You are here:መነሻ ገፅ»arts»news admin - Sendek NewsPaper
news admin

news admin

ዜጋን እየገደሉ መቀጠል

Wednesday, 06 December 2017 13:06

 

በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከሚማሩ የ2ኛ እና የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ከግማሽ በላዮቹ ፅሁፍ ማንበብ እንደማይችሉ የከተማዋ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ባደረኩት ጥናት አረጋግጫለሁ ብሏል። ይሄ ምን ማለት እንደሆነ የሚገባው ከአፉ ላይ ነጥቆ ለልጁ የትምህርት ቤት እየከፈለ ለሚያስተምር ወላጅ ነው። በከተማ አካባቢ አሁን ባለው ሁኔታ አንድ ልጅ ሁለተኛ ክፍል ደረሰ ማለት የመዋዕለ ህፃናት ቆይታውን ጨምሮ  ቢያንስ አምስት አመታትን በትምህርት ገበታ ላይ አሳልፏል። ታዲያ በአምስት ዓመታት የትምህርት ቤት ቆይታው ማንበብ አለመቻል ማለት ምን ማለት ነው? እንኳን አዲስ ነገርን ለመያዝ ፈጣን አእምሮ ያላቸው ታዳጊዎች ቀርተው አዋቂ ሰውም ቢሆን በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ማንበብና መፃፍ የማይችልበት ምክንያት አይኖርም። አሁን እየተሰማ ያለው ነገር ግን አስደንጋጭም አሳዛኝም ነው። አንድ ልጅ ወደ ትመህርት ቤት ሲሄድ የመጀመሪያ አላማው ማንበብና መፅፍን መልመድ ነው። ሌሎች ሌሎች ነገሮች ከዚህ ቀጥለው የሚመጡ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ልጆች ምን ሲሰሩ እየዋሉ ነው ማንበብ እንኳን ያቃታቸው? ለእነዚህ ተማሪዎች የተመደቡ መምህራንስ ምን ሲሰሩ ነው የሚውሉት? ተደጋግሞ እንደሚባለው ትምህርት ቤቶች ቀጣይ ሀገር ተረካቢ ዜጐች የሚፈጠሩባቸው የሁሉም መሠረት የሆኑ ተቋማት በመሆናቸው ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃሉ። በተለይ ህፃናት እና ታዳጊዎች ደግሞ በለጋ እድሜያቸው እና በንፁህ አእምሯቸው ሊቀበሏቸው የሚችሏቸውንና የሚገባቸውን ነገር አግኝተው ማደግ ካልቻሉ በኋላ ላይ ለማስተካከል የሚደረገው ጥረት እጅግ አድካሚ ነው የሚሆነው። ምክንያቶቹ ምንም ይሁኑ ምንም እያንዳንዱ ትምህርት ቤት ተፈትሾ ህፃናት እድሜያቸውን የሚወጥን እውቀትና ግንዛቤ ኖሯቸው እንዲያድጉ የማድረጉ ጉዳይ ሊተኮርበት ይገባል። አንድ ልጅ ፊደልን ማንበብ ሳይችል እንዴት ሆኖ ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላኛው ሊያልፍ ይችላል? የሚለው ጉዳይ ከስር መሠረቱ መፈተሽ የሚያስፈልገው ይመስለኛል። ካልሆነ ግን ትምህርት ቤቶቹ ዜጐችን እየገደሉ መቀጠላቸው አይቀሬ ነው።

አቶ ስንታየሁ - ከቄራ¾

ቁጥሮች

Wednesday, 06 December 2017 13:04

 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

400 ቢሊዮን ብር          የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ

159 ቢሊዮን ብር          በ2017 የተሰጠው ብድር

ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ    የባንኩ ደንበኞች ብዛት

ከ1ሺህ 240 በላይ         የባንኩ ቅርንጫፎች ብዛት

150                   ባንኩ በየዓመቱ በአማካይ የሚከፍታቸው ቅርንጫፎች

ምንጭ፤ አዲስ ልሳን ጋዜጣ ህዳር 23 ቀን 2010¾


በጥበቡ በለጠ

 

በዚህች ምድር ላይ በሰው ልጅ አዕምሮ ከተሰሩ አስደማሚ ጉዳዮች መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ምስጢር ሆነው ስለቆዩት የቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ህንፃዎችና ራሱ ቅዱስ ላሊበላስ ቢሆን ማን ነው? በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው።


እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ 10 አብያተ ክርስቲያናት ትንግርት ሆነው ብቅ አሉ። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት የታነፁት ከአንድ አለት ውስጥ ተፈልፍለው ነው። ስማቸውም ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያናት ወይም በእንግሊዝኛው Rock hewn Churches ይባላሉ።


እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ማለትም UNESCO ምድር ላይ ካሉ እፁብ ድንቅ ኪነ-ሕንፃዎች መካከል እንደ ትንግርት እየቆጠራቸው ስለ እነሱ ብዙ ፅፏል። ከዚህ ሌላም የሰው ልጅ ሁሉ ቅርስ ናቸው ብሎ በዓለም መዝገብ ላይ ካሰፈራቸው በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።


ንጉስ ላሊበላ እነዚህን አብያተ-ክርስቲያናት ለምን ሰራቸው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ጥንታዊ ሠነዶች እንደሚጠቁሙት፣ ኢትዮጵያዊያን በድሮ ጊዜ ወደ እየሩሳሌም በእግራቸው እየተጓዙ ተሳልመው ይመጡ ነበር። ታዲያ በዚህ ጉዞ ውስጥ በርካቶች በግብፅ በረሀ ውስጥ በሽፍቶችና በቀማኞች ይገደሉ ነበር። ይዘረፉ ነበር። ብዙዎች ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም በእግር ተጉዘው ወደ ሀገር ቤት በህይወት የሚመለሰው በጣም ጥቂቱ ነበር። ታዲያ የሕዝቡ ሞት እና እንግልት ያሳሰበው ቅዱስ ላሊበላ ዳግማዊት ኢየሩሳሌምን በኢትዮጵያ እገነባለሁ ብሎ ተነሳ። እናም በ23 ዓመታት ውስጥ በሰው ልጅ አዕምሮ ድንቅ የሚባሉትን 10 ኪነ-ህንፃዎችን ከአንድ አለት ፈልፍሎ ካለምንም የኮንስትራክሽን ስህተት ሠርቶ ጨረሰ።


እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ግን መልስ የሌላቸው። ከነዚህም መካከል እነዚህን ኪነ-ህንፃዎች የሰሯቸው ጥበበኞች በቁጥር ስንት ነበሩ? የሚል ጥያቄ። ግን ማንም ሊመልሰው አይችልም። ሌላው ጥያቄ 23 ዓመታት ሙሉ እንዲህ አለት እየፈለፈሉ ሲሰሩ ለምን ስህተት አልፈፀሙም? ለምን ፍፁም እንከን የለሽ አድርገው ሠሩት? ማነውስ በዘመኑ አርክቴክት የነበረው? የኪነ-ህንፃዎቹ ዲዛይን ምን ላይ የተነደፈው? ማነውስ ከአለት ፈልፍዬ ይህን ተአምር ልስራ ብሎ መጀመሪያ ያሰበው? ብዙ የማይመለሱ ጥያቄዎች አሉ። ለዚህም ነው ላሊበላ የምድሪቱ ትንግርት ነው የሚባለው።
የላሊበላ ምስጢራት ተዘርዝረው አያልቁም። ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ኩነ-ህንፃዎቹ በሙሉ ማለት ይቻላል የታላላቅ ፍልስፍናዎችና አመለካከቶች ማንፀባረቂያ የሆኑ ምልክቶች አሉት። ግድግዳው በሙሉ ጥበብ ነው። ከ6 ሚሊየን ይሁዲዎችን እንዲገደሉ ያደረገው አዶልፍ ሂትለር ይጠቀምበት የነበረው የስዋስቲካ ምልክት ከ800 ዓመታት በፊት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ተንፀባርቀዋል። የግሪኮች መስቀል የሚባለው ባለ ድርብ የመስቀል ቅርፅ ከዛሬ 800 ዓመታት በፊት ላሊበላ ላይ ነበሩ። በአስረኛው መቶ ክፍለ ዘመን አውሮፓ ውስጥ ተዋጊዎች ነበሩ የሚባሉት በስም አጠራራቸው ቴምፕለርስ /መስቀላዊያን/ ተብለው የሚጠሩት ይይዙት ነበር የሚባለው መስቀል ክሩዋ ፓቴ ይባላል። ይህ የመስቀል ቅርፅ ላሊበላ ላይ አለ። እናስ ላሊበላ እነዚህን መልክቶች ከየት አመጣቸው? አወዛጋቢ ጥያቄ ነው።


የሚገርመው ነገር፣ አንዳንድ ፀሐፊያን እነዚህን የመስቀል ቅርጾች እያዩ የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰጡ ቆይተዋል። በመስቀሎቹ ቅርፅ ምክንያት እነዚህን የቅዱስ ላሊበላን ኪነ-ህንፃዎች የሰሯቸው ከውጭ ሀገር የመጡ ባለሙያተኞች ናቸው በማለት የፃፉ አሉ። እውን የሰራቸው ማን ነው?


የላሊበላን ኪነ-ህንፃዎች የሰሯቸው እነማን ናቸው? የሚለው ጥያቄ ከዛሬ 400 ዓመታት ጀምሮ አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቶ ነበር። አወዛጋቢ ያደረገው ፖርቹጋላዊው አገር አሳሽ ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ በ1520 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለአራት ዓመታት ቆይቶ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ ባሳተመው መፅሐፉ የገለፀው ነው።


አልቫሬዝ ሲገልፅ በኪነ-ሕንፃዎቹ አሠራር በእጅጉ ተደንቋል። እኔ ያየሁትን ብፅፍ የሚያምነኝ የለም ብሎ ተጨንቋል። እንዲህም ብሎ ፃፈ።


እኔ ያየሁትን ላላያችሁ ሰው እንዲህ ናቸው ብል የሚያምነኝ የለም። ነገር ግን ያየሁት ሁሉ ዕውነት መሆኑን በሃያሉ እግዝአብሔር ስም እምላለሁ።


እያለ ፖርቹጋላዊው ቄስ እና ፀሐፊ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ስለ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ትንግርታዊ አሠራር ፅፏል።


ከዚያም ሲገልፅ እነዚህን አብያተ-ክርስያናት ማን ሰራቸው ብዬ ስጠይቅ ፈረንጆች ናቸው ብለው ቄሶች ነገሩኝ ብሎ ፅፏል። ከዚያ በኋላ የመጡ አጥኚዎች በሙሉ በፈረንጆች የተሰሩ ናቸው እያሉ ፅፈዋል። የቅዱስ ላሊበላ ገድል ወይም ገድለ ላሊበላ ደግሞ የሚናገረው ሌላ ነው። ገድለ ላሊበላው ፈረንጆች ሰሩት አይልም። ገድለ ላሊበላው ጉዳዩን ወደ መንፈሳዊ ፀጋነት ይወስደዋል። እነዚህ ኪነ-ህንፃዎች የተሰሩት መላዕክት እያዘዙት በቅዱስ ላሊበላ አማካኝነት እንደሆነ ነው የሚገልፀው። “ስራው ረቂቅ ከመሆኑ የተነሳ ከመላዕክት ውጭ በሰው እጅ ብቻ እንዲህ አይነት ተአምራዊ ኪነ-ህንፃ ሊሰራ አይችልም” በሚል የዕምነት ሰዎች ይከራከራሉ። ክርክሩ አያልቅም። ምክንያቱም ኪነ-ህንፃዎቹ ምስጢር ናቸውና!


ግን የዛሬ 60 ዓመት ላይ የኢትዮጵያ የነፃነት አርበኛና ሞደርናይዘር የብልፅግና አመላካች የነበረችው እንግሊዛዊቷ ሲልቪያ ፓንክረስት በዚህ በላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ላይ የሚሰነዘሩት አስተያየቶች ቆረቆሯት። እርሷ ደግሞ ሰዓሊ ናት። ጋዜጠኛ ናት። ደራሲ ናት። እናም ላሊበላ ላይ መመራመር ጀመረች። እነዚህን ኪነ-ህንፃዎች ማን የሰራቸው ብላ ጠየቀች። ብዙ የውጭ ሀገር ፀሐፊያን ፈረንጆች እንደሰሯቸው እየተቀባበሉ ፅፈዋል። እናም ይህ አባባል ሲልቪያን ቆረቆራት።


ስለዚህም የላሊበላን አብያተ-ክርስቲያናት የሚመስሉ ኪነ-ህንፃዎች በሌሎች ሀገሮች መኖርና አለመኖራቸውን ለማወቅ ሲልቪያ ፓንክረስት ዓለምን ማሰስ ጀመረች። በግበፅ፣ በእስራኤል፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በህንድ፣ በቻይና ብሎም በልዩ ልዩ የጥንታዊ ስልጣኔዎች መገኛ በሚባሉት ስፍራዎች በሙሉ ዞረች። ኢትዮጵያንም ዞረች አየች። ውስጠ ሚስጢሯን አጠናች። ከዚያም Ethiopia A Cultural History የተሰኘ ግዙፍ መፅሐፍ አሳተመች። በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ስለ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ-ክርስያናት አሠራር ለመጀመሪያ ጊዜ የተደራጀ ጥናትና ምርምር የሰራች የኢትዮጵያ ፍፁም ወዳጇ የሆነች ሴት ሲልቪያ ከወደ እንግሊዝ ትጠቀሳለች።


የሲልቪያ ፓንክረስት ዓለምን የማሰስ ጉዞ ማጠናቀቂያው የሚከተለው ነው። አንደኛ የቅዱስ ላሊበላን ኪነ-ህንፃዎች የሚመስሉ አሠራሮች በየትኛውም ሀገር በዚያ ዘመን እንዳልተሰሩ አረጋገጠች። እንደ ሲልቪያ መከራከሪያ፣ ፈረንጆች ሰርተውት ቢሆን ኖሮ በፈረንጅ ሀገር ቅርፃቸውና አሻራቸው ይኖር ነበር ብላ ፃፈች። ግን የለም። እንደ ሲልቪያ ገለፃ፣ የቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ህንፃዎች አሠራር የተቀዳው ከዚያው ከኢትዮጵያ ውስጥ ነው።


የጥንታዊ አክሱማውያን ጥበቦች በላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ላይ ሙሉ በሙሉ ተንፀባርቀዋል። ከአለት ላይ ፈልፍሎ ኪነ-ህንፃዎች መስራት ማነፅ የኢትዮጵያዊያኖች የጥንታዊ ስልጣኔያቸው ነው። “ቅዱስ ላሊበላም እነዚያን አሠራሮች ፍፁም ውበትና ለዛ አላብሶ አስደማሚ አድርጐ ሠራቸው እንጂ የውጭ ሀገር ሰው ፈፅሞ አልነካቸውም” እያለች ሲልቪያ ፓንክረስት በጥናትና ምርምር መፅሀፏ ገልፃለች።


ታዲያ እነዚህ የኢትዮጵያ ብርቅ የጥበብ ውጤቶች የሆኑት አብያተ-ክርስትያናት በአሁኑ ወቅት ክፉኛ አደጋ ውስጥ ናቸው። የመሰንጠቅ እና የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። እናም ጉድ ከመሆናችን በፊት ሁሉም አካላት ላሊበላን ሊጠብቀው ይገባል። ኢትዮጵያ ስትጠራ ቀድሞ ብቅ የሚል የስልጣኔ መገለጫ ነውና።

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ በትላንትናው ዕለት አጽድቋል። አዋጁ ይዞት ከመጣው በአዎንታ ከሚጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ ለእናቶች ከወሊድ በፊትና በወሊድ ወቅት ሊሰጣቸው የሚገባውን የዕረፍት ጊዜ አንጻራዊ በሆነ መልኩ ማሻሻል መቻሉ ይጠቀሳል። በዚህ አዋጅ ድንጋጌ መሠረት ለሴት የመንግሥት ሠራተኞች የድህረ ወሊድ ፈቃድ 60 ቀናት የነበረውን ወደ 90 ቀናት ከፍ እንዲል ተደርጓል።

በተጨማሪም አዋጁ የጽንስ መቋረጥ ችግር ያጋጠማት ሴት በቂ ፈቃድ እንድታገኝ ማስቻሉ፣ የትዳር አጋር በተመሳሳይ ሁኔታ ፈቃድ የሚያገኝበት ሁኔታ ማካተቱ በአዎንታ የሚጠቀስ ነው።

የአስተዳደር በደሎችን በነጻ ፍርድቤት ለማየትና ለመወሰን እንዲቻል ራሱን የቻለ የአስተዳደር ፍርድቤት እንዲቋቋም በአዋጁ መደንገጉ ለሠራተኞች ትልቅ የምስራች ነው።

ሌላው በተሻረው አዋጅ አንድ የመንግስት ሠራተኞች ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ ከሥራው ከተለየ መ/ቤቱ ይህንን ካወቀበት ቀን ጀምሮ ለ6 ወራት የስራ መደቡን ክፍት አድርጎ መጠበቅ እንዳለበት ተደንግጓል። አንዳንድ ሠራተኞች በወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ በነጻ ሲለቀቁ ወደስራቸው ለመመለስ 6 ወር አልፎአችሃል በሚል የሚከለከሉበት ሁኔታ መኖሩ ከፍትሐዊነት አንጻር ተገቢ አለመሆኑን በመገንዘብ ከዚህ አንጻር አዋጁ ማሻሻያ አድርጓል። በወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ በነጻ ስለመለቀቃቸው ማስረጃ ከቀረበ መስሪያ ቤቱ ባለው ክፍት የስራ መደብ ቀደም ሲል ሲከፈለው የነበረውን ደመወዝ እያገኘ ሥራውን እንዲያከናውን በአዲሱ አዋጅ እንዲደነገግ መደረጉ ተገቢ ነው።

እነዚህና መሰል የሕግ ድንጋጌዎች በተለይ የመንግሥት ሠራተኞችን መብትና ጥቅም በማስከበር ረገድ በአዎንታ የሚታዩ ናቸውና እርምጃው ይበል የሚያሰኝ ነው።¾

ጽዮን ማርያም

Wednesday, 06 December 2017 13:00

በጥበቡ በለጠ

 

ጽዮን ማርያም በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ውስጥ የምትገኝ በምድራችን ላይም እጅግ ጥንታዊ ከሆኑ የክርስትና ማዕከል መካከል አንዷ ናት። ጽዮን ማርያም የብዙ ጉዳዮች መገለጫ ናት። በዚህች ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው አስርቱ ትእዛዛት የተፃፉበትና የተቀረፁበት ፅላት ወይም ፅላተ-ሙሴ የሚገኝበት ምድር ነች። በክርስትናው ዓለም ውስጥ ቅዱስ ስፍራ ተብለው ከሚጠሩት መካከል ግንባር ቀደሟ ነች።


ይህች ቤተ - ክርስትያን ሕዳር 21 ቀን ዓመታዊ ክብረ በዓሏ፣ ንግስናዋ ነው። ታዲያ በዚህ ክብረ በዓል ላይ ለመታደም ከዓለም ዙሪያ አያሌ ቱሪስቶች አክሱም ከተማ ታድመዋል። ከተማዋ በሃይማኖቱ ተከታዮች በቱሪስቶች ተጨናንቃለች።


በክርስትናው ዓለም ውስጥ ትኩረት በመሳብ አክሱም ፅዮንን የሚያክል ስፍራ የለም። ምክንያቱም የፈጣሪ ትዕዛዛት ያሉበት ቦታ ስለሆነ እና ከዚህ በላይ ደግሞ በምዕመናን ዘንድ የሚታንበት ማስረጃ ስለሌለ ጽዮን ማርም በክርስትናው ዓለም ውስጥ ጎላ ብላ ትጠቀሳለች።


ጽላተ-ሙሴ ዛሬ 3ሺ ዓመት ከእየሩሳሌም መንበሯ ተወስዶ ወደ “ኢትዮጵያ መምጣቱ ይነገራል” ያመጣው ደግሞ ቀዳማዊ ምኒልክ ነው” የንግስት ሣባ ልጅ።
ጽዮን ማርያም የጽላተ - ሙሴ መቀመጫ ከመሆኗም በላይ ኢትዮጵያዊው ንጉስ ኢዛና ወደ ክርስትና ሲቀየር በዘመናዊ መልክ ፅዮን ማርያምን ከዛሬ 1600 ዓመታት በፊት አነጻት። እናም የኢትዮጵያ አስተዳደርና የሀይማኖት ማዕከል ሆነች።


የኢትዮጵያ ነገስታት ወደ ስልጣን ሲመጡ መጀመሪያ አክሱም ጽዮን ሔደው የንግስና ቆብ የሚጭኑበት የአመራር ስፍራ ናት። ኢትዮጵያ እንድትመራ፣ ሕዝቦችዋ መሪ እንዲኖራቸው ቀብታ የምትልክ ቤተ-ክርስትያን ነበረች።


አክሱም ጽዮን እንደ ቅዱስ ያሬድ አይነት የዜማና የመዝሙር ሊቅ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ለዚህች ምድር ያፈራች ስፍራ ናት።
ከዚህ ሌላም ፈላስፋዎቹን እነ ዘርአያዕቆብን እና ወልደ ሕይወትን የፈጠረች ምድር ነች።


አክሱም ታላላቅ መሪዎች እነ ካሌብና ገብረመስቀልን የመሣሰሉ የስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በእምነትም በአገር አመራርም ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ገናና ነገስታት አፍርታለች። ዓፄ ካሌብ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ውስጥ ድንቅ ኪነ-ሕንጻዎችና በማነጽ፣ የስልጣኔ ተምሳሌት የሆኑ፣ የሀገርንም ዳር ድንበር ለማስከበር ዓፄ ካሌብ ወደር የማይገኝላቸው ገናና መሪ ነበሩ።


አክሱም ሌላም አስገራሚ መሪ ነበራት። ይህ ሰው ንጉስ ባዜን ይባላል። የንጉስ ባዜን ታሪክ እንደሚያወሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት ኢትዮጵያን ለስምንት ዓመታት መርቷታል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ደግሞ ወደ እየሩሳሌም ቤተልሔም ሔዶ ኢየሱስን ያየ የኢትዮጵያ ብቸኛው መሪ እንደሆነ ታሪክ ገድሉ ይተርካል። የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ አይቶ ወደ ኢትዮጵያ ሀገሩ መጥቶ ከዚያም ለስምንት ዓመታት ሀገሩን እንደመራ ይነገርለታል።


ይህ ንጉስ ከዚህች ዓለም በሞት ከተለየ በኋላም የተቀበረበት ቦታም በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪካዊ ሆኖ የቱሪስት መስዕብ ከሆነ ቆይቷል። መካነ መቃብሩ የሚገኘው ከአክሱም ወደ አድዋ በሚወስደው አውራ ጎዳና፣ ከአክሱም ከተማ መውጫ ላይ ወደ ግራ ከሚገኝ ኮረብታማ ግርጌ ነው። ለመካነ መቃብሩ ምልክት እንዲሆንም በደንብ የተጠረበና ቁመቱ 6 ሜትር የሆነ አንድ ባለግርማ ሀውልት ተተክሎበታል። ይህ መካነ መቃብር ተቆፍሮ የወጣው በ1957 ዓ.ም ነው። ደረጃዎቹም ከድንጋይ የተፈለፈሉ ደረጃዎች አሉት። ውስጡም አደራሽ አለ። ይህ አስገራሚ ንጉስ ባዜን፤ ገና ያልተነገሩለት እጅግ ብዙ ታሪኮች አሉት። ወደፊት እናወጋለታለን።


አክሱም ጽዮን የአለምን ስልጣኔና ግስጋሴ ችግርና ስኬትን ሁሉ እያየች እየታዘበች የኖረች የረጅም ዘመን መካነ ታሪክ፣ የሰው ዘር ሁሉ ሄዶ እንዲጎበኛት እንዲያያት የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /UNESCO/ የሚመከርባት አክሱም ተወስቶ የማያልቅ ታሪክ አላት።


የፅሁፍ ጥበብ የተንጸባረቀባት፣ ትምህርት ያበበባት፣ የሊቃውንተ መናሀሪያ ሆና ኖራለች።


በዮዲት ጉዲት መነሳት አክሱም እየተዳከመች ሄደች። ፈራረሰች። ወርቃማ ታሪኳም ከዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ተዳከመ።


በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም በተነሳ የእርስ በርስ ጦርነት አክሱም ጽዮን ፈራረሰች። ከዚያም አገር ሲረጋጋ በ1635 ዓ.ም አፄ ፋሲል ከጎንደር ወደ አክሱም ሄደው የጎንደር የኪነ-ጥበባት ቅርስ የሚታይበትን ቤተ-ክርስትያን አሰሩላት። ይህ የአፄ ፋሲል ኪነ-ህንፃ ዛሬም በግርማ ሞገሱ ድምቀት አክሱም ከተማ ላይ ተገማሽሮ ይታያል።


አሁን ደግሞ አጅግ ዘመናዊ ሆኖ የሚታየውን ግዙፉን የፅዮን ማርያምን ቤተ-ክርስትያን ያሰሩት አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው። ባለቤታቸው እቴጌ መነንም በ1845 ዓ.ም ባለ አንድ ፎቁን የፅላት ቤት አሰርተዋል።


አክሱም ፅዮን የኢትዮጵያ የእምነት፣ የታሪክ፣ የፍልስፍና የአስተዳደር፣ የብዙ ነገሮች መገለጫ ናት። የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲው የአለማችን የክርስትና ዕምነት ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሄነሪ ሊዊስ ጌት wonders of the African world የተሰኘውን ትልቁን ዶክመንተሪ ፊልማቸውን ሲሰሩ አክሱምን “የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የስልጣኔ ማዕከል” ሲሉ ገልጸዋል። ዘጠኝ ሰዓታትን የሚፈጀው ይህ ግዙፍ ዶክመንተሪ ፊልም የአክሱም ጽዮንን ሙሉ ታሪክ ሁሉ ዘርዝሮ የሚያሳይ ነው።


ግርሀም ሀንኩክ የተባለው ጋዜጠኛና ጸሐፊ The sign & the seal በተሰኘው መጽሐፉ “አክሱም ጽዮን ውስጥ ፅላተ ሙሴን አገኘሁ” ብሎ በመፃፉ የአለም ታሪክ ተቀይሯል።


ምክንያቱም ፅላተ-ሙሴ በምድር ላይ ሁሉ ተፈልጎ ጠፍቷል። ኢትዮጵያ ግን አለኝ እኔ ዘንድ ነው ብላ የምትናገር ሀገር ብቻ ሳትሆን ብዙ ማስረጃዎችንም የምታቀርብ ምስጢራዊት ሀገር መሆኗን አያሌ ጸሐፊያን ገልፀዋል።


ህዳር 21 ቀን ይህች የኢትዮጵያ እና የዓለም የክርስትናው ተከታይ ሕዝብ ሁሉ የእምነት መገለጫ የሆነውን ጽላተ-ሙሴን የያዘችው አክሱም ጽዮን በየዓመቱ ትነግሳለች። ታሪኳን ስንመረምር ኢትዮጵያ ምን ያህል የምድሪቱ አስገራሚ ሀገርና መኩሪያ እንደሆነች እንገነዘባለን።¾

 

·        ዶ/ር አክሎግ ቢራራ እና ፕ/ር አለማየሁ ገ/ማርያም

በኦንላይን ተሳታፊ ይሆናሉ

በይርጋ አበበ

በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር የውይይት መድረክ ለተከታታይ አራት ሳምንታት ሊያካሂድ መሆኑን ሰማያዊ ፓርቲ አስታወቀ።

የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ጌታሁን ባልቻ በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገሩት የፊታችን እሁድ የሚካሄደው የመጀመሪያው የውይይት ርዕስ “ምሁራንና የአገር ሸማግሌዎች በወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው ሚና” የሚል ነው።

“የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም፣ የህግ ባለሙያው ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም፣ የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና የአፍሪካ ሰላምና እርቅ ኢንስቲትዩት ሊቀመንበር ዶ/ር ሸዋፈራው ኩራቱ ውይይቱን ይመሩታል ሲሉ አቶ ጌታሁን ተናግረዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት ምሁራን በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙት ዶ/ር አክሎግ ቢራራ እና ፕ/ር አለማየሁ ገብረማርያም በኦንላይን የውይይቱ ተሳታፊ እንደሚሆኑ የገለፁት አቶ ጌታሁን፤ ውይይቱ በቀጥታ በኦንላይን የሚተላለፍ መሆኑንም ተናግረዋል።

የምክክር ውይይቱ ለአራት ተከታታይ ሳምንታት የሚቀጥል ሲሆን የፊታችን እሁድ የሚጀመረው የውይይት መድረክ ከጠዋቱ 2፡30 እስከ 7፡00 በአምባሳደር ሲኒማ አዳራሽ ይካሄል ሲሉ አቶ ጌታሁን ገልጸዋል።

 

በይርጋ አበበ

ከጉራጌ ብሄር ህዝቦች አንዱ የሆነውን “የክስታኔን ማህበረሰብ” ቋንቋ የሚገልጸው እና በክስታንኛ አማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀው መዝገበ ቃላት የፊታችን እሁድ በብሄራዊ ቴአትር ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወልደማሪም ይመረቃል።

መዝገበ ቃላቱን ያዘጋጁት የክስታኔ ጉራጌ ህዝብ የልማት ማህበር እና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲሆኑ መዝገበ ቃላቱን አዘጋጅቶ ለማጠናቀቅ ስምንት ዓመት እና ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጥቶበታል።

ከመፅሐፉ አዘጋጆች አንዱ የሆኑት አቶ ጥላሁን አትሬሶ በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ መዝገበ ቃላቱ እንዲዘጋጅ የተፈለገበት ዓላማ የክስታኔ ቋንቋ እየጠፋ ስለመጣ ለቋንቋው ህልውና ማቆያ ሲባል ነው።

መዝገበ ቃላቱን ለማዘጋጀት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አቶ ታምራት ጉርሙ በመሪነት የተሳተፉበት መሆኑን የገለፁት አቶ ጥላሁን፤ እሳቸው እና አቶ ታምርአየሁ ሲማ ደግሞ ከክስታኔ ህዝብ ልማት ማህበር ተወክለው ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

“መዝገበ ቃላት ማዘጋጀት ከባድ ሥራ እና ከፍተኛ ወጭ ይጠይቃል” ያሉት አቶ ጥላሁን፤ “ለዝግጅቱ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ገንዘብ እና ልዩ ሙያዊ እገዛ የሰጠን የክስታኔ ብሄረሰብ ህዝብ ነው። ያለእነሱ ድጋፍ ከ8000 ቃላት በላይ ያሉትን መዝገበ ቃላት አዘጋጅተን ማቅረብ አንችልም ነበር” ብለዋል።

በቋንቋው የተጻፈ ታሪክ የሌለው ህዝብ ህልውናው አደጋ ላይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጥላሁን፤ መዝገበ ቃላቱ የተዘጋጀው “በጠባብ ብሄርተኝነት ስሜት ሳይሆን ማንነትን የማስቀጠል ስራ ነው። የክስታኔ ህዝብ የዘመናት እምነቱ ‘ከኢትዮጵያ የጠበበ አገር የለምንም’ የሚል ነው” በማለት ተናግረዋል። መፅሀፉ በ772 ገፆች የተዘጋጀ ሲሆን 300 ብር የመሸጫ ዋጋው ነው።

ዶ/ር ሒሩት ወልደማርያምን ጨምሮ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ይገኛሉ።   

ኢዴፓ በውዝግብ ውስጥ

Wednesday, 29 November 2017 12:54

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ መገለጫ ከሆኑት አብይ ክስተቶች መካከል አንዱ የፓርቲዎች ውስጠ ዴሞክራሲ አናሳ መሆን ነው። ሁሉም ፓርቲዎች በሚያስብል መልኩ ውስጣቸው መግባባትና መደማመጥ ያልሰፈነበት በመሆኑ የምርጫ ሰሞን ድምቅ ብለው ታይተው እንደ አደይ አበባ ቶሎ ይጠፋሉ። በዚህ የተነሳም አማራጭ ሃሳብ የሚፈልገው የአገሪቱ ህዝብ በእነሱ ድርጊት ተስፋ የቆረጠ ይመስላል።

ባሳለፍነው ሶስት ሳምንት የቀድሞ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ አመራሮች ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ተቀላቅለው ሰላማዊ ትግሉን እንደሚያስቀጥሉ መዘገባችን ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በአመራሮቹ መካከል መከፋፈል እንደተፈጠረ የሚያመለክት ምልክት እየታየ ነው። ፓርቲው ለዝግጅት ክፍላችን በላከው ደብዳቤ የአመራር ለውጥ ማካሄዱን አመልክቷል። ለአለፉት አራት ዓመታት የፓርቲው ፕሬዝዳንት ሆነው የቆዩትን ዶ/ር ጫኔ ከበደን በአቶ አዳነ ታደሰ መተካቱን የፓርቲው መግለጫ አመልክቷል። እዚህ ውሳኔ ለመድረስ ያስገደደው ገፊ እና ሳቢ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? የፓርቲው የውስጥ ደንብስ ይህን ይፈቅዳል ወይ? ጠቅላላ ጉባኤ እንዳንጠራ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከለከለን ሲል የነበረው ኢዴፓ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ለምን ጠቅላላ ጉባኤውን አልጠራም? የሚሉና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረን ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

የደብዳቤው ይዘትና አንደምታ

“ኢዴፓ በውይይት የሚያምን ፓርቲ ነው። ለዚህም ነው መንግሥት ለድርድር ሲጠራን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በድርድሩ ተሳታፊ የሆነው” ሲል ደብዳቤው ይጀምራል። ይህ ለመገናኛ ብዙሃን “እንዲያውቁትና እንዲያሳውቁት” ተብሎ የተላከው ደብዳቤ ፓርቲው ከድርድሩ መውጣቱን በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት የተወሰነ መሆኑን ይገልጻል። አያይዞም ከድርድሩ ለመውጣት ያቀረበው ምክንያት “በድርድሩ ፓርቲው የወከላቸውን ሰው ለመቀየር ብንፈልግ ኢህአዴግ ሊፈቅድልን አልቻለም” ሲል ያስታውቃል።

ኢዴፓ በፓርቲዎች ድርድር ሊቀመንበሩ ዶ/ር ጫኔ ከበደ እና በፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ወንድወሰን ተሾመ ተወክሏል። ከትናንት በስቲያ ለዝግጅት ክፍላችን ኢዴፓ የላከው ደብዳቤ የሚለውም በድርድሩ አንሳተፍም ሳይሆን የምንሳተፍ ከሆነ ከኢዴፓ ተወክለው በድርድሩ የሚሳተፉ የፓርቲው አባላት በሌላ ይቀየሩ የሚል ነው። ይህን ደግሞ ለድርድሩ ጋባዥ ኢህአዴግም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር መድረክ ደጋግሞ በደብዳቤ ማሳወቁን ገልጿል።

 

ኢዴፓ ከድርድሩ ለምን ወጣ?

ፓርቲው ለዝግጅት ክፍላችን በፃፈው ደብዳቤ ከድርድሩ ለመውጣትና በድርድሩ ለመቆየት ያቀረበው ቅድመ ሁኔታ አለ። ኢዴፓ ድርድሩን በተመለከተ የወሰደውን አቋም ሲያስታውቅ “ባለፈው ዓመት ጥር ወር በኢህአዴግ ጋባዥነት በተጀመረው የድርድር መድረክ ላይ ፓርቲያችን ተሳትፎ ማድረግ ጀምሮ ነበር። ሆኖም ፓርቲው በድርድሩ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲኖረው በማሰብ በግንቦት 23 ቀን 2009 ዓ.ም፣ በነሐሴ 11 ቀን 2009 ዓ.ም እና በጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም በተፃፉ ደብዳቤዎች በተደጋጋሚ በድርድሩ ተሳታፊ የሆኑ ተወካዮችን መቀየሩን ቢያሳውቅም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። እኛ በማናውቀው ምክንያት የድርድር መድረኩ ፓርቲው የወከላቸውን ተወካዮች ከመቀበል ይልቅ የፓርቲው ውክልና የሌላቸውን ሰዎች የድርድሩ አካል አድርጎ መቀጠሉን መርጧል። በዚህ ምክንያት በድርድሩ ላይ እየተወሰኑ ያሉ ውሳኔዎች ፓርቲው የማያውቃቸው ሲሆን ከዚህም በኋላ በ13/02/2010 ዓ.ም ፓርቲው በደብዳቤ ያሳወቃቸውን ተወካዮች ተቀብላችሁ ድርድሩ ላይ ተሳትፎ እንድናደርግ ካላደረጋችሁ ኢዴፓ ከዛሬ ህዳር 18 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የድርድሩ አካል እንዳልሆነ እንገልፃለን” ሲል በአቶ አዳነ ታደሰ ፊርማ በወጣ ደብዳቤ ገልጿል።

ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እያካሄድኩ ነው ሲል በሚጠራው ድርድር ላይ ኢዴፓ የተወከለው በሊቀመንበሩ ዶ/ር ጫኔ ከበደ እና በህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ወንድወሰን ተሻለ ሆኖ እያለ ከትናንት በስትያ ለመገናኛ ብዙሃን የተላከው ደብዳቤ ግን የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ መሆናቸውን ያበስራል።

ፓርቲው በድርድሩ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ሁለቱ ተደራዳሪዎችና አንዱ አደራዳሪ (የፓርቲው ጥናትና ምርምር ኃላፊው አቶ ዋሲሁን አሰፋ) አይወክሉንም ሲል ለድርድሩ መሪዎች ደብዳቤ የፃፈው ለምንድን ነው? እነማንንስ ነው የወከላችሁት? ስንል ለአቶ አዳነ ታደሰ ጥያቄ አቅርበንላቸው ነበር። አቶ አዳነ ሲመልሱም “በሶስቱ ሰዎች ምትክ የተወከሉት አቶ ኤርሚያስ ጋሻ፣ ወይዘሪት ጽጌ ጥበበ እና እኔ (አቶ አዳነ ታደሰ) ነን። ይህን ያደረግንበት ምክንያት በፓርቲያችን ብሔራዊ ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ነው” ብለዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ አዳነ ታደሰን ወደ ፕሬዝዳንትነት የመጡበት መንገድ አግባብነት አለው ወይ? ምርጫ ቦርድስ የሰጣችሁ ምላሽ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ አቶ አዳነ ሲመልሱ “የፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 4 ቁጥር 17 ብሔራዊ ምክር ቤት በፈለገው ጊዜ አመራሮቹ ላይ እርምጃ ሊወስድ ይችላል ይላል። ለምርጫ ቦርድም በደብዳቤ አሳውቀናቸው እስካሁን ደብዳቤውን ባይቀበሉም ከዋና ፀሐፊው ጋር ባደረግነው የቃል ውይይት ጥያቄያችንን እንደሚቀበሉን ቃል ገብተውልናል” ብለዋል።

በሌላ በኩል የአቶ አዳነ ታደሰን ምላሽ ተቃውመው አስተያየታቸውን ለሰንደቅ የሰጡና ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የፓርቲው ሥራ አሥፈፃሚዎች “ድርጊቱ ህግን ያልተከተለ እና ሕገ ወጥ ስለሆነ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። የተደረገውን ሕገ-ወጥ ስራም ለምርጫ ቦርድ አሳውቀናል። በህግም እየተከታተልነው ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

 

 

የፓርቲው ሌላ ገፅታ

25 አባላት ያሉት የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በተፈቀደለት ሥልጣን መሠረት ሶስት ሥራ አስፈፃሚዎችን ከኃላፊነት ዝቅ አድርጓል ሲሉ አቶ አዳነ ይናገራሉ። ለዚህ ንግግራቸው ያቀረቡት አስረጅ ሃሳብ ደግሞ ፓርቲውን ላለፉት አራት ዓመታት በሊቀመንበርነት የመሩትን ዶ/ር ጫኔ ከበደን ከኃላፊነታቸው በማንሳት አቶ አዳነን በምትካቸው ሾሟል። የጥናትና ምርምር ኃላፊ የነበሩትን አቶ ዋሲሁን አሰፋን ከኃላፊነትና ከሥራ አስፈፃሚነት በማንሳት የጥናትና ምርመር ቦታውን ደግሞ ለዶ/ር ጫኔ ከበደ ሰጥቷል። አቶ ዋሲሁንን ወደ ብሔራዊ ምክር ቤት ዝቅ ብለው እንዲሰሩ ተደርጓል ብለዋል።

ይህን የአቶ አዳነ ምላሽ የማይቀበሉት የፓርቲው አመራሮች ግን የተካሄደውን አሰራር እንደሚቃወሙት ገልጸው ጉዳዩንም በህግ እየተከታተሉት እንደሆነ ተናግረዋል። አሁን በኢዴፓ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን አሰራርም ፓርቲውን ችግር ላይ የሚጥል መከፋፈል እንደተፈጠረ የሚናገሩት የሰንደቅ ምንጮች፤ ጠቅላላ ጉባኤ ሳይካሄድ የቆየውም ለዚህ ሲባል ነው ብለዋል። “ጠቅላላ ጉባኤ ቢካሄድ አሁን ያለው የአንጃ ቡድን የሚጠብቀውን ስለሚያውቅ የተለያዩ ሰበቦችን እየፈጠረ ጠቅላላ ጉባኤው እንዳይካሄድ ሲያደርግ ቆይቷል” ሲሉ ለሰንደቅ አስተያየታቸውን የሰጡ የኢዴፓ አመራሮች ተናግረዋል።

“ፓርቲው ውስጥ መከፋፈል ነግሷል። ከዚህ መከፋፈል ጀርባ ደግሞ የቀድሞው ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሉው አሉ” ሲሉ የሰንደቅ ምንጮች ይገልጻሉ። አቶ አዳነ ታደሰ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። ፓርቲው በተለመደው የተረጋጋ መንገድ እየተጓዘ መሆኑን ገልፀው “ይህን ወሬ የሚያወሩት በብሄራዊ ምክር ቤት ውሳኔ የተከፉ አመራሮች ናቸው” ሲሉ መልሰዋል።

አቶ አዳነ ለመገናኛ ብዙሃን በፊርማቸው የላኩት ደብዳቤ ላይ የፓርቲው ፕሬዝዳንት መሆናቸውን በተዘዋዋሪ የሚገልፅ ቢሆንም ሕትመት እስከገባንበት ትላንት ከሰዓት በኃላ ድረስ ፕሬዚዳንትነታቸው በምርጫ ቦርድ ዕውቅና አላገኘም።  በዚህ ጉዳይ ምርጫ ቦርድ ያለውን አስተያየት እንዲሰጠን ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም ከፓርቲው ባገኘነው መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው ግን ምርጫ ቦርድ አዲሱን የኢዴፓ ካቢኔ ሹም ሽር ላይ ገና ውሳኔ አላሳረፈም።። ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር የተራዘመው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ የፊታችን የካቲት 27 ቀን እንደሚካሄድ አቶ አዳነ ተናግረዋል። አቶ አዳነ አያይዘውም ለረዥም ጊዜ ጉባኤ ሳይካሄድ የቆየው እንደሚባለው በውስጣችን ችግር ስላለ ሳይሆን በአገሪቱ ተጥሎ የቆየው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳንሰበሰብ እና መግለጫ እንዳንሰጥ ስለከለከለን ነው። አሁን ግን የጠቅላላ ጉባኤ አመቻች ኮሚቴ ተዋቅሮ ለጉባኤው ዝግጅት እያደረግን ነው” ብለዋል።

 

 

ማስተካከያ

 

13ኛ ዓመት ቁጥር 637 በወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ ከሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት ጋር ባደረግነው ቃለ ምልልስ “ከአየር ኃይል አዛዥነታቸውና ከህወሓት/ኢህአዴግ አባልነታቸው ራሳቸውን ካገለሉ…” የሚለው፤ “በጡረታ እንዲያገሉ ከተደረጉ በኋላ” በሚል ይታረም።

“ኢህአዴግ ስልጣን መልቀቅ የነበረበት በ1987 ዓ.ም ነበር” የሚለው “ከ1987 ዓ.ም በኋላ ወጣቱና የተማረው ኃይል ስልጣኑን እንዲረከብ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበረበት” በሚል ይስተካከል።

ለተፈጠረው ስህተት አንባቢያንን እና ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖትን ይቅርታ እንጠይቃለን።¾

   

በሀገራችን በተለይ በአዲስ አበባ ያለውን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍ እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መካከል አንዱ አውቶቡሶችን መግዛት ነው። መንግስትም በተደጋጋሚ እያደረገ ያለው ነገር ይሄንኑ ነው። በቅርቡ በርካታ ቁጥር ያላቸውን አውቶቡሶች ገዝቶ ወደ ዘርፉ እንደሚያስገባ መንግስት ባለፈው አስታውቋል። ኃላፊነቱን በመወጣቱ መንግስት ሊመሰገን ይገባዋል። ነገር ግን ይህ የአውቶቡስ ግዢ ብዙ ጊዜ ያስከተላቸው ጣጣዎች አሉ። ከዚህ በፊት እንዳየነው የሚገዙት አውቶቡሶች ጥራታቸው ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ ያገለግላሉ ከተባለው ጊዜ በግማሽ ባነሰ ጊዜ ውስጥ እየተበላሹ እና ከአገልግሎት ውጪ እየሆኑ ነው። በዚያ ላይ አንድ ጊዜ መለዋወጫ የለም ሌላ ጊዜ ደግሞ ኃላፊነቱ የኔ አይደለም በሚል ውዝግብ ብልሽታቸው ተጠግኖ ወደ አገልግሎት መግባት እንኳን ሳይችሉ የተቀመጡ በርካታ አውቶቡሶች አሉ። በነገራችን ላይ ከዚህ ቀደም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተበላሽተው የቆሙና ለመጠገን አንዱ ወደ ሌላው እያላከከ ተገትረው የቀሩት የቢሾፍቱ አውቶብሶች ጉዳይ ከምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የምናውቀው ነገር የለም። አውቶብሶቹ ተጠግነው ወደ ስራ ገብተው ይሁን ወይ ደግሞ እዚያው ቆመው ዝናብና ፀሀይ እየተፈራረቀባቸው ይሁን የሚያውቁት እነርሱ ብቻ ናቸው። የእነዚህኞቹ አውቶብሶች ጉዳይ መፍትሄ ሳያገኝ አሁን ደግሞ ሌሎች አውቶብሶች ሊገዙ መሆኑ ዜና ተነግሮናል። ያሉትን ጠግኖ ወደ አገልግሎት ማስገባቱ ነው ወይስ አዲስ መግዛቱ ነው አዋጪው? የሚለውን ጥያቄ ራሱ መንግስት ይመልሳል። ነገር ግን እነርሱ አድበስብሰው ቢያልፉትም እኛ እንደማንረሳው ሊያውቁት ይገባል። 

 

                           ቃል ኪዳን ተካልኝ - ከአዋሬ

ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሃት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን ያካሄደውን ግምገማ ተከትሎ በከፍተኛ አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዱ ተሰምቷል።

 

ህወሀት በወሰደው በዚሁ እርምጃው የፓርቲውን ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ኘሬዝደንት የሆኑትን አቶ አባይ ወልዱ ከሥራ አስፈፃሚነት አባልነት ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዝቅ ብለው እንዲሰሩ ወስኗል።


አቶ በየነ ምክሩ የኤፈርት ምክትል ሥራ አስፈጳሚ፣ ከፓርቲው ሥራ አስፈፃሚነት ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዝቅ ያደረገ ሲሆን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ባለቤትና የኤፈርት ዋና ሥራ አስፈጳሚ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲታገዱ ወስኗል።


በተጨማሪ ደግሞ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት አቶ አለም ገብረዋህድ እና አምባሳደር ዶ/ር አዲሳሌም ባሌማ በማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ ተደርጓል።


ይህ እርምጃ በጥልቀት የመታደስ አካል ነው ተብሏል። ህወሀት/ኢህአዴግ እንዲህ ዓይነት ቁርጠኛ እርምጃ ሲወስድ ከኦህዴድ/ኢህአዴግ ቀጥሎ ስሙ የሚጠቀስ ሆኗል። ኦህዴድ አቶ ሙክታር ከድርን፣ ወ/ሮ አስቴር ማሞን፣ አቶ ዳባ ደበሌን ከከፍተኛ ሃላፊነት በማንሳት ወጣቶቹን አመራሮች ወደፊት ማምጣቱ አሁን ፓርቲው እያገኘ ላለው ሰፊ ሕዝባዊ ተቀባይነት እንደእርሾ የሚወሰድ ቁርጠኝነት ነው።


ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ እና በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች ሰፊ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከታየ በኋላ ኢህአዴግ ችግሩ በራሱ ውስጥ መኖሩን በማመን የጥልቅ ተሀድሶ ለማድረግ ከአንድ ዓመት በፊት የወሰነ ሲሆን በዚህ ግዜ ውስጥ ተሀድሶው ከፍተኛ አመራሩን እምብዛም ያልነካ መሆኑ በሰፊው ሲያስተቸው ቆይቷል። ይነስም ይብዛ የኦህዴድ እና የህወሀት እርምጃ ለዚህም ተግባራዊ ምላሽ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።


የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄም በተመሳሳይ መንገድ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ የማጥራት ሥራውን እንዲያካሂድም ይጠበቃል። ሕዝባዊ ኃላፊነት ተቀብለው ግን ሕዝባዊ ተግባር ማከናወን ያልቻሉ፣ ሥልጣንን የግል ጥቅምና ክብር ማስጠበቂያ አድርገው የሚያዩ በየደረጃው ያሉ ሹመኞች ተሰናብተው በአገልጋይ ሹሞች ሊተኩ ይገባል።


ነባሩን አመራር በአዲስ ሀይል መተካቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕዝብ ቅሬታ የሚያቀርብባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች መልስ ለመስጠት ሕገመንግሥት እስከማሻሻል ድረስም ቢሆን እርምጃ እንደሚወሰድ የተገባው ቃል ሊከበርና ሊተገበር ይገባል።

Page 2 of 186

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us