You are here:መነሻ ገፅ»arts»news admin - Sendek NewsPaper
news admin

news admin

በይርጋ አበበ

ለ26 ዓመታት በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የመንግስት ስልጣን የዞ የቆየው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በወቅታዊ የአገሪቱ ችግር ዙሪያ ከተቃዋሚ (ተቀናቃኝ ወይም ተፎካካሪ በሉን ይላሉ) ፓርቲዎች ለመወያየት ግብዣ አቅርቦላቸው ወደ ውይይት ለመግባት ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ። ኢህአዴግን ጨምሮ ሰማያዊ፣ መኢአድ፣ መድረክ፣ ኢራፓ፣ ኢዴፓና ሌሎች 22 ፓርቲዎች የሚያደርጉት ውይይት ዓላማው ከ2008 ዓም ኅዳር ወር ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አማራ ክልል በተዛመተው ህዝባዊ ተቃውሞ (አንዳንዶች ቁጣ ይሉታል ኢህአዴግ ደግሞ ልማቱ ያመጣው ተቃውሞ ሲል ይጠራዋል) በመንግስትና በአገር ላይ ስጋት በማሳረፉ መፍትሔ ለመፈለግ ነው። ከፓርቲዎቹ ውይይት (ተቃዋሚዎች ድርድር እንጂ ውይይት አና ክርክር ብሎ ነገረ የለም። ኢህአዴገ የጠራን እንድንደራደር ካልሆነ ጥሪውን መቀበል አንፈልግም ሲሉ ይገልጻሉ) ቀደም ብሎ ደግሞ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአገሪቱ ላይ መታወጁ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ላለፉት 26 ዓመታት በአንድ ፓርቲ አመራርነትና አስተሳሰብ ብቻ እየተመራች መቆየቷ ይታወቃል። በ2002 ዓም በተካሄደው አራተኛው ዙር ምርጫ በኋላ ራሱን አውራ ፓርቲ (dominant party) ብሎ መጥራት የጀመረው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በ2007 ዓም የተካሄደውን ምርጫም ሙሉ በሙሉ የፌዴራልና የክልል ፓርላማ መቀመጫ ወንበሮችነ ጠቅልሎ ያሸነፈ መሆኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወቃል። ሆኖም ከአምስተኛው ዙር ምርጫ ማግስት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞዎቸ መነሳታቸውን ተከተሎ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ የአገሪቱ የምርጫ ህግ እንደሚሻሻል የፌዴሬሽን እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶችን የስራ ዘመን መክፈቻ ሲያበስሩ አስታወቀው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትረ ኃይለማሪያም ደሳለኝም ቢሆኑ የምርጫ ህጉ መስተካከል እንዳለበት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገለጹ ሲሆን ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ሲባልም ህገ መንግስቱ ሳይቀር መሻሻል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተው ነበር።

 ከኦሮሚያና አማራ ክልሎች ግጭት ማግስት ጀምሮ አገራቀፍ የውይይትና የምክክር ጉባኤ እንዲካሄድ አገር ወዳድ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲያስታውቁ ቆየተው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ለሁሉም አገረ አቀፍ መዋቅር ላላቸው ፓርቲዎች የድርድር የምክክር ወይም የውይይት ጥሪ አቅርቦ በጥር 10 ቀን 2009 ዓም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አዳራሽ መገናኛ ብዙሃን ባልታደሙበት (ኢቢሲ እና ሌሎች መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ብቻ ታድመዋል) መልኩ የድርድሩ፣ የክርክሩ ወይም የውይይቱ ቅድመ ሁኔታ ላይ ምክክር ሲያደርጉ ውለው ለጥር 25 ቀን 2009 ዓም ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ተለያዩ። ፓርቲዎቹ ለድርድሩ ለውይይቱ ወይም ለክርክሩ አስፈላጊ ነው የሚሏቸውን ነጥቦች ዘርዝረው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ለሆኑት አስመላሽ ገብረስላሴ እንዲሰጡ በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት ሃሳቦቻቸውን ገልጸው አስታወቁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየሳምንቱና በየ15 ቀኑ ፓርቲዎቹ እየተገናኙ ወይይት ድርድር ወይም ክርክር እያካሄዱ ይገኛሉ።

መጋቢት 24 ቀን 2009 ዓም የተካሄደውን ውይይት አስመልክቶ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮችና የኢህአዴግ ተወካዮች ጋር የሰጡንን አስተያየት ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

 

የድርድሩ ጊዜ መራዘም

ኢህአዴግና የተወሰኑ ፓርቲዎች ድርድር ውይይትና ክርክር በሚል ርዕስ እንዲወያዩ ሀሳብ ሲያቀርቡ መድረክ ሰማያዊ ኢዴፓ መኢአድና ኢራፓን ጨምሮ ሰባት ፓርቲዎች በአንድ ሰነድ ሶስት አይነት የመወያያ ርዕስ አያስፈልግም የተጠራነው ለድርድር እስከሆነ ድረስ ከድርድር ውጭ በሌላ ርዕስ ዙሪያ አንሰበሰብም ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። በርዕስ አለመግባባት ምክንያት የአንድ ቀን ጉባኤው የተቋረጠው የፓርቲዎቹ ውይይት ወደ ድርድር በቀጥታ ለመግባት የመጓተት ነገር ይታይበታል ሲሉ የቅድመ ድርድር ሂደቱን የሚገልጹ ሰዎች አሉ። ይህን በተመለከተ ለሰንደቅ ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ “እኛ ወደ ድርድሩ የገባነው ከድርድሩ አንዳች ረብ ያለው ውጤት አናገኛለን ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ነገር ግን ቃላትን እየሰነጠቁ ሂደቱን ማራዘም የምንጠብቀውን ተስፋ እንዲመነምን እያደረገው ሲሆን በፓርቲያችን ላይም ችግር እየፈጠረብን ይገኛል። ለድርድር ከተጠራንበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ወራት ብቻ 12 የፓርቲያችን አባላት ታስረው የት እንዳሉ አናውቅም” ሲሉ የድርድሩ ሂደት መራዘሙን በቅሬታ ገለጸዋል።

የኢዴፓው ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው ቅድመ ድርድር ሂደቱ መራዘሙ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸው ምክንያቱን ሲያስቀምጡም “22 ፓርቲዎች የሚሳተፉ በመሆኑ እና ሁሉም ሀሳቡን የሚያቀርብ በመሆኑ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከምንም በላይ አስፈላጊ የሆነውና ሁላችንንም ሊገዛን የሚችለው የስነ ስርዓት ደንቡ ስለሆነ በዚያ ላይ ሰፊ ውይይት አድርገን መቅረጽ ይኖርብናል” ሲሉ ተናግረዋል። ዶክተር ጫኔ አክለውም “በድርድር መልኩ እስከተሰበሰብን ድረስ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም” ሲሉ የድርድሩ ስነ ስርዓት ደንብ ዝግጅት ጊዜ ወሰደ የሚባለው ለተሻለ ውጤት መሆኑን ገለጸዋል።

የመኢአዱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ ደግሞ የድርድሩ ቅድመ ዝግጅት ሂደት ዘግይቷል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። አቶ ሙሉጌታ “ዋናው ነገር መፍጠኑ ሳይሆን መግባባቱ ስለሆነ ለዚህ ደግሞ ሰፊ ውይይት እያደረግንበት እንገኛለን። ስለዚህ ዘግይቷል ብሎ ለመናገር ጊዜው ገና ነው” ብለዋል።   

ርዕሱ ያላግባባቸው ተደራዳሪዎች

 “ኢህአዴግ እንደራደር ብሎ ጠርቶ ውይይትና ክርክርም በሰነዱ ላይ ይካተት ብሎ መቅረቡ ለማደናበር ነው” ሲሉ የሚገልጹት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመነበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ሀሳባቸውነ ሲያጠናክሩ “በመሰረቱ አሁን የመጣውን የውይይት ክርክርና ድርድር የሚል ርዕስ ኢህአዴግ ለማደናገር ያመጣው እንጂ አነሳሱ ለድርድር ነበር። እንደሚታወቀው ድርድርም ሆነ ክርክር ወይም ውይይት የየራሳቸው የሆነ ስርዓት አላቸው። ሶስቱም በአንድ ሰነድ ሊሆኑ አይችሉም። ኢህአዴግ በመጀመሪ ሲጠራን ለድርድር ብሎ ቢሆንም አሁን የሚታየው አዝማሚያ ግን ወደኋላ የማፈግፈግ ሰሜት ነው” ብለዋል።

የአቶ የሽዋስን ሀሳብ የሚያጠናክሩት የኢዴፓው ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው “አርብ ባደረግነው ውይይት ሰፋ ያለጊዜ ወስደን የተነጋገርነው በርዕሱ ላይ ነበር። እኛን ጨምሮ የተወሰኑ ፓርቲዎች ድርድር እንጂ ክርክርም ሆነ ውይይት የማንቀበል መሆናችንን ገልጸናል። ኢህአዴግና ሌሎች ደግሞ ሶስቱም ሀሳቦች እንዲካተቱ ጠይቀዋል። ሌሎቹ ደግሞ ድርድርና ክርክር የሚሉትን ነጥቦች ይዘው መሄድ ይፈልጋሉ። በዚህም ምክንያት መግባባት ባለመቻላችን በሰነዱ ይዘት ላይ እንድንወያይ ተደርጎ ከዚያ በኋላ ርዕሱ እንዲወሰን ነው ተነጋግረን የተለያየነው” ሲሉ ሶስት ጉዳዮችን የያዘውን ሰነድ ፓርቲያቸው እንደማይቀበለው ገልጸዋል። 

ዶክተር ጫኔ ከመወያያ ሰነዱ ርዕስ በተጨማሪም በዓላማውና ዓላማውን ለመቅረጽ በወጡ ሀሳቦች ላይ አንዳንድ ቃላትና ሀረጎች ትርጉማቸው አሻሚ በመሆናቸው እንዲሻሻሉ ለማድረግ ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል። የኢዴፓው ሊቀመንበር “አሻሚ ትርጉም ያላቸው ቃላት” ያሏቸውን ሲገልጹም “ለምሳሌ በኢህአዴግ ከቀረበው ሀሳበ ላይ የሚሻሻሉ ህጎች ካሉ ማሻሻል የሚል ይገኝበታል። እኛም ይህን ሀሳብ ስንመለከተው መሻሻል ያለባቸው ህጎች እንዲሻሻሉ ተብሎ ይስተካከል እንጂ “ካሉ” የሚለው ቃል የገባው ለማደናገር ካለሆነ በስተቀር ህጎች እንዲሻሻሉ እኮ ነው የተሰበሰብነው ብለን አቋማችንን ገልጸናል። በእኛ በኩል የቀረበውንና ኢህአዴግ ሃሳብ የሰጠበት ደግሞ አሳሪ የሆኑ ህጎቸ ሁሉ ይሻሻሉ የሚለውን ሲሆን አሳሪ የሚለውን ገላጭ ቃል መጠቀማችን ገና ወደ ድርድር ከመግባታቸሁ በፊት አቋመ እየወሰዳችሁ ይመስላል ሲል ተከራክሯል። በሌላ በኩል ደግሞ የብሔራዊ መግባባት እውን እንዲሆን የሚለው ሀረግ ላይ “እውን መሆን” በሚለው ሀሳብ ዙሪያ ሰፊ ውይይትና ንግግር አካሂደንበታል” ሲሉ የካቲት 24 ቀን 2009 ዓም ፓርቲዎቹ ያካሄዱትን ውይይት ውሎ ገልጸዋል።

መኢአድም በድርድር እንጂ በውይይትና ክርክር በሚሉ ርዕሶች ላይ መወያየት እንደማይፈልግ አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

በመርፌ ቀደዳ እንደመሹለክ

“ኢህአዴግ ለይስሙላ ካልሆነ በቀር በሰጥቶ መቀበል የማያምን ፓርቲ ስለሆነ አሁን የተጠራው የድርድር ሂደትም ውጤት ሊያመጣ አይችልም” ሲሉ ስጋታቸውን የሚገልጹ ወገኖች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ “በጥልቅ ተሃድሶ” ውስጥ የሰነበተው ኢህአዴግ “ለአገር ሰላምና ለህዝብ ደህንነት አልፎ ተርፎም ለራሱ ህልውናም ሲል ድርድሩን ከልቡ ያደርገዋል” ሲሉ ሀሳባቸውን የሚሰነዝሩ ወገኖች አሉ። የመጀመሪያውን ሀሳብ የሚያራምዱት ወገኖች ሀሳባቸውን ሲያጠናክሩም “ኢህአዴግ ሰጥቶ በመቀበል አምኖ ለተቀናቃኞቹ ስልጣንን እስከማጋራት የሚያደርስ ድርድር ያደርጋል ማለት ዘበት ነው። ለተቀናቃኞቹ ጥረታቸው ግመልን በመርፌ ቀዳዳ እንደማሾለክ ነው” ይላሉ።

በዚህ ዙሪያ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የመኢአድ፣ የሰማያዊና የኢዴፓ አመራሮች “ሂደቱ የቱንም ያህል የተጓተተ ቢሆን እና ኢህአዴግ የቱንም ያህል የራሱን ጥቅም ብቻ የሚያሳድድ ፓርቲ ቢሆንም ዳር ላይ ቆሞ ከመመልከት ተሳትፎ አድረጎ ማየት የተሻለ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ “ከአስር ዓመት በኋላ ከጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ስብስብ ውጭ የሆኑ ፓርቲዎችንም ለድርድር መጋበዙ ይሁንታ የምንሰጠው ጅምር ነው” ያሉ ሲሆን የድርድርን አስገዳጅነት ሲገልጹም “ይህ በፍላጎት (በኢህአዴገ ፍላጎት ላይ ለማለት ነው) ላይ ብቻ የተመሰረተ ሳይሆን አገርን ህዝብንና ራስነ (ኢህአዴገን) ለማዳን የመጨረሻው አማራጭ ነው። ምንም እንኳ እስካሁን ያሉት ሂደቶች መልካም የሚባሉ ባይሆንም ኢህአዴግ ለራሱ ህልውና ሲል ከልቡ ሊያካሂደው ይችላል ብለን እናስባለን” በማለት የፓርቲያቸውን እምነት ገልጸዋል።

የመኢአዱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ በበኩላቸው “ከድርድሩ ቅድመ ዝግጅት የታዘብነው ተስፋ አስቆራጭነት ሳይሆን ተስፋ ሰጭ መሆኑን ነው። ለ11 ዓመታት የተዘጋውን በር ከፍቶ ከተፈካካሪ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ለማድረግ መጀመሩ በራሱ ተስፋ ሰጭ ሂደት ነው።” ያሉ ሲሆን አያይዘውም “የታሰበውን ያህል ውጤት ሊመጣ ይችላል ወይ? ለሚለው እሱን ወደፊት የምናየው ነው። የታሰበውን ያህል ውጤት ባይመጣ እንኳ ፈፅሞ ውጤት አይመጣም (አታመጡም) ማለት ስህተት ነው” ሲሉ ከድርድሩ ተስፋ የሚያደርጉትን ተናግረዋል።  

የመድረኩ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ደግሞ እስካሁን የተካሄደው ስብሰባ ብዙም ተስፋ ሰጪ አለመሆኑን ተናግረዋል። ሆኖም ከነገው ስብሰባ በኋላ ነገሮች ሊለወጡ እንደሚችሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል። የኢዴፓው ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ በበኩላቸው የድርድሩን አስፈላጊነት ገልጸው ሆኖም በተለይ እንደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያሉ ጉዳዮች በፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ እና በፖለቲካ ምህዳሩ ላይ የሚያሳርፈው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ ስለሆነ ሊታሰብበት እንደሚገባ ተናግረዋል።¾

 

አንዳንድ ሰዎች በተሳሳተ አነጋገር ላይ እርማት ሲደረግ “ቋንቋ መግባቢያ ስለሆነ ሰው እንደ ፈለገ ቢናገረው ምናለበት” ሲሉ ይሰማሉ። አዎ ቋንቋ መግባቢያ ነው። ነገር ግን መግባቢያነቱ የሚሰምረው በትክክል ሲነገር ወይም ሲጻፍ ብቻ ነው። ስህተት ሆኖ ሲነገር ግን ሌላ ቢቀር ማደናገሩ አይቀርም። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ ወሎ ውስጥ በገጠር አካባቢዎች በሁለተኛና በሦስተኛ ሰው (በርስዎና በሳቸው) መካከል የተሳሳተ አነጋገር ይሰማል። እሳቸው መጥተው ነበር ለማለት እሰዎ (እርስዎ) መጥተው ነበር እያሉ ሲያወሩ ይሰማል። ልክ በጎጃም አባባል አልበላሁም ለማለት “አልበልቸም” እንደሚለው አነጋገር መሆኑ ነው። ጎጃምኛው አለመለመዱ ነው እንጅ ስህተት አይመስለኝም። ታዲያ አንድ መንደርኛውን አነጋገር የረሳ ወሎየ ዘመዶቹ ዘንድ (ጋ) ሄዶ ሲጫወት የገጠሬው ዘመዱ “ያንዬ እስዎ ሞተው ሃዘን ላይ ሆነን” ሲለው “እረ ተው ምቸ ሞትኩ እኔ” ሲል ደነገጠ ይባላል። ያ ገጠሬው ሰው ሊል የፈለገው “ያንየ እሳቸው ሞተው ሀዘን ላይ ሆነን” ለማለት ነው። ስለዚህ ቋንቋ በትክክል ካልተነገረ ወይም ካልተጻፈ መግባባት ሳይሆን ማደናገርን ነው የሚፈጥረው-ከላይኛው ምሳሌ እንዳየነው።

ዛሬ የቋንቋ ብልሽት በብዙ መልክ ይታያል። የፈረንጅኛ ቃላት፣ ያውም የተሳሳቱ አባባሎችን ካልጨመሩ ሃሣባቸውን መግለጽ የማይችሉ የሚመስላቸው ሰዎች ብዙ ናቸው። ፋዘር፣ ማዘር፣ ፍሬንድ የሚሉት ቃላት በሰፊው ሲነገሩ ይሰማል። ሽማግሌዎችና አሮጊቶችም ፋዘር፣ ማዘር ሲሉ መሰማት ጀምሯል። ለምን ቢባል “ዘመናዊ” ለመሆን ነዋ! “አባት፣ እናት፣ ጓደኛ ካለ አንድ ሰው ስልጡን እንዳልሆነ ነው የሚታሰበው” አለኝ አንድ ወያላ ሲያብራራልኝ። ለመሆኑ ፋዘር፣ ማዘር የሚባሉት የሰንት ዓመት ሰዎች ናቸው ብዬ ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ የሚገርም ነው። “ወንዱን ፋዘር የምንለው ትንሽ ሽበት ካወጣ ወይም ጸጉሩ ከተመለጠ ነው። ሴትዋም ሻሽ ካሠረች ያው ማዘር ነች” አለ እየሳቀ። ወያላዎች ግራንድ ፋዘር (ግራንድፓ) ወይም ግራንድ ማዘር (ግራንድማ) የሚሉትን የእንግሊዝኛ ቃላት ስለማያውቋቸው ያርባ አመትም ሆነ የሰማንያ ዓመት ሰው ያው ፋዘር ነው የሚባለው። ሴትዋም ያው ማዘር ነች። እነኝህ ፋዘር፣ ማዘር፣ ፍሬንድ የሚሉት ቃላት ትርጉሞች በሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እንደሚገኙ የሚታወቅ ነው። ቁልምጫዊ ዘይቢያቸው ሳይቀር አለ። ለምሳሌ በአማርኛ አባቴ፣ አባብዬ፣ እማማ፣ እማምዬ፣ ጓደኛዬ፣ ጓዴ ወዘተ የሚሉ ቃላት አሉ። የቅርብ ዘመድንና የቤተሰብ አባላትን በቁልምጫ ለመጥራትም ብዙ ቃላት አሉ። ታላቅ ወንድምን፣ ወይንም አጐትንም ሆነ የቅርብ ወንድ ዘመድን፣ ጋሽየ፣ ወንድምዓለም፣ ወንድምጋሼ፣ ጥላዬ ማለት እንደሚቻለው ሁሉ፣ ለሴት እህትም ወይም አክስት፣ እታለም፣ እትአበባ፣ አክስቴ ማለት ይቻላል።

ሌላው በብዛት ስህተት ሲስተናገድበት የሚታየው/የሚሰማው በግዕዝና በአማርኛ እርባታ ላይ ነው። ብዙ ሰዎች በግዕዝ በተረባው ቃል ላይ ቶች፣ ዎች ወይም ኖች በመጨመር የብዙ ብዙ አነጋገር ስህተቶችን ሲፈጽሙ ይሰማሉ። የሚከተሉትን እንመልከት!

የአማርኛ ዕርባታ (ነጠላ-ብዙ)

ሊቅ         ሊቆች

አስተማሪ    አስተማሪዎች

ሕፃን        ሕፃኖች

ቄስ          ቄሶች

መነኩሴ      መነኩሴዎች

ካህን         ካህኖች

ዲያቆን       ዲያቆኖች

ንጉሥ        ንጉሦች

እንስሳ        እንስሶች

ገዳም         ገዳሞች

ጳጳስ          ጳጳሶች

ባህታዊ        ባህታዊዎች

 የግዕዝ ዕርባታ (ብዙ)

ሊቃውንት

መምሕራን

ሕፃናት

ቀሳውስት

መነኮሳት

ካህናት

ዲያቆናት

ነገሥታት

እንስሳት

ገዳማት

ጳጳሳት

ባህታውያን

ጸያፍ ዕርባታ (የብዙ ብዙ)

ሊቃውንቶች

መምሕራኖች

ሕፃናቶች

ቀሳውስቶች

መነኮሳቶች

ካህናቶች

ዲያቆናቶች

ነገሥታቶች

እንስሳቶች

ገዳማቶች

ጳጳሳቶች

ባህታውያኖች

ባሁኑ ጊዜ በጣም ገንኖ የሚታየው ሌላው ስህተት በ ጋ እና ጋር መካከል ያለው ያጠቃቀም ውዥንብር ነው። በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው “አማርኛ መዝገበ ቃላት” እንደሚገልጸው ጋ የሚለው ፊደል “አንድ ነገር የት እንደሚገኝ የሚያመለክት ቃል” ነው። መጽሐፉ ጠረጴዛው፣ እዚያ ነው። ጋር የሚለው ቃል ደግሞ “አብሮ” የሚለውን ሃሣብ የሚገልፅ ነው። ስለዚህ ጋ ዘንድ ሲሆን ጋር ደግሞ አብሮ ማለት ነው። ምሳሌ፣ እኔ ዛሬ ወንድሜ ጋ እሄድና ከሱ ጋር ሄደን ምሳ እንበላለን። ስለዚህ ጋ የሚለው ዘንድ ማለት ሲሆን ጋር የሚለው ቃል ግን አብሮ ማለት ነው። ለምሳሌ ስልክ ተደውሎ የት ነው ያለኸው ሲባል ወንድሜ ጋ ነኝ (ወንድሜ ዘንድ ነኝ) መሆን ነው ያለበት መልሱ። ዛሬ ግን ጋ ለማለት ጋር በማለት ውዥንብር እየተፈጠረ ነው። መጽሐፉ የት ነው ያለው? ብለህ ስትጠይቅ ከበደ ዘንድ ነው ለማለት ከበደ ጋር ነው ይልሃል። ትክክል ያልሆነ አነጋገር ነው። የቃና ቴሌቪዥን ተዋንያን ሳይቀሩ የተሳሳተውን የቋንቋ አገባብ ይዘው ጋ የሚለውን ጋር እያሉ ነው የሚያወሩት። ከአንድ ሰዓት በኋላ ወንድሜ ጋ (ቤት) እሄዳለሁ ለማለት፣ ከአንድ ሰዓት በኋላ ወንድሜ ጋር እሄዳለሁ እየተባለ ነው። ስህተት ነው።

ሌሎች በባዕድ ቋንቋዎች የምንሠራቸው አስቂኝ ስህተቶች አሉ። አንድ ልጅ አባቱ ያልሆነውን ሰው ፋዘር ወይም ዳዲ ብሎ ሊጠራው አይችልም። አንድ ጊዜ አራት ኪሎ አንድ ፈረንጅ ታክሲ ውስጥ ሆኖ ወጣቶች ከበው ገንዘብ ስጠን ለማለት ፋዘር፣ ዳዲ እያሉ ሲያስቸግሩት ደርሼ ገላግየዋለሁ። “ፋዘር ዳዲ ሞኒ ሞኒ” እያሉ በግራና በቀኝ ሲጮሁበት ፈረንጁ ተናዶ I swear I did not father any of these kids (ከነኝህ ልጆች አንዱንም እንዳላስወለድኩ እምላለሁ ነበር ያለው።) ሌላው አስቂኝ ቃል ክላስ የሚለው ነው። ሆቴል ስትገቡ እንግዳ ተቀባዩ ክፍል ይፈልጋሉ ለማለት ድፍረት በተሞላ አነጋገር ክላስ ነው የሚፈልጉት ነው የሚላችሁ። ክላስ ወይም ክላስሩም የመማሪያ ክፍል ነው እንጅ የመኝታ ክፍል አይደለም። የኛም የውጭውም ቋንቋ እንደዚህ ተዘበራርቋል።

በየቀኑ በስህተት የሚነገሩ የውጭ አገር ቋንቋዎችና ቃላት ብዙ ናቸው። አመሰግናለሁ ለማለት ቴንክዩ ወይም ታንክዩ የሚሉ ብዙ አሉ። የቋንቋው ባለቤቶች እንግሊዞች ግን ትክክለኛውን ቃል ለማውጣት ምላስን በላይኛውና በታችኛው ጥርሶቻችን መካከል ብቅ አድርጎ መልሶ ወደ ውስጥ በመሰብሰብ የሚፈጠር ድምፅ ነው ይላሉ። ያን ድምፅ በአማርኛ መጻፍ ባይቻልም ሳንክዩ ለሚለው ቃል ነው የሚቀርበው።

ባሁኑ ጊዜ ቋንቋን ከሚያበላሹ ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የመገናኛ ብዙሐን ሰራተኞች በተለይ የቴሌቪዥንና የሬድዮ ጋዜጠኞች ናቸው። እጅግ በጣም ጥሩ፣ በጣም ቆንጆ የሚሉትን የአማርኛ ገላጭ ቃላት አሪፍ በሚል የአረብኛ ቃል ለውጠዋቸዋል። አገሩ ሁሉ አሪፍ፣ አሪፍ እያለ ነው። “አሁን ደግሞ “አሪፍ” ሙዚቃ እንጋብዛችኋለን” ማለት የተለመደ የሬድዮ ጣቢያ አነጋገር እየሆነ መጥቷል። ከፈረንጅ ጥገኝነት ወደ አረብ ጥገኝነት በቀላሉ እየተሽጋገርን ይመስላል። ምንም እንኳን ቋንቋ ይወራረሳል፣ ያድጋል ቢባልም የሚወራረሰውም የሚያድገውም የራስ ቋንቋ የማይገልጸውን የሚገልጹ የባዕድ ቃላት ሲገኙና በግልጽ በሥራ ላይ መዋል ሲያስፈልጋቸው ነው። ዛሬ ቀኑ፣ ዓየሩ፣ ጥሩ ነው፣ ቆንጆ ነው፣ ተወዳጅ ነው ወዘተ ለማለት ሁሉም የሚሸፈነው “አሪፍ” በሚለው ቃል ሆኗል። ቃሉ በጣም ከመወደዱ የተነሳ በረጅም ቅላጼ ነው የሚነገረው። ይህ ደግሞ የራሳችንን ቋንቋ ማሳደግ ሳይሆን ለባዕድ ቋንቋ ጥገኛ መሆንና የራስን ቋንቋ ማዳከም ነው። እንድንግባባ እኔም ቃሉን ልዋሰውና አሪፍ የጥገኝነት ባህሪ ነው ልበላችኋ!

ሰርተፊኬት የሚለው ቃል በሰፊው ተለምዶ በሬድዮና በቴሌቪዥን ሲነገር በጽሁፍም ሲቀርብ ይታያል። የቋንቋው ባለቤቶች ሰርቲፊኬት ነው የሚሉት። ስለዚህ እኛ ቃሉን በትክክል ለመጠቀም ወይ ባለቤቶቹ እንደሚሉት ሰርቴፊኬት ማለት አለብን አለዚያም በራሳችን ትርጉም የምስክር ወረቀት ማለቱ ይመረጣል። ሌላው ተመሣሣይ ችግር ያለው ፕረስ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ነው። ቃሉ ከሕትመት ሥራ ጋር ማለት ከመጫን፣ ከማተም ጋር የተያያዘ ስለሆነ በእንግሊዝኛ ፕረስ የሚለው አነባበብ ይስማማዋል። እኛ ግን ለራሳችን የሚስማማን ፕሬስ ነው በማለት ቃሉን ከትክክለኛው አነጋገር ከፕረስ ወደ ፕሬስ ወስደነዋል። ይህ ድርጊት ምንም ምክንያታዊ አይደለም። አሁንም ሌላው ከትክክለኛ አነጋገር ወደ ተሳሳተ አባባል በልማድ የተወሰደና በስህተት እየተነገረ የምሰማው ኦሎምፒክ የሚለው ቃል ነው። ቃሉ በእንግሊዝኛ OLYMPIC (ኦሊይምፒክ) ነው። የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለማለት OLYMPIC GAMES ነው የሚባለው። ባንድ ወቅት አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ኦሊይምፒክ የሚለውን ቃል ኦሎምፒክ ብሎ በስህተት አነበበው። ከዚያ ወዲህ እኛ አገር ትክክለኛው አነባበብ ተሽሮ ኦሎምፒክ ሆኖ ቀረ።

ወደ ጣልያንኛ ቋንቋ ደግሞ እንሂድ። በመኪና ላይ ከሁዋላ የሚመጡትን ተሽከርካሪዎች ለመቆጣጠር በግራና ቀኝ ያሉት መስትዋቶች በጣልያንኛ ስፔኪዮ ነው የሚባሉት። ከተጠራጠሩ የጣሊያንኛ ቋንቋን በደምብ የሚያውቅ ሰው ይጠይቁ ወይም የኢጣልያንኛ መዝገበቃላትን ይመልከቱ። በኛ አገር ግን ሕዝቡ በሙሉ ስፖኪዮ ሲል ነው የሚሰማው። ስፖኪዮ አይደለም ስፔክዮ ነው ብለህ ብታርመው ሰው ሁሉ ይስቅብሃል። ብዙዎቻችን ይበልጥ ከሚያውቁ ሰዎች ጠይቀን ከመማር ስህተታችንን ይዘን መኖር የምንመርጥ ይመስላል።

SERIES ተመሣሣይ፣ ተዛማጅ ወይም ተከታታይ ማለት ነው። Series of books ማለት ተከታታይ መጸሕፍት ማለት ነው። በቴሌቪዥን የምንሰማው ማስታወቂያ ግን SERIOUS (ሲሪየስ) of books እየተባለ ነው የሚነበበው። SERIOUS የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ደግሞ ኮስታራ፣ ቁም ነገረኛ፣ ምራቁን የዋጠ ማለት ነው። ሁለቱ የእንግሊዝኛ ቃላት አነባበባቸውም፣ ትርጉማቸውም የተለያየ ነው። አንድ ሰው አነባበቡን በትክክል የማያውቀው የባዕድ ቃል ሲገጥመው በግምት ከማንበብና መሣቂየ ከመሆን ይልቅ ያንን ቋንቋ የሚያውቀውን ሰው ጠይቆ መረዳት ወይም የዚያን ቋንቋ መዝገበ ቃላትን ማየት ያስፈልጋል።

የዘመኑን ቋንቋ በተመለከተ ሌላው አነጋጋሪ ቃል ማለት የሚለው ነው። ማለት ግልጽ ያልሆነን ሃሣብ ለማብራራት፣ ለመግለጽ የምንጠቀምበት ቃል እንደሆነ ለሆሉም ግልጽ ይመስለኛል። አንድን ቃል ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ለመተርጎም ይህ ቃል ምን ማለት ነው፣ ይህ ጽንሠ ሃሣብ ምን ማለት ነው ወዘተ እያልን በቃሉ ስንጠቀም ኖረናል። ያሁኑ አዲሱ አጠቃቀም ግን “ማለት ነው” የሚሉትን ሁለት ቃላት ትርጉም የሌላቸው ያደርጋቸዋል። አሁንም በዚህ በተሳሳተ መንገድ በቃሉ እየተኩራሩ የሚጠቀሙት ሕዝብን ማስተማር የማገባቸው የመገናኛ ብዙሐን ሰዎች ናቸው። ያሳዝናል! ጥቂት ምሳሌዎችን ልጥቀስ።

ከዜናው በኋላ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የተዘጋጀውን የትንተና ጽሑፍ እናቀርባለን ማለት ነው። ለዚህ አረፍተ ነገር መጨረሻ ሆነው የገቡት “ማለት ነው” የሚሉት ሁለት ቃላት ለአረፍተ ነገሩ ምንድን ነው የጨመሩለት? “ከዜናው በኋላ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የተዘጋጀውን የትንተና ጽሁፍ እናቀርባለን የሚለው በቂ አይደለም? ለምንድን ነው “ማለት ነው” የተባሉት ሁለት ቃላት የተጨመሩት? ሌላ ምሳሌ፣ ዘንድሮ ትምሕርቴን በደንብ ተከታትዬ የመጀመሪያ ዲግሪየን ከያዝኩ ሥራ ሳልፈልግ በቀጥታ ለሁለተኛ ዲግሪ ማለት ለማስተርስ እመዘገባለሁ ማለት ነው። አሁንም በዚህ አረፍተ ነገር የመጀመሪያው ማለት ትክክል ሲሆን መጨረሻ ላይ የገቡት “ማለት ነው” የሚሉት ሁለት ቃላት ግን ፈጽሞ አስፈላጊ አይደሉም።

የጠቃሽ አመልካች ሥራዋን እንዳታከናውን ተጽዕኖ እየደረሰባት ነው። ስለሆነም አባቴን ለማየት ወደ አገር ቤት እሄዳለሁ በማለት ትክክለኛው አነጋገር ፈንታ አባቴ ለማየት ወደ አገር ቤት እሄዳለሁ ሆኗል የዘመኑ አነጋገር። አባቴን፣ እናቴን፣ አገሬን እወዳለሁ የሚለው ትክክለኛ አነጋገር ቀርቶ አባቴ፣ እናቴ፣ አገሬ እወዳለሁ ሆኗል አሪፉ የዘመኑ አነጋገር። በዉ ካዕብና በው ሳድስ መካከል ያለው ልዩነት እየጠፋ በመሄድ ላይ ነው። በላሁ በማለት ፈንታ በላው እየተባለ ይጻፋል። ለመሆኑ ወዴት እየሄድን ነው? አደግን፣ ሠለጠንን ተባለና ፊደሎቻችንን መለየት ከማንችለበት ደረጃ ደረስን ማለት ነው?

የባዕድ ቋንቋዎችን በትክክል ለማወቅ መሞከርና በትክክል በጥቅም ላይ ማዋል ተገቢ ነው። ከራስ ቋንቋ በላይ (ለዚያውም በተሳሳተ መልኩ) ለባዕድ ቋንቋና ቃላት ጥገኛና ተገዥ መሆን ግን ጤነኛ አስተሳሰብ አይመስለኝም። አመሰግናለሁ።

* አቶ ማዕረጉ በዛብህ አንጋፋ ጋዜጠኛ ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ክፍል ማኔጂንግ ኤዲተር ናቸው።

 

የመኪና ማቆሚያ ችግር መዲናችንን ከተበተቧት ችግሮች መካከል አንዱ ነው። ከችግሩ የተነሳ ብዙዎች መኪናዎቻቸውን ለማቆም የሚመርጡት ለእግረኞች ታስቦ በተሰሩ መንገድ ላይ አሊያም በመኪና መንገድ ጥጋጥግ ላይ ነው። የከተማዋ የመኪና መንገዶች ደግሞ ዕድሜ ጠገብ ከመሆናቸው  እና በጊዜው በነበረው የመኪና ብዛት መጠን የተሰሩ ከመሆናቸው የተነሳ አሁን ያለውን የተሸከርካሪ መጠን በአግባቡ ማስተናገድ የሚችሉ አይደሉም። የመንገዶቹ ጥበት ሳያንስ ዳር ዳራቸው ላይ መኪና ማቆም ለእግረኛውም ሆነ ለአሽከርካሪዎች ፈታኝ ነው። እግረኞችም ለተሽከርካሪ በተፈቀደ መንገድ ላይ ለመሄድ ይገደዳሉ። ይሄ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሀገራችን ቀዳሚው ገዳይ ለሆነው የትራፊክ አደጋ መስፋፋት ዋና ምክንያት ነው። ተሽከርካሪ እና እግረኛ እየተጋፉ በሚሄዱበት ከተማ ላይ አንዴት የትራፊክ አደጋ በዛ ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ይሄ ጥሩ እና በቂ ምላሽ ነው። መኪና ደርቦ ለማለፍ በሚደረግ ጥረት በርካታ አደጋዎች እንደሚርሱ በየዕለቱ የምንሰማውም ከዚህ የተነሳ ነው።

 

ቋሚ የሆነ የመኪና ማቆሚያ አለመኖር የሚያስከትለው አደጋ በዚህ ብቻ የሚያቆም አይደለም። ከዚሁ ከመንገዶች ጠባብነት ጋር ተያይዞ በመንገድ ዳርና ዳር ላይ ተሽከርካሪዎች በሚቆሙበት ወቅት ለእግረኛው ብቻም ሳይሆን ለሌሎች አሽከርካሪዎች መንገድ ይዘጋሉ። በዚህ ደግሞ በአስቸኳይ ማለፍ የሚያስፈልጋቸው እንደ አምቡላንስ እና የእሳት አደጋ ማጥፊያ ተሽክርካሪዎች ለማለፍ ሲቸገሩ እያስተዋልን ነው። እነዚህ ተሽከርካሪዎች ተግባራቸው ህይወት የማዳን ተግባር እንደመሆኑ እንቅስቃሴያቸው በደቂቃዎች እንኳን ቢዘገይ የሰው ህይወት ላይ ውሳኔ የመስጠት ጉዳይ ነው። ምንም እንኳን በቂ የሆነ የመኪና ማቆሚያዎች በመዲናዋ ባይኖሩም በተለይ በተሽከርካሪ መንገድ ጥግና ጥግ ላይ ተሽከርካሪዎች እንዳይቆሙ በማድረግ እነዚህን ከባድ ውሳኔዎች ማስቀረት ይቻላል፤ ያስፈልጋልም። በእርግጥ የውጭ ሀገራት መሪዎች በሚመጡበት ወቅት አሽከርካሪዎች ተሸከርካሪያቸውን በመንገድ ዳር አቁመው መሄድ እንደሌለባቸው ሲነገር እና ሲከለከል እናያለን። ነገር ግን በዘላቂነት ሲተገበር እና ዜጎችን የመታደግ ስራ ሲሰራ አናይም። ለሌላው አካል ታይታ ብቻም ሳይሆን ለዘላቂ መፍትሔ በማሰብ ቢሰራ መልካም ነው።

 

                              አቶ ሃይሉ ሰብስቤ - ከፊቼ

ቁጥሮች

Wednesday, 08 March 2017 11:54

የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርት

61 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር            በ2015

 

63 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር            በ2016

 

69 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር            በአሁኑ ወቅት ያለው ምርት

 

                                 ምንጭ፡- የዓለም ገንዘብ ተቋም

40 በ60 ወይንስ 100%

Wednesday, 08 March 2017 11:50

አዲስ አበባ ከበርካታ ማህበራዊ ችግሮችዋ መካከል የመኖሪያ ቤት ችግር በቀዳሚነት የሚነሳ ነው። በ1997 ዓ.ም እንደገና በድጋሚ በ2005 ዓ.ም በጠቅላላው ወደአንድ ሚሊየን የሚጠጋ ሕዝብ በመኖሪያ ቤት ፈላጊነት ምዝገባ አከናውኗል። አስተዳደሩም በነደፈው የቤቶች መሃግብር መሠረት ለቤት አልባው ህብረተሰብ ቤት ሰርቶ ለማስረከብ ቃል ገብቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። ይህም ሆኖ እስካሁን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተጠቃሚ መሆን የቻለው ሕዝብ ጠቅላላ ቁጥር 200 ሺ እንኳን መድፈን አልቻለም። ይህም የቤት ልማት ፕሮግራሙ እጅግ አዝጋሚና ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር አብሮ ማደግና መጓዝ እንዳልቻለ ጠቋሚ ነው።

 

የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ሰሞኑን በተለይ በግንባታ ላይ የሚገኙትን የ40 በ60 መኖሪያ ቤቶች የደረሱበትን ደረጃ ለጋዜጠኞች በማስጎብኘት መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም የፊታችን ቅዳሜ ዕለትም እነዚሁ ፕሮጀክቶች ለምረቃ እንደሚበቁም ተነግሯል። የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ መጠናቀቅ ካለባቸው ጊዜ እጅግ ዘግይተውም እንኳን መጠናቀቅ አልቻሉም። ከምንም በላይ ደግሞ ስሙም እንደሚያስረዳው 40 በመቶ ሕዝቡ እንዲቆጥብ ቀሪውን 60 በመቶ በባንክ ብድር በማቅረብ ቤት አልባውን ሕብረተሰብ የቤት ባለቤት የማድረግ መርሃግብሩ ተረስቶ መቶ በመቶ መቆጠብ ለቻሉ ብቻ በዕጣ ቤት ለማከፋፈል የተያዘው ዕቅድ አስደንጋጭ ነው። መንግስት ለሕዝብ የገባውን ቃል ማክበር ያልቻለበት፣ ለውጡም ለምን ሊከሰት እንደቻለ ለሕዝብ ግልጽ ማብራሪያ ያልሰጠበት መሆኑ በተለይ ከዛሬ ነገ ቤት ላገኝ እችላለሁ በሚል ተስፋ ሰንቆ ለተቀመጠው ከ160 ሺ ያላነሰ የ40 በ60 ቤት ፈላጊ ህብረተሰብ ትልቅ መርዶ ሆኗል። ዜጎች መንግሥትን በማመን ብቻ ወደፕሮግራሙ ገብተው ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ሲቆጥቡ ቢቆዩም ባላወቁት ምክንያት የ40 በ60 መርሃግብር ወደ መቶ በመቶ መቀልበሱ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል።

 

በአሁኑ ወቅት ወደ 16 ሺ ያህል መቶ በመቶ ክፍያ የፈጸሙ ግለሰቦች ግንባታቸው የተጠናቀቁትን 1 ሺ 290 ያህል ቤቶች በዕጣ ለማደል የታሰበ መሆኑ ይፋ ሆኗል። ሌላው ከ140 ሺ በላይ ያለው ቀሪ ተመዝጋቢ ህዝብ መቼ እና እንዴት የቤቱ ባለቤት መሆን እንደሚችል የሚዳሰስና የሚጨበጥ መረጃ የለውም። አስተዳደሩ ወደዕጣ ማውጣት፣ ወደመመረቅ ከመሸጋገሩ በፊት እነዚህን ሕዝባዊ ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ መልስ ሊሰጥባቸውና ከሕዝብ ጋር መተማመን ሊፈጥርባቸው ይገባል። 

በይርጋ አበበ

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ለቡ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መንደር (ICT village) በሚባለው ቦታ ላይ ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ማዕከል ሊገነባ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር። ሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ የተባለ አገር በቀል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ድርጅት የሚያስገነባው የሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ማዕከል ግንባታ ከአራት ዓመታት በኋላ እንደሚጠናቀቅ የተገለጸ ሲሆን ለማዕከሉ ግንባታም 39 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ አስፈልጓል። 480 ሚሊዮን ብር ደግሞ ለግንባታው የሚያስፈልግ የገንዘብ መጠን ሲሆን 980 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ፍጆታ እንደሚያስፈልገውም ተገልጿል። ከዚህ የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ደግሞ 100 ሜጋ ዋት የሚሆነው የሚገኘው ተፈጥሮ “ከለገሰችን ከጸሀይ ብርሃን ነው” ሲሉ የማዕከሉ ኃላፊዎች ተናግረዋል።

የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የማዕከሉን ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሲሆን በወቅቱም “ዘርፉን እንደመንግስት ትኩረት እንሰጠዋለን። በተለይ ባላደጉ አገሮች ላይ የሚታየውን የእድገት ክፍተት ለመሙላት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚና ከፍተኛ ነው” ሲሉ አስታውቀዋል። ዶክተር ደብረጺዮን አያይዘውም ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሰው ኃይል (እውቀትን) ብቻ የሚጠይቅ ኢንቨስትመንት መሆኑን ገልጸው “በዚህ በኩል ደግሞ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከየትኛውም አገር የማናንስ ነን። በመሆኑም ይህን ዘርፍ መንግስታችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ያበረታታዋል” በማለት ተናግረዋል።

የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ በእምነት ደምሴ በበኩላቸው “ላለፉት 13 ዓመታት በስራ ላይ ቆይተናል። እስካሁን በነበረን የስራ ዘመንም በውስን አቅም እየሰራን የቆየን ሲሆን ከዚህ በኋላ በሰፊ ካፒታል ወደ ግንባታ መግባታችን በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር የሚያሰችለንን እና ከእነ ጎግል ወይም አማዞን ጋር ለመፎካከር አንድ ደረጃ የሚያቀርበንን አቅም መፍጠር ያስችለናል“ ሲሉ አዲስ ስለሚገነባው የሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ማዕከል በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። አቶ በእምነት አያይዘውም “እንደሚታወቀው ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን ካፒታል የሚፈልገው የአእምሮ ሀብትን ሲሆን ይህም በየዓመቱ ከዩኒቨርስቲዎቻችን በሚመረቁት ባለሙያዎች ዘርፉን ለማሳደግ አመቺ ይሆናል። አገራችን ለሶፍትዌር የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት የሚቻለው ከ70 እስከ 80 በመቶ የአእምሮ ሀብትን ካፒታል ብቻ የሚጠይቀውን ሶፍትዌር በአገር ውስጥ ማምረት ሲቻል ነው። ምክንያቱም ሶፍትዌር በተሻለ አቅም፣ በውስን ካፒታልና በሰው አእምሮ መመረት የሚችል ነው” ያሉ ሲሆን መንግስትም ከውጭ የሚገዙ ሶፍትዌሮች ላይ የሚጥለውን ታክስ በመጨመር በአገር ውስጥ የሚያመርቱትን ተቋማት እንዲያበረታታ ጥሪ አቅርበዋል።

ሲኔት ሶፍትዌር ሶሉሽን ቴክኖሎጂስ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን ላለፉት 13 ዓመታት በዘርፉ ተሰማርቶ የቆየ ሲሆን አዲስ የሚገነባው የሶፍትዌር ልማት ማዕከልም ባለአራት ብሎክ ነው። ከግንባታው መጠናቀቅ በኋላም ከ1,100 ለሚልቁ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ በእምነት ደምሴ ተናግረዋል።¾

በይርጋ አበበ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ 121ኛውን የአድዋ ድል በዓል በጣምራ እንደሚያከብሩ ገለጹ።

የመኢአድ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ እና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንዳስታወቁት የመታሰቢያ በዓል ዝግጅቱ የሚካሄደው በመኢአድ ዋና ጽ/ቤት ይሆናል። በዝግጅቱም ታሪካዊ ጽሁፎችና መነባንቦች እንደሚቀርቡ የተገለጸ ሲሆን ጥሪ የተደረገላቸው ምሁራንና እንግዶችም እንደሚሳተፉ የፓርቲዎቹ አመራሮች ተናግረዋል።

ዝግጅቱ የፊታችን ቅዳሜ ከቀትር በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን ክፍት መሆኑን ያስታወቁት የመኢአድ ምክትል ሊቀመንበር “በዝግጅቱ ላይ የመኢአድንና የሰማያዊ ፓርቲዎችን አመራሮች ጨምሮ በፖለቲካ ፓርቲዎቸ ድርድር ላይ ከእኛ ጋር እየሰሩ ያሉት አራቱ ፓርቲዎች (ኢራፓ፣ ኢዴፓ፣ መኢዴፓ እና ኢብአፓ አመራሮች ተሳታፊ ይሆናሉ” ሲሉ አስታውቀዋል። በፕሮግራሙ ላይ መታደም የሚፈልጉ ሁሉ እንዲገኙም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

121ኛው የአድዋ ድል በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ የተከበረው ባሳለፍነው ሀሙስ የካቲት 23 ቀን 2009 ዓ.ም መከበሩ ይታወሳል።¾

 

በያሬድ አውግቸው

የተለያዩ  አለም አቀፍ የዜና ማሰራጫዎች የአሜሪካዎቹ ፌደራልና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች  ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ  በሰባት  የኣለማችን ሀገራት ዜጎች ላይ  ያስተላለፉትን ወደ ሃገሪቱ ያለመግባት እገዳ  ውድቅ  ማድረጋቸውን  በቅርቡ አሰምተውናል።  ይህንንም ተከትሎ ፕሬዝደንቱ ህጉን የፍርድ ቤት ንትርክን ለማምለጥ በሚያስችል መልኩ አሻሽለው ለመተግበር  እንቅስቃሴ ላይ  ይገኛሉ ። በተመሳሳይ የጎረቤታችን ኬንያ ፌደራል ፍርድ ቤት የሃገሪቱ መንግስት የዳዳብ የስደተኞች መጠለያን ለመዝጋት ያስተላለፈውን ውሳኔ  ውድቅ ማድረጉም  ከቅርብ ግዜ ዜናዎች መካከል ይጠቀሳል። ምንም እንኳን ውሳኔዎቹ በላይኛዎቹ ፍርድ ቤቶች ሊለወጡ የሚችልበት እድል ያለ ቢሆንም ሂደቱ ግን  አስፈጻሚ አካላቱ ተቆጣጣሪ እንዳላቸው ያሳያል። የዚህ ጽሁፍ አላማ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የተከለከሉ የሰባቱ ሃገራት ዜጎች አሊያም  የዳዳብ ስደተኞች መጠለያ ነዋሪ ሶማሊያውያን መብት መከበርን  ለማንሳት አይደለም። ይልቁኑም የሁለቱ ሃገራት የፍትህ ስርዓት የደረሰበትን የነጻነት ደረጃ ለማንሳትና ለሃገራችን  የፍትህ ስርዓት ተመሳሳይ ነጻነት በመመኘት እንጂ።

በኔ እምነት በተለይ የኬንያው የፍትህ ስርዓት  ብዙ ልንማርበት የሚገባ እንደሆነ ይሰማኛል።  ጉዳዩን ልንማርበት ይገባል ለማለት ያስደፈረኝ ፍርድ  ቤቶቹ ውሳኔ ያስተላለፉት በውስብስብና  የመንግስት ወገን መከራከሪያዎች የመከሰት እድላቸው ሰፊ በሆነባቸው ጉዳዮች መሆኑ ነው። ሁለቱ ሃገራት  በአለም አቀፍ አሸባሪ ተቋማት መዝገብ ላይ ካላቸው የቀዳሚ ኢላማነት ደረጃ አንጻር የሽብር ተግባራት  የመከሰት እድላቸው የእርግጠኛነት ደረጃ  ይደርሳል ለማለት ይቻላል።  ይህም የፍርድ ቤቶቹ ውሳኔዎች  መብትን በማስከበር የሚቆም ሳይሆን በሃገራቱ ላይ አደገኛ አደጋ ይዞ ሊመጣ የሚችል ያደርገዋል።  ለዚህም ነው ዶናልድ ትራምፕ የሽብር አደጋ ከተከሰተ ተጠያቂው  የሃገራቸው  ፌደራል ፍርድ ቤት ነው ያሉት። አስገራሚው ጉዳይ የሁለቱም ሃገራት ፍርድ ቤቶች በዚህ አጣብቂኝ መካከል ቆመው  የሃገራቸውን ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ጭምር ለማስከበር  ወደ ኃላ የማይል ነጻነት ያላቸው መሆኑ ነው።

የሃገራችን የፍትህ ስርዓት  በተግባር ያለበትን ነጻነት ለመናገር ጥናት የሚፈልግ መሆኑ ባያጠያይቅም ምኞቴ ግን  የሃገራችን የሲቪክ ማህበራት እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሰብዓዊ መብት ተቋማት በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት ጥለው የኬንያውን ያህል ክብደትና ሪስክ ባላቸው ትልልቅ ጉዳዮችም ጭምር  የመንግስትን ከፍተኛ አካል በህግ ፊት መሞገት የሚያስችል ነጻነታቸውን ሲጠቀሙ መመልከት ነው። ለምሳሌ እንደ ኬንያው ውስብስብና ሰፊ ሪስክ / Risk/ ያላቸውን ጉዳዮች ትተንየሚኒስትሮችምክርቤትበስልጣንዘመኑከሚያስተላልፋቸውብዛት ያላቸውውሳኔዎችመካከልቢያንስአንዱእንዲሻሻል የፍርድ ቤት የክርክር መዝገብ የሚከፍቱ የሲቪክማህበራት  ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቶች  ውሳኔ ሰጥተው የነጻሜዲያውየትንታኔ  ርእስሲሆኑ መመልከት  ህዝቡበፍትህስርዓቱላይያለውንመተማመን  ይጨምራል። ምክንያቱም የየትኛውም የአለማችን ሃገር ተመሳሳይ ደረጃ ያለው አካል  እንደ አሜሪካና ኬንያ አስፈጻሚ አካላት  የሃገር ውስጥም ይሁን አለም አቀፍ ስምምነቶች  ሊጥሱ  የሚችሉበት ሁኔታ ስላለ።  ሌላው ምሳሌ መንግስት  ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር ከሚዋዋላቸው ብዛት ያላቸው የብድር ስምምነቶች መካከል  ቢያንስ አንዱ አዋጭ ባለመሆኑ ሌላ አማራጭ ይፈለግለት ከሚል ሲቪክ ማህበር አስፈጻሚው አካል የፍርድ ቤት ሙግት ሲገጥመው መመልከት  የሲቪክ ማህበራትን ሚና ከቃላት በላቀ  ጥልቀት የሚያስተምር  ሊሆንም ይችላል።  መንግስት በታችኛው ፍርድ ቤት  የሚያካሂደው ክርክር ውድቅ ሆኖበት ወደ ቀጣዩ  ፍርድ ቤት ጉዳዩን  ወስዶ ሲከራከር ማየትም እንዲሁ በፍትህ ስርኣቱ ላይ ያለን የዜጎች እምነት ያሳድጋል።

እነዚህን ሁሉ ምሳሌዎች ማንሳቴ መንግስት ውሳኔዎቹ ውድቅ ሲሆኑበት  ለመመልከት ካለ ተራ ፍላጎት የመነጨ አይደለም።  ይልቁንም  አስፈጻሚው አካል ውሳኔዎቹን በገለልተኝነት የሚፈትሽለት አካል መኖሩ  ለራሱም  ስለሚጠቅመው እንጂ።  ምክንያቱም አስፈጻሚው አካል  ህገ መንግስቱን& ሌሎች ሃገራዊ ህጎች ወይም አለም አቀፍ  ስምምነቶችን ሊጥስ የሚችልበት ሁኔታ  ይኖራል::

ለማጠቃለል የሲቪክ ማህበራትና የፍርድ ቤቶች ነጻነት መጠናከር ለሰብኣዊ መብቶች መከበር ለብልሹ አሰራሮች መወገድና ሃብትን በተሻለ ለመጠቀም እንዲሁም የመጭውን ትውልድ መብቶች ከማስጠበቅ ኃላፊነት አንጻር የሁላችንንም በተለይ የመንግስትን  ቁርጠኝነት ይፈልጋል።   

 

ከአባ መላኩ

የዓድዋን ድል 121ኛ ዓመትን ለመዘከር ጥቂት ቀኖች ቀርተውናል። ስለ ዓድዋ ድል አንጸባራቂነትና ዘመን ተሻጋሪነት በርካታ የታሪክ ተመራማሪዎች የየራሳቸውን ምስክርነት ሰጥተዋል። ሁሉም የታሪክ ጸሃፊዎች የዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን፣ ከዚያም አልፎ የመላ ጥቁር ህዝቦችን ታሪክ ቀያሪ ክስተት እንደሆነ ይስማማሉ። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊያኖች ልዩነታቸውን አቻችለው አገራቸውን ሊወር የመጣውን ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የአውሮፓ ሃይል በኋላቀር መሳሪያ መመከት መመከት ችለዋል። ለዓድዋ ድል መገኘት ዋንኛና ትልቁ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልዩነታቸውን አቻችለው አንድነታቸውን አጠናክረው ወራሪውን የቀኝ ገዥ ሃይል መመከት በመቻላቸው ነው።


የዓድዋ ድል አውሮፓዊያን አፍሪካን የሚያዩበትን የተሳሳተ መነጽር እንዲለውጡት አስገድዷቸዋል። በአውሮፓዊያን ስለአፍሪካ ያላቸውን የንቀት አተያይ እንዲያጤኑት፣ ጥቁሮች ለመብቶቻቸው የሚሞቱ መሆናቸውን እንዲረዱት አድርጓቸዋል። አውሮፓዊያን አፍሪካን የሚወስዷት የኋላቀርና አቅም የሌላቸው ህዝቦች መኖሪያ አድርገው የነበረውን አስተሳሰብን ያስወገደው የዓድዋ ድል ነው። የዓድዋ ድልን የተመለከቱ የአለም ጥቁር ህዝቦች የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄ እንዲያቀጣጥሉ ሞሯል ሆኗቸዋል። ወራሪውን ኃይል ጨምሮ በዘመኑ የነበሩ አውሮፓ ሃያላን መንግስታት በአፍሪካን ለመቀራመት የሚያደርጉትን ሩጫ እንደገና እንዲያጤኑት አስገድዷቸዋል። ለአብነት የኢትዮጵያን ነፃና ሉዓላዊ አገርነትን ሳይወዱ በግድ እንዲቀበሉ ሆነዋል። ከዓድዋ ድል ማግስት ምዕራባዊያኖች በአዲስ አባባ ኤምባሲያቸውን ከፍተው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ጀምረዋል።


የዓድዋ ድል ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን በአንድ ጥላ ማሰባሳብ የቻለ አለምን ያስደመመ ታላቅ ተጋድሎ ነው። የዓድዋ ድልን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በመካከላቸው ያሉትን በርካታ ልዩነቶቻቸውን ወደጎን በማድረግ የጋራ ጠላታቸው የሆነውን የውጭ ወራሪ ለመመከት መዝመታቸው ነው። ሁሉም የአፍሪካ አገሮች እዚህ ግባ በማይባል ትግል አገራቸውን ለአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አሳልፈው ሲሰጡ ኢትዮጵያዊያኖች ግን በተጋድሎ የአገራቸውን ዳር ድንበር ማስከበር ችለዋል።


እንደ ዶናልድ ሌቪን ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚሉት የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ ህዝቦች የኋላ ታሪካቸው የትብብር ማሳያ ነው ሲሉ ጽፈዋል። አዎ ይህ አባባል ትልቅ መልዕክት ያለው ነው። የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ስንቅና ትጥቃቸውን ተሸክመው በእግራቸው ሺህ ኪሎሜትሮችር ተጉዘው የአውሮፓ ዘመናዊ መሳሪያን የታጠቀን ጦር ገጥመው ድል ማድረግ መቻላቸው ምን ያህል ጥልቅ የአገር ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳይ ነው። የዓድዋ ድል የአያቶቻችንን የአገር ፍቅር ጽናት ያረጋግጣል፤ የዓድዋ ድል የአያቶቻችንን የመቻቻል ባህል ያሳያል፤ የዓድዋ ድል አያቶቻችን በመካከላቸው ያለውን ልዩነቶች እንዴት በአግገባብ እንደያዙት ያስተምራል፤ ባዕዳን በልዩነታቸው እንዳይጠቀም እንደተከላከሉ ያሳያል ፤ አዎ አዲሱ ትውልድ ከዓድዋ ድል በርካታ መልካም ነገሮችን ሊቀስም ይገባል።


በዓድዋ ጦርነት ወቅት የታየው የአንድነትና የትብብር መንፈስ ሁኔታ አለምን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን መሪዎችን ጭምር የሚያስገርም ነበር። ጥሪ የደረሰው የትኛውም ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ለጦርነቱ ስኬት የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። ሁሉም በአቅሙ ስንቅ ከማዘጋጀት እስከ ግንባር መሰለፍ ድረስ ተሳትፎ አድርጓል።


በቅኝ ግዛት ዘመን የአውሮፓ ወራሪ ኃይሎች አፍሪካን ለመቀራመት ይጠቀሙበት የነበረው ቀዳሚ ስትራቴጂ ከፋፍለህ ግዛው የሚባለውን ስትራቴጂ ነበር። ወራሪው የኢጣሊያ ሃይልም የኢትዮጵያ ህዝቦችን የትግል መንፈስ ለማዳከም ሲል የተለያዩ የመከፋፈያ ስልቶችን ለመጠቀም ቢሞክርም ህብረተሰቡ በአገሩ ሉዓላዊነት ላይ አንደራደርም በማለቱ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው ሊሳካለት አልቻለም።


የአባቶቻችን የአንድነት የትግል መንፈስ ለአሁኑም ሆነ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ትምህርት ሊሰጥ የሚችል ነው። እንደእኔ እንደኔ ዛሬ ያ የአያቶቻችንና መንፈስ ያስፈልገናል። በቅርቡ እንደተመለከትነው አንዳንድ ወገኖች የግብጽና ኤርትራ መንግስታትን ድብቅ አጀንዳ ለማሳካት ሲሯሯጡ ተመልክተናል። እነዚህ አካላት አያቶቻችን ለአገራቸው አንድነት ሲሉ የከሰከሱትን አጥንት ያፈሰሱትን ደም እየረገጡ እንደሆነ ያስተዋሉት አይመስለኝም።


በቅኝ ግዛት ማስፋፋት ሩጫ ወቅት የአውሮፓ ወራሪ ሃይል በርካታ የአፍሪካ አገሮችን በቀላሉ ማንበርከክ ቢችሉም ኢትዮጵያ ግን ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ጦር አሳፍራ በመመለስ ለነጻነቷ አሻፈረኝ የሚሉ ህዝቦች መኖሪያ መሆኗን በተግባር አሳይታለች። ኢትዮጵያዊያን ልዩነታቸውን ማቻቻል የሚችሉ፣ ምንም ያህል የውስጥ ቅራኔ ቢኖራቸውም የጋራ ጠላት በመጣ ጊዜ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አንድ መሆን የሚችሉ መሆናቸውን በአድዋ ድል በተግባራ አሳይተዋል።


ለጦርነት ስኬት ዘመናዊ መሳሪያ ብቻውን ፋይዳ እንደሌለው ይልቁንም የአላማ ጽናትና ፍቅር ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያዊያን ለአለም አረጋግጠዋል። ጣሊያኖች በወቅቱ ለራሳቸው ዘመናዊ መሳሪያና በቂ ዝግጅት በሰጡት ትልቅ ግምት እንዲሁም ኢትዮጵያዊያንን የተከፋፈሉና ኋላቀር መሳሪያ የታጠቁ ናቸው በሚል ስሌት ሳቢያ የአውሮፓው ግዙፍ ሰራዊት በኢትዮጵያ አገር ወዳድ አርሶ አደሮች ሽንፈትን ተከናንቧል። በዚህም ሳቢያ በቅኝ ገዠዎች ዘንድ ትልቅ መደናገርን ፈጥሯል።


ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው ለዓድዋ ድል ሰኬት የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የነበራቸው ልዩነት ወደጎን በማድረግ በወራሪው ጠላት ላይ በጋራ መሰለፍ መቻላቸው ነው። አዎ ኢትዮጵያዊያን ሁሌም በውስጥ ጉዳያቸው ማንም ጣልቃ እንዲገባ እንዲሁም ማንም የውጭ ሃይል የአገራቸውን ህልውና እንዲደፍር አይፈቅዱም። ለዚህ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። በቅርቡ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት የኤርትራው መንግስት ኢትዮጵያ ተከፋፍላለች፤ ከእንግዲህ ህዝቡ በአንድነት ሊቆም አይችልም በሚል የተሳሳተ እሳቤ ወረራ ፈጽሞ ነበር። ይሁንና ኢትዮጵያዊያን ምንም አይነት ልዩነት ቢኖራቸውም በአገር ጉዳይ ላይ አንድ ናቸው። ይህንንም በተግባር አሳይተዋል። የኤርትራ መንግስት ለዓመታት የገነባውን ሰራዊት በቀናት ምናልባትም በወራት ውስጥ ነበር የወራሪውን ሃይል አከርካሪ መስበር የቻሉት። ይህ ነው አንድነት፤ ይህ ነው ኢትዮጵያዊነት።


አያቶቻችን ባላቸው የአገር መውደድና የጀግንነት መንፈስ ወራሪውን የጣሊያን ጦር መመከት መቻላቸው አገራቸውን ከቅኝ ግዞት ታድገዋታል። እኛንም በራሳችን ስብዕና እንድንኮራ አድርገውናል። እኛም ድህነትን በመዋጋት የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማውረስ ይኖርብናል። በመሆኑም የዚህ ትውልድ ገድጅ መሆን ያለበት ድህነትን መዋጋት ነው። የድህነት ወጊያ ደም አይጠይቅም፤ አካል መጉደልንም አይጠይቅም፤ ከዚህ ትውልድ የሚፈለገው በተሰማራበት የስራ መስክ በታማኝነትና በቅንነት ህብረተሰብን ማገልገል ብቻ ነው።


የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያኖች በቅኝ ግዛት ላይ የማያወላዳ አቋማቸውን ያስመሰከሩበት ትልቅ ገድል ነው። የዓድዋ ድል የፍትህ መጓደልን ሰዎች በጋራ መከላከል እንደሚችሉ የሳየ ታላቅ የዓለማችን ክስተት ነው። ምክንያቱም በዚያን ወቅት፣ እንደዚህ ያለ ታላቅ ህዝባዊ ተጋድሎ በየትኛውም የዓለም አገር ተደርጎ አይታወቅም።


ዓድዋ የመላው አፍሪካዊያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝብ ከዚያም አልፎ የመላው ፍትህ የተጓደለበት ህዝብ ድል ነው። የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ድል ሊቀስመው የሚገባ ዋናው ትምህርት በአገራዊ ጉዳይ ላይ ልዩነት ማድረግ እንደማይገባ ነው። የውስጥ ችግሮቻች እንዳሉ ሆነው ከውጭ የሚቃጣ ወረራንም ይሁን ከውስጥ የሚነሳን አገር የማፍረስ ዘመቻን በጋራ የመከላከል ኃላፊነትን ካለፉት ትውልዶች ልንማር ይገባል።

በሳምሶን ደሳለኝ

ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ለሶስት ቀናት ይፋዊ ሥራ ጉብኝት ሰሞኑን አዲስ አበባ ነበሩ። ፕሬዚደንቱ አዲስ አበባ ሲገቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ እና የውጭ ጉዳዩ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ አቀባበል አድርገውላቸዋል። አቀባበሉም ዲፕሎማሲያዊ ትርጉሙ ላቅ ያለ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

በቆይታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ እና ከፕሬዝደነት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር በሁለቱ ሀገሮች መካከል እና በቀጠናው ጉዳዮች ዙሪያ መመካከራቸው ተነግሯል። በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በሁለቱ ሀገሮች መካከል ስምምነቶች ተፈርመዋል። በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮችም መክረዋል ተብሏል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ባለፉት አምስት አመታት በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል የነበረው  ዲፕሎማሲያዊ መቀዛቀዝ ይስተዋልባቸው ነበር። ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ካገኘች ማግስት ጀምሮ እ.ኤ.አ. እስከ 2013 ድረስ በደቡብ ሱዳን ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነት ከመከፈቱ በፊት በሁለቱ መንግስታት መካከል ጠንካራ የመተማመን ዲፕሎማሲ ነበር። ከዚህም በላይ ደቡብ ሱዳን እንደመንግስት እራሷን ችላ እንድትቆም የዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብም ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲያዊ እና የጸጥታ ድጋፍ እንዲያደርግላት የኢትዮጵያ መንግስት ሚና ከፍተኛ እንደነበረ የአደባባይ እውነት ነው።

ሆኖም ግን በ2013 በደቡብ ሱዳን በተነሳው የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት አቋም የገለልተኝነት ሚና አልነበረውም የሚል ክስ ከፕሬዚደንት ሳልቫኪር ማያርዲት በኩል መቅረቡን የዲፕሎማቲክ ምንጮች ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ ለዶክተር ሪክ ማቻር በኢትዮጵያ ውስጥ መጠለያ መስጠቷ ወገንተኛ አስብሏታል የሚሉ ወገኖችም አሉ። የኢትዮጵያ መንግስት የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ አካባቢን ወደ ኢኮኖሚ ኮሪደሮች ለመቀየር ካለው ሩቅ ግብ አንፃር፣ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ወገንተኛ የሆነ ሚና ሊኖረው እንደማይችል ይልቁንም ተጠባቂ እና ተገማች የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንደሚያራምድ አንስተው የሚከራከሩ ባለሙያዎችም በሌላ ወገን ይገኛሉ።

ሌላው በእነሳልቫኪር የሚመራው የደቡብ ሱዳን መንግስት፣ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መንግስት ጋር ያላትን ጥብቅ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት በማንሳት የኢትዮጵያን እቅስቃሴ ከአሜሪካ መንግስት ፍላጎት ጋር ተመጋጋቢ አድርገው ሲከሱ ይደመጣሉ። ከ2013 እስከ 2015 የተነሳው የእርስ በእርስ ጦርነት መቋጫ ለማበጀት የሽግግር መንግስት በማቋቋም ችግሮቹን ለመፍታት ብዙ ርቀት ቢኬድም፣ የሽግግር መንግስቱ ም/ፕሬዝደንት የነበሩት ዶክተር ሪክ ማቻር ከሽግግር መንግስቱ መውጣታቸውን ተከትሎ መሰረታዊ ለውጦች በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ውስጥ እንዲወለዱ ሆነዋል።

የዶክተር ሪክ ማቻር ከሽግግር መንግስቱ መውጣት ካስቆጣቸው ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። የዶክተር ሪክ ማቻር እርምጃ ባለድርሻ አካላት ያልመከሩበት ከመሆኑም በላይ ዶክተሩ የወሰዱት እርምጃ የእሳቸው ፍላጎት ብቻ ተደርጎም አልተወሰደም። ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስትም ዶክተር ሪክ ማቻር የተቃዋሚው ጎራ መሪ መሆናቸውን እውቅና በመንሳት ከኢትዮጵያ ግዛት ለቀው እንዲወጡ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፎል። በአሁን ሰዓት በደቡብ አፍሪካ በቁም እስር ላይ ዶክተር ሪክ ማቻር እንደሚገኙ ይታወቃል። እንዲሁም በዶክተር ሪክ ማቻር ምትክ ምክትል ፕሬዝደነትሆነው ለተሾሙት ለጀነራል ታባን ኢትዮጵያ እውቅና ሰጥታለች።

ለዚህም ነው፣ ባሳለፉነው ሳምንት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ መግባታቸው ተከትሎ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የነበረውን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ቦታው ለመመለስ ያለው ፋይዳ ትልቅ ተደርጎ የሚወሰደው። በተለይ ግብፅ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ግብፅን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ለዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ ስታሳየው ለነበረው “symbolic diplomacy” ተመጣጣኝ ምላሽ የሚሰጥ እርምጃም ተደርጎ የሚወሰደው።

ከሁሉ በላይ ግን የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ ሱዳን ከሚገኙ ማኅበረሰቦች ከፍተኛውን ቁጥር ውክልና ካላቸው ከዲንካ ጎሳ ለተገኙት ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ሙሉ እውቅና ሰጥቶ ለመስራት መዘጋጀቱ ተገቢነቱ ምትክ አልባ ነው። በተለይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አንፃር አደጋ ውስጥ ሊጥሉ የሚችሉ ክፍተቶችን ለመዝጋት ያለው ፋይዳ በጣም ከፍተኛ ነው።

ለምሳሌ በጃንዋሪ 10 ቀን 2017 ፕሬዝደንት ሳልቫኪር ማያርዲት በግብፅ ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ተከትሎ፣ ለፕሬዝደንቱ ቅርብ ናቸው የተባሉት አብርሃም ቾል ለNyamilepedia ዜና ማሰራጫ እንደተናገሩት “ደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ጥቅሟን ለኢትዮጵያ መሥዋዕት አታቀርብም” ብለዋል። አያይዘውም፣ “ደቡብ ሱዳንን በማስቀደም ተስማምተናል። ለዚህም ነው፣ ከግብፆች ጋር የተወያየነው። እነሱ ከሌሎች ጎረቤት ሀገሮች በተሻለ አቅርቦት አድርገዋል” ሲሉ አንፃራዊ አገላለጽ ተጠቅሟል።

ይህንን ከላይ የሰፈረውን የሚዲያ ጦርነት ሊከፈት የተቻለው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ፈጣን ገቢራዊ ምላሽ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ባለመስጠቱ ነው። ይህም ሲባል በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ያልነበሩ እንደግብፅ እና ኤርትራ የመሳሰሉ ሀገሮች በሁለቱ ሀገሮች መካከል በተፈጠረው ክፍተት ፍላጎታቸውን ለማራመድ አጋጣሚዎች እንዲፈጠሩ በማስቻሉ ነው!!

ከዚህም በላይ የግብጹ ፕሬዚደንት አል-ሲሲ እና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳል ቫኪር ማያርዲት የነጭ አባይ ውሃን መጠን በማበልጸግ ዙሪያ እና ከሕዳሴው የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ሥውር አፍራሽ ሥራዎችን ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ዓብይ ሚዲያዎች ዘግበውታል። አንዳንዶቹ መገናኛ ብዙሃን ስምምነቱን መጥፎ ስምምነት (“dirty deal”) ሲሉ ጠርተውታል። ይህም ሌላው ከግብፅ በኩል የተከፈተው የሚዲያ ጦርነት ነው።

እንደነዚህ ዓይትን የሚዲያ ጦርነቶችን ለመከላከል የኢትዮጵያ መንግስት ደቡብ ሱዳኖች በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ እምነት እንዲኖራቸው መስራት የግድ ይላል። ጥሩ ማሳያ የሚሆነው፣ ባለፈው ሳምንት በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተደረሰው ስምምነት ነው። ይኸውም፣ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ነዳጅ ለማስገባት እና ደቡብ ሱዳን የኤሌትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ለመውሰድ የሚያስችላትን መሰረተ ልማት ለመዘርጋት ተስማምተዋል። እንዲሁም፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ ኢነርጂና መሰረት ልማት ዝርጋታዎች በተመለከተ ስምምነቶችን ፈጽመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ እንደገለጹት፣ “ኢትዮጵያ በቅርቧ ካላችው ደቡብ ሱዳን ነዳጅ መጠቀም የሚያስችላት መሰረት ልማት ለመዘርጋት ተስማምታለች። በእኛ በኩል እስከ ደቡብ ሱዳን ድንበር ድረስ መንገዶች ተገንብተዋል። በደቡብ ሱዳን ውስጥ ነዳጅ እስከሚገኝባቸው አካባቢዎች መሰረተ ልማት የመዘርጋት ሥራ በፍጥነት እናከናውናለን” ብለዋል። ከዚህም በላይ የኢኮኖሚ ግንኙነቱን ለማጠናከር ነፃ የሰውና የዕቃ እንቅስቃሴዎች መኖርና የተደረጉ ስምምነቶችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ሁለቱም መሪዎች ተናግረዋል።

የኢኮኖሚ ግንኙነቱን ለማጠናከር ከጋምቤላ ፓርክ ፓሎውግ እና ከዲማ በራድ ወደ ቦማ ባር የሚወስዱ መንገዶች ግንባታ ለመጀመር ወስነዋል።

መሪዎቹ ግንኙነቱን ለማጠናከር የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ በዓመት ሁለት ጊዜ እና በጉባኤ ደረጃ የሚካሄደው ስብሰባ በዓመት አንድ ጊዜ ለማካሄድም መግባባት ላይ ደርሰዋል፤ የደቡብ ሱዳንን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በነሐሴ ወር 2015 በአዲስ አበባ ለተፈረመው ስምምነት ተፈፃሚነት በጋራ ለመስራትም ተስማምተዋል።

የደቡብ ሱዳናውያንን አንድነት ለማጠናከርና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ ብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድ በፕሬዚዳንት ሳልቫኪር የተደረገው ጥሪ ተግባራዊ እንዲሆን በጋራ እንሰራለን ብለዋል፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በደቡብ ሱዳንና በቀጣናው የተፈጠረው ድርቅ የሰው ሕይወት ሳያጠፋ ለመከላከል ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፤ ፈጣን የእርዳታ ድጋፍ ካልተደረገ የሰው ሕይወት የመጥፋት ዕድል በጣም ሰፊ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

ሁለቱ አገራት የመንገድና ድልድዮች ትብብር፣ በመንገድ ግንባታ፣ የኢነርጂና የጤና መስኮች የትብብር የመግባቢያ ሰነድ፣ የድንበር ንግድ ፕሮቶኮል፣ አማራጭ የንግድ ስምምነት፣ የተግባቦት፣ የመረጃና የሚዲያ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ግንኙነቶች ወደ ተግባር በፍጥነት ከገቡ ግብፅ በደቡብ ሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል የነበረውን ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሰብራ በመግባት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የእጅ አዙር ተፅኖዎችን ለማሳረፍ የምታደርጋቸውን ጠንክራ እንቅስቃሴዎችን ወደ ውርዴ ለመቀየር ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው። እንዲሁም በርግጥ የአስመራ አገዛዝ በደረሰበት ወቅታዊ የፖለቲካ ቁመና የግብፅ አጀንዳ ማስፈጽም የሚችልበት አቅም ይኖረዋል ተብሎ ባይገመትም፣ መፈረጋጡ ስለማይቀር በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተደረሰው ስምምነት ፈጥኖ ተግባራዊ ከሆነ አብሮ ምላሽ የሚያገኝ ነው የሚሆነው።¾


Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100
Page 9 of 160

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us