You are here:መነሻ ገፅ»arts»news admin - Sendek NewsPaper
news admin

news admin

 

በይርጋ አበበ

 

እድገት በተስፋ የነጋዴዎች አክሲዮን ማህበር (ኢቢኤም) ይባላል። በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጃክሮስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ ሲሆን በ3ሺህ 739 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የንግድ ማዕከል ነው። አክሲዮን ማህበሩ የተቋቋመው ከ20 ዓመት በፊት ከመርካቶ የልማት ተነሽዎች ያቋቋሙት ሲሆን በ146 መስራች ማህበራት 50 ሺህ ብር የተከፈለ ካፒታል እንደጀመሩት ከማህበሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከ80 በላይ የንግድ ሱቆችን ይዘው የገበያ ማዕከል በየዓመቱ የትርፍ ህዳጉ እየጨመረ ሄዶ በአሁኑ ሰዓት ተቀማጭ ንብረትን (ፊክሲድ አሴትን) ጨምሮ በድምሩ የ80 ሚሊዮን ብር ጌታ ሆኗል።

 

20 ዓመት ሙሉ በስራ ላይ የቆየው ማህበር ከአንድም ሁለት ሶስቴ የመፍረስና የመዳከም ስጋት ተጋፍጦ ማለፉን የሚገልጹት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ወርቅነህ፤ ‹‹ጉዳዩ ፍርድ ቤት ድረስ እስከሚዘልቅ ድረስ ማህበሩ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። ነገር ግን በሽማግሌ አስታራቂነት ችግሩ ሊፈታ ችሏል›› ብለዋል። ችግሩ ከተቀረፈ በኋላም በአራት ተርሞች (አራት ፌዝ) ግንባታው የተካሄደ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥም በአገሪቱ የሚገኙ አንደኛ ደረጃ የሴራሚክስና የኮንስትራክሽን ግብአት አቅራቢዎችን ጨምሮ ሲኒማ ቤት፣ ጅምናዚየም እና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ የንግድ ተቋማትን አከራይቶ ገቢውን እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።

 

ከመስከረም 2 ቀን 1990 ዓ.ም ጀምሮ የተመሰረተው ኢቢኤም የገበያ ማዕከል ውጤታማ ለመሆኑ ምክንያቱን ፕሬዝዳንቱ ሲናገሩ ‹‹አምራችና ሻጭን ከገዥ ጋር ለማገናኘት የተቋቋመበት ቦታ (ጃክሮስ) ተጠቃሚ አድርጎታል›› ያሉ ሲሆን፤ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ከ20 ዓመት በፊት አክሲዮን ማህበሩ ከመርካቶ የልማት ተነሽዎች ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚመለከተው ክፍል ጥያቄ ሲያቀርቡ መንግስታዊው ተቋም የሰጠው ራዕይ የተላበሰ ውሳኔ እንደሆነ ገልጸዋል።

 

የአክሲዮን ገበያ በኢትዮጵያ ብዙም እድገት እያሳየ አለመሆኑ ይታወቃል። አብዛኞቹ በኪሳራ ላይ መሆናቸውን ደጋግመው በሚያወጧቸው ሪፖርቶች ገልጸዋል። እስካሁን ባለው የአገሪቱ የአክሲዮን ገበያ ታሪክም ከኪሳራ ነጻ መሆን የቻሉ ተብለው የተለዩት በባንክ ዘርፉ የተሰማሩት እንደሆኑ ይገለጻል። ሁሉም ባይባሉም በርካቶች በኪሳራ ከገበያ እየወጡበት ባለው የአክሲዮን ዘርፍ እድገት በተስፋ እንዴት ስኬታማ ሊሆን እንደቻለ ቀደም ሲል ፕሬዝዳንቱ በገለጹት መልኩ አስረድተዋል። ሆኖም ከጋዜጠኞች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ‹‹20 ዓመት ሙሉ ቤት በማከራየትና ሰርቪስ በመስጠት ነው የቆያችሁት። በሌላ መስክ ለመሰማራትና ኢንቨስት ለማድረግ ምን አስባችኋል?›› የሚል ነበር። አቶ ቴዎድሮስ ሲመልሱም የተነሳው ጥያቄ ትክክል መሆኑን ገልጸው፤ ሆኖም በተጠና መልኩ ገንዘቡን ወደሌላ ኢንቨስትመንት መስክ ለማዋል እየታቀደ እንደሆነ ገልጸዋል። እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ ኢቢኤም ሊሰማራባቸው ይችላሉ ተብሎ ከሚጠበቁት ዘርፎች መካከል አንዱ የሪል እስቴት ኢንቨስትመንት ይሆናል።

 

ሌላው ለአቶ ቴዎድሮስ የቀረበላቸው ጥያቄ በአገሪቱ የተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በገበያው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ ይነገራል። በተከራዮቻችሁ ላይ የፈጠረው ችግር አለ ወይ? የሚል ነበር። ፕሬዝዳንቱ ሲመልሱ የፖለቲካው አለመረጋጋት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደፈጠረ ገልጸው የእነሱ ተከራይ ደንበኞቻቸው ግን ገበያው ላይ ልዩነት በሚፈጥር መልኩ ተገልጋይን የሚጎዳ ውሳኔ አለማሳለፋቸውን ገልጸዋል። አቶ ቴዎድሮስ ሲናገሩ ‹‹ተከራይ ደንበኞቻችን አብዛኞቹ በአንደኛ ደረጃ የኮንስትራክሽን አቅራቢ ድርጅቶች በመሆናቸው ኃላፊነት በሚሰማው መልኩ ነው ግብይታቸውን የሚያካሂዱት›› ብለዋል።

የመብራቱ ነገር

Wednesday, 16 May 2018 13:28

የመብራት ጉዳይ በሀገራችን ህዝብን ከሚያማርሩ ነገሮች አንዱ ከሆነ ውሎ አድሯል። በመካከሉ በተወሰነ ደረጃ መሻሻል አሳይቶ ትንሽ ፋታ አግኝተን ነበር። ነገር ግን ከሳምንታት በፊት ጀምሮ ተመልሶ መጥፋቱን ቀጥሎበታል። እንዲያውም ይባስ ብሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለዚያውም ለረጅም ጊዜ መጥፋት ጀምሯል። ለኃይል መቋረጡ የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም ምክንያቶቹ ግን አሳማኝ አልሆኑም። የኃይል መቋረጡ በግለሰብ ቤት ደረጃ ብቻ የሚታይ ሳይሆን፤ የትላልቅ ፋብሪካዎችን ጭምር ስራ የሚያስፈታ ነው። ስለዚህ ያለውን ችግር በግልፅ ተናግሮ በጋራ መፍትሄ ማፈላለጉ ይመረጣል። በዚህ አይነት ግን ስራችንን መስራት አልቻልንም። ይህ ችግር ዞሮ ዞሮ ከግለሰብ እለታዊ ገቢ አልፎ በሀገር ገቢ ላይም ከፍተኛ ኪሳራን የሚያስከትል መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

                             

አቶ መሐመድ ሁሴን ከመርካቶ      

 

ቁጥሮች

Wednesday, 16 May 2018 13:20

 

345 ሚሊዮን ኩንታል             በተያዘው በጀት ዓመት የዋና ዋና የምግብ ሰብሎችን ምርታማነት ለማድረስ የተያዘው ዕቅድ፤

 

538 ሺህ 563 ቶን                ባለፉት ስምንት ወራት ለውጭ ገበያ የቀረቡ የጥራጥሬ፣ አገዳና የብርዕ ሰብሎች መጠን፤

 

478 ነጥብ 53 ሚሊዮን ዶላር       ከእነዚህ ምርቶች የተገኘው ገቢ፤

 

12 ሚሊዮን ኩንታል              ለ2010/11 ምርት ዘመን ግዢ የተፈፀመበት ማዳበሪያ መጠን፤

 

           ምንጭ ፡- የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ከአንድ ወር በፊት በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር ለተቀናቃኝ ሀይሎች የአብረን እንስራ ግብዣ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

ለዚሁ ግብዣ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) ግንባር ቀደም ሆኗል። በዚህም መሠረት መንግስት ለኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ጋር ድርድር መጀመሩን በይፋ ሰሞኑን ገልጿል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እንደገለጸው የአገሪቱን ህገ መንግስት ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን መንግሥት በገለጸው መሠረት፤ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰላም ጥሪ ማስተላለፉን አስታውሷል።

በዚህም መሠረት መቀመጫውን ከሃገር ውጭ ካደረገውና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) ተብሎ ከሚጠራው ድርጅት ጋር ድርድር አድርገዋል ብሏል መግለጫው።

ድርድሩ ይሳካም፣ አይሳካም መንግስት ለዘላቂ ሰላም የወሰደው እርምጃ ይበል የሚያሰኝ ነው።

ሌሎችም ተቀናቃኝ ኃይሎች የትጥቅ ትግል ያወጁት ጭምር ከመንግሥት ጋር በመነጋገርና በመደራደር በሠላማዊ መንገድ ለመታገል ቢሞክሩ አትራፊ ይሆናሉ።

መንግሥትም የፓለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ ለህዝብ የገባውን ቃል ሊተገብር ይገባል።

 

-    የባለሥልጣናት ቆይታ በሥራ አፈፃፀማቸው ይወሰናል፤

 

በውጭ አገራት ባንኮች አካውንት ያላቸው ባለስልጣናት በአካውንቶቻቸው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይፋ አደረጉ፡፡

ጠቅላይሚኒስትሩ እንዳሉት በተለይም በውጭ አገራት ባንኮች አካውንት ያላቸው ባለስልጣናት በአካውንቶቻቸው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ለዚህም አገራት ትብብር እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትላንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሰብስበው በስራዎቻቸውና አሰራር ዙሪያ ገለጻና ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መድረክ ላይ የራሳቸውን ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፤ በዚሁ ጽሁፋቸውም የአመራር ጥበብን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል። የህዝበ አገልጋይ ምን አይነት ሰብዕና ሊላበስ እንደሚገባና ምን አይነት አገልግሎት በምን አይነት ጊዜና ቦታ መስጠት እንዳለበትም በተለያዩ አብነቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ገለጻቸው ወቅት እንዳሉትም፤ ሳምንታዊው የካቢኔ ስብሰባ ከአርብ ወደ ቅዳሜ መለወጡንና ሚኒስትሮች አርብ በስብሰባ ስም ጊዜ ማባካን እንደሌለባቸውና መደበኛ ስራቸውን እንዲሰሩ አሳስበዋል።

አገሪቷ እያደገች መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ አድጋለች ከማለት ባሻገር በተጨባጭ ህዝቡ ምን ያህል ተጠቅሟል የሚለውን መፈተሽና ማረጋገጥ አለብን ሲሉም አስታውቀዋል።

እያንዳንዱ የመንግስት አመራርም አሰራሩን ግልጽና ለህዝብ የማይደበቅ ማድረግ እንደሚገባውም ዶክተር አብይ አሳስበዋል።

እያንዳንዱ ሚኒስትር ከዚህ በኋላ ለስብሰባ ሲመጣ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ሚኒስትር ሃሳብ አመንጪ እንጂ አቃቂር አውጭ አይደለም” ሲሉም ነው አጽንኦት የሰጡት።

ከባለስልጣናት ጉዞ ጋር በተያያዘም ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም በውጭ አገራት ባንኮች አካውንት ያላቸው ባለስልጣናት በአካውንቶቻቸው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ለዚህም አገራት ትብብር እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የፌዴራል መንግስት የካቢኔ አባላት የሥራ ኃላፊነት የቆይታ ጊዜ የሚወሰነው ኃላፊዎቹ በሚኖራቸው የሥራ አፈፃፀም ምዘና መሰረት ብቻ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታውቀዋል።

ከዚህ በኋላም የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ልዩ ልዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ከሚከታተሏቸው ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ጋር የስራ ስምምነት መፈጸም እንደሚገባቸውና ስራቸውን በዚህ አግባብ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

        

ዜና ትንታኔ

 

አቶ ካሳሁን ኃ/ማሪያም፤

ከትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርነት ተነሱ

 

በትራንስፖርት ሚኒስቴር የትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በመሆን ላለፉትሃያ ሁለት ዓመታት ያገለገሉት አቶ ካሳሁን ኃ/ማሪያም ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡

ሰኞ ዕለት በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አሕመድ በተፃፈ ደብዳቤ ከኃላፊነት መነሳታቸው ታውቋል፡፡ በምትካቸው በትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ አብዲሳ ያደታ ዝቅ ተደርገው እንዲተኳቸው ተወስኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እየወሰዱት ያለው የሪፎርም እርምጃ ተገቢነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚወድቅ አይደለም፡፡ የጀመሩት ሪፎርም መሰረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ እና አዲስ የሚሾሙ ሰዎች ከሕግ በታች መሆናቸውን ግንዛቤ የሚወስዱበት የአሿሿም ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ለማስጨበት ሁለት መሰረታዊ ነገሮች መሟላት አለበት፡፡

አንደኛው፣ አዲስ የሚሾሙ ሰዎች ቀድሞ ከነበረው ኃላፊ ወይም ባለስልጣን በትምህርት ዝግጅት ከፍ ያሉና ለሚሾምበት ኃላፊነት ተዛማጅ የሙያ ባለቤት መሆናቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ሁለተኛ፤ ከኃላፊነት የሚነሱ ሰዎች በሰሯቸው ጥፋቶች ልክና መጠን በሕግ የሚጠየቁበት አሰራር መዘርጋት አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል አዲስ ተሻሚዎች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ከሕግ የበላይነት ማምለጥ እንደማይችሉ አውቀው እንዲገቡበት እድል ይፈጥራል፡፡ የሚወሰደው እርምጃም በሕግም በሕዝብ ፊት ቅቡል ይሆናል፡፡

እንደማሳያ ለማስቀመጥ፣ አቶ ካሳሁን ኃ/ማሪያም ይመሩት የነበረው የትራንስፖርት ባለስልጣን መስሪያቤት በየቀኑ በመኪና አደጋ ከሚቀጠፈው ዜጋ አንስቶ እስከ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ግብዓት እስከማቅረብ የነበረው አሉታዊ ሚና በቀላል የሚተመን አይደለም፡፡

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲመለከቱት የሚያስፈልገው ዋና ነጥብ በትራንስፖርቱ ዘርፍ በአንድም በሌላ መልኩ ከገዢው ፓርቲ ጋር ቁርኝት ያላቸው በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች እና በግል የትራንስፖርት ዘርፍ ተደራጅተው ያሉ ማሕበራት መካከል ያለው ያልተመጣጠነ የገበያ ውድድር ሊታረም የሚገባው ነው፡፡ ልማታዊ መንግስት የግሉ ዘርፍ መሰማራት በማይችልበት የሚሳተፍ የገበያ ስርዓት የሚከተል እንጂ፣ በግሉ ባለሃብት ሊሸፈን በሚችል ዘርፍ ተሻሚ የገበያ ስርዓት አይከተልም፡፡ በዚህ ዘርፍ ከገበያው ውድድር በባሰ የትራንስፖርት ባለስልጣን መስሪያቤት በገነገነ ኔትዎርክ በመያዙ የሚያስከትለው አሉታዊ ጉዳት በጊዜም በገንዘብም የሚተመን አይደለም፡፡

በአስረጂነት ለማሳየት በሰንደቅ ጋዜጣ በተደጋጋሚ ያሰፈርነውን የግሉ የትራንስፖርት ማሕበራት ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ የተፈጸመውን የአሰራርና ግድፈቶች በዚህ መልኩ ማቅረብ ተገቢ ነው የሚሆነው፡፡

የትራንስፖርት ማኅበራት ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ የገጠማቸው ተግዳሮቶች ምን ይመስላሉ?

 

1.የፍ/ብ/ሕግ ድንጋጌዎች ተጥሰው ህጋዊ ማኅበራት እንዲፈርሱ ተደርገዋል፣

በህግ አግባብ የተቋቋሙት ማኅበራት ህጉ በሚፈቅደው መሠረት ሊፈርሱ ይችላሉ። የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን መ/ቤት ግን የፍ/ብ/የሕግ ድንጋጌዎችን በመመሪያ በመሻርና ማኅበራት የሚፈርሱበት የህግ አግባብ በመጣስ ማኅበራትን አፍርሷል። ማሕበራት በሕግ የሚፈርሱበት አግባብ፣ በማኅበሩ የመመስረቻ ፅሁፍና የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት (ፍ/ብ/ህ/ቁ454)፤ በማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ውሣኔ (ፍ/ብ/ቁ460)፤ በፍርድ ቤት ውሣኔ (ፍ/ብ/ቁ461)፤ የማኅበሩ ዓላማና ክንውኑ ህገወጥ ወይም ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆነ እንደሆነ በአስተዳደር ውሣኔ (ፍ/ብ/ቁ462) ብቻ መሆኑ በፍ/ብ/ሕጉ በግልፅና በማያሻማ ሁኔታ ተደንግጎ እያለ፤ የባለሥልጣኑ መ/ቤት ግን ቁጥራቸው ከ80 በላይ የሆኑ በህግ አግባብ የተቋቋሙ ማኅበራት በአደረጃጀት ሰበብ እንዲፈርሱና ህልውናቸውን እንዲያጡ አድርጓል።

 

2.     የማኅበራት ሃብትና ንብረት እንዲመዘበርና እንዲባክን ተደርጓል፣

የባለሥልጣኑ መ/ቤት በህግ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የማኅበራት ሃብትና ንብረት ተገቢ ጥበቃ እንዲደረግለት የሚያስችል የአፈፃፀም መመሪያ ማውጣትና መተግበር ሲገባው፣ በአንፃሩ ህጋዊ ሰውነትና ህልውና ያላቸውን ማኅበራት ከህግ አግባብ ውጭ እንዲፈርሱና ህልውናቸውን እንዲያጡ በማድረግ ሃብትና ንብረታቸው ለብክነትና ለምዝበራ እንዲጋለጥ አድርጓል።

ማኅበራት የአደረጃጀት ለውጥ ያድርጉ ቢባል እንኳን በቅድሚያ ሃብትና ንብረታቸው እንደዳይባክንና እንዳይመዘበር የሚያደርግ የአፈፃፀም እርምጃዎችን ማስቀደም ሲገባውና ሐብትና ንብረቱ የፍ/ብ/ሕጉ በሚያዘው መሠረት አዲስ ወደተደራጁት ማኅበራት እንዲተላለፍ ማድረግ ሲገባው፤ ሃብቱና ንብረቱ የደረሰበት እንዳይታወቅ በማድረግ ለተፈፀመው ጥፋት ሊጠየቅበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

 

3.     የሎጅስቲክስ አስተባባሪ ባለመኖሩ በማኅበራት ላይ የሚደርስ ጉዳትን በተመለከተ፣

በሃገራችን የሎጅስቲክስ አስተባባሪ ማዕከል የለም። ይህም በመሆኑ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ግዙፍ ጭነቶች፣ ማዳበሪያ፣ የምግብ ስንዴ፣ የኮንስትራክሽን ብረቶች፣ ኮንቴነሮች….ወዘተ በጊዜ ሠሌዳ ተቀናብረው ወደብ እንዲደርሱ ስለማይደረግ፤ የትራንስፖርት አቅርቦቱ ከአቅም በላይ እንዲሆንና ወደብ ላይ ከፍተኛ ክምችት እንዲፈጠር ይደረጋል። በዚህ ጊዜ የትራንስፖርት ባለሥልጣን የትራንስፖርት ቅንጅቱን ለማስተባበር ሲል በትራንስፖርት ማኅበራት ላይ አላስፈላጊ ወከባና ጫና ይፈጥርባቸዋል፡፡ ይህም ሲባል ማኅበራት ካላቸው የጭነት ተሽከርካሪ ኃይል በላይ የጭነት ኮታ እየመደበና ማኅበራቱ ኮታውን ማንሳት በማይችሉበት ጊዜ ማኅበራቱን ከሥራና ከአገልግሎት እስከማገድ ይደርሳል።

ከዚህም በተጨማሪ የጭነት ተሸከርካሪዎችን ለመቆጣጠር በሚል ሰበብ ጋላፊና ደወሌ ላይ የመቆጣጠሪያ ኬላ በማቋቋም፤ የገቢና የወጪ ተሸከርካሪ ሹፌሮች ለኪራይ ሰብሳቢነት እንዲጋለጡ ዳርጓናል።

 

 

4.     የህገወጥ ማኅበራት እንቅስቃሴ ባለመቆጣጠር የሚፈፀሙ ህገወጥ ድርጊቶች፣

አዋጅ መሠረት የተደራጁ ብዙ ህጋዊ ማኅበራት እንዳሉ ሁሉ፤ ህጋዊ መስፈርቶችን ሳያሟሉ በየስርቻው የተቋቋሙ “የትራንስፖርት ማኅበራት” ተብዬዎች እንደ አሸን ፈልተዋል። እነዚህ “ማኅበራት” በህጋዊነት መስመር ስለማይመሩ በተለያዩ የድለላ የግንኙነት መስመሮች ጭነቶችን በከፍተኛ ዋጋ እየወሰዱና በህጋዊ ማኅበራት ውስጥ የተደራጁትን የጭነት ተሽከርካሪዎችን በደላላ እያግባቡ ዋጋ በመቀነስ ጭነቶችን ያጓጉዛሉ። በዚህም ከፍተኛ ጥቅም ያጋብሳሉ።

የትራንስፖርት ዋጋን የሚያንሩ እነዚህ ህገወጥ ማኅበራት መሆናቸው ሳይታወቅ ህጋዊ ትራንስፖርተሮች የማጓጓዣ ዋጋውን በማናር ይፈረጃሉ። የባለሥልጣኑ መ/ቤት እነዚህን ህገወጦች እንዲቆጣጠር በህጋዊ የትራንስፖርት ማኀበራት ለሚቀርብለት ማሳሰቢያ ጆሮ አይሰጥም።

 

 

5.የሞዴል የመተዳደሪያ ደንብ ትርጓሜ

በአዋጁ 468/1997 አንቀጽ 13 ስለማኅበራት መቋቋም በተደነገገው ቁጥር 5 ላይ፣ “ ባለሥልጣኑ የማኅበራት ሞዴል የመተዳደሪያ ደንብ ያወጣል” የሚል ሰፍሯል። ይህን የድንጋጌ አግባብ ከህግ አውጭው ፍላጎት ውጭ በመተርጎም፣ “ማኅበራት እንደጥንካሬያችን እና እንደተጨባጭ ሁኔታዎች የራሳችንን የመተዳደሪያ ደንብ እንዳናወጣ ገደብ አስቀምጠው፤ ሁሉም ማኀበራት በባለሥልጣኑ መ/ቤት በሚወጣ ሞዴል የመተዳደሪያ ደንብ አንድ ወጥ በሆነ መልኩ እንድንገዛ የሚያደርግ መመሪያ ቁጥር 1/2006 በጥቅምት 2006 ዓ/ም አውጥቷል።”

ይህም በመሆኑ የማኅበራትን የፈጠራ ችሎታና የውድድር መንፈስ የሚያቀጭጭ ከመሆኑም በላይ ሞዴል የመተዳደሪያ ደንቡ፣ ማኅበራት የሚተዳደሩበት የራሳቸው የመተዳደሪያ ደንብ እንዳይኖራቸው፤ ከሦስተኛ ወገን ጋር ያላቸውን ግንኙነት በራሳቸው ፍላጎት እንዳያራምዱ፤ ሃብትና ንብረት የማፍራት እንቅስቃሴያቸው በባለሥልጣኑ መ/ቤት ይሁንታ ብቻ እንዲፈፀም እና የውስጥ አደረጃጀታቸውና አመራራቸው በነፃነት እንዳያራምዱ ተግዳሮት እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል።

 

 

6.የትራንስፖርት ኦፕሬተር የደረጃ አሰጣጥ መሥፈርትና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1/ 2006 በማኅበራት ህልውናና እድገት ላይ ያስከተለው ችግር

የትራንስፖርት ባለሥልጣን በጥቅምት 2006 ዓ.ም “….የድንበር ተሻጋሪ የጭነት ትራንስፖርት ኦፕሬተር የደረጃ አሰጣጥ መሥፈርት የሙያ ብቃት ማረጋጫ የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1/2006 “በሚል ስያሜ አንድ መመሪያ አውጥቷል።ህ መመሪያ ዓላማ አድርጎ የተነሳው ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ትራንስፖርት ዘርፍን ለማዘመን ነው ቢባልም በተግባራዊ የአፈፃፀም ውጤቱ ግን አዋጁን በመመሪያ በመሻር በርካታ ችግሮችን አስከትሏል።

በተግባር ከተከሰቱት ችግሮች መካከል፣ በደረጃ መሥፈርቱ መመሪያ መሠረት ተሸከርካሪዎች የተሰሩበት ዘመንና እድሜያቸውን በዋና መሥፈርትነት በመጠቀም ከ1 እስከ 10 ዓመት እድሜ ያላቸው በደረጃ 1፤ ከ10 እስከ 20 ዓመት እድሜ ያላቸው በደረጃ 2፤ ከ20 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው በደረጃ 3 እንዲደራጁ ከመደረጉም በላይ በእያንዳንዱ ደረጃ የእድሜ መሥፈርት የሚካተቱ ተሽከርካሪዎች እንደገና በመጫን አቅማቸው በመለየት ከ300 ኩ/ል በላይ የመጫን አቅም ያላቸው በ“ሀ” እንዲሁም እስክ 299.9 ኩ/ል የመጫን አቅም ያላቸው በ“ለ” እንዲመደቡ ይደረጋል።

ይህ አደረጃጀት፡- ተሽከርካሪዎቹ በደረጃው የእድሜ ጣሪያ ላይ ሲደርሱ ከነበሩበት ማኅበር ደረጃ ወደ ቀጣዩ የማኅበር ደረጃ እንዲሸጋገሩ ይገደዳሉ። ተሽከርካሪዎቹ በየጊዜው ከማኅበር ወደ ማኅበር እንዲፈናቀሉ በሚደረግበት ጊዜ የተሽከርካሪው ባለንብረት ለዓመታት በነበረበት ማኅበር የአባልነት ቆይታው ወቅት ለማኅበሩ ያስገኘው የገንዘብ፣ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ የሃብትና የንብረት እሴቶችን ጥሎ እንዲሄድ ይገደዳል።

ሌላው፣ የማኅበራት ሃብትና ንብረት ባለቤትና ተቆጣጣሪ እንዳይኖረው፣ እንዲባክንና ለግል ጥቅም እንዲውል የሚያደርግ አሠራር ከመሆኑም በላይ የተሸከርካሪ ባለንብረቶች ገንዘብና አቅማቸውን አስተባብረው ወደ ላቀ ተቋማዊ የትራንስፖርት የእድገት ደረጃ አደረጃጀት ለመሸጋገር የሚዲርጉትን ጥረት የሚያመክን እጅግ ከፍተኛ ጎጂ የሆነ አሠራር ነው።

እንዲሁም ማኅበራት ይህ ለትራንስፖርት ዘርፉ እድገት ጎጂ የሆነውን የአደረጃጀት ሥርዓት ተጠንቶና ጉዳቱ ታውቆ አፋጣኝ የእርምትና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ለባለሥልጣኑ መ/ቤት ማሳሰቢያ ቢያቀርቡም የባለሥልጣኑ መ/ቤት ማሳሰቢያውን ካለመቀበሉም በላይ አማራጭ የማሻሻያና የማስተካከያ አደረጃጀት ለማቅረብ አልቻለም።

በመሆኑም ማኅበራት በአሁኑ ጊዜ ከተጋረጠባቸው የጥፋት መንገድ ለመላቀቅ የሚያስችላቸው በጋራና በአንድነት ተደራጅተው ህጋዊና ሠላማዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ አማራጭ አካሄዶችን ለመከተል ተገደዋል።

ከመነሻው መመሪያው በአዋጁ 468/1997 አንቀጽ 12 ተራ ቁጥር 2 “..በህዝብ የንግድ የመንገድ ማመላሻ ሥራ ላይ ሰዎችና ድርጅቶች በአዋጁ አንቀጽ 13 መሠረት የሚቋቋም ማኅበር አባል በመሆን ወይም የማኅበር አባል ሳይሆኑ ሥራቸውን በግል ሊያካሂዱ ይችላሉ..” የተሰኘውን ድንጋጌ ይሽራል። በመመሪያው መሠረት እያንዳንዱ የጭነት ተሽከርካሪ የማኅበር አባል የመሆን ግዴታ ተጥሎበታል።

በአዋጁ አንቀጽ 13 ተራ ቁጥር 4 “….በህዝብ የንግድ የመንገድ ማመላለሻ ሥራ ላይ የተሰማራ ማንኛውም ሰው ወይም ድርጅት በአንድ ጊዜ በአንድ የስምሪት መስመር   ውስጥ ከአንድ በላይ በሆኑ ማኅበራት ውስጥ አባል ሊሆን አይችልም….” የሚለው የአዋጅ ድንጋጌ በመመሪያ ተሸሮ ሁለትና ከዚያ በላይ የጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረት የሆነ “ሰው“ በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ማኅበራት ውስጥ እንዲደራጅ ተገዷል። በመሆኑም መመሪያው ባለንብረቱ የጭነት ተሽከርካሪዎቹን በአንድ ዕዝ ሥር ለመቆጣጠር ያለውን ህጋዊ ችሎታ ነፍጎታል።

ከላይ ለማሳያ አስቀመጥነው እንጂ፣ በአስር ሺ ተሽከርካሪ የሰው ሞት እንደሚሰላ የሚገነዘበው የትራንስፖርት ባለስልጣን በመኪና አደጋ የሚሞተውን የሰው መጠን በተዛባ ሁኔታ እንደሚያቀርብ ይታወቃል፡፡ ይኸውም፣ 750ሺ ተሽከርካሪ መኖሩ ቢነገርም፣ ከዚህ ውስጥ ምን ያሉ መኪና ምን ያህሉ ተሳቢ መሆኑ በግልፅ አይቀመጥም፡፡ ተሽከርካሪ ሲባል ሞተር ያለው ተንቀሳቃሽ ማለት ነው፡፡ ባለስልጣን መስሪያቤቱ ግን ተሽከርካሪ የሚቆጥረው ተሳቢውን ደምሮ ነው፡፡ ስለዚህም በአስር ሺ መኪና የሚለካው የሰው ሞት፣ ትክክለኛ አሃዙን አያሳይም፡፡

የተደረገው ለውጥ ከአናት መምጣቱ አንድ ነገር ሆኖ፣ በትራንስፖርት መስሪያቤት ያለውን የተበላሸ ኔተዎርክ መበጠስ ካልተቻለ ለውጥ መጠቀብ አይቻለም፡፡ ከዳሬክተሮቹ ጀምሮ መበወዝና ማስተካከል ቀጣይ ስራ መሆን አለበት፡፡

 

 

 

“በዝዋይ ማረሚያ ቤት ሰብዓዊ ጥቃት ተፈጽሞብናል”

አቶ አግባው ሰጠኝ

በይርጋ አበበ

የሰማያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ምክር ቤት አባልና የሰሜንን ጎንደር ሰብሳቢ አቶ አግበው ሰጠኝ ‹‹ማረሚያ ቤት ከፍተኛ ስቃይና ድብደባ ተፈጽሞብናል›› ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናገሩ፡፡

አቶ አግባው ሰጠኝን ጨምሮ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ስዊድናዊው ዶክተር ፍቅሬ ማሩ እና ሌሎች በእነ መቶአለቃ ማስረሻ ሰጤ መዝገብ የተከሰሱ እስረኞች ትናንት ተፈተዋል፡፡ የእስር ቆይታቸውንና የታሰሩበትን ምክንያት ለሰንደቅ ጋዜጣ በስልክ የተናገሩት አቶ አግባው ‹‹ለምርጫ 2007 እየተዘጋጀሁ በነበረበት ወቅት የመተማ መሬት ያላግባብ ለሱዳን ተሰጥቷል ብለህ ለኢሳት መረጃ ሰጥተሃል በሚል የሽብር ክስ ነበር የታሰርኩት፡፡ ነገር ግን ከሽብር ወንጀል ነጻ ከተባልኩ በኋላ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ እጃችሁ አለበት ተብለን እንደገና በእስር ቤት እንድንቆይ ተደረገ›› ብለዋል፡፡

አቶ አግባው አያይዘውም በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተነሳውን እሳትና ቃጠሎውን አስመልክቶ ሲናገርም እኛ በማናውቀው ነገር ክስ ተመሰረተብን፡፡ በዚህ ሂደትም በዝዋይ ማረሚያ ቤት ሰብአዊ ክብራችንን እና አካላችን የሚያጎድል ድብደባ ተፈጽሞብናል›› ሲሉ በማረሚያ ቤት የነበራቸውን ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ እስር ላይ ቆይተው ትናንት ከዝዋይ ማረሚያ ቤት የወጡት አቶ አግባው “ሚያዝያ 30 በነበረን ቀጠሮ የክሳችን አንቀጽ ተቀይሮ እንደምንፈታ ተነገረን፡፡ ነገር ግን መቶአለቃ ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ 12 በእኛ መዝገብ የተከሰሱ ወንድሞቻችን ከሚያዝያ 30 የፍርድ ቤት ውሎ በኋላ የት እንዳሉ አናውቅም፡፡ በዚህም ስጋት ገብቶናል” ብለዋል፡፡

በእነ መቶአለቃ ማስረሻ ሰጤ መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸው እስር ላይ ከቆዩት 38 ታራሚዎች መካከል በትናንትናው ዕለት አቶ አግባው ሰጠኝ፣ ዶክተር ፍቅሬ ማሩ፣ አቶ ሲሳይ ባቱ እና አቶ ከበደ ጨመዳ ከእስር ተፈተዋል፡፡

 

በይርጋ አበበ

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ብትሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በለምኖ አዳሪዎችና ጎዳና ተዳዳሪዎች ብዛት ተለይታ እየታወቀች ሲሆን ይህን ችግር ለመቅረፍም ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት እየሰራሁ ነው ሲል ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናገረ፡፡

የድርጅቱ የሚዲያ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ነጋሽ በዳዳ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገረው ድርጅቱ ለምኖ አዳሪዎችንና ጎዳና ተዳዳሪዎችን በቅርቡ ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች ለማንሳት ዝግጅቱን እንደጨረሰ ተናግሯል፡፡ “ሰዎቹን ከጎዳና ካነሳችሁ በኋላ የት ታደርሷቸዋላችሁ›?› የሚል ጥያቄ ከሰንደቅ ጋዜጣ የቀረበለት የሚዲያ ዳይሬክተሩ “ከአዲስ አበባ ማረፊያ በኋላ በአምስት ክልሎች ባሉን ማሰልጠኛ ማዕከላት ገብተው እንዲሰለጥኑ ይደረግና ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ እናመቻቻለን፡፡ ይህን የምናደርገው ደግሞ ከመንግስት ጋር በመተባበር ነው” ሲል መልሷል፡፡

ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ የለምኖ አዳሪዎችንና ጎዳና ተዳዳሪዎችን ሲያነሳ ቢቆይም የተገኘው ለውጥ ምን ያህል የተጠበቀውን ያህል እንደሆነ የገለጸው ጋዜጠኛ ነጋሽ በዳዳ፤ “በተለይ በለምኖ አዳሪዎች ላይ ጥሩ ውጤት አግኝተናል፡፡ ጎዳና ተዳዳሪዎችንም ቢሆን አፋር በሚገኘው ማሰልጠኛ ማዕከል በመግባት ተገቢውን ስልጠና አግኝተው ራሳቸውን በሚችሉበት የስራ መስክ የተሰማሩ ብዙዎች ናቸው” ብሏል፡፡

ለምኖ አዳሪዎችና ጎዳና ተዳዳሪዎችን ከማንሳት በተጨማሪ ወላጅ የሌላቸውን ህጻናት በማንሳት ትግራይ ክልል “ቃላሚኖ እና ውቅሮ” በሚገኙት የድርጅቱ ማዕከላት በማስገባት እያሳደገ መሆኑን የገለጸው የሚዲያ ዳይሬክተሩ፤ “በቅርቡ ከጋምቤላ ክልል ጋር በመነጋገር በአምስት ዓመት ውስጥ 65 ሺህ ወጣቶችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ለማስገባባት ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ አቦል ከተማ ላይም ቦታ ተረክበን በቅርቡ ወደ ስራ እንገባለን” ብሏል፡፡

ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት እና የጋምቤላ ክልል የደረሱበትን ስምምነት አስመልክቶ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት በሰጡት መግለጫ “በክልላችን በቂ የተፈጥሮ ሀብት እና የሰው ሀይል አለን፡፡ ይህን የሰው ሀይል እና የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ተጠቅሞ ወጣቶቻችን ስራ እንዲፈጥሩ ለማድረግ ስልጠናውን በደስታ ተቀብለነዋል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከሶስት ዓመት በፊት በአፋር ክልል ስልጠና ወስደው በግብርና መስክ ለመሰማራት የሚጠባበቁ 3700 ወጣቶች እስካሁን ወደ ስራ አልገቡም፡፡ መቼ ወደ ስራ ይገባሉ? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሰጠው ጋዜጠኛ ነጋሽ ‹‹ችግሩ የተፈጠረው በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትና በሜቴክ በኩል መሰራት የነበረባቸው ስራዎች ባለማለቃቸው ነበር፡፡ አሁን ግን የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ በስማቸው (በወጣቶቹ) እንዲሆን በእኛ፣ በግብርና እንስሳት ሚኒስትር እና በሜቴክ በኩል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ ብድርም መንግስት እንደሚለቅና ወጣቶቹም ወደ ስራ እንደሚገቡ ይጠበቃል›› ብሏል፡፡ ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት በ1981 ዓ.ም በትግራይ ክልል ነበር የተመሰረተው፡፡

አስራ ሶስት አመት ያልሞላትን ታዳጊ ህፃን አስገድዶ የደፈረው ተከሳሽ ሰይድ ታጂ በፈፀመው ወንጀል የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ልደታ ምድብ ጽ/ቤት በመሰረተው ክስ በጽኑ በእስራት ተቀጣ።

የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ የወንጀል ህግ አንቀጽ 627(2) ስር የተመለከተዉን በመተላለፍ ጥቅምት 4 ቀን 2009 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡00 ስዓት ሲሆን በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ቀበሌ 36 ልዩ ቦታዉ አብነት ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ ብትናገሪ እገልሻለሁ በማለት አስገድዶ የደፈራት በመሆኑ በፈፀመው በህፃናት ልጆች ላይ የሚፈፀም የግብረ ስጋ ድፍረት በደል ወንጀል በፌዴራል ዐቃቤ ህግ ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡

ተከሳሽ ክሱ ተነቦለት እንዲረዳው ከተደረገ በኋላ ድርጊቱን የፈፀምኩት ተስማምተን በፍላጎት እንጂ አስፈራርቻት አይደለም፡፡ ነገር ግን በፈጸምኩት ድርጊት ጥፋተኛ ነኝ ሲል የተከሳሽነት ቃሉን ቢሰጥም ዐቃቤ ህግ ተከሳሽ ድርጊቱን መፈፀሙን የሰው እና የሰነድ ማስረጃ በማያያዝ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

ክሱን የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 7ኛ ወንጀል ችሎት የግራ ቀኙን ማስረጃ ከተመለከተ በኃላ ተከሳሽ በተከሰሰበት ወንጀል ጥተኛ ብሎታል፡፡

የቅጣት አስተያየት እንዲያቀርብ የተጠየቀው ዐቃቤ ህግም ተከሳሽ የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመው ከቅርብ ዘመዱ ጋር በመሆኑ በማክበጃ ተይዞ ተከሳሽን ሊያስተምር ሌሎችን ሊያስጠነቅቅ የሚችል ቅጣት እንዲቀጣ አመልክቷል፡

ተከሳሽ በበኩሉ እናቱን የሚረዳ እና ተማሪ፤ እድሜውም ወጣት መሆኑን ባቀረበው ማስረጃ ሁለት የቅጣት ማቅለያ ተይዞለት ሚያዚያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት በ15 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል ሲል የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቦአል፡፡

 

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ስናስብ የኢትዮጵያ የፕሬስ ይዞታ ከዓመት ዓመት ያለመሻሻል ጉዳይ የሚዘነጋ አይሆንም። የጋዜጠኝነት ሙያ ተሟጋቾችም ሃገሪቱን ለመገናኛ ብዙሃን ሥራ አስቸጋሪ ከሆኑ ቦታዎች መካከል ይመድቧታል።


በዚህ ዓመት ግን በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች መፈታትና ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተሰሙት ቃላት በዚህ ወቅት ለበርካቶች ተስፋ የሰጠ ይመስላል።


ፍሬው አበበ አሁን በህትመት ላይ ካሉት ጥቂት ጋዜጦች መካካል የምትገኘዋ 'ሰንደቅ' ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነው።


ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ቅድመ ሳንሱርን ማንሳቱና የወጡት ሕጎች ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እውቅና እንዲያገኝ በማድረግ በሃገሪቱ ነፃ ፕሬስ እንዲፈጠር አመቺ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ማድረጉን ይናገራል።


አሁን ባለው ሁኔታ ዋነኛው ችግር ብሎ የሚያስበው የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት የአመለካከት ችግርን ነው። በተለይ ፕሬሱን በተመለከተ ያለው አመለካከት እንደ ጠላት የመፈረጅ እንደሆነ ይናገራል።


በዚህም ባለፉት 26 ዓመታት ብቅ ብለው የነበሩት ጋዜጦች እንዳለ ጠፍተው "በሚያሳዝን ሁኔታ ኢትዮጵያን የምታክል ትልቅ ሃገር ሦስት ብቻ በአማርኛ የሚታተሙ ጋዜጦች የቀሩባት ሆናለች" ይላል።


በፈቃዱ ሞረዳ ደግሞ ለ15 ዓመታት የጦማር ጋዜጣ አዘጋጅና አሳታሚ ሆኖ ሰርቷል። በመጀመሪያዎቹ የፕሬስ ነፃነት ዘመን አስቸጋሪና ተግዳሮቶች የበዙበት እንደነበር የሚያስታውስው በፈቃዱ፤ ሥራውን ስለሚወደው ፈተናውን ተቀብሎ የሙያውን ስነ-ምግባር በተቻለ መጠን አክብሮ እውነትን ለማቅረብ ይጥር እንደነበር ይናገራል።


የነበሩት አንዳንድ ጋዜጦች ፕሬሱን ለጥቃት የሚያጋልጡ ሥራዎችን ይሰሩ እንደነበር የሚናገሩ ሰዎች እንደነበሩ የሚያስታውሰው በፈቃዱ ነገር ግን "መንግሥት ፕሬሱን ስለማይፈልገው ምንም መልካም ነገር ብንሰራ ከማጥቃት ወደኋላ አይልም። እንዲያውም በሸሸነው እርምጃ መጠን ይከተለን ነበር" ሲል ይደመጣል።


በወቅቱ የተለያዩ ወከባዎችና ክሶች ይቀርቡበት እንደነበር የሚዘክረው በፈቃዱ ሥራዉን በሚሰራበት ወቅት ዘወትር የሚያሳስበው ነገር እንዳልሆ ግን ይናገራል።


በጋዜጠኝነት ሥራው ውስጥ በስድስት ወር ጊዜ ለዘጠኝ ጊዜ ታስሮ የተፈታው በፈቃዱ ይህ ሁኔታ ሙያዉን እንዲተው ባያደርገውም መጨረሻ ላይ ግን ነገሮች እየጠነከሩ ሲመጡ በተለይ የቤተሰቡ ሁኔታ ያሳስበው ጀመር።


አምስት ያህል ክሶች ከጋዜጠኝነት ሥራው ጋር በተያያዘ ሲከታተል የነበረው በፈቃዱ በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ መጨረሻውን እስር ቤት ሊያደርገው እንደሚችል በማሰብ ከሃገር መውጣትን የጨረሻው አማራጭ አደረገ።


"እስራት ሰለቸኝ፤ ፈሪ ሆንኩ። ሃገሬን ጥዬ ስወጣ ያለተዘጉ ክሶችና የእስር ትዕዛዞች ወጥተውብኝ ነበር። ስለዚህ በእነዚህ ክሶች የእኔ እስር ቤት መግባት የሚያስገኘው ትርፍ ስላልታየኝ መሰደድና ሌላ አማራጭ መፈለግን" ምርጫው አደረገ።


የአዲስ ነገር ጋዜጣ ማኔጂን ኤዲተር የነበረው መስፍን ነጋሽ፤ የጋዜጠኝነት ሥራን የተለያዩ ነገሮችን ለመማር ዕድልን ያገኘበትና ይነስም ይብዛ ለሃገር አስተዋፅኦ ያደረገበት የህይወቱ አካል እንደሆነ ይናገራል።


መስፍን በፕሬስ ሥራዉ ውስጥ በተለይ የመንግሥትን ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች ላይ ሲሰሩ ህጋዊና መዋቅራዊ እንቅፋቶች ይገጥሟቸው እንደነበር ያስታውሳል።


ከመንግሥት በኩል በአዘጋጆቹ ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሚገልፅ መረጃ ከታማኝ ምንጮች ስላገኙ በግል በደረሱበት ውሳኔ መሰረት አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ከሃገር እንደተሰደዱ ይናገራል መስፍን።


ነገር ግን ማሳደዱ ከሃገር ከወጡ በኋላም አላበቃም ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በደረ-ገፅ በኩል የጋዜጣዋን ሥራ ለማስቀጠል ያደረጉትን ጥረት ተከትሎ በአንዳንዶቹ የጋዜጣዋ አዘጋጆች ላይ በሌሉበት ክስ ተመሰረተባቸው።

 

አዲሱ መሪ. . .


በቅርቡ ወደጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበሩ የመጡት ዶክተር አብይ አህመድ ከቀድሞዎቹ መሪዎች በተለየ ለውጦችን ለማምጣት እንደሚፈልጉ ሲናገሩ እየተደመጡ ነው።


ፍሬው አበበ እንደሚለው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በንግግራቸው የሃሳብ ብዝሃነትን በተመለከተ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግራዋል። "ይህ ማለት ደግሞ በቀጥታ ፕሬስን የሚመለከት በመሆኑ፤ በገቡት ቃል መሰረት ይህንን ተግባራዊ ያደርጋሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ይላል።


ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በውጪ ያሉ ጋዜጠኞች ወደሃገራቸው መጥተው እንዲሰሩ እንደሚፈልጉ የተናገሩትን ነገር መልካምና በበጎ መታየት እንዳለበት የሚያምነው በፈቃዱ፤ ነገር ግን በቅድሚያ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች እንዳሉ ይጠቁማል።


ከውጪ የሚተላለፉ ስርጭቶችን ማፈን ማቆምና አሳሪ የሆኑት ሕግ ላይ መሻሻሎችን ማድረግ ቃልን በተግባር ለማሳየት አንድ እርምጃ መሆኑን የሚጠቅሰው በፈቃዱ፤ እንደሱ በስደት ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ላይ የተከፈቱ ክሶችና ውሳኔዎች መሰረዛቸው በይፋ እንዲነገር ይጠብቃል።


ይህ ከተደረገና በሩ በቀና ልቦና ከተከፈተ "ወደሃገሬ ተመልሼ "ጦማር' ጋዜጣን መልሶ ለማሳተምና እንዲሁም በሌሎች የሚዲያ ሥራዎች ለሀገሬ የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚቀድመኝ የለም" ይላል።


"ኢትዮጵያ በተግባር ብቻ ሳይሆን በቃልም የቆሰለች ሃገር ስለሆነች በቃል መታከም አለባት" የሚለው መስፍን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚቀበለውን አይነት መልዕክት እያስተላለፉ ነው ይላል።


ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ነፃነት ማክበርን በተመለከተ በተዘዋዋሪ መንገድ ከተናገሩት ባሻገር ግልፅ ባለሁኔታ የተናገሩት ነገር እንደሌለ የሚጠቅሰው መስፍን "ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ለዜጎች ሳይከበር፤ ለጋዜጠኞች ብቻ የሚከበር መብት አይሆንም" ይላል።


ያለውን ሁኔታ ለማስተካከል ፍላጎቱ ካለ፤ በእስር ላይ ያሉትን ጋዜጠኞች መልቀቅና የተከሰሱትንም ክሳቸው እንዲሰረዝ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ከበፍቃዱ ጋር ይስማማል።


በተጨማሪም "የፕሬስ ህጉንና የፀረ-ሽብር ህጉን መሰረዝ ካልሆነም አፋኝ የሆኑትን ክፍሎቻቸውን እንዲለወጡ ማድረግ እንዲሁም ጋዜጠኞች ሥራቸውን እንዲያከናውኑ በሁሉም መስኩ አመቺ ሁኔታን መፍጠር በጣም ያስፈልጋል" ባይ ነው።


ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያቀረቡት ያለው ግብዣ ከልብ ከሆነ ከንግግር ባሻገር መንገዱን የሚያመቻች ተጨባጭ ተግባራትን ከወዲሁ መጀመራቸውን የሚያመለክቱ ሥራዎችን መሬት ላይ ማሳየት አለባቸውም ሲል ያክላል።
መስፍን መሬት ላይ ያለው ሁኔታ እስከተቀየረ ድረስ በራሱ በኩል ወደ ሃገሩ ተመልሶ የጋዜጠኝነት ሥራውን ለመጀመር ፍላጎቱ እንዳለውም ይናገራል።


"ከሃገር የመውጣቱ ውሳኔ ከባድ እንደነበረው ሁሉ ወደ ሃገር የመመለሱ ውሳኔም ቀላል አይሆንም" የሚለው መስፍን ነገር ግን ሁኔታዎች እስከተቀየሩና የሚፈልገውን ለመሥራት አመቺ ሁኔታ እስከተፈጠረ ድረስ ለመመለስ አያመነታም።


የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር ወደ ተግባር የሚሻገር ከሆነ በበርካቶች ዘንድ የፈጠረው መልካም ስሜት የተዳከመውን የፕሬስ ሥራ እንዲያንሰራራ በር ሊከፍት ይችላል የሚለው የበርካቶች እምነት ይመስላል።


https://www.facebook.com/BBCnewsAmharic/

Page 5 of 220

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us