደሚያሳየው ከሆነ ዝናብ ዘንቦበት የማያውቀው ኪንግስተን ከተማ የዚያን ቀን ኃይለኛ ዝናብ ወረደበት። ታዲያ በዚህ ዝናብ ውስጥ ሆኖ ለንጉሡ ያለውን ከፍተኛ ደስታ እና ስሜት ህዝቡ ሲገልፅ ይታያል። የጃማይካ እና የኢትዮጵያ ትስስርም የዘላለም መሰረቱን የጣለውም የዚያን ቀን ይመስላል።

ጀማይካዊያኑ ወይም ራስ ተፈሪያዊያን እየተባሉ የሚጠሩት ሰዎች ላለፉት አራት ዓመታት በአሜሪካ፣ በእንግሊዝና በጀማይካ እንዲሁም እንደ ሜክሲኮ ባሉ የደቡብ አሜሪካ ሐገራት የኢትዮጵያንና የጀማይካን ግንኙነቶች በተመለከተ ትልልቅ ኤግዚብሽኖችን አዘጋጅተዋል።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
12499 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us