You are here:መነሻ ገፅ»arts»news admin - Sendek NewsPaper
news admin

news admin

በአዳማ ለአስር ቀናት የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ “በኦሮሚያ ክልል ፖለቲካ ውስጥ ያገባኛል” ከሚሉ በሀገር እና በውጭ ሀገር ከሚገኙ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በጋራ ለመስራት ውሳኔ አሳልፏል።

በግልጽ ቋንቋ ለማስቀመጥ ከኦሮሞ ሕዝብ ብዛት እና ፍላጎት አንፃር ሲመዘን በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ጥረት ብቻ ምላሽ መስጠት ከበድ ይላል፤ ፈጽሞ አይቻልም ብሎም መደምደም አደጋች ነው። ቁም ነገሩ ያለው በአሳታፊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሕዝብ ሥልጣን በሚያዝበት መንገድ ኃላፊነት ለመቀበል አንድ ኦሮሚያን የሚወክል ፓርቲ ከበቃ፤ ከሕዝብ ድጋፍ ጋር የሚጠበቅበትን ምላሽ ለመስጠት አይቸገርም። ምክንያቱም በምርጫ አሸናፊውም፣ ተሸናፊም፤ ከምርጫ ውጤት በኋላ በኦሮሚያ ጉዳይ ላይ በአንድነት ለመቆም ስለማይቸገሩ ነው። ይህን ለማምጣት፣ በኦሮሚያ ፖለቲካ ውስጥ የሚገፋ ባለድርሻ አካል እንዳይኖር ጠንክሮ መስራት ይጠበቃል።


ሁለተኛው፣ የማዕከላዊ ኮሚቴው አጀንዳ የነበረው፣ “የሀገሪቷን፣ የአፍሪካን እና የዓለምን የፖለቲካ ሁኔታ በመገምገም የህዝባችንን ጥቅም እና ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ” የመከሩበት ጉዳይ ነው። ከዚህ አጀንዳ መረዳት የሚቻለው በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሕዴድ ሥራ አስፈፃሚ፣ የኦሮሚያን ክልል ከ“Geography center” ወደ “Political center” ለማሸጋገር የወጠኑትን እቅድ ነው። በርግጥ ክልሉ ካለው የሕዝብ ብዛት እና የቆዳ ስፋት አንፃር ኦሮሚያ የፖለቲካ ማዕከል መሆን ከቻለች፣ የዴሞክራሲ ምህዳር ከመስፋቱም በላይ በሀገሪቷ ውስጥም መረጋጋትን ለማምጣት ምትክ አልባ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።


ሶስተኛው፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው የቀድሞውን የኢፌዴሪ ፕሬዝደነት ነጋሶ ጊዳዳን ለማገዝ የወሰነው ውሳኔ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ በአቋም መለየትና የተለያ አስተሳሰብ መያዝ የሚያስከፍለው ዋጋ በጣም ከባድ ነው። በ1993 በኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠረው የአስተሳሰብ እና የኃይል አሰላለፍ ልዩነት “አሸንፎ” የወጣው ቡድን “ተሸነፈ” በተባለው ቡድን ላይ የተከተለው መንገድ እንደደርግ ተቀናቃኝ ኃይሎች ናቸው ብሎ፤ እርምጃ አለመውሰዱ በበጎነት ቢታይለትም፣ ከማሕበራዊ ተሳትፎቸውና ከሚገባቸው የአገልግሎት ጥቅም ውጪ እንዲሆኑ የተደረገበት መንገድ ግን አስተማሪነት የሚጎድለው ነው።


የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ሊጠብቅላቸው የፈለገው መብቶች ተገቢ ናቸው። ሆኖም ማዕከላዊ ኮሚቴው ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የተከለከሉት ጥቅማጥቅሞች በሕገወጥ መንገድ ነው ብሎ ከወሰደ፤ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አቅርቦ በፌደራል ደረጃ ጥቅማቸው እንዲከበር መሥራት አለበት፤ ይገባልም። ምክንያቱም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከሚጠበቅላቸው ጥቅም በላይ፣ የህግ የበላይነትን ማስፈጸም ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው። አስተማሪነቱም ተደማሪ ነው።


አራተኛው፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በቅርቡ የወሰነው ውሳኔ በፍጥነት ለመተግበር መዘጋጀቱን ገልጿል። ማዕከላዊ ኮሚቴው የፓርቲውን ውሳኔ ለመተግበር ያለውን ቁርጠኝነት ይፋ ማድረጉ፣ በቅርቡ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቀነመናብርት በጋራ የሰጡትን መግለጫ ያጠናክራል። እንዲሁም ሊቀመናብርት በሰጡት መግለጫ አቀራረባቸው የተለያየ በመሆኑ በተለያዩ ወገኖች ቀርበው የነበሩ መላምቶችን ወደ አንድ መስመር ሊከታቸው ይችላል። መረጋጋትም የማምጣት እድሉ ከፍተኛ ነው።


አምስተኛው፤ በኢሕአዴግ ምክር ቤት ውስጥ ከሚሳተፉት የኦሕዴድ 45 አባላት መካከል አስሩን አሰናብቷል። አባላቱን ማሰናበቱ የድርጅቱ መብት ነው። ሆኖም ከኃላፊነት ያነሳቸው አባላት በኦሕዴድ ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው በመሆኑ ለምን እንደተነሱ ይፋ ቢደረግ ውሳኔ ሙሉ ይሆን ነበር። በተለይ የተነሱት አባላት በሌሎች እህት ድርጅቶች ከተነሱት አባላት ጋር ተመሳሳይነት ያለው እርምጃ በመሆኑ ነው።


በመጨረሻ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያወጣውን መግለጫ የሚመጥን የፖለቲካ ቁመና ለመያዝ ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠብቀው እሙን ነው። ከላይ ያሰፈርናቸውን ያልተሄደባቸው መንገዶች ለመሄድ መሞከሩም በውሳኔ ደረጃ፣ ያስመሰግነዋል።

የጭድ እሳት

Wednesday, 07 February 2018 13:17

 

አለማየሁ አሰጋ

 

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ሰሞኑን “ኢራፓ ኢሕአዴግን የመገነዝ ኃላፊነት የለበትም!!” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችና በኢህአዴግ መካከል በመካሄድ ላይ ከሚገኘው ድርድር በራሱ ውሳኔ መውጣቱን አሳውቆናል።


ኢራፓ፣ በአገሪቱ የመንግስት ታሪክ የአመለካከት፣ የመደራጀትና ለፖለቲካ ስልጣን የመፎካከር ፖለቲካዊ መብቶችና ነጻነቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ያረጋገጠው የኢፌዴሪ ህገመንግስት ውጤት ነው። ይህ ህገመንግስት በስራ ላይ በዋለባቸው ያለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት በፌደራልና በክልላዊ መንግስታት ደረጃ የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከትን የሚያራምዱ በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተዋል። በነጻነትም አመለካከታቸውን በማራመድ ለፖለቲካ ስልጣን ሲፎካከሩ ቆይተዋል። ፓርቲዎቹ እንደየባህሪያቸው አመቺ ባሉት መንገድ የፖለቲካ ተሳትፎ እያካሄዱ ይገኛሉ። ኢራፓም ከእነዚህ አንዱ ነው።


በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቱ እስካሁን በተካሄዱ አምስት ምርጫዎች ላይ ተሳተፈዋል። በተለይም እስከ ሶሰተኛው ዙር ምርጫ ደረስ በርካታ ፓርቲዎች በፌደራል እና በክልሎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ውስጥ ውክልና ለማግኘት በቅተው ነበር።


ይሁን እንጂ ከአራተኛው ዙር ምርጫ በኋላ ምርጫዎቹ አሳታፊ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ የነበሩ ቢሆንም፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በ50+1 አብላጫ የምርጫ ስርዓት በተወዳደሩባቸው የምርጫ ክልሎች አሸናፊ ሆነው በምክር ቤቶች ውስጥ ውክልና ማግኘት አልቻሉም። በአራተኛው ዙር ምርጫ ኢህአዴግ በተወዳደረባቸው አራት ክልሎች ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደሮች ከሁለት መቀመጫዎች በስተቀር ሁሉንም አሸንፎ ነበር። በአምስተኛው ዙር ምርጫ ደግሞ በተወዳደረባቸው ክልሎች ሙሉ በሙሉ መቀመጫዎቹን ማሸነፍ ችሏል። የአፋር፣ የኢትዮጵያ ሱማሌ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የጋምቤላ፣ ከፊል ሐረሪ ክልሎች ደግሞ በየክልሎቹ አሸናፊ በሆኑ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወክለዋል።


በየምርጫዎቹ ላይ ተወዳድረው የምክር ቤት መቀመጫዎችን ማሸነፍ ያልቻሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከ50 በመቶ በታች የሆነ የጥቂት መራጮች ድምጽ አግኝተዋል፤ ይህ ሁኔታ ከፍተኛው የስልጣን አካል የሆኑ የፌደራልና የክልል መንግስታት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ውስጥ በሚፈለገው ደረጃ የህዝብ ድምጽ ሊሰማ የማይችልበትን ሁኔታ አስከትሏል።


የኢፌዴሪ መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም ይህ የህዝብን ተሳትፎ የሚገድብ ሁኔታ ተገቢ አለመሆኑን አምነው የአገሪቱን የዴሞክራሲ ምህዳር ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ በማስፋት የህዝብ ድምጾች ያለገደብ ሊሰሙ የሚችሉበት ስርዓት መዘርጋት አለበት የሚል አቋም ያዘ። ይህን ማድረግ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ጥሪ አቀረበ።


ይህን ተከትሎ በ2009 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ከተጀመረው ከዚህ ድርድር ውስጥ ጥቂት ፓርቲዎች ራሳቸውን ቢያገሉም አስራ ሰባት ያህል ፓርቲዎች ግን የሚደራደሩበትን አጀንዳ ወስነው ወደድርድር ገብተዋል። ድርድሩ አሁንም በመካሄድ ላይ ይገኛል። የድርድሩ ዓላማ የምርጫ ህጎችን በማሻሻል የፖለቲካ ምህዳሩን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ በማስፋት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁሉም የህዝብ ድምጾች ሊሰሙ የሚችሉበትን የምርጫ ስርዓት መፍጠር ነው።


በዚህ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አስራ ሁለት የድርድር አጀንዳዎች ላይ ተስማሙ። ለድርድር ከተያዙት ጉዳዮች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ፣ የምርጫ ህግ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቀዳሚዎቹ ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያግዛሉ የተባሉት የፀረ-ሽብር ህግ፣ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት ህግ፣ የበጎ አድራጎትና ማህበራት ማደራጃ አዋጅ፣ የታክስ አዋጅ እና የመሬት ሊዝ አዋጅ በዋና የድርድር አጀንዳነት ተይዘዋል። የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ ሁኔታም በንኡስ የድርድር አጀንዳነት ተይዟል።


ኢራፓ እስካሁን በተካሄዱት ከምርጫ ጋር ተያያዥነት በሆኑ የድርደሩ ዋነኛ ጉዳይ የነበሩት አዋጆች ላይ በሰጥቶ መቀበል መርህ ተደራድሮ በርካታ የአዋጆች አንቀጾች እንዲሻሻሉ፣ እንዲሰረዙና እንዲቀየሩ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተስማምቷል። ፓርቲው ከተመሰረተ ጀምሮ በብቸኝነት በፕሬዝዳንትነት ሲመሩት የነበሩት አቶ ተሻለ ሰብሮ ለስልጠና በሚል ወደአሜሪካ ከተጓዙ በኋላ ነበር ከድርድሩ መውጣቱን ያሳወቀው። በዚህ ወቅት የጸረሽብርተኝነት አዋጁ ላይ ነበር ድርድሩ ሲደረግ የነበረው። ኢራፓ በጸረ ሽብር አዋጁ ላይ ለድርድር ያቀረበው ሃሳብ አዋጁ ሙሉ በሙሉ ይቀየር የሚል ነበር። በመሰረቱ ኢራፓ ይህን አቋም የያዘበትን አሳማኝ ምክንያት አላቀረበም። አዋጁ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ በምን አይነት ህግ መተካት እንዳለበትም አላመለከተም፣ ይዞ የቀረበው አማራጭ ህግም የለም።


በመጨረሻም “አዋጁ ሙሉ በሙሉ ይለወጥ የሚለው አቋሜ ተቀባይነት ካላገኘ በድርድሩ አልቀጥልም” የሚል አቋም ያዘ። የተቀሩት ፓርቲዎች ግን እንዲሻሻሉ በተስማሙባቸው የጸረሽብርተኝነት አዋጁ አንቀጾች ላይ የህግ ባለሞያ ማብራሪያ እንዲቀርብ ወስነው ይህን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።


በመሰረቱ ድርድር በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚመራ ነው። ኢራፓ እኔ የሰጠሁት አቋም ተቀባይነት ካላገኘ በድርድሩ አልቀጥልም ማለቱ፣ ይህን የሰጥቶ መቀበል የድርድር መርህ ይጻረራል። እስካሁን በሰጥቶ መቀበል መርህ ሲደራደር የቆየው ኢራፓ ድንገት አዲስ አመል አብቅሎ ከድርድሩ ለመውጣት የመወሰኑ ነገር ሰበብ ፍለጋ ይመስላል። ይህ ከድርድሩ የመውጣት አቋም ከፓርቲው የመነጨ መሆኑም ያጠራጥራል።


በተለይ ከፕሬዝዳንቱ የውጭ አገር (አሜሪካ) ጉዞ ጋር ተያይዞ ሲታይ፣ ድርድሩ ህገወጥ የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸውን እንዳያረክስባቸው በሚሰጉ በውጭ አገር ያደፈጡ ተቃዋሚዎች ተጠልፈው ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ይጭሯል። የአሜሪካው ግብዣ ራሱ ከድርድሩ መውጣትን መስዋዕት በማድረግ የተገኘም ሊሆን ይችላል። ከድርድሩ መውጣት የገንዘብ ድጋፍም ሊያስገኝ ይችላል። እድሜ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠላቶች፤ ዶላር ሞልቷል።


ያም ሆነ ይህ፤ ኢራፓ ከድርድሩ መውጣቱን በይፋ ያበሰረበት በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የተለቀቀ መግለጫ፤ በድርድሩ ሂደት ምንአልባት ኢሕአዴግን ወደ ሕዝባዊነት፣ ሕዝቡን ደግሞ ወደ ሥልጣን ባለቤትነት ሊቀይሩ የሚችሉ እድሎች እንደሚፈጠሩ ተስፋ በመሰነቅ፣ ራዕይ ፓርቲም ወደ ድርድሩ ሊገባ ችሏል። ሆኖም ግን ኢሕአዴግ በአሳዛኝ ሁኔታ ድርድሩን ለሕዝባዊ ትግሉ ማዳፈኛ፣ ይውረድልን ጥያቄው ማስታገሻ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ማስተንፈሻ፣ ለራሱ ደግሞ የማጣጣሪያ ትንፋሽ መግዢያ፣ አድርጎ ሲጠቀምበት ከርሟል ይላል። አያይዞም የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ የድርድሩ የዓመት ጉዞ ለአገራችንም ሆነ ለሕዝባችን ያበረከተው ምንም ፋይዳ እንዳልነበረው ገምግሟል . . . ብሏል። በኢራፓ መግለጫ ላይ የሰፈሩት ሌሎች ሃሳቦች የተለመዱ ባዶ ጩኸቶች በመሆናቸው፣ ከላይ የተጠቀሰውን የመግለጫውን አንኳር ጉዳይ ነጥለን ከእውነታው አኳያ እንመለከት።


ኢራፓም የተሳተፈበት ድርድር፣ በመግለጫው ላይ እንደተገለጸው ፋይዳ የሌለው አልነበረም። ይህ ነጭ ውሸት ነው። ድርድሩ ሁሉም የህዝብ ድምጾች፣ አናሳ ድምጾችም ጭምር በመንግስት ውስጥ ውክልና አግኝተው የሚደመጡበትን ሁኔታ በመፍጠር የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ የተደረሰበት ነው። ኢራፓ ለዚህ የድርድሩ ውጤት ዋጋ መስጠት አልፈለገም።


ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያስታውሰው ኢራፓም እንደሚያወቀው፣ ድርድሩ በምርጫ አዋጆች ነበር የጀመረው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሰነምግባር ደንብና የምርጫ አዋጁ ላይ ድርድር ተካሂዶ በርካታ አንቀጾች እንዲሻሻሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከእነዚህ መካከል ህገመንግስታዊ ማሻሻያን እስከማድረግ የሚዘልቀው በምርጫ ህጉ ላይ የሰፈረውን የምርጫ ስርዓት የሚቀይር ስምምነት ተጠቃሹ ነው። ይህ ስምምነት የድርድሩ ታሪካዊ ውሳኔ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።


በድርድሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በኢፌዴሪ ህገመንግስትና በምርጫ ህጉ ላይ ያለው የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት ተሻሽሎ፣ የአብላጫና የተመጣጣኝ ውክልና ቅይጥ እንዲሆን ተስማምተዋል። በቅይጥ የምርጫ ስርዓቱ፤ 80 በመቶ በአብላጫ ምርጫ ድምፅ፣ 20 በመቶ ደግሞ በተመጣጣኝ ድምፅ የፓርላማው ወንበር እንዲያዝ ስምምነት ላይ ተደርሷል።


የአብላጫና ተመጣጣኝ ድምጽ ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ስርዓት በፌዴራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በክልል ምክር ቤቶች እንዲሁም በአዲስ አበባና ድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ የሚደረግ እንዲሆንም ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል፤ ኢራፓም ጭምር። ፓርቲዎቹ የተስማሙበት የአብላጫና ተመጣጣኝ ቅይጥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልና ስርዓት አሁን ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ላይ 110 ተጨማሪ መቀመጫዎች እንዲኖር ያደርጋል። ታዲያ ከዚህ በላይ ለህዝብ ፋይዳ ያለውና ለስልጣን ባለቤትነት እድል የሚያመጣ ውሳኔ ምን ይሆን?


ከላይ የተገለጸውን የምርጫ ስርዓቱን እስከማሻሻል የሚዘልቀው የድርድሩ ስምምነት ታሪካዊ ነው። ይህ ስምምነት ተደራዳሪ ፓርቲዎቹንም በታሪክ ተጠቃሽ ያደርጋቸዋል። ኢራፓ እንደሚገመተው በውጭ ኃይሎች ግፊት ወይም ማባበል ከታሪካዊው ድርድር መውጣቱ ይህን ታሪካዊ ድርሻን በመወጣት ተጠቃሽ ሊያደርገው ይችል የነበረውን እድል እንደመግፋት ይቆጠራል።


ኢራፓ ከድርድሩ ለመውጣት መወሰኑ በተለይ ውጭ አገር የሚገኙ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን የማፍረስ ፍላጎት ያላቸውን፣ ይህን ለማድረግ ከሃገሪቱ ጠላት ጋር እስከማበር የዘለቁ ቡድኖችን ጭብጨባ ሊያስገኝለት ይችል ይሆናል። ዶላርም ሊያስገኝ ይችል ይሆናል። የአገሪቱን ዴሞክራሲ በማጎልበት የህዝቡን የልማትና የሠላም ፍላጎት ከሟሟላት አንጻር ሲታይ ግን ቀሽም ውሳኔ ነው።


ኢራፓ በእልህ አስጨራሽ ሰላማዊ ትግል ራሱን እያጎለበተና ተመራጭ እየሆነ ከመዝለቅ ይልቅ፣ በውጫዊ ግፊት ጯሂ አቋሞችን በማንጸባረቅ እንደ ጭድ እሳት ቦግ ብሎ ጠፍቶ ሰሞነኛ ፓርቲ መሆን እየመረጠ መሆኑን ሊያስተውል ይገባል። በዚህ አካሄድ ፕሬዝዳንቱ በተደጋጋሚ የቪኦኤ የአማርኛ ፕሮግራም እንግዳ መሆን ይቻሉ ይሆናል። ፓርቲያቸውን ራሱን ችሎ የቆመና የህዝብ ድጋፍ ያለው፣ የስልጣን ውክልና ሊረከብ የሚችል ግዙፍ ፓርቲ ማድረግ ግን አይችሉም።

 

በይርጋ አበበ


በአዳማ ለአስር ቀናት ሲካሄድ የነበረው የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አስራ አራት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ላይ እርምጃ በመውሰድ ተጠናቀቀ፡፡


ማዕከላዊ ኮሚቴው አስር አባለቱን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አሰወጥቷል፡፡ ከተሰናበቱ መካከል ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ አቶ ሶፊያን አሕመድ፣ አቶ ደምሴ ሽቶ፣ አቶ በከር ሻሌ እና ሌሎች ይገኙበታል፡፡


በአራት አባላት ላይ እገዳ ሲጥል፣ ለአንድ አባል ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቋል፡፡

 

ማዕከላዊ ኮሚቴው የቋም መግለጫ በማውጣትም አቋሙን አንጸባርቋል፡፡ የተሰጠውም ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

ከኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ

የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

 

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተጀመረው የለውጥ ጉዞና የወደፊት አቅጣጫ ለ10 ቀናት ዝርዝር ግምገማ በማድረግ ዛሬ ማምሻዉን በስኬት አጠናቋል፡፡


ግንባራችን ኢህአዴግም በጥልቅ ለመታደስ የጀመረውን ንቅናቄ ዳር ለማድረስ በቅርቡ ራሱን ገምግሞ አቅጣጫ ማስቀመጡ የሚታወስ ሲሆን ከግምገማው በመነሳትም ሀገራችን ኢትዮጵያና ክልላችን በፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች ያለችበትን ሁኔታ በዝርዝር በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡


አስር ቀናት በፈጀው የአሁኑ ውይይታችን፣ የሕዝባችን ሰላምና አብሮነት በምንም መልኩ አደጋ ውስጥ እንዳይገባ የክልላችን ሕዝቦች እና መሪ ድርጅቱ ኦህዴድ በቅንጅት በመስራት የሀገራችንን ሕልውና መታደግና የተጀመረውን የለዉጥ ጉዞ በስኬት እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡ ድርጅታችን ከሚታወቅባቸው መለያ ባህሪያቱ እያንደንዱ ጉድለቶቹን ያለማመንታት መቀበልና ለማረም ጥረት ማድረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ የዴሞክራሲያዊ ድርጅት ባህሪይ በመሆኑ ከሕዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ማድመጥ፣ ሕዝቡን ከልብ ይቅርታ የመጠየቅና የእርምት እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በዝርዝር በመምከር አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡


የፌዴራል ስርዓቱን አደጋ ውስጥ ሊጥሉ የሚችሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለይቶ አፋጣኝ እርምጃዎችን በመውሰድ የሕዝቡን መሻት ማሳካት ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን በዝርዝር ተመልክቷል፡፡ ፍትሃዊ የኃብት ክፍፍል፣ አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓት፣ ሰላምና ፍትህ እንዲሰፍን በጥብቅ ዲስፒሊን በመስራት የሕዝብ እርካታን ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው መሰረታዊ አጀንዳ ስለመሆኑ መክሯል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከመላዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመተባበር የሀገራችንን ቀጣይ ጉዞ የማቅናት ሚናውን ዛሬም እንደትላንቱ መጫወት እንደሚገባውም ተወያይቷል፡፡


በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በዴሞክራሲ አግባብ በማጠናከር የጋራ አላማችንን ለማሳካት ርብርብ ማድረግና የሀገሪቱን ሕልውና ከአደጋ መከላከል እንደሚገባ በዝርዝር በመምከር አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡


የፌዴራላዊ ስርዓታችንን አደጋ ላይ የጣሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን፣ ሕዝቡ በመሪ ድርጅቱ ላይ እንዲያምጽ ያስቻሉ የመልካም አስተዳደር እጦቶችን፤ ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ መሆኑን በመዘንጋት በርስትነት ይዞ ለግል ምቾትና ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን፣ በነጻነት ተዘዋውሮ የመስራት መብትንነፍጎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦችን እስከማፈናቀል የደረሰ ድርጊትን፤ በኢንቨስትመንት ስም የመንግስትና የህዝብ መሬት መመዝበሩን፤ እንዲሁም የሕዝቦች ሰላምና ጸጥታ መደፍረሱን እና የመሳሰሉትን እየተፈጸሙ ያሉ አደገኛ ድርጊቶችን ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ አምርሮ በመታገል የሀገራችንን ሕልውና መታደግ ልዩ ትኩረት የሚሹ አበይት ጉዳዮች መሆናቸውን በዝርዝር ተመክሮባቸዋል፡፡


ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከሰቱ ግጭቶች የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ የሕዝቦች በሰላም ዉሎ ማዳር፣ ወጥቶ መግባት ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቃል፡፡ ለእነዚህ ችግሮች መከሰት ኃላፊነቱን ወስዶእርማት ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ አጽንኦት ሰጥቶ በመምከር አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡


የፌዴራል ስርዓቱን አደጋ ላይ በመጣል ግላዊና ቡድናዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ በንጹሃን ዜጎች ሕይወት ላይ አደጋ ያደረሱና በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ፀያፍ ድርጊቶችን የፈጸሙ ኃይሎች በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ፣ እንዲሁም መሰል ስህተት እንዳይደገምና የሕግ የበላይነት በመላ ሀገሪቱ እንዲሰፍን ለማስቻል ሕዝቦችንን በማሳተፍ ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የግድ መሆኑን ከግንዛቤ አስገብቶ ማዕከላዊ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡


ቀንደኛ የሕልውናችን ጠላት ድህነት መሆኑ ቢታወቅም ይህንን ጠላት ለመዋጋት በመንግስት፣ ድርጅትና ሕዝብ ትስስር ሊሰራ እንደሚገባውና አዳዲስ ሃሳቦችን አያፈለቀ አመራር የመስጠት ጉዳይ ከድርጅታችን እንደሚጠበቅ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡


ኃብት ማመንጨት ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊ የኃብት ክፍፍል እንዲኖር ማስቻል፣ የኃብት አጠቃቀምንም ከብክነት የጸዳ ማድረግ፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ አሰራር በማስፈን ሕዝቡ እንዲያለማ ከማስቻል በዘለለ የመቆጣጠር ሚናውንም ከፍ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡


አዳጊ ኢኮኖሚን የሚያንኮታኩቱ መጥፎ ልማዶችን በተለይም ሙስና፣ ኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ፍላጎቱን ማኮላሸት፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ማስተጓጎል፣ ማንኛምውም የገበያ ፍትሃዊነትን የሚያዛቡ አሉታዊ ተግባራትን አጥፍቶ በምትኩ በዘመናዊነት የታገዘ ፍትሃዊ አሰራርን መዘርጋት፣ ያልተገባ የጥቅም ትስስር ያላቸዉን ሰንሰለቶች በጥናት ላይ በመመሰረት የመበጣጠስ ተግባር በተቀናጀና የሪፎረም ሥራውን በሚያሳልጥ መልኩ እንደሚፈፀም አቅጣጫ ተቀምጠዋል፡፡


ሕገመንግስታዊ ድንጋጌዎች ሳይሸራረፉ ተግባር ላይ እንዲውሉ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ዜጎች ካለምንም ስጋት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዲሰሩ በማስቻል በፍትህ ስርዓቱና በፖሊሲ ስርዓታችን ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሊያስገኙ የሚችሉ ሁለንተናዊ ሪፎርም ማከናወን እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡


ከክልሎች ጋር የጀመርነዉን ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ህግ መንግስታዊነቱን ጠብቆ እንዲቀጥልና ፌዴራላዊ ስርዓታችን ይበልጥ መጠናከር የሚችልበት ሁኔታ አጽንኦት ተሰጥቶት ተመክሮበታል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ የመቻቻል፤ የመደጋገፍና አብሮ መኖር እሴቶችን ያዳበረ በመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመከባበርና በፍቅር አብሮ በመኖር የሁሉም ዜጎች መብት በእኩል እንዲከበር ከወንድም ሕዝቦች ጋር አብሮ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ጥላቻን በጥላቻ፣ ክፉተግባርን በሌላ ያልተገባ ድርጊት መመከትሊቆም ይገባዋል፡፡ በመሆኑም ተከሰቱ ለሚባሉ ችግሮች ሁሉ መፍትሄው ፍትሃዊና ሕጋዊ የትግል ስልትን መከተል መሆኑ ታምኖበት ከጥፋት ተግባራት በመታቀብኦሮሙማን በሚያጎላአቃፊ መሆን እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡


ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝቦች ጋር የነበረንን መልካም ግንኙነት በመመለስ እንደ ወንድማማች ሕዝቦች የባይተዋርነት ስሜት እንዳይፈጠር በሚያስችል መልኩ በታላቅ የኃላፊነት ስሜት እንዲመራግዚያዊ ችግሮችን ፈተን ለዘላቂ የጋራ ጥቅሞቻችን በወንድማማችነት መንፈስ እነድንረባረብ የሶማሌም ይሁን ሌሎች ብህረ ብሄረሰቦች በኦሮሞ ባህልና የገዳ ስርዓተ ባስተማረን መልኩ በፍቅርና በአብሮነት እንዲኖሩ ለማስቻል ሕዝቡ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል፡፡


የሐሳብ ልዩነቶችን ማጥፋት አስቸጋሪ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ስለሆነም ሁል ጊዜ ለውይይትና ለክርክር አውድ ማስፋት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ፍላጎትን በውይይት እንጂ በኃይል የማስረጽ ዝንባሌ እንዳይታይ በቀጣይነት መስራት እንደሚያስፈልግም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡


ዛሬ አድገው የሀገራቸውን ህዝብ ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ ያሻሻሉ ሀገራት ታሪክ ሲመረመር በአገራዊ ጉዟቸው ውስጥ ሕዝባዊ አመጽን ያስተናገዱ፣ የወጣቶች ቁጣ የደረሰባቸውና መሰል አጋጣሚዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መቀልበስ የቻሉትየዘላቂ ልማት ባለቤት እንደሆኑ ታሪካቸው ያሳያል፡፡ በመሆኑም በወጣቶች ላይ የሚታየውን ፍትህ የመሻት ቁጣ ሀገርን በማያፈርስ መልኩ ከሃይል በፀዳ ሁኔታ ሰላማዊ የትግል ስልት እንዲከተሉ በማስተማር የዴሞክራሲ ባህልን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ኮሚቴው ያምናል፡፡ ዋነኛ ሚናውም የተሻለች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር በመሆኑ የተሻለች ሀገር ብቻ ሳይሆን ብቁ ተረካቢ ወጣቶችን ማፍራት እንደሆነም ይገነዘባል፡፡


በአለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለው ድርቅ፣ ግጭት፣ ስደት፣ የሕዝብ መብዛት ያልተደራጀ ኢኮኖሚና ያልደበረ የዲሞከራሲ ባህል ባለበት ሀገር ነገሮች እንዲባባሱ ከማድረግ አልፎ የሀገር ህልውናን አደጋ ውስጥ እስከመጣል እንደሚደርስ ታውቆ የተሻለች ሀገር የመፍጠሩና ብዙ ተረካቢ የማፍራቱ ተግባር በጥንቃቄና በኃላፊነት ስሜት እንዲከወን በዝርዝር ተመክሯል፡፡


ይህንንም ከማሳካት አኳያ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖችን ከጊዜያዊ መጠለያ ወደ ቋሚ ቦታ ማስፈር፤ የወጣቶችን የስራ አጥነትን በመቀነስ የኑሮ ሁኔታቸውን ማሻሻል፤ የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮችን ማስተካከል፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ማዘመን፤ ፍርድ ቤት፣ አቃቤህግ፣ ፖሊስ፣ የወረዳና የቀበሌ መዋቅሮችን መልሶ ማደረጀት፤ ሰላምና ፀጥታ በማስከበር የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገኙበታል፡፡


በመላ የሀገራችን ህዝቦች ይሁንታ አፋን ኦሮሞ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን ድርጅታችን ይሰራል፡፡ በተጨማሪም በሂደት ላይ ያሉና ያልተጠናቀቁ መሰረታዊ የህዝብ ጥያቂዎች በጥብቅ ዲስፕልን እዲፈጸሙ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡


በድርጅቱ ተጠያቅነትን ለማረጋገጥ፤ መድረኩ የሚጠይቀውን የትግል ልክ በብቃት ለመፈፀም፣ በቀጣይም ጥንካሬውን አጎልብቶ መጓዝ ይችል ዘንድ 14የኢህአዴግ ምክር ቤት አባላት እንዲተኩ እና 4 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም እሰከሚቀጥለው ጉባኤ እንዲታገዱና አንድ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በማስጠንቂያ እንድታለፍ የወሰነ ሲሆን የዉስጠ ድርጅት ዲሞክራሲ የማስፋትና የአመራሩን የሃሳብና የተግባረ አንድነት ይበልጥ ማጠናከር በቀጠይነት እዲሰራበት ተመክሮዋል፡፡


ለዘመናት ትከሻህ ላይ ተጭኖ የነበረውን የጭቆና ቀንበር ለመስበር ሁልጊዜም ታሪክ እየዘከረው የሚኖር አኩሪመስዋዕትነት ከፍለሃል፡፡ በከፈልከው መስዋዕትነት ከሌሎች ወንድሞችህ ጋር በመሆን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር፤ እኩልነት፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲና ሁሉን አቀፍ መብቶች የተረጋገጡባትን የበለፀገች ሀገር ለመገንባት መሰረት ጥለሃል፡፡ በተጀመረው የግንባታ ሂደት ውስጥ የመጡ ተስፋ ሰጪ ድሎች እንዳሉ ሁሉ የጭቆና መሰረት የሆኑ አስተሳሰቦችና አሰራሮችን የሚፈጥሩ አዝማሚያዎችም ይታያሉ፡፡ በነዚህ አዝማሚያዎች ላይም የጀመርከውን ትግል አጠናክረህ መቀጠል ያንተም ሆነ የወንድም ሕዝቦች የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡


የመደብ ጭቆና ምን ያህል አስከፊ እንደሆና አዎንታዊ ለውጥን እንደሚገታ ባለፈው ታሪክህ ካንተ በላይ የሚገነዘብ የለም፡፡ በአሁኑም ሰዓት ተመሳሳይ መደባዊ ጭቆና ዳግም በሀገራችን እንዳያቆጠቁጥ ትግልህን አጠንክረህ መቀጠል ይገባሃል፡፡


በሁሉም የታሪክ ምዕራፎች ኢፍትሃዊነትና ጭቆናን ባለመቀበል ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን መስዋዕትነት እየከፈልክ ወደ ድል ስትራመድ እንደነበረው ሁሉ አሁንም ሀገራችንን የገጠሟትን ፈተናዎች በታጠቅከው የገዳ ስርዓት ቱባ ባሕል መሰረት ብሄር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በማቀፍና ከጎንህ በማሰለፍ ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ህልውና በማስጠበቅ ለውጧን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የማስቀጠል ኃላፊነትህን እንዲትወጣ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

 

የተከበራችሁ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች


የክልላችንም ሆነ ሀገራዊ ለውጦች ያለወጣቱ ተሳትፎና መሪነት የሚታሰብ አይደለም፡፡ በዚሁ መሰረት እስካሁን በሀገራችን የመጡ ለውጦች በወጣቱ ተሳትፎና አኩሪ መስዋዕትነት የመጡ መሆናቸውን ኦህዴድ ይገነዘበዋል፡፡ ወጣቶቻችን በሁሉም መስክ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴና መልካም ጅምሮች ወደ ላቀ ድል እንዲሸጋገሩ በባለቤትነት መሳተፍና ኃላፊነትን መወጣት፣ ይህንንም በተደራጀ መልኩ መተግበር ይገባዋል፡፡ ወጣቱ በሁሉም መስክ የሚያደርገውን ትግል ምክንያታዊና ሳይንሳዊ በሆኑ ሃሳቦች እየተመራ፤ ዴሞክራሲያዊነትን በጠበቀና ተደማሪ ለውጦችን በተንከባከበ መልኩ የሁሉም መብት ተከብሮ፣ የሀገራችንም ህልውናና የክልላችን ሰላም እንደተጠበቀ የሚቀጥልበት አካሄድ እንዲረጋገጥ ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ድርጅታችን ኦህዴድ ጥሪውን ያቀርባል፡፡


በሁሉም የታሪክ ምዕራፍ ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ባለፈበት የትግል ሂደት ውስጥ እናንተም መስዋዕትነት ከፍላችኋል፡፡ አሁንም በደረስንብት የትግል ምዕራፍ ውስጥ ከሕዝባችሁና ከመሪው ድርጅታችሁ ኦህዴድ ጋር በመሰለፍ ዋንኛው ሥራ የሆነውን ሃሳብን የማፍለቅና የትግሉን አቅጣጫ በጥናትና በምርምር የማሳየት የማይተካ ሚናችሁን እንደሁል ጊዜው መወጣት ይኖርባችኋል፡፡ ድርጅታችን ኦህዴድ፣ ምሁራንን ባላቸው አደረጃጀትም ሆነ በግል ክህሎታቸው፣ እውቀትና የአመራር ብቃትም ጭምር አብሮ ለመስራት የጀመረውን ሥራ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ አጠናክሮ ለመቀጠል ወስኗል፡፡ በዚሁ መሰረት የተከበራችሁ የኦሮሞ ምሁራን የጀመራችሁትን ጠንካራና ተኪ የሌለው ሚናችሁን በመወጣት አጠናክራችሁ ትግሉን እንድትቀጥሉ፣ ለስኬትም እንድትረባረቡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡


የኦሮሞ ሕዝብ ባደረገው ትግል የራሱን ክልል መስርቶ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታትና ራዕዮቹን ለማሳካት ትልቅ የመንግስት መዋቅር ዘርግቷል፡፡ በዚህ መዋቅር ውስጥ የሕዝባችንን ችግር መፍታት የሚቻለው ከእውቀትና ክህሎት በተጨማሪ ጠንካራ ዲሲፒሊን ባለው የመንግስት ሰራተኛ ነው፡፡ በመሆኑም፣ በመንግስት መዋቅር ውስጥ እየፈጠረበት ያለውንየመብት ጥሰት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ እየተስፋፋ ያለው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ኢ-ፍትሃዊነትና የዴሞክራሲ እጦት ችግሮችን ለመፍታት የክልላችን መንግስት ሰራተኞች ቁልፍ ሚና አላችሁ፡፡ ሕዝባችንን አንገት ያስደፋውን ዋነኛ ችግሩን በመቅረፍ ብልጽግናን ለማስፈን፣ የማስፈፀም አቅምን ለማጎልበት፣ ቀን ከሌሊት ተግታችሁ የመስራት ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡


በክልላችን ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ከሕዝባችን ጋር በተለይም ከወጣቶች ጋር በመቀናጀት የሕዝባችንን ጥቅምና ሀብት ሲዘርፉ የነበሩ ኮንትሮባንዲስቶች ላይ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም በክልላችን የተጀመረውን ሪፎረም ለማደናቀፍ ዝርፊያ ድርጊታቸውን ማስቀጠል የሚፈልጉ የተደራጁ ኪራይ ሰብሳቢዎች የከፈቱትን ጥቃት ለመመከት በግንባር ቀደምነት ተሰልፋችሁ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍላችኋል፡፡ በዚሁም የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ሕልውና እንዲቀጥል ድርሻችሁን በመወጣት ከአደጋ እየታደጋችሁ ትገኛላችሁ፡፡


የኪራይ ሰብሳቢዎች ቡድን በመንግስት ስልጣን የመክበር አባዜ ከስር ተነቅሎ፣ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ እስኪሸነፍ ድረስ የጀመራችሁትን ትግል ሕዝብን በማሳተፍ በከፍተኛ ዲሲፒሊን ሕዝባዊ ኃላፊነታችሁን መወጣት ይገባችኋል፡፡ በክልላችን አስተማማኝ ሰላምና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ እንዲሁም ፍትህ የሰፈነበት እንዲሆንና ዜጎቻችን መብታቸው ተከብሮ ስርዓት አልበኝነት እንዳይኖር የተሰጣችሁን ተቋማዊ ኃላፊነት ከሕዝብ ጋር በመቆም ሕዝባዊ በሆነ መንፈስ እንድትወጡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡


ተንሰራፍቶ የቆየውን ጭቆና ለማስወገድ ሕዝባችን ሲያካሄድ በነበረውን መራራ ትግል ውስጥ የመርነት ሚናን ተቀብለህ መስዋዕትነት በመክፈል የዛሬው ምዕራፍ ላይ እንዲደርስ የበኩልህን አስተዋፅኦ አበርክተሃል፡፡ ጠንካራ ድርጅት ያላ ጠንካራ አባል ሊታሰብ አይችልም፡፡ ኦህዴድ ያለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲወጣ አሁን በደረሰበት የትግል መድረክ የሚመጥን ቁመና እንዲኖረው ለማስቻልና ለማስቀጠል የድርጅታችን አባላት የድርጅታችሁን አላማ በጥብቅ ዲስፒሊን ለማሳካት ቀን ከሌሊት መታገል ይገባችኋል፡፡ ሕዝባችን በተለያየ ደረጃ እያደረገ ባለው ትግል ውስጥ አባሎቻችን በግንባር ቀደምነት በመሳተፍና በመምራት ችግሮችን በኃላፊነት መፍታት ይገባቸዋል፡፡ አሁን የደረስንበት የትግል ምዕራፍ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት በቅድሚያ በመክፈል ለሌሎች ምሳሌ በመሆን የድርጅታችሁን ተልዕኮ በተሰማራችሁበት መስክ ሁሉ በማሳካት የሕዝባችንን ጥያቄ በአፋጣኝ እየመለሰ፣ ትግሉን በግንባር ቀደምነት በመምራት አዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ኃላፊነቱን የሚወጣ፣ ጠንካራና ከለውጥ ጋር ራሱን የሚያሳድግ ድርጅት እውን እያደረጉ መጓዝትኩረት የሚሻ በመሆኑ ይህንንም በብቃት መወጣት ይገባችኋል፡፡


በኦሮሞ ሕዝብ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ባላችሁ እውቀትና ኃብት በተደራጀም ሆነ ባልተደራጀ መልኩ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ለመወጣት ስታደርጉ የነበረውን ርብርብ የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እንደነበሩ እና መድረኮችም አስቸጋሪ እንደነበሩ ኦህዴድ ይገነዘባል፡፡ በሕዝባችን አንድነትናሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ፣ ባላችሁ ተሞክሮዎና ትስስር፣ በኃብትና በመሳሰሉት ሁሉ እንድትሳተፉና የሕዝባችንን ችግር በጋራ እንድንፈታ፤ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችም እንዲመቻቹ ኦህዴድ ጠንክሮ እንደሚሰራ ሊያረጋግጥ ይወዳል፡፡ በዚሁ መሰረት በውጭ ሀገር የምትኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች በሕዝባችን ጥቅም ላይ ያለምንም ድንበርና ልዩነት በጋራ እንድንሰራ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡


ድርጅታችን ኢህአዴግ፣ በሀገራችን ሕዝቦች ላይ የተጫነውን ጸረ-ዴሞክራሲ፣ ድህነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና ኋላቀርነትን ለመፍታት ባደረገው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ድሎችን ማስመዘገብ የጀመረው በውስጡ ያለውን ችግር በተከታታይ በመፈተሽና በመፍታት ላይ ነው፡፡ በቅርቡ በኢህአዴግ ደረጃ በተደረገ ግምገማ በእህት ድርጅቶቹ መካከል የተፈጠረው ያልተገባ ግንኙነት በሂደትም ወደ ጥቅም ቡድተኝነት እያደገ በመምጠቱ የነበረው ግንኙነት እያሻከረ እንዲሄድ አድረገዋል፡፡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴም ጉዳዩን በጥልቀት በመገምገም ማንኛውም ግንኙነቶች መርህና መርህ ላይ ብቻ እንዲመሰረቱና ዴሞክራሲያዊ ትግልን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ ለማስቻል ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቶበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በዚሁ መሰረት የእህት ድርጅቶች አሁን በደረስንበት የትግል ምዕራፍ በግንባራችን ኢህአዴግ ተገምግመው አቅጣጫ የተቀመጠባቸውን ጉዳዮች ያለምንም መሸራረፍ እንዲፈፀሙና የሕዝባችንን ጥያቄ ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት ርብርብ እንድናደርግ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡


በብዝሃነት ለተገነባች ሀገራችን ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የህልዉና ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው፡፡ እንደ ነብር ዥንጉርጉር የሆነው የእርስ በእርስ ግንኙነታችን የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ የሚያስችል አሰራርና ባህል ማዳበር ያስፈልገዋል፡፡ ከሃይል የፀዳ፣ በዉይይትና በምክክር የሚያምን፣ ይበልጥ ለሀገር የሚበጅ ሃሳብ የሚፈልቅበት የውይይት ባህል እንዲዳብር የፖለቲካ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዋይነትና አርቆ አሳብነት የሚፈተንበት ጊዜ መሆኑ ግለፅ ነው፡፡ በመቀራርብና በመነጋገር የፖለቲካ ባህላችንን እንድናሻሽል ብሎም የሀገራችንን መፃኢ ዕድል በጋራ ማበጀት እንችል ዘንድ ተቀራርበን እንድንሰራ ድርጅታችን ይፈልጋል፡፡


ዴሞክራሲ ለሀገራችን ሕዝቦች የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ለመገንባት የሀሳብ ልዩነቶች የሚስተናገዱበት ማዕቀፍና አሰራር እንዲሁም ባህልና አስተሳሰብ እንዲዳብር የፖለቲካ ፓርቲዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ኦህዴድ በሚገባ ይገነዘባል፡፡ የሀገራችን ሕዝቦች አማራጭ ሀሳቦች እየቀረቡለት በዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚጠቅመውን ሃሳብ እንዲመርጥ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሕገመንግስቱ የተቀመጡ ቃልኪዳኖች ያለመሸራረፍ እንዲተገበሩና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ኦህዴድ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፖርቲዎች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ በጥልቅ ተወያይቶበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በዚሁ መሰረት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገራችንና በሕዝባችን የጋራ ጥቅምላይ ከድርጅታችን ኦህዴድ ጋር አብራችሁን እንድትሰሩ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡


የኢትዮጵያ ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በችግርም ሆነ በመልካም ጊዜ በጋራ ተፈትነው ትላንትን መሻገር ችለዋል፡፡ ለገጠማቸው ፈተናዎችምእኩል የታገሉና መሰዋትነት የከፈሉ ህዝቦች ናቸው፡፡ ሀገራችን ህልዉ ሆና እድትቀጥል ከማስቻላቸዉ ባሻገር በዓለም ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቀለም እንዲኖራት አድርገው ለዛሬ ትውልድ አሰረክበዋል፡፡ በአባቶቻችን ተጋድሎ የተገነባችውን ኢትዮጵያ እኛም አስውበንና አንድነቷን አስጠብቀን ለቀጣይ ትዉልድ የማሻገር ታርካዊ ኃላፍነት አለብን፡፡ በአንድ እጅ ማጨብጨብ አይቻልምና ይህን ሀላፍነታችን በብቃት እንድንወጣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር፣ የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት፣ የተጀመረው መልካም ጅማሮ ዳር እንዲደርስ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለስኬቱ በጋራ እንድንረባረብ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡


የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴየ10 ቀናት የለዉጥ ግምገማ ቆይታ ድርጅቱ ለሃገራችን ሰለም ልማትና ዴሞክራሲ ጉዞ ስኬት እንዲሁም ለህዝቦች እኩል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከመቼዉም ግዜ በላይ በላቀ ቁርጠኝንትና ተነሳሽነት ለማከናዉን ዝግጁነቱን ያረጋገጠበት መድረክ እነደሆነ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አረጋግጦዋል

 

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ
ጥር 29/05/2010 ዓ.ም

 

 

በይርጋ አበበ

 

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ታሪክ ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ወጣቶች የመጡበት ጊዜ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ጀምሮ ባሉት አስር ተከታታይ ዓመታት ሙዚቃውን በአዲስ ስራ የተቀላቀሉትን ድምጻዊያን ቁጥር በትክክል ይህን ያህል ነው ብሎ መጥቀስ ባይቻልም በርካቶች መሆናቸውን ለመናር ግን አያዳግትም። በተለይ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ የመገናኛ ብዙሃኑን ዘርፍ መቀላቀሉን ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት ወደ 15 የሚጠጉ የመንግስት እና የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና ለ20 የቀረቡ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች መከፈታቸው ሙዚቀኞች ስራቸውን በስፋት እንዲያቀርቡ ሳይረዳቸው አልቀረም ተብሎ ይታሰባል። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ዘመኑ የመረጃ እና የመዝናኛ መሆኑ በራሱ አርቲስቶቹ ስራቸውን ይዘው ለህዝብ እንዲቀርቡ ሳይረዳቸው እንዳልቀረ ይነገራል።


ባለፉት አስር ዓመታት ለህዝብ ከቀረቡ የሙሉ አልበም ስራዎች ይልቅ በነጠላ ዜማ የቀረቡ ስራዎች በርከት ያሉ ናቸው። ለአርቲስቶቹም ቢሆን ከሙሉ አልበም ይልቅ በነጠላ ዜማ መቅረቡ አዋጭ መንገድ ሳይሆን አልቀረም። አንጋፋዎቹና ታዋቂዎቹ ድምጻዊያን ሳይቀሩ በነጠላ ዜማ ከህዝብ ጋር እየተገናኙ ባለበት በዚህ ዘመን ጥቂቶች በመጡበት ፍጥነት ከህዝቡ ጋር ሲገናኙ በርካቶች ደግሞ የህዝቡን ጆሮ ማግኘት ተስኗቸው ይታያል። በዚህ በኩል ድምጻዊ ጌትሽ ማሞ ‹‹ተቀበል›› እያለ ያዜማቸው ሁለት ነጠላ ዜማዎች (ተቀበል እና እንከባበር) ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፉለት ስራዎቹ ሲሆኑ ከሙሉ አልበሙ በላይ ገቢ እና እውቅና ያስገቡለት እንደሆኑ ተነግሯል። በቅርቡ ይለቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ‹‹ተቀበል ቁጥር ሶስት›› ከወዲሁ ረብጣ ገንዘብ ያስገኘለት ስራ እንደሆነ በስፋት ተነግሯል። በዛሬ የመዝናኛ አምድ ዝግጅታችን በነጠላ ዜማዎቻቸው ከህዝብ ጋር መገናኘት ከቻሉት ወጣት ድምጻዊያን መካከል የሁለቱን ወጣቶች ስራዎች እንመለከታን የድምጻዊ አበበ ከፈኒ (ሹሚ) እና ወንድወሰን መኮንን (ወንዴ ማክ)። ሁለቱ ወጣት ድምጻዊያን በኦሮምኛ (አበበ) እና በአማርኛ (ወንዴ ማክ) ከህዝብ ጋር የተዋወቁባቸውን ነጠላ ዜማዎች አቅርበዋል። ወጣቶቹ እስካሁን ሙሉ አልበም ባያወጡም (ወንዴ ማክ ለፋሲካ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል) ለህዝብ ባቀረቧቸው ነጠላ ዜማዎች ተወዳጅነትን አትርፈዋል። ቅኝታችንም በዚሁ ዙሪያ የሚያተኩር ነው።

 

የወንዴ ማክ እና አበበ ከፈኒ ሙዚቃዎች ቅኝት


ጋሻው አዳል ‹‹በምን አወቅሽበት በመመላለሱ›› ሲል የተጫወተውን ተወዳጅ ዜማ ወንድወሰን መኮንን ‹‹ምን ይጥራሽ›› ሲል ከጋሻው አዳል ላይ የራሱን ግጥሞች በማከል አቀነቀነው። ምንም እንኳን የጋሻው አዳልን ዘፈን ዜማ እና ግጥም የሰሩት ድምጻዊ አያሌው መስፍን (በዜግነት አሜሪካዊ) ወንዴ ማክን በአደባባይ ቢዘልፉትም ወጣቱ ድምጻዊ ግን ዘፈኑን የዘፈነው የጋሻው አዳልን ቤተሰቦች አስፈቅዶ እንደሆነ ተናግሯል። ‹‹ምን ይጥራሽ እና አለሁ›› የተባሉትን ሁለት ዘፈኖች ከጋሻው አዳል ዘፈን ላይ የራሱን ግጥም እንደጨመረበት የተናገረው ወንድወሰን መኮንን፤ ከሁለቱ ዘፈኖች በተጨማሪ ሙሉ በሙሉ በራሱ ግጥምና ዜማ የተሰራላቸውን ስምንት ዘፈኖች ለህዝብ በማቅረብ ችሎታውን አሳይቷል።


ወንዴ ማክ በህዝብ ተወዳጅነትን ካተረፉለት ዘፈኖቹ መካከል ‹‹አባ ዳማ›› አንዱ ነው። የሸዋ ኦሮሞ እና የጎጃም ስልተ ምት ያለው ዘፈኑ በሳል ግጥሞችንና ጆሮ ገብ ዜማን የተላበሰ ነው። ከዘፈኑ ላይ ግጥሞችን ስንዘግን፤

‹‹ብርሃን ጠፋፍቶ ቢጋርደን፤
በእኔም ባንቺም ልብ ፍቅር አለን።
ለጊዜው ቀመር እዚህ አድርሶናል፤
መተማመኑን ሽረናል።
ሁሉ በእጅህ ነው የጋጣው ጌታ፤
እስቲ አንድ ፈረስ ስጠኝ ለማታ።
……….
ከአውድማው ላይ የሚያውቁን
ከዳር ሆነው የሚሞቁን።
ቀዩን ከነጭ ከሰርገኛ፤
ቆጥረው ሚለዩን እነሱ መለኛ።
ቂሙን እርሽው ቂሙን ልርሳው፤
ስንለያይ ነው ለእኛ አበሳው።
አዲስ ሆኖ ዛሬ ቀኑ፤
በባለፈው ይቅር መባዘኑ።
እጄን ያዥው አጥብቂና፤
እንድናልፈው የኑሮን ፈተና።›› የሚሉትን እናገኛን።

እነዚህ ስንኞች ሰዎች (ፍቅረኞችም ቢሆኑ) በአንድ ላይ ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ምክረ ሃሳቦች ናቸው። እንደ ድምጻዊው እምነት ተፈጥሯዊ ልዩነቶችን ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ተጨምረውበት መተማመን ሲጠፋ ፍቅር እንዴት እንደሚጎዳ የሚናገረው ይኸው ዘፈን፤ ቂምን ረስቶ ቀንን በአዲስ ፍቅር መጀመር የተሻለ እንደሆነ ይገልጻል። በዚህ ላይ መጽሃፍ ቅዱስ ራሱ ‹‹ያለፈውን የመከራ ዘመን አላስብባችሁም›› እንዳለው ዛሬም ኢትዮጵያዊያን በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ የመሪዎችን ወይም የገዥዎችን ስህተት እያነሱ በጅምላ በህዝብ ላይ በመጫን በህዝቦች መካከል መተማመን፣ መፈቃቀር፣ አንድነት እና አብሮ መኖርን እንዲተው ማድረግ ትርፉ መለያየት እንደሆነ ይህ የወንዴ ማክ ዘፈን እየነገረን ነው። ለዚህ ነው ‹የጊዜው ቀመር እዚህ አድርሶናል፤ መተማመኑን ሽረናል›› ያለው።


በኦሮምኛ ቋንቋ እና በኑዌር (ጋምቤላ) ዘፈኖችን አዘጋጅቶ ከምስል ጋር ያቀረበው አበበ ከፈኒ (ሹሚ) ደግሞ የኦሮሚያን ሙዚቃ ኢንደስትሪ እያነቃቃ ያለ ወጣት ነው። አበበ የመጀመሪያ ስራው የሆነው ‹‹መጋል ወረ ቃሉ›› የተባለ ዘፈን ሲሆን መቼቱን ወሎ ላይ ያደረገ ዘፈን ነው። ወሎ የቆንጆ አገር እየተባለ ተደጋግሞ የሚነገርላት አገር ስትሆን እረኛው በዋሽንት፣ አዝማሪው በመሰንቆ፣ ወልይ በድቢ፣ ድምጸ መረዋ እናቶች በወፍጮ ሳይቀር ስለ ወሎ ቁንጅና ደጋግመው ተቀኝተውላታል እንዲህ ሲሉ።


‹‹በእናቷም በአባቷም ወረሂመኖ ናት፤
እንደ በልጅግ ጥይት ትመታለች አናት።
አረጎ አፋፉ ላይ ያገኘናት ልጅ፤
በእጅ አትንኩኝ አለች በከንፈር ነው እንጂ።
ባቄላ ምርቱ እንጂ አያምርም ክምሩ፤
ይምጣ የወሎ ልጅ ከእነምንሽሩ።››

 

የአገራችን ታዋቂ ድምጻዊያንም ቃላት እስኪያጥራቸው ዜማ እስኪጠፋባቸው የወሎን ቁንጅና ሲሹ በመሰንቆ ሲያሻቸው በጊታር አዚመውልናል። ከእነዚህ ድምጻዊያን መካከል አንዱ ሆኖ የቀረበው ደግሞ ወጣቱ አበበ ከፈኒ ነው። ለስለስ ባለ ዜማ እና ጆሮ ገብ በሆነ ድምጹ ያዜመው ‹‹መጋል ወረ ቃሉ›› ዘፈን አበበን ከህዝብ ጋር ያስዋወቀው ሲሆን እየቆየም ሌሎች ስራዎችን ይዞ መምጣት ችሏል። በተለይ በቅርቡ የለቀቀው ‹‹ጅማ›› የተሰኘ ስራው ቋንቋውን በሚችሉት ብቻ ሳይሆን ቋንቋውን ለማያውቁትም ዘፈኑን ሰምተው እንዲወዱት ተደርጎ የተሰራ ስራ ነው።

 

ዓለምን በነጠላ
የኮፒ ራይት ጉዳይ የዘርፉን ዋና ተዋንያን መቅን የሚስፈስስ ፈተና ሆኖ መቅረቡ ድምጻዊያኑ ከሙሉ አልበም ስራቸው ታቅበዋል የሚል ምልከታ እንዲፈጠር አድርጎታል። ዘመኑ ያፈራቸው ቴክኖሎጂ ውጤቶች ደግሞ አንድን ሙዚቃ በቀላሉ ለሌላ ሰው ማስተላለፍና ዘፈኑን በነጻ እንዲጠቀም ማድረጉ ደግሞ ሰዉ አልበም ገዝቶ ሙዚቃ የማዳመጥ ባህሉ እየቀነሰ የመጣ ይመስላል። በዚህ የተነሳም ዘፋኞች የሚጠቀሙት ዘዴ ሙዚቃቸውን በፕሮዲዩሰር እንዲታተም በማድረግ ወጪያቸውን መቀነስ ነው። ይህ ደግሞ ሊሳካ የሚችለው በከፍተኛ ደረጃ ወዳጅነትና ተፈላጊነት ባላቸው ድምጻዊያን ላይ እንጂ በወጣቶችና ልምድ ቢኖራቸውም ተፈላጊነታቸው እዚህ ግባ የማይባሉ ድምጻዊያንን ሙዚቃዎች ፕሮዲዩስ የሚያደርግ ድርጅት ማግኘት ከባድ እየሆነባቸው መጥቷል።


ይህን የተረዱት ወጣት ድምጻዊያን ነጠላ ዜማ ያወጡና ለመገናኛ ብዙሃን በተለይም ለቴሌቪዥን ጣቢዎች ይሰጣሉ። ዘፈኗ በቴሌቪዥን ተደጋግማ ስትታይ ተወዳጅ ከሆነች ተጨማሪ አዱኛዎችን ይዛ ትመጣለች። ይህም ኮንሰርት ይባላል። በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መካከለኛው ምስራቅ ለኢትዮጵያዊያን ወጣት ዘፋኞች ምቹ የኮንሰርት መድረክ የሆነላቸው ይመስላል። አንዳንድ ወጣቶች በአንድ ወይም ሁለት ነጠላ ዜማዎች ብቻ ተወዳጅነትን በማትረፋቸው ኑሯቸውን መቀየር ሲችሉ ታይተዋል።


ከእነዚህ ወጣቶች መካከል አንዱ ወንዴ ማክ ነው። ወጣቱ ድምጻዊ ሁሉንም ዘፈኖቹን ሙሉ በሙሉ የዜማ እና የግጥም ስራዎች ራሱ የሚሰራቸው ሲሆን ጆሮ ገብ በሆነ ድምጹ የተነሳም ስራዎቹ ተወዳጅ ሆነውለታል። ‹‹ምን ይጥራሽ፣ ሺ ሰማኒያ፣ ሽርሽር፣ ኢትዮጵያ የማናት፣ የኔ ማር፣ አለሁ፣ ይምጣ ያማረው፣ ታገቢኛለሽ ወይ፣ አባ ዳማ እና በቅርቡ ለህዝብ የቀረበው ‘አንድነት’›› የተሰኙ ለአንድ ሙሉ አልበም የቀረቡ ነጠላ ዜማዎቹ ወጣቱን ድምጻዊ በህዝብ እንዲወደድ አድርገውታል። በዚህ የተነሳም በዓለም ዙሪያ እየተንቀሳቀሰ ስራዎቹን ለህዝብ ያቀርባል። ዓለምን በነጠላ ይዞራል ማለት ነው።


ከዓሊ ቢራ እስከ አቡሽ ዘለቀ ድረስ በዘለቀው የኦሮምኛ ሙዚቃ ታሪክ እንደ ታደለ ገመቹ፣ ጃምቦ ጆቴ፣ አጫሉ ሁንዴሳ፣ ጌታቸው ኃይለማሪያም እና ሰለሞን ደነቀ በድንቅ ስራዎቻቸው ተደንቀው ያለፉ እና አሁንም እያስደነቁና እየተደነቁ ያሉ ድምጻዊያን ናቸው። መጋል ወረ ቃሉን ይዞ ብቅ ብሎ ሌሎች ስራዎችን እየጨማመረ የመጣው ወጣቱ አበበ ከፈኒ ወደ ፊት በኦሮምኛ ሙዚቃ አብቦ የሚታይ እንደሆነ ሙዚቃዎቹን ያዳመጡ ሁሉ ይናገሩለታል።

 

መደምደሚያ


ቀደም ባለው ክፍል በተቀመጡ ምክንያቶች አርቲስቶች ሙሉ አልበም መስራቱን ትተው በነጠላ ዜማ ብቅ ማለትን እንደመፍትሔ ወስደውታል። በተለይ ወጣት ድምጻዊያን ነጠላ ዜማን ሰርተው በዩቲዩብ መረጃ መረብ መልቀቅና በዚያ ላይ እውቅናን እያገኙ መምጣት እንደ ስኬት ያዩት ይመስላል። በእርግጥ በነጠላ ዜማ ከህዝብ ጋር ተዋውቆ ተወዳጅነትንና ተቀባይነትን ካገኙ ሙሉ አልበምን ይዞ መምጣት ጥሩ መፍትሔ ነው። ይህን ሳያደርጉ በቀጥታ ሙሉ አልበምን ይዘው በመቅረብ ቶሎ ወደ ህዝቡ መግባት ካልቻሉት ተወዳጅ አርቲስቶች መካከል አሁን በህይወት የሌሉት እዮብ መኮንን እና ሚኪያ በኃይሉ ይጠቀሳሉ። ሁለቱ ድምጻዊያን በሁሉም መመዘኛ ለአድማጭ ተስማሚ አልበም ሰርተው ቢያቀርቡም ቶሎ ወደ ህዝብ ጆሮ ሊገቡ አልቻሉም ነበር። ይህ የሆነው ደግሞ ምናልባትም ከአልበሙ በፊት ህዝብ ሊያውቃቸው ስላልቻለ ዘፈናቸውን ለማድመጥ እንደተቸገረ ይታመናል።


የእነ እዮብን ችግር የተመለከቱ መፍትሔ ብለው የሚስቀምጡት ከአልበም በፊት በነጠላ ዜማ ከህዝብ ጋር መተዋወቅ ጥሩ እንደሆነ የሚመክሩ አሉ። ሆኖም ዕድሜ ልክን በነጠላ ዜማ ብቻ ከህዝብ ጋር መኖር ስለማይቻል ለሙያው ተፈጥረናል የሚሉ ወጣቶች ከተወሰኑ የነጠላ ዜማ ስራዎቻቸው በኋላ በሙሉ የአልበም ስራ ከህዝብ ጋር ቢገናኙ መልካም ሳይሆን አይቀርም።


በዚህ ዝግጅት የተመለከትናቸው አበበ ከፈኒ እና ወንዴ ማክም ሆነ ሌሎች የዘመናችን ወጣት የነጠላ ዜማ ዘመን አቀንቃኞች ከህዝቡ ያገኙትን አቀባበል (ጥሩ ሆኖ ካገኙት) አይተው ለህዝብ ይመጥናል ያሉትን የሙሉ አልበም ስራ ይዘው ቢመጡ መልካም ነው የሚሉ አድማጮች ቁጥር ቀላል አይደለም።

 

በይርጋ አበበ

 

የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ በሁለት ሚሊዮን ብር በደብረ ታቦር ከተማ ያስገነባው የአጼ ቴዎድሮስና የልጃቸው ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ሃውልት ትናንት ተመርቋል።


የደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ደጀኔ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለጹት ሀውልቱን መርቀው የከፈቱት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ያለው አባተ እና የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሒሩት ካሳው ናቸው። በሃውልቱ ምረቃ ላይ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት በተጨማሪ ሃውልቱን ያስገነባው የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዓለማየሁ ከበደን ጨምሮ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ፕሬዝዳንቶች ተገኝተዋል።


የሃውልቱን መገንባት ተከትሎ ከሰንደቅ ጥያቄ የቀረበላቸው የከተማው ነዋሪ የሆኑት አቶ ነጋ ጥሩነህ ‹‹የአጼ ቴዎድሮስን የታሪክ ሰሪነት እና አገር ወዳድነት መንፈስ ለወጣቱና ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ጥሩ አጋጣሚ ነው። ይህን ታሪክ ልጆቻችን እንዲያውቁት ከተደረገ አገርን መገንባትና አንድነቷን አስጠብቀን ማስቀጠል ያስችለናል። ለዚህ ደግሞ ለአገራቸው ውለታ የሰሩ ኢትዮጵያዊያንን ማክበር እና መዘከር ተገቢ ነው። ዛሬ ሃውልቱ ሲመረቅ ደስታዬን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ የተደሰትኩትም ልጆቼን ስለ አገራቸው እንዲያውቁ የሚረዳኝን ታሪክ ስላገኘሁ ነው›› ሲሉ በሃውልቱ ምረቃት የተሰማቸውን ተናግረዋል።


ደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ ከአጼ ቴዎድሮስና ከልጃቸው ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ሃውልት በተጨማሪ በደብረ ታቦር ሆስቲፓል ለህሙማን አገልግሎት የሚውል ባለ አራት ፎቅ ህንጻ በ100 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ያስረከበ ሲሆን በዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ባለ ሁለት ፎቅ ህንጻ በ18 ሚሊዮን ብር ማስገንባቱን አቶ ጥላሁን ደጀኔ ጨምረው ተናግረዋል።


የደብረ ታቦር ሆስፒታልን ወደ ሪፈራል ደረጃ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ዩኒቨርስቲው የመደገፍ ቁርጠኛ ፍላጎት ሲያሳይ መቆየቱን የገለጹት አቶ ጥላሁን፤ ለሆስፒታሉ አገልግሎት የሚውል የህክምና መሳሪያ በ20 ሚሊዮን ብር ገዝቶ ማስገባቱንም ገልጸዋል። እነዚህን ህንጻዎች ለማስገንባትም ዩኒቨርስቲው ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አውጥቷል። 


 

የድምጻዊት ሄለን በርሄ ሁለተኛ አልበም የሆነው ‹‹እስቲ ልየው›› የፊታችን አርብ ወሎ ሰፈር በሚገኘው ‹‹ማማስ ኪቺን›› ይመረቃል። በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የአርቲስቷ አድናቂዎች የሚገኙ ሲሆን ከአልበሙ ውስጥ ፊታውራሪ የተሰኘው ዘፈን የቪዲዮ ክሊፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ የሚበቃ ይሆናል።


በተያያዘ ዜና የፍቅረኞች ቀን የካቲት 7 በኔክሰስ ሆቴል እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። አዘጋጆቹ ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት መግለጫ እንዳስታወቁት በዕለቱ ታዋቂ አርቲስቶች የፍቅር ታሪካቸውን የሚያካፍሉ ሲሆን የኮሜዲያ ስራዎችን ጨምሮ ግጥም፣ መነባንብ፣ ወግ እና የሳልሳና የቲዊስት ዳንስ የፕሮግራሙ አካል እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
ፕሮግራሙን ለመታደም ምግብ እና መጠጥን ጨምሮ ለጥንዶች 1300 ብር መሆኑን አዘጋጆቹ ጨምረው አስታውቀዋል።

 

በይርጋ አበበ

 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ የተለያዩ የድሮን ካሜራዎች መብዛታቸውን ተከትሎ ከደህንነት እና ከአውሮፕላን በረራ ጋር በተያያዘ ካሜራዎቹ ወደ አገር ቤት በሚገቡበትና ስራ ላይ በሚውሉበት ጉዳይ ቁጥጥር ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ገለጸ።


የአቪየሽኑ ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው በጽ/ቤታቸው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ረቂቅ የድሮን መመሪያ ሰነዱን የሚመለከታቸው አካላት እየተመለከቱት ሲሆን ዝግጅቱ ተጠናቆ በቅርቡ ሊጸድቅ እንደሚችል ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የድሮን ካሜራዎች እስካሁን ይህ ነው የተባለ ጉዳት ባያደርሱም በተለይ ከደህንነትና ከግለሰብ ነጻነት (privacy) ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ጥያቄ ይነሳባቸዋል። ሲቪል አቪየሽኑም ይህን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መመሪያውን ለማውጣት መገደዱን ዳይሬክተሩ ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ተናግረዋል።


በኢትዮጵያ ማንኛውንም በአየር የሚበር መሳሪያ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ፣ እንዲመረት፣ እንዲሰራ እና እንዲሸጥ ፈቃድ የሚሰጠው በ1937 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ነው። በድሮን ካሜራዎች ላይ መመሪያ ለማውጣት የተገደደውም በዚህ ኃላፊነቱ ምክንያት መሆኑን ዳይሬክተሩ ጨምረው ተናግረዋል።


የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም የሚባል ውጤት እንዳለው በተደጋጋሚ ጊዜ ከተለያዩ ተቋማት እውቅና ቢሰጠውም አሁንም ችግሮች እንዳሉበት ይነገራል። በተለይ በሰው ሀይል አያያዝ እና በግዥና ንብረት አስተዳደር በኩል ቅሬታ የሚቀርብበት ባለስልጣኑ አሉብኝ ያላቸውን ችግሮችም ዳይሬክተሩ አስቀምጠዋል። በተለይ የአቪየሽን ስራ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመራ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በሲቪል ሰርቪስ ስር መተዳደሩ ሰራተኞች ለስራቸው ተመጣጣኝ ክፍያ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። ይህን ተከትሎም በድርጅቱ ውስጥ ብቃትና ልምድ ያለው የሙያ ሰራተኛ (በናቪጌሽን መስክ) በቂ ደመወዝ ከፍሎ ለመቅጠር መቸገሩን ኮሎኔል ወሰንየለህ ተናግረዋል።


በእቃ ግዥ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በተመለከተ ከመገናኛ ብዙሃን ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በድርጅቱ ሁሉም አሰራሮች ግልጽነትን የሚከተሉ መሆናቸውን ገልጸው አለ የተባለው ችግርም ከጊዜ ወዲህ በድርጅቱ ውስጥ ችግር ፈጣሪ ግለሰቦች ከተነሱ በኋላ መስተካከል እንዳለ ገልጸዋል።


የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ከብሔራዊ አየር መንገዱ በተጨማሪ ለ12 የአየር በረራ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች የብቃት ማረጋገጫ የሰጠ ሲሆን፤ በመላው አገሪቱም ለአራት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች ማረጋገጫ ሰጥቷል።


 

በይርጋ አበበ

 

ከዚህ ቀደም Think and Grow Rich በሚለው መጽሀፉ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው የስነ ልቦና መጽሃፍ አዘጋጁ ናፖሊዮን ሂል ‹‹Outwitting The Devil›› መጽሃፍ በ75 ብር ለኢትዮጵያ ገበያ ቀርቧል። በህይወት እያለ ጽፎት ቤተሰቦቹ ያሳተሙት ይኸው ‹‹Outwitting The Devil›› መጽሃፍ ከዚህ ቀደም በካናዳ ስተርሊንግ አታሚዎች ታትሞ በ15 የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ለንባብ በቅቶ ነበር። የዚህ መጽሃፍ ሙሉው ቅጅ በኢትዮጵያ ታትሞ በ75 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን ክብሩ መጽሃፍት መደብር ደግሞ የመጽሃፉ ዋና አከፋፋይ ነው።
መግቢያውንና ሌሎች መጽሃፉን ገላጭ ጽሁፎችን ጨምሮ 300 ገጾች ያሉትን ‹‹Outwitting The Devil›› በአርትኦትነት የሰራው የ ‹‹Rich Dad and Poor Dad›› መጽሃፍ አዘጋጅ ሻሮን ልችተር ነው። መጽሃፉ ከክብሩ መጽሃፍ መደብር በተጨማሪ በሁሉም መጽሃፍ አዟሪዎች እጅ እና በተመረጡ መጽሃፍት መደብሮች ይገኛል።

 

በጥበቡ በለጠ

 

መጪው የካቲት ወር ነው። በኢትዮጵያ አብዮት ውስጥ ባለታሪክ ወር ነው። ውድ አንባብዎቼ የዛሬ 43 ዓመት እና ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያት በኢትዮጵያ ውስጥ የወጣት፣ የሠራተኛው፣ የገበሬው እና በመጨረሻም ወታደራዊ እንቅስቃሴ መጥቶ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ስርአተ መንግሥት ወደቀ። ኢትዮጵያንም ለሦስት ሺ ዘመናት እየተፈራረቀ ይመራት የነበረው ሰለሞናዊው ሥርወ-መንግሥት ወደቀ። ከዚህ ስርአት መውደቅ ጋር ተያይዞ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋቁመው፣ ከዚያም ወደ ግጭት አምርተው ኢትዮጵያውያን በሚዘገንን መልኩ አለቁ። ይህን የኢትዮጵያዊያንን አሣዛኝ ክስተት፣ ታሪክ ፀሐፊያን እንዴት ገለፁት በሚል ርዕስ ጥቂት ቆይታ እናደርጋለን።
ኢትዮጵያ በ1968 እና 69 ዓ.ም ላይ ታሪኳ በእጅጉ አሣዛኝ ነበር። ብዙ ሺ ወጣቶች በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር ግጭቶች አልቀዋል። በ1960ዎቹ ብቅ ያሉት ባለ አፍሮ ፀጉራም ወጣቶች፣ በማርክስ፣ በኤንግልስ እና በሌሊን አስተምህሮቶችና ፍልስፍናዎች የተራቀቁት የኮሚኒስት እና የሶሻሊዝም ርዕዮት የሚያስተጋቡት እኒያ ወጣቶች በእርስ በርስ ግጭት ሕይወታቸው ረግፏል።


ለመሆኑ የ1967፣ 68፣ 69፣ ዓ.ምረቶች የኢትዮጵያ ወጣቶች እልቂት መንስኤም ምንድን ነው? ለምን ትውልድ እንደ ቅጠል ረገፈ? ዛሬ ላይ ቆመን ወደ ኋላ ስናይ ገዳይም ሟችም በምን ሁኔታ ውስጥ ሆነው መጥፎ ታሪክ ያስመዘገብነው?


እነዚህ ጥያቄዎች ብዙ ፍልስፍናዊ ማብራሪያ እና ትንታኔ የሚጠይቁ ናቸው። ነገር ግን ዋና ዋናዎቹን ከልዩ ልዩ ምሁራን የታሪክ ድርሣን ውስጥ ያገኘኋቸውን ምክንያቶች ላጫውታችሁ።
በ1950ዎቹ ውስጥ ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ወርቃማ ዘመኗ ነበር። ለምሣሌ በዚያን ዘመን የአፍሪካ የእግር ኳስ ዋንጫ አሸናፊ የሆነችበት ነው። ስለዚህ በእግር ኳሱ መንግሥቱ ወርቁን የመሣሰሉ የኳስ ጠቢቦች የመጡበት ወቅት ነው። በማራቶን ሩጫም በባዶ እግሩ ሮጦ አለምን ጉድ ያሰኘ ባለድል አበበ ቢቂላን የመሣሰሉ ዝና ብዙ ሰዎች ከዋክብት ሆነው ብቅ አሉ።


በሙዚቃው አለም፣ በረቂቅ ሙዚቃና ፍልስፍና ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ተአምር ሊያሣይ ጐልቶ የወጣበት፣ የክብር ዘበኛ፣ የምድር ጦር፣ የፖሊስና የሌሎችም የሙዚቃ ቡድኖች ኢትዮጵያ ላይ የገነኑበት፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ እና ሙሐመድ አህመድ በወርቃማ ድምፃቸው ሙዚቃን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ወደ ላይ ከፍ ያደረጉበት ዘመን ነበር።


በስዕል ጥበብ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን የሽልማት ድርጅት ተሸላሚዎቹ እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ የአብስትራክት ስዕል ጠቢቦቹ ገብረክርስቶስ ደስታ እና እስክንድር ቦጋሲያን ፍክትክት ብለው የወጡበት ወርቃማ ዘመን ነበር።


በድርሰት አለም በተለይ በልቦለድ ሥነ-ፅሁፍ ውስጥ እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪው ፍቅር እስከ መቃብር ብቅ ያለበት፣ ታላቁ የሥነ-ፅሁፍ ሰው ክብር አቶ ሀዲስ አለማየሁ የደራሲያን አባት ሆነው የመጡበት ዘመን ነበር።
የትምህርት ተቋማት፣ ከተሞች፣ መንገዶች፣ ሕንፃዎች እየፈኩ የመጡበት፣ እንደ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና እናታቸው ወ/ሮ ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያን ማንነት እና አኩሪ ታሪክ ለአለም በሰፊው ያስተዋወቁበት ወቅት ነው።


ዘመን ሰበር የብዕር ባለቤቶቹ ታላቁ ሰው ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ የለዛና የቁም ነገር ብዕር ባለቤት አብዬ መንግሥቱ ለማ፣ ከብዕሩ ጫፍ ወርቅ የሆነ ታሪክ የሚንፈለፈልለት ብርሐኑ ዘሪሁን፣ እውነት ነው ብሎ ለሚያምነው ጉዳይ ደረቱን የሚሰጠው ሰማዕቱ ደራሲ አቤ ጉበኛን የመሣሠሉ ፀሐፌ-ተውኔቶች፣ ደራሲያንና ባለቅኔዎች ያን ዘመን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የጥበብ ብርሃን ረጩ።


እነዚህና ሌሎችም ጉዳዮች እየጐመሩ ሲመጡ ከኢትዮጵያ አልፎ ባህር ማዶ ያለውን ዕውቀት ሰብስበው እንዲመጡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አያሌ ወጣቶችን ወደ ውጭ ሀገራት ለትምህርት መላክ ጀመሩ።
ወጣቶቹ ሩሲያ፣ ቻይና፣ አውሮፓ፣ አሜሪካ እና ሌሎችም ሀገራት ሄዱ፣ ተማሩ። በወቅቱ ሀገራት በኮሚኒስት፣ በሶሻሊስት እና ከዚያ ባለፈ ደግሞ በካፒታሊስት አስተሣሰቦች የተቃኙ ነበሩ። በተለያዩ ሀገራት የለውጥ አብዮቶች፣ ስር ነቀል ለውጦች ይካሄዱ ነበር፡፣ የማርክስ፣ የኤንግልስ እና የሌኒን ፍልስፍናዎችን ወራሾች በመሆን የኢትዮጵያ ወጣቶች አዲስ መንገድ ጀመሩ።


የሶሻሊስት ንቅናቄዎችን አስተሣሰቦችን በማንበብ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ለየት እያሉ መጡ። በሃይማኖት እና በኢትዮጵያዊ ግብረ ገብ ያደጉ ወጣቶች አዲስ አውሮፓዊ ፍልስፍና ውስጣቸው ሲገባ፣ አብሯቸው የኖረውን ጥንታዊ ማንነታቸውን እያስለቀቃቸው መጣ።


ወጣቶቹ ኢትዮጵያን የሚያዩበት መነፅር መስታወቱም ሆነ ፍሬሙ የተሰራው በውጭ ሀገራት ባገኙት ትምህርትና ፍልስፍና ሆነ።
ያንን ዘመን በመኖርና በማጥናት መፃህፍትን ካሣተሙ ሰዎች መካከል ጳውሎስ ሚልኪያስ አንዱ ናቸው። እርሣቸው ያሣተሙት መፅሃፍ Haile Selassie, Western Education and Political Revolution in Ethiopia የሚሰኝ ነው። ወደ አማርኛ ስናመጣው ኃይለስላሴ፣ የምዕራባውያን ትምህርት እና የፖለቲካ አብዮት በኢትየጵያ የሚሰኝ ነው።


ታዲያ በዚህ መፅሐፍ ውስጥ እምናገኘው ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በተለይ ከባህር ማዶ ያለውን የፖለቲካ ፍልስፍና አምጥተው ኢትዮጵያ እንድትለብሰው፣ እንድትታጠቀው ሙከራ አደረጉ።
አንዱ የሩሲያን የፖለቲካ ፍልስፍና ሊያላብሣት ሲሞክር፣ ሌላው የቻይናን፣ ሌላው የአውሮፓን፣ ሌላው የአሜሪካን፣ ሌላውም እንደዚያ እያለ ሊያላብሳት ሲጥር ኢትዮጵያ መልኳን፣ አምሣያዋን አጣች የሚሉ የዘመኑን ታሪክ የፃፉ ብዕረኞች ይገልፃሉ።


በዘመኑ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ጠፋ የሚሉ ብዕሮች አሉ “መሬት ላራሹ” የሚለው መፈክር እንዳለ ተገልብጦ ከሩሲያ መጣ። Land For Peasant የሚለው የሩሲያ አብዮት አንዱ መቀስቀሻ ወደ ኢትዮጵያም ሲመጣ መሬት ላራሹ በሚል መሬት አንቀጥቅጥ እንቅስቃሴዎችን አመጣ። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደኖረ የሚነገርለት ፓትሪክ ግሊስ የተባለ ታሪክ ፀሐፊ በእንግሊዘኛ ቋንቋ The Dying Lion:- Feudalism and Modernization in Ethiopia የተሰኘ መፅሐፍ አሣትሟል። መፅሃፉን ወደ አማርኛ ስንመልሰው እየሞተ ያለው አንበሣ፣ ፊውዳሊዝም እና ዘመናዊነት በኢትዮጵያ የሚል ርዕስ ይኖረዋል።


በዚህ መፅሃፍ ውስጥ እንደሚጠቀሰው ከሆነ የኢትዮጵያ አብዮት በሁለት ቅራኔዎች የተሞላ ነበር። አንደኛው ከውስጥ ባለ ለረጅም ጊዜ በኖረው የሀገሪቱ ማንነት እና አዲስ በመጣው ዘመናዊ አስተሣሰብ መሀል የሚያስታርቅ ድልድይ ሣይኖር ኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ፈነዳ።


በዚህ የአብዮት ፍንዳታ ወቅት መለዮ ለባሹ ወታደር ወደ ሥልጣን መጣ። አብዮቱ እየተወጠረ የመጣ ስለነበር የመነጋገር፣ የመቻቻል፣ አንዱ የሌላውን ኃሣብ ተቀብሎ የማስተናገድ ባህል አልነበረም። መሐል ላይ የሚያገናኝ የኃሣብ ድልድይ አልተሰራም ነበር። የመገናኛ ድልድይ ባለመኖሩ ተኩስ ተጀመረ።


ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ሰደድ፣ አብዮት ጥበቃ፣ ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር እየተባባለ ኢትዮጵያዊ የተማሪ ወጣት እርስ በርሱ ተላለቀ።
ኤድዋርድ ኪሲ የተሰኙ ታሪክ ፀሐፊ Revolution and Genocide in Ethiopia & Cambodia የተሰኘ መፅሃፍ አሣትመዋል። መፅሐፉ አብዮትና ዘር ማጥፋት በኢትዮጵያ እና በካምቦዲያ ምን ይመስል እንደነበር ብዙ ዋቢዎችን በማንሣት የሚዘክር ነው። ያንን አስፈሪ የእልቂት ዘመን በታሪክ ድርሣን ውስጥ ያስቃኛል።


ታዲያ ብዙ ፀሐፊያን እንደሚገልፁት ኢትዮጵያ ውስጥ በቀይ ሽብር እና በነጭ ሽብር እልቂት እየተመተረ የወደቀው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሀገሬ ኢትዮጵያን እኔ በጣም እወዳታለሁ በሚል የኃሣብ ፍጭት ምክንያት ነው። ይህን የኢትየጵያን ፍቅር በአግባቡ ባለመነጋገር፣ ባለ መቻቻል፣ ባለመከባበር፣ ምክንያት መግለፅና ማሣደግ አልተቻለም። እናም ብዙ ሺ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ አንደ ቅጠል ረገፉ።


በርካታ ፀሐፊያን በመፃህፍቶቻቸው እና በጥናቶቻቸው እንደሚገልፁት ኢትዮጵያ ሰላምን የሚያስከብሩ ተቋማት ስለሌሏት፣ የሰብዓዊ መብት መጠበቂያ ጠንካራ ተቋማትን ባለማቋቋሟ፣ የመነጋገርና የመቻቻል ባህል ባለማዳበሯ፣ የሕግ የበላይነትን የሚያስከብሩት ኃይሎች ስራቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ለተከሰተው የኢትዮጵያዊያን እልቂት እንደ ምክንያት ያስቀምጡታል።
ይቀጥላል

 

በይርጋ አበበ


በአዳማ ከተማ ስብሰባ እያካሄደ ያለው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) የቀድሞውን ርዕሰ ብሔር ደክተር ነጋሶ ጊዳዳን ጥቅማጥቅም እንዲከበር ወሰነ።


ከ1987 እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን ለሰባት ዓመታት በርዕሰ ብሔርነት አገልግለው ራሳቸውን ከፓርቲውና ከኃላፊነት ያገለሉት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከ1997 ዓ.ም በኋላ ከመንግስት የሚደረግላቸው ጥቅማጥቅም እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል። በዚህ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የቀድሞ ፕሬዝዳንትነት በመሆናቸው ሊያገኙት የሚገባቸው በህግ የተፈቀደላቸው ጥቅማጥቅሞች ይሰጠኝ ሲሉ መጠየቅቸው ይታወቃል። መንግስት በበኩሉ፤ ዶክተር ነጋሶ በ1997 ዓ.ም ምርጫ በደንቢ ዶሎ ወረዳ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግላቸው መወዳደራቸውን ገለልተኛ ከመሆን ስለሚያግዳቸው ጥቅማቸውን ማቋረጡን መግለጹ የሚታወስ ነው።


በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ከመገናኛ ብዙሃን ጥያቄ የቀረበላቸው ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ “ቢዘገይም ኦህዴዶች ያደረጉትን አመስግነዋል” ብለዋል። አያይዘውም የጤንነታቸው ሁኔታ ጥሩ አለመሆኑን ተከትሎ በመድሃኒት ራሳቸውን እየጠበቁ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።
የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ጥቅማጥቅም እንዲጠበቅላቸው ያስተላለፈው ውሳኔ አንድ ተሸከርካሪ እና የውጭ አገር የህክምና ወጪያችን መሸፈንን እንደሚያካትት መረጃዎቹ ያሳያሉ። 

Page 3 of 200

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us