ኢትዮጵያን እና ቋንቋዋን በአውሮፓ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ መማሪያ ያደረገው ጀርመናዊ አውግስቶ ዲልማን ከ1815-1886

Wednesday, 11 June 2014 13:43

በጥበቡ በለጠ

 

ዛሬ የማወጋችሁ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን፣ ግን ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ የዋለን አንድ የቋንቋ ሊቅን ነው። ይህ ሰው ከዛሬ አንድ መቶ ሃምሳ ዓመት በፊት የኢትዮጵያን ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ አጥንቶ ለአለም ያስተዋወቀ ነው። ኢትዮጵያ ሐገራችንን በልዩ ልዩ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የጥናትና የምርምር ማዕከል እንድትሆን ያደረጋት ሰው ነው። ይህ ሰው ኢትዮጵያ ጥንታዊት ሀገር እንደሆነች በውስጥዋም ለአለም ዜጎች ሁሉ የሚተርፍ የሥልጣኔ ሀብት እንዳላት የመሰከረ የባህር ማዶ ሰው ነው። በእርሱ ፅሁፎች የተነሳ የጀርመን ሀገር ልዩ ልዩ ዩኒቨርስቲዎች፣ የእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ፣ ካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ፣ የኢጣሊያ ሀገር የሚገኙ የተለያዩ የምርምር ተቋማት እና ሌሎችም በዚያን ዘመን የዚህን ሰው መፃሐፍት መሠረት አድርገው ኢትዮጵያን የጥናትና የምርምር ትኩረታቸው አድርገው እንዲወስዷት ውለታ የዋለልን አውሮፓዊ ነው። ይህ ሰው ጀርመናዊው አውግስቶ ዲልማን ይባላል።

አውግስቶ ዲል ማን በኢትዮጵያ ፍቅር ከወደቁ የውጭ ሀገር ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ዲልማን ከ120 ዓመታት በፊት ከአውሮፓ ተነስቶ ኢትዮጵያን አጥንቶ የብዙ ሺ ዘመን የባህል፣ የቋንቋ፣ የህዝቦች መኖርያ እና የበርካታ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ባለቤት መሆኗን በፅሁፎቹ ካረጋገጠ በኋላ አንድ ዳጎስ ያለ መፅሐፍ አሳተመ። ይህ መፅሐፍ ስለ ጥንታዊው የኢትዮጵያ የግዕዝ ቋንቋ መሰረት አድርጎ የፃፈው ነው።

እንደ ዲልማን መግቢያ እና ገለፃ፣ ግዕዝ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይም ካሉ ጥንታዊ ቋንቋዎች መካከል አንዱ ነው። በዚህም የተነሳ በውስጡ የተመራማሪዎችን ቀልብ የሚገዙ ጉዳዮች እንዳሉትም ይገለፃል። ቋንቋው በጥቁር ህዝቦች ታሪክ ውስጥ በፅሁፍ ተቀምጦ ስለአለፉት ዘመናት የሚተርክ የታሪክ ቅርስ ከመሆኑ አንጻር ሊመረመር፣ ሊጠና እንደሚገባ ከዛሬ 120 ዓመታት በፊ ጀርመናዊው አውግስቶ ዲልማን በመፅሐፉ መግቢያ ላይ ገልፆታል።

ከዚህ ገለፃው በኋላም አውሮፓውያን እና የሌሎች ዓለም ሰዎችም ግዕዝን እንዲያጠኑት እና እንዲመራመሩት የሚያስችላቸውን መፅሀፍ አሳተመላቸው። መፅሀፉ ስለ ግዕዝ ቋንቋ አፈጣጠር፣ የድምፅ አወጣጥ፣ ስለፊደላቱ፣ ስለ ስርዓተ ነጥቡ፣ ባጠቃላይ ስለ ቋንቋው ሰዋሰው እና መዋቅር የሚተነትን የማስተማሪያ ሰነድ አዘጋጀ። ሰዎች የግዕዝ ቋንቋን በቀላሉ የሚያውቁበትን መንገድ የሚመራን መፅሐፍ አሳተመ ዲልማን።

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ልንል እንችላለን። አንድ ጀርመናዊ ከመቶ ሃያ ዓመታት በፊት ወደ ሀገራችን መጥቶ ስለ ራሳችን ቋንቋ አጥንቶ ከዚያም ሌሎችም እንዲማሩበት መንገድ የሚከፍት ጥናት ሲሰራ ማየት ያስገርማል። እኛ እንደ ዋዛ እያየን የተውነውን ግዕዝ እርሱ ግን በውስጡ ምስጢር አለ፤ እውቀት አለ፤ ታሪክ አለ፤ ሳይንስ አለ፤ ፍልስፍና አለ እያለ ለባህር ማዶ ሰዎች የግዕዝ መማሪያ አዘጋጀ።

ጀርመናዊው ደልማን በዚህ ብቻም አልቆመም። ሌላ አንድ በእጅጉ የሚያስገርመንንም ታሪክ ያከናወነ ሰው ነው። ዲልማን ግዕዝን አውሮፓውያን እንደ እራሳቸው ቋንቋ ወስደው እንዲያጠኑት እና እንዲመራመሩበት የግዕዝ ቋንቋ መዝገበ ቃላት /ዲክሽነሪ/ አዘጋጀላቸው። መዝገበ ቃላቱ ግዕዝን በላቲን ቋንቋ አድርጎ አውሮፓውያን እንዲያነቡት፣ በቀላሉ እንዲረዱት፣ አውቀውም ምርምር እንዲያደርጉበት የሚያስችል መፅሐፍ አዘጋጀ።

በዚህ የተነሳ የግዕዝ ቋንቋ በልዩ ልዩ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች የጥናትና የምርምር ቋንቋ ሆኖ እንዲመጣ አውግስቶ ዲልማን ትልቅ ውለታ አበርክቷል። አውሮፓውያንም በሀገራቸው ውስጥ ግዕዝን እንደ አንድ የቋንቋ ትምህርት በዩኒቨርስቲዎቻቸው አማካይነት እንዲማሩት እና እንዲመረቁበት የሚያስችል የእውቀት መንገድ የቀየሰ የቋንቋ ሊቅ ነው።

እርግጥ ነው እዚህ ላይ አንድ መገለፅ ያለበትም ጉዳይ አለ። ይህም የግዕዝን ቋንቋ አውሮፓውያን ማጥናት የጀመሩት ከዲልማን በፊት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ገና ከ13ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ አውሮፓውያን የግዕዝን ቋንቋ እየተመራመሩበት እንደነበር ጥናቶች ያመለክታሉ። ለምሳሌ የመጀመሪያው የግዕዝ ሰዋሰው የታተመው በ1661 ዓ.ም ነው። ይህ ማለት የዛሬ 343 ዓመት ግድም ነው። ታዲያ በዚያን ዘመን የታተመውንም የግዕዝ ሰዋሰው ያዘጋጀውና ያሳተመው ጀርመናዊው ኢዮብ ላይፋ የተባለ ሰው ነው። ይህ ሰው የግዕዝን ቋንቋ ያወቀው የዛሬ 343 ዓመት ወደ አውሮፓ ከሔዱት ኢትዮጵያዊ መነኩሴ ከአባ ጎርጎሪዎስ ዘንድ ነበር። ግዕዝን ከእርሳቸው ዘንድ ተምሮ ለቋንቋው የሰዋሰው መፅሐፍ ያዘጋጀ የጥናት ሊቅ ነው።

ይህ ሰው መች በዚህ ብቻ አቆመ። ሌላ አስገራሚ እና አስደንጋጭ መፅሐፍም የዛሬ 343 ዓመት አሳትሟል። መፅሐፉ የአማርኛ ቋንቋ ሰዋሰው ሲሆን፣ ታዲያ በዚያን ዘመን አማርኛ ገና ራሱን ችሎ ለመቆም የሚውተረተርበት ወቅት ነበር። ከግዕዝ ውስጥ ተፈልቅቆ የወጣው አማርኛ፣ ሥርዓቱን የፃፈለትና መፅሐፍ ያሳተመለት ከዛሬ 300 ዓመታት በፊት የኖረው ጀርመናዊው ኢዮቭ ሉዶልፍ እንደሆነ መምህር ደሴ ቀለብ “ትንሳኤ ግዕዝ” በሚል ርዕስ ባሳተሙ ዳጎስ ባለ መፅሐፋቸው መግቢያ ላይ ጠቅሰውታል።

ከእዮብ ለይለፉ በመለጠቅም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጆሜር የተባለ ሰው እና ፔተን እንዲሁም ማሪያ ቪክቶሪየስ የተባሉ የቋንቋ ተመራማሪዎች ግዕዝን አጥንተው ቋንቋውን አውሮፓውያን እንዲያውቁት መፃሕፍት አሳትመዋል።

እነዚህና ሌሎችም ዛሬ ያልጠቀስኳቸው የቋንቋ ተመራማሪዎች ግዕዝን ቢያጠኑትም ነገር ግን የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን እንደሆነው እንደ አውግስቶስ ዲልማን ያለ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ አልቻሉም። ዲልማን ኢትዮጵያ እና የግዕዝ ቋንቋ በተለያዩ የአውሮፓ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በትምህርት እንዲሰጡ ማድረግ የቻለ የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቋንቋ እና ባህል ብሎም የታሪክ ፊት አውራሪ የሆነ አውሮፓዊ ነው።

ለመሆኑ ይህ የጀርመን ተወላጅ የሆነው አውግስቶ ዲልማን ማን ነው?

ዲልማን የተወለደው እ.ኤ.አ ሚያዚያ 25 ቀን 1823 ዓ.ም ኢልንን በተባች በጀርመን ግዛት ውስጥ ነው። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ታሪክን ባህልን እና ቋንቋን ብሎም ሃይማኖትን እየተማረ አደገ። በኋላም ቱቢንገን በተባለ የጀርመን ዩኒቨርስቲ ውስጥ የነገረ ሃይማኖት መምህር ሆነ።

የዲልማን አባት የተማረ እና የትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሁሉ የነበረ ነው። ልጁ ዲልማንም በትምህርቱና በእውቀቱ የዳበረ እንዲሆን ብዙ አድርጎለታል።

ዲልማን የዓለምን ታሪክ በየዩኒቨርስቲው እየዞረ ሲያነብ ፓሪስ እና ለንደን ውስጥ ያነበባቸው የኢትዮጵያ ታሪኮች ስሜቱን ነኩት። ስለዚህ ትኩረቱን ወደ ኢትዮጵያ አድርጎ ሀገሪቱን ያጠናት ጀመረ።

ዲልማን ኢትዮጵያን ሲያጠና በተለይ ከዓለም ላይ የጠፋውን እና በመጨረሻም ከኢትዮጵያ ብቻ የተገኘውን የመፅሐፍ ቅዱስ አንድ ክፍል ውስጡን መሰጠው። ይህ በዓለም ላይ ጠፍቶ የነበረው የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል መፅሐፈ ሄኖክ ይባላል። ከኢትዮጵያ ደግሞ ጀምስ ብራስ የተባለ የስኮትላንድ ተጓዥ ሰርቆት ወደ አውሮፓ ወሰደው። የዛሬ 150 ዓመት ዲልማን አውሮፓ አግኝቶት በዚህ በመፅሐፈ ሄኖክ ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር አድርጎ መፅሐፍ አሳተመ።

አውግስቶ ዲልማን ኢትዮጵያ ላይ በርካታ ጥናቶችን እያደረገ አያሌ ጉዳዮችን አሳትሟል። እነዚህ የህትመት ውጤቶች ጥቂቶቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቢገኙም አብዛኛዎቹ በጀርመን፣ በለንደን እና በፓሪስ ከተሞች ውስጥ ባሉ ትልልቅ ቤተ-መፃሐፍቶች ውስጥ ናቸው።

     ይህ የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ላይ እጅግ ተመስጦ እና ፍቅር የነበረው ጀርመናዊ በመጨረሻም የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝቷል። አውግስቶ ዲልማን ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር በርካታ ውለታ አበርክቶ እ.ኤ.አ ሐምሌ 7 ቀን 1894 ዓ.ም ማለትም የዛሬ 120 ዓመት ጀርመን በርሊን ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ዲልማን ለኢትዮጵያ ቋንቋ እድገት ባበረከተው ውለታ ሁሌም ስሙ የሚነሳ የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ባለዝና ነው።


ይምረጡ
(17 ሰዎች መርጠዋል)
12046 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us