ተአምረኛው ዛፍ - ሞሪንጋ

Wednesday, 04 June 2014 12:45

በጥበቡ በለጠ

 

በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ማህበረሰቦች አካባቢ ለምግብነት የሚያገለግለው ሞሪንጋ /ሽፈራሁ/ እየተባለ የሚጠራው ዛፍ ተአምረኛ ነው እየተባለ ነው።

የተለያዩ ዓለማቀፍ የምግብ ጥናት የሚያደርጉ ምሁራን በሞሪንጋ ላይ ባካሔዱት ምርምር ዛፉ በውስጡ አምቆ የያዘው ንጥረ ነገር ለሰው ልጆች ሁሉ ጠቀሜታ እንዳለው ይገልፃሉ።

ማሪያ ጄክ ሼፕርድ የተባሉ የህክምና ሰው ለ15 ዓመታት በተክሉ ላይ ባደረጉት ጥናት በርካታ አዎንታዊ ነገሮችን እንዳገኙበት ይገልፃሉ።

እንደ እርሳቸው አባባል ሞሪንጋ በውስጡ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ንጥረ ነገር እንደያዘ እና ለሰው ልጅ ጤና ጠቃሚም መሆኑን ያስረዳሉ። ሰዎች ከመጠን ባለፈ ውፍረት የሚቸገሩ ከሆነም ሞሪንጋ በስርዓት ከተጠቀሙ ችግራቸው እንደሚቀንስላቸው ተናግረዋል። ከዚህ ሌላ ከልዩ ልዩ በሽታዎችም እንደሚከላከል ገልጸዋል።

በመላው ዓለም የታወቀው እና መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ዲስከቨሪ ቻናል ተብሎ የሚጠራ የሚዲያ ተቋም /The Miracle Tree/ “ተአምረኛው ዛፍ” በማለት ዶክመንተሪ ፊልም ሰርቶለታል።

ሞሪንጋን መመገብ ጤንነት ነው። ለሰውነትም ጥንካሬ ይሰጣል ነው የሚለው ዶክመንተሪ ፊልሙ።

ሞሪንጋ በአፍሪካ፣ በኤዥያ፣ በደቡብና በመካከለኛው አሜሪካ ውስጥ በተወሰኑ ማህበረሰቦች ብቻ እንደሚዘወተርም ተመራማሪዎቹ ይገልፃሉ።

ሞሪንጋ የሚገርመው ባህሪው ደረቅ በሆነ አካባቢ ላይ ለምለም ሆኖ መብቀሉ እና ሌሎች ተክሎች አልበቅል እያሉ በሚያስቸግሩበት ስፍራ ላይ ለሰዎች ጥቅም ሊሰጥ ዥርግግ ብሎ የሚመጣ ዛፍ ነው። ሞሪንጋ ደግ እና ቸር የሆነ ዛፍ ነው ይሉታል ሳይንቲስቶቹ።

ሞሪንጋ በውስጡ ዘይት አለ። አያሌ ቫይታሚኖችን አምቆ የያዘ ተክል ነው። Vitamin A በውስጡ ይዟል።

ዶ/ር ሞኒካ የተባሉ ተመራማሪም Miracle Tree ብለው መፅሐፍ አሳትመውለታል። ይህ ሞሪንጋ ዛፍ በአለም ላይ አስደናቂ ዛፍ ነው ሲሉም ተናግረውታል።

የህክምና ባለሙያ የሆኑት ሞኒካ ሲናገሩ፣ ዛሬ በአለም ላይ የልብ በሽታ፣ ካንሰርን ሌሎችም የሰውን ልጅ እያጠቁት ነው። ለዚህ መከላከያም አትክልቶችን መመገብ በጣም ጥሩ ነው። አትክልቶች የራሳቸው የሆነና የተወሰነ ጠቀሜታ አላቸው። ሞሪንጋ ግን በውስጡ በርካታ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ አስገራሚ ሆኗል ይላሉ።

ሞሪንጋ የሌለው ነገር የለም እየተባለ ነው። Vitamin E በውስጡ እንዳለ ሲነገር ሌላው ሳይንቲስት ደግሞ ፕሮቲንም ይዟል ይላሉ። ፕሮቲንን ከቅጠላ ቅጠል ማግኘት እምብዛም የተለመደ አይደለም። ሞሪንጋ ግን በዚህ የታደለ ነው ይላሉ ተመራማሪው።

ሌላው ሳይንቲስት ደግሞ ኃይል ሰጪ ነው። ያጠነክረናል በማለት ሞሪንጋን ይገልጹታል። ሞሪንጋ ሃያ ከሚሆኑ የተክል ንጥረ ነገሮች ውስጥ 18ቱን በመያዝ ትልቁን ስፍራ ይይዛል ባይ ናቸው ተመራማሪዎቹ።

ሞሪንጋ በውስጡ አሚኖ አሲድ የተባለው ንጥረ ነገርንም እንደያዘ ተገልጿል። አሚኖ አሲድ እንዲህ በቀላሉ የሚገኘው ሞሪንጋ ውስጥ ነው ተብሏል።

በአፍሪካ ውስጥ የህፃናት ሞት በስፋት ይታያል። ነገር ግን ሞሪንጋ ባለባቸው አካባቢዎችና ሞሪንጋን በሚመገቡ ስፍራዎች ችግሩ በእጅጉ እንደሚቀንስም ይወሳል። ስለዚህ ሞሪንጋ ልጆችንም የሚታደግ ዛፍ እንደሆነ እየተወሳ ነው። የድሃን ልጆች የሚንከባከብ ተክል ነው እየተባለም ነው።

  • ሞሪንጋ ውድ ያልሆነ፣ ነገር ግን በጣም የሚያገለግል ዛፍ ነው
  • ሳይንቲስቶች ሲናገሩ ይህን ዛፍ ደግመን ደጋግመን ልንተክለው ልናስፋፋው ይገባል ይላሉ።
  • ሌላው ሳይንቲስት ሲናገሩ ሞሪንጋ በውስጡ ይህን ሁሉ ነገር መያዙ እና ጠቀሜታ መስጠቱ ያስገርማል ብለዋል።
  • ለ15 ዓመታት ሞሪንጋን ያጠኑት የህክምና ሴት ሲናገሩ ሞሪንጋ የአልሚ ንጥረ ነገሮች ምንጭ ነው። በውስጡ አያሌ ጉዳዮችን ይዟል ሲሉ ተናግረዋል።

     ስለዚህ በሀገራችን ውስጥስ ስለ ሞሪንጋ የሚደረጉ ጥናቶችና ምርምሮች ምን ይመስላሉ የሚለውን ደግሞ መነጋገሪያ ብናደርገው መልካም ነው።

ይምረጡ
(35 ሰዎች መርጠዋል)
19111 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us