You are here:መነሻ ገፅ»arts»news admin - Sendek NewsPaper
news admin

news admin

ቁጥሮች

Wednesday, 22 March 2017 12:26

በ2009 ዓ.ም የዕለት ደራሽ እርዳታ

598 ሚሊዮን ዶላር        ለምግብ ነክ የሚያስፍልገው ወጪ፤

 

350 ሚሊዮን ዶላር        ምግብ ነክ ላልሆኑ አቅርቦቶች የሚያስፍልገው ወጪ፤

 

1 ቢሊዮን ብር            መንግሥት እስካሁን የመደበው ገንዘብ፤

 

                  ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ መጋቢት 8 ቀን 2009 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ወረዳ 1 በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚታወቀው አካባቢ መጋቢት 2 ቀን 2009 ምሽት ላይ የደረሰው የቆሻሻ መደርመስ አሰቃቂ አደጋ የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥትን አሳዝኗል። አደጋው ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ በሀገር ውስጥም በውጪ ሀገርም የሚገኙ ወገኖች ተጎጂዎችን ለመርዳት፣ ለማጽናናት እየተንቀሳቀሱ መሆኑም የሚያስመሰግን ነው። በሌላ በኩል የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ተጎጂ ወገኖችን ለመርዳት በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራ ኮምቴ አዋቅሮ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑም በአዎንታ የሚታይ ነው።

 

ይህም ሆኖ የዕርዳታ አሰባሰቡ ወጥነት ይጎድለዋል። ሁሉም በየፊናው ዕርዳታ ጠያቂና ሰብሳቢ የሆነበትን ሒደት እያስተዋልን ነው። ማህበራዊ ድረገጾችን በመጠቀም በተመሳሳይ ዓላማ የዕርዳታ ጥሪ የሚያቀርቡ ወገኖችም አሉ። እዚህም እዚያም ሰው የአቅሙን በመለገስ ወገኖቻንን በዘላቂነት ለመደገፍ መታሰቡ ቅዱስ ተግባር ቢሆንም በዚህ መካከል አንዳንድ ግለሰቦች ክስተቱን ለግል መጠቀሚያነት እንዳያውሉት መጠንቀቅ ተገቢ ነው።

 

እናም በመንግስትም ሆነ በግል እየተደረጉ ያሉ ዕርዳታ የማሰባሰብ ሒደቶች ተጠያቂነት ባለው መልኩ በቅንጅት ወደሚካሄዱበት አቅጣጫ ሊመጡ ይገባል። ቅንጅቱ ሁለንተናዊ ጥቅም አለው። አንደኛው ዕርዳታው በተበታተነ መልክ እንዳይሰባሰብ ይረዳል። የተገኘውን ሐብት በቁጠባና ለትክክለኛ ዓላማ ለመጠቀም ቅንጅቱ የተሻለ አማራጭ ነው። ከተአማኒነትም አንጻር ያለው ዋጋ የትየለሌ ነው። ለዚህ በጎ አድራጎት ተግባር የሚንቀሳቀሱ አካላትም በቅንጅት መስራት ትክክለኛ አማራጭ መሆኑን በመረዳት በተናጠል የሚያደርጉትን ሩጫ ቆም ብለው ሊያጤኑት ይገባል።

ድብርት እንደ ጤና ቀውስ

Wednesday, 22 March 2017 12:20

 

ዮሴፍ አለሙ 
  
ድብርት /depression/ በአለማችን ቀዳሚ በሚባል ደረጃ  ጤናን በማጉደልና በጤና ላይ  እክል በመፍጠር  አሁን አሁን ከቁጥጥር  ውጭ እየሆነ የመጣ አስከፊ የጤና ውጥረት መሆኑን ዩናይትድ ኔሺን የአለም የጤና ድርጅት ኢጀንሲ እንደፈረንጆች አቆጣጠር  የካቲት 14፣ 2017 ዓ.ም  በጥናታዊ  ዘገባዉ ገለፀ።
ጥናታዊ ዘገባውን መሰረት በማድረግ   በፕላኔታችን ላይ ከ300 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች  የድብርት ሰለባ  መሆናቸውን ኤጄንሲው በዘገባው ላይ  በጥናት የተደገፈ ግምቱን አስቀምጧል፤  ይህ ማለት ኤጄንሲው በዘገባው ላይ እንደ ሚያሳየን ከ4.4 በመቶ በላይ የሚሆነው የአለም ህዝብ የድብርት እክል እስረኛ  መሆኑን በቀላሉ መገመት ይቻላል፤  ከዚህም ውስጥ  ሴቶች፣ ወጣቶችና ሽማግሌዎች  ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚሼፍኑ ጥናታዊ ሪፖርቱ ይጠቁማል።


በየአመቱ  ደግሞ ከ800 ሺ  ያላነሱ ሰዎች በድብርት እክል እራሳቸውን ይገድላሉ እንደ  ዩናይትድ ኔሽን የአለም የጤና ድርጅት ጥናታዊ ዘገባ መሰረት። ከእነዚህም ውስጥ  ወሳኝ ቁጥር ያላቸው ሟቾች  ከ15 እስከ 29 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አዋቂ ወጣቶች ናቸው። ከ2005-2015 የድፕሬሺን ሕመምተኞች ቁጥር 18 በመቶ እድገት ማሳየቱን ጥናታዊ ሪፖርቱ አክሎ ይገልፃል።


በፕላኔታችን ላይ የደቡብ ምስራቅ ኤዥያና የምራባዊ ፓስፊክ ክልሎች የመጄመሪያዎቹ የድብርት በሽታ ተጠቂዎች መሆናቸዉን  ኤጄንሲው  በጥናቱ  ያሳያል፦ ደቡብ ምስራቅ ኤዥያ 27 በመቶ እና የምዕራብ ፓስፊክ አገሮች ደግሞ 21 በመቶውን በመሸፈን  አንደኛና ሁለተኛ የድብርት ተጠቂዎች መሆናቸውን የጤና ኤጄንሲው በስዕል አስደግፎ ዘገባዉ ላይ አስቀምጦታል። እንዲሁም  የምስራቅ ሜዲትራኒያን ክልል 16 በመቶ፣ የአሜሪካ ክልል 15 በመቶ፣ የኢሮፕ ክልል12 በመቶ እና አፍሪካችን ደግሞ  9 በመቶ በመሸፈን ከ3 እስከ 6 ባለው ደረጃ የድብርት እክል ተጠቂዎች መሆናቸውን  ይህ ጥናታዊ ዘገባ ያሳያል።


ድብርት /የአእምሮ እክል/ ከማህበረሰቡ ጋር በሚፈጠሩ ውስብስብ  ግንኙነቶች፣ ስነ-ልቦናዊ በሆነ ክፍተት እንዲሁም ተፈጥሮአዊ  በሆነ ምክኒያት ሊከሰት እንደሚችል ዘገባው ይጠቁማል።
ድብርት ህይወታችንን እለት እለት ከሚፈታተኑት  ለአጭር ጊዜ ከሚሰማን የስሜቶች  ወከባ  እንዲሁም ሙድ/mood /ብለን በተለምዶ ከምንጠራው  የሙድ መለዋወጥ ጋር የተለየ መሆኑን ሪፓርቱ ይጠቅሳል። የድብርት  ተጠቂዎች ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሀዘንና መከፋት  ወይንም ደግሞ ደስታ ሊፈጥሩ በሚችሉ ነገሮች ላይ ፍላጎት ማጣትና የቀን ተቀን የህይዎት ተግባሮቻቼው ላይ  ፍሬ እንዳይኖራቼው ግዴለሾች እንዲሆኑ  ዋነኛዎቹ የድብት ምልክቶች ናቼው እንደ ኤጄንሲው ዘገባ።


የፊታችን መጋቢት ላይ ከሚከብረው አለም አቀፋዊ የጤና ቀን አስቀድሞ በወጣው በዚሁ ሪፖርት መሰረት የበሽታው  ስርጭት በአዋቂዎች ላይ በተለይ ደግሞ የ60 አመት ጎልማሶች ላይ ፈጣን በሚባል ሁኔታ ማንሰራራት  መቻሉንና አስከፊ በሚባል መጠን እያደገ ቢመጣም  በህፃናቱም ላይ  መታየት መጀመሩን  ሪፖርቱ ይገልፃል።ድፕሬሺን ለረጅም ጊዜ ከቆየና  መካከለኛ  ኦር በጣም አደገኛ የሚባል ደረጃ  ላይ ሲደርስ ጤናን በአስከፊ ሁኔታ በመበጥበጥ  አልፎም እራስን አስቶ እስከማጥፍት ይጋብዛል።


ድብርት በዋናነት ከሶስት ነገሮች  ሊመነጭ እንደሚችል፦ ከማህበራዊ፣ ከስነ -አእምሮአዊ ቀውስ እንዲሁም በተፈጥሮአዊ ምክኒያቶች ሊከሰት እንደሚችል፤ በተጨማሪም ድብርት በበሺተኛው ላይ ብዙ የአእምሮ  ጭንቀትን /more stress /በመፍጠር  በሽተኛው የመኖር ተስፋ እንዲያጣና  ፈፅሞ  የበሽተኛውን ህይዎት በማበላሸት አስከፊ መሆኑን  ዩናይትድ ኔሺን የአለም የጤና ድርጅት/  WHo/ በዘገባው አክሎበታል።
ድፕሬሺንን ለመቀነስ  ትምህርትን መሰረት ያደረገ  ዝግጅት በመቅረፅ  ስለበሺታው አስከፊነት፣ መንስኤውን፣ የበሽታውን ፀባይና ምልክቱን እንዲሁም መከላከል የሚቻልበትን ዘዴ ለህብረተሰቡ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠትና ሙያተኞች ታች ወርደው ከህብረተሰቡ ጋር የልምምድና የትግበራ ጊዜ እንዲኖራቸው  በማድረግ ይልቁንም የማያቊርጥ ሙያዊ ድጋፍና የክትትል  ዘመቻ በማድረግ በሽታውን መግታት እንደሚቻል  ዩናይትድ  ኔሺን  ኤጄንሲ  ጥናታዊ እይታውን አስቀምጧል።


ብዙ አይነት የስነ - አእምሮአዊ ቀውስ ክብካቤ እንዲሁም ከተለያየ የስነ-ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚወለዱ ችግሮች ከመፍትሄአቼው ጋር በዚሁ ሪፖርት ተጠቅሷል። የጤና አምራች ድርጅቶችም  ልዩ ልዩ የስነ-ልቦ /psychology/ እና የስነ-አእምሮ /psychiatry / ምዘናና ክብካቤዎችን በድብት ተጠቂ ለሆነው ማህበረሰብ  ማቅረብ አለባቸው ሲል ዩናይትድ ኔሺን ኤጄንሲ በጥናታዊ ሪፖርቱ ያሳስባል።
በጤናው ዘርፍ እየሰሩ ያሉ  ኦር  እሰራለው የሚል መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የሚከተሉትንና ሌሎችንም  የስነ-አእምሮ ክብካቤ ላይክ


- የቢሄቤራል አክሺን /  Behavioural  Action/
- የኮግኒቲቭ  ቢሄቤራል ቴራፒ /Cognitive Behavioural therapy --CBT/
- የኢንተርፐርሰናል ሳይኮ ቴራፒና/Interpersonal Psychotherapy ...IPT/
- የአንቲ ዲፕረሳንት ሚዲኬሺን/ Antidepressant Medication / ለተጎጂ በሺተኞች ማቅረብ ሀላፊነታቼውም እንደሆነ ኤጄንሲው  በዘገባው ላይ ጥሪ  አድርጒል።
ነገር ግን ከምርመራ ውጤቶች መካከል   የአንቲ ዲፕሬሳንት  /antidepressant/   ህክምናዎች       ለህፃናት መስጠት እንደማይፈቀድና  ለጎረምሶችና ለኮረዶችም ቢሆን አፋጣኝ  በሚባል መልኩ ይህ አይነቱን ህክምና መስጠት  እንደማይቻል ጥናታዊ ሪፖርቱ  ያስጠነቅቃል ።ምክኒያቱ ደግሞ በታዳጊ ህፃናት ላይ እንዲሁም በታዳጊ ወጣቶች  ላይ የፀባይ ለውጥ በመፍጠር በእድገታቼው ተፅኖ ሊያደርግ ይችላል  ሲል ኤጄንሲው ይጠቁማል።
በተጨማሪም እንደዚህ የመሳሰሉ ፈት ለፈት  በግልም ሆነ በቡድን የሚሰጡ የስነ-አእምሮአዊም ሆነ የስነ-ልቡና  ክብካቤ ህክምናዎች /psychiatry  or psychological treatments/ መሰጠት ያለባቼው በዘርፉ ላይ በተካኑ ባልሙያዎች እንዲሁም ወሳኝ ክትትልና ሙያዊ ድጋፍን መሰረት ባደረገ የሀኪሞች  እገዛ መሆን እንዳለበት የአለም የጤና ድርጅት  በጥናታዊ ዘገባው ያሳስባል።¾

 

·         ሆስፒታሉ፣ የሜዲካል እና የነርሲንግ ዩኒቨርስቲን ያካትታል፣

·         ታሪክን ያንጸባርቃል፤ ሥነ ምኅዳርን የሚጠብቅ ቴክኖሎጂ ይጠቀማል፣

·         ለሀገሪቱ የሕክምና ቱሪዝም ፍሰት አስተዋፅኦ ያደርጋል፣

 

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ “ተዋሕዶ ዲፕሎማቲክ ሜዲካል ሲቲ” የተሰኘ ኹለገብ የሕክምና ማዕከል፣ በ400 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚገነባ ያስታወቀ ሲኾን፤ የፕሮጀክት ስምምነቱንም፣ ሌጀንደሪ ሜጋኮርፕ ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋራ መፈራረሙን ገለጸ።

 

ስለ ፕሮጀክቱ ስያሜና ሒደት ማብራሪያ የሰጡት የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ የመግባቢያ ሰነዱን ከድርጅቱ ጋራ ለመፈራረም፣ የተለያዩ የጥናት ሥራዎች መሠራታቸውንና የቦታ መረጣም መካሔዱን ጠቅሰው፤ የፕሮጀክቱ ስያሜም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና ባሕርይ በአገናዘበ መልኩ የተሰጠ መኾኑን፣ ስምምነቱ በኮሚሽኑ አዳራሽ በተፈረመበት ወቅት ገልጸዋል።

 

በይዘቱ፣ በጠቀሜታውና በፋይናንስ ረገድ ግዙፍና በደረጃውም የዓለም የጤና ድርጅትን መስፈርት በማሟላት ተግባራዊ እንደሚኾን የጠቆሙት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር አግደው ረዴ፥ በዓለም አቀፍ ጨረታ አሸናፊ ከሚኾነው ድርጅት ጋራ፣ በመጪው ሚያዝያ ወር የግንባታ ውል ከተፈጸመ በኋላ፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጸሎትና ቡራኬ የመሠረት ድንጋዩ እንደሚቀመጥ አስታውቀዋል።

 

ኹለገብ የሕክምና ማዕከሉ፥ በአዲስ አበባ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ፣ በእንጦጦ ተራራ ላይ በሚገኝ 210ሺሕ ካሬ ሜትር አጠቃላይ ስፋት ባለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ቦታ ላይ ነው፣ የሚያርፈው። ከእዚኽም ውስጥ፣ በ67ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ በአንድ ጊዜ 600 ሕሙማንን አስተኝቶ ማከም የሚያስችል ዘመናዊ ሆስፒታል፤ በ28ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ፣ የሜዲካል እና የነርሲንግ ዩኒቨርሲቲ ሕንጻዎች እንደሚገነቡ፣ ኮሚሽነር ዶ/ር አግደው አስረድተዋል፤ ድጋፍ ሰጭ ኾነው የሚያገለግሉ የአስተዳደር ሕንጻዎች፣ የውስጥ ለውስጥ መሠረተ ልማቶች፣ የመንገድ፣ የሜካኒካል፣ የአይሲቲ ሥራዎችን እንደሚያጠቃልልም ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልጸዋል። 

 

የሌጀንደሪ ሜጋኮርፕ ድርጅት ተወካዮች በበኩላቸው፣ “ሀገሪቱን ከምትወክለው ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ጋራ በትብብር ለመሥራት እዚህ ደረጃ በመድረሳችን ትልቅ ኩራትና ክብር ይሰማናል፤” ብለዋል። የፕሮጀክቱ ግንባታም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊ ታሪክ፣ ባህልና ትውፊት እንደሚያካትትና የአካባቢውን የዕፀዋትና ደን ሥነ ምኅዳር የሚጠብቅ ትልቅ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም መኾኑን አስረድተዋል።

 

በግንባታው ወቅት በጊዜአዊነት 10ሺሕ800 ለሚኾኑ ሰዎች አዲስ የሥራ ዕድል ሲከፍት፣ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ደግሞ፣ ለ5ሺሕ ያህል ባለሞያዎች፣ በቋሚነትና በኮንትራት ተጨማሪ የሥራ መስክ በማስገኘትና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመደገፍ የራሱ የኾነ ሚና ይኖረዋል፤ በትምህርቱም ዘርፍ፣ በየዓመቱ ለመቶ ያህል የሜዲካልና ከ200 በላይ ለሚኾኑ የነርሲንግ ተማሪዎች የትምህርት ዕድል በመክፈት ለማኅበረሰቡ የላቀ አገልግሎትና የተሻለ ሕክምና የሚሰጥ የተማረ የሰው ኃይል እንደሚያፈራ ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፤ አያይዘውም፣ ሀገሪቱ፣ የሕክምናውን ሞያ ከሥነ ምግባሩ ጋራ የተካኑ ዶክተሮችን እንድታፈራ በማስቻል፣ ለሕክምና ቱሪዝም ፍሰት አስተዋፅኦ ያደርጋል፤ ብለዋል ኮሚሽነሩ።

 

በመሪ ዕቅዱ መሠረት፥ አምስት የግንባታ ምዕራፎች ያሉት ፕሮጀክቱ፣ የቁፋሮ ሥራው በቀጣዩ ዓመት ኅዳር 2010 እንደሚጀመርና በአምስት ዓመታት ለማጠናቀቅ መታቀዱ የተመለከተ ሲኾን፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም፣ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አማካይነት የላቀና ዘመኑን የሚዋጅ ማኅበራዊ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችላት ተገልጿል። 

በይርጋ አበበ

ላለፉት 70 ዓመታት በመንፈስ የጠነከሩ ወጣቶችን በማፍራት ለአገራቸው ጠቃሚ ዜጋ እንዲሆኑ ሲሰራ የቆየው የወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ) በኢትዮጵያ ስራ የጀመረበትን 70ኛ ዓመት ሊያከብር መሆኑን ገለጸ። የአፍሪካ ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበርም 40ኛ ዓመት የምስረታ በአሉን በአዲስ አበባ ያከብራል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር በ12 ጽ/ቤቶች በመታገዝ በስነ ተዋልዶ ጤና፣ በስፖርት፣ በትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በስራ ዝግጅት ለበርካታ ወጣቶች አገልግሎት መስጠቱን የገለጸ ሲሆን መግለጫወ አያይዞም “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ በኬኒያ ናይሮቢ የሚገኘው የአፍሪካ ወወክማ ህብረት ጽ/ቤት አዲስ አበባ እንዲከፈት እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል። የአፍሪካ ወወክማ 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉንም ከኢትዮጵያው ወወክማ ጋር ለማክበር ስምምነት ላይ ተደርሷል” ሲል አስታውቋል። የማህበሩ 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የሚከበረው በጊዮን ሆቴል መሆኑን ያስታወቀው መግለጫው የፊታችን ዓርብ ደግሞ የበዓሉ መክፈቻ እንደሚሆን አስታውቋል።

ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር እኤአ በ1844 በእንግሊዝ አገር የተመሰረተ ሲሆን ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ለዓለም አቀፉ የወወክማ ማህበር ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ድርጅቱ በ1938 ዓም በኢትዮጵያ በይፋ ስራ መጀመሩን ወወከማ ኢትዮጵያ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አስታውቋል።¾ 

 

ተሸከርካሪዎችን ወደ ሀገር ማስገባት የሚችሉት እነማን ናቸው?

-    በተሽከርካሪ አስመጪነት የንግድ ፍቃድ ያላቸው በዘርፉ የተሰማሩ አስመጪዎች፤

-    በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሽከርካሪ ማበረታቻ የተፈቀደላቸው ኢንቨስተሮች፤

-    በውጭ ሀገር ከ5 ዓመት በላይ ኖረው ጠቅልለው ወደ ሀገር ተመላሽ የሚሆኑ ዲያስፖራዎች ወይም ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመኖር የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎች/እነዚህ ማስገባት (ማስመጣት የሚችሉት አንድ የግል መገልገያ አውቶሞቢል ብቻ ነው/።

የአንድ ተሽከርካሪ ቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ እንዴት ይተመናል?

የመኪና ቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ የሚተመነው በመኪናው የሲ.ሲ መጠን፣ መኪናው በተመረተበት ጊዜ እና መኪናው በተገዛበት ዋጋ ነው። እነዚህን ሶስት መተመኛዎች ከዚህ እንደሚከተለው ቀርበዋል።

 

 

1.      የሲ.ሲ መጠኑን መሠረት በማድረግ

ይህ የተሽከርካሪውን የሞተር ጉልበት/ የሲሊንደር አቅም/ መሠረት ያደረገ ነው።

1.1.    የተሽከርካሪው የሲሊንደር ዘይት ከ1300 ሲ.ሲ በታች ከሆነ

-    ተገጣጥሞ የሚገባ ያለቀለት 125.0075%

-    ለመገጣጠም የሚገባ 59.975%

1.2.    የተሽከርካሪው የሲሊንደር ይዘት ከ1300- 1800 ሲ.ሲ ከሆነ

-    ተገጣጥሞ የሚገባ ያለቀለት 176.24%

-    ለመገጣጠም የሚላክ 96.2%

1.3.    የተሽከርካሪው የሲሊንደር ይዘት ከ1800 በላይ ከሆነ

-    ተገጣጥሞ የሚገባ ያለቀለት 244.55%

-    ለመገጣጠም የሚላክ 100.05

2.      ለማነፃፀሪያ ሲባል አንድ ዓመት ወደፊትና ወደኋላ የሆነ የምርት ዘመን ማለት ነው።

ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ሲገቡ የእርጅና ቅናሽ ከተሽከርካሪው የምርት ዘመን በመነሳት እስከ ሶስት ዓመት መጨረሻ ድረስ ከፎብ /Free on Board ore FOB/ ላይ በየዓመቱ የሚደረግ የ10 በመቶ ቅናሽ ሲሆን ቅናሹ ከ30 በመቶ አይበልጥም

 

ተሽከርካሪው ከተመረተበት ቀን ጀምሮ የሚደረገው የእርጅና ቅናሽ

የቆየበት የአገልግሎት ዘመን በመቶኛ

ከአንድ ዓመት በታች             0%

አንድ ዓመት                    10%

ሁለት ዓመት                    20%

ሶስት ዓመትና ከዚያ በላይ         30%

ይህ በአንቀጽ የተደነገገ ሲሆን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ከተመረቱ በኋላ ምንም አይነት አገልግሎት ወይም ጥቅም ላይ ሳይውሉ ከአንድ ዓመት በኋላ የቆዩ ቢሆንም የእርጅና ቅናሽ ሳይደረግባቸው አዲስ በነበሩበት ጊዜ ያለው ዋጋ የቀረጥና ታክስ ማስከፈያ ዋጋ ተደርጎ ይወሰዳል።

$13.      የተገዛበት ዋጋ

በጉምሩክ ተቀባይነት ሲያገኝ የተገዙበት ዋጋ ላይ በአስመጪ እስከ ኢትዮጵያ መግቢያ በር ድረስ የተከፈሉ/ የሚከፈሉ አጠቃላይ ወጪዎችን በአዋጅ 859/2006 አንቀጽ 96 መሠረት በመደመር እና የተሽከርካሪ የታሪክ ምጣኔን በማባዛት ማስላት ነው።

ሆኖም የተገዙበት ዋጋ (FOB Price) በጉምሩክ ተቀባይነት በሚያገኝበት ጊዜ በመረጃ ተቋም ካለው ተመሳሳይ (አንድዓይነት) ተሽከርካሪዎች ጋር በማነፃፀርያ ዋጋ በመውሰድ ተጨማሪ ወጪዎችን በመደመርና ከታሪፍ አመዳደቡ ጋር በማነፃፀር የተገኘውን ውጤት ባለው ወቅታዊ የውጭ ምንዛሬ ቀረጥና ታክሱን ማስላት ይቻላል።

ተሽከርካሪዎች የዋጋ አተማመን ስሌት

1.  ለአዲስ ተሽከርካሪዎች (For new car)

Duty paying value = FOB + Freight + insurance + other cost 

2.  ላገለገሉ ተሽከርካሪዎች (For used car)

DPV = (FOB - depreciation) + Freight + insurance + others

ተጨማሪ ክፍያዎች በተጨባጭ መረጃ እና ማስረጃ ሊተመኑ ካልቻሉ በአዋጁ አንቀጽ 96 በተደነገገው መሠረት በሚከተሉት ሁኔታዎች በማስላት በቀረጥና ታክስ ማስከፈያ ዋጋ ይካተታሉ።

የትራንስፖርት ወጪ /Freight/ = 5% of FOB value

የኢንሹራንስ ወጪ /insurance/ + 2% of FOB value

መግለጫ

ያገለገሉ ተሽከርካሪ የምንለው በተመረተበት የምርት ዘመን በኋላ ጥቅም ላይ የቆየ ባለሞተር ተሽከርካሪ ነው።

የፎብ ዋጋ (FOB price)

ማለት የዕቃው መሸጫ ዋጋ እና በላኪ ሀገር እስከ የመጨረሻ መጫኛ ቦታ (ወደብ) ደረስ ለዕቃው የተከፈለ/ የሚከፈል ወጪ ድምር የሚያመለክት አንዱ የአለም አቀፍ የንግድ ስምምነት ዓይነት (INCOTERM) ሲሆን በመርከብ ለማስጫን፣ በማጓጓዝ፣ ለማራገፍ፣ ለመንከባከብ የወጣ ሲሆን ለኢንቨስትመንትና ሌሎች የሚወጡ ወጪዎችን አይጨምርም።

የሲ.አይ .ኤፍ ዋጋ (CIF price)

ማለት የዕቃው የመጫኛ ዋጋ እና በላኪ አገር እስከ የመጨረሻ ቦታ (ወደብ) ድረስ ለዕቃው የተከፈለ/ የሚከፈል ወጪ፣ የኢንሹራንስ፣ ዕቃውን ለማጓጓዝ የወጣ ወጪ ድምር የሚያመለክት አንዱ የዓለም አቀፍ የንግድ ስምምነት ዓይነት (INCOTERM) ሲሆን እስከ ኢትዮጵያ የጉምሩክ ክልል የመጀመሪያ መግቢያ በር ድረስ ዕቃውን ለማስጫን፣ ለማራገፍ፣ ለመንከባከብ እና ለዕቃው የተከፈሉ/ የሚከፈሉ ሌሎች ተጨማሪ ወጪዎችን ይጨምራል።

ምንጭ፡- ገቢዎና ጉምሩክ ባለሥልጣን

 

ክብርት ወ/ሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ በ1882 ዓ.ም ጥር 21 ቀን ከአባታቸው ከፈ/ጥሩነህ ወርቅነህ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ሰራዊት ተሰማ ወሎ ጠቅላይ ግዛት ደሴ ከተማ ልዩ ስሙ ሸዋበር በሚባል ቦታ ተወለዱ። ከአክስታቸው ጋር በንጉስ ሚካኤል ቤተመንግስት የቤተክህነት ትምህርት እየተማሩ አደጉ። 16 ዓመት ሲሆናቸው ለየጁው ባለበት ለራስ ዓሊ ልጅ ለቀኝ አዝማች ጓንጉል ዓሊ ተዳሩ። በ1922 ዓ.ም ሁለተኛ ባላቸውና ዳ/ማ ዓምደሚካኤል ኃ/ስላሴን በስጋ ወደሙ አገቡ።

ክብርት ወ/ሮ ቀለመወርቅ ጥሩህ ሀገራችን በጠላት ስትወረር የአርሲ ጠቅላይ ግዛትን ያስተዳድሩ ነበር። ባለቤታቸው ወደ ጦር ግንባር ሲዘምቱ እሳቸው ቀሪውን የሀገሬውን ጦር ለጦርነት ያዘጋጁ ነበር። በመጀመሪያ በአርሲ ጠ/ግዛት ላይ የመሸገውን የጠላት ጦር ድል በመምታት አድናቆትን አገኙ። በዚህ የተበሳጨው የጠላት ጦር ገደብ በሚባለው ቦታ በአውሮፕላን የቦንብ ናዳ አወረደባቸው። የያዛችሁት መንገድ አያዋጣችሁም እጃችሁን ስጡ እያለ ዛቻና ማስፈራራት አደረገባቸው። እሳቸው ግን አልተበገሩለትም። በሲዳሞም አደጋ ለመጣል የመጣውን በሰውና በመሳሪያ ኃይል የሚበልጠውን ጦር ድል በማድረግ ለፈጣሪያቸው ምስጋና አቀረቡ። የጠላት ኃይል እየበረታ ስለመጣ ከልዑል ራስ እምሩ ጦር ጋር ለመቀላቀል ጉዞ ወደ ሆሳእና አደረጉ። ነገር ግን የራስ እምሩ ጦር መበተኑን ስለሰሙ ጉዞ ወደ ኮሎ አደረጉ። የሀገሪቱን ሁኔታ ከደ/መርእድ በየነ ጋር ይወያዩ ነበር። ከዚያም የኦሞን ወንዝ ተሻግረው ከጎፋ በገለብ አድርገው የእንግሊዝ ቀኝ ግዛት ወደ ነበረችው ኬንያ ገቡ። ባለቤታቸው ከንጉስ ነገስቱ ጋር ኢየሩሳሌም መግባታቸውን አረጋገጡ። ነሐሴ 12 ቀን 1929 ዓ.ም ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱና ከሳቸው በፊት ከተሰደዱት ጋር ተቀላቅለው አራቱን ዓመት በፆም በፀሎት አሳለፉ።

አገራቸው ነፃ ስትሆን ጥቅምት 5 ቀን 1935 ዓ.ም ወደ ሀገራቸው በደስታ ተመለሱ ወ/ሮዋ ለፈፀሙት ተጋድሎ የአንድ ዓመት የአርበኝነት ባለ አንድ ዘንባባ ኒሻን ሌሎችም ልዩ ልዩ ኒሻኖችና የሴቶች የራስ ወርቅ ከንጉሰ ነገስቱ እጅ ተሸልመዋል። ወ/ሮዋ ደስታን በደስታነቱ መከራውንም እንደ መከራነቱ በትእግስት ቀብለዋል። አባትና እናት የሌላቸው ህፃናትን በማስተማር፣ ጧሪ የሌላቸውን በመደገፍ ድሆችን በመርዳት በጠቅላላው ለበጎ ነገር ቀዳሚ በመሆን ሕይወታቸው አሳልፈዋል። ከብዙ መረጃዎች አንዱ ይህ በስማቸው የሚጠራው ት/ቤት ነው። አንድ ልጅ ሳይኖራቸው የብዙ ሺህ ልጆች እናት ለመሆን በቅተዋል። ክብርት ወ/ሮ ቀለመወርቅ ለሰው ልጅ በተሰጠው ሕግ መሠረት ተራቸው ደርሶ ሰኔ 4 ቀን 1954 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ንጉሱና ንጉሳውያን ቤተሰቦች በተገኙበት በአርበኞች መካነ መቃብር በመንበረ ፀባኦት ቅ/ስላሴ ቤተክርስቲያን የዘለዓለም እረፍት አደረጉ።

የወ/ሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ ት/ቤቱ የእድገት ጉዞ

ዘመናዊ ትምህርት ወደ ሀገራችን ከገባ ጀምሮ እንደ አሁኑ ብዛት ባይኖራቸውም በትልልቅ ከተሞች ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል። ከነዚህም መካከል የወ/ሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ ት/ቤት አንዱ ነው። ይህ ት/ቤት ከመገንባቱ በፊት በተለምዶ ሰሜን ማዘጋጃ ቤት እየተባለ ከሚጠራው በስተምስራቅ ከአስፋልቱ ማዶ ለመማር ማስተማሩ አመቺ ባልሆነ ቦታ በአንድ ግለሰብ ቤት ውስጥ በተጎሳቆለ ቦታ መስፍነሐረር ተብሎ የሚጠራ ከ1ኛ-8ኛ ክፍል የሚሰጥበት ት/ቤት ነበር።

ቦታው ለወ/ሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ መኖሪያ ቤት ቅርብ ስለነበር ሁኔታውን በመመልከት ለማሻሻል ያሰቡበት ይመስላል። በተጨማሪም ወደፊት ስማቸውን የሚያስጠራ ልጅ አለመኖሩ በጣም ያሳሰባቸው ስለነበር ምን ማድረግ እንደሚገባቸው በደንብ አድርገው ያሰቡበት ይመስላል። ለዚህም ነው የግል ቦታቸውን ከነካርታው ወስደው ለንጉስ በስሜ የሚጠራት ቤት ይሰራልኝ በማለት ፈቃድ የጠየቁት። ይህም የግል ቦታን ለወገን ልጆች የመማሪያ ጥቅም እንዲሆን በመስጠት ወ/ሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ የመጀመሪያ እናት ያደርጋቸዋል።

ንጉሱም ጥያቄያቸውን በመቀበል በዘመኑ ወደነበሩት የትምህርት ሚኒስቴር ወስደው እንዲያቀርቡ በመንገር አሰናበቷቸው። በዚህ መካከል ነገሩ ሳይፈፀም ገና በዳዴ ጽናት እያሉ በ1954 ዓ.ም ሐምሌ 4 ቀን ወ/ሮ ቀለመወርቅ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ። ት/ሚ ቦታውን ተረከበ በ1955 ዓ.ም መሰረቱ ተጥሎ ወዲያው በአንድ ዓመት ውስጥ ስለተጠናቀቀ ከ1956 ዓ.ም በጥቅምት ወር ቀደም ሲል በተጠቀሰው ት/ቤት ውስጥ ሲማሩ ከነበሩት ተማሪዎች ከ1ኛ -6ኛ ክፍል ይማሩ የነበሩት ከነመምህራኖቻቸው ወደዚህ ት/ቤት በመምጣት ስራ ጀመሩ።

በጊዜው የነበሩት ተማሪዎች ቁጥር ባይታወቅም በ24 ከፍሎ በእያንዳንዱ ክፍል ከ50 ያላነሱ ተማሪዎች 15 መምህራን እንደነበሩ በወቅቱ በመምህርነት ያገለገሉ የነበሩ መምህራን ይናገራሉ። ቦታው ከዚያን ቀደም ትላልቅና ሰማይ ጠቀስ ዛፎች የበቀሉበት፣ በውስጣቸው ሰዎች የሚተላለፉባቸው ቀጫጭን መንገዶች እንደነበሩባቸው የእድሜ ባለፀጎች ይናገራሉ።

በመቀጠልም ት/ቤቱ በየጊዜው መሻሻሉን አላቋረጠም። ዙሪያው የሽቦ አጥር የነበረው ወደግንብ ተቀይረዋል። የወ/ሮ ቀለመወርቅን መልካም አርአያ በመከተል ወ/ሮ ወለተማርያም የተባሉ እናት ከፍተኛ ገንዘብ ወጭ በማድረግ በስተጀርባ ያለውን ባለ 13 የመማሪያ ክፍሎች ያለው ህንጻ አሰርተዋል። ተፈጥሮ የነፈገቻቸውን የመውለድ ፀጋ በመልካም ስራቸው በሺ የሚቆጠሩ ልጆች እናት ለመሆን በቅተዋል። በዚህ ት/ቤት የተማሩ ከያንያን እና ደራሲያን፣ ዳኞችና ጠበቆች፣ መምህራን፣ ዶክተሮች፣ ፓይለቶች እየሆኑ በልዩ ልዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

በመቀጠልም በ1976 ዓ.ም አንድ ባለ አራት በር ህንፃ ተስርቶ ለዕቃ ግምጃ ቤት ለማእከልና ለተለያዩ ከአገልግሎት ጥቅም ውጭ ለሆኑ ዕቃዎች ማስቀመጫ በመሆን በአገልግሎት ላይ ውሏል። በ1980 ዓ.ም አንድ 12 መቀመጫዎች ያለው የተማሪዎች መፀዳጃ ቤት፣ የኳስ ጨዋታ መመልከቻ ትሪቡን ደረጃ፣ ቤተ መፃህፍት የመሳሰሉት ተሰርተው ከፍተኛ የመሻሻል እድገት አሳይቷል። በ1990 ዎቹ ደግሞ ቀደም ሲል ከነበሩት በተሻለ እያንዳንዳቸው ባለ አንድ ፎቅ የሆነ ሁለት ህንጻዎች ተገንብተዋል። ከነሱም ውስጥ 8ቱ የመማሪያ ክፍሎች ስለነበሩ በጊዜው የነበረውን የክፍል ጥበት ከማቃለላቸውም በላይ የሰባተኛና የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ሙሉ ቀን እንዲማሩ ረድተዋል። ሌሎችም ክፍሎች ቤተመጻህፍትና ልዩ ልዩ አገልግሎት በመስጠት ይገኛሉ።

አሁን ባለንበት ደግሞ G+4 የቤተመፃህፍትና G+4 የሆነ አዲስ መንታ ህንጻ መማሪያ ክፍል ተሰርቷል።

የትምህርት ደረጃዎችን በተመለከተ፡-

በ1955 ዓ.ም ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል /1-6/

በ1976 ዓ.ም መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ሰባተኛና ስምንተኛ /1-8/ ለመሆን ችሏል ወደፊትም ወደ ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ እንደሚያድግ የተረጋገጠ እና ብሩህ ተስፋ የሚታይበት ነው።

የትምህርት ቤቱ ስም ባደረገው የአርባ አራት ዓመት ጉዞ ያለአንዳች ችግር ተጉዞ ከዚህ አልደረሰም። አንድ ጊዜ አንድ ትልቅ ችግር አጋጥሞት ነበር። ይኸውም በ2004 ዓ.ም ወደ ከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ት/ቤትነት አደገ። በ1990ዎቹ ዓመታት በአዲስ አበባ ያሉ ት/ቤቶች አብዮታዊ ስም ሲሰጣቸው ወ/ሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ ትምህርት ቤት የሚለው ስም ተለውጦ አብዮታዊ ስም ይሰጥ የሚሉ ወገኖች ሀሳብ አቅርበው ብዙ ግጭትና ክርክር ከተደረገ በኋላ ለግል ጥቅማቸው ማዋል ሲችሉ በሕይወታቸው እያሉ 18ሺህ /18000/ ካሬ ሜትር የድሆች ልጆች ይማሩበት ብለው በፈቃዳቸው የሰጡ እናት ተራማጅ እንጂ አድሃሪ ሊባሉ አይገባቸውም የሚለው ድምጽ በዝቶ ስለተገኘ ስሙ ከተደቀነበት የመለወጥ አደጋ ሊያመልጥ ችሏል።

 ሰዎች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ያልፋሉ። መልካም ስራ ግን ምንግዜም ከመቃብር በላይ ይኖራል። ታሪክም ሊረሳው አይችልም።

አረጋዊ ገ/ኢየሱስ ወ/ሰናይት

1999 ዓ.ም አዲስ አበባ        

በለውጥ እንደገና መወለድ

Wednesday, 15 March 2017 12:49

ምስጋናው ግሸን ወልደ አገሬ

 

ንስር አሞራ እስከ ሰባ ዓመት በሕይወት የመኖር ጸጋ ተሠጦታል። ነገር ግን ይህን 70 ዓመት የዕድሜ ፀጋን አጣጥሞ ለመኖር አርባኛ ዓመቱ ላይ በሕይወቱ ወሳኝ የሚባል ውሳኔን ማሳለፍ ይጠበቅበታል። ይኸውም ንስሩ አርባኛ ዓመት ዕድሜው ላይ እነዛ ረዥምና እንደልብ የሚተጣጠፉት ጥፍሮቹ እንደ እንጨት ይገራሉ። ስል የነበረው ማቁርቱም ወደ አንገቱ ይታጠፍና ምግቡን አንድኖ እንዳይዝ ያግደዋል። የገረጀፉት ላባዎቹም ከደረቱ ላይ ተጣብቀው የመብረር ሥራውን አስቸጋሪ ያደርጉበታል። በዚህ ወቅት ንስሩ ሁለት ወሳኝ አማራጮች ይጠብቁታል። አንድም ሞትን አሜን ብሎ መቀበል ወይም ደግሞ አንድ መቶ ሃምሳ ቀናት ሚፈጅን ፈታኝ የለውጥ ሂደት ማካሄድን። በለውጡ ሂደት ለማለፍ ከወሰነ ቀጣዮችን ተግባራት መፈጸም ይጀምራል። በመጀመሪያ ንስሩ ከፍ ብሎ ከወጣ ተራራ አለት ላይ ይቀመጥና የታጠፈውን ማንቁርቱንና ጥፍሮቹን  ከአለቱ ጋር ደጋግሞ በመምታት ወልቀው እንዲወድቅ ያደርጋል።

የገረረውና የታጠፈውን ማንቁርት እንዲሁም ጥፍሮቹን አውልቆ ከጣለ በኋላ ከስር የወጣው ሙሽራ ማንቁርትና ጥፍር እስኪጠነክር ድረስ ለቀናቶች ይታገሰዋል። ማቁርቱና ጥፍሮቹ ከጠነከሩ በኋላ ቀጣይ የሚጠብቀው ተግባር የደረቁትና ከደረቱ ጋር ተጣብቀው እንደልብ ከመብረር ያገዱተን ላባዎች እየነጨ በማራገፍ በአዲስ እንዲተኩ ማድረግ ነው። ይህን እልህ አስጨራሽና አንድ መቶ ሃምሳ ቀናት ወይም አመስት ወራት የፈጀውን የለውጥ ጉዞ ካካሄደ በኋላ ዳግም ውልደቱን የሚያበስር ቀጣይ ሰላሳዎቹን ዓመታትም በትኩስ ኃይል መኖር የሚያስችል ለውጥ አደረገ ማለት ነው። በዚህ ሁኔታም የዳግም ውልደቱን በረራ ወደ ሰማይ ተነጥቆ ይጀምራል።

ብዙውን ጊዜ አዳዲስ ክስተቶችን ተገንዝቦና ተላምዶ በለውጡ ተጠቃሚ ለመሆን እልህ አስጨራሹን ለውጥ ሂደትን መታገስ ይጠይቃል። የቆዩና ያፈጁ አስተሳሰቦችን ከእሳቤ ውስጥ ማስወገድ፤ ከቆዩና ኋላ ቀር ልማዶች እራስን ነፃ ማድረግ አሁን የተፈጠረልንን ጥሩ እድል ለመጠቀም ያስችላል። በለውጥ እንደገና መወለድ ማለትም ይኸው ነው።

ምንጭ፡ Story of the Eagle¾

 

በጥበቡ በለጠ

 

ደራሲ ሲጠፋ፣ ደራሲ ሲሠወር አገር ባዶ ይሆናል። እኔም ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ የምገባው ደራሲ ሲጠፋ ነው። ደራሲ ማለት ሐገር ነው። በውስጡ የዚያች ሐገር ሕዝብ' ባሕል' ፖለቲካ አስተሣሠብ ስነ-ልቦና አሉት። የደራሲ ደም እና አጥንት ውስጥ  የሐገርና የሕዝብ ታሪክ አለ። እናም አንድ ደራሲ የዚህ ሁሉ ጉዳይ ተሸካሚ ነው። ይህን ሸክሙን ይዞብን ከሔደ በርግጥም ተጐጂዎቹ እኛ ነን። ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታም ያንን በውስጡ ያለውን የሕዝብና የሐገር ታሪክ ይዞብን የት እንደገባ አጣሁ። ደራሲና ጥበበኛስ አይሠደድ ትላለች ገጣሚት ሜሮን ጌትነት። እናም ዛሬ ፍቅረማርቆስ ደስታን ያያችሁ ንገሩን እባካችሁ እላለሁ።

 

ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ በልዩ ልዩ የድርሰት ስራዎቹ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ የሐመር ብሔረሰብ ላይ መሠረት አድርጎ የፃፋቸው ልቦለዶቹ ደራሲውንና ማህበረሰቡን ታዋቂ አድርገውታል። “ከቡስካ በስተጀርባ” የተሰኘው ልቦለድ መፅሐፍ በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ የሚገኙትን ሐመሮችን እና አጎራባቾቻቸውን ውበትና ለዛ ባለው ቋንቋ በመግለፁ ፍቅረማርቆስን ጠንካራ የብዕር ሰው አድርጎታል።

 

ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከደቡብ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር “ሕያው የጥበብ ጉዞ” በሚል ርዕስ የፍቅረማርቆስን መጽሐፍ መሰረት በማድረግ የጉዞ ዝግጅት አድርጎ ነበር። ፍቅረማርቆስም በጉዞው ላይ ነበር። እኔም ከ50 ከሚልቁ ተጓዦች መካከል አንዱ ስለነበርኩ ሐመሮችን እና ፍቅረማርቆስን አንድ ላይ ሆነው ለማየት አጋጣሚው ተፈጠረልኝ።

 

ሐመሮችና ፍቅረማርቆስ ደስታ እጅግ ይዋደዳሉ። በእጅጉ ይከባበራሉ። ፍቅረማርቆስ ደስታ ውልደቱም ሆነ እድገቱ ከሐመሮች በጣም በሩቅ በምትገኘው ጎጃም ውስጥ ነው። ግን የእህል ውሃ ነገር ሆነና የጎጃሙ ጉብል ትምህርቱን ከዩኒቨርስቲ ሲያጠናቅቅ መምህር ሆኖ ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን ያመራል። በወቅቱ ቦታው እጅግ ኋላ ቀር /ሪሞት/ የሚባል እንደነበር ይታወቃል። ፍቅረማርቆስን ግን ማረከው። ወደ ሀመሮች መንደር ዘለቀ። የሐመሮች ጓዳ ጎድጓዳ ውስጥ ገባ። ጎጃሜው በሀመሮች ውስጥ ተዋዋጠ።

ፍቅረማርቆስ ደስታ በሐመር ብሔረሰቦች ማንነት ውስጥ ራሱን ከተተ። ሐመሮችም ተቀበሉት። ወደ ውስጣቸው አስገቡት። እናም ይሔ የሩቅ አገር ሰው በሐመሮች ፍቅር ተነድፎ ሲቀላቀላቸው እነርሱም በባህላቸው መሰረት የሐመር ብሔረሰብ አባል ሊያደርጉት ተማከሩ። የሐመር ባሕል እጅግ ተወዳጅ ሰው ከመጣ ጡት አጣብቶ የብሔረሰቡ አባል የማድረግ የቆየ ዘልማድ አለው። እናም ፍቅረማርቆስ በሐመር ባሕል መሰረት እናትና አባት ተሰጥቶት የሐመሮች አባል ሆነ። ወንድምና እህቶችም ከዚሁ ብሔረሰብ አገኘ። ፍቅረማርቆስ ለሐመሮች ልዩ ሰው፤ ተወዳጅ ሰው ሆነ።

 

በሐመሮች ፍቅር ተነድፎ የወደቀው የሳይንስ መምህር የሆነው ፍቅረማርቆስ፣ ስለነዚሁ ድንቅዬ ማህበረሰቦች ለሌላው ላላያቸው ማህበረሰብ ሊያካፍል ብዕሩን ይዞ ተነሳ። በመጨረሻም “ከቡስካ በስተጀርባ” - ድንግል ውበት፣ የተሰኘ ባለ 150 ገፅ መጽሐፍ በጥቅምት ወር በ1987 ዓ.ም አሳተመ። መጽሐፉ ልቦለድ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ መሰረት ያደረገው በተጨባጭ ባህላዊ ርዕስ ጉዳዮች ላይ ነው። ሐመሮች ምን አይነት ህዝቦች እንደሆኑ ልቦለዳዊ ቀለም ሽው ሽው አድርጎበት ፈካ ብለው እንዲታዩ አደረጋቸው።

 

ፍቅረማርቆስ ደስታ የሐመሮች የእድሜ ልክ ድልድይ ሆነ። ሐመሮችን ከሌለው ከቡስካ በስተጀርባ ማዶ ካለው የዓለም ህዝብ ጋር አገናኛቸው። ሐመሮችን ለማየትና ከነርሱ ጋር ለመጨዋወት ብዙ ሰዎች የጉዞ አቅጣጫቸውን ወደዚያ አደረጉ። ሐመሮች ገናና ሕዝቦች ሆነው የጥበበኞችን ልብ መስረቅ ጀመሩ። ፊልም ለመስራት፣ ሙዚቃ ለማቀነባበር፣ ስለ ባህልና ቋንቋ ለማጥናት አያሌዎች ሐመሮችን መረጡ። መሸጋገሪያ ድልድዩ የፍቅረማርቆስ ደስታ የብዕር ትሩፋቶች ነበሩ።

የፍቅረማርቆስ ደስታ መጽሐፍ በ1987 ዓ.ም “ከቡስካ በስተጀርባ” -ድንግል ውበት -ተብላ ለህትመት ስትበቃ የማስተዋወቂያ ፅሁፍ መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ናቸው። እርሳቸውም ሲገልፁ የሚከተለውን ብለዋል፡-

 

“ፍቅረማርቆስ በዚህ ቀዳሚ ድርሰቱ ከሐመሮች ጋር ኖሮ፣ ማዕዳቸውን ተቋድሶ፣ ውሃቸውን ጠጥቶ፣ በአፋቸው ተናግሮ በአጠቃላይ እነሱን ሆኖ መልሶ ይሔው እንዲህ ናቸው ይለናል። ባልተወሳሰበ አገላለፅ የተተረከ ብሩህነት ያለው፣ የገፀ-ባህሪያቱ ድርጊትና ማንነት የሚታይበት፣ ታሪኩን እስከ ማብቂያው እንድንከታተል የሚያደርጉ አጋጣሚዎችና ሁነቶች ያሉበት ልብ-ሰቃይ ድረሰት ነው።” በማለት ተ/ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ይገልፁታል።

 

ከዚህ መጽሐፍ ህትመት በኋላ ብዙ ኢትዮጵያዊያን እና የሌሎች ሀገሮች ሰዎችም ሐመሮችን አወቁ። የሐመሮች የቅርብ ወዳጆች ሆኑ። ሐመሮች በብዙ ሰዎች ቤት ታሪካቸው ገባ። ከቡስካ ተራራ ማዶ እና ከቡስካ ተራራ ግርጌ ያሉት ሀመሮች የሰውን ቀልብ ገዙት። ዛሬ ከዋናዎቹ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዱ ሐመሮች ሆነዋል። ከዓለም ጋር በስፋት ያገናኛቸው ድልድይ ደግሞ ፍቅረማርቆስ ደስታ ነው።

 

ይሔ የሐመሮች ውህድ የሆነው ፍቅረማርቆስ ከአያሌ ደራሲያንና ጋዜጠኞች ጋር ሆኖ በሐመሮች መካከል ከሶስት ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን ተጉዞ ነበር። በተለይ አያሌ ሐመሮች በሚገኙበት ቱርሚ ከተማ ውስጥ ህዝቡ ግልብጥ ብሎ በመወጣት ፍቅረማርቆስ ደስታን እና አብረውት የመጡትን ደራሲያን ተቀበሏቸው። በወቅቱ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር ፍቅረማርቆስ ለሐመሮች ልዩ የቤተሰብ እንግዳቸው ነበር። ቱርሚ ቀውጢ ሆነች።

 

ቱርሚ አካባቢ የሚኖሩት ሐመሮች ቆለኛ ሲሆኑ ዲመካ ተብሎ በሚጠራው ከተማ እና ከቡስካው ተራራ ግርጌ ያሉት ሐመሮች ደግሞ ደገኞች ናቸው። ወደ እነርሱም ዘንድ አምርተን ነበር። በአጠቃላይ ግን ሐመሮች ውስጥ ፍቅረማርቆስ ደስታ ልዩ ስብእና ያለው ተከባሪ ሰው ነበር።

ታዲያ ይሔ ደራሲ ሐመሮችን በዚህ ሁኔታ ከጎበኘናቸው በኋላ ሐገር ለቆ ጠፋ። በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ውስጥ እንደሚኖር ይነገራል። የፖለቲካ ጥገኝነትም ጠይቋል ተብሏል። ድንገት ከሐመሮች ጉያ ወጥቶ የጠፋ የሐመሮች ተወዳጅ ልጅ ነው።

 

ከሰሞኑ ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ ትውስ ያለኝ በብዙ ምክንያት ነው። ነገር ግን በዋናነት በኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የቋንቋና የባህል ታሪክ ላይ ያዘጋጀሁትን ጥናት ስመለከት ከሀመሮች ርዕስ ውስጥ ገባሁ። ሀመሮች ሲነሱ ፍቅረማርቆስም አብሮ ብቅ ይላል። ለእኔ ደግሞ ብዙ መረጃም የሰጠኝ ሰው እርሱ ነበር። የሀመሮች መዝገብ በተገለጠ ቁጥር ፍቅረማርቆስ ደስታ ብቅ ይላል።

 

ሐመሮች ፈጣሪ አላቸው። የሐመሮች ፈጣሪ /እግዚአብሔር/ ቦርጆ ይባላል። ቦርጆ ለሐመሮች መሬትን፣ ሰማይን፣ የሰው ልጅንና ከብቱን እንስሣቱን ሁሉ ፈጥሯል። በሐመሮች እምነት ቦርጆ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ነው የሚያደርገው። አልፎ አልፎ ብቻ ድንቅን፣ ወረርሽኝን እና ሌሎች ችግሮችን ቦርጆ ይልክባቸዋል። ይሔ ደግሞ የሚሆነው ቦርጆ ሲቆጣ ነው። ሕዝቡን ሲቀጣ አንዳንዶች ቦርጆ ቢቆጣ ነው ፍቅረማርቆስ ከሐመሮች ጉያ ወጥቶ በነጮቹ አለም መኖር የጀመረው ይላሉ።

 

በሐመሮች ባህላዊ እምነት ውስጥ ‘ቢታ’ ተብሎ የሚጠራ መላእክ አለ። ይህ መላእክ የሐመሮች የሐይማኖት መሪ ነው። ቀያሽ ነው። ሐመሮችና ፈጣሪያቸው ¢ቦርጆ¢ ሲቀያየሙ በመሀል ሆኖ የሚያስታርቅና የሚያግባባ ነው። ለሐመሮች የሚለምንላቸው ከፍፁሙ ፈጣሪያቸው ጋር ለማገናኘት ነው። እናም ቦርጆ እንዴት ፍቅረማርቆስን ከነርሱ አርቆ አስቀመጠው? የእምነት ድልድያቸው ቢታ ወደ ፈጣሪያቸው ቦርጆ ዘንድ ቀርቦ የፍቅረማርቆስን ጉዳይ ያቀርብላቸው ይሆናል። ፍቅረማርቆስ እንኳን ከሐመሮች ከእኛም ዘንድ በጣሙን ከራቀ ቆየ። ድምፁም ወሬውም ጠፍቷል።

 

ሐመሮች ቁጥራቸው 46ሺ 532 ሲሆን ከዚህ ውስጥ 38ሺ 354 ህዝብ አንድ ቋንቋ (ሐመርኛ) ብቻ የሚናገርና የሚሰማ /Monoligual/ ነው። ቋንቋቸው ከአፍሮ ኤዥያቲክ ምድብ የሚቀመጠው ኦሞቲክ ተብሎ የሚጠራ ነው። አርብቶ አደሮች የሆኑት እነዚህ ሕዝቦች በቀላሉ መጤን/አዲስ ሰውን/ የሚቀበሉ ናቸው። ፍቅር ሰጥተው ፍቅር መቀበል የሚችሉ ናቸው። የቡስካ ተራሮችን የሚያሞቅላቸው የነበረው ፍቅረማርቆስ ደስታ ስውር ስላለባቸው ቦርጆን በቢታ አማካይነት መጠየቃቸው አይቀርም።

 

በሐመሮች ባህል ምርቃትና እርግማን አለ። ምርቃት ¢ፊቴ¢ ይባላል። እርግማናቸው ኤርባ ይባላል። ለፍቅረማርቆስ ምርቃት ሲያዥጎደጉዱለት በአይኔ አይቻለሁ። ከሐገርና ከሐመሮች ርቆ መቆየቱ ምርቃት ይሁን እርግማን ለይቶ ማወቅ አይቻልም። ነገር ግን ከጉያቸው የወጣው ደራሲ ፍቅረማርቆ የምርቃታቸውና የፍቅራቸው ተፅእኖ ወደ ስድስት መፃህፍትን እንዲያሳትም አድርጎታል። ወደ አራት የሚጠጉ ኢትኖግራፊክ ዶክመንተሪ ፊልሞችን ሰርተዋል።

 

ሐመሮች መጪውን ዘመን አርቀው ይተነብያሉ። በእድሜ የገፉ አባቶች መጪውን ዘመን አሻግረው ያያሉ። የሰማይ ላይ ከዋክብትን እና ጨረቃን በመቃኘት ውሳኔ ያስተላልፋሉ። ኬንድ የተባለ ቦታ ሐመሮች እንዲሰበሰቡ ያደርጋሉ። ህዝቡ ከመጣ በኋላ ስለ ከዋክብት ሁኔታ ያስረዳሉ። በሐመር ባህል መሰረት ወንድና ሴት ከዋክብቶች አሉ። ወንዱ ¢ኢዚንሄኔ¢ ሲባል፣ ሴቷ ደግሞ ኢዚኒማሆ ትባላለች። ሁለቱ ከዋክብት በፀሐይ ዙሪያ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ተረድተው አባቶች ስለ ሐመሮች መፃኢ ግዜ ይናገራሉ። ሐመሮች ስነከዋክብት አስትሮኖመሮች ናቸው። የስነ-ፈለክ ተመራማሪዎች። እናስ ከዋክብቱ ስለ ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ ምን ብለዋቸው ይሆን? ለምን ጠፋ?

 

በይርጋ አበበ

 

ከ100 ሚሊዮን የማያነስ ህዝብ እንዳላት የሚነገርላት ኢትዮጵያ፣ የህዝብ ብዛቷንና ሰፊ የቆዳ ስፋቷን ያህል ዘርፈ ብዙ ችግሮችና ቋጠሮዎች ተብትበው የያዟት አገርም ነች። በዚህም የተነሳ በአገሪቱ ድህነት ተንሰራፍቶ የሚታይ ሲሆን በተለይ ከቅር ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በይፋ እንደገለጸው የስርዓቱም ሆነ የአገሪቱ ስጋት የሆነ ስር የሰደደ ሙስና ተንሰራፍቶባታል።

የአገሪቱን የፖለተካ ስልጣን ይዞ መንግስት የመሰረተው ኢህአዴግ “ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ እገነባለሁ” ብሎ ቢገልጽም አገሪቱ ውስጥ ግን በተደጋጋሚ ሚከሰት ድርቅ ዜጎቿን ለቸነፈር የአገሪቱን ኢኮኖሚም ለከባድ ፈተና ሲዳርገው ይታያል። የአገሪቱ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽ/ቤት መቀመጫ መሆኗን ተከትሎ የበርካታ ዲፕሎማት መናገሻ ብትሆንም እንደ ስሟ ሳይሆን ከስሟ በተቃራኒ በቆሻሻ የተከበበች ከተማ ሆናለች። እኤአ በ2003 ቶጎ ሎሜ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካ መሪዎች ስበሰባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ አዲስ አበባ መሆኑ ቀርቶ የሊቢያዋ ትሪፖሊ እንድትሆን የአህጉሩን መሪዎች ማግባባት የጀመሩት የቀድሞው የሊቢያ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ “አዲስ አበባ የምንሄደው ቆሻሻ ለማሽተት ነው? ስለዚህ ከቆሻሻዋ ከተማ ይልቅ ትሪፖሊ የህብረቱ መናገሻ ልትሆን ይገባል” ሲሉ ነበር የተናገሩት።

በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትረ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ በነዳጅ ዘይት ሀብት አቅላቸውን የሳቱትን ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊን ሲከራከሩ “እውነት ነው ከተማችን ቆሻሻ በዝቶባት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አገራችን ቆሻሻ ታሪክ የላትም” ሲሉ ነበር የመለሱላቸውና የህብረቱን መቀመጫ በአዲስ አበባ እንዲጸና ያደረጉት። አዲስ አበባ ከዚያን በፊትም ሆነ በዚያን ጊዜ (እኤአ ከ2003) ጀምሮ ቆሻሻዋ በዝቶ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንደ አጀንዳ ሆኖ አከራከሮ ነበር። ሰሞኑን ደግሞ ይኸው የአዲስ አበባ ቆሻሻ ክምር ከ70 በላይ የአዲስ አበባ ዜጎችን ቀርጥፎ በልቷል።

በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ቤንትሌይ መኪና አዲስ አበባን ከረገጠበትና የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መኪና ነጅ (ሾፌር) ራሳቸው ንጉሱ ሆነው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች መኪና ካሽከረከሩበት ጊዜ ጀምሮ አዲስ አበባ በየዓመቱ በርካታ ተሽከርካሪዎች የሚገቡባት ከተማ ሆናለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት መኪኖች አብዛኞቹን በጉያው የያዘው የአዲስ አበባ መንገድም በየእለቱ የመኪና አደጋ ሳይስተናገድበት መዋል ከብዶታል። ይህ የመኪና አደጋም በፓርላማ ቀርቦ እስከማወያየት ደርሷል።

ድርቅ ቆሻሻ እና የመኪና አደጋ አገሪቱንም ሆነ ዜጎቿን እየፈተኑ ያሉ ወቅታዊ ችግሮች ሲሆኑ መንግስትም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያሳየው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ምን ይመስላል? የጉዳት መጠኑ ምን ያህል ይሆናል? ወደፊትስ የሚኖረው ፈተና እና የመፍተሔ ሀሳብ ምንድን ነው? የሚሉትን ነጥቦች ከዚህ በታች እንመለከታለን።

 

 

የችግሮቹ መጀመሪያ

የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ዳፋውን ያሳረፈው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድህነት ጎጆውን በሰራባቸው አገሮች ላይ ሲሆን በተለይ ኢኮኖሚያቸውን በግብርና (አርብቶ እና አርሶ አደር) ላይ በመሰረቱ አገሮች አሉታዊ ተጽእኖው የከፋ ነው። ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚትዎሮሎጂ ኤጄንሲ በተገኘ መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው ከ1900 እስከ 2009 ዓም ድረስ ባሉት ዓመታት 26 ጊዜ ኢትዮጵያ ላይ ኤልኒኖ ድርቅ አስከትሏል። ከኤልኒኖ በተጨማሪም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 30 ዓመታት ተጨማሪ የድርቅ አደጋዎች በአገሪቱ ላይ ተከስተዋል።

አዲስ አበባ ከተማ የአገሪቱ ርዕሰ መዲና መሆኗን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር (ከአገሪቱ ከተሞች በአንጻራዊነት) ያለው ህዝብ የሚኖረው በአዲስ አበባ ነው። ይህ በመሆኑ ደግሞ የፍጆታ መጠን ከፍተኛ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የሚወገዱ ተረፈ ምርቶችም የዚያኑ ያህል ከፍተኛ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የከተማው ነዋሪ ቁጥርና የሚያስወግደው ተረፈ ምርት (ቆሻሻ) ከፍተኛ መጠን ያለው ቢሆንም የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓታችን ደካማ መሆኑ ደግሞ ችግሩ የከፋ እንዲሆን አድርጎታል። አገሪቱ የምትከተለው የአካባቢ ጥበቃ ወደ ተግባር አለመለወጡ “በተለይም ቸልተኛ ባለስልጣናትና አምባገነን ባለሀብቶች በፈጸሙት ጋብቻ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው ለቆሻሻ መከማቸት አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው” ሲሉ ዶክተር ዘካሪያስ አምደብርሃን ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ ናገረዋል።

በቅርብ ጊዜ በወጣ መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው ደግሞ አገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ከስምንት መቶ ሺህ የማይበልጡ መኪኖች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት በአዲስ አበባ ይገኛሉ። አዲስ አበባ ከ30 ሺህ ኪሎ ሜትር ስኩየር በታች የቆዳ ስፋት ያላት ከተማ ስትሆን በከተማዋ የተገነቡ መንገዶች በከተማዋ ከሚገኙ መኪኖች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በቂ አለመሆናቸውን ለዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ አስተያየታቸውን የሰጡ ሰዎች ተናግረዋል።

 

 

ቀጣይ ፈተናዎች

የፌዴራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኤጄንሲ ኮሚሽን ባወጣው መረጃ በአሁኑ ወቅት ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፈላጊ መሆናቸውን አስታውቋል። ነገር ግን ይህ አኃዝ ከፍ ሊል እንደሚችል ደግሞ አስተያየታቸውን የሰጡን ምሁራን ተናግረዋል። ይህ አኃዝ በራሱ ከፍተኛ ሲሆን በቀጣይ በሶማሌ ክልል ድርቁ ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ መግለጻቸው ደግሞ ይበልጥ የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አመላካች ነው። ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ በአፋር ክልልም ድርቁ ሊከፋ እንደሚችል ግምቶች እንዳሉ በኮሚሽነር ምትኩ የተገለጸ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል (በአሁኑ ወቅት ብቻ ወደ ሶስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለርሃብ ስጋት የተጋለጠበት ክልል ነው) እና በአማራ ክልልም ተጨማሪ የድርቅ ስጋት ያንዣበበባቸው ናቸው።

በቅርቡ ይፋ በሆነ የዓለም ሚዲያዎች መረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ አጎራባች በሆኑት በሶማሊያ በኬኒያ እና በደቡብ ሱዳን ድርቅ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን በሶማሊያ ወደ 200 የሚጠጉ ዜጎች ሞተዋል። ኬኒያ እና ደቡብ ሱዳን ደግሞ ድርቁ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን አውጀዋል። እነዚህ አጎራባች አገራት በተለይም ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ከድርቁ በተጨማሪ ባለባቸው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በርካታ ዜጎቻቸው እግራቸው ወደመራቸው የሚሰደዱ ሲሆን ኢትዮጵያ እና ኬኒያ ደግሞ የመጀመሪያ መጠጊያቸው ናቸው። ከጦርነቱ ላይ ድርቁ ተጨምሮ በሁለቱ አገራት ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ የበረታ ሊሆነ ሰለሚችል ኢትዮጵያ ደግሞ ከራሳ ችግር በዘለለ ድንበር ተሻጋሪ ችግር ተጨምሮባት የበለጠ ስጋት ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ይጠበቃል።

የትራፊክ አደጋን በተመለከተ ደግሞ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ጽ/ቤት ባገኘነው መረጃ ለማወቅ እንደቻልነው ባለፉት ስድስት ወራት በቻ 244 ዜጎች ህይወታቸው አልፏል። ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረትም ወድሟል። በዚህ ዓመት የደረሰው የጉዳት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም ከ60 በመቶ በላይ ብልጫ አለው። ይህን አደጋ በተመለከተ በቅርቡ ከፓርላማ አባላት የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም “በመቶ ዓመት የአገራችን የመኪና ታሪክ በአሁኑ ወቅት እየገባ ያለው መኪና ብዛት እጅግ ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛል። ምንም እንኳን የተሽከርካሪ ብዛት እንደምክንያት የሚገለጽ ቢሆንም የአደጋው መጠን እየከፋ መሄዱ ግን እጅግ አሳሳቢ ነው። መንግስት ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን የመንጃ ፈቃድ አሰጣጡ ላይም ማሻሻያ ሊደረግለት ይችላል” ያሉ ሲሆን “በዋናነት ግን ከኤች አይ ቪ ኤድስ ባልተናነሰ አገራዊ ንቅናቄ ሊደረግበት ይገባል” ሲሉ የአደጋውን መጠንና ሊያስከትለው የሚችለውን የከፋ ጉዳት ገልጸዋል።

የአሜሪካው ሲ ኤን ኤን ቴሌቪዥን እና የእንግሊዙ ቢቢሲ አዲስ አበባ በደረሰው የቆሻሻ መደርመስ አደጋ የዘገቡ ሲሆን የአደጋውን ጥልቀትም ገልጸዋል። ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት የዘገቡት የቆሻሻ መደርመስ አደጋ ወደ 70 የሚጠጉ ዜጎችን መቅጠፉ ሳይሆን፤ አሳሳቢነቱ አገሪቱ የቆሻሻ አወጋገድ ፖሊሲ የላትም ወይ የአካባቢ ጥበቃ ላይስ ምን ትሰራ ነበር? የሚሉ ጥያቄዎች የሚያስነሳ ክሰተት ነው። ዶክተር ዘካሪያስ አምደብርሃን እና በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ አስተማሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ምክሩ ለሰነደቅ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ያረጋገጡትመ ይህንኑ ነወ።

የአዲስ አበባን ቆሻሻ በሰንዳፋ ከተማ እንዲጣልና በምትኩም ቆሻሻው በፋብሪካ መልክ ተቀይሮ ለአገልግሎተ እንዲውል ከፈረንሳይ መንግስት በተገኘ ድጋፍ ወደ ስራ የተገባ ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ መሆን አልቻለም። ከወራት በፊት የሰንዳፋ አካባቢ አርሶ አደሮች ቆሻሻ አናስደፋም በማለታቸው አዲስ አበባ በቆሻሻ ክምር ተሞለታ መሰንበቷ የአንድ ሰሞን የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሆኖ ነበር። እንደዚህ አይነት እንዝህላልነት ያለባቸው የአፈጻጸም ስህተቶች ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ናቸው ሲሉ ምሁራኑ የአደጋውን አስከፊነትና የወደፊት ስጋት ገልጸውታል። ከዚሁ የቆሻሻ ናዳ መደርመስ በዘለለ ደግሞ ወደፊትም ሆነ አሁንም ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፈታኝ የሆነው የአካባቢ ንጽህና ጉድለት ነው። ከተማዋ የህዝብ መጸዳጃ ቤት በስፋት የላትም። የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦዎችም ቢሆኑ አስተማማኝ ባለመሆናቸው ወደ ፊት ከአሁኑ የባሰ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ምሁራኑ አሰተያየታቸውነ ሰጥተዋል።

 

 

የተዘነጋው የፖለቲካ ቁርጠኝነት

በአንድ አገር ውስጥ የሚከናወኑ የልማት ስኬቶች ተመስጋኙ መንግስት መሆኑ ግልጽ ነው። በዚያኑ ያህል ደግሞ መሰራት ሳይገባቸው ባለመሰራታቸው ለህዝብና ለአገር ክፍተት የፈጠሩ ዘርፎች ሲነሱ አብሮ የሚነሳው የፖለቲካው መዘውር የሆነው መንግስት ነው። ከላይ ለተገለጹት ሶስት ግዙፍ ጉድለቶች መንግስት እንደ አገር አስተዳዳሪነቱ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይጎደለው እንደነበር የገለጹት ዶክተር ዘካሪያስ ምክንያታቸውነ ሲያስቀምጡም “መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ፓረቲዎች ፍላጎታቸው ስልጣን እንጂ ስልጣኔ አይመስለኝም። የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ የተሰራው ስራ ምንድን ነው ብለህ ብትጠይቅ መልሱ ምንም ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በድርቁ አደጋም ሆነ በትራፊከ ደህንነቱ ጉዳይ ከሙያዊና አገራዊ ኃላፊነት ይልቅ ፖለቲካዊ ጉዳዮቸ ቅድሚያውን ስለሚይዙ ወሳኝ የሆኑት ጉዳዮቸ መዘንጋታቸውን ተናግረዋል።

የባህርዳር ዩኒቨርስቲው አስተማሪ አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው “መንግስት ምንም የሰራው ስራ የለም ባይባልም በራሱ መገናኛ ብዙሃን የሚያስተላልፈውን ሰኬቱን ያህለ በድክመቱ ላይ ቢሰራ መልካም ነበር። የራሱ ሚዲያዎች በድክመቱ ላይ ባይሰሩ እንኳን የመንግስትን ድክመት የሚያመለክቱ መገናኛ ብዙሃን የሚያወጧቸውን ዘገባዎች በበጎ ተመልክቶ የማስተካከያ ስራ ቢሰራ መልካም ነበር” ብለዋል። በአገሪቱ የደረሰውን ድርቅ ተከትሎ ሊወሰድ ሰለሚገባው የመፍትሔ ሀሳብ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም “ምንም መደባበቅ ሳያስፈልግ የጉዳቱን መጠን ገልጾ ለተረጂዎች ድጋፍ ማፈላለግ ያስፈልጋል” በማለት ተናግረዋል።

በቆሻሻ ድርመሳው ጉዳይ አስተያየታቸውን የሰጡን አቶ ደምሴ የተባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ በበኩላቸው “የመሬት ፖሊሲው ሊፈተሽ ይገባል” ሲሉ የገለጹ ሲሆን ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም “እነዚያ ምስኪን ወገኖቻችን እዚያ ቦታ ገብተው ያለቁት የመንግስት የመሬት ፖሊሲ የፈጠረው ችግር ነው እንጂ ማንም በንጹህና በተመቻቸ አካባቢ መኖር የሚጠላ የለም። ህገ መንግስቱ የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ነው። ሆኖም መንግስት መሬትን በራሱ ቁጥጥር ስር አውሎ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት እንዳይሆኑ ስላደረጋቸው የራሳቸውን አማራጭ ፍለጋ ሲሄዱ እንደዚህ አይነት አደጋ ደረሰ” ሲሉ ሀሳባቸውን አብራርተው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በቆሻሻ ድርመሳው አደጋ የተሰማውን ሀዘን ገልጾ ተገጂዎች በዘላቂነት የሚደገፉበትን መንገድ እንደሚያመቻች በመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች በኩል አስታውቋል። የድርቁን አሳሳቢነት አስመልክቶ የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽነሩ በቅርቡ እንዳስታወቁት የኢትዮጵያ መንግስት አቋም አሁንም በራሱ አቅም ለመቋቋም መሆኑን ነው።¾


Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100
Page 7 of 160

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us