news admin

news admin

 

በተረፈ ወርቁ (ምንጭ ግዮን መጽሔት)

1. እንደ መንደርደሪያ


የደቡብ አፍሪካው የነጻት ታጋይ፣ አርበኛና የዓለም ሰላም የኖቤል ተሸላሚው፣ ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ፣ ከ27 ዓመታት የወኅኒ ግዞት ወጥተው፤ እርሳቸውና ሕዝባቸውን እጅግ አሰቃቂ ለሆነ ግፍና መከራ የዳረጋቸውን የአፓርታይድ ዘረኛ መንግሥትንና የሥርዓቱ ቀንደኛ አቀንቃኝ ለሆኑ መሪዎችና ደጋፊዎች- ከልብ የሆነ ይቅርታ ማድረጋቸውን ባወጁበት፣ ለሕዝባቸው ባደረጉት ታሪካዊ ንግግራቸውም፤ ‹‹ለነገይቱ ደቡብ አፍሪካ ብሩሕ ተስፋ ያለን ብቸኛው መንገድ ወይም አማራጭ ‹‹የፍቅር፣ ‹የመደመር› የዕርቀ-ሰላም መንገድ ብቻ›› መሆኑን ባወጁ ማግሥት የለንደኑ ታይምስ/Times መጽሔት በፊት ሽፋን ገጹ ላይ የኔልሰን ማንዴላን ትልቅ ምስል ያካተተ አንድ ወቅታዊ ዘገባ ይዞ ወጥቶ ነበር።


‹ታይምስ› የኔልሰን ማንዴላ የካርቱን ምስል ይዞ የወጣበት መንገድ በወቅቱ ብዙዎችን ያስገረመና ያነጋገረ ጉዳይ ሆኖ ነበር። መጽሔቱ የማንዴላን የራስ ቅል በጣም አግዝፎ የተቀረው አካላቸውን ደግሞ ትንሽ አድርጎ ነበር በካርቱን ምስሉ ያወጣቸው። የዚህ የማንዴላ የካርቱን ምስል አንድምታም፤ “በኃይላቸው፣ በሰራዊታቸው ብዛትና በጠብመንጃ ኃይል ሳይሆን በአእምሮአቸው ታላቅነትና ብስለት፣ በፍቅር፣ በቅን ልቦ እና በማስተዋል ሕዝባቸውን፣ ሀገራቸውን የሚመሩ፣ ብልህና ታላቅ የሆነ መሪን አፍሪካ አሁን ገና አገኘች፤” የሚል መልእክትን ለማስተላለፍ ነበር ይህን የማንዴላን የካርቱን ምስል የተጠቀመበት።


በእርግጥም ሥልጣን የፈጣሪና የሕዝብ አደራ መሆኑን የዘነጉ፣ ሥልጣን ርስተ-ጉልት በሆነባት አፍሪካችን፣ ኢትዮጵያችን- ለሥልጣናቸው ሲሉ በገዛ ሕዝባቸው ላይ ጦር ለማዝመት ወደኋላ የማይሉ፣ የአፍሪካን በደም አበላ እንድትዋኝ፣ ምድራችን የደም-ምድር/አኬል-ዳማ እንድትሆን ያደረጉ፣ ከአውሬ ያልተለዩ አምባገነን መሪዎችን ባየንባት አኅጉራችን/ኢትጵያችን፣ የምርጫ ኮሮጆ ገልብጠውና የሕዝብን ድምፅ ወዲያ ብለው ‹‹ሥልጣን ወይም ሞት!›› በሚል መፈክር ሕዝባቸው ላይ የጥይት ውርጅብኝ የሚያዘንቡ ቡኩኖችን፣ በሙስና፣ በሌብነት ላይ የነገሡ አልጠግብ ባይ፣ ‹‹የቀን ጅቦችን››፣ ግብዞችንና አስመሳዮች፣ የእውነትና የፍትሕ ጠላቶች ነፍስ ሥጋችንን ባስጨነቁባት ኢትዮጵያችን- የአፍሪካዊውን፣ ታላቅ ጀግና የማንዴላን/የማዲባን፤ ‹የእውነት፣ የፍቅር፣ የዕርቀ-ሰላም መንገድ የሚከተል በፍቅር ልብ፣ በአእምሮ ብስለትና በማስተዋል ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን የሚመሩ መሪዎችን ማግኘት እንደ ታላቅ የምስራች የሚቆጠር ነው።


ምዕራባውያኑ ታላላቅ ሚዲያዎች ለዚህም ይመስላል ‹የሰላም፣ የዕርቅ ሰው› የሆኑትን ኔልሰን ማንዴላን እንዳሞጋገሷቸው፣ ከፍ እንዳደረጓቸው ሁሉ በተመሳሳይም ሰሞኑን እንደ ዋሽንተግተን ፖስት፣ ዘጋርዲያን ያሉ ጋዜጦችና ታላላቅ የመገናኛ ብዙኃን የሀገራችንን፣ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትር የዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ‹የፍቅር፣ የዕርቀ-ሰላም ጉዞ› ከግምት ውስጥ በማስገባት ‹‹ዳግመኛው አፍሪካዊው ማንዴላ›› ሲሉ ለመጥራት የተገደዱት።

2. ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በማንዴላ የፍቅር እና የዕርቅ መንገድ…!!


“Ethiopia always has a special place in my imagination and the prospect of visiting Ethiopia attracted me more strongly than a trip to France, England, and America combined. I felt I would be visiting my own genesis, unearthing the roots of what made me an African.” (Long Walk to Freedom Nelson Mandela/1994)


‹‹ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በእኔና በሕዝቤ ልብና ማንነት ውስጥ ያለው ሥፍራ እጅጉን ክቡርና የተለየ ነው፤ በዓለማችን ከሚገኙ ታላላቅ ሀገራት መካከል ከፈረንሳይ፣ ከኢንግላንድና ከአሜሪካ ሀገራት ጉብኝቴ ይልቅ፤ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ቅርስና የአፍሪካዊ ማንነቴ ሥርና መሠረት የሆነችውን ሀገረ ኢትዮጵያን መጎብኘት በእኔና በሕዝቤ ልብ ውስጥ ልዩ ትርጉም፣ ልዩ ስፍራ አለው።›› (ኔልሰን ማንዴላ)


በውድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ፣ በሕዝባቸውና በአፍሪካ ምድር ፍቅር፣ ዕርቀ-ሰላም፣ ብልጽግና ይሰፍን ዘንድ ምኞታቸው የሆነው የሀገራችን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ ቅዳሜ ዕለት በተጠራው ታሪካዊና ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ በለበሱት ካኔተራ/ቲሸርት ላይ የደቡብ አፍሪካውያን፣ የፀረ-አፓርታይድ ታጋይና የነጻነት አርበኛ፣ ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ ምስል እንዲሆን መፍቀዳቸው የእኚህን ታላቅ አፍሪካዊ አድናቂያቸው ብቻ ሣይሆኑ በተግባርም የእርሳቸውን የዕርቀ-ሰላም መንገድ ለመከተል መወሰናቸውን የሚያሳብቅ ነው።


ደቡብ አፍሪካውያን ‹‹ታታ ማዲባ (ታላቁ አባታችን)›› በሚል የሚጠሯቸውና የሚያሞኳሽዋቸው ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ የሀገራቸውን፣ የሕዝባቸውንና የእርሳቸውን እንደ መርግ የከበደ የመከራ፣ የግፍና የጭቆና ታሪክ፣ የአፍሪካንና ሕዝቦቿን ዘመናት የባርነትና የቅኝ ግዛት አሰቃቂ፣ የመከራ ዘመናት- በፍቅር፣ በይቅርታ ዘግተው፣ ለ27 ዓመታት ከቀዝቃዛው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ማዶ- በሮቢን ደሴት ወኅኒ ቤት ተግዘው፣ በዘረኛው የአፓርታይድ መንግሥት የውድ እናታቸውንና የበኩር ወንድ ልጃቸውን እረፍተ-ሞት ላይ እንኳን እንዳይገኙ ማእቀብ ተጥሎባቸው፣ እንደ መርግ የከበደ የእናታቸውን ህልፈት ለብቻቸው ሆነው በኀዘንና በቁጭት በትር እንዲገረፉ የፈረደባቸውን፤


ከትግል አጋራቸውና ከውድ ሚስታቸው ጋር እንኳን በስድስት ወር አንድ ጊዜ ለሠላሳ ደቂቃ ብቻ እንዲገናኙ የወሰነባቸውን … ያን በእርሳቸውና በሕዝባቸው ላይ አስከፊ የሆነውን የዘረኝነት ቀምበር የጫነባቸውን፣ መራራና አሰከፊ፣ የሰቆቃ ሥርዓት ይቅር ብለው በአፍሪካ፣ በዓለም ፊት አዲስ ታሪክ የጻፉት፤ የአፍሪካ ጥቁር አፈር ውድ ልጅ የሆኑት ማንዴላ የዶ/ር ዐቢይ ሕያውና ታላቅ ተምሳሌት ሆነው በቅዳሜው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ደምቀው ታይተዋል።


እኚህ የሀገራችን ጠቅላይ ሚ/ር የዶ/ር ዐቢይ ታላቅና ሕያው ተምሳሌት የሆኑ፣ የዕርቅና ሰላም ሰው፣ ደቡብ አፍሪካዊው የነጻነት ታጋይና አርበኛ፣ ኔልሰን ማንዴላ ከ27 ዓመታት ግዞት ነጻ በተለቀቁበት እ.ኤ.አ. የካቲት 11 ቀን 1990 ደስታቸውን ለመግለጽ ለተሰበሰቡ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን ሕዝባቸው፣ በኬፕታውን ከተማ ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ነበር ያሉት፤


I stand here before you not as a prophet but as a humble servant of you, the people. Your tireless and heroic sacrifices have made it possible for me to be here today. I therefore place the remaining years of my life in your hands.


ደቡብ አፍሪካውያን ሕዝቤ ሆይ! በፊታችሁ የቆምኩት እንደ ነቢይ ሳይሆን እንደ ትሑት አገልጋያችሁና ታዛዣችሁ ሆኜ ነው፤ የእናንተ ድካም የለሽ፣ ጀግንነታችሁና መሥዋዕትነታችሁ የዛሬ የነጻነት ቀን ዕውን እንዲሆን አድርጓል፤ ስለሆነም እናንተን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል ቀሪ የሕይወት ዘመኔን በእጃችሁ አደራ እተዋለሁ።


እንደ አፍሪካዊው ጀግና ኔልሰን ማንዴላ ሁሉ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድም በሔዱበትና በተገኙበት የተለያዩ መድረኮች ሁሉ በሚያደርጓቸው ንግግሮቻቸውና ተግባራቸው የሕዝብ አገልጋይነታቸውን ለማስመስከር፣ በፍቅር፣ በቅን ልቦና እና ትሕትና ተግተው በመሥራት ላይ ናቸው። አይሁዳዊው፣ ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን፣ ‹‹ትጋት ለሰው የከበረ ሀብት ነው፤›› እንዲል ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ- ሀገራቸው፣ ኢትዮጵያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በመጓዝ የፍቅርን፣ የሰላምንና የዕርቅን ዘር ለመዝራት እየደከሙ፣ እየተጉ ነው። ‹‹ፍቅር ያሸንፋል!›› በሚል መርሕም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት ረጅም ዓመታት ጥላቻና መከፋፋት፣ መበላላትና መለያየት ለነገሠበት የሀገራችን የፖለቲካ የጨለማ መንገድ ላይ ፍቅር ብርሃን ይበራበት፣ ይቅርታ ጎሕ ይደምቅበት ዘንድ እየተጉ፣ ሕዝባቸውን፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውንና ፓርቲያቸውን ኢሕአዴግን ጭምር እያተጉ ነው።

3. ፍቅር ያሸንፋል!


ደቡብ አፍሪካዊው የነጻት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ፤ ‹‹ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት እርሳቸው፣ የሕዝባቸውና የመላው ጥቁር ሕዝቦችና በአጠቃላይ የሰው ልጆች ሁሉ ግዙፍ ታሪክና ገናና ሥልጣኔ መነሻ፣ የሰው ልጆች የነጻነት የተጋድሎ ክቡር ተምሳሌት… ወዘተ መሆኑን ባወጁበት ‹Long Walk to Freedom› በሚል ረጅሙን የትግል ሕይወታቸውን በተረኩበት መጽሐፋቸው፤ ‹‹ፍቅር በማንኛውም ልብ ውስጥ በተፈጥሮ አለ፤ በተቃራኒው ጥላቻ ግን በትምህርት እንጂ በተፈጥሮ አይገኝም።›› እንዳሉት ሁሉ ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ ይህን የፍቅር፣ የዕርቀ-ሰላም መንገድ ለመጓዝ ረጅሙን ጉዞ ተያይዘውታል።


ዶ/ር ዐቢይ ባሳለፍነው ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ በተጠራው ታሪካዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የማንዴላ ምስል ያረፈበትን ካኔተራ ለብሰው መምጣታቸው እኔም ለውድ ሀገሬ፣ ለዚህ ባለ ታሪክና ታላቅ ሕዝብ ‹የማንዴላን/የማዲባን የፍቅር፣ የሰላም፣ የእርቅ መንገድ እከተላለሁ!› በሚል መርሕ፤ የኢትዮጵያዊነትን የፍቅርና የአንድነት ቃል ኪዳን ከሕዝባቸው ጋር አብረው ለማደስ ቃል የገቡበት፣ ለውድ ሀገራቸውና ለውድ ሕዝባቸው ምኞታቸውና ሕልማቸው ‹‹ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት፣ መደመር›› መሆኑን ዳግመኛ ያረጋገጡበት ታሪካዊ፣ ታላቅ ዕለት ነው ማለት ይቻላል።


ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ማግሥት ጀምሮ ፍቅርን፣ ይቅርታን፣ ሰላምንና ዕርቅን በማወጅ ሀገራቸው ኢትዮጵያ በቀደመ ታሪኳ ወደነበራት ገናና ሥልጣኔ፣ የታላቅነት፣ የክብር ሰገነት ላይ ትመለስ ዘንድ መወጣጫ መሰላሉ፣ እንደ ሀገር ለመቀጠል ያለን ብቸኛ አማራጭ፤ ‹አንድነት፣ ኅብረት፣ መደመር ነው፤ በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ፍቅር፣ ሰላም እንዲናኝ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ!› በማለት ደጋግመው ጥሪያቸውን ለሕዝባቸው አስተላልፈዋል።


ጠቅላይ ሚ/ሩ በዚሁ ፍቅርን፣ ሰላምንና ዕርቅን ባስቀደሙበት ጉዞአቸው ከሀገራችን ኢትዮጵያ ውጪም ከምሥራቅ አፍሪካ እስከ ሰሜን አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ድረስ ተጉዘው ለሕዝባቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር በተግባር ጭምር አሳይተውናል።

 

4. ቅዳሜ ሰኔ 16ን በጨረፍታ፡-


የቅዳሜው ሰኔ 16 ቀን የድጋፍ ሰልፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የፍቅር፣ ዕርቀ-ሰላም ጥሪ፣ ግብዣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ድንበር ሳይለያቸው፣ ሳይከፋፍላቸው በአንድነት ሆነው፤ ‹‹እኛም ከጎንህ ነን፣ ኢትዮጵያና ሕዝቧን ታላቅ የማድረግ ክቡር ራእይህም ተካፋዮች ነን። ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ ‹‹ሕልም ሕልማችን፣ ቁጭትህ ቁጭታችን፣ ናፍቆትህ ናፍቆታችን፣ ተስፋህ ተስፋችን ነው!›› በሚል የዘመናት ናፍቆት፣ ታላቅ ስሜትና ጉጉት- ኢትዮጵያውያን ሁሉ በፍቅር የታደሙበት ነበር የቅዳሜው ዕለት የመስቀል አደባባዩ ታሪካዊ ሰልፍ።


በአንፃሩም ደግሞ ‹‹የእውነት፣ የፍትሕ፣ የፍቅር፣ የሰላም ጠላቶችን ያስደነገጠ፣ ያስበረገገና የክፋት ምክራቸው የተናደበት፣ ታሪክ በወርቀ ቀለሙ የከተበው ደማቅና ታሪካዊ ሰልፍ ሆኖ ነው ያለፈው። ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ በቅዳሜው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በደረሰው የቦምብ ጥቃት አደጋ በኋላ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታ ባስተላለፉት መልእክታቸው እንዳሉትም፤


‹‹የጥፋት፣ የክፋት ኃይሎች ሆይ፡- ከብረት በጠነከረ በኢትዮጵያዊነት የፍቅር፣ የአንድነት ቃል ኪዳን፣ ብርሃን የፈነጠቀበት ጎዞአችንን ለማጨለም፣ ደስታችንን ለመረበሽ ያደረጋችሁት ሙከራ አልተሳከላችሁም፤ ደግሞ መቼም አይሳካላችሁምም። በዚህ ክፋታችሁ፣ ጥፋታችሁ መካከል እንኳን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለፍቅር፣ ለሰላም፣ ለአንድነት የዘረጉት ክንዳቸው አልታጠፈም፤ አይታጠፍምም። በሀገራችን የጀመረው የፍቅርና የአንድነት ጠል፣ ዝናብ መዝነቡ ይቀጥላል፤ በጭራሽ ወደኋላ አንመለስም!!››


ዕለቱ ይቅርታ ከፍ ያለበት፣ ፍቅር የነገሠበት ነበር። በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን የነጻት ተጋድሎ፣ በክቡር ደማቸው ከፍ ያለው አረንጓዴው፣ ቢጫውና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማችን በክብር ከፍ ብሎ የታየበት ነበር። በአጭሩ የሰልፉ ኅብረ ብሔራዊነት፣ ታላቅ ትዕይንት ግን ቃላት ከሚገልጸው በላይ እጅግ ልዩ ነበር። ያልተሰማ የመፈክር ዓይነትና ያልተሰማ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የድል ዜማ አልነበረም። ላለፉት ሃያ ዓመታት የታሰሩ መፈክሮችና ዜማዎች በነጻነት አዲስ አበባን ጎዳናዎች አድምቀውት ነበር የዋሉት። ሕፃን፣ ወጣት ወንዶችና ሴቶች፣ አርበኞች፣ አርጋውያን፣ ካህናት፣ መነኮሳት፣ ሼኽዎች... ብቻ ምንም የቀረ የኅብረተሰብ ክፍል አልነበረም ማለት ይቻላል። ፍቅር ያሸነፈበት፣ ደማቅና እጅግ የተዋበ ሰልፍ ነበር!!


በኢትዮጵያ ፍቅር ነፍሳቸው የተማረከ፣ በእናት ምድራቸው የአንድነት የተጋድሎ ታሪክ ብሔራዊ ኩራት መንፈሳቸው ከፍ ያለ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በፍቅር ሸማ ጥበብ ደምቀው በደስታ እንባ የታጠቡበት ቀን ሰኔ 16 ዕለት ቅዳሜ!! በዚህ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የእናት ሀገራችንን ሰንደቀ ዓላማ በክብር ከፍ አድርገው የተሸከሙና የሚያውለበልቡ አርጋውያን አባቶችና እናቶች በእንባ እየታጠቡ የኢትዮጵያን አምላክ በደስታ ሲቃ ተውጠው ሲያመሰገኑ ማየት ልዩ የሆነ ስሜትን የሚያጭር ነበር። ይህ ፍቅር፣ ሰላም እና የይቅርታ መንፈስ በሀገራችንና በሕዝባችን መካከል ጸንቶ ይቀጥል ዘንድ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ጸሎትና ምኞት ነው።


‹‹Let Unity, Discipline and Peaceful Action become the Hallmark of Everything We Do! Viva Peace! Viva Democracy!›› (Nelson Mandela/Madiba)


‹‹አንድነት፣ ጨዋነትና ሰላምን መርሕ ያደረገ የለውጥ እንቅስቃሴ፤ በምናደርጋቸው በማንኛውም ድርጊታችን ዋና ቁልፍ ጉዳይ ይሁን! ቪቫ ለሰላም! ቪቫ ለዲሞክራሲ!››
ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለሀገራችን!

ጊዜ ጠባቂ ቦንብ

Wednesday, 04 July 2018 12:51

ዳንኤል ክብረት (http://www.danielkibret.com)

 

አንድን ሕዝብ ወይም ማኅበረሰብ በተመለከተ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚደረጉ አሉታዊ የገጽታ ግንባታዎች ውጤታቸው ከሚታሰበውም የከፋ ነው። በዓለም ላይ አደጋ ላይ የወደቁ ማኅበረሰቦችን ታሪክ ስንመለከት ከሁለት ወገን የመጡ አካላት የቆሰቆሱት እሳት ያስከተለውን ረመጥ እናይባቸዋለን። አንደኛው እነርሱን ከሚወደው ወገን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከሚጠላቸው ወገን ነው።


የተጠቂው ወገን ነኝ የሚለው አካል ያልተሰጠውን ውክልና እየወሰደ የሚፈጽማቸው ተግባራትና የሚያቀርባቸው ሐሳቦች በተቃራኒ ሆነው ነገሩን ለሚቆሰቁሱት ቢላዋ ያቀብላል። በጣት የሚቆጠሩ ልዩ ተጠቃሚዎች ሚሊዮኖችን ወክለው ለመታየት ይጥራሉ። እፍኝ የማይሞሉ አቀንቃኞች የማኅበረሰቡ አፈ ጉባኤ አድርገው ራሳቸውን እየሾሙ የሚናገሯቸው ንግግሮች የዚያ ማኅበረሰብ አቋም መስለው እንዲታዩ ይተጋሉ።


በአንድ ማኅበረሰብ ስም ጥቅም የሚያገኙ አካላት በየዘመናቱ ይፈጠራሉ። በክርስትናና በእስልምና ስም በተፈጸሙ ወረራዎች፣ ዝርፊያዎች፣ ቅኝ ግዛቶች፣ ጦርነቶችና ጭቆናዎች ተጠቃሚዎቹ አማንያኑ አይደሉም። ተጠቃሚዎቹ በእምነቱና በአማንያኑ ስም የሚነግዱት አካላት ናቸው። እነዚህ አካላት እምነቱንም ሆነ አማንያኑን የሚፈልጓቸው ለሁለት ነገር ነው። ለምክንያትነትና ለከለላነት። መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንደሚባለው ግለሰባዊ ስግብግብነትና የሥልጣን ጥመኝነት ላስከተለው ክፉ ተግባር የተቀደሰው ሃይማኖት ምክንያት እንዲሆን ይፈለጋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ዘራፊዎቹና ገዳዮቹ እንዳይነኩ እምነቱን ለሽፋንነት ይፈልጉታል። እነርሱን መንካት እምነቱን መንካት ተደርጎ እንዲወሰድ። በዘር ከለላ ተከልለው የሚበዘብዙና የሚጨቁኑ ሰዎችም ይሄው ነው መንገዳቸው።


በአንድ ማኅበረሰብ ስም የሚነግዱት አካላት በሌላው ማኅበረሰብ ዘንድ የሚፈጥሩት የተበላሸ ሥዕልም አለ። የእነርሱ መጠቀምና ክብር፣ ሥልጣን ማግኘትና መግዛት የማኅበረሰቡ ተደርጎ እንዲወሰድ ያደርጉታል። በተለይ ደግሞ ግልጽነትና ጠያቂነት ባልዳበረበት ማኅበረሰብ ውስጥ እገሌ እና እገሊት፣ ይሄና ያ፣ እንዲህና እንዲያ ሁሉንም የሚገልጡ ማሳያዎች ተደርገው ይወሰዳሉ። ይህ ደግሞ ለጅምላ ፍረጃ ያጋልጣል። አበበ ተጠቀመ ማለት አበበ የተገኘበት ማኅበረሰብም ተጠቀመ ማለት ነው ተብሎ ይወሰዳል። አበበም እንደዚያ እንዲሆንለት ይፈልጋል።


ከዚህ ባሻገር ደግሞ ዐውቀውና ሳያውቁት ሌላውን ማኅበረሰብ የማጥላላት፣ የማናናቅና የመፈረጅ ዘመቻ የሚያደርጉም አሉ። አንዳንዶቹ ግለሰብን ከማኅበረሰብ መለየት ያቃታቸው ናቸው። አንድ በሬ ከወጋቸው በሬዎችን ሁሉ የሚጠሉና ሊያርዱ የሚነሡ ናቸው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ምንጊዜም የሚጠቀሰው በአይሁድ ማኅበረሰብ ላይ የደረሰው ነው። ምንም እንኳን ክርስቶስን የተቃወሙት፣ ያስፈረዱበትና የሰቀሉት ከአይሁድ ወገን የተገኙ ባለሥልጣናትና ጥቅመኞች ቢሆኑም፣ የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያትና ክርስቲያኖችም ከአይሁድ ወገን የተገኙ ነበሩ። በተደጋጋሚ በየዘመናቱ የተገለጠው ግን ስለ ሰቃዮቹ አይሁድ እንጂ ስለ ክርስቲያኖቹ አይሁድ አልነበረም። በጅምላ ‹አይሁድ ይህንን አደረጉ› እየተባለ የተነገረው ነገር ከ40 ሚሊዮን በላይ አይሁድ ያለቁበትን ጥፋት በየዘመናቱ አምጥቷል።


በዘመነ ክርስቶስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አይሁድ እንደነበሩ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ይናገራል። ከእነዚህ መካከል ግን በክርስቶስ መከራና ሞት የተሳተፉት ከአምስት ሺ አይበልጡም። መከራው ግን ለሁሉም ተረፈ።


በየማኅበራዊ ሚዲያው፣ በየቀልዶቻችንና በየዘፈኖቻችን የምናስተላልፈው አንድን ወገን የማስጠላትና የማክፋፋት ዘመቻ ማጣፊያው የሚያጥር ነው። በልጆቻችን አእምሮ ውስጥ የሚቀመጡት እነርሱ ናቸው። ልጆቻችን ስለዚያኛው ማኅበረሰብ የሚኖራቸውን አመለካከት የሚቀርጹት በነዚህ ጽሑፎች፣ ቀልዶችና ዘፈኖች ነው። በሀገራችን አንድን ማኅበረሰብ የሚያጥላሉ ዘፈኖች ቦታ እንዲያገኙ ተደርገዋል። አንድን ማኅበረሰብ ለይተው የሚያጠቁ የፕሮፓጋንዳ ቃላት ተፈጥረዋል፤ አንድን ማኅበረሰብ ለይተው የሚያሸማቅቁ መግለጫዎች በባለሥልጣናት ደረጃ ተሰጥተዋል። እነዚህ ሁሉ ከሌሎቹ ጋር እየተደመሩ የተጠቂነት ስሜት የሚሰማው፣ ራሱን ወደመከላከል የሚገባ፣ ሕልውናው አደጋ ላይ መድረሱን ያመነ ማኅበረሰብ ፈጥረዋል። እንዲህ ያለው ማኅበረሰብ ሲፈጠር ደግሞ ከድልድይ ይልቅ ግንብ እየገነባ ከሌላው ጋር መራራቅንና መከለልን ይመርጣል።


በአውሮፓ ከ16ኛው መክዘ በኋላ ለተስፋፋው የፀረ ሴማዊነት ስሜት የታላቁ ጸሐፌ ተውኔት የሼክስፒር ‹የቬነሱ ነጋዴ› ቴአትር አስተዋጽዖ ማድረጉ ይነገራል። የቬነሱ ነጋዴ ዋና ገጸ ባሕርይ ሻይሎክ የተባለ ገብጋባ ይሁዲ ነው። ሻይሎክ የዕብራይስጥ ስም አይደለም። ነገር ግን ‹ሳላን› ከተሰኘውና የሴም የልጅ ልጅ፣ የዔቦር አባት ከሆነው ሰው ስም የተቀዳ መሆኑ ይታመናል። የሻይሎክ ገብጋባነትና ጭካኔ ለከት የለውም። ከእርሱ ገንዘብ የተበደረው ክርስቲያኑ አንቶኒዮ መክፈል ቢያቅተው መያዣው ከአንቶኒዮ ሰውነት የሚቆረጥ አንድ ሙዳ ሥጋ ነው። አንቶኒዮ ብድሩን መክፈል አቃተው። ሻይሎክም ሙዳ ሥጋውን ከአንቶኒዮ ሰውነት ቆርጦ ለመውሰድ ተነሣ።


ሼክስፒር ይህንን ድራማ የጻፈበት የኤልሳቤጥ ዘመን (Elizabethan Era -1558-1605) የሚባለው ጊዜ እንግሊዞች በፀረ ሴማዊነት የተለከፉበት ዘመን ነበር። ከ1290 ጀምረው ከእንግሊዝ የተባረሩት አይሁድ ወደ እንግሊዝ ለመግባት አይፈቀድላቸውም ነበር። የድራማው መቼት በሆነው ቬነስ ደግሞ አይሁድ ይጠላሉ፤ ለጥቃት የሚያጋልጥ የተለየ የመለያ ልብስ እንዲለብሱ ይገደዳሉ። በሼክስፒር ዘመን የነበሩ ድርሰቶች፣ ቀልዶች፣ ሥዕሎችና ድራማዎች አይሁድን ገብጋቦች፣ ክፉዎችና አጭበርባሪዎች አድርገው የሚስሉ ነበሩ። የሼክስፒርን ድርሰቶች ያጠኑ ሊቃውንትም ‹የቬነሱ ነጋዴ› ቴአትር ‹የቬነሱ ይሁዲ› እየተባለ ይጠራ እንደነበር ይገልጣሉ። ይህም ክሪስቶፈር ማርሎዊ ከደረሰው ‹የማልታው ይሁዲ› ቴአትር ጋር ያመሳስለዋል። በ‹የማልታው ይሁዲ› ቴአትር ውስጥ የሚገኘው ይሁዲው ባራባስ እንደ ሻይሎክ ክፉ ነው። የቬነሱ ነጋዴ የሚያልቀው ሻይሎክ ወደ ክርስትና ሲመለስ ነው።


ይህ በሼክስፒር ድርስት ውስጥ የተሳለው ይሁዲ ገጸ ባሕርይ አይሁድ ቀድሞ ከተሳሉበት ገጽታ ጋር ተደምሮ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታዩበትን መነጽር አበላሸው። ስለ እነርሱ ክፉ መናገር፣ መጻፍና መቀለድ የተፈቀደ መሰለ። ለእነርሱ የሚከራከርም ጠፋ። በኋላ ዘመን በአይሁድ ላይ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ያመጡት እነዚህን የመሰሉ ድርሰቶች፣ ቀልዶችና ዘፈኖች ነበሩ።


ዛሬም እኛ ኢትዮጵያውያን ከሁለቱም ወገን ልንርቅ ይገባናል። የሌላችሁን የማኅበረሰብ ውክልና ለሥልጣናችሁ፣ ጥቅማችሁና ለክብራችሁ ስትሉ የምታቀነቅኑ ተቆጠቡ። ማንም አልወከላችሁም። የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤትም ይህንን አያረጋግጥላችሁም። ሕዝቡ ያላለውን በሕዝብ ስም አትናገሩ። እናንተ ስትጠግቡ ሕዝቡ እንደጠገበ አታስመስሉት፤ እናንተ ሲያማችሁም ሕዝቡ እንደታመመ አታስቃስቱት። እናንተ ስትራቡ ሕዝብ የተራበ አድርጋችሁ አትሳሉት፤ ዕዳችሁን ብቻችሁን ውሰዱ።


በሌላ በኩል ደግሞ ስለ አንድ ሕዝብ በጅምላ የሚነገሩ የጥላቻ ንግግሮች፣ ቀልዶች፣ ጽሑፎች፣ ዘፈኖች፣ ግለሰቦችን ጠቅመው ሕዝብን ይጎዳሉ። ይበልጥ ደግሞ በልጆቻችን አእምሮ ውስጥ ተቀርጸው እንደ ጊዜ ጠባቂ ቦንብ ይቀመጣሉ። ለሕዝብ ሲባል ግለሰቦችን መተው እንጂ ለግለሰቦች ሲባል ሕዝብን ማጥፋት ሕጋዊም ሞራላዊም አይደለም።

 

ከተፈሪ ብዙአየሁ ዶርሲስ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ሰላም ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እጅግ ወሳኝ ነው። ከሁሉ የሚበልጠው ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ህዝቦች ጋር እንደ የጉርብትናቸው የደም፣ የባህል የቋንቋ እና የሃይማኖት ትስስር አላቸው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት እምብርት ናት።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ከእነዚህ ሀገራት ጋር ባላት የመልካም ጉርበትና ትስስር ብቻ ሳይሆን በእነርሱ የውስጥ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይወሰናል።

ፖለቲካቸው፣ ሃይማኖታቸው፤ ኢኮኖሚያቸው እኛን ባይወክል የኛን የመወሰን አቅሙ የማይካድ ነው።

እነዚህ ጎረቤት ሀገራት ለኢትዮጵያ ህልውና ወሳኝ ባይሆኑም እንኳን በስኬትዋም ሆነ ውድቀትዋ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል። በመሆኑም የትላንት ማንነታቸውን እና የዛሬ ፍላጎታቸውን መለየት ለኢትዮጵያ መጻኢ የዉስጥ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ እና የዉጭ ግኑኝነትዋ   ወሳኝ ነው።

ለዚህ ነዉ ኢትዮጵያ ለራስዋ ስትል እነርሱን የማቀፍ ስራ መስራትዋ የግድ ነው የሚባለዉ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የእነዚህ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ቀጠና በውስብስብ ፖለቲካ የተሞላ ነው። ሁሉም የቀጠናው ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ ሁለቱ ሱዳኖች፣እና ኬኒያ ከውስጥ በሚነሱ የጎሳ ፖለቲካን ጨምሮ እስከ አለም አቀፍ ሃያላን ሀገራት የጥቅም ፖሊሲ ጥግ ድረስ ከሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት በተለየ መልኩ በአንጻራዊነት በተከታታይ ግጭቶች እና ቡራቡሬ ትርምስ ይታወቃሉ።ለ150 አመታት ያላባራውና ጊዜ እና ክስተትን ጠብቆ የሚነሳው እነዚህ ሃያላን ሀገራት ለራሳቸው ጥቅሞች ሲሉ በየሀገራቱ መካከል የዘሩአቸው አረሞች አፍሪካዉያን መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር እንደ አዲስ ከተዳፈኑበት እየተቀጣጠሉ የዚህን ቀጠና ሀገራት በግልም በጋራም ዋጋ እያስከፈሉ፣ እድገቶቻቸውን እያሽመደመዱ ይገኛሉ። በሌላ በኩል እነዚህ የዚህ ቀጠና የአፍሪካ ሀገራት ይህንን አረም በጋራም ሆነ በግል ለመከላከል እንዳይከለከሉ የየግል እጀንዳዎቻቸውን ሳይጨርሱ ተጨማሪ የቤትም ሆነ የጎረቤት ስራዎች ይሰጣቸዋል። አፍሪካ በአጠቃላይ ምስራቃዊ አፍሪካ በተለይ በአሁኑ ዘመን ካሉት ሀያላን ሀገራት ተጽእኖ ነጻ የሆኑበት ጊዜ በታሪክ ወደ ሁዋላ ተኪዶ በራሳቸው ሀያላን በነበሩበት ጊዜ እንጅ የቅርብ ጊዜ ትዝታ የላቸውም።

ከታሪክ እንደምንረዳዉ እና እየሆነ ካለዉ በመነሳት በዚህ በ150 አመታት ውስጥ የአፍሪካ ቀንድን ያመሱአት ሀገራት የሚከተሉ ናቸዉ።

1.  የእንግሊዝ እና የጣሊያን በቀይ ባህር ላይ ያላችው ፍላጎት በኢትዮጵያና በኤርትራውያን መካከል ያላባራ ቁርሾ ጥሎ ማለፉ እና ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ሀገር ማድረጉ፣

2.  የግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ባለት ጥቅም የበላይነትዋን ለማስጠበቅ የምታደርገው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ አለማባራቱ፣

3.  የፈረንሳይ በጂቡቲ ላይ የመቆየትዋ እና አወጣጥዋም የወቅቷን ኢትዮጵያ እንጅ የነገይቷን ሁኔታ ያላገናዘበ ዉሳኔ በማድረግ አዳፍና የሄዴችው እሳት ኢትዮጵያ በጅቡት ጉዳይ ላይ መቼም አቅም እንዳይኖራት ማድረጉ፣

4.  የእንግሊዝ፣ የጣሊያን፣ እና የፈረንሳይ በሱማሊያ በነበራቸው ትንቅንቅ ውስጥ ለታላቋ ሱማሊያ መፈጠር ጽንሰ ሀሳብ ማኖር እና የኢትዮ ሶማሌ ያልበረደለት ጫና፣  

5.  በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሶቪዬት ህብረት/የሩስያ እና አሜሪካን መር ምእራባውያን የተቃራኒ አይዶሎጂ ፍትግያ ውስጥ የተፈጠረው ቂርሾ አለማባራት፣

6.  ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ የአሜሪካን መር አለም አቀፍ የሽብርተኝነት ቁጥጥር ዘመቻ ለኢህአዴግ መር ኢትዮጵያ መንግስት በቀጠናው ላይ እንድተፏንን እድል ማግኘት፣

7.  በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ጉዳይ የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ከኢትዮጵያ የተነሳ ግልጽ አቋም አለመያዝ እና ገለልተኛ አካል መሰየም አለመቻል፣

8.  የቻይናዎች የንግድ እና የኢኮኖሚአቸዉ ተጽእኖ በቀናነዉ መስፋፋት ብሎም ገበያውን የመቆጣጠር አዝማሚያ የአሜሪካን እና የምዕረባዉያንን ትኩረት መሳብ፣

9.  የሀብታሞቹ እስላማውያን ሀገራት የራሳቸው የሆነ ርእዮተ አለም አልባዎቹ ሱማሊያውያን እና ባልተረጋጋችው የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ውስጥ ሃይማኖታዊ ተጽእኖ የመፍጠር ፍላጎት፣

10.የሰሜናዊ ሱዳን ርእዮተ አለም ጠንካራና ላለመበግር ተጋድሎነ ተመረኩዘዉ ሌሎቹ ሃብታም ሙስሊም ሀገራት ድጋፍ መቀጠል ቀጠናውን ለመቆጣጠር መሞከር ለምትተጋዉ አሜሪካ የትንኮሳዎች ምከንያት መሆን፣

11.የኬንያዉያንን የሊበራሊዝም ተጽእኖ ኢኮኖሚ መንግስት መር ፓርቲዉ እና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ምእራበዉያን ለራሳቸዉ ፍጆታ በሚመች መልኩ ለመቅርጽ የሚፈጥሩት የዉስጥ ጫና፣

12.በቀጠናዉ ገናና ከመሆን ፍላጎት የመነጨ ዉሉ የጣፋበት የኢህአዴግዋ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ኢኮኖሚ ባለቤቷ አቅጣጫ ለሊበራል ዲሞክራቶች አለመመቸት ከዚህም የተነሳ የራሷን ሳታበስል የሌላዉን ለማማሰል ስትሞክር ብዙ ጠላቶችን በቀጠናዉ ማፍርቷ፣ እና የመሳሰሉት ናቸዉ።

እነዚህን ነጥቦች ወደፊት አንድ በአንድ በመንሳት በኢትዮጵያ አዲሱ አመራር አቅጠጫ ዉስጥ ያላቸዉን ተጽእኖ እንደምቹ ሁኔታነት እና የስጋት ምንጭነታቸዉ ከመነፍትሔ አቅጣጫቸዉ ጭምር ለመዳሰስ ይሞከራል።

ጎረቤቶችዋን ያላማከለ ስራ ኢትዮጵያን እንደማያዋጣት አዲሱ አመራር የተገነዘበ ይመስለኛል። ለዚህም ነዉ የዉጭ ግንኙነቱን ከጎረቤት ሀገራት በተለይም በደም፣ በሃማኖት፣ በባህል እና በኢኮኖሚ የተሳሰሯትን ጎረቤቶችዋ የጀመረችዉ። አዲሱ አመራር በሳልነቱን የሚያመላክቱ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ከጎረቤቶችዋ እንድትታረቅ እና ከዚህ በፊት ባጠፋቻቸዉ ጉዳዮች ካሉም የማባበል ስራ ለመስራት ብሎም የአዲሱን አመራር የወደፊት አቋም እና አቅማቸዉንም ጭምር ለማሳየት የተሰራዉ ስራ እነርሱን ብቻ ሳይሆን አለምአቀፍ ማህበረሰቡንም አስደምሟል። የዚህ ጽኀሁ ማጠንጠኛ ይህ ከቶ በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተሞከረ ስልት በጥንቃቄ እና በብስለት መመራት ያስፈልገዋል ነዉ። የኢትዮጵን ትንሳዔ የማይፈልጉ ጠላቶቻችን በዉስጥም በዉጭም ዓይናቸዉ የሚቀላ ወዳጆች ሞልተዉናል። ጥንካሬዎቻችንን በመለየት ድካሞቻንን/ስህተቶቻቸን በማወቅ በተፈጠሩ አጋጣሚዎች በድል ሲቃ ሳንዘናጋ ስጋቶቻችን ላይ መስራት የግድ ነዉ።

ከዚህ የተነሳ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ እንደ ከዚህ በፊቱ እንደማይቀጥል እስክናረጋግጥ ድረስ ምሁርን፣ ተመራማሪዎች በብዕሮቻችን ፖለቲካኞቻችንን ማንቃት የግድ ነዉ እላለሁኝ።

የአዲሱ ጠ/ሚ/ር የለዉጥ ፍጥነት በኢህአዴግ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን መላዉን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵዉያንን እያካለለ ይገኛል። ኢትዮጵያ በለዉጥ ጎዳና ዉስጥ ናት የሚያስብሉ በጎ ጅምሮች ከዉስጥም ከዉጭም ይታያሉ። የለዉጡ አቅጣጫ እና ፍጥነት በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዉስጥም አብዮት አስነስቷል። የጠ/ሚ/ሩ የለዉጥ እርምጃዎች የተፎካከሪ ፓርቲዎችን ሃሳብ/አጀንዳዎች በተግባር ወስደዉባቸዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንታገልለታልን ሲሉ የነበሩትን የዲሞክራሲ አቅጣጫዎች ሳይቀር በተግባር እየመለሱ የሚሉትን እያሳጡአቸዉ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ዓላማቸዉን ወስደዉባቸዉ ኢህዲጋዊ አድርገዉታል። ማጋነን ካልሆነ በቀር የአንዳንዶችን የፖለቲካ ማኒፌስቶ በእርሳቸዉ በተግባር እርምጃ ያለቀ እስኪመስል ድረስ አዲሱን ኢህአዴግ ተቀላቀሉ የሚሉ ይመስላል። በዚህ ሁኔታ ጠንክሮ ከቀጠለ፣ ኢትዮጵያ ከዉስጥም ከዉጭም ከሰከነች፣ የተፎካከሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ብዛት ሳያስፈልገን በሁለት ጽንፍ ቢደራጁ ኢትዮጵያን ወደፊት ማራመድ ይቻላል ብዬ የግሌን አስተያየት እሰጣለሁኝ።

በዚህ አጋጣሚ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሚቀጥለዉ ምርጫ እንድንመርጣቸዉ ካሰቡ አሁን በተፈጠረላቸዉ አጀንዳቸዉን የማቅለል ስራ በአዲሱ የኢህአዴግ አመራር ከተሰራላቸዉ መጪዋን የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚወስን የበሰለ ፖለቲካ የአፍሪካ ቀንድ ተሳትፎዋን ጨምሮ ለኢትዮጵያ በሰከነ መልኩ ያለማንም ጫና ግንባር ፈጥረዉ ትዉልድን ያሳተፈ ስራ ሰርተዉ ቢያቀርቡልን ታሪክ አይረሳቸዉም ብዬ እገምታለሁ።

መጪዉ ጊዜ ብሩህ ነዉ!¾

እምነታችንን አትሸርሽሩት

Wednesday, 04 July 2018 12:51

ችግር ሲገጥም መረዳዳት ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነው። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይሄን ባህላችንን የሚሸረሽሩ እና እርስ በርሳችን እንዳንተማመን የሚያደርጉ ክስተቶች እየተስተዋሉ ነው። በተለይ የጤና እክል የገጠማቸው በርካታ ሰዎች ህክምና ለማግኘት ከፍተኛ ገንዘብ ሲጠየቁ እርዳታ መጠየቅ እና ህዝቡም የመተባበር ሁኔታው ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ያም ሆኖ እውን ለህክምና ተጠየቅን የሚባለው ገንዘብ ይሄንያህል ይደርሳል ወይ የሚለው ብዙዎቻችንን ጥያቄ ያጭሩብን ነበር። አሁን እዚህም እዚያም የምንሰማቸው ነገሮች ደግሞ በተቸገሩ ሰዎች ስም ከህዝበ የሚሰበሰብ ገንዘብ የአንዳንድ ግለሰቦች መጠቀሚያ እየሆነ መምጣቱን ነው። ነገሩ በጣም አሻሚና ለማመንም ላለማመንም የሚከብድ ነው። በዚህ መካከል እውነተኛ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እገዛውን ሳያገኙ ህይወታቸውን መስዋዕት እስከማድረግ የሚደርሱበት አጋጣሚ ይፈጠራል። እየሰማነው ያለነው ነገር ወደ መጨካከን እና እርስ በርስ እምነት ወደማጣት እየመራን ነው። የሚሰሩት አሻጥሮችም ከሁሉም በላይ በሰው ህይወት ላይ የሚሰሩ አሻጥሮች መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። እንዲህ አይነቱን እኩይ ስራ የምትሰሩ ሰዎች እባካችሁ መጨካከንን አትንዙብን።

                              አስቴር ደገፉ - ከሳሪስ 

ቁጥሮች

Wednesday, 04 July 2018 12:50

 

2 ሚሊዮን 55 ሺህ 623                    ባለፉት ዘጠኝ ወራት የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑ ህጻናት፤

 

289 ሚሊዮን 425 ሺህ 983 ብር        ለዚህ የምገባ ፕሮግራም የወጣ ወጪ፤

 

570 ሚሊዮን ብር               በ2008 ዓ.ም ለፕሮግራሙ ወጪ የተደረገ ገንዘብ፤

 

2 ነጥብ 7 ሚሊዮን               በ2008 ዓ.ም የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የነበሩ ህፃናት፤

 

1 ነጥብ 1 ሚሊዮን               በ2009 ዓ.ም የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ የነበሩ ህጻናት ቁጥር፤

 

ምንጭ፡- ትምህርት ሚኒስቴር

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አሕመድ በኢህአዴግ ተመርጠው ወደመንበረ ሥልጣን ከመጡ 90 ቀናት አለፉ። በዚህ አጭር ጊዜያት ውስጥ የሕዝብን ሥነልቦና መያዝ የሚችሉ የለውጥ እርምጃዎችን ወስደዋል። ከእነዚህ መካከል፡-

የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ማድረጋቸው በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በተለይ የግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታት ዓለም አቀፍ ክብርና ምስጋና አትርፎላቸዋል። በሥራ ላይ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲሻር አድርገዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁትን ግንቦት 7፣ ኦነግ እና ኦብነግ ፍረጃቸው እንዲነሳ የሚደነግገው አዋጅ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የጸደቀ ሲሆን ሕጉ ለፓርላማ ቀርቦ ከሰኔ 30 ቀን 2010 በፊት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ለፖለቲካዊ የእርቅ ድርድር መጥራት፤ በየዓለማቱ የሚኖሩ ዜጎች ወደአገራቸው ገብተው እንዲሰሩ ያደረጉት ጥሪ የሚጠቀስ ነው። ይህንንም ተከትሎ አንዳንድ ተቀማጭነታቸው በውጭ አገር የሆኑ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ወደ አገራቸው መምጣት ጀምረዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እንዲጠበቅ ቁርጥ አቋም በመውሰዳቸው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጭምር ከፍተኛ የይዘት መሻሻል ማሳየቱት ችሏል። የግሉ ሚዲያ ተስፋ ማንሰራራቱ፣ ተዘግተው የነበሩ መገናኛ ብዙሃን መከፈታቸው ተጠቃሽ እርምጃዎች ናቸው።

የኢትዮ ኤርትራ ለዓመታት የቆየው ሠላም አልባ፣ ጦርነት አልባ ግንኙነት እንዲሻሻል ባቀረቡት የሠላም ሃሳብ በኤርትራ መንግሥት ተቀባይነት አግኝቶ ተስፋ ሰጪ ግንኙነት ወደመመስረት ተሸጋግሯል።

አንዳንድ ለሥራና ለዜጎች መብትና ነጻነት እንቅፋት የሆኑ ሕጎች ማለትም የበጎ አድራጎትና የማህበራት አዋጅ፣ የጸረ ሽብር አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነጻነት አዋጅ ለማሻሻል የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩ እንዲሁ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው።

አንዳንድ በመንግሥት ይዞታ ስር የነበሩ መንግሥታዊ ተቋማት በከፊል ወደግሉ ዘርፍ እንዲዛወሩ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ የተላለፈው ውሳኔ በብዙዎች ዘንድ በአዎንታ የታየ ነው።

ጠ/ሚኒስትሩ ባለፉት ሶስት ወራት ላደረጓቸው ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች ሕዝብ አደባባይ ጭምር በመወጣት ዕውቅና ሰጥቷል፣ አመሰግኗል።

ይህም ሆኖ ግን ይህ ለውጥ የጎረበጣቸው አንዳንድ ወገኖች እዚህም እዚያም ቅሬታቸውን ከማሰማት አልፈው ብጥብጥና ሁከት ለማቀጣጠል በመሞከር ላይ መሆናቸውን መንግስት ገልጿል። አንዳንዶቹ በሕግና በሥርዓት የተመረጠን መሪ በይፋ፣ በአደባባይ የመዝለፍና የማዋረድ ተግባር ውስጥ ገብተው መታየታቸው አሳዛኝ ነው። መቃወም መብት ቢሆንም የአንድን አገር ጠ/ሚኒስትር ስብዕናና ክብር በሚያጎድፍ መልኩ መቀስቀስና መግለጫ መስጠት በሕግ የሚያስጠይቅ የወንጀል አድራጎት ነው።

እናም እንደ አገር መከባበር፣ ጥሩ ለሠራ በአግባቡ ዕውቅና መስጠት ቢቀድም ሁሉንም ወገን አትራፊ መሆን ያስችላል፤ በሕዝብ ዘንድም ያስከብራል።¾

 

ደራሲ ደሳለኝ ስዩም በ61 ብር ለገበያ ያቀረበው እህ’ናት ወይም የሀፍረት ቁልፍ በያዝነው ሳምንት ለንባብ በቅቷል።

ደራሲና ጋዜጠኛ ደሳለኝ ስዩም ከዚህ ቀደምም ሌሎች መጽሃፍትን ለአንባቢያን ያቀረበ ሲሆን ይህ በሶስት ክፍሎች የተከፈለና 196 ገጾችን የያዘ ነው። የአጻጻፍ እንግድነት የሚታይበትና የስነ ፅሁፍ አዋቂዎችን ቀልብም የሚስብ እንደሆነ ደራሲው አስታውቋል።

 

በይርጋ አበበ

የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችንና የመጅሊስ አባላትን በጽ/ቤታቸው ያነጋገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነ የመጅሊስ ምርጫ እንዲካሄድ ወሰኑ፡፡

 

የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባሉ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ መሀመድ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለጹት ከመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች፣ ከመጂሊስ እና ከምሁራን የተውጣጣ የምርጫ አመቻች ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተባባሪነት በትናንትናው ዕለት ተዋቅሯል፡፡

 

በዚሁ መሰረትም በሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በኩል ኡስታዝ አቡበከር አህመድ መሀመድ፣ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል እና ኡስታዝ ሸምሰዲን ሰይፉ   ሲመረጡ፤ በመጅሊስ በኩል ደግሞ ሼህ ሀጂ ኡመር፣ ፕሬዝዳንቱ ሼህ መሀመድ አሚን እና ሼህ ሃጂ ከድር ተመርጠዋል፡፡ ከዚሁ ኮሚቴ ጋር አብረው እንዲሰሩ የተመረጡት ገለልተኛ አባላት ደግሞ ዶክተር መሀመድ ሀቢብ፣ ዶክተር እድሪስ መሀመድ እና ሼህ መሃመድ ጀማል አጎናፍር በኮሚቴው ተካተዋል፡፡

 

እንደ ኡስታዝ አቡበከር ገለጻ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አሰባሳቢነት የተመሰረተው ኮሚቴ ነጻና ገለልተኛ መጅሊስ ለመምረጥ ጥናት እንዲሰሩና የጥናታቸውን ውጤትም አቅርበው የመጅሊሱ ምርጫ በፍጥነት እንዲካሄድ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ‹‹የሙስሊሙ ችግር የእኔ የሚለው ጠንካራ ተቋም አለመኖሩ ነው›› ያሉት ኡስታዝ አቡበከር፤ አሁን የተመረጠውን እና እውቅና የተሰጠውን ኮሚቴ የሚያደናቅፍ ማንኛውም አካል በመንግስት ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል፡፡

 

ኡስታዝ አቡበከር የሙስሊሙ ማህበረሰብ አሉት ያሉትን ችግር ሲገልጹም ‹‹ሙስሊሙ ማህበረሰበብ እንደ ዜጋ በዚህች አገር እድገትና ብልጽግና የራሱን ሚና እንዲጫወትና የድርሻውን እንዲወጣ የሚያስተባብር፤ ህዝብ የመረጠው መሪ ማጣቱ እየከፋፈለ እና እየለያየ ሙስሊሙን ማህበረሰብ አዳክሞት ቆይቷል›› ብለዋል፡፡ ኡስታዝ አቡበከር አያይዘውም ‹‹ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ግልጽ የሆነ የመንግስት ጣልቃ ገብነት በመኖሩ ተቋሙ ነጻ ሆኖ ህዝብን ከማገልገል ይልቅ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ሆኖ በመቆየቱ ነው ተቃውሞ ይዘን የተነሳነው›› ብለዋል፡፡

 

በይርጋ አበበ

 

ደራሲ በሐይሉ ገብረእግዚአብሔር ከዚህ በፊት ‹‹ኑሮ እና ፖለቲካ›› የሚሉ ባለ ሶስት ቅጽ መጽሃፍት ለአንባቢያን ያቀረበው ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ነው። ከኑሮና ፖለቲካ ቀደም ብሎ ደግሞ ‹‹እኔም ልረሳው ተቃርቤያለሁ›› የሚለውን ‹‹መንታ መልኮች›› የተሰኘ የአጭር ልቦለድ ስብስብ መጽሃፍ በ1997 ዓ.ም አሳትሟል።

በእነዚህ ስራዎቹና ከተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ በአምደኝነት በሚጽፋቸው ‹‹የወግ›› ጽሁፎች የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለያዩ መድረኮች ተጋብዞ የሚያቀርባቸው ወጎችም ታዳሚያንን እየቆነጠጡ አስተማሪዎች ናቸው። ይህ ወጣት ደራሲም በቅርቡ ‹‹ፖለቲካ አልወድም እና ሌሎችም›› የተሰኘ የወግ ሲዲ ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት ላይ ነው። በቅርቡ (ምናልባትም በቀጣዮቹ ሁለት ሶስት ቀናት) ለገበያ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ አዲስ የወግ ሲዲ ዙሪያ ጸሀፊው ለሰንደቅ ጋዜጣ አጠር ያለ ቃለ ምልልስ ሰጥቷል።

 

 

የሲዲው እሳቤ

‹‹ፖለቲካ አልወድም እና ሌሎችም›› በውስጡ ሰባት ወርደ ሰፊ የወግ ጽሁፎችን ያካተተ ሲሆን ሁሉንም ወጎች አድምጦ ለመጨረስ 1፡20 ይወስዳል። ሃሳቡ እንዴት ተጸነሰ ለሚለው ጥያቄ አጠር ያለ ምላሽ የሰጠው ደራሲ በሀይሉ ‹‹በተለያዩ መድረኮች ላይ ያቀረብኳቸው ወጎች ነበሩ። እነዛን ወጎች አድማጮች ስለወደዷቸውና ለሰፊው ህዝብም መድረስ ስላለባቸው ዋጋው አዋጭ ባይሆንም በህዝብ ጥያቄ እንዲታተሙ ሆነዋል›› ብሏል።

ከዚህ በፊት ግጥሞች እንጂ ወጎች በሲዲ ሲታተሙ አይታወቅም። በዚህ ጉዳይ ላይ ሲናገርም ‹‹ከእኔ በፊት በእውቄ (በእውቀቱ ስዩም) ስራዎቹን በሲዲ አቅርቧል ጊዜው ረዘም ስላለ ተዘንግቶ ይሆናል እንጂ። ከበእውቄ በተጨማሪም ደረጀ በላይነህ እንዲሁ ስራዎቹን በሲዲ አሳትሞ ለአድማጭ አቅርቧል። እኔ እስከማውቀው የእኔ ሲዲ ሶስተኛ መሆኑ ነው›› ሲል ተናግሯል። ሆኖም የሲዲ ስራ አድካሚ እንጂ አትራፊ አለመሆኑን ይናገራል።

ፖለቲካ እና በሀይሉ

በቅርቡ ስልሳ ደራሲያን በጋራ ባሳተሙት ‹‹ደቦ›› የተባለ የጋራ መጽሀፍ ላይም ‹‹ከምር ፖለቲካ አልወድም›› ሲል አንድ ጽሁፍ አሳትሟል። ደቦ ላይም ሆነ በግሉ ያሳተማቸው ሶስት መጽሃፍት እና አንዲሱ ሲዲ ላይ ፖለቲካን ያካተቱ ናቸው። ከፖለቲካ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ወጣት ነህ ወይ? ስንል ጠይቀነው ሲመልስም፤ ማንም ሰው ከፖለቲካ ውጭ እንደማይሆን ገልጾ፤ ‹‹ኑሮ በፖለቲካ፤ ፖለቲካም በኑሮ ይገለጻሉ። ከዚህ በተጨማሪም ቀደም ሲል እንደ አዲስ ጉዳይ የመሳሰሉና አሁን ደግሞ ግዮን የመሳሰሉ መጽሔቶች ጋር አብሬ መስራቴ ከፖለቲካው ጋር እንድቆራኝ ሊያደርገኝ ችሎ ይሆናል እንጂ ማንም ከፖለቲካ ውጭ አይደለም። የመጽሔቶቹና ጋዜጦቹ ተጽእኖ ታይቶብኝም ይሆናል›› ይላል።

ከዚህ ቀደም ኑሮና ፖለቲካ በሚለው መጽሀፉ ላይ ‹‹መዋጮ መዋጮ ›› ሲል አንድ መታጥፍ አቅርቦ ነበር። አሁንም በአዲሱ ሲዲው በመንግስት መዋጮ ከሚጠየቅባቸው መስኮች አንዱ የሆነውን ‹‹ኮብል ስቶንን›› የተጠቀመ ሲሆን የሲዲውን ስዕል ትርጉም እንዲነግረን ላቀረብንለት ጥያቄ መልሱን በቀጥታ ከማቅረብ ይልቅ ‹‹ጊዜ እና አድማጭ ይፍታው›› ሲል በአጭሩ መልሷል።

ልማት የተረጋጋ ፖለቲካ ለጸብራቅ ሲሆን በበሀይሉ ‹‹ፖለቲካ አልወድም›› ሲዲ ላይ የሰፈረው የኮብል ስቶን ምስልም ጥራቱን ለተመለከተ ‹‹የኮስሞቲክስ ፖለቲካ ውጤት›› የሆነውን የመንግስትን ‹‹ስንኩል›› የልማት ስራ ለማሳየት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ሆኖም ደራሲው የስዕሉን ትርጓሜ ለመግለጽ ፍላጎት አላሳየምና ‹‹ትርጉሙ ይህ ሊሆን ይችላል›› የሚባለው ከደራሲው ፈቃድና እውቅና ውጭ ነው።

በይርጋ አበበ

 

በኢትዮጵያ እና ሱዳን አዋሳኝ ድንበር በሆነው የጎንደር ምዕራባዊ ዞን መተማ ከተማ አካባቢ በተነሳው ግጭት ሰዎች መሞታቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዘላለም ልጃለምን ዋቢ አድርጎ የአማራው ክልል መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።

ግጭቱ የተፈጠረው ትናንት ማለዳ ሲሆን የግጭቱ ምክንያትም የእርሻ መሬት መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው መናገራቸው ተገልጿል። በግጭቱ እስከ ትናንት አመሻሽ ድረስ በኢትዮጵያዊያን በኩል ሁለት አርሶ አደሮች የሞቱ መሆኑን አስተዳዳሪው ተናግረዋል። ከግጭቱ በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቦታው መግባቱ ተገልጿል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘላለም ልጃለም እንደገለጹት የእርሻ መሬቱን ለረጅም ዓመታት እየተጠቀሙበት የሚገኙት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ናቸው። አሁን ግን የሱዳን አመራሮች ‹‹የእርሻ መሬቱን መጠቀም ያለብን እኛ ነን››  የሚል ሀሳብ አቅርበዋል። ሃሳቡ ተገቢነት የሌለዉ መሆኑንም ለአካባቢዉ የሱዳን አመራሮች አስረድተናል ነው ያሉት አቶ ዘላለም። የሱዳን አመራሮች ግን ሃሳቡን ባለመቀበላቸዉ መግባባት እንዳልተቻለ አቶ ዘላለም ጨምረው ተናግረዋል። ግጭቱ የተከሰተዉ በመተማ ወረዳ ደለሎ ቁጥርየእርሻ እና የኢንቨስትመንት ቦታ እና በሱዳን ባሶንዳ ዞን መካከል በሚገኝ ቦታ ነዉ።

የሰንደቅ ምንጮች ከቦታው ባደረሱን መረጃ እንደገለጹት ደግሞ በአካባቢው በተደጋጋሚ ጊዜ ተመሳሳይ ግጭት ሲፈጠር የቆየ ቢሆንም የአሁኑ ግን ካለፉት ጊዜያት በተለየ እና በተቀናጀ መልኩ የተከፈተ ጦርነት ይመስላል ብለዋል።  

ጉዳዩን ለማጣራት ወደ አማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ደውለንላቸው ነበር። ሆኖም አቶ ንጉሱ ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አልቻልንም።

በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ጠቅላይ ሚኒስት ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ካርቱም አቅንተው ከፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ጋር የመከሩት ከወራት በፊት ነበር። ፕሬዝዳንት አልበሽርም አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራት ግንኙነት ሰላማዊና ሁለቱንም አገራት ተጠቃሚ በሚደርግ መልኩ እንደሚሆን ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረውም ነበር።

Page 6 of 229

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1010 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us