You are here:መነሻ ገፅ»ኪነ-ጥበብና ባህል

 

የቀድሞው የአውራምባ ታምስ እና ጎግል ጋዜጦች አዘጋጅና ዘጋቢ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ከሰባት ዓመት እስር በኋላ ከእስር በወጣ በወራት ልዩነት “ኢትዮጵያዊነትን የመመለስ ተጋድሎ” የሚለውን መጽሀፉን ለአንባቢያን አቀረበ።

“እስር ቤት በነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ እጽፋቸው የነበሩ ስራዎችን ነው በአንድ ላይ አሰባስቤ ያሳተምኩት” ሲል ለሰንደቅ ጋዜጣ የተናገረው ጋዜጠና ውብሸት ታዬ፤ እንዳለፉት መጽሀፎቹ ሁሉ የአሁኑ መጽሃፉም አገራዊ ጉዳዮችን የያዘ ነው። 120 ብር ከአንባቢያን ኪስ የሚጠይቀው “ኢትዮጵያዊነትን የመመለስ ተጋድሎ”፤ 228 ገጾች የመጽሀፉ ከፍታ ልኬቶች ናቸው።

ጋዜጠኛ ውብሸት በዚህ ስራው በብዛት ስለ እስር ቤት ቆይታውና ብሎም በእስር ቤት ስላጋጠሙት የኢትዮጵያዊያን ሰቆቃ የሚዳስስ ሲሆን፤ አገሪቱ ውስጥ ያሉ መጽሃፍ አዟሪዎች “ኢትዮጵያዊነትን የመመለስ ተጋድሎ”ን አንባቢን ባሉበት ቦታ ለማድረስ እጃቸው ላይ ይዘውት ይዞራሉ። አንባቢንና የመጽሃፍ ገዥዎች ወደ መጽሃፍ አከፋፋዮች መደብር ጎራ የሚሉ ከሆነ ደግሞ በአከፋፋዮች መደብር መደርደሪያ ላይ “ኢትዮጵያዊነትን የመመለስ ተጋድሎ”ን በክብር ተቀምጦ ገኙታል። ለሸሬታ የቀረበበት ዋጋ 120 ብር ብቻ መሆኑን ግን ልብ ይሏል።

 

የካፍ ኢንስትራክተሩ አብርሃም ተክለሀይማኖት ያዘጋጀውና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሮች ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገው መጽሃፍ ባሳለፍነው ቅዳሜ በአዲስ አበባ አክሱም ሆቴል የተመረቀ ሲሆን የፊታችን ቅዳሜ ደግሞ በመቀሌ ይመረቃል።

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ውድቀት ከራሱ ከኢንስትራክተር አብርሃም ጀምሮ ሁሉም የዘርፉ ተዋንያን ተጠያቂ መሆናቸውን በመጽሃፉ ያሰፈረው አብርሃም ተክለሀይማት፤ በተለይ መሰረታዊ የስልጠና እና የአደረጃጀት ችግሮች ዋናዋናዎቹ ችግሮች መሆናቸውን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ራእይ አልባ በሆኑ ሰዎች መያዙን የሚገልጸው ይኸው የአሰልጣኝ አብርሃም ተክለሀይማት መጽሀፍ፤ አጥፊ የማይጠየቅበት እንዲያውም አይዞህ በርታ የሚባልበት የእግር ኳስ አስተዳዳሪዎች መብዛታቸው ኳሱን የኋሊት እንዲጓዝ ምክንያት መሆኑን ይገልጻል።

መጽሀፉ 81 ብር ከሽልንግ ለአንባቢያን (81.50 ብር) የቀረበበት ዋጋ ሲሆን 247ኛው ገጽ ደግሞ የመጽሃፉ የመጨረሻ ክፍል ነው። ሁሉም መጽሃፍ አዟሪዎችና አከፋፋዮች መጽሀፉን ለአንባቢን ለማድረስ በእጃቸው ያስገቡት ሲሆን ህትመቱን ታሪክ አታሚዎች ሰርቶታል።

 

ወጣቷ ገጣሚ ትዕዘዘው ክንዴ አለንጋ የተሰኘውን ሸንቋጭ ግጥሟን የፊታችን እሁድ በብሔራዊ ቤተ መጽሀፍትና ቤተ መዛግብት ኤጄንሲ አዳራሽ ታስመርቃለች።

ቀደም ሲል ጎንደር ከተማ ላይ የተመረቀው ይኸው አለንጋ የተሰኘ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስኮችን የሚዳስስ ግጥም፤ ዕሁድ ከቀትር በኋላ ሲመረቅ አንጋፋና ወጣት የጥበብ ሰዎች ታድመው ምርቃን ያደምቁታል ተብሏል። በምረቃው ዕለትም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች አትሮኖሱ ላይ ወጥተው የመረጡትን የመጽሃፉን ክፍል እያነበቡ ታዳሚያንን ያዝናናሉ።

ከፖለቲካ እና ማህበራዊ ትንኮሳ በዘለለ ፍቅርን፣ ባህልን እና ጥበብን የሚዳስሰው የትዕዘዘው ክንዴ ግጥም 89 ገጾችን ይዟል። አንባቢን ገዝተው ሊያነቡት ቢሹ ደግሞ ግማሽ መቶ ብር ብቻ እንዲከፍሉ መጽሃፍ አዟሪዎችና አከፋፋዮች ይጠይቋቸዋል።

 

በዶክተር ቸርነት ገብረ ክርስቶስ የተጻፈውና 160 ብር ከሸማቾች ኪስ ወጪ እንዲደረግለት የሚጠይቀው ዲባቶ መጽሃፍ ለገበያ ቀረበ፡፡

በ371 ገጾች የታቀፈው ይኸው መጽሃፍ የህክምናን ሙያ በልቦለድ መልክ አዘጋጅቶ ያቀረበ ሲሆን በሁሉም መጽሃፍት መደብሮችና አዟሪዎች እጅ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

‹‹ዲባቶ›› ማለት ዶክተር ማለት ሲሆን የመጽሀፉ ደራሲ ዶክተር ቸርነት ገብረክርስቶስ ለረጅም ዓመታት በአገር ውስጥ የተለያዩ የህክምና ተቋማት ሲያገለግሉ የቆዩና አሁን እያገለገሉ ያሉ ምሁር ናቸው፡፡

 

በይርጋ አበበ

‹‹ወጥቼ አልወጣሁም›› በሚል ርዕስ የታተመው የአቶ ያሬድ ጥበቡ መጽሀፍ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ለሁለተኛ ጊዜ ታተመ።

ከኢህአፓ እስከ ኢህዴን ያለውን የትጥቅ ትግል ከተራ ተዋጊነት እስከ አመራርነት ታግለው ያታገሉትና አሁን በስደት የሚኖሩት አቶ ያሬድ ጥበቡ የተጓዙበትን መንገድ የሚገልጸውን መጽሃፍ ያሳተሙት ባሳለፍነው ሳምንት ነበር። 344 ገጾችን የያዘው ‹‹ወጥቼ አልወጣሁም›› መጽሀፍ 121 ብር ለገበያ የቀረበበት ዋጋ ነው። መጽሀፉን በዋና አከፋፋይነት ለገበያ ያቀረበው ‹‹ሀ ሁ መጽሀፍት መደብር›› ነው።

የሀሁ መጽሀፍት መደብር ባለቤት አቶ ፈንታሁን ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ መጽሀፉ ገበያ ላይ በመፈለጉ በዚህ ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ ታትሞ ለገበያ እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

 

በይርጋ አበበ

 

በኢትዮጵያ የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት የኪነ ጥበቡን ዘርፍ በተለይም በሰዓሊያን ላይ በመጥፎነቱ የሚታወስ መሆኑን ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ካፒታል ጋዜጣ (ክራውን አሳታሚዎች) የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ “ኪነ ጥበብና የኪነ ጥበቡ ተዋንያን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት” በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። በውይይቱ የተገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ሰዓሊያን ባነሱት ሃሳብ ላይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በኢትዮጰያ ያለው የኪነ ጥበብ በተለይም የስዕሉ ዘርፍ እድገቱ አሁንም አዝጋሚ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በተመለከተ ደግሞ ከሌሎች አገሮች ተመሳሳይ ሙያ ጋር ሲነጻጸር ወደኋላ የቀረ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ማህበር የቀድሞ ፕሬዝዳንት አርቲስት ስዩም አያሌው በበኩሉ “የእኛ ተቀዳሚ ደንበኞች ቱሪስቶችና የውጭ አገር ዜጎች ነበሩ። ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገራችን የተፈጠረው የፖለቲካ አለመጋጋት የቱሪዝሙን ዘርፍ ተጎጂ ማድረጉን ተከትሎ የእኛ ጥቅምም አብሮ ተጎድቷል” ሲል ተናግሯል። 

ከመስከረም 2009 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 20 ወራት ውስጥ ለሁለት ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተጣለ ሲሆን በተለይ በ2009 ዓ.ም አገሪቱ ከአስቸኳይ ጊዜ ውጭ ሆና ያሰለፈችው ሁለት ወራትን ብቻ ነበር። በዚህ ዓመትም ከየካቲት 23 ቀን ጀምሮ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ የሚሆን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ በስራ ላይ መሆኑ ታወቃል።

 

ዳክ ኮምዩኒኬሽን “ዳጉ” የመገናኛ ብዙሃን ሽልማት እና ድግስ የተባለ ፕሮግራም ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

የዳሪክ ኮምዩኒኬሽን እና የፕሮግራሙ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ማናዬ እውነቱ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለጸው፤ ዳጉ የመገናኛ ብዙሃን ድግስ እና ሽልማት ሚያዝያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ይፋ ከተደረገ በኋላ በተለያዩ ሆቴሎች በቋሚነት በየወሩ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ ህዝብ ግንኙነትና የኮምዩኒኬሽን ባለሙያዎች እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተገናኝተው ስለሙያው የሚወያዩበትና የሚመክሩበት ዝግጅት ነው።

ዝግጅቱ ዓመቱን ሙሉ ወሩ በገባ በመጨረሻው ሳምንት ሰኞ ሲካሄድ የሚቆየው ፕሮግራም በዓመቱ መጨረሻ በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ታላላቅ ስራዎችን ሰርተው ያለፉ የሚዲያ ባለሙያዎች የሚዘከሩ ሲሆን የዚህ ዓመት የፕሮግራሙ መታሰቢያ ለጋዜጠኛ ደስታ ምትኬ ተበርክቷል። ጋዜጠኛ ደስታ ምትኬ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ የመጀመሪያው የህትመት ጋዜጠኛ ናቸው።

 

የደራሲ ገስጥ ተጫኔ አስረኛ ድርሰት የሆነው “የበቀል ጥላ” ረጅም ልቦለድ ነገ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ይመረቃል።

የ328 ገጾችን በረከት የታደለውና 70 ብር አንባቢያንን የሚያስከፍለው የበቀል ጥላ ነገ ሲመረቅ የደራሲው የቅርብ ወዳጅ ዘመዶች፣ ጸሀፊያን፣ የመገናኛ ብዙሃ ባለሙያዎች እና አርቲስቶች ታዳሚ ይሆናሉ።

ደራሲ ገስጥ ተጫኔ ከዚህ ቀደም “ነበር ቁጥር 1 እና 2” በሚሉት መጽሃፋቸው በአንባቢያን ዘንድ በስፋት ይታወቃሉ። ከሁለቱ መጽሃፎች በተጨማሪም “የናቅፋው ደብዳቤ፣ እናት ሀገር፣ የቀድሞው ጦር፣ የማክዳ ንውዛት” እና ሌሎችም መጽሃፎችን ለአንባቢያን ያበረከቱ ደራሲ ናቸው። መጽሃፉ በሁሉም መጸሃፍት መደብሮች እና መጽሃፍ አዟሪዎች እጅ የሚገኝ ሲሆን ቀደም ብሎ እንደተገለጸው የመጽሃፉ ሸሬታ (የወጋ ተመኑ) 70 የኢትዮጵያ ብር ብቻ ነው።

አርቲስት አበበ አርአያ ከሰሞኑ “ጊዜ” የሚል ርዕስ የሰጠውን አልበሙን አስመርቋል። አርቲስቱ ከዚህ ቀደም እምበር ተጋዳላይ፣ አይርስአከን፣ ዓደይ፣ ቁረፅ በሎ፣ ይአኽለኒ እና ሌሎች የትግል ዘፈኖችን ለአድናቂዎቹ አድርሷል። አዲሱ ግዜ አልበም በአክሱም ሆቴል እንደዚሁም 22 አካባቢ በሚገኘው ፍሪደም ሀውስ በተከታታይ ተመርቋል። ድምፃዊው ሁሉም የጊዜ አልበም ሙዚቃዎቹ በትግርኛ የተሰሩ መሆኑን ገልጾ አልበሙ ከፍቅር ጀምሮ እስከ ሀገር ፍቅር ድረስ ያሉ ሙዚቃዎቹን በአልበሙ ውስጥ ያካተተ መሆኑን አመልክቷል።

 

የደራሲ ፍሰሃ ያዜ ካሴ ስድስተኛ መጽሃፍ የሆነው “የሳጥናኤል ጎል ኢትዮጵያ ቁጥር 2” በያዝነው ሳምንት ለንባብ ቀርቧል።

ደራሲ ፍሰሃ ያዜ ካሴ ከዚህ ቀደም “የሳጥናኤል ጎል ኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ የሰጠው መጽሃፉ በርካታ ሺህ ቅጂዎች የተሸጡ ሲሆን፤ የዚያው መጽሃፍ ቀጣይ ክፍል የሆነው ይህ መጽሃፍ በኢ-ልቦለድ መልክ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል። 360 ገጾች ያሉት ይኸው የሳጥናኤል ጎል ኢትዮጵያ ቁጥር 2 ትንሿ ስታዲየም ጀርባ በሚገኘው “ሀሁ” መጽሃፍት መደብር በኩል የሚከፋፈል ሲሆን 121 ብር ከ50 ሳንቲም ደግሞ ለገበያ የቀረበበት ዋጋው ነው።

የሳጥናኤል ጎል ኢትዮጵያ ቁጥር 2፤ ኢትዮጵያን በሌሎች አገራት ዐይን እንዴት እንደምትገለጽ፣ የሰለጠኑ አገራት በሀብትና በክብራቸው ዓለምን ከሚዘውሩት በተለይም ጂ 20 ከሚባሉት አንጻር ኢትዮጵያ ያላትን ትውፊት እና ባህል ከሀይማኖት እና ከቀዳሚው ገናና ታሪኳ ጋር እያነጻጸረ ያቀርባል።  

Page 1 of 42

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us