You are here:መነሻ ገፅ»arts»news admin - Sendek NewsPaper
news admin

news admin

 

ከዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ)

የተሰጠ መግለጫ

 

አገራችን ኢትዮጵያ በቁጥር ከ80 በላይ የሆኑ ብሔርና ብሔረሰቦች ያሏት አገር መሆንዋ ይታወቃል።

እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች በቁጥራቸው ልክ የሆኑ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮችና ሌሎችም የማንነታቸው መገለጫ እሴቶች አሏቸው።

ሁሉም አንዱ የሌላውን በማክበር፣ እርስ በርስ በመግባባትና በመተሳሰብ ኖረዋል። እየኖሩም ነው።

 

በአስከፊ ሥርዓቶች የሰፈነባቸውን ብሔራዊ ጭቆና ለማስወገድም አብረው ታግለዋል። አሽቀንጥረው የጣሉት ያ ሥርዓት ዳግም እንዳይመጣ፣ ፍጹም የሆነ እኩልነት፣ ሰላምና ፍትህ የሠፈነበት ሥርዓት እንዲገነባ ለማድረግ አሁንም አንድ ላይ ሁነው ባልተቋረጠ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ላይ ናቸው።

 

ይሁን እንጂ፣ አልፎ አልፎ ከአነዚህ በተመሳሳይ የትግል ሰልፍ ላይ ከሚገኙ ሕዝቦች ውስጥ በአንዳንዶቹ ዘንድ ተከስቶ የሚገኝ አንዳንድ አስከፊ ተግባር ሲታይ ያስገርማል። ያሳዝናልም። ወደጎን የሚካሄድ ትግልም አለ እንዴ? ያሰኛል።

 

ህዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም በዝዋይ ውስጥ በዎላይታና በኦሮሞ ብሔረሰቦች መካከል ተፈጠረ በተባለው አለመግባባት ምክንያት የበርካታ የዎላይታ ወገኖቻችን ሕይወት ሊጠፋ ችሏል። በርካቶችም ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል፤ ያልቆሰሉት ተሰብስበው፣ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲባል በአንድ ካምፕ ውስጥ እንዲቆለፍባቸው ተደርጓል። የአንዳንድ ዎላይታ ተወላጆች ቤት ንብረት እንዲቃጠል መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል። በጭራሽ በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል ይፈጠራል ተብሎ የማይታሰብ ድርጊት ሆኖ ተገኝቷል።

 

የፀቡ መነሻም በአንድ የኦሮሞ ተወላጅና በአንድ የዎላይታ ተወላጅ መካከል ከተፈጠረ አለመግባባት ጋር በተያያዘ ሁኔታ እንደሆነ ይገለጻል። በተባለው ዓይነት ሂደት የተፈጠረ አለመግባባት ባለድርሻ በሆነ የኦሮሞ ተወላጅ ላይ ደርሷል የተባለ ከፍተኛ ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ አሳዝኖናል። እናወግዛለንም።

 

ፀቡ የተከሰተው የዎላይታ ሕዝብ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ካለው የጥላቻ ስሜት እንዳልሆነ፣ እንደይደለ፣ የማንም ሕሊና አሳምሮ ይረዳዋል። የዎላይታ ሕዝብ የኦሮሞ ሕዝብን በአገሪቱ ለመልካም ሥርዓት ግንባታ በተመሳሳይ የትግል ሜዳ ላይ የተሠለፈ የትግል አጋሩ አድርጎ ያስባል እንጂ ሌላ እምነት የለውም።

 

በዚህ ዓይነት ሁኔታ በሚታዩ ሕዝቦች መካከል አልፎ አልፎ በቤተሰብ መካከል የሚከሰት ዓይነት ችግር ቢከሰትም፤ መጠኑ የከፋ ከሆነ፣ ለፍርድ አቅርቦ፣ ተመጣጣኝ ቅጣት ማስወሰን፤ መለስተኛ ከሆነም፤ በግልፅና በመለስተኛ እርምጃ ለማቃለል መሞከር ይገባ ነበር። ሳይሆን ቀርቶ ከላይ እስከተጠቀሰ ደረጃ መድረስ አሳዝኖናል።

 

በማኅበራዊም ሆነ፣ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች በተወሰኑ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች አባላት በሆኑ ግለሰቦች መካከል የሚፈጠር አለመግባባት በሁለቱ ሕዝቦች መካከል እንደተፈጠረ ችግር በማስመሰል መንቀሳቀስ የሂደቱን ሁኔታ ግራ ከማጋባት በስተቀር ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። የኦሮሞ ሕዝብም በዎላይታ ሕዝብ ላይ በዚሁ ዓይነት ሂደት ያምፅበታል ተብሎ አይታሰብም።

 

በኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት መካከል ተቀላቅለው የሚገኙ የዎላይታ ብሔረሰብ አባላት፣ ልክ በዎላይታ ውስጥ እንደሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች የሚያደርጉት ዓይነት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ አድርገው የሚጠበቅባቸውን ከመፈፀም ሌላ ጎጂ ነገር እንደማያስቡ፣ አስበውም እንደማያውቁ እየታወቀ፤ የብዙ ዎላይታዎች ሕይወት እንደጠፋና ቀሪዎችም አካባቢውን ለቀው እንደሄዱ ማድረግና የመሳሰሉ ተግባሮች ጨርሶ የማይመጥኑ እርምጃዎች መሆናቸው መታመን አለበት።

 

ሕዝብ እንደ ሕዝብ ሊጠይቅባቸው የሚገቡ ጉዳዮችም ሆኑ፣ ጥፋቶች በሕዝቡ በራሱ የተፈጸሙ ብቻ ሆነው መገኘት አለባቸው። የግለሰቦችን ጥፋት የህዝብ እያስመሰሉ የከፋ ጉዳት በሕዝብ ላይ እንዲደርስ ማድረግ ተገቢ አይደለም።

 

በመሆኑም፡-

1.  በቅንነት በዕለታዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተሰልፈው ሠላማዊ ተግባር በሚፈጽም በዎላይታ ሕዝብ ላይ የደረሰውን አስከፊ ጥቃት አጥብቀን አንቃወማለን።

2.  በተከሰተው ችግርና አለመግባባት ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ለሁለቱም ብሔረሰቦች አባላት የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እንገልጻለን።

3.  በወገኖቻችን ላይ ግድያ የፈጸሙ ግለሰቦች ጉዳይ እየተጣራ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲደረግ አበክረን እንጠይቃለን።

4.  በዎላይታና በኦሮሞ ሕዝቦች መካከል ያለ ለዘመናት የዘለቀ ወንድማዊ አንድነት በዚህና በመሳሰሉ ትርጉመ-ቢስ በሆኑ ደካማ ምክንያቶች እንዳይሸራረፍ ሁለቱም ህዝቦች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እናሳስባለን።

 

ከዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ)

ህዳር 6 ቀን 2010 ዓ.ም

አዲስ አበባ¾

“ሳተናው እና ሌሎች”

Wednesday, 22 November 2017 12:33

 

ደራሲ፤ ደረጀ ትዕዛዙ

አስተያየት - በማዕረጉ በዛብህ

ይህ አሁን እየኖርንበት የሚገኘው ዘመን ለኛ ለኢትዮጵያውያን በብዙ መልኩ ካለፉት ዘመናት የተለየ ነው። ከዘመኑ ጋር ለመጓዝ የምናደርገው ጉዞ እስከ ዛሬ ካየነው ጊዜ ሁሉ ይበልጥ ፈጣንና ለየት ያለ ይመስላል። መቀሌ ወይም አምቦ ዛሬ ጥዋት የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ማታ በቪኦኤ እንሰማዋለን ወይም በኢሳት እናየዋለን ወይም ደግሞ በፌስቡክ እናነበዋለን። መረጃን ከማግኘት አንፃር ደህና ነን። እያደግን ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል። በፖለቲካው፤ በኤኮኖሚውና በማህበራዊ ኑሮ ዕድገት ጉዟችንም እጅግ የፈጠነ ግስጋሴ ባይሆንም መጠነኛ እንቅስቃሴ መኖሩ አይካድም፡፤ ዘመኑ ራሱ አስጋሪ ነው ያሰግራል። የሰው ልጅ ሁሉ ያንዲት ዓለማቀፋዊ ጎጆ ነዋሪ ሆኗል እየተባለ ከሌላው ዓለም ተነጥዬ ወደኋላ ልቅር ቢባልስ መቼ ይቻላል!

የዕድገት መለኪያ ጥራትና ጥልቀት ነው ብለን ካላከረርን/ካላከበድን በስተቀር አንዳንድ ጠቃሚ የዕድገት እንቅስቃሴ በአገራችን መታየታቸውን ጨርሶ መካድ ያስቸግራል። በዝች ጽሁፍ ስለጥቂት የዕድገት እንቅስቃሴዎች ጥቂት ለማለት ያህል ከፍተኛ ትምህርትን (tertial education) እና ስነፅሁፍን እንውሰድ፤

ከፍተኛ ትምህርትን በተመለከተ አነጋጋሪ የሆነውን የጥራትን ጉዳይ ለጊዜው ወደ ጎን ትተን፣ ከመጠን አንጻር መስፋፋትን ስናይ በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ የሚታየው የከፍተኛ ትምህርት ዕድገት የሚደነቅ ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ ከ40 ያላነሱ የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች አሏት ይባላል። እንዲሁም በስነጽሁፍ በኩል የሚታየው የመፃሕፍት ሕትመት ምርት ዕድገት ይሁን ምን በብዛት ይፃፋል፣ ይታተማል፣ ይሰራጫል፣ ይሸጣል።

እነኚህን ቁም ነገሮች እንደመነሻ ያህል አነሳሁ እንጂ የዝች አጭር ጽሁፍ ትኩረት “ሳተናው እና ሌሎች” ስለተባለችው ትንሽ መጽሐፍ ጥቂት ለማውጋት ነው። የመፅሐፍዋ ዋና አርዕስት/ ስም የሆነው ሳተናው የተባለው ወጣት የጋዜጠኝነትን ሙያ የሚወክል ገጸ ባህሪ ነው። ሳተናው የገጽ ባህሪው ዕውነተኛ ስሙ አይደለም። አለቃው ያወጣለትና የሥራ ጓደኞቹም ሳተናው ፈጣኑ፣ ጎበዙ፣ እንደማለት አስበው የተቀበሉት የአድናቆት መጠሪያው ሆነ እንጅ እውነተኛ ስሙ አይደለም። ደራሲው የሳተናውን እውተኛ ስም አልነገረንም። ዝርዝር መረጃን ከመስጠት አንጻር ደራሲው ንፉግ ቢጤ ይመስላል። የአንባቢን ቀልብ በማንጠልጠል ነው አጫጭር ልቦለዶቹን የሚጨርሳቸው።

ለምሳሌ ሳተናው አንድ የቀድሞ ጋዜጠኛ ኋላ ግን በሌላ ሥራ ባለሥልጣን ከሆኑ ሰው ጋር ቃለምልልስ ያካሄዳል። ያንን መረጃ በሬድዮ ለማቅረብ በከፍተኛ ጉጉት ሲጠብቅ መቅረጸ-ድምጹ ንግግሩን ሳይቀርጽ በመቅረቱ ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ ይወድቃል። ቃለ-መጠይቅ ሰጪውን ሲደውልላቸው ወደ ውጭ አገር በመሄድ ዝግጅት ላይ እንዳሉ ገልጸው. . . “ከሳምንት በኋላ እመለሳለሁ፤ ያኔ የዜና ቋንጣ ካልሆነብህ እንጂ ደግሜ” ይሉታል። የሳተናው አጭር ልቦለድ እዚያ ላይ ነው የሚያልቀው። ይህ በጋዜጠኞች ላይ ከሚደርሱ አስቸጋሪ ፈተናዎች አንዱ ነው።

ደራሲው በአጫጭር ልቦለድ ጽሁፎቹ የሚፈጥራቸውን ገጸ ባህሪያትን ሲገልጻቸው ለአንባቢ እንደፎቶግራፍ ጎልተው ነው የሚታዩት። ለምሳሌ የድሮ የትምህርት ጓደኛውንና ኋላ አሜሪካ በዲቪ ሄዶ ወደ ቀድሞ መንደሩ ተመልሶ ሊጠይቀው የመጣውን የቅጽል ስሙ ታታ የተባለውን ጓደኛውን ሲገልጸው በፎቶግራፋዊ ዕይታ የሚያቀርበው ነው የሚመስለው። ካገር ቤት ወጥቶ ትምህርት ቤት ሲገባ የነበረውን ገጽታ እንደሚከተለው ነበር የሳለው፤

“ታታ” ወንዳፍራ ነበር ስሙ፤ አጎቱ ዘመናዊ የቀለም ትምህርት ይቅሰም ብለው ከገጠር ያስመጡት ሰሞን የነበረው ሁኔታ መቸም የሚረሳኝ አይደለም። በሰፊ ቁምጣው ቢል ቢል የሚሉ ሰላላ እግሮቹ የሰንበሌጥ ያህል አቅም ያላቸው አይመስሉም። የመጫሚያ አልባው ተረከዙ ንቃቃት ሳንቲም ይደብቃል የሚባል አይነት ነው። እንቅፋት ሲነድላቸው የኖሩት አውራጣቶቹ ደድረዋል። በጠራራ ፀሐይ እስከ አፍንጫው የሚጀቦንበት ጋቢው ከራሱ ይከብዳል። በግራ ጎኑ ደገፍ የሚልበት በትሩ ለቄንጠኛ አቋቋሙ ተገን ሆናው ሳቅን ይፈጥርበት ነበር።”

ያ ታታ ወንዳፍራ ነው፣ ሕይወቱ በማይታመን መልክ በጣም ተለዋውጦ፣ ከአሜሪካ ድረስ መጥቶ ወደ ቀድሞ ሰፈሩ ድሃ ወዳጆቹን ስለመጠየቁ፣ ስለ አለባበሱ፣ ስለ አነጋገሩ ማማርና እቤት ድረስ ይዟት ስለመጣው አውቶሞቢል ነው ደራሲው ያቀረበው ንጽጽራዊ ገለጻ። ከአንድ የኢትዮጵያ ገጠር ታዳጊ ሰው አሜሪካ ሄዶ አድጎና በልጽጎ እስኪመለስ ያለው ልዩነት የተገለጸበት ቋንቋና ስነጽሁፋዊ ለዛው ወጣቱ ደራሲና ጋዜጠኛ ያለውን ሥነጽሁፋዊ አቅም የሚጠቁም ይመስለኛል።

ሌላ ማሳያ ደግሞ ልጥቀስ። “ጉማጅ ፀጉር” በሚል ርዕስ በጻፉት አጭር ልቦለድ ሦስት የአንድ ቤተሰብ አባሎችን ያቀርባል-ግርማ የከባድ መኪና ሹፌር፣ ከቤቱ አልፎ የጎረቤቶቹን ኑሮ የሚደግፍ ደግ ሰው፣ ባለቤቱ እልፍነሽና ታናሽ እህቷ ታሪኳ ናቸው። የግርማ ባለቤት የሆነችው የእልፍነሽ መልክ እንደነገሩ ሲሆን በተለይ የእህቷ የታሪኳን መልክና ውበት አስደናቂነት ደረጃ እንደሚከተለው ነው የገለጸው።

“ሦስትዮሽ የተጎነጎነው ፀጉሯ በጀርባዋ ቁልቁል ወርዷል። በጠይም ገጿ ላይ ስርጉድ የሚለው የጉንጯ መሀል ባትስቅም ያምርባታል። በደረቷ ግራ ቀኝ ያሞጠሞጡት ጡቶቿ ሴትነቷን አልቆታል። አልባሌ ቀሚስዋም ውበቷን መጋረድ አልተቻለውም።”

እልፍነሽን ሲገልፅ ደግሞ “እልፍነሽ ሁሌም እሷነቷን ከእህቷ ጋር ስታነፃፅር በብዙ እጥፍ ውበቷ ስለሚጣጣልባት ውስጧ ይቆስላል። ቅላቷ መስህብ ሆኖ ግርማን ጣለላት እንጂ፤ ቅርጽ አልባ ውፍረቷ፣ ሰፋፊ አፍንጫዋና ባህሪዋ ማንንም ባላቀረበ ነበር። ከመልክ አንጻር የእናት ሆድ ዥንጉርጉር የሚባለው በአግባቡ ገቢራዊ የሆነው በእርሷ ላይ መሆኑ ያበግናታል፣” ይላል።

አቶ ግርማ የባለቤቱን እህት የታሪኳን የትምህርት ጥረት መከታተልና ማበረታታት፣ ይወዳል። “ከማትሪክ ውጤትሽ አንፃር የኮሌጅ ትምህርትሽ ይከብድሻል ብዬ አልሰጋም። … ግን በርትተሸ ማጥናት ነው። ከ… የሚያስፈልግሽን መጽሐፍቶች ንገሪኝ እገዛልሻለሁ። እሺ፣” ነበር ያላት። አንድ ሌሊት ላይ፣ የታሪኳ ዕድገትና ውበት መጨመርና ትኩረት መሳብ በቤተሰቡ ላይ እጅግ አስደንጋጭና አሳዛኝ ድራማ እንዲፈጠር አደረገ። ይህንን ጉድ በራሱ በደራሲው ቃላት ላውጋችሁ።

እኩለ ሌሊት ላይ ሚስቱን ከተኙበት ካጠገቡ ያጣት ግርማ በሰማው ጩኸት ተደናግጦ “መብራቱን ሲያበራው ባለቤቱ ሦስትዮሽ የተጎነጎነ ሁለት ጉማጅ ዘለላ ፀጉር በግራ እጇ፣ በቀኟ ደግሞ እንደ ተወለወለ የሳንጃ ጫፉ የሚያብለጨልጭ መቀስ ይዛ መሀል ወለሉ ላይ እርቃኗን ቆማለች-እልፍ ነሽ። ድንጋጤ ያደነዘዛት ታሪኳ ግን “ወይኔ አምላኬ” ስትል የሞት ሞቷን ተነፈሰች። እልፍነሽ የከሰል ፍም የመሰሉ አይኖቿ እንደፈጠጡ አልጋቸው ጠርዝ ላይ ስትቀመጥ “ታሪኳ ባዶ የሆነ መሀል አናቷን እየደባበሰች በድንጋጤና በፍርሃት ደንዝዛ እዛው እመኝታዋ ላይ ቁጢጥ አለች።” ሲል ነው ደራሲው “ጉማጅ ፀጉር” የሚለውን በ7 ገጽ ያቀረበውን አጭር ልብወለድ የጨረሰው። ቅልብጭ ያለች ታሪክና ቅልብጭ ብላ የተቋጨች የአጭር ልቦለድ ትረካ፤

ደረጀ ትዕዛዙ ገጣሚም ነው፣ “ፅኑ ፍቅር” በሚለው ግጥሙ በከፊል እንዲህ ይላል፤

“ፍጡራን ተረቱ

ወዥንቢጦችም ጨመቱ

ንፋስ ድንፋቱን አደበ፤

ሰላም በምድረ ገጽ ረበበ

“ጭርርር” አለ ሌሊቱ፣

በትንሳኤ ሞት ሰዓቱ።

ስለ ግላዊ የሕይወት ፍልስፍናው ሲነግረን ደግሞ “የማይታጠፍ ዕውነታ” በሚል ርዕስ እንዲህ ይለናል፤

“ውበት እድሜን ተግኖ ላይኖር

      -ጊዜ ጉዘቱን ላይገታ

ሰማይ ከምድር ላይገጥም

      -ፅልመት ወጋግታን ላይረታ

ትንኝ ዝሆንን ላታክል

      -እግዜር ሰይጣንን ላይፈታ

ዓለም ዘልዓለም ላትኖር

      -ሕይወትም ሞትን ላይረታ

ለምን ነው መጨነቅ? የሚሆነው ሊሆን

      የማይሆነው ላይሆን።”

መልካም ሥራ ሁሉ አልፎ-አልፎ እንከን አያጣውም እንዲሉ “ሳተናው እና ሌሎችም” ከበድ ያለ የሕትመት ችግር ገጥሟታል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለሕትመት ሥራ ዕድገት የሚያደርገው አስተዋፅኦ የሚደነቅ እንደመሆኑ፣ ለስነፅሁፍ ሥራም እድገትና ጥራት የራሱ አበርክቶ ሊኖረው ሲገባ፣ ዛሬ በሀገራችን በሕትመት በሚቀርቡት ሥራዎች ላይ የሚታዩት ስህተቶች እያደግን ሳይሆን ቁልቁል እየወረድን መሆናችንን እያመለከቱ ያሉ ይመስላል። “ሳተናውና ሌሎች”ም ከዚህ የዘመኑ ችግር ያመለጡ አልሆኑም። አንድ መጽሐፍ አታሚ ድርጅት እያተመ ባለው መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩትን ርዕሰ-ጉዳዮች ተሳስቶ ሁለት ጊዜ ካተመ ለኔ አንድ ልረዳው የማልችል ችግር አለ። ጃጃው አታሚዎችና ዲቨሎፐርስ የተባለው የሕትመት ድርጅት ይህንኑ ነው ያደረጉት። “ምን ይወጠኝ” እና “እድናለሁ” በሚሉ ርዕሶች የተጻፉት ሁለት አጫጭር ልቦለዶች እያንዳንዳቸው ሁለት ጊዜ በመታተማቸው የመጽሕፍዋ ገጽ ብዛት ከ112 ወደ 128 ደርሰዋል። አሳታሚውም አታሚዎችም እንዴት ይህንን ትልቅ ስህተት ሊያዩ እንዳልቻሉና መጽሐፉ እንዲሁ እንዲሰራጭ እንዳደረጉ የተሰጠ መግለጫ ወይም የተጠየቀ ይቅርታ የለም። ይህ ተስፋ የሚጣልበትን የደራሲውን ጉዞ አጠያያቂ እንዳያደርገው እሰጋለሁ።

መጽሐፍዋ ጥሩ ተስፋም ትጠቁማለች። ከብዙ አገሮችና ከኛም እንደምንገነዘበው ጋዜጠኞች ከሙያቸው ጎን-ለጎን የስነጽሁፍ ፍቅርም የሚያዛቸውና በሁለቱም ተቀራራቢ ሙያዎች የሚደነቁ ሥራዎች የሰሩ ሰዎች እንዳሉ የታወቀ ነው። የሚኖራቸውን ርዕዮተዓለማዊ አቋም ትተን፣ እንደፋሽስቱ ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ቀንደኛው የደቡብ አፍሪካ ዘረኛ መሪ ቬርውርት፣ እንደ ታዋቂው የምዕራብ አውሮፓ ግዙፍ ሰው፣ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል፣ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃዋህላል ሄህሩ፣ አሜሪካዊው ደራሲ ሄሚንግወይ ያሉት የታወቁ የዓለማችን ሰዎች የተደነቁ ደራስያን ከመሆናቸው በፊት ጋዜጠኞች የነበሩ ናቸው። ባገራችንም ይኸው ዝንባሌ ታይቷል። በደራሲነታቸው የሚደነቁት በዓሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘርይሁን፣ ዘውዴ ረታ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ አሐዱ ሳቡሬ፣ ማሞ ውድነህ፣ ሽፈራው መንገሻ፣ አጥናፍሰገድ ይልማ ከጋዜጠኝነት ወደ ሥነ ጽሁፉ የተሸጋገሩ ናቸው።

ባሁኑ ወቅት ደግሞ ይህ ዝንባሌ ከሚታይባቸው ወጣቶች እኔ እስከማውቀው ድረስ ደረጀ ትዕዛዙ አንዱ ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል። የደራሲ ጳውሎስ ኞኞንና የደጃዝማች ክንፉ ኪዳኔን… የሕይወት ታሪክ በመጻፍ ደረጃ ከላይ የጠቃቀስኳቸውን ጋዜጠኞችና ደራስያን የሙያ ቅርስ ለመቀላቀል እየሰራ ያለ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

     

 

በአብዩ ግርማ (www.abyssinialaw.com)

 

የኮንዶሚኒየም ቤትን (የጋራ ህንፃን) አስመልክቶ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 370/1995 ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስተዳደሩን ቤቶች የማስተላለፍ ኃላፊነትና አፈፃፀሙን ለመወሰን በወጣው አዲስ ነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ቁጥር 19/97 አንቀፅ 14 (2) ላይ የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ የደረሰው ሰው ዕጣው ከደረሰው ቀን አንስቶ እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለሶስተኛ ወገን በሽያጭ ወይም በስጦታ ለማስተላለፍ የማይችል ስለመሆኑ ተመልክቷል።


ባለ ዕጣው እጣ ከደረሠው ቀን ጀምሮ አምስት ዓመታት ሳይሞላ ቤቱን አስመልክቶ በማናቸውም ሁኔታ የባለቤትነት መብቱን ለማስተላለፍ ውል እፈፅማለሁ ቢል የሠነዶች ማረጋገጫ ፅ/ቤት በዚህ ሕግ መሠረት አምስት ዓመት ሳይሞላ ማስተላለፍ እንደማይቻል በመግለፅ ተዋዋዮችን ይመልሳል።


የሠነዶች ማረጋገጫ ፅ/ቤት ሳይሄዱ በመንደር ውል የባለቤትነት መብታቸውን የሚያስተላልፉትም ቢሆኑ የሚያደርጉት ውል በሕግ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑ ሕጉ ከመከልከሉ ባሻገር ይህንኑ በሚያጠናክር መልኩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 13 የሰበር መዝገብ ቁጥር 65140 መጋቢት 10 ቀን 2004 ዓ.ም. አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቶበታል።


ታዲያ ሕጉ በዚህ መልኩ የወጣ እና የሰበር ሰሚ ችሎትም በዚህ መልኩ የወሰነ ቢሆንም በእኔ በኩል ይኼ ሕግ በሕብረተሰቡ ውስጥ እየፈጠረ ካለው ችግርና ከመሠረታዊ የንብረት ባለቤትነት መብቶች አንፃር መሻሻል ይኖርበታል ባይ ነኝ። ይኸውም፡-


ድንጋጌው ከመሠረታዊ የንብረት ባለቤትነት መብቶች ጋር የተጣጣመና የህዝብን ጥቅም ያስከበረ ነውን?


በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግስት አንቀፅ 40 ላይ ዜጎች የግል ንብረት ባለቤት የመሆን መብት እንደተከበረላቸው እንዲሁም ይህ የንብረት መብት ንብረት የመያዝ፣ የመጠቀም እና የሌሎችን ዜጎች መብቶች እስካልተቃረነ ድረስ ንብረትን የመሸጥ፣ የማውረስ ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን እንደሚያካትት ተመልክቷል። በፍትሐብሔር ሕጉም ከቁጥር 1151 ጀምሮ በተመለከቱ ድንጋጌዎች መሠረት ንብረት የማፍራት፣ በራሱ በንብረቱ ወይም ከፍሬው የመጠቀም እና የባለቤትንት መብትን የማስተላለፍ መብት የተጠበቀ ነው። በመሆኑም ዜጎች የኮንዶሚኒየም ቤቶችን እንደ ሌሎች ንብረቶች የማፍራት፣ በራሱ በቤቱ የመጠቀም ወይም አከራይተው ከፍሬው የመጠቀም እንዲሁም የንብረቱን ባለቤትነት በሽያጭ፣ በስጦታ ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብታቸው የተከበረ ነው። ሆኖም ከእነዚህ ሶሰት መሠረታዊ የንብረት መብቶች መካከል ቤቶቹን የማስተላለፍ መብት በአዲስ ነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ቁጥር 19/97 አንቀፅ 14 (2) መሠረት ገደብ ተጥሎበታል። ይኸውም የጋራ ሕንፃው ለባለ እጣው ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አምስት ዓመታት ድረስ ማስተላለፍ አይችልም የሚል ነው።
ይህ ድንጋጌ በአዋጁ ሊካተት እና የኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤትነት የማስተላለፍ መብት ገደብ ሊጣልበት የቻለው በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 40 (1) ላይ የህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል ሕግ እንደሚወጣ በሚያመለክተው መሠረት ነው። በዚሁ መነሻነት በአዋጅ ቁጥር 19/97 አንቀፅ 14 (2) ላይ በእጣ የደረሰን የጋራ መኖሪያ ቤት እጣው ከደረሰ እስከ አምስት ዓመት ድረስ የባለቤትነት መብት ማስተላለፍ አይቻልም የሚለው ድንጋጌ የተካተተው የህዝብ ጥቅም ለማስከበር ነው በሚል ነው።

 

በእርግጥ ድንጋጌው የሕዝብ ጥቅም ያስከብራል?


በአዋጁ መግቢያ ላይ እንደተመለተው የአዋጁ ዓላማ ፍትሐዊ፣ ግልፅ፣ ቀልጣፋና ውጣ ውረድ በሌለው ቀላል በሆነ ሥርዓት፣ የከተማዋን ነዋሪዎች ከፍተኛ የመጠለያ ችግር መቅረፍ፣ የተጠቃሚዎችን የፆታ ተዋፅኦ በሚያረጋግጥና የገቢ አቅምን ባገናዘበ መልኩ ዜጎችን የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻል ነው። ዜጎችም የቤት ባለቤትነታቸው በእጣ ከተረጋገጠላቸውና ከመንግስት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ አጠናቀው ከከፈሉ እንዲሁም ቤቱን ከተረከቡ በኋላ አስገዳጅ በሆነ ሕግ ምክንያት ለአምስት ዓመታት ያህል የቤቱን የባለቤትነት መብት በምንም መልኩ ማስተላለፍ አይቻልም መባሉ ለባለ ዕድለኛውም ሆነ ለሌላው ጠቀሜታው ምኑ ላይ ነው? ዜጎችስ በዕድለኛነታቸውና ገንዘባቸውን ከፍለው ባገኙት የመኖሪያ ቤት ላይ አምስት ዓመት ካልሞላው በስተቀር በሽያጭ፣ በስጦታ ወይም በሌላ መንገድ ማስተላለፍ አትችሉም በሚል ክልከላ መደረጉ እና የግዴታ የቤት ባለቤትነታቸው ለአምስት ዓመታት እንዲቆይ መደረጉ የባለቤትነት መብትን ከማጣበብ በስተቀር ጠቀሜታ አለውን? ዜጎች ባለቤትነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ የሚጠቅማቸው በቤቱ እየኖሩ መጠቀም ወይም እያከራዩ ከፍሬው መጠቀም ወይም ቤቱን ያዋጣኛል በሚሉት ዋጋ ሸጠው ወይም በሌላ መልክ ማስተላለፍ መሆኑን መወሰን ያለባቸው ከመንግስት ይልቅ እራሳቸው ዜጎች መሆን የለባቸውም? የባለቤትነት መብትን ማስተላለፍ ለአምስት ዓመታት ተከልክሎ ከአምስት አመታት በኋላ መፈቀዱ ለባለ ዕጣው እና ለሕዝቡ የሚያመጣው ምን የተለየና መሠረታዊ ጠቀሜታ አለው? የሚሉት ጥያቄዎች ድንጋጌው ለሕዝቡ እያበረከተ ያለውን ጠቀሜታ ከማሳየት ይልቅ የንብረት ባለቤትነትን የማስተላለፍ መብት ያለ ተጨባጭ ምክንያት ገደብ እንደተጣለበት ያሳያል።

 

ድንጋጌው ባለእጣዎች የባለቤትነት መብታቸውን ከማስተላለፍ አግዷቸዋል?


ከአዋጅ ቁጥር 19/97 አንቀፅ 14 (2) በተቃራኒ በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ኮንዶሚኒየሞች (የጋራ ህንፃዎች) ተሠርተው ለባለ እድለኞች ከተላለፉ አምስት ዓመት ያልሞላቸው በርካታ ቤቶች ከባለ እድለኞች ለሌሎች ሠዎች በሽያጭ ተላልፈዋል። የሚተላለፉበትም መንገድ ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታውን ጠብቆ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1723 እና 2878 መሠረት በሠነዶች ማረጋገጫ ፅ/ቤት (በውል አዋዋይ ፊት) በሚደረግ መንግስት በሚያውቀው ውል ሳይሆን ሌሎች ሕጋዊ ሽፋኖችን በመጠቀም በድብቅ ነው።


ይኸውም በተለምዶ በማሕበረሰቡ ውስጥ እንደ ዜጋ እንደምናየው በተግባርም በፍርድ ቤቶች ባሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚታየው ቤቱ ለባለ እጣው ከተላለፈ አምስት ዓመት ያልሞላውን ቤት የቤቱን ካርታና ተያያዥ ሠነዶችና ቤቱን ለገዢ በማስረከብ፤ የቤቱን ሽያጭ ዋጋ እጥፍ ወይም ከዚያ በላይ ሳይቀበሉ ከገዢ እንደተበደሩ የሚገልፅ የብድር ውል በሠነዶች ማረጋገጫ ፅ/ቤት ወይም ከዚያ ውጭ የሚደረግ ውል በመፈረም፤ እንደ ሻጮቹ ታማኝነትም በሕጉ የተቀመጠው የአምስት ዓመት ጊዜ ሲደርስ በሠነዶች ማረጋገጫ ፅ/ቤት የቤት ሽያጭ ውል ተፈፅሞ ሕጋዊነቱ የሚጠበቅበትና በሻጩ እንደተወሰደ ተደርጎ በተፈረመው የብድር ውል መሠረት ብድሩ እንደተመለሰ የሚገልፅ ሰነድ ተፈርሞ ሽያጩ የሚከናወንበት ሁኔታ በሠፊው እየታየ የሚገኝ የሽያጭ ስርዓት ነው። ለባለእጣው ከተላለፉ አምስት ዓመት ያልሞላቸውና በዚህ መልኩ ሽያጫቸው የተከናወኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶችንም ቤቱ ይቁጠራቸው። በመሆኑም ሕብረተሰቡ ወይም ባለእጣዎች ሕጉ አምስት ዓመት ሳይሞላ መሸጥን ቢከለክልም በተለያዩ መንገዶች የባለቤትነት መብት የማስተላለፍ ሂደቱ እየተከናወነ ይገኛል።

 

ድንጋጌው በልማት ተነሺ በሆኑና ምትክ የኮንዶሚኒየም ቤት በተሠጣቸው ላይ ተፈፃሚ ሊሆን ይገባል?


በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 40 (8) መሠረት የግል ንብረት ባለቤትነት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ተመጣጣኝ የሆነ ካሣ በመክፈል የግል ንብረትን ለመውሰድ እንደሚችል በተመለከተው መሠረት በርካታ ቦታዎች ላይ እንደምናየው ለልማት በሚነሱ አካባቢዎች ነዋሪዎች ለሆኑ ሰዎች መንግስት በምትክነት ኮንዶሚኒየም ቤቶች ይሰጣል። የኮንዶሚኒየም ቤቶችንም በእጣ ሳይሆን በልማት ምክንያት በፈረሰባቸው ቤት ምትክነት ያገኙ ዜጎችም ቢሆኑ ልክ ቤቱን በእጣ እንዳገኘ ሠው ቤቱን ካገኙበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለሌላ ሰው እንዳያስተላልፉ ክልከላ ይደረግባቸዋል። ሆኖም አዲስ ነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ቁጥር 19/97 አንቀፅ 14 (2) በግልፅ የኮንዶሚኒየም ቤት እጣ የደረሰው ሰው ዕጣው ከደረሰው ቀን አንስቶ እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለሶስተኛ ወገን በሽያጭ ወይም በስጦታ ለማስተላለፍ የማይችል ስለመሆኑ ተመልክቶ እያለ ከእጣ ውጭ የኮንዶሚኒየም ቤት በምትክነት በተረከቡ ሠዎች ላይም ተፈፃሚ መሆኑ የዜጎችን የንብረት ባለቤትነት የማስተላለፍ መብት በእጅጉ የሚጎዳ ነው።

 

ድንጋጌው በኅብረተሰቡ ውስጥ ምን ችግር እያስከተለ ነው?


ከላይ ከፍ ብሎ እንዳየነው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሽያጭ በድብቅ ሁኔታ ከተከናወነ በኋላ አምስት ዓመቱ ሞልቶ ገዢ ወገን ባለእጣውን (ሻጩን) የቤቱን የባለቤትነት ስም እንዲያዞር በሚጠይቅ ጊዜ የሽያጩ ዋጋ በተሻሻጡበት ጊዜ ከነበረው በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ ያለው በመሆኑ ባለዕጣው የዋጋ ልዩነቱን ከግንዛቤ በማስገባት በብድር ውል የፈረምኩትን የገንዘብ መጠን ከፍዬ ቤቴን እወስዳለሁ በሚል በሚፈጠር አለመግባባት እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ገዢው በብድር ውሉ የተፈረመውን የብድር ገንዘብ ባለዕጣው ይክፈለኝ በሚል በተቃራኒው ደግሞ ባለዕጣው ገዢው ይዞት የሚገኘው ቤት ባለ ንብረት መሆኔን የሚያስረዳ ማስረጃ ስላለኝ ቤቴን ይዞብኛል ይልቀቅልኝ በሚል የሚቀርቡ ክሶችና ክርክር እየተደረገ የሚወሰንባቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው። ድንጋጌው አምስት ሳይሞላ የባለቤትነት መብት ማስተላለፍ አይቻልም በሚል በመከልከሉ ምክንያት በሌላ ሕጋዊ ሽፋን የሚደረጉ የተሸሸጉ የቤት ሽያጭ ውሎች ሻጭና ገዢዎችን ላልተገባ የፍርድ ቤት ክርክርና ወጪ እየዳረገ ይገኛል።

 

መደምደሚያ


በመሆኑም አዲስ ነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ቁጥር 19/97 አንቀፅ 14 (2) የኮንዶሚኒየም ቤት እጣ የደረሰው ሰው ዕጣው ከደረሰው ቀን አንስቶ እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለሦስተኛ ወገን በሽያጭ ወይም በስጦታ ለማስተላለፍ የማይችል መሆኑን በሚገልፅ ሁኔታ መደንገጉ መንግሥት ሊያሳካው ካሰበው መሠረታዊ የፖሊሲ ሃሳብ፣ ከመሠረታዊ የንብረት መብቶች፣ ለሕዝቡ በትክክል እያበረከተ ካለው ጥቅምና ፋይዳ እንዲሁም ድንጋጌው የባለቤትነት መብት ማስተላለፍን አስመልክቶ ጊዜን መሠረት ያደረገ ገደብ ማስቀመጡ ሕብረተሰቡ ላይ እያደረሰ ካለው ችግር አንፃር አዋጁን ያወጣው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በድጋሚ ቢያጤነው ባይ ነኝ።

ዛሬም እየሞከርን ነው!

Wednesday, 22 November 2017 12:17

ሰሞኑን እየሰማናቸው ያለናቸው ነገሮች እነዚህ ሰዎች ሀገር እየመሩ ነው ወይስ በዘመኑ ቋንቋ “ሙድ እየያዙ” ነው? አስብሎናል፡፡ በሀገራችን እየተሰሩ ካሉ ግዙፍ ስራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹን የያዘው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ስራዎቹን አዘግይቷል የሚል ወቀሳ በተደጋጋሚ እየተሰነዘረበት ነው፡፡ እርሱም በአፀፋው አሻጥሮች እየተሰሩበት መሆናቸውን እና የጥላቻ ወሬዎች እየተነዙበት እንደሆነ እየገለፀ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር እነዚህ ሰዎች ኃላፊዎቻቸውን አለመረዳታቸው ነው፡፡ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ተወጥተው ይኸው ሰርተናል ከማለት ይልቅ እገሌ ይሄን አለ፤ እገሌ ይሄን ጻፈብኝ እያሉ ከእነሱ የማይጠበቅ አሉባልታን ማሰማት ጀምረዋል፡፡ እነርሱ እንደ ስራ ፊት የሆነ ያልሆነውን እያነሱ አንዱ ወደ ሌላው እየወረወረ በሚወነጃጀሉበት ወቅት ብዙ ስራዎችን መስራት በቻሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜም የሚሰጡት መልስ እየሞከርን ነው የሚል ብቻ ነው፡፡ የእነሱ የሙከራ ጊዜ ማለቂያ የሌለው በሆነ ቁጥር እኛ ደግሞ የምንከፍለው ዋጋ እየከበደን ነው፡፡ ሌላ ሌላውን ተወት ብናደርገው እንኳን በስኳር እጦት ምክንያት በቅርቡ የነበረው ስቃይ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ይባስ ብሎ ስኳርን ከውጭ ሀገር ለመግዛት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር መመደቡን መንግሥት ገልጿል፡፡ እዚህ ጋር ስራውን አንቀው የተቀመጡት ያሾፉብናል፤ እዚያ ጋር ደግሞ ከፍተኛ ወጪ አውጥተን ልንገዛ እየተዘጋጀን እንገኛለን፡፡ አረ ጎበዝ በዚህ አያያዛችን መጨረሻችን ምን ሊሆን ነው? መስራት የማይችል ከሆነ ወይም ኃላፊነቱን መወጣት ካቃተው አልቻልኩም ብሎ ለሚችል መስጠት ማንን ገደለ? አለመቻልን ማወቅ በራሱ ትልቅ ችሎታ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ከችግርና ከውድቀት ሌላ ወሬ የምንሰማበት ጊዜ እየናፈቀን ነው፡፡ 

 

                           አርአጣ ስጦታው - መገናኛ

 

በይርጋ አበበ

40 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎበት ከመቶ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያንንና ለመላው አፍሪካ የጤና ፕሮግራም ተመልካቾች አዲስ ፎርማት ይዞ ቀርቧል። የጤና ጣቢያው መሠረቱን ዱባይ አድርጎ አዲስ አበባ ደግሞ የሥርጭት አድማሱን መነሻ ተክሏል። ናይል ሳት እና ዩቴል ሳት ደግሞ መገኛዎቹ ሲሆኑ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ደግሞ የፕሮግራሙ ልሳኖች ናቸው። ሚሊዮን ብሮችን ይዞ የአልኮል ማስታወቂያ በመስኮቴ አያልፍም” ሲል አቋሙን የገለፀው አፍሪኸልዝ ቴሌቪዥን ጣቢያ “ዓላማዬ ለህዝብ በጎና ረብ ያለው ነገር አቅርቤ ትርፍ ማግኘት ነው” ሲል በጣቢያው ኃላፊዎች በኩል አስታውቋል። በዚህ የቴሌቭዥን ጣቢያ ምሥረታ እና ቀጣይ ጉዞዎች ዙሪያ ትኩረት ያደረገውን ዘገባ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

ጣቢያው በምሥረታ ዋዜማው

አፍሪኸልዝ ቴሌቭዥን ይዞ የተነሳውን የረጅምና አጭር ጊዜ ግብ ያቀረቡት የቴሌቭዥን ጣቢያው ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰር ዶ/ር ሜሎን በቀለ “ማህበረሰቡ የራሱን ጤና በራሱ መፍጠርና መንከባከብ እንዲችል ትክክለኛ የጤና መረጃዎችና ትምህርቶችን በመቀበል ጤናማ ማህበረሰብ መገንባት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ዶክተር ሜሎን የጣቢያውን መከፈት ይፋ ባደረጉበት መግለጫቸው አክለው ሲናገሩም “በሀገራችን በጤና ላይ ያተኮረ ጋዜጠኝነት እንዲስፋፋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ነው” በማለት አብራርተዋል።

ህብረተሰቡን በጤና መስክ ግንዛቤ እንዲኖረው ከማስቻል እና የጤና ዘጋቢ ጋዜጠኞችን ከማፍራት በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት አሳክቼዋለሁ ያለውን የጤናውን ዘርፍ ስኬቶች ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ተሞክሮ እንዲሆን ማሳየት ጣቢያው አንዱ የተነሳበት ነጥብ መሆኑን በመክፈቻው ማብሰሪያ ወቅት ተገልጿል።

ጣቢያው ህልሙን ለመኖር ወይም ራዕዩን እውን ለማድረግ በሰው ኃይል በኩል ምን ያህል ተደራጅቷል? ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ ቀድሞ ያስቀመጠው ምላሽ “ከ40 የሚበልጡ ሃኪሞችን እና የሚዲያ ባለሙያዎችን ያካተተ ነው። በዚህም የተነሳ በጣቢያው የሚተላለፉ የጤና ፕሮግራሞች ደረጃቸውን የጠበቁ እና በስፔሻሊስት ሀኪሞች ክትትልና ማብራሪያ የሚሰጥባቸው ይሆናሉ” ሲል ይፋ ያደርጋል። ለዚህ ደግሞ ከደረጃ በታች ወይም የሙያ ሥነ-ምግባር ያልተላበሱ ፕሮግራሞች ለህዝብ እንዳይቀርቡ የሚከታተል በጠንካራ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ የሚመራ ኤዲቶሪያል ኮሚቴ ማዋቀሩን የጣቢያው ኃላፊዎች ተናግረዋል። ከፍተኛ የምርምር ሥራ የሚከናወን እንደሆነም ኃላፊዎቹ አክለው ገልፀዋል።

የጣቢያው የገቢ ምንጭ እና የማሥታወቂያ ፖሊሲው

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ማሥታወቂያዎችን ይዘት፣ የጊዜ ርዝማኔ፣ ስለሚተላለፉበት መንገድ እና ተያያዥ ጉዳዮች የሚደነግግ አዋጅ አውጥቷል። በአዋጁ ከተጠቀሱት ህጎች መካከል በኦዲዮ ቪዥዋል ብሮድካስት ጣቢዎያች ለጤና ጎጂ እና አልኮል መጠጦች፣ እንደ ጥሬ ሥጋ የመሳሰሉ ምግቦች አይተዋወቁም ይላል። አፍሪኸልዝ ቴሌቭዥን ደግሞ የጤና “ጣቢያ” እንደመሆኑ መጠን በጣቢያው ሥለሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ይዘት ምን አቋም አለው? የሚል ጥያቄ ለጣቢያው ኃላፊዎች ቀርቦላቸው ነበር።

ኃላፊዎቹ ሲመልሱ እንዲህ አሉ “እርግጠኛ ሆነን የምንናገረው የቱንም ያህል አጓጊ ገንዘብ ቢቀርብልን የቢራ ምርቶች በእኛ ጣቢያ አይተላለፉም” ሲሉ ፈርጠም ብለው ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ እንደምክንያት ተደርጎ የቀረበው “ጣቢያው ህዝቡን ጤናችሁን ጠብቁ” እያለ በሌላ በኩል ደግሞ “ትንሽ ጎንጨት አድርጉ” ብሎ መምከር ሙያዊ ሥነ-ምግባር የተከተለ ባለመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል። የትራፊክ ደህንነት ፕሮግራም የሚዘግብ ፕሮግራም በቢራ ፋብሪካ ስፖንሰር እንደተደረገው አይነት እርስ በእርሱ የሚጣረስ አሰራር በአፍሪኸሊዝ ቲቪ እንደማይስተናገድ ነው የተገለፀው።

ታዲያ ይህ ከሆነ ገቢያችሁ ምን ይሆናል? ተብሎ ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ ጣቢያውን በገንዘብ የሚደግፉ አጋር አካላት እንዳሉት ኃላፊዎቹ ተናግረው፤ ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ የተሻለ የገበያ አማራጭ እና የማሥታወቂያ አሰራር እንደሚከተሉ ገልፀዋል። “በተለይም” ይላሉ የቴሌቭዥን ጣቢያው ኃላፊዎች “በተለይ የወተት ማሥታወቂያዊችን ብንመለከት ‘እንትን ወተት መጣላችሁ ግዙ እና ተጠቀሙ’ አይነት ሥለምርቱ ውስጠ ይዘት የማይገልፅ ማስታወቂያዎችን አስቀርተን ሥለ ወተቱ ይዘት እና ሥለሚያስገኘው ጠቀሜታ ሙያዊ ማስታወቂያ በመሥራት ተመራጭ ሆነን እንመጣለን” ብለዋል። ሌሎች የማሥታወቂያ መንገዶችን ተከትለው የጣቢያውን ገቢ እንደሚያሳድጉም ተናግረዋል።

መልዕክቶቹ እንዴት ይተላለፋሉ?

የህክምና ሙያ እንደሌሎች ሙያዎች ሁሉ የራሱ የሆኑ ሙያዊ ቃላት (professional Jargons) ያሉት ሙያ ነው። እነዚህ ቃላት ደግሞ እንኳን በቴሌቭዥን በሚገልጽበት ፍጥነት ቀርቶ ሀኪሙና ታካሚው ፊት ለፊት ተቀምጠውም ሊግባቡባቸው አይችሉም። በዛ ላይ የአገራችን ህዝብ የትምህርት ደረጃ ሲታሰብ ደግሞ የቃላቱ “ምስጠራ” ይበልጥ ከባድ ይሆናሉ። በዚህ መልኩ ያሉ ችግሮችን ቀርፎ ህብረተሰቡ በሚገባው መልኩ እንዴት ይተላለፋል? የሚል ጥያቄ ለአፍሪኸልዝ ቴሌቪዥን ኃላፊዎች ቀርቦላቸው ነበር። ከጋዜጠኞቹ ለቀረበው ጥያቄ መልስ የሰጡት ኃላፊዎች የተባለው ችግር መኖሩንና እነሱም ለረጅም ጊዜ ያሰቡበት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም “ለተማረውም፣ ላልተማረውም ሆነ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል በሚገባው መጠን እንዲሰማ ተደርጎ ተቀርጿል” ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በቋንቋ ምክንያት ተመልካቹ እንዳይቸገር ከአማርኛው በተጨማሪ በሌሎች አገርኛ ቋንቋዎችም ፕሮግራሞች እንደሚያሰራጭ ተናግረዋል።

የጣቢያው ሌሎች ፕሮግራሞች

አንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ በቀን ለ24 ሰዓት ስርጭት ሲጀምር በተለይም አንድን ሙያ ብቻ ማዕከል አድርጎ ሲጀምር የፕሮግራሞች መደጋገም፣ የሃሳብ መናጠብ እና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች ይፈትኑታል። አፍሪኸልዝ ቴሌቭዥንም ዋና ጭብጡ ጤና ላይ ብቻ አድርጎ በመነሳቱ የሀሳብ መናጠብ ገጥሞት ፕሮግራሞችን እየደጋገመ በማቅረብ ተመልካችን እንዳያሰለች ምን የቀየሰው መንገድ አለ? ለህዝብ መረጃን ለማድረስ የዜና ቡድኑ ምን ያህል ጠንካራ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም።

ለሁለቱም ጥያቄዎች መልስ የሰጡት የጣቢያው ኃላፊዎች “የጤና ነገር ሰፊ ነው። ገና ያልተነካ በመሆኑ የሃሳብ መናጠብ አይገጥመንም” ሲሉ በእርግጠኝነት ተናግረዋል። በተለያዩ የጤና ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ የፕሮፌሽናል ባለሙያዎች ሰፊ ማብራሪያ በአስተማሪነትና በአዝናኝነት መንገድ ተዘጋጅቶ ስለሚቀርብ የሀሳብ እጥረት እንደማይፈጠር በቂ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።

ጣቢያው ሲመሠረት ዋና ሃሳቡ የጤና ፕሮግራሞችን ማስተላለፍ ቢሆንም የዜና ሰዓት ጠብቆ ወቅታዊ መረጃዎችንም እንደሚያስተላልፍ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል። ለመገናኛ ብዙሃን በተበተነው ጋዜጣዊ መግለጫ ወረቀት እንደተመለከትነው “በህክምናው ዓለም የተገኙ አዳዲስ ግኝቶችን፣ ለጤና ጠቃሚ ምክሮችን፣ በሽታን የመከላከል ዘዴዎችንና አደጋን የመከላከል ዘዴዎችን፣ አዝናኝና ቀለል ባለ መልኩ ያቀርባል” ይላል። ከዚህ በተጨማሪም ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መረጃዎች ባይኖሩበትም ሌሎች የመረጃ ዘገባዎች እና የስፖርት ዘገባዎችን ጣቢያው የሚያስተላልፍ መሆኑን ኃላፊዎቹ በአንደበታቸው ገልጸዋል።

ቴሌቭዥን ጣቢያው ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆንና “ረብ” ያለው ሥራ ይዞ ለመቅረብም ከተለያዩ የሙያ ማህበራት፣ ፖሊሲ አውጭዎች እና ሌሎች ማህበራት ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

መደምደሚያ

አፍሪኸልዝ ቴሌቭዥን ጣቢያ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የመጀመሪያው የጤና ጉዳዮች የሚተላለፍበት የቴሌቭዥን ጣቢያ ነው። ይህ ጣቢያ በልዩነት ለመምጣት ለዓመታት ጥናት ላይ መቆየቱን ኃላፊዎቹ የተናገሩ ሲሆን፤ አምስት የዳይሬክተሮች ቦርድ የሚመራው ጣቢያ ነው። ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ እና የፖለቲካ አስተሳሰብ ወገንተኝነት የፀዳሁ ነኝ ሲል የገለፀው አፍሪኸልዝ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኃላፊዎች እንደተናገሩት እና ድርጅቱ እንዳስቀመጠው ራዕይ የሚቀጥል ከሆነ በእውነትም ለአገሪቱ ህዝብ ጥሩ አማራጭ ሆኖ ይቀርባል ሲሉ አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡ ምሁራንና ሌሎች ሰዎች ተናግረዋል። ዋናው ነገር ጤና! ጤና ለሁሉም!!         

ቁጥሮች

Wednesday, 22 November 2017 12:15

በ2010

19 ቢሊዮን ብር                        ወደ ውጭ ከሚላኩ የብርዕ እና አገዳ እህል፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህል፣ ቡና እና አትክልትና ፍራፍሬ ለማግኘት የታቀደው ገቢ፤

 

6 ነጥብ 77 ቢሊዮን ብር             ለአገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ለመሸጥ የታሰበው ምርትና አገልግሎት ዋጋ፤

 

7 ነጥብ 74 ሚሊን ኩንታል          ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ለመግዛት የታሰበው ምርት መጠን፤

 

4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር               ለስንዴ፣  ዘይትና ስኳር የሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ግዢ የተመደበው ዋጋ፤

 

   ምንጭ ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ፣ በኦሮሚያ ክልሎች በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲጠቀሙ የተገኙ ሰዎች ይቅርታ ወይንም፣ ምህረት ተደረገላቸው የሚሉና ቀለል ተደርገው የሚነገሩ ዜናዎች በተለይ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን መስማት የተለመደ ሆኗል። ሰሞኑንም በተመሳሳይ ሁኔታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተቀጠሩና ዕድገት ያገኙ የመዲናዋ ሠራተኞችና አመራሮች እስከ ታህሳስ ወር አጋማሽ ራሳቸውን ካጋለጡ በይቅርታ እንደሚታለፉ የሚገልጽ ቀነ ገደብ አስቀምጧል።

 

አዎ! ችግሩ ሥሩ ሰዶ የትምህርትን አግባብነትን ጥያቄ ውስጥ እስከመጣል ደርሷል። አንድ በወጉ የስምንተኛ ክፍል ያላጠናቀቀ ሰው ገንዘብ ስላለው ብቻ በቀላሉ በውጭ ሀገር ከሚገኙ ከስመ ጥር ዩኒቨርሲዎች ጭምር ዲግሪና ዲፕሎማ እንደሸቀጥ መግዛት የሚችልበት ሕገወጥ አሠራር መኖሩ የሚታወቅ ነው።


በሀገር ውስጥም ሐሰተኛ የትምህርት ሰነዶችን አስመስሎ ከመሥራት በተጨማሪ በግልና በመንግሥት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዳንድ የሥራ መሪዎች አለአግባብ ከመበልጸግ ፍላጎት ጋር ተያይዞ የሠርተፊኬት ሽያጭ ያጧጧፉበት ሁኔታ መኖሩ የአደባባይ ሐቅ ነው። በተለይ በመንግሥት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አስፈላጊው ሰነድ ልክ ትምህርታቸውን እንደተከታተሉ ተደርጎ ተዘጋጅቶላቸው ዲግሪና ዲፕሎማ የሚሰጣቸው ግለሰቦች ለማጋለጥ እንኳን በማያስችል ሁኔታ መደረሱ እንደሀገር ማሳዘኑ አይቀርም።


ለዚህ መነሻ ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም ዋንኛው ግን የሙስናና ብልሹ አሠራር በተለይ በመንግሥታዊ ተቋማት እየተስፋፋ መምጣትና የመንግሥት የቁጥጥርና ክትትል አቅም መዳከም ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። የሙስናና ብልሹ አሠራር የወንጀል ተጠያቂዎችን ደግሞ በአስተዳደር ይቅርታ በመስጠት ወይንም ምህረት ማድረግ ለቀሪው ሕዝብ የሚሰጠው መልዕክት እጅግ አደገኛ ነው። አስፈጻሚው አካል በወንጀል ጉዳይ እጁን አስገብቶ ለፈለገው ይቅርታ ሰጪ ሆኖ የመታየቱ ነገር ከፍትሕ ዓላማ ጋር በእጅጉ የሚቃረንና በዜጎች መካከል አድልኦ የሚፈጥር ነው።


እናም በቅድሚያ የችግሩን ምንጭ ማወቅና ማከምን ማስቀደም ይገባል። እንደሀገር በሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመዋጋት የተያዘው ዘመቻ በአስተማማኝ መልኩ ማሳካት ካልተቻለ የዚህ ብልሽት ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖች ሰዶ በማሳደድ ብቻ የሚመጣ ለውጥ አይኖርም። ይህ ማለት በጥፋት የሚጠረጠሩ ሰዎች ሊጠየቁ አይገባም ማለት ሳይሆን ሥርዓትን ማስተካከል ከእሳት ማጥፋት እርምጃ በዘለለ ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት ይረዳል ለማለት ነው።
ሌላውና ሁለተኛው ነጥብ በወንጀል አድራጎት የሚጠረጠሩ ሰዎችን ጉዳያቸውን በአስተዳደር አይቶ ይቅርታ በማድረግ ማባበልም ወንጀልን ከመዋጋት፣ ጥፋተኞችን ከማረምና ከማስተማር አንጻር ያለው ፋይዳ ሲመዘን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ከፍ ብሎ የሚታይ ነው። እናም የክልል መንግሥታት ጉዳዩን በጥንቃቄ ሊያዩትና እርምጃቸውም ዘላቂ መፍትሔ ከማስገኘት አንጻር ያለውን ፋይዳ ሊመረምሩት ይገባል። 

የ37ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ የሚገኘው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ከትጥቅ ትግሉ ዘመን አንስቶ ባለፉት የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት የህይወትና የጉልበት መስዋዕትነቶች ለከፈሉ ታጋዮቹ ዕውቅና እንደሚሰጥ አስታወቀ።

 

የብአዴን ማዕከላዊ ኮምቴ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው በፕሮግራሙ ከ1983 ዓ.ም በፊት አንስቶ ለታገሉና 8 ሺህ ለሚደርሱ ታጋዮች በህዝባዊነታቸውና በዓላማ ጽናታቸው ገፍተው በመዝለቃቸው የአኩሪ ተጋድሎ ዕውቅና ይሰጣቸዋል።


ብአዴን አያይዞም “ይህ የዕውቅና መድረክ ለነባር ታጋዮች ምስጋናና እውቅና የምንሰጥበት ብቻ ሳይሆን ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ድርጅቱን ተቀላቅለው እየታገሉ የሚገኙና በጠቅላላው አዲሱ ትውልድ ክቡር አላማቸውንና የሚያካሂዱትን ትግል አጠናክረው እንዲቀጥሉ መነሳሳትን እንደሚፈጠር ይታመናል” ብሏል።


ማዕከላዊ ኮምቴው በዚሁ መግለጫው በብአዴን አመራርና አባላት ውስጥ አጋጥሞ የነበረውን የህዝባዊነት አስተሳሰብ መዳከምና በተግባር ውጤታማ ያለመሆን ችግር ተከትሎ በህዝቡ ግፊትና በድርጅቱ ጣምራ ጥረት የጥልቅ ተሀድሶ እየተካሄደ እንደሚገኝ ያስታውሳል። የጥልቅ ተሀድሶ የአንድ ዓመት ንቅናቄያችን የድርጅቱን አመራር ወደ ቀድሞ ህዝባዊ ባህሪው መመለስ የሚያስችሉ የአስተሳሰብ ግልጽነቶችን ማስጨበጡን ጠቅሷል።


የለውጥ ንቅናቄው አመራሩ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህሪውን በህዝቡ ተሳትፎ የበለጠ እያጎለበተ በሚሄድበት ደረጃ ላይ እንዲገኝ አስችሎታል ሲል ጠቅሷል።


የ37 ዓመት ጎልማሳው ብአዴን በሚያስተዳድረው የአማራ ክልል ዕድሜውን የሚመጥን ልማትና እድገት አላስመዘገበም በሚል በተቀናቃኞቹ በተደጋጋሚ ትችት የሚቀርብበት መሆኑ ይታወሳል። 

 

 

በሳምሶን ደሳለኝ

 

የቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. የሳዑዲ ንጉሳዊ አገዛዝ አሥራ አንድ ልዑላን፣ በሥራ ላይ የነበሩ አራት ሚኒስትሮች፣ የቀድሞ ሚኒስትሮች እና ባለሀብቶች “በጸረ-ሙስና ዘመቻ” ሽፋን ጠራርጎ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ለጥያቄ በሚል በቁም እስር ውስጥ ካስቀመጣቸው ሳምንት አልፎታል።


ወጣቱ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን በሳዑዲ ዓረቢያ በፖለቲካ በንግድ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑትን እና በውሃቢዝም አስተምህሮ ከፍተኛ ሊሂቃን የሆኑ መንፈሳዊ ሰዎችን ለቀጣይ የንግስና መንገዱ ላይ እንቅፋት ይሆናሉ ብሎ በመስጋት እየጠረጋቸው ይገኛል። የ32 ዓመቱ አልጋ ወራሽ ልዑል ሰልማን የራሱን የፖለቲካ ምኅዳር ለማጠናከር የወሰደው እርምጃ ምን ያህል ርቀት እንደሚወስደው አሁን ላይ ማንም መገመት አይችልም።


መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሳዑዲ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ወይም የሳዑድ ቤተሰቦች በቁጥር 15ሺ ይደርሳሉ። አብዛኛው የንጉሳዊ ቤተሰቦቹ ሃብት የሚገኘው 2ሺ በሚሆኑ ግለሰቦች እጅ ነው። ከ15ሺዎቹ የሳዑድ ቤተሰቦች 4ሺ ልዑላን ናቸው። የአልጋ ወራሽ ልዑል ሰልማን የጸረ ሙስና ዘመቻ በከፍተኛ ፍጥነት በመጓዝ አጠቃላይ ታሳሪዎቹን ከሳዑዲ ቤተሰቦች የታሰሩትን ጨምሮ 1ሺ 700 አድርሶታል። ከጸረ-ሙስናው ዘመቻ ጋር በተያያዘም የመካከለኛው ምስራቅ ጂዖ-ፖለቲካ በከፍተኛ ፍጥነት እየተለዋወጠ ይገኛል።


የመካከለኛው ምስራቅ ጂዖ-ፖለቲካ በፍጥነት ለመቀያየር ዋና ዋና ምክንያቶችን ከሳዑዲ አንፃር ተይለር ዱርደን ሲዘረዝሩ፤ ያልተጠበቀ እና ከፍተኛ የውስጥ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን የማጥፋት እርምጃ መወሰዱ፣ ትልቅ ውስጣዊ የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ለውጥ መደረጉ፣ ከአሜሪካ በፖለቲካ በፋይናንስ እና በሚሊተሪ ጥገኛ ከመሆን መሸሽ፣ ከቻይና ጋር በጥልቅ ግንኙነት መተሳሰር፣ አስገራሚ በመሆነ መልኩ ከሩሲያ ጋር በኢኮኖሚ እና በሚሊታሪ ግንኙነት መመስረት እና ከእስራኤል ጋር የትብብር እና የወዳጅነት ግንኙነቶች መጠናከር ናቸው።


በተለይ በአሜሪካ ኒክሰን አስተዳደር እና በቀድሞ በሳዑዲ ንጉስ ፋይሰል መካከል ከ41 ዓመታት በፊት በሚስጥራዊ የተደረገውን ስምምነት ብሎምበርግ ወደኋላ መለስ ብሎ ሲገልጸው፣ አሜሪካ ከሳዑዲ ዓረቢያ ነዳጅ ትገዛለች በምላሹ ወታደራዊ እርዳታ እና ወታደራዊ ቁሶች ታቀርባለች፤ ሳዑዲ በበኩሏ ከነዳጅ ሽያጭ የምታገኘውን ቢሊዮን ዶላር ገቢን የአሜሪካን የግምጃ ቤት ሰነድ መግዛት እና ለአሜሪካ ኢኮኖሚ ፈሰስ ታደርጋለች።


በዋሽንግተን የመካከለኛው ምስራቅ የውድሮ ዊልሰን ዓለም ዓቀፍ ማዕከል ተመራማሪ ዴቪድ ኦታዌ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ከ41 ዓመት በፊት የተፈረመውን ሚስጥራዊ ስምምነት አስመልክቶ እንደተናገረው፣ የግምጃ ቤት ሰነድ መግዛት ዋናው ስትራቴጂው የሳዑዲ የነዳጅ ገንዘብ ወደ አሜሪካ በምልሰት አዙሪት ውስጥ በመክተት ከአሜሪካ ገበያ እንዳይወጣ ማድረግ ነው ብሎታል። ከሳዑዲ ዓረቢያ የግምጃ ቤት ግዢ የሚገኘው ገንዘብ ለአሜሪካ ጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ለማምረቻነት የሚቀርብ ነው።


ሌላው የሳዑዲ ውስጣዊ የፖለቲካ ጡዘት የሚጀምረው ንጉስ ሳልማን እ.ኤ.አ. በ2015 ወደ ንግስና ሲመጡ ነው። በተለይ ደግሞ ልዑል አልጋ ወራሽ ሰልማን መሐመድ ቢን መሾማቸውን ተከትሎ ነው። ሰልማን የመጀመሪያው ሥራ አድርጐ የወሰነው በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ መሆን ነው። ይህም ሲባል፤ ሳዑዲ በሱኒ ተጽዕኖ ይመራ የነበረውን መንግስት ስትደግፍ፤ ኢራን በበኩሏ በመንግስት ላይ ጦር መሳሪያ ያነሱትን የሁዚ አማፂያንን ደግፋ ቆመች። በግልጽ ሳዑዲ እና ኢራን የውክልና ጦርነት ውስጥ ገቡ።


እ.ኤ.አ. በ2017 ሳዑዲ ዓረቢያ ኳታርን አሸባሪዎችን በመደገፍ እና ሰይጣናዊ ሥራዎችን በመፈጸም ድርጊት ከሰሰች። ኳታር በበኩሏ ለዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ሳዑዲ ዓረቢያ በኳታር ንጉሳዊ ቤተሰቦች ላይ የሥርዓት ለውጥ ለማድረግ እየሰራች መሆኗን በመጥቀስ ከሰሰች። ከዚህ ጋር በተያያዘ ባልተጠበቀ ፍጥነት እና አጋጣሚ ኢራን ከኳታር መንግስት ጎን በመቆም የሳዑዲን እንቅስቃሴ ለመቀልበስ ተሰለፈች። ይህም በመሆኑ ሳዑዲና ኢራን በአዲስ መልኩ ወደ ውክልና ጦርነት ውስጥ ገቡ።


እንዲሁም በሶሪያ ምድር ለአምስት አመት በተደረገው ጦርነት ኢራን የበሽር አላሳድ መንግስትን ወግና ስትቆም፤ ሳዑዲ አረቢያ በበኩሏ የአል-አሳድን መንግስት ከሚቀናቀኑ ሃይሎች ጋር አበረች። በተያያዘም የሶሪያ ሕጋዊ መንግስት የሆነውን የበሽር አላሳድ መንግስትን ሩሲያ በቀረበላት ጥሪ መሰረት ድጋፍ ማድረጓን ተከትሎ፤ የበሽር አላሳድ መንግስት ከመወድቅ ተረፈ። ሶሪያም እንደመንግስት ከመንግስታዊ ውደቀት ተረፈች። ኢራንም በገባችው የውክልና ጦርነት በሳዑዲ አረቢያ ላይ ድል ተቀዳጀች። ከፍተኛው እገዛ የሩሲያ ቢሆንም።


ሳዑዲ አረቢያ ከላይ በተዘረዘሩት ዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ሁኔታዎች መነሻ ውጥረትና ውድቀት ላይ እየተገኘች፣ ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን በልዑል አልጋ ወራሽ ሰልማን መሐመድ ቢን የተመራው “የጸረ-ሙስና ዘመቻ” በፖለቲካ በንግድ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑትን እና በውሃቢዝም አስተምህሮት ከፍተኛ ሊሂቃን የሆኑ መንፈሳዊ ሰዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ቀድሞ በተፈጠረው ውጥረት ላይ አዲስ ነዳጅ አፈሰሰበት። ከፀረ-ሙስና ዘመቻው አንድ ቀን ቀደም ብሎም በየመን የሚገኙት የሁዚ አማፃያን የባልስቲክ ሚሳኤል ወደ ሳዑዲ ዋና ከተማ ሪያድ አወናጭፈዋል፤ ሆኖም ግን በአሜሪካ እርዳታ ከሽፏል። ሳዑዲ ዓረቢያ በበኩሏ ድርጊቱን ተከትሎ፣ የተተኮሰው ሚሳኤል ኢራን ሰራሽ በመሆኑ ኢራን ጦርነት ከፍታብኛለች ስትል ከሳለች።


 

ከላይ ባስቀመጥናቸው ነጥቦች መነሻ የመካከለኛው ምስራቅ ጂኦ-ፖለቲካን ለመቆጣጠር በሳዑዲ አረቢያ እና በኢራን መካከል እየተደረገ ባለው ትግል፣ በኢራን የበላይነት እየተጓዘ ይመስላል። ምክንያቱም ሳዑዲ አረቢያ በየመን ያዋቀረችው የሱኒ ፖለቲካ ኃይል ጥምረት ከሽፏል፤ ኳታር ባልተጠበቀ መልኩ ወደ ኢራን ሄዳለች፤ ኢራን በኢራቅ ፖለቲካ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆናለች። ሳዑዲ አረቢያ ውስጣዊ የፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ በመግባት ያልተረጋጋ መንግስት ባለቤት ስትሆን፣ ኢራን በምርጫ መንግስት መመስረቷን ቀጥላለች።


በዚህ ሒደት ተስፋ የቆረጡት የሳዑዲ ንጉስ እና አልጋ ወራሽ ዓለምን ባደናገጠ መልኩ የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳድ ሃሪሪን አግተው በሪያድ መያዛቸው በስፋት እየተወራ ነው። በጉዳዩ ላይ ሳዑዲ አረቢያ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሳድ ሃሪሪ ማስተባበያ ከመስጠታቸውም በላይ ውንጀላውን ውድቅ አድርገውታል። በአንፃሩ የሊባኖስ ፓርላማ እና ፕሬዝደንቱ ሳድ ሃሪሪ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። የሂዝቦላ መሪው ሃሰን ነስረላ በበኩላቸው ሳዑዲ ዓረቢያ ሊባኖስ ላይ ጦርነት አውጃለች ሲሉ ከሰዋል።


የጂኦ-ፖለቲካ ውጥረቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው፤ አልጋ ወራሽ ልዑል ቢን ሰልማን የ2030 ዕቅድ አውጥተው ኢኮኖሚውን ማጠናከርና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ በነዳጅ ምርት ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስ፣ ከሶስተኛ አገሮች የሚኖሩ የንግድ ልውውጦች በነዳጅ ምርት ላይ ከሚያተኩሩ ይልቅ በሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት 500 ቢሊዮን ዶላር እያፈላለጉ ይገኛሉ። አንዱ ማስፈጸሚያ መንገዳቸው አድርገው የወሰዱት ለእስር ከዳረጓቸው ሰዎች 800 ቢሊዮን ዶለር የሚገመት ሃብት እንዳይንቀሳቀስ እገዳ መጣል ነው። በነዳጅ ምርት ላይ ተሰማርተው ቱጃር ለሆኑት ባለሀብቶች የአልጋ ወራሹ እቅድ ተቀባይነት ባለማግኘቱ በአፀፋው ለእስር መዳረጋቸው ይነገራል።


ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ መፍቀድን ጨምሮ በተለይ ለምዕራቡ ዓለም የቀረቡ አስተምህሮቶችን ወደ ሳዑዲ በመሳብ (Modern Muslim)፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት የሚተጉት ንጉሡና አልጋ ወራሹ እየተሞካሹ፣ እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ ዘመናዊነትንና አዲስ ዓይነት ምልከታ የማምጣቱ አካሄዳቸው በወጣቱ ክፍል ድጋፍ አግኝተዋል። ይሁንታን ያስገኘላቸው ቢሆንም፣ በአንፃሩ ግን በወግ አጥባቂዎቹና ለዓመታት ንግዳቸውን እየተቀባበሉ በቆዩት የሳዑድ ቤተሰቦች ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት ለማግኘት ተቸግረዋል።


የብሔራዊ ዘቡንና የባህር ኃይሉን አዛዥ ቀይረዋል። ይህም ከንጉሡ ጀርባ የልዑል አልጋ ወራሹ ጡንቻ አለ አስብሏል። በሳዑዲ የአሲር ግዛት ምክትል ገዢ ልዑል መንሱር ቢን ሙክሪን ከብዙ ባለሥልጣናት ጋር የቅኝት ሥራ ጨርሰው ወደ ሳዑዲ በመመለስ ላይ እያሉ ሔሊኮፕተራቸው በሳዑዲና በየመን ድንበር ተከስክሶ መሞታቸው የሚታወስ ነው። ሔሊኮፕተሩ የተከሰከሰበት ምክንያት አልታወቀም። ከመሬት በተተኮሰ ሚሳኤል መመታቱን የሚገልፁ ሪፖርቶች ወጥተዋል። ይህም አልጋ ወራሹ ሥልጣኑን ለማራዘም የሚያደርገው ጥረት አንድ አካል ተደርጎ ተጠርጥሯል።


በተጨማሪም በሳዑዲው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን የሚመራው የፀረ ሙስና ኮሚቴ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው መካከል ቢልየነሩ ልዑል አልዋሊድ ቢን ታላል፣ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር ኢብራሒም አል አሳፍ፣ የሳዑዲ ባህር ኃይል ኮማንደር አብዱላህ አል ሱልጣን፣ የኤምቢሲ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ባለቤት አልዋሊድ አል ኢብራሒም፣ ባለሀብቱ ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ፣ እንዲሁም የሳዑዲ ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን የቀድሞ ገዥ አሚር አል ዳባጋ፣ ቢሊየነሩ ልዑል አዋሊድ ቢን ታላል፣ የብሔራዊ ዘብ ሚኒስትሩ ልዑል ሚተብ ቢን አብዱላህ፣ የኢኮኖሚና ፕላኒንግ ሚኒስትሩ ልዑል አደል ፋኪ፣ የኦሳማ ቢን ላደን ወንድምና የቢን ላደን ግሩፕ ሊቀመንበር ባክር ቢን ላደን በሪያድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ሪትዝ ካርልተን በእስር ላይ ይገኛሉ።

 

ቻይና አዲሷ አስፈላጊ ሀገር


በማርች 2012 የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ሳዑዲን ይጎበኛሉ ተብለው ቢጠበቁም ሳይጎበኙ ቀርተዋል። ይህንን ተከትሎ ከ41 ዓመት በፊት በአሜሪካ እና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል የነበረውን ሚስጥራዊ ግንኙነት በሚጥስ መልኩ ንጉስ ሰልማን በማርች 16 ቀን 2017 ከፍተኛ ቁጥር ያለው ልዑካን በመምረት ወደ ቤጂንግ ተጉዘው ጉብኝት አድርገዋል። ከቻይና መንግስት ጋርም የ60 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የንግድ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል። በስምምነት ሰነዱ ከታቀፉት መካከል የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ኩባንያ “Aramco” እና “China North Industries Group Corp (Norinco)” ይገኙበታል። እንዲሁም ይህ ስምምነት ሳዑዲ ኢኮኖሚዋን ከአሜሪካ ጥገኝነት ለማላቀቅ የተደረገ ተደርጎ ተወስዷል።


ንጉስ ሰልማን በቻይና ቆይታቸው፣ ቻይና በመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ብዙ ሚና መጫወት እንደምትችል በማንሳት ተሳታፊ እንድትሆን ጋብዘዋል። በዚህም ሳያበቁ እ.ኤ.አ. በኦገስት 2017 አዲስ የ70 ቢሊዮን ዶላር በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በኃይል አቅርቦት፣ በፖስታ አገልግሎት በኮሚኒኬሽን እና በሚዲያ ዙሪያ አብረው ለመስራት ስምምነት ፈጽመዋል።


ንጉስ ሰልማን ሩሲያን በጎበኙ ጊዜ ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር የጦር መሳሪያ ግዢ እና በሃይል አቅርቦት ዙሪያ ከመፈራረማቸውም በላይ S-400 የተባለ ዘመናዊ የአየር መቃወሚያ መሣሪያ ገዝተዋል።


ሳዑዲ አረቢያ በመካከለኛው ምስራቅ የኢራንን ተፅዕኖ ለመቋቋም እየሰራች ሲሆን፤ በሌላ መልኩ ለ41 ዓመት ከአሜሪካ ጋር የነበራትን ሚስጥራዊ ግንኙነት በቻይናና በሩሲያ ለመተካት እየተጋች ነው። በአካባቢው እና በዓለም አቀፉ የጂኦ-ፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ የገባችው ሳዑዲ አረቢያ ቀጣይ ጉዞዋ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ ሆኗል። 

 

በይርጋ አበበ

 

ያለፉትን 26 ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ በደንብ ላጤነ ሰው የሚያገኘው እውነታ መልኩ ጉራማይሌ አካሄዱ የሰካራም እርምጃ የሚሉት አይነት ነው። በተለይ በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉት ኃይሎች አንድ እርምጃ ወደ ፊት ተራመዱ ሲባል ሁለት እርምጃ ወደኋላ እየተመለሱ፤ ሄዱ ሲባል ሲመለሱ፣ ቆሙ ሲባል እየወደቁ እዚህ ደርሰዋል። ህዝቡም ከገዥው ፓርቲ ውጭ ያሉ አማራጭ ሃሳቦችን ለማግኘት የተቃዋሚዎችን ጓሮ ሲመለከት የአንዳንዶቹ በራሳቸው በፓርቲዎቹ አባላትና አመራሮች እሾህና አሜኬላ ተዘርቶበት በቅሎ ጓሮውን ወሮታል። የተወሰኑት ደግሞ ከፓርቲው ውጭ በሆኑ ኃይላት (እንደ ፓርቲዎቹ እምነት የመንግሥት ሥውር እጆች) በዘሯቸው አራሙቻዎች ተውጠዋል። በዚህ የተነሳም የተቃውሞውን ጎራ የፖለቲካ አካሄድ ሕዝቡ በሙሉ ልቡ ሊቀበለው አልቻለም። በመሆኑም ተደጋግሞ እንደተባለው “ወይ ተባበሩ አለዚያ ተሰባበሩ” ሲል አቋሙን በግልፅ ሲያሰማ ቆይቷል።


ወዲህ ደግሞ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “እንዳለመታደል ሆኖ ጠንካራ ተቃዋሚ የለንም” ብለው መናገራቸው ይታወሳል። የፖለቲካ ልሂቃኑ ግን “ኢህአዴግም ሆነ አቶ መለስ ሞጋች ሃሳቦችን ተቀብሎ ማስተናገድ አይችሉም። ለዚህ ደግሞ አመላካቹ በ1997 ከቅንጅትና ከኅብረት የገጠማቸውን ፈተና መቋቋም ሲሳናቸው ታይተዋል” ሲሉ የአቶ መለስን ሃሳብ ውድቅ ሲያደርጉት ተስተውሏል።


የዚህ ሃሳብ አራማጆች አስተያየታቸውን ሲያጠናክሩም ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በ2002 እና 2007 የተካሄዱ ሁለት አገር አቀፍ ምርጫዎችን ጠራርጎ ማሸነፉን ያስታወሱና በተለይም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አብዛኛው ክፍል ለተነሳው ግጭት አንዱ እና ዋናው ምክንያት የሁለቱ ምርጫዎች ውጤት ነው ሲሉ ይናገራሉ። የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ተሾመ እና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ይህን ሃሳብ ከሚያራምዱ ፖለቲከኞች መካከል ይመደባሉ።


አቶ ሙላቱም ሆነ አቶ የሽዋስ ገዥውን ፓርቲ በሚተች ንግግራቸው “ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳይጠናከሩ መንግሥት ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል” ይላሉ። ከ2001 እስከ 2006 ዓ.ም ባሉት አምስት ዓመታት ጠንካራ ተቃዋሚ ሆኖ የነበረው አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በአንድ ጀምበር ክፍልፍሉ ወጥቶ የቀድሞ አመራሮቹ ፓርቲውን ለቀው ወጡ። በፓርቲው አመራሮች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት የዳኘው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የባለቤትነት ተገቢነቱን በእነ አቶ ትዕግሥቱ አወሉ በመተካቱ እነ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፍራውን፣ እነ አቶ ተክሌ በቀለን ጨምሮ ከ250 በላይ የፓርቲው አመራሮች (ከወረዳ እስከ ፌዴራል ባሉ መዋቅሮች) ፓርቲውን ለቀው ወጡ። እነዚያ አመራሮች ሰሞኑን ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር በአባልነት ታቅፈው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መሳተፍ እንደሚፈልጉ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ይህን ተከትሎም የሰሞኑ አብይ የፖለቲካ ዜና ለመሆን በቅተዋል።


የቀድሞ የአንድነት አመራሮች በሰማያዊ ፓርቲ አባልነት ታቅፈው ለመታገል ምን አነሳሳቸው? የሰማያዊ ፓርቲ ምላሽስ ምን ይመስላል? እንዲሁም ቀጣይ የፓርቲው ጉዞስ ምን መልክ ይኖረዋል? የሚሉትን ሃሳቦች እያነሳን ከዚህ በታች እንመለከታቸዋለን።

 

ጉዞ ወደ ዳግም ፓርቲ ምሥረታ እና የከሸፈ ጥረት


በ2002 ዓ.ም በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ፓርላማ መግባት የቻሉት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባሉ አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ ከቀድሞ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት የሥልክ ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር። አቶ ግርማ ስለ አዲሱ ፓርቲ ምሥረታ ጅማሮ ከተናገሩ ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ይመሠረታል የተባለው ፓርቲ ቀርቶ አመራሮቹ (ከወረዳ እሥከ ፌዴራል ያለው የቀድሞ አንድነት አመራር) ከሌላ ፓርቲ ጋር በአባልነት ታቅፈው መታገልን እንደ አማራጭነት ወሰዱ።


ይህ ለምን ሆነ? ብለን የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የቀድሞውን ተጠባባቂ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ተክሌ በቀለን ጠይቀናቸው ነበር። አቶ ተክሌ ሲመልሱም፤ “አንድነት ፓርቲ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሰፊ ተቀባይነት ያለው መሆኑ ይታወቃል። ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ካዳከመው በኋላ እንደገና በሌላ ፓርቲ ተመልሰን በመንቀሳቀስ ከአራት ክልሎች ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጋ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ችለን ነበር። የተለያዩ አክቲቪስቶችንም በፓርቲው ምሥረታ ሂደት እንዲቀላቀሉን ጥያቄ አቅርበንላቸው ተወያይተናል። ነገር ግን የአብዛኛው ሰው አስተያየት አዲስ ፓርቲ ከመመስረት ይልቅ ያሉትን አጠናክሮ መሄድና የተለመደውን አሰራር ትቶ እውነተኛ ፓርቲዎችንና በርዕዮተ ዓለም የሚመሳሰለንን መቀላቀል ይሻላል የሚል ስምምነት ተደረሰ። በዚህ ምክንያት አዲስ ፓርቲ የመመስረት እቅዳችንን ትተን ወደዚህ ሃሳብ ልንመጣ ችለናል” ሲሉ ተናግረዋል።


የቀድሞዎቹ የአንድነት አመራሮች አዲስ ፓርቲ ለመመስረት የአምስት ክልል ድጋፍ የግድ ያስፈልጋቸው ነበር። ከአራት ክልል ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጋ ድጋፍ ያገኙት እነ አቶ ተክሌ የአምስተኛውን ክልል ድጋፍ ለማግኘት ዝግጅት አድርገው ነበር። ፊርማም ማሰባሰብ ጀምረው እንደነበር ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። ሆኖም ይላሉ አቶ ተክሌ፤ “ሆኖም በአገር ውስጥና ውጭ አገር ባለን መዋቅር ባደረግናቸው ውይይቶች የተሳታፊዎች፣ የምሁራንና የደጋፊዎቻችን ፍላጎት አዲስ ፓርቲ ከመመስረት ይልቅ ያሉትን ማጠናከር እንደሚሻል ስለነገሩን የአዲሱን ፓርቲ ምሥረታ ወደጎን ልንለው ችለናል” ብለዋል።


51 የቀድሞው አንድነት አመራሮችም ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ለመግባት ውሳኔ ላይ የደረሱት በዚህ መልኩ ነው ማለት ነው።

 

ሰማያዊን ለመቀላቀል የተደረገ ቅድመ ዝግጅት


አቶ ተክሌ በቀለ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት የቀድሞዎቹ አመራሮች ከዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ሁለት ዓመታትን የፈጀ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱም ሌሎች አማራጭ ፓርቲዎችን ሳይቀር ተቀላቅሎ ለመሥራት ፍላጎትና ጥረት ተደርጎ ነበር። በተለይ ለዚህኛው አማራጭ ተቀዳሚ ምርጫ ሆኖ የቀረበው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ነበር። ሆኖም መድረክ አባል ፓርቲዎቹ ክልላዊ ስለሆኑ በዘውግ ፖለቲካ መሳተፍ አግባብ አለመሆኑን ተወያይተው ሃሳባቸውን ሊቀይሩ ችለዋል።


ከዚህ ሌላ አማራጭ ሃሳብ ሆኖ የቀረበው መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ወይም ሰማያዊ ፓርቲ ጋር አብሮ መሥራት የሚለው ሆነ።


የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው ይህን ውሳኔ የሰማያዊ ፓርቲ ፍላጎትም እንደነበረ ተናግረዋል። አቶ አበበ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ “አቶ የሽዋስ የፓርቲውን አመራር ቦታ ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ ዋና ትኩረት አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው አንደ እነሱ ያሉ (የአንድነት የቀድሞ አመራሮችን) የፖለቲካ እውቀትና የትግል ልምድ ያላቸው ፓርቲውን ተቀላቅሎ የፖለቲካ ምህዳሩን ስለሚሰፋበት መንገድ መምከር ነበር። በመሆኑም በግልና በተናጠል ከማነጋገር ጀምሮ ‘ለቀድሞ የአንድነት አመራሮች’ በሚል የደብዳቤ መጥሪያ አዘጋጅተን እስከመጥራት ደርሰን ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።


አቶ ተክሌ በቀለ ደግሞ፤ “እኛ በተናጠልም ሆነ በቡድን ሰፊ ውይይት አድርገናል። ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ የእኛ አመራር አባላት በራሳቸው ወጭ አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ተወያይተናል፤ ከዚያ በኋላ ነው ወደ ውሳኔ የገባነው” በማለት ሰፊ ጊዜ ወስደው እንደተወያዩ ተናግረዋል።

የሰማያዊ ፓርቲ ቀጣይ ጉዞ

 


በአቶ ይልቃል ጌትነት ይመራ የበረው የሰማያዊ ፓርቲ ካቢኔ በፓርቲው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ከተሰናበተ በኋላ አዲስ ሥራ አስፈፃሚ መርጦ ወደ ሥራ ከገባ አንድ ዓመት አልፎታል። የአቶ የሽዋስ አሰፋ ካቢኔ ወደ ሥራ መግባቱን ባሳወቀበት የመጀመሪያ ሳምንት ሊቀመንበሩ አቶ የሽዋስ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አካሂደው ነበር። በወቅቱ በሰጡት ቃለምልልስም “ሰማያዊ ፓርቲ በቀጣዮቹ የትግል ጉዞዎች የሚያካሂደው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር እስከ ውህደት ተጉዞ ጠንካራ የአማራጭ ኃይል ሆኖ መቅረብ ነው” ብለው ነበር።


በዚህ መሠረትም በወጣቶች የተዋቀረው ሰማያዊ ፓርቲ እና በልምድም በዕድሜም ከገፉት የመኢአድ መሪዎች ጋር በመነጋገር ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ስለሚሰሩባቸው ጉዳዮች ተስማምተው አብረው መሥራት ከጀመሩ አንድ ዓመት ሊሆናቸው ነው።


የሁለቱ ፓርቲዎች አብሮ የመሥራት ሂደት በተግባር የታየበትን አብይ ተግባርም እያከናወኑ ነው። የሰማያዊ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ እና የመኢአዱ ሊቀመንበር ዶ/ር በዛብህ ደምሴ በሰሜን አሜሪካ ጉዞ አድርገው ከደጋፊዎቻቸው ጋር መገናኘት ችለዋል። በዚህ ጉዟቸው ከሁለቱ ፓርቲ ደጋፊዎችና የፖለቲካ ተሳትፎ ከሚያደርጉ ምሁራን መቼ ነው ተጠናክራችሁ የምትቀርቡት? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።


አቶ የሽዋስም ሆኑ ዶ/ር በዛብህ ሲመልሱ “መኢአድና ሰማያዊ ለውህደት የሚያደርጉት ጉዞ እየተጠና ነው” ብለው ነበር። ይህን አባባል የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉም ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ አረጋግጠዋል።


ሆኖም የቀድሞ አንድነት አመራሮች ወደ ሰማያዊ ሲመጡ በመኢአድ በኩል ምን አይነት ስሜት አሳደረ? ውህደቱን በተመለከተስ ምን አንድምታ አለው? ብለን ለአቶ አበበ እና አቶ ተክሌ ጠይቀናቸዋል። ሁለቱ ፖለቲከኞች ሲመልሱም “መኢአድና አንድነት ለመዋሃድ ሙከራ አድርገው ያልተሳካው በውጫዊ ተፅዕኖ ምክንያት ነው። አሁን ደግሞ ያ አጋጣሚ ሲፈጠር መኢአድ በደስታ የተቀበለው ጉዳይ ነው። እኛም (ሰማያዊ ፓርቲም ሆነ ወደ ሰማያዊ የገቡት የቀድሞ አንድነት አመራሮች) አጥብቀን የምንፈልገው ነበር” ብለዋል።


ሁለቱ አመራሮች አክለውም፤ መኢአድና ሰማያዊ ወደ ውህደት ሄደው የሚፈጠረው ፓርቲ ጠንካራ ሆኖ ሰፊ የሕዝብ ተቀባይነት ይኖረውና ገዥውን ፓርቲ መገዳደር የሚችል እንደሚሆን እምነታቸውን ተናግረዋል።


በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተቃዋሚው ጎራ ከሚታማባቸው ዘርፈ ብዙ ድክመቶቻቸው አንዱ የሥልጣን ጥመኝነት ነው። በተለይ አንዳንዶቹማ መሪዎቻቸው ለረጅም ጊዜ በመሪነት ስለቆዩ ፓርቲውን ከግለሰቦቹ ለይቶ ማየት እስከሚቸግር ድረስ ተዋህደዋል። የአንድነት የቀድሞ አመራሮች ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ሲገቡ የሥልጣን ጉዳይ እንዴት ይታያል? ስንል መጠየቃችን አልቀረም። አቶ ተክሌ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፤ “እኛ ወደ ሰማያዊ የገባነው ‘በተራ አባልነት’ ፓርቲውን ለማገልገል እንጂ ወደ አመራርነት ካልመጣን ብለን አይደለም” ሲሉ ሥልጣን ሳይሆን ሥራን እንዳስቀደሙ ተናግረዋል።


አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው “የሰማያዊ ፓርቲ ሥራ አመራርነት ቦታ የሚሰጠው በእውቀትና በችሎታ በ(Merit) ነው። በመሆኑም የተሻለ ሰው ከመጣ ወደ አመራርነት አሳድጎ እንዲሰራ ለማድረግ የማይቸገር ሥራ አስፈፃሚ ነው ያለን። በመሆኑም ከቀድሞ የአንድነት አመራሮች መካከልም ወደ ሥራ አስፈፃሚነት ሊመጡ የሚችሉ ይኖራሉ” ብለዋል።


ሰማያዊ ፓርቲ እና የቀድሞ አንድነት አመራሮች በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ተከትሎ አብሮነታቸው የውሃ እና ዘይት ጥምረት ወይስ የሥጋና የደም? የሚለውን ለማየት ጊዜው ገና ቢሆንም ሂደቱ እና እቅዱ ምን መልክ እንዳለው ጠይቀናቸው ነበር።


የአቶ አበበ አካሉም ሆነ የአቶ ተክሌ በቀለ ምላሽ፤ በአመራሮቹ መካከል ሰፊ እና ጥንቃቄ የታከለበት ውይይት መካሄዱን፣ በእውቀትና በአገራዊ ስሜት የተሞላ ኃላፊነትን ለመወጣት ቁርጠኝነት ያለበትና የሕዝብ አደራ ሳይቀር የተቀበሉበት እንደሆነ የሚያመለክት ነው። ከዚህ በመነሳትም ጠንካራ አንድነት በመፍጠር የአገሪቱን የዴሞክራሲ ምህዳር በማስፋት ለሕዝብ ጥያቄ ጥሩ አማራጭ ሆነን እንቀርባለን ብለዋል።

 

Page 4 of 186

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us