You are here:መነሻ ገፅ»arts»news admin - Sendek NewsPaper
news admin

news admin

በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያጋልጡ እድል ተሰጥቷቸዋል። በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በየክልሉ በርካታ ሰዎች ራሳቸውን ያጋለጡ ሲሆን ራስን የማጋለጫ ጊዜውን እስከማራዘም የደረሰ ትብብርም እየተደረገላቸው ነው። ነገርየው ለውጥ ማምጣት ከቻለ መልካም ነው። ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ራሳቸውን እንዲያጋልጡ እድል መሰጠቱ የአንድ ሰሞን አጀንዳ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ እንዲኖረው ማድረግ ግን ያስፈልጋል። ዋናው ጥያቄ የሚሆነው እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ካጋለጡ በኋላ የሚከተለው ነገር ምንድን ነው? የሚለው ነው። እነዚህ ሰዎች ይብዛም ይነስም ደሞዝ እየተከፈላቸው የራሳቸውን ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ናቸው። በአንድ ሰው ጥላ ስርም ሌሎች በርካታ ሰዎች ይኖራሉ። ስለዚህ በዚህ ሰው ላይ የሚወስደው ማንኛውም እርምጃ ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን እነዚህን ሰዎችም ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይኖርበታል። ይሄ ሲታሰብ ደግሞ ማጋለጥ፣ ያለማጋለጡ ጉዳይ ሳይሆን በቀጣይ ምን ሊከሰት እንደሚችል ማሰቡ ይከብዳል። በሌላ በኩል ደግሞ ድርጊቱ ወንጀል እንደመሆኑ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ስለዚህ ለማጋለጥ ከመሯሯጡ በፊት በቀጣይ የእነዚህ ሰዎች ማረፊያ ምን እንደሆነ ሊጠና እና ሊታሰብበት ይገባል።

 

ሌላው ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ የችግሩ መንስኤ ምንድን ነው? የሚለው ነው። ችግሩ አሁን የጀመረ ሳይሆን ቀደም ብሎ የተጀመረ ነገር ግን አሁንም ድረስ የቀጠለ ችግር ነው። ለዚህ ወንጀል ተባባሪ የሆነ በየመንደሩ ውስጥ ሀሰተኛ ማስረጃዎችን የሚያዘጋጁ በርካታ ተቋማት እንዳሉ ይታወቃል። ነገር ግን እነዚህን ተቋማት ለመቆጣጠር እና ከድርጊታቸው ለማስቆም እየተሄደበት ያለው መንገድ ምን ያህል ርቀት ተጉዟል የሚለውንም እግረ-መንገድ መፈተሽ ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ ግን ለእውቀት ሳይሆን ለወረቀት ሲባል ብቻ በገንዘብ የሚደረገውን የትምህርት ማስረጃ ሸመታ በቀላሉ ማስቆም ከባድ ነው የሚሆነው። ችግሩን መቅረፍ የሚቻለው ምንጩን በማድረቅ ብቻ ነው።

                           ዘላለም ንጉሴ - ከሾላ   

ቁጥሮች

Wednesday, 17 January 2018 13:22

215 ሚሊዮን ዶላር                ባለፈው ሩብ ዓመት ወደ ውጭ ከተላከ ቡና የተገኘው ገቢ፤

 

882 ሚሊዮን ዶላር                ባለፈው ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበው ቡና ማግኘት የተቻለው ገቢ፤

1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር          በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከሚላክ የቡና ምርት ለማግኘት የታቀደው ገንዘብ መጠን፤

270 ሺህ ቶን                       በዚህ ዓመት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የታቀደው የቡና ምርት መጠን፤

 

    ምንጭ - የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ግብይት ባለስልጣን

የኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮምቴ ተነጋግሮ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲባል የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ፍርደኛ እና ፍርደኛ ያልሆኑ እስረኞች ለመልቀቅ መወሰኑን ልክ የዛሬ አሥራ አምስት ቀን ተነግሮናል፡፡ የግንባሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮምቴ ውሳኔ በበርካታ ዜጎች ውስጥ የተደበላለቀ ስሜትን ፈጥሮ የነበረ ሲሆን አፈፃፀሙ መዘግየቱ ግን የግንባሩን ቁርጠኝነትና ለውሳኔው ተገዥነት ላይ ከበድ ያለ ጥርጣሬን አስከትሏል፡፡

 

እጅግ ዘግይቶም ቢሆን የፌዴራል የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሚኒስትሩ ከፌዴራል እና ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በድምሩ 528 እስረኞች ከዛሬ ጀምሮ እንደሚፈቱ ገልጸዋል፡፡ ከክልሎች ለምን ደቡብ ብቻ ለሚለው ጥያቄ የተሰጠው መልስ ሌሎች ክልሎች ስላላቀረቡ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ መልስ ስለሚፈቱ እስረኞች ጉዳይ ከፖለቲካ ውሳኔ ባሻገር በቂ ዝግጅት አለመደረጉን ጠቋሚ ነው፡፡


ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እስረኞች የሚፈቱበት መስፈርት የሚከተሉት ናቸው ብሏል፡፡
- ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን የመናድ እንቅስቃሴ ላይ ያልተሳተፉ ወይም ያልመሩ፣
- በከፍተኛ የኢኮኖሚ አውታሮች ላይ ጉዳት ለማድረስ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ያልተሳተፉ ወይም ያልመሩ፣
- የሰው ህይወት ያላጠፉ ወይም በአካል ላይ ከባድ ጉዳት ያላደረሱ፣
- በሥርዓቱ ተጠቃሚ ሆነው ሳለው በሌሎች ገፋፊነት ወደ ሁከትና ብጥብጥ የገቡ ናቸው ሲል ያስቀምጣል፡፡


በዚህ መሰፈርት መሠረት ሊፈቱ የሚችሉት በተራ ደረቅ ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ብቻ ይመስላል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ከሕገመንግሥቱ ጋር ተያይዞ በቀረበባቸው ክስ የታሠሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና ይፈታሉ መባል የመስፈርቱን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው፡፡


እናም ኢህአዴግ በገባው ቃል መሠረት የተሻለ ሃገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ከልብ ቁርጠኝነት ካለው በተለይ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊፈታ ይገባል፡፡ ነገሮችን በቅድመ ሁኔታ ለመሸብለል መሞከሩ ቀናኢነትንና ለመታደስ ያለ ቁርጠኝነትን አያሳይምና ጉዳዩ ሰከን ብሎ እንደገና ቢያጤነው እንላለን፡፡

በይርጋ አበበ

 

የፌዴራል ፖሊስ “ቄሮ” ላይ ምርመራ አደርጋለሁ ማለቱን ተከትሎ መግለጫው በስህተት ተተርጉሟል ሲል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ገለፀ።


የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ትናንት በጽ/ቤታቸው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ወቅታዊ መግለጫ፤ በኦሮሚያ ክልል ለተነሳው ግጭት የፌዴራል ፖሊስ በቄሮዎች ላይ ምርመራ እንደሚያደርግ መግለጹን ተከትሎ የመንግስት አቋም በማይገልፅ መልኩ መግለጫው ተጣሞ ቀርቧል ብለዋል።


ዶ/ር ነገሪ “በኦሮሞ ባህል፣ ቋንቋ እና የገዳ ሥርዓት ትዳር ያልመሰረቱ ወጣት ወንዶች ቄሮ ይባላሉ። ነገር ግን ሆን ብለው አላስፈላጊ ትርጉም በመስጠት እና አንዳንዶች ደግሞ ከጠላት ጋር በማያያዝ ከሽብር ቡድኖች ጋር እያያያዙ የሚያናፍሱት ወሬ አላስፈላጊ አጀንዳ በመሆኑ መንግሥት የሚጋራው እንዳልሆነ ለመጠቆም እፈልጋለሁ” ብለዋል።


ሚኒስትሩ ቄሮ የሚባል ህጋዊ እውቅና ያለውም ሆነ ህቡዕ ቡድን እንደሌለ ገልጸው “ቄሮ የሚለውን ቃል ብቻ በመውሰድ የሆነ የሥራ ፈት ቡድን አድርጎ መቅረጽ ትክክለኛ አጀንዳ አይደለም። እነዚህን ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ አጀንዳ ተቀርፆላቸዋል” ብለዋል።


የፌዴራል ፖሊስ በቄሮዎች ላይ የጀመረውን ምርመራ አቋርጧል ወይ? ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ነገሪ፤ “የመንግስት አጀንዳ እነዚህን ወጣቶች ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ማድረግ ነው። ነገር ግን ማንም ሰው ወጣትም ይሁን በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኝ ቢሆን እና በየትኛውም ክልል የሚኖር ቢሆን በወንጀል ከተሳተፈ ከተጠያቂነት አያመልጥም። ስለዚህ በአጠቃላይ ቄሮዎች ላይ ሳይሆን ምርመራ የሚደረገው ወንጀል ከፈፀሙ አካላት ጋር በሙሉ ነው። የፌዴራል ፖሊስም ይሁን መንግሥት ያቋቋማቸው በክልል ደረጃም ያሉ ህግ አስከባሪዎች አስፈላጊውን የህግ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ አይሉም” ሲሉ የመንግሥትን አቋም ይፋ አድርገዋል።

በይርጋ አበበ

መሳይ ፕሮሞሽን ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚያካሂደውየታላቅነት የክብር መታሰቢያከየካቲት 10 ቀን 2010 . ጀምሮ በስድስት ዘርፎች ይካሄዳል።

የፕሮግራሙ አዘጋጅ አቶ መሳይ ሽፋው ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ፕሮግራሙ የሚካሄደው ለአገራቸው አንቱታን ባተረፉ አራት ኢትዮጵያዊያን የሀገር ባለውለታዎች ስም ነው። በእግር ኳሱ መስክ ኢትዮጵያን 31 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመለሷት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ የኢትዮጵያ የጃዝ ሙዚቃ አባት የክብር / ሙላቱ አስታጥቄ፣ የበርካታ አርቲስቶች አስተማሪው ክብር / ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) እና የብዙሃኑ እናት የክብር / አበበች ጎበና የዘንድሮውየክብር ለታላቅነት የክብር አምባሳደሮችናቸው።

አዘጋጆቹ ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለፀው የካቲት 10 ቀን 2010 . በአራቱ ኢትዮጵያዊያን ስም የደም ልገሳ የሚካሄድ ሲሆን፤ በዕለቱም 1 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ደም ይለግሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።

በክብር / ሙላቱ አስታጥቄ መሪነትደም ይለግሱየሚል የጃዝ ሙዚቃ ኮንሰርትም ይካሄዳል። በዕለቱም ኮንሰርቱን የሚታደሙ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ወደ ብሔራዊ ደም ባንክ እየሄዱ ደም እንዲለግሱ ይደረጋል።

በአካባቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ተጨማሪ መርሃ ግብር መዘጋጀቱን የገለፁት አዘጋጆቹ ይህምቀጠሮ በተራራው ላይይሰኛል። በዕለቱም 100 ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም የሚካሄድ ይሆናል። የነፍሰጡሮች የእግር ጉዞም የፕሮግራሙ አካል ነው።

ፕሮግራሙን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ መሆኑን የገለፁት አዘጋጆቹ ሆኖም ዓላማውን የተረዱ ተቋማት (የአዲስ አበባ ኤች አይ /ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ /ቤት፣ አኃዱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ዋይቲ ሕትመትና ማስታወቂያ እና ቬልቪው ሆቴል) ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ተናግረዋል። ዝግጅቱ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ይሆናል።

ከፕሮግራሙ የክብር አምባሳደሮች መካከል አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ የክብር / ሙላቱ አስታጥቄ እና የክብር / ተሥፋዬ አበበ (ፋዘር) በመግለጫው ላይ ተገኝተው ሁሉም በየሙያ ዘርፋቸው ኅብረተሰቡን እንደሚቀሰቅሱ ተናግረዋል። በዕድሜ መግፋት ምክንያት መግለጫው ላይ ያልተገኙት ክብር / አበበች ጐበና ደግሞ መልዕክታቸውን የላኩ ሲሆን፤ በዝግጅቱ የክብር አምባሳደር ተብለው በመመረጣቸው አዘጋጆቹን አመስግነዋል።¾       

 

ፋሲል ሣህሌ

 

አንድ የግል ጋዜጦች ወዳጅ የቱን ከየቱ አስበልጦ ለማንበብ ሲያማርጥ ጥሩ ሐሳብ መጣለትና "ተዓማኒ የሆነውን ብቻ አነባለሁ ተዓማኒውንም ለመለየት የተለያዩ ገጾቹን ማገላበጥና መመርመር ይኖርብኛል" ሲል ወሰነ፡፡ ለምርጫው መሳካት ጥሩ ውሳኔ መወሰኑ እያስደሰተው በእጁ የገባውን በጣም ታዋቂ ጋዜጣ ገጾች ገልበጥበጥ ሲያደርግ በትልቁ የተጻፈ የዜና ዕረፍት ርዕስ ተመልክቶ በተማረኩት ዐይኖቹ በችኮላ ታሪኩን ሲያነብ ሟች በስምም ሆነ በአባት ስም ሞክሼው ሆነው አገኛቸውና በሐዘኔታ ታሪካቸውን ማንበብ ቀጠለ፡፡ ከአረፍተ ነገር አረፍተ ነገር እየደመረ ቁልቁል የባለዜና ዕረፍት ሰውዬውን ታሪክ ሲያነብ ጽሑፉ የራሱ የህይወት ታሪክ መሆኑን ባለመጠራጠሩ "መቼ ነው የሞትኩት?" ሲል መልስ የለሽ ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ ለካ ያም ትልቅ ጋዜጣ በትናንሾቹ ወሬኞች አሉባልታ ተደናብሮ ያልሆነ ዜና አትሞ ማውጣቱን ተረዳና "ከእንግዲህስ ማንንም….!!" አለ አሉ፡፡


ለዚህ አባባል መነሻ የሆነኝ ባለፉት 16 የሥራ ዓመቶቼ ከአስር ጊዜ በላይ ተመላልሼ ጎብኝቼው ስለማውቀው የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን አንድ ተዓማኒነቱ የማያጠራጥር የሚመስል ቁመና ያለው ትልቅ ዓለም አቀፍ የዜና አውታር የዘገበውን ከእውነት የራቀ ሐተታ ማንበቤ ነው፡፡ “… ወርቅ መርዝ የሆነባት ምድር” በሚል ማራኪ ሐረግ የተጀመረው ዘገባ በሀገራችን ብርቅዬነቱን የማልጠራጠረውንና በነበረኝ አጋጣሚ የሥራ ሒደቱን በቃሌ እስከመያዝ ያህል በማውቀው ድርጅት ሕጋዊ ሰብዕና ላይ ከተራ ስም አጥፊነት የማያልፍ አሉባልታ ሲከምርበት ሰምቼና አንብቤ ተገረምኩ፡፡ መገናኛ ብዙኃን የመረጃ ምንጮች ናቸው ብለው ለሚያምኑ ሰዎች እንደዚህ ዓይነቱ ተቋም ኃላፊነት የሚሰማው ለሕዝብ፤ ለፖለቲከኞችና ለመንግሥት እውነታዊ መረጃን የሚያቀርብ አድርገው ይመለከቱታል፡፡


ከጥርጣሬ ለማምለጥ የታደለ አእምሮ ግን በማህበራዊ ድረ ገጾች ሁሉ የተዘገበውን እንደወረደ ከመቀበል ተቆጥቦ የወሬው ምንጭና የዜናው አቀባይ ማነው? ብሎ ይጠይቅና እውነታውን ይደርስበታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በምንኖርባት ምድር ለዘመኑ ኢንተርኔት ተደራሽነት ያለው ማንኛውም ሰው የፈለገውን ዜና ፈጥሮ ማሰራጨት እንደሚችል ማጤን ብልህነት ነው፡፡ እናም አንድን ዜና ስናነብ ቢያንስ በሌላ አንድ ወይም ሁለት ተዓማኒነትን ባተረፉ የዜና አውታሮች ከነምንጩ የተዘገበ ዜና መሆኑን ማረጋገጥ ያሻል፡፡


ትዊተር የተሰኘው ድረ ገጽ ቅርብ ጊዜ ይፋ ባደረገው መረጃ ከ150 ሚሊዮን በላይ ንቁና የማያቋርጡ አባሎች እንዳሉት አሳውቆ እነዚህና ሌሎች ተጠቃሚዎች በየቀኑ ከ350 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ሃሳባቸውን እንደሚያሰፍሩ ዘግቧል፡፡ ይህም አንድ ዜና በምን ያህል ቅጽበትና ስፋት በዓለም እንደሚሰራጭ ያመለክታል፡፡ ነገር ግን ወሬዎች በፍጥነትና በስፋት በአጭር ጊዜ ዓለምን ማዳረስ መቻላቸው የእውነትነታቸው ማረጋገጫ አይደለም፡፡ ፈረንጆች እንደሚሉትም "fast does not always mean accurate":: ለዚህም ነው ከላይ በጠቀስኩት ዘገባ ስሙ የተነሳው ድርጅት የተሰራጨበት መሰረተ-ቢስ ውንጀላና የአሉባልታ ዜና ማህበራዊ ኃላፊነትን አክብሮ፤ ለሰብዓዊ ፍጡር ደህንነትና ጤንነት ተጨንቆ፤ ለህግና ለህግ የበላይነት ቀበቶውን አጥብቆ ቆሞ ለሕሊና ፍርድ ብቃት ባለው ማረጋገጫ ከምንም በደል የጸዳ ንጹህ የማምረት ተግባሩን ጭቃ ሊለውሰው የሚችል እርግጠኛ ዜና መሆን ያልበቃው፡፡


ያ ትልቅና ግዙፍ የዜና አውታር ከ150 ሚሊዮን የተዊተር አምደኞች ዓይነት የአንዱን ፎቶግራፍ ለጥፎና የ350 ሚሊዮን በላይ የግለሰብ ወሬዎች ክምችት ውስጥ የሁለት ሶስቱን ተዓማኒ አድርጎ ዜናውን ሲሰራ ለትዝብት ከመጋለጥና ለክብሩ ወርደት ከመከናነብ ያለፈ ዕርባና ያለው ተደማጭነት ሊያተርፍበት አልቻለም፡፡ የእኔም ትዝብት የእዚሁ ውጤት አካል ነው፡፡ አሳዛኙ ደግሞ ያ የዜና ምንጭ ወሬውን ያገኘው ከግለሰብ መሆኑን አጢኖ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች ሰዎች ጭምር የተሳተፉበት አለመሆኑን አመዛዝኖ የወሬውን ትክክለኛነት ከማጣራት በፊት እከሌ እንደዘገበው ብሎ ማናፈስ የእምቧይ ካብ ከመከመር ያለፈ አለመሆኑን መረዳት ተስኗቸው ለግል ፍላጎታቸው እርካታ ብቻ የሚናወዙና "በወደቀ ዛፍ ላይ ምሳር ይበዛበታል" የሚል ብሂል ተጠቃሚ ለመሆን የተመኙ ብዙዎች መታያታቸው ነው፡፡


ደስ የሚለው ግን አሉባልተኞቹ ያለሙት ዛፍ አይወድቅም፤ ምሳሮችም ተለቅመው ያልቃሉ!! ከሶስት ዓመታት ተኩል በፊት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ለአንድ የህትመት ጋዜጣ በላከው ስንኝ በተመሳሳይ አሉባልታዎች መሰላቸቱን ለማመልከት

"ደግሜ ደግሜ ስሰማው ሰለቸኝ፤
ታከተኝ አሁንስ በቃ እጅ እጅ አለኝ፡፡
የሰውዬው ነገር ምን ዓይነት እድል ነው፤
ሁሌ የምሰማው ዛሬም ነገም ያውነው፡፡
ቅንጣት ያላየውን ወሬ እየቀጠለ፤ ሰው ሁሉ ማማቱን ቢተወው ምናለ?" ሲል አንባቢን አናግሮ ነበር፡፡
ዘረፈው!! አፈሰው!! የማይባል የለ፤ አንዲት ሳንቲም ኪሱ መክተቱ የታለ?


ለዛሬው ርዕሰ ጉዳዩ መነሻ የሆነውን ሐሳብ ተንተርሶ ብዙ እየተባለ ለመሆኑና ትላልቅ ምሁራን ነን ባዮች ሳይቀሩ ለሚያናፍሱት የከንቱ ጥላቻ ወሬ በርካታ መረጃዎችን መደርደር ቢቻልም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች በወቅቱ የሰጡት አርኪ ምላሽ ስለሰጡበት መድገም አያሻም፡፡ በተመሳሳይ አሉባልታዊ ክስ ከዓመታት በፊት በጥቂት ግለሰቦች ተጀምሮ የነበረውን ዘመቻ ለመመርመር የቻለው የዓለም አቀፉ የአካባቢ ደህንነት ጥበቃ ድርጅት እንኳን ጉዳት ደርሶ ይቅርና ከማንም ቀድመው ጉዳት ሊደርስ ይችላል በሚል የበሰለ አመራር የጉዳት ምንጭ ሊሆን የሚችሉ መሰረቶችን በማስወገድና ከዚያ ያለፈ እንኳን ቢፈጠር ከጥርጣሬ ነጻ ለመሆን የፋብሪካውን ዝቃጭ በዘመናዊ መንገድ አጣርተው ለመጠጥ ንጹህ ውኃ መሆኑ ከመረጋገጡ በፊት ከክልሉ አጥር ውጭ እንዳይፈስ የተወቃሽ ኩባንያው የስራ ኃላፊዎች እያከናወኑ ያሉበትን አርአያነት ያለው ተግባር ተመስጋኝና ተሸላሚ አድርጎ ለዓለም ሕብረተሰብ አስተዋውቆት እንደነበር የዘገባዎች ማህደር አገላብጦ መረዳት ለሚሻ መጠቆሙ ይበቃል፡፡


ታዲያ ዛሬን ዛሬ ወለደውና አጋጣሚውን በመጠቀም ነገር ቆስቁሶ በወደቀ ዛፍ ላይ…. ዓይነት ከንቱ ምኞትን በመተው ከላይ በጠቀስኩት ስንኝ ቋጠሮ አስፍሬው እንደነበረው


ሰው ሁሉ………. እርግፍ አርጎ ትቶ የአሉባልታን ነገር፤
እውነትን ጨብጦ በውሸት ሳያፍር፤
ሥራውን አድንቆ ያለአንዳች ጥርጥር፤
ምናለ ቸሩን ሰው ባለሀብቱን ቢያከብር?
የእግዚአብሔር ስጦታ ጸጋው ሳይጎድልበት፤
ከችግር ተላቆ ዳግም እንድናየው ብንጸልይለት!!

እላለሁ፡፡ ምክንያቱም "ዛፉም አይወድቅም ምሳሮችም ተለቅመው ያልቃሉና" ነው!!
በቸር ይግጠመን

 

በአንድነት ቶኩማ

 

የካድሬዎች ስብሰባ ላይ አንድ ጊዜ በአጋጣሚ የመገኘት ዕድል ገጥሞኝ ነበር። በጊዜው የተሰበሰቡት ሁሉ የሚናገሩት አንድ አይነት ቋንቋ ነበር። ተስብሳቢዎች እምነታቸውና ፍርሃታቸው በአንድነት ሆኖ በላያቸው ላይ ወድቆ ነው ሃሳብ ይሰጡ የነበሩት። ግለሰቦች ነፃ አይደሉም ማህበራቸው እንጂ። ተመሳሳይ ምርት ይመስል እጃቸውን የሚያወጡት በአንድነት ነበር። “እስኪ መቼ እና የቱ ድርጅት ነው ይህንን ድርጅት አሸንፌው አውቃለሁ? ብሎ ሲናገር የተሰማው። የሞከሩ ነበሩ።” አለ ስብሰባውን የሚመራው ካድሬ። የራሱ ሃሳብ አይደለም። የራሱ ሃሳብ ኖሮት የሚያውቅ አይመስልም። ራሴን ስሞግት ይህ እንኳ ስህተት ነው፣ ሰው ሳያስብ እንዴት ይኖራል ስል እኖራለሁ ሁልግዜ ሳስበው። ስብሰባው የግንቦት 20 የድል በዓልን ምክንያት በማድረግ የተሰጠ ገለፃ ነበር። በዓሉ በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ነበር። የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች በአምባሻና በፖኘኮርን ደምቋል። ሙዚቃው በየቦታው ተለቋል። ሰው አልባ ድንኳኖች ሽሩባ በተሰሩ እና ከመንደር ለምን እንደተሰበሰቡ በማያውቁ ደካማ እናቶች ጠባቂነት ተተክለዋል። ወጣት የኢህአዴግ አባላት የተለያዩ እና የተለመዱ መዝሙሮችን እየዘመሩ በእየአውራ ጎዳናው በአይሱዚ መኪና ላይ ተጭነው እየሄዱ ይታያሉ።


የአንዳንድ ቀበሌ ስብሰባ ግን ከሚባለው በላይ ደማቅ ነበር። ጥናታዊ ፅሑፎችም ቀርበዋል። ጥናታዊ ፅሑፍ ካድሬያዊ መግለጫ በመሆናቸው ዕውቀታዊነት ይጎድላቸዋል። የተሰበሰበው የዕውቀት ግምትም አናሳ ነበር ማለት ይቻላል። በተለይም የፓርቲው አባላት የአቋም ድጋፍ ለመስጠት ብቻ የተቀመጡ ነበር የሚመስሉት።


ታዲያ በዚያ ስብሰባ ማግስት ነበር ማለት ይቻላል አገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ችግር ውስጥ ወድቃ የታየችው። ባለፈው ዓመት መሆኑ ነው። እንደዚያ ባለ ቀውጢ ወቅት ነበር አንድ ሁኔታዎችን በቅጡ ያልተገነዘበ ግለሰብ (ካድሬ) የኢህአዴግ መንግስትን ጠንካራነት የተናገረው። የሚገርመው ግን ፓርቲው ከጥቂት ቀን በኋላ ነበር ወደ ጥልቅ ተሃድሶ ገብቻለሁ ያለው። ከመግለጫው በኋላ እንዳየነው ‹‹ጥልቁ ተሃድሶ›› ጥልቅ ሳይሆን ‹‹ብቅ ጥልቅ ተሃድሶ›› ሆኖ ነበር የተገኘው። በምን አወቅን ከዓመት በኋላ ሌላ ጠለቅ ያለ ተሃድሶ አደረግን ብለዋልና።


ባለፈው የኢህአዴግ መንግስት ተጠሪ ንግግር ሲያደርጉ የፓርቲያቸውን ሃያልነት በኩራት ገልፀዋል። የኢህአዴግን ታላቅነት በድፍረት ሲናገሩ ተሰምቷል። ከዚህ ውስጥ ኢህአዴግን “የሚችለው የለም” የምትለው ሃረግ ሰቅጣጭ ናት። ምክንያቱም አንድ ቱባ ባለስልጣን ድርጅታችንን ማለትም ኢህአዴግን የሚችለው የለም ሲሉ ያስቃልም፤ ያሳቅቃልም። ለምን ቢባል ከማን ጋር ተወዳድሮ ማንን አሸንፎ የሚለው ስላልተጠቀሰ። ምናልባት ደርግን አሸንፈናል ከሆነ ኢህአዴግ ብቻውን አላሸነፈም። ሌሎች ሃይሎች ነበሩና። ደርግም መሸነፉ እውነት ቢሆን እንኳ ደርግ የተሸነፈው ራሱን ስላሸነፈ ነው የሚል አተያይ አለ።


የተናጋሪው ኢህአዴግን የሚችለው የለም የሚለው ንግግራቸው ምን አይነት ጊዜን ይጠቁማል? የትናንቱን ነው? የዛሬውን ጊዜ አመላካች ነው? ወይስ የወደፊቱን? አሊያም ዘላለማዊ ጀግንነቱን የሚጠቁም ነው? ሃረጉ የወደፊቱን የሚያጠቃልል ይመስላል። ይህ መፈተሽ አለበት።


ሌላው ይህ ሃረግ (ቃል) ከአውድ ጋር አልተጠቀሰም። ማለትም ለምሳሌ “ተቃዋሚ ፓርቲዎች” “ሻቢያ” “ሶማሊያ” “ግብፅ” ወይም ሌላ አካላት አልተጠቀሱም። በዚህ ሁኔታ ማንም አይችለውም የተባለው ኢህአዴግ ከማን ጋር ተወዳድሮ ነው? የሚል ጥያቄን ያጭራል። ከሻቢያ ጋር በነበረው ጦርነት ኢህአዴግነት ሳይሆን ያሸነፈው ኢትዮጵያዊነት ነው። ድሉ የኢትዮጵያዊያን ነው። ምሳሌ ላክል። ኢትዮጵያ ኤርትራን ማሸነፏ ለእኔ ድል አይመስለኝም። ሁለቱ አገሮች ተመጣጣኝ አይደሉምና። በአዲስ አገርና በዘመናት ከቆየች አገር ጋር የሚደረግ ጦርነት እኩልነት የሌለውን ድል ስለሆነ እርሱን እጅግ መዘመር ተገቢ አይደለም። ኢትዮጵያ ጣሊያንን በምኒልክ ጊዜ አሸንፋ ነበር። ምኒልክም ‘ፓርቲያቸውም’ አሁን የለም። በመሆኑም አንድ ጊዜ ጦርነትን ማሸነፍ ሁልጊዜ አሸንፋለሁ የሚል ሃሳብ ማምጣት የለበትም። በጭራሽ። ማሸነፍና መሸነፍ የጦርነት ወይም የውድድር ህግ ነው።


እኔ እንደሚገባኝ ኢህአዴግ ከሃያላን አገሮች ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ፣ እንዲሁም ከቻይና ጋር ተወዳድረው (ተጋጥመው) አሸንፈው የሚችለን የለም እያሉ አይመስለኝም። ኢህአዴግ ያን ያህል ያብጣል የሚል ግምት የለኝም። ማበጥ ግን መብቱ ነው። የእኛ ድርሻ ከተቻለም በዚህ አቅጣጫ ዕብሪት ማስተንፈሻ የሚባል ‹‹እውነተኛ ጥልቅ ተሃድሶ›› ያደርጉ ዘንድ ማመላከት ነው። የዕብጠቱን መጠንና ጥልቀት መመርመር ብቻ ነው ተግባራችን። የዕብጠቱን የመነሻ ፍልስፍናንም የመመዘን ሃላፊነትም ቢኖረንም።
በመሆኑም ህወሓት /ኢህአዴግን ‘የሚችለው የለም’ የሚለውን ቃል ለመዋጥ ብዙዎች ይቸገራሉ። ተቀባይነት የሌለው ሃረግ ነው። ቃል ወይም ወኔ ብቻ ነው። ወኔውንም የተሰነቀው ከጭብጥ አይደለም ወይም ወኔው የተቀዳው ከእውነት አይደለም። ተጣርሶሽ ነው። ለመሆኑ ባለፉት 25 ዓመታት በግልፅ ከዚያም በፊት ከ15 - 17 ዓመታት በስውር ኢህአዴግ የተሸነፈ ድርጅት መሆኑን ያውቃሉ? ማንም ባገኘው አጋጣሚ ዘርሮታል። ለኔ ጥልቅ ተሃድሶው ጥልቅ የሚሆነው የሚከተሉትን ነገሮች ማሸነፍ ከቻለ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ሳይሆን ‹‹ብቅ ጥልቅ ተሃድሶ›› ነው የሚሆነው። በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አካላት ሰሞኑን የተሰጠው መግለጫ ከብቅ ጥልቅ ወደ ጥልቅ መሸጋገሩን የሚከተሉትን ሃሳቦች በተግባር ፈፅሞ ሲገኝ ነው፡፡ እስከአሁን ባስተዋልነው ነገር ግን በሚከተሉት ጉዳዮች ተሸንፏል፣ ማሸነፉን የምናውጅለት፡-

1. ዲሞክራሲን ማስፈን ሲችል፡-
ኢህአዴግ የተሸነፈ ድርጅት እንጂ ያሸነፈ አለመሆኑን የሚያሳዩ ነገሮች ነቅሶ ማውጣት ተገቢ ነው። ኢህአዴግ በሚመራበት ወይም እመራበታለሁ ባለው የድርጅት መርህ ተሸንፎአል። የመጀመሪያው ከስሙ ተነስተን ዴሞክራሲያዊ ያውም የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲ አጐናፃፊ ነኝ ይለናል። ይህ ግን ሐሰት ነው። ለምን ቢባል ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ አይነት ነውና። በኢህአዴግ ውስጥ ዲሞክራሲ የለም። ህዝብም የለም። የድርጅት ሥምና መልክ ምናልባት ይኖራል። አሁንማ ከእነአካቴው ድርጅትም የለም እየተባለ ነው። በዚህ ኢህአዴግ ውስጥ ዲሞክራሲ እንደሌለ ፃድቃን ገ/ትንሳኤ (ሌ/ጀኔራል) እና ገብሩ አስራት ገልፀዋል። ድርጀቱን “ፀረ ዲሞክራሲ ሃይሎች የመሸጉበት” ሲሉ። በመሆኑም በፀረ ዲሞክራሲ ሃይሎች የተሸነፈ ነው። ዲሞክራሲያዊነት የለም። በሌላ በኩል ህዝባዊ ድርጅት ሳይሆን የአድርባዮች ዞን ነው። የጥገኞችና የአለአግባብ መበልፀግ የሚፈልጉ ሃይሎች ምሽግ ነው። ከራሱ ከኢህአዴግ አንደበት እንደሰማነው ከሆነ “ግለኝነት እና ቡድነኝነት - ከመርህ አልባ ግንኙነት ጋር ተጋብቶ ግለኝነት የነገሰበት ድርጅት ነው ማለታቸውን እናስታውሳለን።

2. የመስመር መገለባበጥን ሲያሸንፍ፡-
ምሳሌ ለመስጠት ድርጅቱ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ከልማታዊ መንግስት በቀላሉና ባልተጠና መንገድ አጋብቷል። ከነጭ ኮሚኒስት ወደ ነጭ ካፒታሊስት ተሸጋግሯል። ይህ መሸጋገር የሆነው በአንድ ግለሰብ መገለባበጥ ምክንያት የመጣ ነው። “ሃቀኛ ኮሚኒስት ፅኑ ነው” የሚለውን ዘንግተው ይኖራሉ። እንኳን ህዝባዊ ሊሆን ድርጅታዊ እንኳ መሆን አልቻለም። አውራ ፓርቲና ተቃዋሚ የሚባል ድርጅታዊ ማጥቂያ መሣርያዎች መጣል አልቻለም። የዲሞክራሲ እጥረት ነው። “በምግብ ራሷን ያልቻለች ሃገር” እንደሚባለው “በዲሞክራሲ ራሷን ያልቻለች” የሚል እንዳይጨመርባት ማድረግ ሲችል ነው።

 

3. በወጥ አልባ የመስመር ዕውቀት ከመሸነፍ ሲያመልጥ፡-
የኢህአዴግ አደረጃጀት ወዛደራዊ ዓለም አቀፋዊነት ወይስ ጠባብ መንደርተኝነት? ድርጅቱ በኮሚኒስት መርህ የተመሰረተ ከሆነ ወይም ከነበረ ወዛደራዊ አለማቀፋዊነት ላይ ያጠነጠነ መሆን ነበረበት። አብሮነት ላይ ትኩረት የሚያደርግ። ድርጅቱ ይህን ኮሚኒስታዊ ፍልስፍና ታቅፎ መርሆውን እርግፍ አድርጐ ከመጀመሪያው የጣለ ነው። ብሔርተኛ ያውም ጠባብ ድርጅት ነው። የህወሓት ሰራዊት ከትግራይ ነፃነት በኋላ አልዋጋም ያለው እኮ በጠባብነት ተቀስቅሶና ተቆስቁሶ ስላደገና ስለመጣ ነበር። ድርጅቱ ጠባብነት እየዘረረና እያንደባለለው ያደገ ድርጅት ነው። ኢትዮጵያዊነት የድርጅቱን ዘውገኛ አስተሳሰቡን ሰብሮታል። የድርጅቱ ዘውገኛ አመለካከት የጉልበት መቅኖን ኢትዮጵያዊነት አፍስሶታል። መሸነፍ ማለት ይሄ ነው። ዝረራ። ተሃድሶው ለኢትዮጵያ ለአንድት የሚሰራ ድርጅት ካላደረገው ብቅ ጥልቅ ተሃድሶ እንጂ ጥልቅ ተሃድሶ ሊሆን አይችልም።

 

4. ፀረ - ህገመንግስት ሥርዓት አልበኛነትን ማስወገድ ሲችል፡-
ድርጅቱን ፀረ ህገ መንግስት ፍልስፍናዎች አሸንፈውታል። ህገ መንግስቱን ከለላ ሊያደርግለት ቀርቶ ሊጠብቀው አልቻለም። የፌዴራል አደረጃጀቱ ዋናው ባህልን፣ ቋንቋን እና መልክኣ ምድርን መሰረት አድርጐ ነው ይላል። ነገር ግን ፌዴራሊዝሙን በደንብ በጥልቀት ስንመለከተው ቋንቋን ብቻ መሠረት ያደረገ ነው። በዚህም ቢሆን ይህ አደረጃጀት በደቡብ ክልል አልተሣካም።

5. በመልካም አስተዳደር እጦት ከመሰቃየት ሲድን፡-
ህወሓት/ኢህአዴግ በመልካም አስተዳደር እጦት ተዘርሯል። ታዲያ ምኑ ላይ ነው “አይሸነፍም፣ የሚችለው የለም” የተባለው። ተፈረካክሷል እንጂ። ኢፍህታዊ የሃብት ክፍፍል ኢህአዴግን መጫወቻና መዘባበቻ አድርጐታል። ተሸንፏል። ከዚህ ጋር ድርጅቱ የሙስና መፈልፈያ ሆኗል። ዝሆኔ ሙሰኞች የጥቃቅን ሳር ሙሰኞችን ረግጠዋል። ለነገሩ በጥቃቅን የተደራጁትስ በሙስና ጉዳይ መች የዋዛ ሆኑ! ድርጅቱን ሙሰኛ ብቻ ወሮታል። “ልማታዊ መንግስት” የሚለውን “ሙሰኛና የብድር መንግስት” ቢባል ይሻላል። አንዳንዶች ወጥ ሙሰኛ ወይንም (Systemic) ሥርዓታዊ ሙሰኛ አጥቅቶታል ይላሉ። በዝረራ ተሸንፏልም የምንለው እዚህ ነው። እንዴትስ ማንም አይችለውም ይባላል? ተሃድሶው እውነት የሚሆነው ይህ ሲስተካከል ብቻ ነው።

 

6. በዘውገኛ ወረበሎች (በጋንጐች) ከመወረር አርነት ሲወጣ፡-
ምሣሌ ላንሳ። የንግዱ ማኀበረሰብ ወይም መንግስታዊ ነጋዴዎች ማለትም በዘርና በደም ንክኪ በሃብት የበለፀጉ ግን በመንፈስ የደቀቁ የግል እስር ቤት አላቸው ተብሏል። የነጋዴዎችን እስር ቤት ለመጀመርያ ጊዜ የጠቆሙት ጠቅላይ ምኒስትሩ ናቸው። የነጋዴው ያውም የጥቂቱ ማኀበረሰብ አባላት በሚገባ ኢህአዴግን ዘርሮታል። ወይም አሸንፎታል። ለዚህ ነው ባለፈው የተደረገው ተሃድሶ ብቅ ጥልቅ እንጂ ጥልቅ አይደለም የምንለው።


ተመልከቱ እነዚህ ነጋዴዎች የሃብት አፄዎች ናቸው። በጉልበታቸው አሸንፈው የወጡ። ወጥ ጉልበተኞች። ከእግር ጥፍር እስከ እራስ ፀጉር ማሸነፍን የታደሉ። መሸነፍ የማያውቁ። የፈለጉትን የሚያንቁ። ኢህአዴግን ያሸነፉ የንግዱ ማኀበረሰብ ጥገኛ አባላትን ማንነታቸውን እንዲህ አያቸዋለሁ። የሀብት ጉልበት ያመጣው አፄነት። ‹‹ከመንግስት ጋር በመጋባት የመጣ አፄነት››።
በዘውግ ከለላ የሰለጠነ አፄነት። በስውር የሃብት ምንጭ የመጣ አፄነት። እነዚህ የንግዱ ማኀበረሰብ አፄዎች ኢህአዴግን አሸንፈውታል። ያውም በዝረራ! በምን አወቅን? የአገሪቱ ቁንጮ ባለሥልጣን ነግረውናል! ኢህአዴግን የሚችለው የለም ይበሉን እንጂ አሸናፊው “ሙሰኛው ጠንካራ መሰረት” ያለው ነው ሲሉ ያውም አንድ እጃችን ታስሯል እስኪሉ ያደረሰ የሙስና አፄነት።

7. መንግስታዊ ሙስናን ነቅሎ ጥሎ ስናይ
ድርጅቱን ተቋማዊ ሙስናም ዘርሮታል። የዘውግ ሙስናም ወይም የመንደር ልጆች ሙስናም አንበርክኮታል። የአባላት (አድርባይ) ሙስና አንከባሎታል። የመርህ አልባ አባላት ድርጊት መሣቂያ መሣለቂያ ከዚያም መሣቀቂያ አድርጐታል። ታዲያ ድርጅቱን ማንም አይችለውም እንዴት ይባላል? ሁሉ የሚዘርረው ድርጅት ሆኗል እኮ!። knock out!!! ተሃድሶው ይህን ሽንፈቱን እንዲያሸንፍ ካልረዳው “ብቅ ጥልቅ” ተሃድሶ እንጂ “ጥልቅ” አይሆንም።

 

8. ዝግ በረኝነትን በተከፈተ በር ሲተካ፡-
ከዚህ ሌላ ኢህአዴግን ማንም የማያሸንፈው ድርጅት ነው የምንለው በነፃ ውድድር (ፉክክር) ተሸንፎ ስላየነው ነው። ለምን ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ያዳክማል? ለምን በጡንቻ ያምናል? በውይይት ተሸንፏላ!። ለመሆኑ ኢህአዴግ ውይይት ይወዳል? የኢህአዴግ ጉባዔ የጠንቋይ ስብሰባ ይመስል ባላውቃቢው ይናገራል። ከዚያም ካዳሚዎቹ አሜን ይላሉ። አስጠንቋዮች (ባለጉዳዮች) ተቀብለው ያስተጋቡታል። ጥልቁ ተሃድሶ ድርጅቱን ለውይይት ክፍት ካለደረገው ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ አይደለም።


ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ማለት ይሄ ነው። “የጠንቋይ ማዕከላዊነት።” ፍርሃት ያጠቃው ድርጅት በመሆኑ ውይይትን ይፈራል። ውይይት ለኢህአዴግ የተጠመደ ፈንጅ ነው። ገብሩ አስራት እንደገለፁት እኛ ከተማ ከገባን በኋላ አዲስ ነገር የሆነብንና ለመቀበል የተሳነን ሁለት ነገር ነው ብለውናል።


አንደኛው ሥር ነቀል ተቋማዊ ለውጥ ማድረጋችን ሥህተት ነበር። ምክንያቱም ከሌላው ጋር ለመስራት የማንችል መሆናችንን ያሣያል ብለዋል። ይህም የመጣው ከጠባብነት የተነሳ ነው። የሽምቅ ውጊያ አስተሣሰባችን ይሉታል። ሁለተኛው ችግራችን የፖለቲካ አቅጣጫችን ለመወሰን ምልዓተ ህዝብን አለማሳተፋችን ነው ይላሉ።


እንደ እርሳቸው አባባል በድርጅት ውስጥ የበላይ አካላት አምነን ያፀደቅነው ለህዝቡ ማውረድ ነበር አካሄዳችን። ትክክለኛ ነው፣ ይበጅሃል፣ በማለት አቋማችንን ህዝቡ ላይ መጫን ነበር ባህላችን ብለውናል (ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ ገጽ 149)። ለዚህ ነው የጠንቋይ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ነው የምንለው። ፀረ ውይይት አቋሙ አሁንም መሸነፉን ያሳብቃል። በህወሓት ቋንቋ ዝግ በረኝነት ማለት ይህ ነው።

9. ሰባዊ መብትን አክብሮ ሲገኝ፡-
ህወሓት /ኢህአዴግ ፀረ ውይይት ድርጅት ነው። ይህ ብቻ አይደለም ነፃነት የሚል ስም ይኑረው እንጂ ነፃነትን አያውቅም። “ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጭም” ተብሏል። ነፃ ተቋማትን አጥፍቷል። ነፃ ሚዲያን ከሚገባው በላይ አዳክሟል። ሥራ አጥነት ተበራክቷል። ርሃብና ሞት በዝቷል። የአፈናና የጭቆና ምርቱ በዝቷል። የሰው ልጅ ሰብአዊ መብቶች አልተከበሩም። በመሆኑም ድርጅቱን ኢሰባዊነት አሸንፎታል። የሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተንደዋል ወይም ከሚገባው በላይ ተገድበዋል። ገዳቢ ድርጅት ነው። “ከአምባ-ገነንነት” ወደ “አገር- ገነንነት” ተሸጋግሮአል። አምባ ሰፈር መቀመጫ ማለት ነውና። ኢህአዴግ ከዚያም አልፎአል። ይህን በፍጥነት እርምት ወስዶ እና አሻሽሎ ካልታየ ተሃድሶው ተሃድሶ አይሆንም።

 

10. ዙፋን ናፋቂነትን ሲያርም፡-
ህወሓት/ኢህአዴግ እንደመጣ ወይም አገሪቱን እንደተቆጣጠረ የኢህአዴግ ስልጣን “የዛፍ ላይ እንቅልፍ” ነው ብሎን ነበር። በነገሩ የሳቅን ብዙዎች ነበርን። አሁን ስንመለከተው ግን ኢህአዴግ ውስጥ ሥልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ የሚሆንባቸው ለአዋቂዎችና ጠያቂ (መጠይቃዊ) ባለሥልጣናት ብቻ ነው። ኢመጠይቃዊ ባለሥልጣን ከዛፍ ላይ እንቅልፍ ወደ ዛፍ ላይ ዙፋን ተሸጋግረዋል። ወይም ከዛፉ ላይ እንቅልፍ ወደ የስልጣን ሽርሽር ተሸጋግሯል። ዙፋኑን ነግሰውበታል። መውረድ፣ መውደቅ፣ መንገዳገድ የላቸውም። እነዚህን የመሣሰሉ ነገሮች የሌሉበት ሥልጣን ያለው በዚህ ድርጅት ነው። በስልጣን ማማ ላይ መክተም ብቻ ነው ዋና ግቡ። ድርጀቱ በዙፋን ናፋቂነት ተሸንፏል። እንዲያውም ሥርወ መንግስት መስርቷል። አንዳንዱ ሥልጣንና መስሪያ ቤትማ ርስት ሆኖ እየታየ ነው። ርስታዊ ባላባትነት አሸንፎታል። ስልጣንን ማጋራት አለማወቁ ብቻ ሳይሆን አለመፈለጉን እስካላረመ ድረስ አልታደሰም።

11. መንደርተኝነት ጥሶ ሲወጣ፡-
ድርጅቱ ሌሎችን በጠባብነት እየከሰሰ በጠባብ ሃይሎች የኮሰሰ ነው። መንደርተኝነት ይታይበታል። ከመጀመሪያውም ከሶሻሊስት አለም አቀፋዊ አስተምህሮ አፈግፍጓል። ከኢትጵያዊነትም አፈግፍጓል። ስልታዊ አይደለም አቋማዊ ነው። በትግራይ “የትግራይ ልጆች” ብቻ መታገል ይገባቸዋል የሚለው የበረሃ አቋሙ በቂ ማሳያ ነው። ከአለም አቀፋዊነት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትም በታች የወረደ ነው። በመንደርና በቀበሌ ደረጃ የተዘወገ ነው። ኢህአዴግን የድርጅቶች ሹክቻ አሸንፎታል። በኢህአዴግ ውስጥ የበላይ ሆኖዓል እየተባለ የሚታማ ድርጅት አለ። የበላይ ካለ የበታች አለ። የበታቾቹ በራሳቸው ይህን አምነዋል። የበታችነት የሚሰማቸው የድርጅት አባላት ህዝቡ ይህን ሃሳብ ሲያነሳ እና ሲታገል ይደሰታሉ። በውስጣቸው የታጨቀውን የበታችነት የሚታገልላቸው ስለሆነ ነው። ሌላ አይደለም። ይህ የሚያስደስታቸው ይህ ትግል ምናልባት መዘወሩን አሽቀንጥሮ ወደ ላይ ያስፈነጥረናል ከሚል ሊሆንም ይችላል። ህወሓት ኢህአዴግን አሸንፎታል እየተባለ ይወራል። ይህ እስካልተስተካከለ ድረስ ተሃድሶው ዘበት ነው። ብቅ ጥልቅ ብቻ!

 

12. ተንበርካኪነትን ሲጸየፍ፡-
ኢህአዴግ ተንበርካኪ ነው። ይህን ያሉት እነ ሥየ አብርሃ ናቸው። የኒኦ-ሊብራሊዝም ተቃዋሚው ደንበኛ የኒኦ ሊብራሊዝም ሰለባ ሆኖ ተገኝቷል። ድርጅቱ በውጭ ሃይሎች ላይ የተንጠለጠለ ጥገኛ ድርጅት ነው። የተላላኪ ጦረኝነት (ፕሮክሲይ ዎር) የሚባለው የዚህ ደንበኛ ማሳያ ነው። አንድ ጊዜ ፕሬዝዳንት ኦባማ አሜሪካውያን ሶማሊያ ገብተው አይዋጉም አሉን።
ለምን ለሚለው ጥያቄ ሳይጠየቁ የሰጡት መልስ ኢትዮጵያውያን ጐበዝ ተዋጊ ናቸው አሉን። ይህ ተላላኪነት ነው። ተንበርካኪነት። የኢህአዴግ አንበሳነት በሰላማዊ አሮጊቶችና ህፃናት ላይ ብቻ ነው። ኢህአዴግን ህፃናት አይችሉትም። አሮጊቶችም አይችሉትም። ተንበርካኪነትን ግን ሊቋቋም አይችልም። ፖለቲካዊ ብልጠት አይምሰላችሁ። ሥሪት ነው። አባላቱ አልባኒያ ሆነዋል። አረብን መስለዋል። ሙስሊም መስሎ የሙስሊሙን አለም ለማሳመን የተላከው ግለሰብ ምስክር ነው። ነጭ ኮሚኒስት ሆነዋል። ነጭ ካፒታሊስትም መስለዋል። ሽታቸው ልውጥውጥ የሚለው ተንበርካኪ ስለሆኑ ነው። የሐሰት ፕሮፖጋንዳው ከዚያ የፈለቀ ነው። ድርጅቱ “ኢህአዴግ ማንም አይችለኝም” ለማለት የሞራል ብቃት የለውም። ወይንም በማሸነፍና በመሸነፍ መካከል ያለው የትርጉም ልዩነት አልገባውም። አሊያም እያሸነፈ የሚመስለው በራሱ ጩኸት በዝግ በረኝነት ባህሪው ታፍኖ የካድሬ ስብከት እያዳመጠ ነው።


ኢህአዴግማ መች ኢትዮጵያዊነትን ማሸነፍ ቻለ? ለ4ዐ ዓመት ሊያጠፋው ሞክሮ አልቻለም። ባንዲራውንና የባንዲራውን ክብር ለማጣጣል ሞክሮ ተሸንፏል። የባንዲራ ቀንና ህግ ያስወጣው መሸነፍ ነው። ዝረራ ይባላል። በነፃ ምርጫ ውድድር ተሸንፏል። 1ዐዐ% ያሸነፈው እኮ ብቻውን ድንኳን ወጥሮ ነው። ሰው አልባ ውድድር። ተሃድሶው ኢትዮጵያዊነት እስካለነገሰ ድረስ ተሃድሶ አይደለም።


በሽንፈት ሸለቆ እየተንከባለለ ማንም አይችለውም ማለት አይቻልም። ምናልባት በተሸነፈበት ሸለቆ ውስጥ ያገኛቸውን አንድ ሁለት ትንኞች በእግሩ ደፍጥጧል መሰል ኢህአዴግን የሚችለው የለም የሚባለው ለዚያ ነው።


እንደ እውነቱ ከሆነ ኢህአዴግ ከፍልስፍናውም ርቆ ርቆ አሁን ራሱም የለም። ኢህአዴግ የሚለው ምህፃረ ቃል ሲተነተን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ማለት ነው። አሁን በዚህ ሥም የተመሰረተው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሊሆን አይችልም። በዘውግ ስለተደራጀ የኢትዮጵያን ህዝብ ሙሉ ውክልና ለማግኘት የደነቀረው ቃል ይመስለኛል። ህዝቦች የሚለው አባላት ለማለት ካልሆነ በስተቀር የህዝብ ውክልናው ጥያቄ ውስጥ ነው። ዴሞክራሲው የለም። አብዮት ያካሄደ እንጂ አብዮታዊ (Progressive) ያልሆነ ድርጅት ነው። መስመሩ፣ አመራሩና አካሄዱ የተዛባና ተሃድሶ የሌለው ነው። ለዚህም የተሃድሶው የዘመን ርቀት አመላካች ነው። ለነገሩ በድርጅቱ ግንባር የለም። አዛዥና ታዛዥ ብቻ ነው ያለው። ናዛዥና ተገዥ ነው ያለው። የኢህአዴግ ታጋዮች እንጂ ኢህአዴግ የለም።


በነገራችን ላይ የህወሓት ታጋዮች እንጂ ህወሓት እንደ ድርጅት የለም። ትግራይ ነፃ ወጥታ አላየንማ! የኤርትራ ነፃነት ኤርትራን ነፃ አወጣለሁ ብሎ በተግባር ነፃ መንግስት መሥርቶ አይተናል። ህወሓት ግን መዝሙሩ እንጂ ገቢሩ የለውም። የሥነልቦና፣ የባህልና የታሪክ ትስስሩ አይፈቅድለትም። አልፈቀደለትምም። የትግራይ ሕዝብና መሬት የኢትዮጵያ መሠረትነቱን በቀላሉ የሚለቅ አይደለማ! በመሆኑም ህወሓት ተሸንፎአል። አላማውን አላሳካም። በኢህአዴግና በኢትዮጵያ ጥላ ሥር የተሸጐጠ ድርጅት ነው። አድርባይነት ይታይበታል። ነጥሮ አልወጣም። እንደ ብአዴን ‹‹ህዝባዊ ወያኔ ትግራይ ንቅናቄ (ህወትን)›› ሊሆን አልቻለም። ወይም ከነጻ አውጭነት ወደ ዴሞክራሲያዊ ግንባር መሸጋገር አልቻለም ሌሎችም ድርጅቶች ያሉ አይመስለኝም። በመሆኑም ኢህአዴግ ተብሎ የነበረው ድርጅት አባላት ያለ ኢህአዴግ ሥልጣን ማማ ላይ አሉ። ድርጅቱ ተሸንፏል የምንለው ለዚህ ነው። ጥልቁ ተሃድሶ ከዚህ በላይ ያሉትን ሃሳቦች ካልዳሰሰ ብቅ ጥልቅ ተሃድሶ እንጂ ጥልቅ ተሃድሶ ሊሆን አይችልም። ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› ይሉ ነገር እንዳይሆን!

 

ኢዛና ዘ መንፈስ

 

ኢህአዴግን ጨምሮ ዛሬም ድረስ ያሉ አብዛኛዎቹ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጋሯቸው ተወራራሽ ባህርያት ስለመኖራቸው ደፍሮ መናገር ይቻላል። የመጀመሪያውና ምናልባትም ዋነኛው የሀገራችንን ፖለቲከኞች በእጅጉ የሚያመሳስላቸው ነጥብ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች እንደ ህብረተሰብ በሌላው ዓለም ማህበረሰብ ዘንድ የምንታወቅበት ህብረ ብሔራዊ የጋራ ማንነታችን ከተሰራበት ድርና ማግ የሚመነጩ፤ አወንታዊ አልያም ደግሞ አሉታዊ ጎኖችን የሚወራረሱበት አግባብ መኖሩ ነው። እንዲሁም ደግሞ በተደራጀ መልኩ የሚደረግ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴን ለሀገራችን ህዝቦች አስተዋውቀዋል ተብሎ የሚታመንባቸው፤ የ1960ዎቹ ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ፈላጊ ምሁራን ወጣቶች ላይ በወቅቱ ይንፀባረቅ ከነበረው፤ ግራ ዘመም ዕዮተ-ዓለማዊ አስተሳሰብ ጋር ተያይዞ የሚገለፅ የኢ.ዴሞክራሲያዊነት ግትር አቋም አሁንም ድረስ ሲፈታተነው የማይስተዋል ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ የለም የሚለው አስተያየት እንደ ሁለተኛ የሁሉም ፖለቲካዎች የጋራ ባህርይ ሊወሰድ የሚችል ሆኖ ይሰማኛል።


ይህን ስል ግን የፓርቲ ፖለቲካ ታሪካችን አሉታዊ ዳራም ሆነ ከኢትዮጵያዊያን የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦች ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ስረ መሠረት የሚመነጩት ተወራራሽ ባህርያት የሚገለፁበት አግባብ እያንዳንዱ የሀገራችን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በዕኩል መጠን የሚታይ ተፅእኖውን እያሳደረ ነው ማለታችን አይደለም። ይልቅስ ዛሬም ድረስ ባሉት የሀገራችን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ተደጋግሞ የሚስተዋለው የአመራር አካላት ውስጣዊ የዕርስ በርስ ሽኩቻና የቡድን ጎራ ለይቶ መጠላለፍ ከሚከሰትበት የዘመነ መሳፍት ኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ሴራ የማውጠንጠን ጎጂ ባህል የፀዳ ድርጅት ይኖራል ብሎ መጠበቅ እንደሚያዳግት ልብ ትሉኝ ዘንድ ነው እኔ የፈለግኩት።


በሌላ አነጋገር የመጠን ጉዳይ እንደሁ እንጂ ከላይ ለአብነት ያህል የተነሱት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ስር የሰደዱ ችግሮች አይመለከቱኝም ሊል የሚችል አንድም ፓርቲ፤ ድርጅት፤ ግንባር፤ አሊያም ደግሞ ህብረትና መድረክ ወዘተ በዚህ አገር ውስጥ ይኖራል ተብሎ እንደማይጠበቅ ይታመናል ማለቴ ነው። ይህ አስተያየት የተጋነነ መስሎ የሚሰማው አንባቢ ካለም ደግሞ፤ በተለይም ከ1960ዎቹ ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ ስም እየተመሰረቱ እንታገልለታለን የሚሉትን ዓላማ ከማሳካት አኳያ ብዙም ርቀው ሳይጓዙ ያልተጠበቀ የገዛ ራስ ውስጣዊ ድክመት እያጋጠማቸው ሲፈራርሱና የአንድ ወቅት ታሪክ ሆነው ሲቀሩ ስለተስተዋሉ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስታውስ ዘንድ እመክረዋለሁ።


እንግዲያውስ ይሄን የሀገራችን ፖለቲካና ፖለቲከኞች ከትናንት እስከ ዛሬ የሚታወቁበት እጅጉን ስር የሰደደ ውስብስብ ዕርስ በርስ እየተጠላለፉ ተያይዞ የመውደቅ ችግር፤ እንዴት መፍታት እንደሚቻል ያሳየ ረጅም የትግል ጉዞ ስለመጓዙ የሚነገርለት ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች የፀረ ጭቆና ትግል መስመር ለምን ፈተናዎቹን በማለፍ ረገድ ‹‹ከሌሎች ፓርቲዎች የተሻለ ነው›› የሚያሰኘውን አንፃራዊ ውጤት እያመጣ እንደቆየ ለመመልከት የሚረዱንን አንዳንድ ነጥቦች ለማንሳት ነው እንዲህ መደርደሬ።


ስለሆነም እኔ ገና ከትጥቅ ትግሉ ዘመን ጀምሮ የማውቃቸው ከውስጣዊ ድክመት ለሚመነጭ ፖለቲካዊ ችግር፤ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በተከተለ የግምገማና የውይይት ሂደት አማካኝነት፤ ጎጂውን ሃሳብ ከጠቃሚው እየለዩ የትግሉን ጉዞ ከመገታት የሚታደግ ፖለቲካዊ መፍትሔ ሲያስቀምጡ የተስተዋሉበት የታሪክ አጋጣሚ ጥቂት እንዳልነበር ደፍሮ መናገር ይቻላል። ለዚህ አስተያየቴ ተጨባጭ ምሳሌ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚገባው የትጥቅ ትግሉ ዘመን ታሪክም፤ አንጋፋዎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ህውሐትና ብአዴን የየራሳቸውን ድርብርብ ፈተና ለማመን በሚያዳግት የዓላማ ፅናት እየተሸገሩ ስለመምጣታቸው የምንረዳበት የውስጣዊ ትግል መድረክ እንደሆነም ደፍሮ መናገር የሚቻል ይመስለኛል።


ከዚህ አኳያ መወሳት ይኖርበታል የምለውም ደግሞ ‹‹ኢ.ህ.አ.ፓ.የገደለውን የትግል ወኔ ኢ.ህ.ዴ.ን ነፍስ ይዘራበታል!›› የሚል መፈክር አንግበው የተነሱ ጥቂት ተራማጅ ታጋዮች የዛሬውን ብአዴን፤ የያኔውን ኢ.ህ.ዴ.ን ከመመስረት ጀምሮ፤ የገጠማቸውን ድርጅታዊ የፖለቲካ አቋም መዋዠቅ ችግር ባልተቋረጠ ግምገማና ውይይት አማካኝነት እልህ አስጨራሽ ጥረት አድርገው የትግል መስመራቸውን ለማጥራት የቻሉበት የፖለቲካዊ መፍትሔ አሰጣጥ መድረክና እንዲሁም ህውሐት የአስር ዓመት የትጥቅ ትግል ጉዞውን የገመገመበት የ1977ቱ ጥልቅ ተሃድሶ ነው።


ይሄን ዓይነቱ ከግንባሩ አባል ድርጅቶች የጀርባ ታሪክ ጋር በተያያዘ መልኩ እየዳበረ የመጣ ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ የመፍትሔ አቅጣጫ የማስቀመጥ ጠቃሚ ተሞክሮ፤ ከደርግ ውድቀት በሁዋላም ጭምር ኢህአዴጋዊ የትግል ባህል ተደርጎ እስኪቆጠር ድረስ ሲሰራበት እንደቆየም ይታወቃል። ስለሆነም በ1993ዓ/ም የተካሔደውን ሁሉንም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ያካተተ የተሃድሶ መድረክ ጨምሮ፤ሌሎችም የገዢውን ፓርቲ መሠረታዊ ዓላማ የሚፈታተን የፖለቲካዊ አቋም መዋዠቅ (የአስተሳሰብ ብዥታ) ችግር ሲያጋጥሙ መሰል ፖለቲካዊ መፍትሄ ማስቀመጥ የተለመደ ጉዳይ እንደሆነ ማስታወስ ይቻላል።


እናም ይሄው ኢህአዴግን ከአብዛኛዎቹ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለየ ስፍራ የሚያሰጠው ጠቃሚ የትግል ባህል የሚገለፅባቸው ድርጅታዊ እሴቶች ናቸው ግንባሩ በየወቅቱ የሚያጋጥሙትን ውስብስብ ፈተናዎች ሁሉ፤ እንደ ምንም ተጋፍጦ እያለፈ የትግሉን ጉዞ የማስቀጠል ታሪካዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ በማድረግ ረገድ ቁልፍ የሚባል አወንታዊ ተፅእኖ የሚያሳድሩት። ከዚህ የተነሳም ነው ኢህአዴግ በራሱ ውስጣዊ ድክመቶች ምክንያት ተገዝግዞ ሲወድቅ ማየትን የሚናፍቁት ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች፤ ግንባሩ እንደ አንድ ጠንካራ ገዢ ፓርቲ የሚታወቅባቸውን ጠቃሚ የፖለቲካዊ ትግል ዕሴቶች ለማውደም ያለመ ፈርጀ ብዙ ደባ በመፈፀም ዕኩይ ተግባር ላይ መጠመድን እንደ አዋጭ የትግል ስልት የቆጠሩት።


በተለይም ደግሞ ከ1997ቱ ጠቅላይ ምርጫ በሁዋላ፤ የትምክህተኝነትንና የጠባብ ብሔርተኝነትን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ከከረረና ከመረረ ፅንፈኛ አቋም በመነጨ መልኩ ሲያቀነቅኑ የሚስተዋሉት የተቃውሞው ጎራ ሃይሎች፤ ያለ የሌለ አቅማቸውን አሰባስበው የሚረባረቡት ኢህአዴግ እንደ አንድ በፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግል ሂደት ውስጥ አልፎ የመጣ ገዢ ፓርቲ በረጅሙ የትግልና የድል አድራጊነት ታሪኩ ያዳበራቸውን ጠቃሚ ለፖለቲካዊ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ ማስቀመጫ የድርጅታዊ ባህል እሴቶች ዋጋ ለማሳጣት ያለመ ደባ መፈፀም ላይ እንደሆነ ይታመናል።


እናም እነዚሁ ሃይሎች ከሀገር ቤት እስከ ባህር ማዶ ድረስ በዘረጉት የሴራ ፖለቲካ ፕሮፖጋንዳዊ መረባቸው አማካኝነት የሚያውጠነጥኑት ሃኬት፤ ኢህአዴግ መራሹን ፌደራላዊ ስርዓት ውስጥ -ውስጡን ገዝግዞ ስለመጣል አስፈላጊነት የሚሰበክበት ደባ የመሆኑን ያህል፤ ገዢው ፓርቲ አደጋውን በቅጡ ተገንዝቦ ትርጉም ያለው ለፖለቲካዊ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ የመስጠት እርምጃ እንዳይወሰድ ለማድረግ ያለመ አሉታዊ ተፅእኖ የመፍጠር ግልፅና ህቡዕ እንቅስቃሴ የሚያካሂዱበት አግባብም እጅጉን ቅንነት የጎደለው ኢ-ሞራላዊ ተግባር ነው ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ግን፤ዛሬም ድረስ ኢህአዴግን ‹‹ኢህአዴግ›› ለሚያሰኙት ድርጅታዊ የትግል ባህል ጠቃሚ እሴቶች፤ ህልውና መቀጠል በፅናት ሲቆሙ የሚያስተውሉ የግንባሩ አመራር አካላት እንዳሉ መረዳት አያዳግትም።


ለዚህ ደግሞ አሁን ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ወቅታዊ እውነታ ጋር በተያያዘ መልኩ ያልተለመደ ዓይነት የመፍረክረክ አዝማሚያ የታየበትን፤ የአንዳንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ መራሹ መንግስት የስራ ሃላፊዎች ሰሞነኛ ክስተት ተከትሎ፤ የግንባሩ ስራ አስፈፃሚ ለተከታታይ 17 ቀናት ባካሔደው ዝግ የስብሰባና ግምገማ መድረክ ላይ፤ ያጋጠሙ ፖለቲካዊ ችግሮችን በተለመደው ዴሞክራሲያዊ የውስጥ ትግል ባህል ስለመፍታት አስፈላጊነት ተነስቶ ተስፋ ሰጪ ሊባል ወደሚችል ሀገራዊ የጋራ መግባባት የተደረሰበት ሁኔታ ስለመፈጠሩ የሚያመለክት መልካም ዜና ዓርብ ታህሳስ 20ቀን 2010ዓ/ም ፋና ብሮድካስቲንግ መዘገቡን ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል።


በግልፅ አገጋገር፤ ካለፈው መስከረም ወር 2010 ዓ/ም ጀምሮ ከከፍተኛ የፌደራሉ መንግስት የስራ ሃላፊነታቸው ለመልቀቅ ፈልገው ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጥያቄ ስለማቅረባቸውና በኋላም ጥያቄያቸው ተቀባይነት ስለማግኘቱ ጉዳይ በመገናኛ ብዙሃን እየተዘገበ የሰነበተው አቶ በረከት ስምኦንና አቶ አባዱላ ገመዳ ሰሞኑን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት የተካሔደ ጥልቅ ውይይት ላይ አቋማቸውን ለውጠው በትግሉ ለመቀጠል እንደወሰኑ ጭምር ነው ዜናው አክሎ ያተተው። ታዲያ ከዚህ ወቅታዊ ተጨባጭ እውነታ በተሻለ መልኩ ኢህአዴግ ለፖለቲካዊ ችግሮቹ ፖለቲካዊ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የማስቀመጥ ጠቃሚ የትግል ባህል ያዳበረ ድርጅት ስለመሆኑ የሚያሳይ ማረጋገጫ ያስፈልጋልን ወገኖቼ!? እንደኔ እንደኔ ግን አያስፈልግም ባይ ነኝ።


ስለዚህም፤ ሁለቱ አንጋፋ የኢህአዴግ ታጋዮች (አቶ አባዱላና አቶ በረከት) በዚህ ሀገራችን ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ በምትገኝበት እጅጉን አሳሳቢ የፈተና ወቅት፤ ከታሪካዊው ሃላፊነታቸው የማፈግፈግ አዝማሚያን ያሳዩበት አግባብ፤ ትክክል አለመሆኑን ተረድተው አቋማቸውን ለመቀየር መወሰናቸው፤ ለመላው የትግሉ ሰማዕታት የገቡትን ክቡር ቃል እንደመጠበቅ ሊቆጠር የሚችል የእውነተኛ ታጋይ መገለጫ ባህሪ ነውና እነሆ ልባዊ አድናቆቴ ይድረሳቸው። ምክንያቱም ደግሞ በረከትና አባዱላ፤ ኢህአዴግ መራሹን የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ጉዞ ለቀው መሔድ አይኖርባቸውም ማለት ባይቻልም ቅሉ፤ ሁለቱም አብዛኛውን ዕድሜያቸውን የፈጁባቸው መሰረታዊ የትግሉ ዓላማዎች ለአሳሳቢ ቅልበሳ አደጋ የተጋለጡ መስለው በሚታዩበት በዚህ ወሳኝ ወቅት መሆኑ ግን ፈፅሞ የሚደገፍ ጉዳይ አይደለም።


እንኳንስ በእነርሱ ደረጃ የሚታወቅ ከፍተኛ የኢህአዴግ ነባር አመራርና ይሄው እኛ ራሳችን ከትምክህትና ከጠባብ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ ጋር የሞት ሽረት ሊባል የሚችል ግብግብ ገጥመን ህብረ ብሔራዊውን የፌደራል ስርዓት ከተጋረጠበት በቀለም አብዮተኞች የመፈራረስ አደጋ በመታገድ ረገድ የሚጠበቅብንን አወንታዊ አስተዋፅኦ ለማበርከት ስንሞክር የምንስተዋለው እኮ፤ እልፍ አዕላፍ የትግሉ ሰማዕታት የወደቁለት መሰረታዊ ዓላማ መና እንዳይቀር ነው።


ስለሆነም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ መርሐ ግብር እንዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ስፋትና ጥልቀት እየጨመረ ሄዶ፤ ግንባሩ በሀገራችን የፖለቲካ ፓርዎች ታሪክ ውስጥ የተለየ ስፍራ እንዲይዝ የሚያደርጉትን የውስጣዊ ችግር አፈታት ድርጅታዊ የትግል ባህል ዕሴቶቹን፤ ለተተኪው ወጣት የአመራር ትውልድ ሊያስረክብ የማይችልበት ምክንያት እንደማይኖር የሚያመለክት ነው ማለት ይቻላል በስራ አስፈፃሚው ሰሞነኛ የግምገማ መድረክ ማጠቃለያ ላይ ስለተወሰነው ውሳኔ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዓርብ ታህሳስ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ያስደመጠን ዜና።


ከዚህ አኳያ ሲታይ፤ በተለይም ካለፈው የመስከረም ወር መጀመሪያ 2010 ዓ.ም ወዲህ አንዳንድ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የአመራር አካላትን በእጅጉ የታዘብንበት ከግንባሩ የትግል መስመር የማፈንገጥ አዝማሚያ፤ የከፋ ሀገራዊ ቀውስ ሳያስከትል የጋራ ግንዛቤ ተወስዶበታል የሚል ተስፋ ብናሳድር ተገቢ እንደሚሆንም ነው የሚሰማኝ። በእርግጥም ደግሞ ስርዓቱን እንደ ስርዓት ላልተጠበቀ የቅልበሳ አደጋ የሚያጋልጥ ፖለቲካዊ የአመለካከት ችግር ሲያስከትልብን እየተስተዋለ ያለው መሰረታዊ ጉዳይ፤ እውነተኛውን የኢህአዴግ ታጋይ ለጊዜያዊ ጥቅም ሲል ብቻ የግንባሩ አባል ድርጅቶች መዋቅር ውስጥ ተሰግስጎ ከሚያምታታው አድር ባይ መለየት የሚያስችል ትክክለኛ የአቋም መለኪያ መድረክ መጥፋቱ እንጂ ሌላ አይደለም።


ስለዚህም መላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈርጀ ብዙ መስዋእትነትን ባስከፈላቸው የዘመናት ፀረ ጭቆና ትግል የተቀዳጁትን ሕገ መንግስታዊ መብትና ነፃነት እንደተራ ነገር ቆጥረው የቀለም አብዮት ሰለባ ሊያደርጉት ከሚሹት ፅንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር መሞዳሞድን እንደ ‹‹መቻቻል›› ወይም ደግሞ የተለየ እውቀት እንደሚጠይቅ የፖለቲካ ጥበብ ሊወስዱት የሚቃጣቸው አድርባዮች እስካሉ ትርጉም ያለው ለውጥ አይመጣምና ሊታሰብበት ይገባል እላለሁ።

 

 

በይርጋ አበበ

 

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሥራ አስፈፃሚነት የተሰናበቱ ነባር ታጋዮችን ያካተተ ስብሰባ ለ17 ቀናት አካሂዶ ከጨረሰ በኋላ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። ከፓርቲው መግለጫ ማግስት ደግሞ የግንባሩ አባል ደርጅቶች ሊቃነመናብርት (የኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ህወሓት እና ደኢህዴን) ሊቀመንበሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ለሁለት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ብቻ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።


የፓርቲዎቹ አመራሮች ሰፋ የለ ሰዓት የፈጀውን መግለጫ ሲሰጡ ዋንኛ ትኩረታቸው በግንባሩ እና በአባል ፓርቲዎቹ ግንኙነት ላይ ያተኮረ ሲሆን ተጨማሪ አገራዊ ጉዳዮችን የዳሰሰ ነጥብም ታክሎበታል። በተለይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ከእስር ቤት መፍታት እና ማዕከላዊ የሚባለውን የምርመራ ማዕከል (እንደ አቶ ኃይለማርያም ገለፃ የደርግ ማሰቃያ ቤት) ዘግቶ ሙዚየም ማድረግ የሚሉት የበርካታ የፖለቲካ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች ሆነዋል።


በእነዚህ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት በማድረግ ምሁራን እና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግረን ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉን አድርገናል። የምሁሩን (ዶ/ር ምህረት አየነው ከፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ) እና ፖለቲከኞቹ (አቶ የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እና አቶ ሙላቱ ገመቹ የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር) የሰጡትን አስተያየት ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

የትኞቹ የፖለቲካ እስረኞች?

 

ላለፉት ረጅም ዓመታት ኢህአዴግ “የፖለቲካ እስረኛ የለም” በሚለው አቋሙ ፀንቶ ቆይቶ ነበር። ታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ሊቃነመናብርት መግለጫ ላይ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ “ለተሻለ ብሔራዊ መግባባት በራሳቸው ጥፋት የታሰሩ የፖለቲካ አመራሮችን እንዲፈቱ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል። የአቶ ኃይለማርያም መግለጫ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ሆነ አባላት የፖለቲካ እስረኞች መሆናቸውን ባይገልፅም ፖለቲከኞች መታሰራቸውን ግን አመላካች ነው። ለዚህም ሲባል የፓርቲዎቹ አመራሮች ከእስር መፈታትና የተመሰረተባቸው ክስ እንዲቋረጥ መደረግ ለአገራዊ ብሔራዊ መግባባት የተሻለ በር ከፋች እንደሆነ መግለጻቸው ፓርቲው “የፖለቲካ እስረኞች የሉም” ከሚለው አቋሙ ማሻሻያ ማድረጉን ያመለክታል ሲሉ ምሁራኑ ይናገራሉ።


የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዳይሬክተሩ ዶ/ር ምህረት አያሌው እንደሚሉት “መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን በተመለከተ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ትርጓሜ ሲሰጠው ቆይቷል። እኔ እስከማውቀው ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች እንደሌሉ ነው፤ የመንግስት አቋም የነበረው። አሁን የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ ሲባል በመጀመሪያ ደረጃ የትኞቹ ናቸው የሚፈቱት? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው። ምክንያቱም ብዙዎቹ የታሰሩት በሽብር ድርጊት ክስ ነው። አሁን አቶ ኃይለማርያም የተናገሩትን ተከትሎ ህዝቡ እየጠበቀ ያለው እነማን ይፈታሉ? እያለ ነው። ሂደቱስ ምን መልክ ይኖረዋል? የሚሉትን ነጥቦች ማየት ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።


የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው “በፖለቲካ ሰበብ የታሰሩ ፖለቲከኞች መፈታት የእኛ ብቻ ሳይሆን የህዝቡም ጥያቄ ነበር። የኢህአዴግ አመራሮች እዚህ ውሣኔ ላይ የደረሱት በህዝብ ያለማቋረጥ ተቃውሞ የፈጠሩት ተፅእኖ ውጤት ነው” ሲሉ ኢህአዴግ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ለመፍታት የደረሰበትን ውሳኔ ምክንያት ተናግረዋል። አቶ ሙላቱ አክለውም “በኢህአዴግ አመራር ደረጃ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ከእስር እንፈታለን ተብሎ ሲነገር እኛም ሆነ ህዝቡ ወይም የታሰሩ ፖለቲከኞች ቤተሰብ ተስፋ ያደረግነው ቃል የተገባው ቶሎ እንደሚፈፀም ነበር። ነገር ግን ቃል በተገባው መሠረት ፖለቲከኞቹ እስካሁን አልተፈቱም። ከዚህም የባሰው ደግሞ የእኛ አባላት በዚህ ሳምንት በወለጋ ታስረዋል” ብለዋል። “ከ25 ዓመት በኋላ የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን ያመነው ኢህአዴግ የህዝብ ቁጣ ገደቡን ጥሶ ስለመጣ ነው” ያሉት አቶ ሙላቱ፤ “ኦፌኮ በስርዓቱ ብዙ የተጎዳ ፓርቲ ነው። ከተወሰንን ዕድለኞች በስተቀር አብዛኛው የፓርቲያችን ስራ አስፈፃሚ አባላት እና እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አባሎቻችን የሚገኙት እስር ቤት ነው። ጽ/ቤቶቻችን ተዘግተዋል” ሲሉ ኦፌኮ ከኢህአዴግ የገጠመውን ፈተና ገልፀዋል።


የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ደግሞ “ቀደም ሲል የፖለቲካ እስረኛ የለም ሲሉ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እሰረኛ የለም ማለት ፀሐይ በምስራቅ ትወጣለች የሚለውን ዓለም አቀፍ እውነታ (General truth) መካድ ነው። ቢያንስ የፖለቲካ እስረኛ መኖሩን ማመናቸውና ለመፍታት መወሰናቸውን እየገለፁ መሆኑ ጥሩ ነው። እንዲሁም የቀድሞ ማዕከላዊ እንደሚዘጋም ገልፀዋል። ዝርዝሩን ትተነው እነዚህ ሁለት ውሳኔዎች ተግባራዊ ከሆኑ መልካም ነው ብለን መውሰድ እንችላለን። ነገር ግን ማዕከላዊን ብቻ መዝጋቱ በቂ አይደለም። ምክንያቱም እኔ ራሴ በ2006 ዓ.ም ማዕከላዊ ሳለሁ ስቃይ ደርሶብኛል። እኛ እዚያ እያለን ለበርካታ ቀናት በሌላ የምርመራ ቦታ ምርመራ ሲካሄድባቸው (አካላዊ ጥቃት የተፈፀመባቸው ሲሉ ይገልጿቸዋል) የቆዩ ሰዎች ስቃዩ ደርሶባቸው እኛን ሲቀላቀሉ አይቻለሁ። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ መቆም ያለበት ስቃይ ነው። ለዚህ ደግሞ ፀረ-ሽብር እና ፀረ-ሽብር ግብረሃይል የተባሉት በአዋጅ ሊፈርሱ ይገባል። ከማዕከላዊ ውጭ ያሉ ማሰቃያ ቤቶች (ምርመራ ክፍሎች) ሊፈርሱ ይገባል” ሲሉ ማዕከላዊ ወደ ሙዚየም እንዲቀየር መወሰኑን አስመልክቶ ሃሳባቸውን ገልፀዋል።


“የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መፈታት በራሱ እንደ ጅምር ጥሩ ነው” የሚሉት አቶ የሽዋስ፤ “የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እንደ ዶ/ር መረራ፣ አንዷለም አራጌ እና በቀለ ገርባ ያሉ አመራሮች ከእስር ተፈተው መነጋገር አለባቸው። ሌሎችም እስረኞች ከእስር ወጥተው ስለ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መስፈን ውይይት ሊያደርጉ ይገባል። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ሳይኖሩ መነጋገር አይቻልምና። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሰው ሃሳቡን ስለገለፀ ብቻ እንደማይታሰር ዋስትና ሊሰጠው ይገባል። የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ የተሰጠው ውሳኔ እንደመጀመሪያ ሃሳብ ሲታይ ጥሩ ነው አልን እንጂ ከዚያ በኋላ ብዙ የምንነጋገራቸው ነገሮች አሉ።” ሲሉ ከፖለቲካ እስረኞች መፈታት በኋላም ብዙ የቤት ሥራ እንዳለ ተናግረዋል።

 

ቃል የተገባው ዘግይቷል?


አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች መሪዎች የዛሬ ሳምንት ረቡዕ ረፋዱ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከእስር እንደሚፈቱ ተናገሩ። ሆኖም እስካሁን ድረስ (ይህ ፅሁፍ እስከተዘጋጀበት ትናንት ምሽት) አንድም የፖለቲካ እስረኛ በምህረት ከማረሚያ ቤት የወጣ የለም። ይህን በተመለከተ ሃሳባቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡት ዶ/ር ምህረት አየነው “የተባለው እኮ የእስረኞቹ መፈታት የገና ስጦታ ነበር። ነገር ግን ምንም የተሰራ ነገር የለም። ይህ ደግሞ ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት ማጣትን ያስከትላል” ብለዋል።


ዶ/ር ምህረት አክለውም “ልክ እንደ አቶ ኃይለማርያምም ሆነ እንደ ሌሎቹ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ሁሉ እነዚህ ሰዎችም (የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን) በአገራቸው ፖለቲካ ጉዳይ ላይ የመሳተፍ መብት አላቸው። ይህ ህገ መንግስቱም የሚሰጣቸው መብት ነው። ነገር ግን በፖለቲካ ስለተሳተፉ ለምንድነው ወንጀለኛ የሚሆኑት? አቶ ኃይለማርያም እና አቶ ደመቀ በፖለቲካ ሲሳተፉ ወንጀለኛ ያልሆኑት እነዶ/ር መረራ፣ አንዷለም አራጌ እና በቀለ ገርባ በፖለቲካ ሲሳተፉ ወንጀለኛ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን አይደሉም እንዴ? የመንግስት ወገን ሲሆን ፖለቲከኛ፤ ተቃዋሚ ሲሆን ወንጀለኛ ነው ማለት እኔ አይገባኝም” ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እስር በተመለከተ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።


የኦፌኮው ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹም ቃል በተገባው መሠረት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባሎች አለመፈታት ቃል የተገባው እንደዘገየ አመላካች ነው ሲሉ ይናገራሉ። አቶ ሙላቱ ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም “አንድ እስረኛ ትፈታለህ ሲባል እያንዳንዷን ሰዓት ነው የሚቆጥረው። ቤተሰብ ይጨነቃል። ይፈታል በተባለው ቀን አለመፈታታቸው የሚያሳየው መዋቅሩ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ነው። ለምሳሌ ከዚህ በፊትም በቀለ ገርባ እንዲፈታ ተወስኖ በራሳቸው ሚዲያ (በመንግስት ሚዲያ) ገልጸው የነበረ ቢሆንም እንደገና እንዲታሰር ነው ያደረጉት። ይህ ደግሞ የሚያሳየው እነዚህ ሰዎች ለሚናገሩት ነገር ምን ያህል ታማኞች ናቸው ወይም እውነተኛ ናቸው? የሚል ጥርጣሬ እንዲነሳ ነው የሚያደርገን። ህዝቡ ውስጥ ያለው ጥርጣሬም ይህ ነው። ምክንያቱም ህዝብ በመንግስት ላይ እምነቱን ካጣ ቆይቷልና።


በሌላ በኩል ደግሞ ጎሮ ላይ ሻምቡ ከተማ በገፍ እያሰሩ ነው። እፈታለሁ ሲል በሌላ በኩል እያሰረ ስናይ የኢህአዴግ መዋቅር እንዴት እንደሆነ ግራ የሚያጋባ መሆኑን ያሳያል። የላይኛው እፈታለሁ ሲል የታችኛው በገፍ እያሰረ ነው። በየቦታው ፀጥታን ለማስከበር የተለቀቀው የታጠቀ ሃይል አነጣጥሮ ተኳሽ ስለሆነ ብዙ ሰው ገድሏል። ይህ አልሞ ተኳሽ ኮማንድ ፖስት ወደ ካምፑ ካልተመለሰ እና የእስሩ አይነት ካልተስተካከለ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ኢህአዴግ የተወሰኑ ሰዎችን እፈታለሁ ብሎ ቢፈታም እምነቱን አይሰጠውም። ምክንያቱም የህዝብ ጥያቄ የታወቀ ነው። የሥርዓት ለውጥ ነው የፈለገው” በማለት ተናግረዋል።


“አሁን የማናግርህ የታሰሩ አባሎቻችንን ለመጠየቅ ወደቂሊንጦ እየሄድኩ ሳለ ነው” ብለው መናገር የጀመሩት የሰማያዊ ፓርቲው ሊቀመንበር በበኩላቸው “ኢህአዴግና ህዝቡ ላይገናኙ ተለያይተዋል” ይላሉ። አቶ የሺዋስ ሃሳባቸውን ሲያጎለብቱም “እኔ እስረኛ ሆኜ ችግሩን አይቻለሁ። እስረኛ ትፈታለህ ተብሎ በተባለው ቀን ካልተፈታ ስነልቦናው ይረብሻል። ወዳጅ ዘመድም አብሮ ይረበሻል። ኢህአዴግ ሰሞኑን ያደረገውም በእስረኞቹ ላይ ግፍ ነው የፈፀመው። ይፈታሉ የተባሉት ሰዎች ቶሎ አለመፈታታቸው የድርጅቱን (ኢህአዴግን) አለመታመን አመላካች ነው” ሲሉ ተናግረዋል።


አቶ የሺዋስ አያይዘውም “ኢህአዴግን እኮ ለማሻሻል (Reform ለማድረግ) የማይመቸው ታማኝ አለመሆኑ ነው። ኢህአዴግ እንደድርጅትም ሆነ በውስጡ ያሉትን ሰዎች እንደ ግለሰብ እንተማመናለን የምትላቸው አይደሉም። ይህን ለማድረግ የሞራልም፣ የሃይማኖትም ሆነ የምንም ሃይል የሚይዛቸው አይደሉም። እንደማንኛውም አምባገነን መንግስት ዛሬ የሚያሳድራቸውን ዘዴ ብቻ ነው የሚያስቡት። ይህ ደግሞ እንዳይታመኑ ያደርጋቸዋል። ለምሳሌ ሰሞኑን በተናገሩት ላይም ብንመለከት እስረኞችን ትፈታላችሁ ብለው ባለመፍታታቸው ስቃይ ነው የጨመሩባቸው። መግለጫውን ከመስጠታቸው በፊት የሚፈቱትን አጣርቶ ነበር መናገር የነበረባቸው። ምክንያቱም የሰማዊም፣ የኦፌኮም፣ የመኢአድም ሆነ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አባላት፣ በወልቃይት፣ በኦሮሚያም ሆነ በኮንሶ ጉዳይ የታሰሩት ይታወቃሉ። ይህንን አጣርቶ መወሰን ደግሞ ቀላል ነው። ነገር ግን ይህን ሳያደርጉ መግለጫ በማውጣታቸው የስንት እስረኛ ቤተሰብ እየተሰቃየ እንደሆነ መገመት ቀላል ነው። ለእኛም በየጊዜው የሚደወለው ስልክ የሚያሳየው የችግሩን ስፋት ነው።” በማለት ይፈታሉ ተብለው ቃል የተገቡ እስረኞች አለመፈታታቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል።


የአራቱ ፓርቲዎች ሊቀመናብርት መግለጫ ይዘት


የኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ህወሓትና ደኢህዴን ሊቀመንበሮች የሰጡትን “ድንገተኛ” መግለጫ ዶ/ር ምህረት አየነው ሲገልጹት፤ “ያልተሰራ የቤት ሥራ ያመጣው ውጤት ነው” በማለት ነው። ዶ/ር ምህረት ሃሳባቸውን ሲያብራሩም “በአገሪቱ ውስጥ የሆነ የበጎ አድራጎት ህግ አውጥቶ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መያዶችን በማፈን ራሱን እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስዎች አጋልጠ ሰጠ። የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ደግሞ የአገር ውስጥ ተቺ መገናኛ ብዙሃንን በማግለል ህዝቡን ለማህበራዊ ሚዲያ አጋለጠው፤ እንደ እነ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አንዷለም አራጌ እና በቀለ ገርባ የመሳሰሉትን ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን በማሳደድ ራሱን ለፅንፈኛ ዲያስፖራ አጋለጠ። እነዚህ ስህተቶች ፓርቲውን ብቻ ሳይሆን አገሪቱንም ወደ ኋላ ጎትተዋታል” ሲሉ በዝርዝር ይናገራሉ። ዶ/ር ምህረት አያይዘውም “አገሪቱ አሁን የምትገኝበት ደረጃ አሳሳቢ ቢሆንም መንግሥት ግን ይህን ያሰበበት አይመስልም” በማለት ገልፀዋል።


አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው መግለጫውን “ሽሽት የበዛበት” ያሉት ሲሆን ምክንያታቸውን ሲያብራሩም “በመጀመሪያ ለመናገር የመጡበትን ምክንያት ማየት ያስፈልጋል። አባል ድርጅቶቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን እና ቅራኔያቸውን መፍታታቸውን ለመግለፅ ነው። እሱ ደግሞ የእኛ ችግር አይደለም። የህዝቡ ችግርም አይደለም። እኔ በበኩሌ ኢህአዴግ ቢፈርስም ደስ ይለኛል። ዋናው የህዝቡ ጥያቄ ይመለስ የሚለው እንጂ የእነሱ ችግር መፈታት አይደለም።


የመግለጫውን ዝርዝር ይዘት ስናየው ደግሞ መጀመሪያ በወረቀት የገለፁት መግለጫ እና ቆይተው የተናገሩት ደግሞ ሌላ ነው። አሁን ሰሞኑን በተከታታይ እየተናገሩ ያሉት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ይህ ጉዳይ በውስጣቸው አለመስማማት መኖሩን ነው የሚያሳየው። ዞሮ ዞሮ የእነሱ ጉዳይ የራሳቸው ነው፤ የእኛ ፓርቲም ሆነ የህዝቡም ጉዳይ አይደለም። የህዝብ ጉዳይ ያቀረበው ጥያቄ ነው። የህዝብ ጥያቄ ደግሞ የሥርዓት ለውጥ ነው። መብራት አምጣልኝ፣ ውሃ ዘርጋልኝ ወይም መልካም አስተዳደር አስፍንልኝ የሚል አይደለም። ምክንያቱም ይህን እንደማያደርግ ላለፉት 27 ዓመታት አይቶታልና። ድርጅቱም በመግለጫው የህዝብን ጥያቄ በተመለከተ የተናገረው የለም። ይህን ለማድረግም አቅም ያለው አይመስለኝም” ብለዋል።


በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት አቶ ሙላቱ ገመቹም መግለጫውን “ጊዜያዊ ማምለጫ ነው” ብለውታል። ዘለቄታዊ መፍትሄውን በተመለከተ ሲናገሩም አፈና እንዲቆም፣ ነፃ ሚዲያ፣ ነፃ ፍ/ቤት፣ ነፃ የደህንነት ተቋም ሊገነባ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ያቋቋመው የሱፐርቪዥን ቡድን በግጭት ሲናጡ የከረሙትን የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎችን ሁኔታ በአካል ተመልክቶ ታህሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም ሪፖርቱን ለምክርቤቱ አቅርቧል። “የሕዝቤ ጥቅም ተነክቷል” በሚል ኢህአዴግን ተቀይመው መልቀቂያ አስገብተው የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ውሳኔ ወደቀድሞ ሥራቸው ከተመለሱ በኋላ ይህንኑ መድረክ መርተዋል። የሱፐርቪዥኑ ቡድኑ ተልዕኮ ያተኮረው በኦሮሚያ እና በሶማሌ አጎራባች አካባቢዎች ባለፉት ጊዜያት በተፈጠሩት ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን በመስክ ሄዶ በመመልከት በተለይ ከሰብዓዊ ቀውስ አኳያ የደረሰውን ችግር ለምክርቤቱ ሪፖርት ለማድረግ ነው። ቡድኑ ይህን ትልቅ ተልዕኮ ይዞ 13 አባላትን በማቀፍ በ3 አቅጣጫ ወደሁለቱም ክልሎች ከጥቅምት 25 እስከ ህዳር 2 ቀን 2010 መንቀሳቀሱን ገልጿል።

 

የሪፖርቱ አንኳር ነጥቦች


ግጭቱ ከታህሳስ 2009 ዓ.ም ጀምሮ መከሰቱን፤ ነገር ግን ይህ ቡድኑ የመስክ ምልከታ ባደረገባቸው ግዜያት በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ተፈናቃዮች በቂ ዕርዳታና ድጋፍ ሳያገኙ በከባድ ቀውስ ሆነው መመልከቱን፣ በዚህም ምክንያት ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት መሸርሸሩን ታዝቧል፡፡ በተጨማሪም ከሁለቱም ወገኖች በኩል ሞት፣ ከቤት ንብረት መፈናቀል፣ የአካል መጉደል፣ ጾታዊ ጥቃት... መድረሱን አመልክቷል።


ተፈናቃዮች ለዓመታት ለፍተው ያፈሩትን ሐብት፣ ንብረት፣ ገንዘባቸውን ጥለው ከመሰደዳቸውም በላይ የአንድ ቤተሰብ አባላት የተጠፋፉበት ሁኔታ ተከስቷል። ከእነዚህ ተፈናቃዮች መካከል የመንግሥት ሠራተኞች የነበሩ ግለሰቦች ያለደመወዝ ከእነቤተሰባቸው እየማቀቁ የሚገኙበት መሆኑን አጥኚው ቡድን አረጋግጧል።


የቡድኑ አባላት በስራ ላይ በነበረበት ወቅትም በግጭቱ የሰዎች ሞት፣ የእንስሳት መዘራረፍ፣ መፈናቀል ቀጥሎ ነበር። በዚህም ምክንያት ወገኖች በተፈናቀሉበትም ቦታ አለመረጋጋት መኖሩን፣ እናቶች በጫካ ውስጥ ጭምር ለመውለድ መገደዳቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል።


በተጨማሪም የምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕርዳታዎች በበቂ ሁኔታ አለመቅረብ፣ ለተፈናቃይ ወገኖች መቅረብ የነበረባቸው የትምህርት የጤና አግልግሎቶች በበቂ ሁኔታ እየቀረቡ አይደሉም ብሏል።


በአጠቃላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በከፍተኛ ደረጃ መታየቱን በመጠቆም የሰብዓዊ መብት ኮምሽን ጉዳዩን አጣርቶ እንዲያቀርብ ቡድኑ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ አስፍሯል።


የቡድኑ ሪፖርት ህዳር 2 ቀን በየደረጃው ለሚመለከታቸው አካላት በቃልና በጹሁፍ መቅረቡን፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች ለምክርቤቱ ለማቅረብ አለመቻሉን ተጠቅሷል። ይህም ሆኖ የምክርቤቱ አባላት በሪፖርቱ ሳይቀርብ መዘግየት ደስተኛ አለመሆናቸውን ደጋግመው በሰጡት ሀሳብ አንጸባርቀዋል። አንዳንዶችም' ሪፖርቱ ግዜውን የጠበቀ አይደለም። ከዚህ የበለጠ ምን አጀንዳ ሊኖር ይችላል?' ሲሉ መረር ባለ ቃል ጠይቀዋል።


የቅኝት ቡድኑ ግጭቱ የሕዝብ ለሕዝብ አለመሆኑን አረጋግጫለሁ ማለቱን ተከትሎ የምክርቤቱ አብዛኛው አባላት እነዚህ ወንጀለኞች እነማንናቸው፣ ለምንድነው ለፍርድ የማይቀርቡት? የፌደራል መንግሥትስ ለምን ዝምታን መረጠ? በማለት አጥብቀው ጠይቀዋል። ‘መሸፋፈን ይቅር' ያሉ አባላት በወንጀሉ እጃቸው ያለበት ከፍተኛ አመራሮች ጭምር ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ሲሉ ጠንካራ አቋማቸውን ገልጸዋል።


በመድረኩ ላይ በግጭቱ ጉዳይ የተቋቋመው ብሄራዊ ኮምቴ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ የፌደራል አርብቶ አደር ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ፣ የመከላለያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ የፌደራል ፓሊስ ኮምሽነር አቶ አሰፋ አብዩ፣ የብሄራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮምሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በትላንቱ የፓርላማ መድረክ በአስረጅነት ተገኝተዋል።


የፌዴራል አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ ግጭቱ መከሰቱ ከተሰማ በኋላ በፌዴራል መንግሥት በኩል ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸውን ያስታውሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ጳጉሜ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የሁለቱ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በተገኙበት በተደረገ ውይይት ክልሎቹ ግጭቱን እንዲያረጋጉ፣ የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ሆኖም ግጭቱ ሊበርድ አልቻለም ብለዋል፡፡ አያይዘውም መስከረም 6 ቀን 2010 ዓ.ም የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎሣ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ምክክር ተደረገ፡፡ የታሰበውን ያህል ግን ለውጥ አልመጣም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ከመስከረም 8 ቀን ጀምሮ የዕለት እርዳታ ሥራዎች መጀመራቸውን፣ ነገር ግን በየዕለቱ የተፈናቃዩ ቁጥር ይጨምር ስለነበር አቅርቦቱ በቂ አልነበረም፡፡ በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተም ሲያብራሩ እጅግ ከባድ፣ ዘግናኝ እና መቼም መደገም የሌለበት ነው ሲሉ ገልፀውታል፡፡


ዕርዳታ በወቅቱ ለምን ማድረስ እንዳልተቻለ አቶ ምትኩ ካሣ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮምሽነር በሰጡት ማብራሪያ መጀመሪያ ላይ የመረጃ ችግር ነበር። ምን ያህል ሰው ተፈናቀለ፣ የት ነው ያለውና የመሳሰሉ መረጃዎች ሳይሟሉ ዕርዳታ ማቅረብ አስቸጋሪ ነበር ብለዋል። ስራው በጸጥታ ችግርና በመንገዶች መዘጋት ምክንያት ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከአንድ ሳምንት በላይ ጭምር አንድ ቦታ ለመቆም የሚገደዱበት ሁኔታ አጋጥሟል። በተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃቶች መድረሳቸው የተሽከርካሪ ባለቤቶች አንሄድም እስከማለት አድርሷቸዋል፡፡


መልሶ ለማስፈር የሠላም ኮንፈረንስ መካሄድ ነበረበት፣ ይህን ማካሄድ ባለመቻሉ አልተሳካም ብለዋል።


የፌደራል ፓሊስ ኮምሽነሩ አቶ አሰፋ አብዩ የተጠያቂነት ጉዳይ ከሰብዓዊ መብት እና ከወንጀል አንጻር በሁለት መንገድ እየተሰራበት መሆኑን ጠቅሰዋል። ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ግብረ ሀይል አቋቁሞ ወንጀለኞችን ማደን ጀምሯል። በእስካሁኑ ሥራ ከወንጀሉ ጀርባ እንዳሉ የተጠረጠሩ የፖሊስ፣ የልዩ ሀይል፣ የሚሊሽያ፣ የወረዳ አስተዳደር አካላት መኖራቸውን ፍንጭ ሰጥተዋል። እስካሁን በኦሮሚያ በኩል 98 ተጠርጣሪዎች የተያዙ ሲሆን በሶማሌ ክልል በኩል የተያዙት 9 ብቻ መሆናቸውን ኮምሽነሩ ሲናገሩ የፓርላማ አባላት በስላቅ ሳቅ አጅበዋቸዋል። በአጠቃላይ ከሁለቱም ክልሎች ሌሎች 98 ያህል ተጠርጣሪዎች እንደሚፈለጉና የወንጀል ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ በመስጠት ረገድ ከባድ ችግር ማጋጠሙን ይፋ አድርገዋል።


ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር ወደ 126 ከፍ አድርገው ተናግረዋል። ክልሎቹ ተፈላጊ ወንጀለኞች ለፌደራል መርማሪ አካላት አሳልፎ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግር አሰምተዋል። መንግሥት ኃላፊነቱን አልተወጣም ለሚለው ትችት በችግሩ ስፋት የሚመጥን እርምጃ አለመወሰዱን አቶ ደመቀም አምነዋል። ሆኖም ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ያሉበት ኮምቴ በማቋቋም ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል። ተሰርቷል ካሉት መካከል በግጭት አካባቢዎች ከማንኛውም የክልል ታጣቂ ሀይል ነጻ ማድረግ ተችሏል፣ በዚህም እርምጃ አንጻራዊ ሠላም እየመጣ ነው ብለዋል። የሠላም ኮንፈረንሱ ባለመሳካቱ ክልሎች በተመረጡ አካባቢዎች በግዜያዊነት ተፈናቃዮችን እንዲያሰፍሩ ወስነው እየተሰራበት ነው ብለዋል።


ፓርላማው የሱፐርቭዥን ቡድኑን ሪፖርት ጥቂት ማሻሻያዎች አክሎበት በ3 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ተቀብሎታል። 

Page 8 of 200

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us