You are here:መነሻ ገፅ»arts»news admin - Sendek NewsPaper
news admin

news admin

ቁጥሮች

Wednesday, 09 August 2017 12:51

 

10 ቶን      በ2003 ዓ.ም ማለትም የመጀመሪያው እድገትና ትራንስፎርሜሽን መነሻ ወደ ውጪ የተላከ የወርቅ መጠን፣

 

10 ቶን      በ2007 ዓ.ም ማለትም በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን መጨረሻ ወደ ውጭ የተላከው የወርቅ መጠን፣

 

9 ቶን       በ2009 ማለትም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ወደ ውጭ የተላከ የወርቅ መጠን።

 

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ /ሐምሌ 19 ቀን 2009 ዓ.ም ዕትም/

 

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ላለፉት 10 ወራት በሥራ ላይ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው ሳምንት ማጠናቀቂያ ላይ ማንሳቱ የሚታወስ ነው። አዋጁ እንዲወጣ ምክንያት የሆነው በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት በመደበኛ ሁኔታ መቆጣጠር ባለመቻሉ መሆኑም አይዘነጋም። አዋጁ ከ10 ወራት ቆይታ በኋላ አገሪቱ በአንጻራዊ መልኩ ሀገሪቱ በመረጋጋቷ አዋጁ ለመነሳት መብቃቱ መልካም ዜና ነው። ይህ ማለት ግን በሕብረተሰብ ውስጥ ለብጥብጥና ለአመጽ መንስኤ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በበቂ ሁኔታ መልስ አግኝተዋል ማለት ግን አይደለም።  መንግስት በተደጋጋሚ እንዳረጋገጠው የመልካም አስተዳደር ችግር ቁልፍ የሥርዐቱ ችግር ሆኗል። ችግሩ ከችግርነት ባለፈ ግን መጠየቅ ያለባቸው አካላት በጋራም ሆነ በተናጠል እንዲጠየቁ በማድረግ ረገድ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የሄደበት መንገድ ሕዝብን ያረካ ነበር ብሎ መደምደምም አይቻልም። ባለፉት ወራት በአንዳንድ ክልሎች አንዳንድ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪ ናቸው የተባሉ አንዳንድ አስፈጻሚዎች በግምገማ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፤ ይህ ጥሩ ነገር ነው። እርምጃው ግን ምን ያህል ሕዝቡን ያሳተፈ ነበር? ምን ያህል ሕዝቡን ያረካ ነበር ብሎ መጠየቅ ግን ይገባል።

 ገዥው ፓርቲ በውስጡ እያካሄደ ያለው ጥልቅ ተሀድሶ የመንግሥትና የግል ሌቦችን ለመመንጠር የሚያስችል ፍሬ እያፈራ ነው። ይህም ሆኖ ግን ውጤቱ ሕዝብን በሚጠቅምና የሕዝብን ጥያቄ በማወላዳ መልኩ ለመፍታት የሚያስችል እንዲሆን አሁንም ከገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ብዙ ይጠበቃል። የህዝብ ጥያቄ በአስተማማኝ መልኩ መፍታት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ሆነ በሌላ ኃይል ሠላምና መረጋጋትን ማስፈን ወይንም  ማረጋገጥ እንደማይቻል ገዥው ፓርቲ እንዳይዘነጋ ያስፈልጋል።

በተለይ የመንግስት ሥልጣንን ለግል ብልጽግና ለማዋል በመመኘት በሙስናና ብልሹ አሠራር እጃቸው አስገብተዋል በሚል የተጠረጠሩ ባለሥልጣናት፣ ነጋዴዎች ሌሎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ አባሪ ተባባሪ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ለሕግ የማቅረቡ ጥረት ተጠናክሮ፣ ሁሉንም ዘርፎች፣ ከላይ እስከታች ያለውን መዋቅር በፈተሸ መልኩ መከናወን ካልቻለ የህዝብን አመኔታ ለማግኘት ከባድ መሆኑ አይቀሬ ነውና ጉዳዩ በጥብቅ ቢታሰብበት።¾

·         አዲስ ጽላት ለማስገባት በሚል ነባር ታቦትና ቅርሶች ይሰረቃሉ፣ ይለወጣሉ፤ ተብሏል

  ·         ዝርፊያው፥ የጦር መሣርያ በታጠቁ ግለሰቦች እንደሚፈጸም ተጠቁሟል

  ·     ዞኑ፥ ከደብረ ሲና እስከ አንኮበር ተራራ የቱሪስቶች የኬብል ማጓጓዣ ያሠራል

በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናትና በርካታ የታሪክ ቅርሶች በሚገኙበት ሰሜን ሸዋ ዞን የሚፈጸመው የነባር ጽላትና ቅርሶች ዘረፋና ቅሠጣ፣ ከሀገረ ስብከቱ አቅም በላይ እንደሆነ መረጋገጡ ተገለጸ፡፡

ከመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ከቅርስ ዘረፋና ለውጥ ጋራ ተያይዞ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በቀረቡ የምእመናንና የሠራተኞች አቤቱታዎች መነሻ በተካሔደው ማጣራት፣ የሀገሪቱ የታሪክ አሻራ ያሉባቸው በርካታ ቅርሶች፣ የመንግሥት ለውጥ ከኾነበት ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ለተጽዕኖ እየተጋለጡና እየተዘረፉ እንዳሉ ለመረዳት መቻሉን፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ አጣሪ ልኡክ ሰሞኑን ለአስተዳደር ጉባኤው ባቀረበው ሪፖርት ገልጿል፡፡

የጻድቃኔ ማርያም፣ የሸንኮራ ዮሐንስ፣ የሳማ ሰንበት፣ የሚጣቅ ዐማኑኤል፣ የዘብር ገብርኤል እና መልከ ጸዴቅ ገዳማትንና አድባራትን ጨምሮ ከሁለት ሺሕ በላይ አብያተ ክርስቲያናትን አቅፎ የያዘው የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ ቅርሶቹን ለማስጠበቅ የአቅም ውሱንነት እንዳለበት፣ በመስክና በመድረክ በተደረጉት የልኡኩ የማጣራት ሒደቶች ሁሉ ማሳያዎች እንደቀረቡ ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

በሚጣቅ ዐማኑኤል ቤተ ክርስቲያን የነበረ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የብራና ዳዊትና ከዐጤ ምኒልክ የተሰጠ መስቀል ተዘርፎ የደረሰበት እንዳልታወቀና ሀገረ ስብከቱም እንዳልተከታተለው፤ የመንዝ የቀያ ቅዱስ ገብርኤል ጽላት ተሰርቆ ሲፈለግ ቆይቶ ጽላቱን የያዘው ሰው በቁጥጥር ሥር ውሎ በፖሊስ ከተጣራ በኋላ ሲመለስ ነባሩ ቀርቶ አዲስ ጽላት ተለውጦ መመለሱን፤ ከተዘረፉት ቅርሶች ጅቡቲ ድረስ የተወሰዱ መኖራቸውንና አንድ ጽሌ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቅርስ ጥበቃ መመሪያ ጋራ በመተባበር እንዲመለስ መደረጉን፤ በሚዳ ኦሮሞ ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፥ የሀገረ ስብከቱን ይሁንታ ሳያገኝና ማዕከሉን ሳይጠብቅ አዲስ ጽላት ለማስገባት በሚል አግባብነት የሌለው ሒደት መፈጸሙንና ታቦታቱ እስከ አሁን በኤግዚቢት ተይዘው እንደሚገኙ፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት ነን ያሉና የወታደር ልብስ የለበሱ የተደራጁ ግለሰቦች፣ ቄሰ ገበዙንና የጥበቃ ሠራተኞችን በደጀ ሰላሙ አግተው የነጭ ገደል በኣታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን ንብረቶች ዘርፈው መውሰዳቸውን፤ በሌላም ጊዜ ተደራጅተው ሊዘርፉ የመጡ ግለሰቦች ተይዘው በእስር ላይ እንደሚገኙና የጥበቃው አቅም አነስተኛ መሆኑን፤ ደንባ ከተማ ላይ መሸኛ የሌለው ታቦት ተይዞ በሀገረ ስብከቱ አመራር ሰጭነት መቀመጡን፤ ሁለት የቅዱስ ገብርኤል እና ሁለት የቅዱስ ሚካኤል ጽላት መሐል ሜዳ ተገኝተው ቢመለሱም እስከ የስርቆት ሙከራው መቀጠሉን፤ በአፈር ባይኔ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጽላቱ ባይለወጥም የቅርስ ዘረፋው እንዳልቆመ፤ በቁንዲ ቅዱስ ጊዮርጊስ 14 የብራና መጻሕፍት፣ የብር ከበሮ፣ መስቀል፣ ኹለት ኩንታል የተቋጠሩ ንብረቶች ተዘርፈው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ አዋሬ ፖሊስ ጣቢያ ተይዘው ቢመለሱም ዘራፊዎቹ ለ8 ዓመት በሕግ ተፈርዶባቸው ሳለ 5 ዓመት ተቀንሶላቸው በ3 ዓመት እስራት መፈታታቸውን፤ በጃን አሞራ ተክለ ሃይማኖት የብራና መጻሕፍት መጥፋታቸውን፤ የአንኮበር ቅዱስ ሚካኤል ደወል ተሰርቆ በክትትል ላይ እንደኾነ… ወዘተ በማጣራቱ ሒደት ከቀረቡት ማሳያዎች ውስጥ እንደሚገኙበት በሪፖርቱ ተዘርዝሯል፡፡

በቅርስ ዘረፋውና ቅሠጣው ተይዘው የታሰሩ ቀሳውስትና ዲያቆናትም መኖራቸውን በማረሚያ ቤቶችም ማየትም እንደሚቻል በአቤቱታ አቅራቢዎች የተነገረውን ያሰፈረው ሪፖርቱ፤ ዘረፋው የሚፈጸመው፥ የወታደር ልብስ የለበሱና የተደራጁ ግለሰቦች፣ የጥበቃ ሠራተኞችን በማገትና በማታለል እንደሚፈጸም ለሀገረ ስብከቱ የሚደርሱ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩ፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ለልኡኩ ማስረዳታቸውን ጠቅሷል፤ የሀገረ ስብከቱ ቅርስ ክፍል ሓላፊም፣ “በርካታ ቅርሶች በኃይልና በአፈና ተዘርፈውብናል፤ ከተዘርፉት ቅርሶች መካከል አብዛኞቹ ጅቡቲ ሲደርሱ ተይዘው የተመለሱ አሉ፤” ብለዋል፡፡

በማጣራቱ ሒደት የተሳተፉት የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ምንውየለት ጭንቅሎ፣ የቀያ ቅዱስ ገብርኤል ነባር ጽላት በአዲስ መለወጡን አረጋግጠው፣ ይሁንና ነባሩ ጽላት በአዲስ ጽላት እንዲለወጥ ስምምነት የተደረገው፣ በወቅቱ ጉዳዩን በተከታተለው ፖሊስና በሌሎች ካህናት እንደነበርና ፖሊሱ በወንጀል ተከሦ እስር ቤት ከመግባቱም በላይ ከሥራ እንዲሰናበት መደረጉን፣ ካህናቱም በእስር ላይ እንደነበሩ አውስተዋል፡፡

ለዘረፋው መንገድ የሚከፍተው ተጠቃሹ መንሥኤ፣ አዲስ አበባ የሚኖሩ ካህናትም ሆኑ ምእመናን፣ “ተወላጆች ነን” በሚል ከአንዳንድ ግለሰቦች ጋራ እየተመሳጠሩ፣ “ታቦት በበጎ አድራጊነት በድርብ እናስገባለን፤” በሚል የሚፈጥሩት ችግር እንደሆነ ሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ታቦት የሚያስፈልጋቸው አብያተ ክርስቲያናት ጥያቄን በማዕከል እንዲያስተናግድ አሳስቦ፣ “ከአዲስ አበባ በመንደር ካሉ ነጋዴዎች የሚመጡ ጽላት፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ያልጠበቁ፣ የመለወጡ ሒደትም ሕገ ወጥ ተግባር መሆኑን” አስገንዝቧል፡፡ ይህን በሚፈጽሙ አካላት ላይ ሀገረ ስብከቱ ተከታትሎ አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወስድ፣ የመንግሥት አካላትም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አስታውቋል፡፡

ሪፖርቱ አክሎም፣ የዞኑ መስተዳድር ቅርስን ለማስመለስና ዘራፊዎችን ለመያዝ የሚያደርገው ጥረት እንደሚያስመሰግነው ገልጾ፤ በማጣራቱ ሒደት፣ በቅርስ ዘረፋ ወንጀል ተከሠው በሕግ የተፈረደባቸው አንዳንድ ዘራፊዎች፣ የቅጣት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ከእስር እየተለቀቁ በሚል የተሰጠው አስተያየት፣ “አጽንዖት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል፤” ብሏል፡፡

ባለፈው ሚያዝያ ወር አጋማሽ በተካሔደውና የዞኑና የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች በተሳተፉበት የጋራ መድረክ ላይ የተገኙት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ፣ ከሙሰኝነትና የቤተሰባዊ አስተዳደር ጋራ ተያይዘው የተነሡ ውዝግቦች ለመንግሥትም አሳሳቢ እንደሆኑን ሀገረ ስብከቱ ራሱን መፈተሸ እንደሚገባው አሳበዋል፡፡ ዞኑን ለቱሪዝም እንቅስቃሴ አመቺ ለማድረግ አስተዳደሩ ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገ እንዳለም አስረድተዋል፡፡ ዞኑ ባሉትና ቱሪስቶችን ለመሳብ የሚስችሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት የጋራ ተጠቃሚዎች ለመሆን ጥረት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡ ከደብረ ሲና ተራራ እስከ እመ ምሕረት አንኮበር ተራራ ድረስ የአየር ላይ የኬብል ማጓጓዣ ለማሠራት ውጭ ሀገር ድረስ እየተጻጻፍን እንገኛለን፤” ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

 

በጥበቡ በለጠ

ሕፃኑ ሰኔ 12 ቀን 1916 ዓ.ም ባሌ ክፍለ ሀገር ከዱ በሚባል ሥፍራ ከአቶ ሳህሉ ኤጄርሳና ከወ/ሮ የወንዥ ወርቅ በለጠ ተወለደ።

አምስት ዓመት ሲሞላው ትምህርት ይማር ዘንድ አባቱ ወደ ጎባ ይዘውት ሄዱ። ቤተሰቦቹ በሥራ ምክንያት አንድ ቦታ የሚቀመጡ አልነበሩምና መንገዳቸውን ጊኒር ወደ ሚባል ቦታ አደረጉ። እዚህም ብዙ አልቆዩም። ወደ ጎሮ፣ በመቀጠልም ወደ አርከሌ፣ ከዚህ ተመልሰው ደግሞ ሐረር ገቡ። ከቤተሰቡ ጋር ከአካባቢ አካባቢ ሲንከራተት የነበረው ህፃን ትንሽ ፋታ ያገኘው ሐረር ከገባ በኋላ ነበር። ትምህርት ቤት ገብቶ አልፋ ቤት እንዲቆጥር ተደረገ። የሚማረው በፈረንሳይኛ ቋንቋ ነበር።

  ወላጅ አባቱ አሥራ አራት ዓመት ሲሞላው አቶ መንበረ ወርቅ ኃይሉ ለተባሉ ግለሰብ በአደራ ሰጡት። ታዳጊው የወላጆቹን ቤትና ፊደል የቆጠረበትን ቀዬ ለቅቆ ወደ አዲስ አበባ መጣ። አዲስ አበባ መጥቶ ቀበና አካባቢ ከሚገኘው ኮከበ ጽባህ ት/ቤት ገብቶ ትምህርቱን እንደቀጠለ ብዙም ሳይቆይ የማይጨው ጦርነት ኦጋዴን ላይ ተቀሰቀሰ።

የታዳጊው ተስፋ የጨለመው ይሄኔ ነበር። ቤተሰቦቹ የሚኖሩት ሐረርና ባሌ በመሆኑ አጎቶቹና አጠቃላይ ዘመዶቹ ሳይቀሩ ወደ ኦጋዴን ለጦርነት ዘመቱ። ከታዳጊው ዘመዶች መካከል ግን ከጦርነቱ የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም። ሁሉንም የማይጨው እሳት በላቸው። ታዳጊው በየዕለቱ የሚመጣበትን መርዶ እየሠማ እህህ ማለት ሥራው ሆነ። ይባስ ብሎ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ከአባቱ በአደራ የተቀበሉት ብቸኛ አሳዳጊው አቶ መንበረ ወርቅ ኃይሉ አዲስ አበባ ላይ በጣሊያንያውያን በስቅላት ተቀጡ።”

ታዳጊው ብላቴናም ማንም በማያውቀው ከተማ ልቡ በከፋ ሀዘን እንደተሰበረ ብቻውን ቀረ። ምንም እንኳ ታዳጊው በዚህ ቁጭት ከጠላት ጋር ለመፋለም ልቡ ክፉኛ ቢነሳሳም በበረታ የእግር ሕመም ሳቢያ ሐሳቡን እውን ማድረግ አልተቻለውም። እንደውም የእግር ሕመሙ ስለጠናበት ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መሄድ ግድ ሆነበት።

ሆስፒታል ውስጥ እንዳለም ኑሮን ለማሸነፍ፣ እህል ቀምሶ ለማደር የሐኪም ቤቱ ኀላፊ የሆነውን ጣሊያናዊ ጫማ ይጠርግ ነበር። ሕክምናውን እየጨረሰ ሲመጣ ከጣሊያናዊው ጋር በመግባባት እግረ መንገዱን መርፌ መቀቀል፣ ቢሮ ማፅዳት የመሳሰሉ ሥራዎችን ይሠራ ነበር። በኋላም ክትባት እስከ መከተብ ደርሶ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ፈረንሳይኛ ቋንቋ በመቻሉ የጣሊያንኛን ቋንቋን ለመልመድ ብዙም ጊዜ ስላልወሰደበት ለሕክምና ለሚመጡ ሰዎች በአስተርጓሚነት ያገለግልም ነበር።

ወጣቱ ሆስፒታል ብዙ አልቆየም። አንድ ጣሊያናዊ አትክልት ተራ አካባቢ ክሊኒክ ሲከፍት ይዞት ሄደ። ሆስፒታል ሳለ የተማረውን የሕክምና ሙያ ከቀጣሪው ጋር በመሆን መሥራቱን ተያያዘው።

ጣሊያናዊው ወደ አገሩ ሲሄድ ክሊኒኩ ውስጥ ይታከም የነበረ ሌላ ጣሊያኒያዊ ከአትክልት ተራ አለፍ ብሎ “ሎምባርዲያ” የሚባል ሆቴል ውስጥ በቦይነት ቀጠረው። እግረ መንገዱንም የመስተንግዶ ሙያ አሰለጠነው። ይህ ጣሊያንያዊም ብዙ አልቆየም፤ ስለታመመ ወደ አገሩ ተመለሰ።

የወጣቱ እንግልት በዚህ አልተቋጨም። ጣሊንያዊው ወደ አገሩ ከመሄዱ በፊት በያኔው መጠሪያው እቴጌ ሆቴል አስቀጠረው።

ይህ ታሪክ ከተፈፀመ 60 ዓመት እላፊ ሆኖታል። በእንዲህ ዓይነት የህይወት ውጣ ውረድ ያለፈው ሰው ግን ዛሬም አለ።

“የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች እንደምን ናችሁ ልጆች!”በማለት ለአርባ ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ተረት በመተረት ብዙ ኢትዮጵያውያንን በመምከር ያሳደጉት አባባ ተስፋዬ ከላይ የተጠቀሰው ታሪክ ባለቤት ናቸው። ታሪካቸውን ከእቴጌ ሆቴል በመለጠቅ እንዲህ ይተርካሉ፤

“ሆቴሉን ይመራ የነበረው ጣሊያኒያዊ ስልጡን በመሆኔና የወሰደኝ ጣሊያኒያዊ አደራ ስላለበት በጣም ይወደኝ ነበር። በዚህ ምክንያት የሆቴሉ የምግብ ክፍል ረዳት ኀላፊ አደረገኝ።”

አባባ ተስፋዬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዘመናዊ ሙዚቃ ጋር የተዋወቁት እዚህ ሆቴል ውስጥ እንደነበር ሲናገሩ፣ “ሙዚቃ ስለምወድ ክራር እና ማሲንቆ እጫወት ነበር። ሆቴሉ ውስጥ ያገኘሁትን ፒያኖ እየነካካሁ ጥሩ ፒያኖ ተጫዋች ሆንኩ” ብለዋል።

“አንድ ጊዜ ከጣሊያን አርቲስቶች መጥተው ያረፉት እቴጌ ሆቴል ነበር። ትርዒቱን ያቀርቡ የነበረው ሲኒማ ኢትዮጵያ አዳራሽ ስለነበር ቀን ቀን የሚበሉትንና የሚጠጡትን ይዤላቸው ስሄድ የሚሠሩትን በደንብ እመለከት ነበር። ትንሽ ቆይቼ እነሱ ሲሉ የነበሩትን መልሼ እልላቸው ስለነበር ይገረሙና፣ ‹ይሄ ጠቋራ እንዴት ነው የኔን ቃል የሚጫወተው የኔን ቃል እንዴት ነው የሚናገረው› ይሉ ነበር።”

ይሁን እንጂ የሆቴሉ ሥራና ኑሮ ያን ያህል የተመቻቸው አልነበረም። እንደውም ከእሳቸው በሥልጣን ከፍ ካለው ጣልያንያዊ ጋር እንደማይግባቡ ያስታውሳሉ፤

 “ከኔ በላይ ያለው ጣሊያኒያዊ ኀላፊ ጥቁር በመሆኔ አይወደኝም ነበር። አንድ ቀን አምሽቼ ወደ ሥራ ገባሁ። ሰሃንና ጭልፋ ይዤ ወደ ምግብ ማብሰያው ስሄድ ያ የማይወደኝ ጣሊያንያዊ፣ ‹እስካሁን የት ቆይተህ ነው አሁን የምትመጣው› ብሎ በቃሪያ ጥፊ መታኝ። ሰሃኑን አስቀመጥኩትና በጭልፋው ግንባሩን አልኩት። የሆቴሉ ኀላፊ ጩኸት ሰምቶ መጥቶ ሲያይ ሰውየው ደምቷል።”

የአባባ ተስፋዬና የጣሊያንያዊው አለቃቸው ግብግብ በዚህ አልተጠናቀቀም። እንደውም ከአዲስ አበባ ለቅቀው ወደ ሐረር እንዲሄዱ ምክንያት ሆነ። ሌላ መከራ፣ ሌላ ጭንቀት።

“የሆቴሉ ኀላፊ ‹ማነው እንዲህ ያደረገው ብሎ ሲጠይቅ እኔ መሆኔ ተነገረው። አንጠልጥሎ በርሜል ውስጥ ከተተኝና እንዳልወጣ አስጠንቅቆኝ ሄደ። ፖሊስ ሁኔታውን ሰምቶ ሊይዘኝ ሲመጣ አላገኘኝም። ከለሊቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን ጣሊያኑ መጥቶ አወጣኝና የሚስቱን ካፖርት አልብሶ ወደ ቤቴ ወሰደኝ። ‹ነገ በጠዋት ባቡር ጣቢያ እንገናኝ› ብሎኝ ሄደ። በማግስቱ ባቡር ጣቢያ ስደርስ ጣሊያኑ በካልቾ ብሎ ለሌላ የምግብ ቤት ኀላፊ ለነበረ ጣሊያንያዊ አስረከበኝ።”

አባባ ተስፋዬ ከአለቃቸው ጋር በተጣሉ በሁለተኛው ቀን በባቡር ድሬዳዋ ተወሰዱ። ድሬደዋም ሲደርሱ ቀጥታ ያመሩት ወደ ሐረር ነበር። ሐረር ሲደርሱ ግን ዘመድ አልባ አልሆኑም። ከአንዲት አክስታቸው ጋር ተገናኙ። ይህ ለዘመድ አልባው ተስፋዬ ደስ ያሰኘ አጋጣሚ ነበር።

“ድሬደዋ ስደርስ ሐረር በሚሄድ አብቶብስ ከዕቃ ጋር ተጭኜ ሄድኩ። ውስጥ እንዳልገባ የተፈቀደው ለጣሊያኖች ብቻ ነበር። ሐረር ስደርስ አክስት ስለነበሩኝ እያጠያየኩ ሄድኩ። አክስቴ ሲያዩኝ አለቀሱ። ‹እኛ እኮ ሞተሃል ብለን ነበር› አሉና አዘኑ።”

አባባ ተስፋዬ ምንም እንኳ አክስታቸውን አግኝተው ደስ ቢሰኙም የመሥራት ፍላጎትና አቅም ነበራቸውና ያለ ሥራ ቁጭ ማለትን አልፈቀዱም። በማግስቱ ጠዋት ሐረር ወዳለው እቴጌ ሆቴል ቅርንጫፍ ሄዱ። “ኀላፊው ጀርመናዊ ነበር።” ይላሉ አባባ ተስፋዬ ያንን አጋጣሚ ሲያስታውሱ፤

“ኀላፊው ጀርመናዊ ነበር። አዲስ አበባ እቴጌ ሆቴል በቦይነት መሥራቴን ስነግረው ‹በኋላ ተመልሰህ ና!› አለኝ። አዲስ አበባ ስልክ ደውሎ መሥራቴን አረጋግጦ ጠበቀኝና ከሰዓት ስመለስ ቀጠረኝ።”

ሥራ እንደጀመሩ ትንሽ ቆይቶ ጣሊያን ተሸንፎ ኢትዮጵያን ለቆ ወጣ። “ሆቴሉን ልዑል መኮንን ገዙትና ‹ራስ ሆቴል› አሉት።” የሚሉት አባባ ተስፋዬ በሆቴሉ የምግብ ቤቱ ኃላፊ ሆነው እንደተሾሙ ይናገራሉ። በመቀጠልም፣ “መኳንንቱ ወደ ሆቴሉ ለእረፍት ሲመጡ ፒያኖ እየተጫወትኩ አዝናናቸው ነበር።” ይላሉ።

“ጃንሆይ ለጦርነቱ ድጋፍ ላደረጉ የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች ጅጅጋ ላይ መሬት ሰጥተዋቸው ስለነበር ይህን አስመልክቶ በእቴጌ ሆቴል የእራት ግብዣ ተዘጋጀ። በግብዣው ላይ የእንግሊዝና የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ መዝሙር ማርሽ ተመታ። የኛ ይቀጥላል ብዬ ስጠብቅ የለም። ንድድ አለኝና ለጄኔራል አብይ ፒያኖ መጫወት እንደምችልና የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙርን እንድጫወት ጠየቅሁኝ። ስለተፈቀደልኝም በዚያ ወቅት የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር መታሁ። ያኔ ሁሉም ብድግ ብለው ሠላምታ ሰጡ።”

በ1934 ዓ.ም በጦርነቱ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች ይሰብሰቡ የሚል ትዕዛዝ ከመንግስት ተላለፈ። ይህን የመንግስት ትዕዛዝ የሰሙት አባባ ተስፋዬ ከሐረር ተመልሰው አዲስ አበባ እንደመጡ ይናገራሉ። ይሄኔ ነው ወደ ኪነ ጥበቡ ዓለም ጥቅልል ብለው የመግባት ዕድሉ የገጠማቸው።

በ1934 ዓ.ም ግድም ዕጓለ ማውታን ተሰባስበው በሚያድጉበት ት/ቤት ገብተው መማር ቀጠሉ። በ1937 የማዘጋጃ ቴአትር ቤት የቴአትር ፍላጎት ያላቸውን ሲያሰባስብ ሸላይ፣ ፎካሪና ተዋናይነታቸውን የሚያውቁና የሚያደንቁ ባለሥልጣኖች ላኳቸው። ማዘጋጃ ቤት ገብተው ለ11 ወራት ያህል ሙዚቃ፣ የቀለም ትምህርት፣ ፈረንሳይኛና እንግሊዘኛ በነፃ ተማሩ። ለሚቀጥሉት 11 ወራት ያህል ደግሞ በወር 11 ብር እንደ ደመወዝ ይከፈላቸው ነበር። ይሀ እንግዲህ ወደ 1939 ግድም ሲሆን ከትምህርቱ ጋር ምግብ፣ ልብስና መኝታ ተሰጥቷቸዋል። መኝታው ባዶ ፍራሽ ነበር።

ይህ ወቅት እነ ግርማቸው ተ/ሐዋርያት ብቅ ብቅ ያሉበት ጊዜ በመሆኑ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ወቅት ነበር። ይሄኔ አባባ ተስፋዬ ወደ ቴአትሩ መድረክ ብቅ አሉ። በጊዜው ሴት ተዋንያት የሌሉ በመሆኑ ብዙ ቴአትር ላይ የሴት ገፀ ባሕርይን ተላብሰው የሚጫወቱት ወንዶች ነበሩ። ከነዚህ ወንዶች መካከል ደግሞ አባባ ተስፋዬ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ፤

 “የአቶ አፈወርቅ አዳፍሬ ቴአትር ወጣ። አርእስቱን አላስታውሰውም። ብቻ “የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የሚል ነገር አለው። በቴአትሩ ውስጥ ሴት ገፀ ባሕርይ ስለነበረች እንደ ሴቷ ሆኜ የተጫወትኩት እኔ ነኝ። ብዙ ቴአትሮች ላይ ለምሳሌ ‹ጎንደሬው ገ/ማርያም›፣ ‹ቴዎድሮስ›፣ (የግርማቸው ተ/ሐዋርያት) ‹ንፁ ደም›፣ ‹አፋጀሽኝ›፣ ‹መቀነቷን ትፍታ›፣ ‹ጠላ ሻጯ›፣ ‹የጠጅ ቤት አሳላፊ›… በመሳሰሉት ቴአትሮች ላይ ሴት ሆኜ ሠርቻለሁ። ይህም የሆነበት ምክንያት በዚያ ዘመን ሴት ተዋንያን ስላልነበሩ ነው።”

አባባ ተስፋዬ ሴት ሆነው ሲጫወቱ ሜካፑን ( ) የሚሠሩት እራሳቸው ነበሩ። መድረክ ላይ ወጥተው ሲተውኑ ፍፁም ሰው እንደማያውቃቸው እንዲህ በማለት ይናገራሉ፤

“እኔም የሴቶቹን አባባል፣ አረማመድ፣ አነጋገር ሁሉ ስለማውቅ እነሱኑ መስዬ እጫወት ነበር። ተደራሲያኑ ሴት የለም ብለው እንዳይመለሱ ሴት አለ ብለን እንዋሽና እኔ እሠራው ነበር። ብዙ ጊዜ እንደ ሴት ሆኜ ስሠራ ካዩኝ ተመልካከቾች መካከል ለትዳር የተመኙኝ ነበሩ።” 

 አባባ ተስፋዬ ሴት ገፀ ባሕርያትን ተላብሰው የተጫወቱት ለአራት ዓመታት ያህል ነው። ከአራት ዓመታት በኋላ ግን ‹ሰላማዊት ገ/ሥላሴ› የተባለች አርቲስት በመምጣቷ ወንድ ገፀ ባሕርይን ተላብሰው መተወኑን እንደቀጠሉበት ተናግረዋል።

የአባባ ተስፋዬ የቴአትር ሥራ በአገር ውስጥ ብቻ የተገደበ አልነበረም። ወደ ኮርያ ድረስ ሄደው ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን አርበኞችን በፉከራና በሽለላ ይቀሰቅሱ፣ ቴአትርም እየሠሩ ያዝናኑ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዛ በኮሪያ ቆይታቸውም የሃምሳ አለቅነትን ማዕረግ እንዳገኙ ዛሬም ድረስ የሚያነሱት አጋጣሚ ነው። 

በቴአትር ትወና ብቃታቸውና በሙዚቃ ችሎታቸው የወቅቱ ባለስልጣናት በእጅጉ ይገረሙ ነበርና ወደ ጃፓን ሄደው የጃፓንን ቴአትር ቤቶች እንዲመለከቱ ልከዋቸው ነበር። ከሦስት ወራት ቆይታ በኋላም ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ በሳቸው የህይወት ታሪክ ዙሪያ የተጻፉ ጽሑፎች ይናገራሉ። 

ብሔራዊ ቴአትር በ1948 ዓ.ም ሲከፈት በማዘጋጃ ቤት አብረዋቸው ይሠሩ ከነበሩ ተዋንያን ጋር ወደ ብሔራዊ ቴአትር ተሸጋግረዋል። “ፀጋዬ ኀይሉ” የተባሉ ጸሐፊ በጥር ወር 1979 ዓ.ም በታተመው የካቲት መጽሔት ላይ “አባባ ተስፋዬ በብሔራዊ ቴአትር ከተቀጠሩ ዕለት እስከ ጡረታ መውጫቸው ድረስ በተሠሩ ተውኔቶች በሁሉም ላይ ተካፍለዋል ማለት ይቻላል። በቴአትር ቤቱ አንድ ቴአትር ከተዘጋጀ በዚያ ቴአትር ውስጥ ተስፋዬ መኖራቸውን የሚጠራጠር ተመልካች አልነበረም” ሲሉ የአባባ ተስፋዬን የብሔራዊ ቴአትር የሥራ ዘመን ቆይታቸውን ገልፀውታል።

አባባ ተስፋዬ በብሔራዊ ቴአትር ቆይታቸው ከሰባ በላይ ቴአትሮች ላይ የተሳተፉ ከመሆናቸውም በላይ፣ “ብጥልህሳ? ነው ለካ?” እና “ጠላ ሻጭዋ” የተባሉ ተውኔቶችን ጽፈዋል።

“በቴአትር ቤት ቆይታዬ ለሰዎች የሚያስቸግር ቴአትርን እኔ ነበርኩ የምሠራው። የአሮጊት ጠጅ ሻጭ ሆኜ፣ ሌባ፣ ሰካራም ሆኜ እሠራ ነበር። አንድ ቴአትር ላይ አጫዋች፣ ባለሟል፣ ድንክ ሆኜ ሠርቻለሁ።”

በተዋጣ ተዋናይነቱ በሕዝብ ዘንድ የሚታወቀው አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ ስለ አባባ ተስፋዬ የትወና ብቃት ሲናገር፣ “ጋሽ ተስፋዬ ትራጀዲም ኮሜዲም መጫወት ይችላል። ኮሜዲ በሚጫወትበት ጊዜ ዋና ችሎታው የገፀ ባሕሪውን (የድርሰተ ሰቡን) ደም፣ ሥጋና አጥንት ወስዶ የራሱ ያደርገዋል። ይላበሰዋል። በዚህም የደራሲውን ሥራ አጉልቶ ያወጣዋል።” ብሎ ነበር፤

በእርግጥም አባባ ተስፋዬ “ሁሉንም አይነት የቴአትር ዘርፎች ስጫወት (ኮሜዲ፣ ትራጀዲ…) ይሳካልኝ ነበር” በማለት የወጋሁ ንጋቱን አስተያየት ያጠናክራሉ። ፍፁም የተሰጣቸውን ገፀ ባሕርይ ተላብሰው እንደሚጫወቱም ስለራሳቸው ይመሰክራሉ።

“‹ኦቴሎ›፣ ‹የከርሞ ሰው›፣ ‹አስቀያሚ ልጃገረድ› ግሩም ነበር። በተለይ ‹ኦቴሎ› ውስጥ ኢያጎን ሆኜ ስጫወት ብዙ ነገር ደርሶብኛል። ብዙ ሰዎች ጠልተውኝ ነበር። መኳንንቱ ሳይቀሩ ‹የታለ ያ ሰው ያስገደለ› እያሉ ያስፈልጉኝ ነበር። ባልና ሚስት በመኪና እኔን ለመውሰድ ተጠይፈውኝ ሁሉ ነበር። በመንገድ ሳልፍ ወይም አብቶብስ ስጠብቅ፣ ‹እዩት ይሄ እርጉም መጣ!› እያሉ ይሰድቡኛል፤ ይሸሹኝማል።”

አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ አባባ ተስፋዬን የሚያውቋቸው ከዛሬ ሀምሳ ዓመት በፊት ነው። ብዙ ቴአትሮች ላይም አብረው ተውነዋል። ስለአባባ ተስፋዬ የሚሉት ነገር አለ፤

“ተስፋዬ ሳህሉን ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ አውቀዋለሁ። ባለ ብዙ የሙያ ባለቤት ነው። ቢያንስ ቢያንስ ከሰባ በላይ የሚሆኑ ቴአትሮች ላይ ሠርቷል። ‹ስነ ስቅለት› ላይ ጲላጦስን ሆኖ ሲሠራ እንደ ተዓምር ነው የተቆጠረለት። ‹ዳዊትና ኦሪዮን› ላይም ተጫውቷል። ባላምባራስ አሸብር ገ/ሕይወት የጻፉት ‹የንግስት አዜብ ጉዞ ወደ ሰለሞን› የሚለው ቴአትር ላይ አሣ አጥማጅ ሆኖ ሠርቷል። ብሄራዊ ቴአትር ከመጡት ጀርመኖች ጋር እስክንለያይ ድረስ ‹ፊሸር› እያሉ ነበር የሚጠሩት። ‹ኦቴሎ› ላይ ኢያጎን ሆኖ ሲሠራ ብዙ ተመልካቾች፣ ‹ክፋቱንና ጭካኔውን በድምፁ ብቻ ሳይሆን በዓይኑም ጭምር ተናገረለት› ብለው የመሰከሩለት ነው። ፀጋዬ ገ/መድኅንም በጣም አድንቆታል።”

አባባ ተስፋዬ ከሚሠሯቸው ቴአትሮች በተጨማሪ በተለያዩ መድረኮችና በቴሌቪዥን በሚያቀርቧቸው የምትሃት (የማጂክ) ትርዒቶች ይታወቃሉ። ስለምትሃት ችሎታቸው የሚከተለውን ይላሉ፤

“ምትሃቱን ያሰለጠነኝ በጃንሆይ ፈቃድ አንድ እሥራኤላዊ ነው። ኮሪያም አይቼ ስለነበር ትንሽ ትንሽ እችል ነበር። ያንን ሳሳየው ደስ ብሎት አስተማረኝ። በጅምናስቲክ የሚሠሩትን በገመድ ላይ መሄድ፣ አክሮባት አሰለጠነን። ስመረቅ ጃንሆይ ሽልማት ሲሰጡኝ፣ ‹አስተምርበት እንጂ እንዳታታልልበት!› አሉኝ”

“ይሁን እንጂ በዚህ ጥበቤ ያተረፍኩት አድናቆትንና ከበሬታን ሳይሆን በሰዎች ዘንድ መጠላትን ነው” የሚሉት አባባ ተስፋዬ “ሰዉ እውቀት ስለማይመስለው አስማተኛው በማለት ይጠላኝ ነበር።” ሲሉ በሐሳብ ወደ ኋላ ሄደው ያስታውሳሉ።

ከቴአትር ሙያቸው በመለጠቅ አባባ ተስፋዬ በብዙሃኑ የሚታወቁት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን፣ በልጆች ፕሮግራም ላይ በሚያቀርቡት አስተማሪ፣ መካሪና አዝናኝ በሆኑት ተረቶቻቸው ነው። ለ42 ዓመታት በዚህ ፕሮግራም ላይ ያገለገሉት አባባ ተስፋዬ በፕሮግራሙም ብዙ ኢትዮጵያውያን ልጆችን እንዳሳደጉበት ይናገራሉ። ለመሆኑ ወደ እዚህስ ሙያ እንዴት ገቡ!? አባባ ተስፋዬ የሚሉት አላቸው፤

“በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋም ሁሉ ነገር ተዘጋጀ። ኮንትራቱን የያዘው አንድ እንግሊዛዊ ነበር። ያኔ የልጆች ፕሮግራም አልነበረምና ሄጄ ለሳሙኤል ፈረንጅ ነገርኳቸው። ‹አይ ያንተ ነገር!› አሉና እውነትም ኮንትራቱን ሲያዩት የለም። ፈረንጁን ሲጠይቁት ‹ሰው አላችሁ ወይ?› አለ። እኔ እንድሠራ ሳሙኤል ፈረንጁን ጠቆሙት። እስኪ ግባና አሳየኝ ሲል የነበረኝን አስቂኝ ማስክ ይዤ ወጥቼ ያን አጥልቄ አሳየሁት። ባሳየሁት ነገር ተገረመና፣ ‹አንተ እዚህ ምን ትሠራለህ?› አለኝ። ‹አገሬን ስለምወድ ውጪ ወጥቼ መቅረት አልፈልግም። የአገሬ ሰው መቼ ጠገበኝና እንዲህ ትለኛለህ?› አልኩት። ኅዳር 1 ቀን 1957 ዓ.ም ‹ጤና ይስጥልኝ ልጆች የዛሬ አበባዎች!› ብዬ በቴሌቪዥን ቀረብኩ።”

“ለልጅ ልዩ ፍቅር አለኝ። መንገድ ላይ እንኳ መክሬ ተቆጥቼ ነው የማልፈው።” የሚሉት አባባ ተስፋዬ ፕሮግራማቸውን ወላጆች ሳይቀሩ እንደሚወዱት ይናገራሉ።

“በየአጋጣሚው፣ ‹እኛ በእርስዎ ምክር አድገን፣ ልጆቻችንንም በእርስዎ ምክር አሳድገናል› የሚሉኝ ብዙ ናቸው። ልጅ በልጅነቱ ነው መመከር ያለበት ያሉኝ ነገር ከአእምሮዬ አይወጣም።”

አባባ ተስፋዬ ሥራቸው ያስገኘላቸው የሕዝብ ፍቅር እንጂ የገንዘብ ሀብት እንዳልሆነ ደጋግመው የሚናገሩት ነው፤

“ቴሌቪዥን ስገባ መጀመሪያ እንግሊዙ ጥሩ ገንዘብ ይከፍለኝ ነበረ (በወር 175 ብር ነበር የሚከፍለኝ)። በኋላ ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ‹ተስፋዬ አሄሄሄ ወፍ እንዳገሯ ነው የምትጮኸው፤ …እንደ ፈረንጅ አይደለም የምንከፍልህ፤ ሰባ ብር ይበቃሃል› አሉኝ። በፕሮግራም ስለሆነ ጥሩ ነበር። ያም በኋላ ደርግ ሲመጣ 50 ብር አደረጋት። እሱም ጥሩ ነበረ። ግን ሲሄድ ሃያ አምስት ብር አድርጓት ሄደ። አሁን ባሉትም ሃያ አምስት ብር ነው። ሃያ አምስት ብሯንም ቅር አላለኝም። እኔ ልጆች አእምሮ ውስጥ እንድገባ ነው የምፈልገው። ሕግ እንዲማሩ፣ ሲያድጉ እንዳያጠፉ፣ ጎበዝ ተማሪ እንዲሆኑ ነበር የምፈልገው፡ ተረቶቼ ስነ ምግባርን ነበር የሚያስተምሩት።”

አባባ ተስፋዬ ለረዥም ዓመታት በቴሌቭዥን ለልጆች ተረትን ከመተረታቸው በተጨማሪ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋፅዎ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በዛ ያሉ የምስክር ወረቀቶችና ሽልማቶችን ተቀብለዋል። ከነዚህ መካከል የኢትዮጵያ የኪነ ጥበባትና የመገናኛ ብዙኀን ሽልማት ድርጅት በቴአትር ዘርፍ በተዋናይነት የ1991 ዓ.ም የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ያደረጋቸው በዋናነት የሚጠቀስ ነው።

አባባ ተስፋዬ ከኪነ ጥበብ ሥራ ጋር በተያዘ  ግብፅ፣ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ሱዳን እና ሌሎችም አገሮች ደርሰው መጥተዋል።

“ከውጪ ስመጣ ሁሉ ጊዜ ለቅሶ ይይዘኛል።” የሚሉት አባባ ተስፋዬ ከኮርያ እስከ ጃፓንና ጀርመን ድረስ ሄደው ሲመለሱ በእጅጉ የሚያሳስባቸው ያገራቸው አለማደግ እንደሆነ ይናገራሉ፤

“መቼ ነው አገሬ አድጋ የማያት፣ ከሣር ቤት የምንወጣው መቼ ነው። እያልኩ እፀፀታለሁ። ቤቶቹ በቆርቆሮ ሲተኩ ደግሞ መቼ ነው መንገድ የሚሠራው ስርዓት የምንማረው መቼ ነው የሚለው ይቆጨኝ ነበር። በፊት አገሬ መንገድ ስለሌላት በጣም እናደድ ነበር። አሁን ግን እየተሠራ በመሆኑ ደስ እያለኝ ነው። ምነው የኔንም ቤት አፍርሰው መንገድ በሠሩ እላለሁ።”

አባባ ተስፋዬ ለሕፃናት የሚሆኑ አራት የተረት መጽሐፍትን ጽፈዋል። ከመድረክ ላይ የተቀዱ ሁለት ካሴት አላቸው። “ከብሔራዊ ቴአትር ጡረታ ከወጣሁ 24 ዓመት ሆኖኛል።” የሚሉት አባባ ተስፋዬ “አራት የተረት መጽሐፌን፣ ቲሸርቴንና ካሴቴን ትላልቅ ሱቅና ቡና ቤት መንገድ ላይ እያዞርኩ በመሸጥ ራሴን እደጉማለሁ” ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪ አባባ ተስፋዬ ከብሔራዊ ቴአትር በጡረታ  300 ብር ያገኛሉ።

“የወለድኳቸው ሁለት ልጆች ቢሆኑም አንዱ ልጄ ሞቷል።” በማለት የሚናገሩት አባባ ተስፋዬ ከቤተሰባቸው ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ይገልፃሉ። ከአምስት የልጃቸው ልጆችና አራት የእህታቸው የልጅ ልጆች ጋር እህታቸውን ጨምሮ 14 ቤተሰብ አብረው እንደሚኖሩም አያይዘው ገልፀዋል።

ባለቤታቸውም ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየታቸው በፊት በሥራቸው ላይ ያሳድሩት የነበረውን አዎንታዊ ተፅእኖ የሚገልፁት እንዲህ በማለት ነበር፤

 “ባለቤቴ ሥራዬን ትወድልኝ ነበር። በርታ ትለኝ ነበር። ስበሳጭ ስናደድ ለእርሷ ነበር የምነግራት። ‹ግዴለም ተስፋ ቻለውና አሳልፈው› ትለኝ ነበር። ከ 48 ዓመት የትዳር ህይወት በኋላ የዛሬ ሦስት ዓመት ሞታብኛለች።”

አንዱ ልጃቸው ትንሽ ሆኖ ቴአትር እንደሠራ የሚያስታውሱት አባባ ተስፋዬ ኮንጎ ይኖር የነበረው ትልቁ ልጃቸው ሙዚቃ መጫወት ይችል እንደነበር ገልፀዋል። የልጃቸው ልጅ ከአባቱ ጋር ሆኖ የሙዚቃ ክሊፕ ቤታቸው ውስጥ ባለው ስቱድዮ እየሠራ ሲሆን፣ እርሳቸውም በዋና ገፀ ባህርይነት የሚተውኑበት ፊልም ለመሥራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አቶ ተፈራ ተስፋዬ  ይባላሉ። የአባባ ተስፋዬ ሁለተኛ ልጅ ናቸው። “የአራት ዓመት ልጅ ካለሁበት ጊዜ አንስቶ እስከ 1970ዎቹ ድረስ አብሬ እየሄድኩ ቴአትር እመለከት ነበር።” የሚሉት አቶ ተፈራ፣ “ቤት ውስጥ ሲለማመድ አይ ነበር። ግን ምንም አልረዳውም ነበር። ትምህርቴ ላይ ነበር የማተኩረው። ሌላው ዘመኑ ነው መሰለኝ በጣም ስለምናከብረው አንቀራረብም። ግን ምግብ እየተበላ ዝም ብለን እየተጫወትን ድንገት ትዝ ሲለው ጮኾ ያጠናውን ቴአትር ይወጣው ነበር። ብዙ የሚያስቸግረው የፀጋዬ ገ/መድኅን  ቴአትር ነው። ቃላቱ ከበድ ከበድ ያሉ ስለነበሩ እየበላም ሲለማመድ አየው ነበር።”

አቶ ተፈራ የስድስት ዓመት ልጅ እያሉ ቴዎድሮስ ቴአትር ላይ ምኒሊክን ሆነው የተጫወቱ ሲሆን ቴአትሩ ላይ አባታቸው አባባ ተስፋዬ ራስ መኮንን ሆነው እንደሠሩ ተናግረዋል። አጫጭር የቴሌቭዥን ድራማዎች ላይም መተወናቸውንም አያይዘው ገልፀዋል።

ወ/ሮ ወይንሸት ተሾመ የአባባ ተስፋዬ ልጅ ባለቤት ስትሆን እሷም ስለ አባባ ተስፋዬ የምትለው አላት፤

‹አባባ ተስፋዬ የኛ ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብም አባት ናቸው። ልጃቸውን በማግባቴ ለ 19 ዓመታት ያህል አውቃቸዋለሁ። ለ 15 ዓመታት ደግሞ አብረን ኖረናል። ጥሩ አባት ናቸው። ከውጪ ሲመጡ የቤተሰቡ አባል ጎድሎ ማየት አይፈልጉም። ገና ሲገቡ ምሳ በልታችኋል ወይ ይላሉ። ሌላ ቦታ ከተጋበዙ ደውለው ይናገራሉ። ዘመዶቻቸውን ሰብስበው ይይዛሉ።”

ዛሬ አባባ ተስፋዬ 84 ዓመታቸው ነው። ለ 42 ዓመታት ካገለገሉበት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከሥራ እንዲወጡ ተደርገዋል። ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የወጡበትን ምክንያት አባባ ተስፋዬ እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ፤

“ልጆች ይቀርባሉ በዝግጅቱ ላይ። ልጆች እያዘጋጁ አነጋግራቸው ይላሉ ብዙ ጊዜ ቴቪዥኖች። እና ሕፃናቶች ተሰብስበው መጥተው ነበረ - እኔ ጋር። እና ሁል ጊዜ የማደርገው ነው፤ አንድ ትንሽ ህፃን ልጅ ተረት ሲያወራ ‹አንድ ጋና ና ፈረንጅ ነበረ…› ብሎ ጀመረ። እንግዲህ እያዳመጥኩት ነበርና እኔ ምን ምን አልኩት፤ የሕፃን አነጋገር በመጠቀም ‹አንድ ጋያና ፌየንጅ ነበረ። እና እሹ› እያለ ያወራል። እኔ እንግዲህ ጋና እና ፈረንጅ የሚለው ነው አእምሮዬ ውስጥ የመጣው። እንዲህ ዓይነት የእንግሊዞች ተረት አለ። አፍሪካ ሲገቡ አንግሊዞች ለአሽከራቸው በዚህ ሰዓት አብራ፣ በዚህ ሰዓት ደግሞ እንዲህ አድርግ የሚል በመጽሐፍ ላይ የተጻፈ አለ። እና እሱ መሰለኝ። እኔ በፍፁም አላወቅሁም። ይሄንንም ለሥራዬ ሣምንት ስመጣ፣ ‹ሥራ የለህም እኮ ትተሃል› ብላ አንዲት ተላላኪ ልጅ ወረቀት ሰጠችኝ። እኔም ተመልሼ አልሄድኩም። ቀረሁ ቀረሁ… ወዲያው ደግሞ በሬዲዮን፣ ‹በስህተት የተላለፈ ቃል ነው› የሚል ነው መሰለኝ ያስተላለፉት። .. ድሮም ቃላት ይሰነጠቁ ነበር።” 

እዚህ ላይ የጽሑፋችንን መዝጊያ የምናደርገው በሚከተለው አጭር ጽሑፍ ነው፤ “…ልብ በሉ! 40 ዓመታት! በእንደዚህ ዓይነት ኪነ ጥበብ ውስጥ ለረዥም ዘመናት ከቆየ ሰው የሚገኘው ልምድ፣ ዕውቀት፣ ትዝታ፣…በምን ሊለካ ይችላል!? …ትራጀዲ፣ ኮሜዲ፣ “ፋርስ”፣…የሰጧቸውን በትክክል የሚጫወቱ ከዚህ በተጨማሪ ሙዚቀኛ፣ ምትሐተኛ (ማጂሺያን)፣ ዘፋኝ፣ የሕፃናት አስተማሪ፣ የውዝዋዜ አሠልጣኝና አስተዋዋቂም ጭምር ናቸው። ይገርማል! አንድ ሰው እንዴት የአምስት ኪነ ጥበብ ዘርፎች ባለ ሙያ ሊሆን ይችላል!?”

አባባ ተስፋዬ ከአማርኛ ቋንቋ ውጪ የኦሮምኛ፣ የወላይትኛ፣ የጣሊያንኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ችሎታ አላቸው።

 

ማስታወሻ

ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ሐምሌ 22 ቀን 2009 ዓ.ም ለ34ኛ ጊዜ ተማሪዎችን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ባስመረቀበት ሥነሥርዓት ላይ አርቲስት ተስፋዬ ሣህሉ (አባባ ተስፋዬ) በአርአያነታቸው ተመርጠው ከክቡር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ እጅ በተወካያቸው በኩል የዕውቅና ሽልማት አግኝተዋል። ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ.ም በተወለዱ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በአባባ ተስፋዬ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻል።

 

በጥበቡ በለጠ

የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበርካታ ኪነጥበባዊ ሀብት  ባለቤት ነች። ስለ ቋንቋ ብናወራ ከዚህችው ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ውስጥ የፈለቁ ቅኔዎችን፣ ሰዋስዎችን፣ አንድምታዎችን ወዘተ እናገኛለን። ታሪክን ብንጠይ፣ ተዝቆ የማያልቅ የኢትዮጵያውያን ታሪክ ከኖህ ዘመን እስከ እኛው ድረስ ትተርክልናለች። የመንግስት አስተዳደርና ስርአትን ስንጠይቃት ከፍትህ ዶሴዋ፣ “ፍትሀ ነገስት ወፍትሕ መንፈሳዊ” የተሰኘውን የአስተዳደርና የዳኝነት መፅሐፏን ታቀርብልናለች። ስለ ነገስታት ስንጠይቃት “ታሪከ ነገስታትን” ታስነብበናለች። ቤተክርስቲያኒቱ ኢትዮጵያን የተመለከቱ ጉዳዮች በተነሱ ቁጥር የመመለስ ብቃት እንዳላት የብዙ ጥናትና ምርምር ውጤቶች ያሳያሉ። በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ የአስተዳደርና የፖለቲካ ስርአት ውስጥ እስከ አፄ ኃይለስላሴ መንግስት ድረስ ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበረች። ደርግ ሲመጣ ለብዙ ዘመን የነበረችበትን የሀገር አስተዳደር ተሳትፎዋን ወሰደባት። አንዳንዶች ያንን ዘመን ሲገልፁት፣ “ቤተ ክርስቲያኒቱ ፀጋዋን የተጠቀመችበት ወቅት ነው፤” ይሉታል።

በ1995 ዓ.ም አለቃ አያሌው ታምሩን ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር። እንደሚታወቀው አለቃ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ “ሊቀ ሊቃውንት” አንዱ ነበሩ፡፡ የሊቆች ሊቅ ማለት ነው። በወቅቱ አለቃ የጋዜጦች ሁሉ የፊት ገፅ ዜና ነበሩ። እኔም በጥያቄዎቼ መሀል ያቀረብኩላቸው “እርስዎ የመንግስት አሰራርን እና አካሄድን ሁሉ ይተቻሉ፤ በሕግ ደግሞ የተደነገገው መንግስት በሀይማኖት ውስጥ፣ ሀይማኖት በመንግስት ውስጥ ጣልቃ አይገቡም የሚል ነው” አልኳቸው።

አለቃ በአባባሌ ተቆጡ። ማን ባቆመልህ ምድር ላይ ሆነህ ነው ሃይማኖቷ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ አያገባትም የምትለው!? ይኸችው ቤተክርስቲያን አይደለችም እንዴ ከባእዳን ወራሪዎች ኢትዮዽያን የተከለከለችው ቤተክርስቲያን ናት’ኮ ህዝቦችን እያስተባበረች፣ እየመከረች፣ እየገሰፀች ሀገራቸውን በነፃነትና በአንድነት እንዲጠብቁ ያደረገች ይህችው ቤተክርስቲያ ናት’ኮ። ካህናቶቿን እና ሊቃውንቶቿን፣ ታቦቷን ሳይቀር በየጦር አውድማው እያሰለፈች ኢትዮጵያን የጠበቀች የቤተክርስቲያን አይደለችም?! ካህናት ያለቁት ኢትዮጵያዊያን ከባእዳን ወረራ እየጠበቁ ነው! ትምህርትስ ቢሆን ይህችው ቤተ ክርስቲያን አይደለችም እንዴ ያስተማረችና ለወግ ማእረግ ነገስታቶችን ያቀረበችው?! ኢትዮጵያ በቅኝ ገዢዎች መዳፍ ስር እንዳትወድቅ አድዋ ላይም ሆነ በሌሎች አውደ ግንባሮች ላይ ከሰራዊቱ ፊትና ኋላ በመሰለፍ በፀሎትና በምህላም በሱባዔም ፈጣሪዋን እየተማፀነች ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቆም በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅዎ ያደረገችው ቤተ ክርስቲያኒቱ ናት! እና በምን ምክንያት ነው አሁን በኢትዮጵያ አስተዳደር ውስጥ አያገባትም የምትለው?! እያሉ አፋጠጡኝ።

የአለቃ አያሌውን አባባል፣ አገላለፅ ለብዙ ጊዜ አስበው ነበር። በውስጡ ብዙ እውነታዎች አሉት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን በሀገሪቱ የመንግስት ስርዓት ውስጥ ትልቅ ሚና ነበራት። ቤተ ክርስትያኒቱ ቀብታ ያልሾመችው ንጉስ ተቀባይነት የለውም። ከዚህም በተጨማሪ በአያሌ የአስተዳደር ውሣኔዎች ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበራት። ይሄ ሁሉ ፀጋዋ የተነጠቀው ዘመነ ደርግ ሲመጣ ነው። ከአፄ ኃይለስላሴ ጋር አዲዮስ ሃይማኖት ተብሎ ለብቻዋ ተቀመጠች።

ቤተ ክርስትያኒቱ በሀገር አስተዳደር ውስጥ የነበራትን ሚና እንዴት ተነጠቀች? ደርግ ለምን ከለከላት? ምን ጥፋት ሰራች? ሀገርን የጐዳችበት የታሪክ አጋጣሚ አለ? ጥቅሟና ጉዳቷስ ታይቷል? ቤተ ክርስትያኒቱ ይህን የአስተዳደር ፀጋዋን ስትነጠቅ ልክ አይደለም ብሎ የተከራከረላት አለ? ወይስ ቤተ ክርስትያኒቱ ራሷ በደርግ ውሳኔ አምናለች? እነዚህ አንኳር ጥያቄዎች በወቅቱም ሆነ ከዚያ በኋላ እንደ መብት የተጠየቁ አይመስለኝም።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ከመንግስት አስተዳደር ውስጥ እጇን እንድታነሳ የተደረገ ጉልህ ትግል አልነበረም። ቢኖርም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ግራኝ አህመድ ከቱርኮች ጋር በማበር በክርስትያናዊው መንግስት ላይ ያወጀውና ያነሳው ጦርነት ነው። ከ1515-1531 ዓ.ም በነበረው የግራኝ አህመድ ጦርነት ለ15 ዓመታት ኢትዮጵያ ስትፈርስ፣ ስትወድም ቆይታለች። በታሪኳ ከፍተኛ አደጋ ያየችበት ወቅት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም በጐንደር የስልጣኔ ዘመን በአፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግስት ከ1595 ዓ.ም እስከ 1626 ዓ.ም ባለው ዘመንም ቤተ-ክርስትያኒቱ ፈተና ውስጥ ነበረች። ፖርቹጊዞች እና ስፓንያርዶች ባመጡት ሃይማኖት ምክንያት ኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን መመሪያዋ እንደማታደርግ በአዋጅ ተነገረ። ግጭት ተነሳ። ህዝቡ እርስ በርሱ ተላለቀ። በሱስንዮስ አደባባይ ከስምንት ሺ በላይ ምዕመን ሞቷል። ከዚያ በኋላ ነው አፄ ፋሲል ወደ መንበረ ስልጣኑ ሲመጡ መንግስት የተረጋጋውና ሃይማኖቷም የቀድሞ ቦታዋን ያገኘችው። ወደ ኋላ ከሄድንም በዮዲት ጉዲት ዘመን ከ842-882 ዓ.ም ለ40 ዓመታት ይሁዲነትን ለማስፋፋት ባደረገችው ጥረት በርካታ አብያተ-ክርስትያናትና ቅርሶች ከመውደማቸውም በላይ የቤተ-ክርስትያኒቱ ህልውና አስጊ ሆኖ ነበር።

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የታሪክ አጋጣሚዎች ዋናዎቹ የቤተ-ክርስትያኒቱ የፈተና ወቅቶች ነበሩ። እነዚህን በፅናትና በመስዋዕትነት አልፋቸዋለች። ማለፍ ያልቻለችው የደርግ ስርዓትን ነበር። ደከማት መሰለኝ ደርግ ሲቀማት ዝም አለች። ወይም ደግሞ ተስማምታለች ማለት ነው። አልያም የዘመኑ አስተሳሰብና ፍልስፍና አይሎ የአዲሱ ትውልድ ጥያቄ በመሆኑ ቤተ-ክርስትያኒቱ በፀባይ ቦታዋን ለቃለች ማለት ይቻላል።

አዲሱ ትውልድ የኮሚኒስት አስተሳሰብና ፍልስፍና ቅኝት ነው። ያ ደግሞ ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት የለውም። የሃይማኖትን እሳቤዎች ፍርስርሳቸውን የሚያወጣ ነው። ገና ከጅምሩ ፈጣሪ የሚባል የለም በማለት ይጀምራል። ስለዚህ እነ መላእክት፣ እነ ቅዱሳን፣ እነ ሰማዕታት ወዘተ የሚባሉ የሃይማኖቷ መገለጫዎች በዚህ ኰሚኒስታዊ አስተሳሰብ ውስጥ ቦታ የላቸውም። እናም ኮሚኒዝምና ሶሻሊዝም የኢትዮጵያ የፍልስፍና እንዲሁም የአስተዳደር መርሆዎች ሆኑ። የማርክስ፣ የኤንግልስ እና የሌኒን ፍልስፍናዎች ከቤተ-ክርስትያኒቱ በላይ ለደርግ አስተዳደር የቀረቡ ሆኑ። ታዲያ ቤተ-ክርስትያን ምን ትሰራለች!? ከሃይማኖት ይልቅ እነ ማርክስ በጣሙን ተሰበኩ። መድረኩን ከሃይማኖቷ የተረከቡ ሆኑ።

ኢህአዴግ ደርግን ተዋግቶ ሲጥል የሚሰጠው ምክንያት ደርግ አረመኔ፣ አፋኝ፣ ገዳይ በመሆኑ እንዲሁም የዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስለሚያደርግ ነው ይላል። ለመሆኑ ደርግስ ቤተ-ክርስትያኒቱን ከሀገር አስተዳደር ሚና ውስጥ ሊያስወጣት ምን ብሎ ይሆን? እርግጥ ነው በ1960ዎቹ ውስጥ የተቀነቀነው የለውጥ አብዮት ተማረ የሚባለውን ትውልድ የልዩ ልዩ ሀገሮች ፍልስፍናዎች ማርኰት ወስዶታል። ትውልድ ከሃይማኖት አፈንግጦ ሌላ ፍልስፍና አቀንቃኝ ሆኖ የታየበት ወቅት ነበር። በአንፃሩ ከሃይማኖት ሚና እና ፍልስፍና ይልቅ ሌሎች የተደመጡበት ወቅት ነበር ማለት ይቻላል። ፈሪሃ እግዚአብሔር የሚባል ነገር የለም። ፈሪሃ ማርክስ፣ ፈሪሃ ኤንግልስ፣ ፈሪሃ ሌኒን የሚባሉ እምነቶች ከፈሪሃ መንግስቱ ኃይለማርያም ጋር ሆነው 17 ዓመታት ቆይተዋል።

ኢህአዴግ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ላይ መጣ። ወዲያው አቡነ መርቆርዮስ ከሀገር ወጡ። የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ፓትርያርክ ነበሩ በዘመነ ደርግ። ምነው ቢባሉ ለደህንነቴ በመስጋት ነው አሉ። አንድ የሃይማኖት መሪ፣ የራሱን ደህንነት ለመጠበቅ ሃይማኖቱንና ህዝቡን ጥሎ ይሄዳል? የፈለገ የደህንነት ስጋት ቢኖርስ? ለእግዚአብሔር ማደር? ስጋትን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ሰጥቶ የመጣውን ሁሉ በፅናት መቀበልስ እንዴት አልቻሉም? በአቡነ መርቆርዮስ ላይ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ። ሀገርን እና ሕዝብን ጥሎ በመሄድ የመጀመሪያው ፓትሪያርክ ናቸው።

አቡነ ጳውሎስ በዚህ ክፍተት ውስጥ የመጡ የቤተ-ክርስትያኒቱ መሪ ነበሩ። በእርሳቸው ዘመን ደግሞ ቤተ-ክርስትያኒቱ ከውጪያዊ ጫና በላይ በውስጣዊ ችግሮች ተተብትባ ቆይታለች። የጳጳሳት ፀብ፣ የቀሳውስት አቤቱታ፣ የምዕመናን አያሌ ጥያቄዎች፣ የገንዘብ እና የውስጥ አስተደደሮች በማኅበረ ቅዱሳኖች ላይ የሚደረገው ጫና ወዘተ በጉልህ የታዩ ችግሮች ነበሩ። በኢህአዴግ ዘመን ቤተ-ክርሰትያኒቱ ከመንግስት ጋር ሆና አያሌ ተግባራትን ስታከናውን ነበር። ይህም ሃይማኖትና መንግስት በውስጥ ስራቸው ጣልቃ አይገባቡም የሚለው ሀሳብ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።

አንዳንድ ሰዎች ቤተ-ክርስትያኒቱ ከ40 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ይዛ እንዴት በፓርላማ ውስጥ እንኳን አትወከልም ይላሉ። እርግጥ ነው በሀገሪቱ ውስጥ በሃይማኖት ስም በፖለቲካ መደራጀት አይቻልም። ይሁን እንጂ በፓርላማ ውስጥ የድምፅ ውክልና ቢኖር በልዩ ልዩ የፓርላማው ውሳኔዎች ላይ ድምጿ ይሰማ ነበር የሚሉ አሉ። ኦርቶዶክስ የአርባ ሚሊዮን ሕዝቧን ድምፅ ለማሰማት ጥያቄ መጠየቅ አለባት የሚሉም አሉ።

በነገራችን ላይ በፓርላማ ውስጥ የአካባቢ ጥበቃ ወንበር፣ የቤተ-እምነቶች ወንበር፣ የሴት መብት ተከራካሪ ቡድኖች ወንበር፣ የአካል ጉዳተኞችና ድኩማን የውክልና ወንበር ወዘተ ቢኖር ከየአቅጣጫው ድምጾች ይሰማሉ የሚል እምነት አለ። እነዚህ ድምጾች እንደማንኛውም የፓርላማ አባል ተወዳድረው አሸንፈው የሚመጡ ሳይሆን መንግስት በራሱ ፍላጐት የሚደለድላቸው ነው። ፓርላማው ውሣኔ ሲያሳልፍም ድምፃቸው ይቆጠራል። ሀገራችን ወደፊት ይህን አሰራር ከተገበረችው የተሻለ የድምፅ ውክልና ይኖራል ተብሎ ይታመናል።

ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳያችን ስንመለስ፣ ይኸችው ቤተ-ክርስትያን የመነጋገሪያ አጀንዳችን ናት። በሀገር አስተዳደር እና ጥበቃ ላይ ሰፊ ድርሻ የነበራት ቤተ-ክርስትያን፣ አሁን ላይ ሆነን ስናያት ያንን ብቃቷን መተግበር ትችላለች? አሁን ያሉት የሃይማኖት አባቶች ምን ያህል ራሳቸውን ከዘመናዊው አስተሳሰብ ጋር እያገናኙት የሃይማኖቱን አስተምህሮና ፍልስፍና ለትውልድ ያስጨብጣሉ? የሚለው ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል። ለምሳሌ የሊቀ ጳጳሳት ሹመት በራሱ የእድሜ ጣሪያ የለውም? እንደ ልብ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የሚያስተምሩ፣ አንደበታቸው የሰላ፣ ሌላውን ማሳመን፣ ማስተማር፣ መገሰፅ፣ ማስታረቅ ወዘተ የሚችሉ ከአንደበታቸው ማር ይፈሳል የሚባሉ ሊቀ-ጳጳሳትን ማዘጋጀት (ማብቃት) አይቻልም ወይ?

የቤተ-ክርስትያኒቱ አስተምህሮት እየቀነሰ ሲመጣ፣ ድምጿ አልሰማ ሲል እንደ ኰሚኒዝም፣ ሶሻሊዝም ያለ አዳዲስ መጤ አስተሳሰቦች በአንድ ግዜ ገነው ይወጣሉ። ነገ ምንአይነት ፍልስፍናና አስተሳሰብ እንደሚመጣ አናውቅም። ግን ሃይማኖቷ የአያሌ ታሪኰች እና የአስተሳሰቦች ማዕከል በመሆኗ፣ የቋንቋና የሥነ-ጽሁፍ እጅግ በርካታ ስራዎች ባለቤት በመሆኗ፣ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት  በመሆኗ፣ ከ40 ሚሊየን ህዝብ በላይ ተከታይ ያላት በመሆኗ ወዘተ ለኢትዮጵያ እድገትና ትንሳኤ ብዙ ነገር ማበርከት ትችላለች። ጥያቄው ግን እንዴት? የሚል ሲሆን፣ ማንስ ይመልሰው?

 

በሳምሶን ደሣለኝ

ኤሁድ ኦልመርት የቀድሞ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። ኦልመርት የእስራኤል አስራ ሁለተኛ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2009 እንዲሁም ከ1993 እስከ 2003 የእየሩሳሌም ከንቲባ በመሆን አገልግለዋል። የህግ ባለሙያ እና ፖለቲከኛም ናቸው።

 

ኦልመርት በስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ የእስራኤል እና የፍልስጤም የሰላም ድርድርን ማዕቀፍ፤ ከጦረኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ወደ ሰላማዊ የድርድር መድረክ መቀየር መቻላቸው በስፋት ይነገርላቸዋል። ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ጉቦ በመቀበል እና የሕግ ምርመራን አስተጓጉለዋል ተብለው በቀረበባቸው ክስ መነሻ፣ ጥፋተኛ ተብለው ወደ ማረሚያ ቤት ወርደዋል። የጥፋተኝነት ውሳኔው የተደመጠው በ28 ቀን አፕሪል 2014 ነበር።  በሜይ 13 ቀን 2014፣ የስድስት ዓመት እስራት እና 290ሺ የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል።

 

 

ኦልማርት በ1980ዎቹ ነበር፤ በሙስና የተጠረጠሩት። ለበርካታ ጊዜያት በሙስና ተወንጅለው በፖሊስ ምርመራ ተደርጓባቸዋል። እንደ እስራኤሉ ጋዜጠኛ ዮሲ ሜልማን አገላለፅ፤ በኦልመርት ላይ በተደረጉ ተደጋጋሚ ምርመራዎች፤ የተወሰኑ ሰዎች ሙሰኛ እንደነበሩ እንዲያምኑ አድርጓል። ነገር ግን ያለፉባቸውን ዱካዎቹን በመከለል ማስተር አድርጓል ይሏቸዋል። ሌሎቹ ደግሞ ባለስልጣናት ኦልመርትን፤ የመጎንተል ራሮት አለባቸው ብለው ያምናሉ።

 

 

በ2004 ኦልመርት በእየሩሳሌም በሽያጭ እና በሊዝ ፈጽመዋል በተባለ ውንጀላ  ምርመራ ተደርጎባቸዋል። ውንጀላው ከገንዘብ ጋር በተገናኘ ሲሆን፤ ኦልመርት በገንዘብ እንዲጠቀሙ ተደርጓል የሚል ነው። ለሕገወጥ የምርጫ ቅስቀሳ ወይም ጉቦ ተደርጎ የተወሰደ መሆኑን ያትታሉ። ይህም ሲባል ከገበያ ዋጋ በታች 325ሺ የአሜሪካ ዶላር እንዲከፈል አድርገዋል። የዚህ ውንጀላ ምርመራው በይፋ የተጀመረው በሴቴምበር 24 ቀን 2007 ነበር። ሆኖም በቂ መረጃ ባለመገኘቱ በኦገስት 2009 የምርመራ ፋይላቸው እንዲዘጋ ተደርጓል።

 

ሌላው በጃንዋሪ 16 ቀን 2007 በኦልመርት ላይ አዲስ የወንጀል ምርመራ ተደርጓል። ምርመራው የተጠናከረው ኦልመርት የፋይናንስ ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ ፈጽመውታል በተባለ ሙስና ነው። የተወነጀሉት ባንክ ሌውሚ ለመሸጥ በወጣው ጨረታ፣ የጨረታ ሒደቱን በማወክ ለአውስትራሊያው የሪል እስቴት ለባሮን ፍራንክ ሎዊ ለመጥቀም በመንቀሳቀሳቸው ነበር። ፈፅመውታል በተባለው ድርጊታቸው ላይ የእስራኤል ፋይናንስ ሚኒስቴር አካውንታንት በዋና ምስክርነት፤ ቀርቧል። በሰጠው ምስክርነትም፤ ኦልመርትን ወንጅሏቸዋል። በመጨረሻ ግን የእስራኤል የምርመራ ፖሊሲ፤ የተሰበሰቡት መረጃዎች ክስ ለመመስረት በቂ አይደሉም በማለት ምርመራው እንዲቋረጥ አድርገዋል ብሏል። በኦክቶበር 2007 ኦልመርት፤ ለአምስት ሰዓታት በብሔራዊ ወንጀል ምርመራ ቡድን፣ በእየሰሩሳሌም በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የምርመራ ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል። ሆኖም በዲሴምበር 2008 የመንግሰት አቃቤ ሕግ ሞሼ ላዶር፤ በቂ መረጃ ባለመኖሩ የምርመራ መዝገቡን እንዲዘጋ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

 

በኦፕሪል 2007 ተጨማሪ ውንጀላ በኦልመርት ላይ ቀርቧል። ይኸውም፣ የንግድ ኢንዱስትሪ እና የሠራተኛ ሚኒስትር ሆነው፤ የወንጀለኛ ባሕሪ በኢንቨስትመንት ማዕከል ውስጥ አሳይተዋል ብለዋል። አቃቤ ሕጎቹ፤ ኦልመርት በወንድማቸው እና በቀድሞ የንግድ ሸሪካቸው በተወከለ የንግድ ድርጅት ቢዝነስ ጉዳይ ውስጥ የጥቅም ግጭት ውስጥ ገብተው፣ በግል ጉዳዩን ለመመልከት ተንቀሳቅሰዋል። እንዲሁም ኦልመርት፤ በረዳት ሚኒስትሮቻቸው የተወሰኑ ውሳኔዎችን ለወንድማቸው ድርጅት በከፊል እንዲጠቅም አድርገው ውሳኔዎችን በመለወጣቸው ተወንጅላዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በጁላይ 2007 ፓርላማ ፊት ቀርበው የተነሳባቸውን ውንጀላ ሙሉ ለሙሉ ክደዋል።

 

 

በጁላይ 2008 ሃሬተዝ እንደፃፈው፣ በ1992 ኦልመርት ከአንድ አሜሪካዊ ባለሃብት ከጆይ አልማሊያሃ ብድር ወስደው ተመላሽ ክፍያ አለመፈጸማቸውን አጋልጧል። ኦልመርትም፣ በተደረገባቸው ምርመራ ብድር መውሰዳቸውን አምነዋል። በ2004 ኦልመርት 75ሺ የአሜሪካ ዶላር መውሰዳቸውን አስታውቀው፤ ልማሊያሀ የሰጣቸውን ብድር እንድከፍለው አልጠየቀኝም ብለዋል። በተጨማሪም፣ 100ሺ ዶላር ገንዘብ መቀበላቸውን እና በግል የሒሳብ ቋታቸው ውስጥ እንዳስገቡት አቃቤ ሕግ ተናግሮ፤ ኦልመርት ብድራቸውን ስለመክፈላቸው እንደማያውቅ ተናግሯል።

 

 

በሜይ 2008 ኦልመርት በአዲስ የጉቦ ቅሌት ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ በወቅቱ ለሕዝብ ይፋ ተደርጓል። ኦልመርት በበኩላቸው፣ ከጁዊሽ አሜሪካዊ ባለሃብት ሞሪስ ታላነሰኪ ለኢየሩሳሌም ከንቲባነት ለመወዳደር ለምርጫ ቅስቀሳ የሚሆን ገንዘብ መቀበላቸውን አምነዋል። ውንጀላው ግን ለአንድ ጊዜ ሳይሆን ለአስራ አምስት አመታት ከባለሃብቱ ገንዘብ ተቀብለዋል የሚል ነበር የቀረበባቸው። በዚህ ፈፅመውታል በተባለው ተግባራቸው ከሥልጣን እንዲለቁ ግፊት ቢደረግባቸውም አሻፈረኝ በማለት፣ አልመርት ጥያቄውን ውድቅ አድርገውታል። ኦልመርትም እንዲህ ብለው ነበር፤ "I never took bribes, I never took a penny for myself. I was elected by you, citizens of Israel, to be the Prime Minister and I don't intend to shirk this responsibility. If Attorney General Meni Mazuz, decides to file an indictment, I will resign from my position, even though the law does not oblige me to do so."

 

 

እሳቸው እንደዚህ ይበሉ እንጂ፣ ታላንስኪ ሜይ 27 ቀን በፍርድ ቤት ቀርቦ ምስክርነት ሰጥቷል። ይኸውም፣ ከአስራ አምሰት አመታት በላይ ለኦልመርት ከ150ሺ ዶላር የበለጠ ለፖለቲካ ምርጫ ዘመቻ የሚውል በፖስታ አድርጎ መስጠቱን አረጋግጧል። ይህንን ተከትሎ ሴፕቴምበር 6 ቀን 2008 የእስራኤል ፖሊስ በኦልመርት ላይ የወንጀል ክስ እንዲመሰረትባቸው ምክር ሃሳብ አቀረበ። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በፖሊስ ሪፖርት መነሻ፣ በ600ሺ ዶላር ክስ መሰረተባቸው። ከ600ሺ ዶላር ውስጥ 350ሺው በቅርብ ጓደኛቸው ዩሪ ሜሰር ቋት ውስጥ እንደሚገኝ ተያይዞ ይፋ ሆነ። እንዲሁም በ2010 ብሔራዊ የሙስና ምርመራ ዩኒት፣ ኦልመርት ከሆሊላንድ ሪልእስቴት ጋር በተያያዘ ያለውን ጥርጣሬ በይፋ አሳወቀ። ይኸውም፣ ሪል ስቴቱን ፕሮሞት ለማድረግ ጉቦ መቀበላቸው ይፋ አደረገ።

 

 

አጠቃላይ ከላይ የሰፈሩት የኦልመርት ክሶች የመዝገብ ፋይል ተከፈተላቸው። እነሱም፣ "Rishon Tours", "Talansky" (also known as the "money envelopes" affair), and the "Investment Center" በሚል የመዝገብ ስያሜ የመንግስት ዐቃቤ ሕጐች ወደ ክርክር ውስጥ ገቡ። በጊዜው አስገራሚ የነበረው ጉዳይ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ይህንን አይነት የክስ መዝገብ የተከፈተባቸው የመጀመሪያው ሰው፤ ኤሁድ ኦልመርት ናቸው። የፍርድ ሒደቱ ለአምስት አመታት ከተሰማ በኋላ፤ የእየሩስአሌም ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ጊዜ ሆሊላንድ ከሚባለው ሪል እስቴት 160ሺ የአሜሪካ ዶላር መቀበላቸው በመረጋገጡ ለስድስት አመት በእስር እንዲቆዩ ተበይኖባቸው ወደ ማረሚያ ቤት ተወስደዋል። ከስድስት የሚበልጡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጓደኞች እና ባለሃብቶች ተያይዘው ዘብጢያ ወርደዋል። እንዲሁም በ"Talansky" ጉዳይ ተጨማሪ የስምንት ወር እስር ተፈርዶባቸዋል።

 

 

በዚህ የኦልመርት የፍርድ ሒደት፣ የኦልመርት ከፍተኛ ረዳት የነበሩት ወ/ሮ ሹላ ዛከን በሰጡት ምስክርነት፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሁድ ኦልመርት በሙስና የተገኘ ገንዘብ መቀበላቸውን እና እሳቸውም ከተሞሰነው ገንዘብ የድርሻቸውን መውሰዳቸውን አምነው ለፍርድ ቤቱ አጋልጠዋል። ወ/ሮ ይህንን የጀግና ምስክርነት በማቅረባቸው የእስር ጊዜያቸው እና የገንዘብ ቅጣት ተቀንሶሏቸዋል። 

 

 

የኦልመርትን ጉዳይ የያዙት ዳኛ ዴቪድ ሮዜን የፍርድ ውሳኔውን ሲያስተላልፉ የተናገሩት፣ “የሕዝብ አገልጋይ ሆኖ፣ ጉቦ የሚቀበል ወንጀል ከፈጸሙ ከከዳተኞች ጋር ተመሳሳይ ነው” ነበር ያሉት።

 

 

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሁድ ኦልመርት ከሃያ ሰባት ወራት እስር በኋላ፣ የእስራኤል የምህርት ሰጪ ቦርድ ባስተላለፈው ውሳኔ ከማረሚያ ቤት ተለቀዋል።

 

 

ከላይ ስለ ኤሁድ ኦልመርት የክስ ሂደት የሚተርከውን ጽሁፍ ያቀረብነው ያለምክንያት አይደለም። በ80ዎቹ የጀመረው ጥርጣሬ ወንጀል ክስ ፍርድ የሚሰጠን መሠረታዊ ትምህርት በመኖሩ ነው። ከላይ እንደሰፈረው በኤሁድ ኦልመርት ላይ ከ80ዎቹ ጀምሮ የሙስና ጥርጣሬ እና ውንጀላ መኖሩን ያሳያል። በወቅቱ የቀረበው ጥርጣሬ እና ውንጀላ ከረጅም አመታት መረጃ እና ማስረጃ አታካች ፍለጋና ምርመራ በኋላ ፍፃሜውን ያገኘው በ2006 መሆኑን ከግምት ከወሰድን፤ የሙስና መረቦችን ለማግኘት ጠንካራ ስራ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው።

 

ሌላው፣ ሙስና አንድ ሰው ለብቻው የሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት አለመሆኑን ያሳያል። ሙስና ከባለስልጣን፣ ከባለሃብት፣ ከቤተሰብ እና ከሌሎች ኃይሎች ጋር በጋራ የሚፈጸም የተቀናጀ ወንጀል መሆኑ ይጠቁማል።

 

ሌላው፤ ማንም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ከሕግ በላይ አለመሆኑን ጥሩ ማሳያ ነው። ይህንን ለመፈጸም ግን፤ አስፈፃሚውን ሊገዳደር የሚችል ተቋም መመስረት ፋይዳው ብዙ መሆኑን፤ ጥሩ ማሳያ ነው። እንዲሁም ዳኛ ዴቪድ እንዳሉት፣ ኦልመርት ብሩህ አዕምሮና የህዝብ ፍቅር አለው። ለሀገራችን እስራኤል ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከተ ነው። ሆኖም ግን የሕዝብን አገልግሎት የሚመርዝ ሙስና ፈጽሟል፤ ቅጣትም ይገባዋል፤ ብለዋል።

 

 

ሌላው፣ የሙስና ክብደትን ለመፈተሽ ጥሩ አጋጣሚ ተደርጐ የሚወሰድ ነው። ምክንያቱም ለሕዝብ ጥሩ ምሳሌ የማይሆን ማለት እና ሥርዓትን የሚያፈርስ ሙስናን ለመለየት የሚያስችል ጥሩ አብነት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

 

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የሚስችሏትን ትልልቅ የልማት ተግባራት በማከናወን ላይ ስለመሆኗ መስካሪ ማፈላለግ ውስጥ የሚገባ የለም። የኢትዮጵያ መንግስት ከዘረጋው መጠነ ሰፊ የልማት አጀንዳዎች ቢያንስ አብዛኛዎቹ ተሳክተው ማሕበራዊ ፍትህ ለማስፈን የእድገት እና የትራንስፎርሜሽ እቅዶች እየተገበረ ይገኛል።

 

 

ይህን ሁሉ ጥረት ቢደረግም አሁንም 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ምገባቸውን ከመንግስት እጅ የሚጠብቁ ናቸው። እንዲሁም 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በሴፍቲኔት ታቅፈው ወደ ድህነት ወለል ለመጠጋት እየፈለፉ ይገኛሉ። ቀሪው ሕዝብም ቢሆን፣ ከድህነት ወለል ከፍ ለማለት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ እንደሚገኝ ለማንም የሚጠፋ እውነት አይደለም። ይህ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ነው።

 

ይህንን ተጨባጭ የሀገሪቱን ሁኔታ ይለውጣሉ ተብለው ታምነው የሕዝብ ኃላፊነት የወሰዱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አስፈሪም አስደንጋጭ በሆነ የአብይ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ተገኝተዋል። ባክኗል ወይም ተዘርፏል ከተባለው በላይ ምላሽ የሚሻው ጥያቄ፤ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ ለመቀራመት አስተሳሰቡ ከወዴት ነው የመጣው? ከ20 ሚሊዮን በላይ ከድህነት ወለል በታች ዜጎች በሚገኙባት ኢትዮጵያ፤ ቢሊዮኖችን ለመዝረፍ የባለስልጣኖች እና የባለሃብቶች ሞራል በዚህ ደረጃ፤ እንዴት ሊወርድ ቻለ? የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነቱን ይዟል ሲባል ሲነገር የነበረው፤ ሀገር በቢሊዮኖች ደረጃ በምትዘረፍበት ቁመና ላይ መሆኗን ስለእውነት የሚያውቅ ዜጋ ነበርን?

 

እነዚህን ችግሮች ከሥራቸው ለማድረቅ ፍርደኞች ላይ ፍርድ በመስጠት ብቻ የሚታለፍ አይደለም። አጠቃላይ የሀገሪቷ ሲስተም በከፍተኛ ባለሙያዎች ማስፈተሽ እና የማሕራዊ ሳይንስ የጥናት ቡድን በሀገር አቀፍ ደረጃ አደራጅቶ እንደሕዝብ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ አራማጅ እንዴት እንደሆንን መፈተሽ ተገቢ ነው። እንዲሁም የሀገሪቷን የትምህርት ሥርዓት ከግብረገብ አንፃር መቃኘት ሌላው ተጨማሪ አማራጭ ነው። ምክንያቱም ዛሬ ዘራፊ ያልናቸው ሲዘርፉ ያገኘናቸው፤ የዚሁ ሕብረተሰብ ውጤት በመሆናቸው ነው።

 

 

ለማንኛውም፣ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በሙስና ተጠርጥረው ስማቸው የተገለጹት እና ፍርድ ቤት የቀረቡት የሚከተሉት ናቸው። የተጠርጣሪዎች ቁጥር ወደ 45 ማሻቀቡን በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

 

በተለያዩ 14 የክስ መዝገቦች ተከፋፍለው የቀረቡት ከኢትዮጵያና ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፤ ከስኳር ኮርፖሬሽን እና ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ 34 ግለሰቦች ናቸው።

 

ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ኢንጂነር ፍቃደ ኃይሌ /የቀድሞ የባለስልጣኑ ሥራ አስኪያጅ/፣ ኢንጂነር አህመዲን ቡሴር፣ ኢንጂነር ዋስይሁን ሽፈራው፣ ሚስተር ሚናሽ ሌቪ (የትድሃር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ) ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ተጠርጥረው የቀረቡት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከማዕድን ሚኒስቴር እስከ ውሃ ሀብት ድረስ ያለውን መንገድ ሲያሰሩ ያልተገባ ውል መዋዋላቸውን ፖሊስ ለችሎቱ ገልጿል። ተጠርጣሪዎቹ በዚህ ፕሮጀክት ከትድሃር ጋር በመሻረክ 198 ሚሊዮን 872 ሺህ 730 ብር ከ11 ሣንቲም መንግሥትን አሳጥተዋል ሲል ፖሊስ አቅርቧል።

 

ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አቶ አብዶ መሐመድ፣ አቶ በቀለ ንጉሤ፣ አቶ ገላሶ ቡሬ፣ አቶ የኔነህ አሰፋ፣ አቶ አሰፋ ባራኪ፣ አቶ ገብረአናንያ ፃዲቅ፣ አቶ በቀለ ባልቻ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በተጠርጣሪነት የቀረቡት እነዚህ ግለሰቦች ደግሞ በከፍተኛ ኃላፊነት ሲሰሩ፤ ኮምቦልቻ፣ ሐረር፣ ጅግጅጋ እና ጋምቤላ ጎሬ በተሰሩ አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ አስፈላጊ የዲዛይን ጥናት ሳይደረግና ምንም ሕጋዊ ውል ሳይኖር ሆን ተብሎ ዋጋ እንዲጨመር በማድረግ፣ ከአሰራር ውጪ የኮንትራት ውል አዘግይተዋል ነው ያለው ፖሊስ።

 

በዚህም ፕሮጀክቶቹ በመዘግየታቸው 646 ሚሊዮን 980 ሺህ 626 ብር ከ61 ሣንቲም ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው መቅረባቸውን ፖሊስ ጠቅሷል።

 

ከስኳር ኮርፖሬሽን ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ አቶ አበበ ተስፋዬ /በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የአገዳ ተከላ ምክትል ዳይሬክተር/፣ አቶ ቢልልኝ ጣሰው /በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ጠቅላላ ሂሳብ ያዥ/ ሁለቱ ግለሰቦች በጋራ በመመሳጠር ፖሊስ ስሙ ለጊዜው በመዝገብ ካልተጠቀሰው ኩባንያ ጋር የአርማታ ብረት እና ሲሚንቶ በዓይነት ማስረከብ ሲገባ፤ ሳይረከብና ተቀናሽ ሳይደረግ 31 ሚሊዮን 379 ሺህ 985 ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተመልክቷል።

 

ከመተሃራ ስኳር ፋብሪካ አቶ እንዳልካቸው ግርማ፣ ወ/ሮ ሰናይት ወርቁ፣ አቶ አየለው ከበደ፣ አቶ በለጠ ዘለለው ሲሆኑ፤ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በተለይ አቶ እንዳልካቸው፣ ወ/ሮ ሰናይት እና አቶ አየለው በመተሃራ ስከር ፋብሪካ የግዢ ቡድን መሪ እና የውጭ ሀገር የእቃ ግዢ ኃላፊዎች ሆነው ሲሰሩ 13 ሚሊዮን 104 ሺህ 49 ብር ከ88 ሣንቲም ለአቅራቢዎች ያለአግባብ እንዲከፈል በማድረጋቸው፤ እንዲሁም አቅራቢዎቹ ባላቀረቡበት ሁኔታ ላይ 0 ነጥብ 1 በመቶ ቅጣት ማስቀመጥ ሲገባቸው በዚህም 2 ሚሊዮን 743 ሺህ 35 ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል።

 

አቶ በለጠ ዘለለው ደግሞ በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ የፋይናንስ ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ ፋብሪካው ለመሳሪያ እድሳት ያልተሰራበትን 1 ሚሊዮን 164 ሺህ 465 ብር ክፍያ በመፈፀም ተጠርጥሯል።

 

ከኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 አቶ መስፍን መልካሙ /የኦሞ ስኳር ፋብሪካ ቁጥር 5 ምክትል ዋና ዳይሬክተር/ ወይዘሮ ሳሌም ከበደ፣ ሚስተር ጂ ዮኦን /የቻይናው የጄጄ አይ. ኢ. ሲ. ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ/፣ አቶ ፀጋዬ ገብረእግዚአብሔር፣ አቶ ፍሬው ብርሃኔ ሲሆኑ፤ ተጠርጣሪዎቹ በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 ሲሰሩ ከተዘረዘሩት ተጠርጣሪዎች ጋር በመመሳጠር በሥራ ላይ የሚገኘውን ፕሮጀክት ያለአግባብ ውል በመስጠት 184 ሚሊዮን 408 ሺህ ብር ጉዳት በማድረግ ፖሊስ መጠርጠራቸውን ጠቅሷል።

 

ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ አቶ አበበ ተስፋዬ፣ አቶ ዳንኤል አበበ፣ አቶ የማነ ግርማይ ሲሆኑ፣ በተንዳሆ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የቤቶች ልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል አበበ ከፋብሪካው የአገዳ ቆረጣ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ ተስፋዬ ጋር በመመሳጠር የተለያዩ የክፍያ ሰነዶችን በመሰረዝ እና በመደለዝ ለሦስተኛ ወገን ለአቶ የማነ ግርማይ 20 ሚሊዮን ብር ያለአግባብ ክፍያ በመፈፀም እና በዓይነት እና በገንዘብ ሳይመለስ በመቅረቱ ተመሳሳይ መጠን ያለው ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል።

 

በሌላ መዝገብ አቶ አበበ ተስፋዬ፣ አቶ ኤፍሬም ዓለማየሁ እና አቶ የማነ ግርማይ፣ አቶ አበበ እና አቶ ኤፍሬም ከአቶ የማነ ግርማይ ጋር በመመሳጠር ለባቱ ኮንስትራክሽን 2 ሺህ ሔክታር መሬት ምንጣሮ አንድ ሔክታሩን በ25 ሺህ ብር ተዋውሎ ሳለ ሥራውን ከባቱ ኮንስትራክሽን በመንጠቅ ለአቶ የማነ ግርማይ አንዱን ሔክታር በ72 ሺህ 150 ብር የ42 ሚሊዮን ብር ልዩነት እያለው ያለምንም ጨረታ አንዲሰጠው በማድረግ በአጠቃላይ ከ216 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል።

 

አቶ ፈለቀ ታደሰ፣ አቶ ኤፍሬም ደሳለኝ /የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የግዢ እና ንብረት አስተዳደር መክትል ዋና ዳይሬክተር/ አንድ ሺህ ሔክታር መሬት እንዲመነጠር ለባቱ ኮንስትራክሽን በመስጠት ተገቢው ሥራ ሳይሰራ 10 ሚሊዮን ብር ለባቱ ኮንስትራክሽን እንዲከፈል በማድረግ ተጠርጥረዋል።

 

ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አቶ ሙሳ መሐመድ /የሚኒስቴሩ የፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ/፣ አቶ መስፍን ወርቅነህ /የሚኒስቴሩ የፕሮጀክት ባለሙያ/፣ አቶ ዋስይሁን አባተ /የሚኒስቴሩ የሕግ ክፍል ዳይሬክተር/፣ አቶ ታምራት አማረ /የሚኒስቴሩ ባለሙያ/፣ አቶ ስህን ጎበና /የሚኒስቴሩ ባለሙያ/፣ አቶ አክሎግ ደምሴ /የሚኒስቴሩ ባለሙያ/፣ የሚኒስቴሩ ባልደረባ ያልሆኑ፣ ዶ/ር ወርቁ ዓለሙ፣ አቶ ዮናስ መርዓዊ፣ አቶ ታጠቅ ደባልቄ ሲሆኑ፤ ተጠርጣሪዎቹ በሚኒስቴሩ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ላይ ሲሰሩ መንግሥት የፋይናንስ ስርዓቱን ለማዘመን 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር በመውሰድ ለቴክኖሎጂው ማስፋፊያ ሥራ የበጀተውን ገንዘብ ያለ አግባብ በመጠቀም ቴክኖሎጂው ከሚሰሩት ዶክተር ወርቁ ዓለሙ፣ አቶ ዮናስ መርዓዊ እና አቶ ታጠቅ ደባልቄ ጋር በመመሳጠር ቴክኖሎጂው በተገቢው መንገድ አቅም ላላቸው ባለሙያዎች መስጠት ሲገባው ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ጨረታን ሳይከተሉ በማሰራት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል። ተመሳሳይ የገንዘብ መጠን ያልተሰራበትን እንደተሰራ በማድረግ ክፍያ በመፈፀም ነው የተጠረጠሩት።

በአጠቃላይም ተጠርጣሪዎች ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የፕሮጀክት ሥራ የወጣን ወጪ አጉድለዋል ሲልም ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል። ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና ጥያቄ ይፈቀድላቸው ዘንድ ችሎቱን ጠይቀዋል።

 

ፖሊስ በበኩሉ ያልጨረስኩት ሰነድ እና ማስረጃ ስላለ ለምርመራ ተጨማሪ 14 ቀናት ጊዜ ይሰጠኝ በማለት ጠይቋል።

 

ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ ሰነዶችን ሊያሸሹ ይችላሉ በማለትም የጠየቁት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ይሁንልኝ ብሏል።

 

ችሎቱም የፖሊስን ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ለነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

ከዚህ ባለፈም ተጠርጣሪዎች ከጠበቃና ቤተሰብ ጋር እንዳንገናኝ ተከልክለናል በማለት ላቀረቡት አቤቱታ ችሎቱ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ከጠበቃና ቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

 

በተጨማሪም አቶ ጌታቸው አምባዬ በሰጡት መግለጫ በኦሞ ኩራዝ 5 ከቻይና ኤግዚም ባንክ 700 ሚሊዮን ዶላር ከተገኘው ብድር 30 ሚሊዮን ዶላር በኮሚሽን መልክ ሊከፈል እንደነበረ አስታውቀዋል፡፡

 

እንዲሁም በገንዘብ እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር የ20 ሚሊዮን ዶላር እና 19 ነጥብ 1 ማሊዮን ዶላር የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም ለመዘርጋት የወጣውን ጨረታ በቀጥታ ለአንድ ኩባንያ ካለውድድር እንዲሰጥ መደረጉን ይፋ አድርገዋል፡፡ 

ጥቂት ስለ ሐዋሳ

Wednesday, 26 July 2017 13:44

 

ከበቃሉ ተገኘ

የደቡብ ከተማዎች ሁሉ በኩር የሆነችው ሐዋሳ የፍቅር፣ የሠላምና አንድነት እንዲሁም የመቻቻል ተምሣሌት ሕብራዊት ከተማ እየተባለች በነዋሪዎቿ በእንግዶቿም ሣይቀር ዘወትር የሚዘመርላት ያለ ምክንያት አይደለም። ይህ ምርጥ አባባልም የተቸራት እንደ ፀበል ፃዲቅ በነፃ ሣይሆን የሥራዋ ውጤት ስለሆነ ነው።

ከወንዶ ገነት ጀምሮ ዙሪያዋን ከአጀቧትና በተፈጥሮ ፀጋ ከታደሉት ክረምት ከበጋ ልምላሜ ከማይለያቸው አካባቢዎች ዘወትር በገፍ የሚቀርብላት አትክልትና ፍራፍሬ በተጨማሪ የሐዋሳ ሐይቅ የማህፀን ፍሬ የሆነው ዓሳዋ እንደ አቤል መስዋዕት እጅግ ያማረና ለጤናም ተስማሚ ነው። ምን ይሄ ብቻ፤ ቅልቅል የሚያክል የአቦካዶ ፍሬ ከጓሮ ቆርጠው አልያም ከበርዎ አጠገብ በቅናሽ ዋጋ ገዝተው ወይም በአቅራቢያዎ ከሚገኝ ጭማቂ ቤት ጎራ ብለው ጦጣ በማይዘለው ብርጭቆ የአቦካዶ ጭማቂ እየጠጡ ሣይሆን እየገመጡ የፀሐዩን ሙቀትና ተለዋዋጭ ባህሪ የሚያሳየውን ወበቅ ከሐይቁ በሚነሳው መልካምና ነፋሻ አየር እየገሰፁ ነፍስዎን ያቀዘቅዛሉ።

ታዲያ ከተማዋ በፈጣን ልማት ላይ ስለሆነች ነዋሪዎቿ ለልማት ሲሯሯጡ ሲያዩ ለረጅም ሰዓት እንዲቀመጡ ሕሊናዎ አይፈቅድልዎትምና ወደተሰማሩበት ሥራ ይገሰግሳሉ።

ሐዋሳ ከተማ ላይ የተጀመረ የአስፋልት ሥራና መንግሥታዊ ሕንፃ በጥቂት ጊዜ ውስጥ አልቆ ያገኙታል። በተለይም በአሁኑ ሰዓት ሐዋሳ ከድሮው በበለጠ ልማት ላይ ናት። ድሮ ያልነበረና የማያውቁት የኑግ ልጥልጥ የመሰለ አስፋልት በአጭር ጊዜ ውስጥ አልቆና ሥራ ጀምሮ ሲያገኙት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለሁት? ወይስ ከኢትዮጵያ ውጪ? ብለው ማሰብዎ አይቀርም።

ዳሩ ምን ያደርጋል የከተሞች ውበት ነፍሰ ገዳይ የሆነው የቀበሌ ቤት ውቢቷ ሐዋሳንም እንደ ጉንዳን ወሯት ለአይን ማራኪ በሆነው አስፋልት ዳር ሥጋው አልቆ በአጥንቱ ቆሞ ሲያዩ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆንዎን ያረጋግጣሉ።

አልፎ አልፎ በሐዋሳ የሚከሰተው ርዕደ መሬት እነዚህን የራሳቸውን ዕድሜ ጨርሰው በዘመናዊ ቤቶች ዕድሜ የሚኖሩትን አስቀያሚ የቀበሌ ቤቶች ከዘመናዊ ቤቶች ነጥሎ መሬት ከፍቶ እንዲውጣቸው የጸለዩት ፀሎት በውስጡ የሚኖሩትን ምስኪን ወገኖችዎን ሲያስቡ አባት ሆይ የምፀልየውን ፀሎት አላውቅምና ይቅር በለኝ በሚል ፀሎት መልሰው ይሽሩታል። ሐዋሳ ላይ በዚህ ብቻ አይደለም የሚደነቁ በመንግስታዊ መ/ቤቶች ሕጋዊ ጉዳይ ይዘው ከቀረቡ በፍጥነት ይስተናገዳሉ። ይዘው የቀረቡት ጉዳይ አግባብነት የሌለው ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው በሰፊው ሣይሆን በጠባቡ በር እንዲገቡ ተመክረው በክብር ይሰናበታሉ።

አንዳንድ የቢሮ ኃላፊዎች ከጥልቅ ተሃድሶ ስልጠና በኋላም እንኳን የመጀመሪያ ጠባያቸውን ሊያሻሽሉ ቀርቶ ጭራሽ ብሶባቸው ሲያዩ ከተቀቀለ ባቄላ ውስጥ ጥሬ ባቄላ መኖሩን ሲያስታውሱ ከጥልቅ አግራሞትዎ በፍጥነት ይወጣሉ።

የእርስዎ ጉዳይ ከፍ ያለና ከታች ያለው ንዑስ መ/ቤት ሊያስተናግድዎ ካልቻለ ወይም በመስተንግዶው ካልተደሰቱ አቢይና የከተማው አስተዳደር ቁንጮ ወደሆነው ከንቲባ ጽ/ቤት መገስገስዎ አይቀሬ ነው።

እውነት ለመናገር በዚህ መ/ቤት በአሀኑ ሰዓት መልካም አስተዳደር አለ። ብዙ ባለጉዳዮች የሐምሌን ደመና የመሰለ ፊት ይዘው ወደ ከንቲባው ቢሮ ገብተው እንደ መስከረም አደይ ፈክተው ሲወጡ በአይኔ በብረቱ አይቻለሁ። የታላቋና ስመ ገናናዋ ሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ ይባላሉ። በነገሬ ላይ ቴዎድሮስ በመባል የሚጠሩ በርካታ ጀግኖችን አውቃለሁ። ለጊዜው ሶስቱን ብቻ ልጥቀስ።

1.  የኢትዮጵያ ቀኝ ክንፍ የሆነችው በሥልጣኔም ሆነ በሥልጣን ቀዳማዊት ለክብሩ እንጂ ለሆዱ የማይሞት ቢርበው እንኳን ጠግቤአለሁ በቃኝ የሚል የማይስገበገብ፣ የኩሩ ሕዝብ መፍለቂያ ከሆነችው ጎንደር ውስጥ ከትንሿ መንደር ቋራ ላይ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከደሃ ቤተሰብ የተወለደው ነገር ግን ጭንቅላቱ ውስጥ በገንዘብ የማይለካ እምቅ ሀብት የነበረው ኢትዮጵያዊ ጀግና አፄ ቴዎድሮስ አንዱ ነው።

እንደ ቅርጫሥጋ የተከፋፈለችውን ኢትዮጵያ አንድ ለማድረግ ብሎም ኋላ ቀርነትንና ድንቁርናን አስወግዶ ዕድገትና ብልፅግናን ለማምጣት ሲል መቅደላ ኮረብታ ላይ የተሰዋው ሰማዕት አፄ ቴዎድሮስ የጀግኖች መሪዎች አብነት እንዲሁም አርአያና ምሣሌ በመሆኑ የጀግኖች ጀግና ቢባል ያንሰዋል እንጂ አይበዛበትም።

2.  ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮም ከተማ ውስጥ የተወለደው ቴዎድሮስ ገና በአፍላነቱ አለማችን ለሠው ልጆች እንደተፈጠረች ለሰው ልጅ የተፈጠረችው አለምም በሰው ልጅ እንደተበላሸች አለምን መልሶ ለማስተካከልና ለማሳመር የሰውን አስተሳሰብ በወንጌል ትምህርት ማስተካከል አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን ተገነዘበ። ምክንያቱም በፈጣሪ ያላመነ ሕጉንም ያልተከተለ ሰው አውሬ ነውና ከአውሬ ጥፋት እንጂ ልማት አይጠበቅም። አውሬዎች ለዛሬ እንጂ ለነገ አያስቡም። አውሬዎች ከራሳቸው ውጪ ለሌላ ማሰብም አይችሉም። በዚህ ምክንያት ቅዱስ ቴዎድሮስ ዘመናዊ መጓጓዣ ባልነበረበት በዚያ ዘመን በባዶ እግሩና አንዳንዴም በፈረስ ሀገር ለሀገር እየዞረ ወንጌልን በማስተማር በክፉ ሥራቸውና አስተሳሰባቸው ከሰውነት ወደ አውሬነት የተለወጡትን ሰዎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ሣይቀር ከአውሬነት ወደ ሰውነት መልሷል። ይሁንና በመጨረሻ ወንጌልን ያልተቀበሉ በክርስቶስም ያላመኑ አውሬዎች በልተውት በሰማዕትነት አርፏል። ስለሆነም ቴዎድሮስ የቤተክርስቲያን ባለውለታና የአለማችን ጀግና ነው።

1.የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ

እንደሚታወቀው አንድን ከተማ በልማት ለማሳደግና ለእይታ ማራኪ፣ ለኑሮም ተስማሚ ለማድረግ ከንቲባ ጽ/ቤቱ ጉልህ ድርሻ አለው። በሀገራችን ያሉ ከተሞች ዕድገታቸው አፍአዊ ብቻ ሣይሆን ውስጣዊም እንዲሆን ተግተው የሚሰሩ በዘመናዊ መኪና አስፋልት ሰንጥቀው ሲሄዱ በትራንስፖርት እጦት ከአስፋልት ዳር ቆሞ በፀሐይ ሐሩር የሚቀልጠውን ወገናቸውን በጎሪጥ አይቶ ማለፍ ሳይሆን በወገን ፍቅር ልባቸው የሚቀልጥ ይህንና ሌላውንም ችግር ለመቅረፍ ተግተው የሚሰሩ ጀግና ከንቲባዎች ሀገራችን ያስፈልጓታል። በዚህ ረገድ ሐዋሳ ዕድለኛ ናት። በአሁን ሰዓት የምርጥ ከንቲባ ባለቤት ናትና።

ልማታዊ ጀግንነትና ቅንነት ከፊታቸው የሚነበበው መልከ መልካሙና ቁመተ ሎጋው አቶ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ሣይሆን ለከተማውና ለከተማው ሕዝብ የሠጡ ናቸው ቢባል አልተጋነነም። ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነውና።

አብዛኛውን ጊዜ ስብሰባ ስለሚበዛ ብዙ ባለጉዳዮች የየቢሮ ኃላፊዎችን ሲያማርሩ ቢደመጥም እርሳቸው ግን ስብሰባ በሚኖርበት ቀን እንኳን ከስብሰባው ሰዓት በፊትና ከስብሰባው በኋላ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ቢሮ እየገቡ ባለጉዳዮችን ያስተናግዳሉ። አንዳንድ ጊዜ ጽ/ቤታቸው ከመደበኛ ገበያ ዝቅ፣ ከጉልት ገበያ ከፍ በሚል ሁኔታ ባለጉዳይ ተጨናንቆ ቢታይም በአጭር ሰዓት ያንን ሁሉ ሕዝብ አስተናግደው ሲሸኙ የመሰላቸት መንፈስ አይታይባቸውም። እጃቸውም ሆነ አእምሯቸው ንፁህ በመሆኑ የሚሰጉበት ምንም ነገር ስለሌለ ለደወለላቸው ሁሉ ስልክ ያነሳሉ። በትዕግስት ያዳምጣሉ፤ በትህትና ይናገራሉ። ቅንነትና መልካምነት በተፈጥሮ የሚታደሉት ፀጋ እንጂ በሥልጠና የማይገኝ መሆኑ ግልፅ ቢሆንም፤ ለከንቲባነት የታጩ ሁሉ በቅድሚያ ከአቶ ቴዎድሮስ ትምህርት ቢወስዱና ልምድ ቢቀስሙ መልካም ነው። የእርሳቸውን ጀግንነትና የእኔን ስንፍና ሳይ ግርም ይለኛል። ታዲያ እኔም እንደ ቴዎድሮሶች ጀግና እንድሆን ባለኝ መጠሪያ ስም ላይ ደርቤ ቴዎድሮስ ልባል ይሆን? ቴዎድሮስ ሆይ ሺህ አመት ንገስ ከማለት ውጪ ሌላ ምን ማለት እንችላለን?

በሐዋሳ ከተማ በመልካም ስራቸው ምስጋና ሊቸራቸው የሚገባ በርካታ የቢሮ ኃላፊዎች ቢኖሩም ለጊዜው ግን ሁለቱን ልጥቀስ።

 

 

2.የኮንስትራክሽን መምሪያው አቶ እዮብ ብርሀኑ

እኚህ ሰው በተፈጥሮአቸው ብሩህ አእምሮ ያላቸው ሲሆን ሲበዛ ቅን ናቸው። ቀደም ሲል የከተማዋ ህንፃ ሹም ሆነው የሰሩ ሲሆን በስራ ወዳድነታቸውና ብቃታቸው የኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል። ሁላችንም ደስ ብሎን ይደልዎ (ይገባዋል) ብለናል። አቶ እዮብ የተመደቡበት የኃላፊነት ስራ በህገወጥ ግንባታ ምክንያት ከህብረተሰቡ ጋር የሚያጋጭ ቢሆንም መንግስትና ህዝብን አቻችለው ስለሚሰሩ፤ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ለጦርነት ከቢሮአቸው የመጣን ባለጉዳይ አለዝበውና አቀዝቅዘው ይመልሳሉ። ማንም ሰው ከገቢው ይልቅ ወጪው እየበዛ በመቸገሩ ህጋዊ ወዳልሆነ ተግባር እየገባ ባለበት ዘመን እሳቸው ግን ደመወዜ ይበቃኛል የሚሉ ሙስናን የተፀየፉ ኩሩና ጨዋ ኢትዮጵያዊ ናቸው።

የመንገድ ባለፀጋ የህንፃ ደሀዋን ሐዋሳ በነዳጅ ገቢ የበለፀጉ የአረብ ሀገራት እንደ እነ ዱባይና እንደሌሎቹ ለጊዜው የሰማይ ጠቀስ ፎቆች ባለቤት ማድረግ ባይቻልም ከእህቶቿ ከእነ ናዝሬትና ከእነ ባህርዳር ተርታ ለማሰለፍ እየጣሩና እየለፉ ይገኛሉ። ማንኛውም የከተማ ነዋሪ ህንፃ ከመስራት ውጪ ሌላ ህገወጥ ግንባታ እንዳያካሂድ በመከታተልና በመቆጣጠር በተከላካይነት እንዲሰሩ የመደቧቸው ደቀመዛሙርቶቻቸው ከድምፅ የፈጠኑና አራት አይና ናቸው። አራት አይን ስል ሁለቱ አይኖች የእነሱ ሲሆኑ ሁለቱ አይኖች ደግሞ ህገወጥ ግንባታ የሚያካሂደው ግለሰብ ጎረቤት ናቸው። ጎረቤቱ በስልክም ሆነ በአካል ጥቆማ የሚያቀርበው መንግስት በህገወጥ ግንባታ ምክንያት የከተማው ገፅታ እንዳይበላሽ በሚያደርገው ትግል ከመንግስት ጎን ተሰልፎ መንግስትን ለማገዝ ሳይሆን ጎረቤቴ እኔን ቀድሞ ለምን ቤቱን ያድሳል በሚል መንፈስ መሆኑ ግልፅ ነው።

እንደአለመታደል ሆኖ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ይህ አይነት አመለካከት ከደማችን ጋር ስለተዋሀደ በበረኪና ቢያጥቡን በኦሞ ቢዘፈዝፉን አይለቀንም። ሐዋሳ ቀደም ሲል ለጥቂት ባለሀብቶች ለመንግስት መ/ቤቶችና ለትምህርት ተቋማት ካላት ውስን መሬት ላይ በለጋስነት እየገመደለችና እየገመሰች ሰጥታ አሁን ግን እጅ እያጠራት ነው። የከተማ ክልሏን ለማስፋት ብትፈልግም እንደ ክቡር ዘበኛ ዙሪያዋን የቆሙት ተራሮች የይለፍ ፍቃድ አልሰጧትም። የመሬት ባለፀጋው ኦሮሚያ ክልል ከቶጋ እስከ ጥቁር ውሃ ያለውን የተንጣለለ ሜዳ ለሐዋሳ በመስጠት የለጋስነትና የመልካም ጉርብትና አርአያ ቢሆን እንዴት መልካም ነበር።

ያም ሆነ ይህ ሰው እየበዛ ልማቱ እየሰፋ መሬት ደግሞ እየጠበበ ስለሚሄድ ሐዋሳ የመንገድ ባለፀጋ እንደሆነች ሁሉ ህንፃ በህንፃ ትሆናለች። በኢትዮጵያ ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎችን ከቻላችሁ ህንፃ ስሩ ካልሆነ በአሮጌ ቤታችሁ ውስጥ ቁጭ በሉ እንጂ እናድሳለን ብላችሁ ቤታችሁን ትነኩና ዋ የሚለው የህንፃ ህግ አዋጅ ህብረተሰቡን ህንፃ እንዲሰራ ያነሳሳዋል? ከዚህ ይልቅ ልዩ ልዩ ማበረታቻ ለምሳሌ የህንፃውን ዲዛይን እና ፕላን ለሚሰሩ ባለሙያዎች መንግስት ዳጎስ ያለ ደመወዝ ቢከፍልና ወደ ግንባታ ለሚገቡ ልማታዊያን ፕላኑ አለቀልኝ፣ ፀደቀልኝ በማለት ሳይጉላሉ በአስቸኳይ አልቆና ፀድቆ በነፃ ቢሰጣቸው እንዲሁም በረጅም ጊዜ ተከፍሎ የሚያልቅ የባንክ ብድር የሚያገኙበት መንገድ ቢመቻችላቸው ከዚህም ጋር ሕንፃው ተሰርቶ ካለቀ በኋላም የመብራትና የውሃ ፍጆታው ከፍ ስለሚል መብራትና ውሃ በበቂ ሁኔታ የሚያገኙበት መንገድና ወዘተ… ቢመቻች የተሻለ ይሆን ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ። ይሁንና አቶ እዮብ መንግስት ያወጣውን ህግ በተገቢው መንገድ ማስፈፀም እንጂ ብቻቸውን ህጉን ሊያሻሽሉ ስለማይችሉ በተመደቡበት ኃላፊነት በብቃትና በጥራት እየሰሩ ስለሆነ ሊመሰገኑ ይገባል።

 

 

3.በሐዋሳ ከተማ የመናኻሪያ ክ/ከተማ አስተዳደር አቶ መኩሪያ ማኒሳ

እኚህ ሰው በሚደነቅ የአስተዳደር ችሎታቸው ሌላ ኢትዮጵያዊ ለዛ ያልተለያቸው ዘርና ጎሳ እንደ ልጓም የማይስባቸው በቢሮአቸው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያለ አድልዎ በቀና መንፈስ የሚያስተዳድሩ የሐዋሳ የቁርጥ ቀን ልጅ እና ምርጥ ኢትዮጵያዊ ናቸው።

የመናኻሪያ ክፍለ ከተማ ከሌሎች ክፍለ ከተሞች ይልቅ የንግድ እንቅስቃሴ የሚበዛበት በመሆኑ በአስተዳደር ሥራቸው ላይ ጫና ቢፈጥርም በእውቀትና በቅንነት መንግስትንና ህብረተሰቡን እንደ ነብስና ሥጋ አዋህደውና አስማምተው ስለሚሰሩ ምንም አይነት ኮሽታ የለም ማለት ባይቻልም ኮሽታውንም ግን በጥሩ አመራርና በመልካም አስተዳደር ፀጥ ረጭ ያደረጉታል። እንደሚታወቀው ብዙዎቹ ቅርቡን አርቀው ቀላሉን አክብደው ስለሚያዩና በራስ መተማመን ስለሚያንሳቸው እራሳቸው መፈፀም የሚችሉትን ጉዳይ ይህ እኔን አይመለከትም በማለት እንደ ጲላጦስ ሂዱ ወደ ሃና ሂዱ ወደ ቀያፋ በማለት ባለ ጉዳይን የሚያንከራትቱ የመንግስትና የህዝብ ማፈሪያ ባለስልጣናት በሞሉበት ዘመን እንደ ስሙ ህዝብንና መንግስትን የሚያኮራ አስተዳዳሪ ማግኘት ኩራት ብቻ ሳይሆን መታደልም ነው።

የሐዋሳ ባለስልጣናት ሁሉም ማለት ይቻላል። መጽሀፍ ቅዱስ ስለሚያነቡና እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሀገራችን በሰማይ ነው ብለው ስለሚያምኑ ዘረኝነትና ጎጠኝነት እንዲሁም ጠባብነት ፈጽሞ የለባቸውም። ስለሆነም ሐዋሳ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከተማ ናት። ዘረኝነት የጥበብ ሳይሆን የድንቁርና መጀመሪያ የደካማነት መጨረሻ መሆኑን የጥበብ ሰዎች ሁሉ ያውቁታል። ኢትዮጵያ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ የሁሉም ኢትዮጲያዊያን ናት። ሁሉም ክልሎች የኢትዮጵያ ብልቶች ናቸው። አንዱ ብልት ሌላውን ብልት አታስፈልገኝም ሊለው አይችልም አንዱ ብልት ቢታመም ብልቶች በሙሉ ይታመማሉና የኢትዮጵያ ብልቶች ከሆኑት ክልሎች ውስጥ አንዱ ታሞ እንደነበርና ሁሉም ክልሎች በጠና ታመው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ጥቂት የዋህ ወገኖቻችን እንደ ሾላ ፍሬ መንግስትን በድንጋይ ካላወረድን ብለው በፈጠሩት ግርግር እና ኢትዮጵያ በጠና ታማ እንደነበር ይታወሳል።

ባሏን ጎዳው ብላ እንትኗን በሰንጢ እንዲሉ መንግስትን ጎዳን ብለው የወገናቸውንና የእራሳቸውን ንብረት በእሳት አጋይተው እንደነበር እስካሁን ድረስ በየመንገዱ የሚታየው የመኪናዎቻችን ቅሬተ አካል ምስክር ነው። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን አንድነትን እንደ ዝናር ታጥቀን ፍቅርና መዋደድን ተጫምተን የሰላምን ቁር እራሳችን ላይ ደፍተን በሁሉም ነገር ከፊት የነበረችውን አሁን ግን ኋላ የቀረችውን ኢትዮጵያን እናልማ። ይህን ካደረግን ኢትዮጵያ ሀገራችን በበረከት ትሞላለች የጠሏትና የናቋት ሁሉ ከእግሯ ስር ወድቀው ማሪን ይላሉ በኢኮኖሚ የበለፀጉ ሀገራት ሳይቀር ወደ ተስፋይቱ ሀገር ኢትዮጵያ ለመግባት ደጅ ይጠናሉ። በየአረብ ሀገራቱ በስደት የተበተኑ የኢትዮጵያ ልጆች አንፈልጋችሁም ውጡልን ሳይሆን እንፈልጋችኋለን ኑልን ይባላሉ። ስለ ሐዋሳ ያለኝን ዕውነታ በተከታዮቹ የስንኝ ቋጠሮ ልደምድም እና ልሰናበታችሁ።

ውቢቷ ሲዳማ ለምለሚቷ ምድር

የልበ ቀናዎች የደጋጎች ሀገር

ሲዳማ ባንች ላይ እንኮራለን ሁሌ

የገነት ቅርንጫፍ የገነት ምሳሌ

ይህ ሀሰት ከሆነ ይምጣ ምስክሬ

የተንዠረገገው የአቡካዶው ፍሬ

የሲዳማን በዓል ፍቼ ጨምበላላ

እንደ ጎንደር አክሱም እንደ ላሊበላ

ዩኔስኮ አፀደቀው በቃለ መሀላ

ዩኔስኮ ታላቁ የዓለማችን ዕውቁ

መዝገቦታልና በቀለመ ወርቁ

በዓሉን እናክብር ሁላችን በጋራ

በስመ ገናናው በታቦር ተራራ።

“ቅብጥብጧ”

Wednesday, 26 July 2017 13:33

 

በማዕረጉ በዛብህ

ሩስያ እንደነ ሌብ (ሊዮ) ቶልስቶይ፣ ፍዮዶር ደስተየቭስኪ፣ ኢቫን ተርገነቭ፣ ኒኮላይ ጎጎል፣ አንቶን ቼኮቭርና እንዲሁም የኛው አልግዛንደር ፑሽኪን ያሉና ሌሎችም እጅግ የተደነቁ ጥንታውያን ደራሲዎች በየዘመናቸው እጅግ ተናፋቂ የስነጽሁፍ ችቦ ያበሩባት ሥራቸው በመላው ዓለም የተደነቀ የስነ ጥበብ ሰዎች የፈለቁባት አገር ነች። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ልዑካን ቡድን የዚያን ጊዜዋን ሶቪየት ኅብረት ሲጎበኝ የቡድኑ አባል በመሆን፣ የስነጽሁፍ ፍቅር እንደመስቀል ዳመና እሳት የሚንቀለቀልባትና ውቢትዋን ሞስኮን ጎብኝቻለሁ። ከሩስያ ደራስያን ማኅበር መሪዎችና አባሎች ጋር በነበረን የጥቂት ቀናት ግንኙነት የተገነዘብኩት ትልቅ ቁም ነገር ሥነጽሁፍ በሕብረተሰቡ ሕይወት ውስጥ የሕልውና ፍልስፍና በር ከፋችና አስደሳች የኑሮ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን ነው። ወደ አምልኮ በተጠጋ አድናቆት የሚወራው ከላይ ስለ ጠቀስኳቸውና ስለሌሎችም የጽሁፍ ሰዎች ነው። ከለጋስ መስተንግዷቸው በላይ ስለ ስነጽሁፍና ስለስነጽሁፍ ሰዎች የሚደረገው ውይይትና ጭውውት ውስጣዊ ስሜትን የሚኮረኩር የናፍቆት አባዜ የሚያሳድር ነገር ነው። ምነው ስነጽሁፍ በኛም አገር ይህንን የልዕልና ሕዝባዊ ፍቅር ደረጃ ልትደርስ በቻለች ያስብላል።

በአገራችን ለታላቁ ባለ ቅኔና ደራሲ ተውኔት ሎሪየት ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ ምስጋና ይግባውና በሱ አነሳሽነት የምዕራቡ ዓለም ስመጥር ደራሲ ተውኔት የዊልያም ሸክስፒየርን ሥራዎች ለመተርጎም ከተደረገ መጠነኛ ጥረት ሌላ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነቁ የሌሎች አገሮች ደራስያንን ሥራ በአማርኛም ሆነ በሌሎቹ ቋንቋዎቻችን ባለመተርጎማቸው የዓለም አቀፍ ስነጽሁፍ ባህልን በሰፊው ማጣጣም የቻልን አይመስለኝም።

ሰሞኑን ለስነጽሁፍ ወዳጆች ከተበረከቱት አዳዲስ ያገር ውስጥ መጻሕፍት መካከል በአጭር ልቦለድ ድርሰቶቹና በጸሐፊ ተውኔትነቱ በዓለም የተደነቀው የሩስያው የአንቶን ፓቪሌቪች ቼኮቭ “ቅብጥብጧ” የተባለችው 256 ገጽ መጽሐፍ በአማርኛ ተተርጉማ ለንባብ በቅታለች። ተርጓሚዋ ጽኑ የስነ ጽሁፍ ፍቅር ያላትና የሩስያኛ ቋንቋን በከፍተኛ ደረጃ በመተርጎም የምትታወቀው አንጋፋ ጋዜጠኛ ትዕግሥት ፀዳለ-ኀሩይ ነች። በመሆኑም የታላላቁ የሩስያ ደራስያን ዘመን አይሽሬ ሥራዎች ወደ አማርኛና ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚተተረጎሙበት ጊዜ እንዲደርስ የስነጽሁፍ አማልክት ፈቅደው ይሆን የሚያሰኝ ነው። ወ/ሮ ትዕግሥት “ወርቃማው ዘመን” ስለምትለው የሩስያ ደራስያን ሥራዎች በናፍቆት ትዝታ ካነሳች በኋላ በተለይ ስለ አንቶን ቼኮቭ ድርሰቶችና የሕይወት ታሪክ በጣፈጠ አማርኛ እያስነበበችን ነው። ለአንዳንዶቻችን ለዓለማቀፋዊ ስነጽሁፍ ንባብ ያለንን አምሮት ለመቀስቀስ ጥረት እያደረገች ይመስላል። ቅብጥብጧ የቼኮብን 22 አጫጭር ልቦለድ ወጎች የያዘች የመጀመሪያዋ የአማርኛ ትርጉም መጽሐፍ ስትሆን የመጽሐፉዋን የአንዷ አጭርልቦለድ ታሪክም የጋራ ርዕስ ነች።

በዝች አጭር ጽሁፍ የምሞክረው ስለ ትርጉሙ ደረጃ ወይም ጥራት አስተያየት ለመስጠት አይደለም፣ ምክንያቱም ሩስያውኛውን ቋንቋ ልክ እንዱ ቪየትናሚዝኛውና እንደቻይኒዝኛው አላውቀውም። ስለመጽሐፉ ይዘት ደራሲው ቼኮቭ ነውና አያሌ የሚደነቁ ነገሮች ቢኖርም እኔን ይበልጥ ያስገረመኝ ትርጉሙ የቀረበበት የአማርኛው ቋንቋ ዕድገት፣ ውበትና ጣዕም ነው። አንዳንድ ምሳሌዎች ለማቅረብ እንዲያመቸኝ ቅብጥብጧ ስለ ተባለችው አጭር ልቦለድ አንዳንድ ነገሮችን አነሳሳለሁ። በዝች አጭር ልቦለድ ወግ ጎልተው የሚታዩ ገጸባህርያት የህክምና ባለሙያ የሆነው ዶ/ር ስቲፓኖቪች ዲሞብ (ዲማ) እና ባለቤቱ አልጋ ኢቫኖቭና ናቸው። ሁለቱ የወደፊት ፍቅረኞች የተዋወቁት ዶ/ር ዲሞቭ የኢቫኖቭናን አባት ህክምና በሚከታተልበት ጊዜ ሲሆን ሰውየው ከሞቱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው የተጋቡት። ዲሞቭ በኋላ እንደምንረዳው እጅግ ተደናቂ የሆነ የሳይንስ ሰውና፣ የተከበረ ሃኪም ሲሆን በተፈጥሮው ዕወቁኝ፣ አድንቁኝ የሚል ጠባይ የሌለው ትሁት ሰው ነው። ባለቤቱ ኦልጋ በተቃራኒው ከታወቁ የስነጥበብ ሰዎች ጋር መተዋወቅ የምትወድና፣ እነሱን እቤቷ ለመጋበዝ እንደ መሯሯጥ የምትወደው ሌላ ነገር የሌላት ሴት ነች።

“ኦለጋ ኢቫኖቭና ትዘፍናለች፣ ፒያኖ ትጫወታለች. . .

. . . ከአማተር አርቲስቶች ጋር ትተውናለች። ይህ ሁሉ ደግሞ እንዲሁ የተገኘ አይደለም ተሰጥኦ ቢኖራት ነው”. . . ታዋቂ ሰዎችን ታመልካቸዋለች። በየሌሊቱ በሕልሟ ሳይቀር ታልማቸዋለች፣ እንደውሃ ይጠሟታል፣ ሆኖም ግን ምንም አድርጋ ከጥሟ ለመርካት አልቻለችም” ይላል ቼኮቭ አድናቆት ይሁን ሂስ ባልለየለት አረፍተ ነገር (ገጽ33)። እነዚህ ባልና ሚስት፣ ሴትየዋ ያላትን የለት ተለት ኑሮና ደስታ በስነጥበብ የታወቁ አርቲስቶችን ለመተዋወቅና ለማስተናገድ ጧት ማታ ስትዳክር ትሁቱ ባለቤቷ ዶ/ር ዲሞቭ ደግሞ የባለቤቱን እንግዶች በመጡ ቁጥር ሳይሰለች “እባካችሁ ጌቶቼ እህል ቅመሱ” ሲል በመቀበል ይታወቃሉ።

ዶ/ር ዲሞቭ ከሞተ በኋላ ጓደኛው ዶ/ር ኮሮስቴሌቭ እንደገለፀው እጅግ በጣም የሚደነቅ ባለሙያና ልዩ ሰው ነበር። “ሞተ! የሞተውም ራሱን መስዋዕት በማድረጉ ነው፣ አቤት ለሳይንስ ምን ዓይነት ጉዳት ነው!” አለ ኮሮስቴሌቭ። በመቀጠል “ሁላችንም ተሰብስበን ከእሱ ጋር ብንወዳደር አንዳችንም ከአጠገቡ አንደርስም. . . በጠራራ ፀሐይ ብርሃን ፋኖስ ተይዞ ቢፈለግ እንኳ የማይገኝ ሊቅ ነበር!. . . “ምን ዓይነት ግብረገብነት ነበረው!. . . ደግ፣ ንጹሕ፣ ሁሉን የሚወድ ልብ ያለው፣ ሰው አይደለም - መስትዋት እንጂ! ሳይንስን አገልግሎ ለሳይንስ ሲልም ሞተ” ሲል ነበር ኮሮስቴሌቭ ስለ ዴሞቭ ጨምሮ የመሰከረው።

ዲሞቭ፣ ኮሮስቴሌቭ እንደሚለው ትልቅ ባለሙያ፣ ሁሉ ነገር የተሳካለት ምርጥ ሰው ሲሆን ባለቤቱ ኦልጋ ኢቫኖቭና ግን ብዙ ችግር አለባት። ሕይወቷ በታወቁ የስነጥበብ ሰዎች ታዋቂነት አምልኮ በሽታ ተመዝብሯል። ስለሆነም የኔ ነው የምትለው የራስዋ ሕይወት የላትም። አንዳንድ ጊዜ የምትወደውና የምታስብለት የሚመስላት ባለቤቷ ዲሞቭ ከርሷ ጋር ይኖራል እንጂ እርሷ ከርሱ ጋር አትኖርም። ለማልቀስ ብዙ ሰብዓዊ ችግር ማግኘት የለባትም፣ ዝም ብላ በያአጋጣሚው ታለቅሳለች። ቅብጥብጥ ነች። የ25 ዓመት ወጣት፣ ቆንጆ ሰዓሊ፣ ከሆነው ከርያቦቭስኪይ ጋር የመሠረተችው ጸያፍ የፍቅር ግንኙነት ከደስታና ከሰላም ይልቅ ለጭንቀትና በየደቂቃው ለመከፋት ዳርጓታል። ባዲሱ ሰዓሊ ፍቅር እየተቃጠለች “ለእሱ (ለባለቤትዋ) ለተራውና ለተለመደው ዓይነት ሰው እስከዛሬ ድረስ ያገኘው ደስታ በቂ ነው። በቃ ያሉትን ይበሉ፣ ቢያሻቸው ያውግዙኝ፣ ይርገሙኝ፣ እኔ ደግሞ ለእልሁ ሁሉንም አደርገዋለሁ. . . አደርገውና እሞታለሁ. . . በሕይወት ውስጥ ሁሉንም መሞከር አስፈላጊ ነው!” የምትል “ጀግና” ሆናለች።

ምስኪኑ ዲማም እየተታለለ መሆኑ እየገባው ከመሄዱ የተነሣ “የህሊና ቁስል ያለበት ይመስል የባለቤቱን ዓይን በቀጥታ ፊት ለፊት ማየት አቃተው” ብዙ ሳይኖርም ከአንድ በሽተኛ “ሕፃን የጉሮሮ ተላላፊ በሽታን ሕዋስ በቱቦ መጥጦ” በሽታው ስተላለፈበት በጠና ታሞ ሞተ። ባለቤቱ ቅብጥብጧ ኢሻናቫና በባልዋ ላይ የምታካሄደው አመንዝራና ማጋጣነት በድብብቆሽ መጋረጃ ሊሸፈን ቢሞከርም ቅሉ በብዙ ባልና ሚስቶች የጋብቻ ሕይወት ውስጥ ያለ የሰው ተፈጥሯዊ እውነታ መሆኑን ነው ቼኮቭ ያሳየን።

ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ይህች አስተያየት ጽሁፍ የመጽሐፏን ጥራትና ደረጃ ከትርጉሙ አንጻር ለመገምገም ባይሆንም ስለትርጉም ስራው ጥያቄ  ማንሳት አስፈላጊ ሆኖ ይታየኛል። ወይዘሮ ትዕግሥት ትርጉሙን በተመለከተ “ለአንቶን ቼኮቭ ታማኝ በመሆን ከፃፈው ሳልቀንስም ሆነ ሳልጨምር ቃል በቃል ትርጉም የሚቻለኝን ሁሉ አድርጊያለሁ” ብላለች በመግቢያዋ ላይ። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ነጥብ ላነሳ እወዳለሁ። እንደሚታወቀው በትርጉም ሥራ ሁለት ዓይነት የታወቁ ዘዴዎች አሉ። አንደኛው ወ/ሮ ትዕግስት እንዳለችው የቃል በቃል ትርጉም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚተረጉመውን ጽሁፍ ወይም ንግግር ወስዶ ቁም ነገሩን በጥልቀት ከመረመሩት ከተረዱ በኋላ Adaptation በተባለው ጥበብ በራስ ባህላዊ የስነ ጽሁፍ ወይም የንግግር ስልትና ቋንቋ መተርጎም ነው። በተለይ ለልቦለዳዊ ስነጽሑፎች የሚመረጠው ይኸው የትርጉም ዘዴ ይመስለኛል። እኔ የሩስያኛን ቋንቋ ባለማወቄ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመከራከር የሚያበቃኝ አቋም ባይኖረኝም ትርጉሙ ይበልጥ Adaptation ነው ብዬ እንዳስብ ያደረጉኝን አንዳንድ ምሳሌዎች አነሳለሁ።

በገጽ 36 ዶ/ር ጂሞቭ (ዲማ) . .. “ሁለቱን ጣቶችን ቆርጫቸው ኖሯል። ልብ ያልኩት ቤት ከገባሁ በኋላ ነበር” ይላል። “ልብ ያልኩት” የሚለው አነጋገር ልብ አለ ከሚለው የመጣ ሲሆን ትርጉሙም አስተዋለ፣ አተኩሮ ተመለከተ ማለት ነው። ልብ አለ የሚለውን አነጋገር አስተዋለ ወይም አተኩሮ ተመለከተ ሲል የሚተረጎመው አማርኛ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ (1993) ነው። የአካሎቻችን ዋና አዛዥ አዕምሮ ሲሆን የአዕምሮን ሥራ ብዙውን ጊዜ ለልባችን የምንሰጥ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን።  ለምሳሌ ሳይኮሎጂ የተባለውን ሳይንሳዊ ቃል ስነ-አዕምሮ ወይም ስነ-ሕሊና ብለን በመተርጎም ፈንታ ስነ-ልቦና በማለት በሰፊው ሲነገር፣ ሲጻፍና ሲነበብ ይሰማል። እንግዲህ ጥያቄው “ልብ አለ” የሚለው አነጋገር በመጽሐፉዋ ውስጥ በተቀመጠው ትርጉም መሠረት በሩስያዊኛ ቋንቋ ቃል-በቃል አለ ወይስ በዘወርዋራ እሳቤ በአዳኘቴሽን ዘዴ ተተርጉሞ ነው የሚል ነው።

ዲማ አሁንም በዚያው ገጽ “የኔ ሆድ አሁንስ አልቀናህ አለኝ” ይላል “የኔ ሆድ” ና “አልቀናህ አለኝ” የሚሉት አነጋግሮችስ የቃል በቃል ትርጉሞች ናቸው ወይስ ለሩስያዊኛ አነጋገር ይቀርባሉ ተብለው የተወሰዱ ናቸው? ትርጉማቸው ይቀራረባል ተብለው የተወሰዱ ከሆኑ የአዳኘቴሽን ትርጉም ውጤት ነው የሚሆኑት። አንድ ሌላ ምሳሌ ልጥቀስ። በገጽ 113 አሊኺን የተባለው የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ አባቱ ለትምህርት ያወጣለትን ገንዘብ ለመክፈል ወደ ግብርና እንደገባ ሲናገር “አንድ ቁራሽ መሬት ጦም አላሳደርኩም” ይላል። ይህ አነጋገር ለኔ ፍፁም ኢትዮጵያዊ ምናልባትም ፍፁም አማርኛዊ ሆኖ ነው የሚሰማኝ። አሁንም የሚነሳው ጥያቄው ከላይ እንደተነሳው ስለሆነ ክርክሩን አልደግመውም። ይህን ነጥብ ያነሳሁት ስለ ትርጉም ሥራ እግረ መንገዳችንን ትንሽ እንድንነጋገር ነው እንጂ የመጽሐፉ ትርጉም የተዋጣለት መሆኑን ማስተባበል የሚቻል አይመስለኝም። ውብ ከመሆኑ የተነሳም “ቼኮቭ በአማርኛ ጽፎት ይሆን እንዴ?” የሚል አስተያየት ቢነሳም አያስገርምም።

ሌላው ስለመፅሐፉ ቅርጽ የማነሳው ነጥብ አለ። የመጽሐፉ ዲዛይን (ቅርጽ) ከፊት ሽፋኑ ይዘት ጀምሮ ከተለመደው ያገራችን መጻሕፍት ሕትመት ገጽታ ለየት ያለ ይመስላል። የሴት ወይዘሮዋ (የቅብጥብጧ) የተሽቀረቀረው ውብና ባህላዊ አለባበስ ፎቶግራፍና በገጹ ላይ የሰፈሩት የተለያዩ ቀለሞች አንድነትና ኅብረት የመጽሐፉን ውጫዊ ዕይታ ልዩ ውበት የሰጠውና አንባቢን እንዲስብ የሚያደርግ ይመስላል። ወደ ውስጥ ሲገባ ከወጎቹ የሕይወት እውነታን አንፀባራቂነትና ከቋንቋው ውበትና ጣፋጭነት ሌላ “በግርጌ ማስታወሻዎቹ፣” “በቼኮቭ አባባሎችና” “ማብራሪያ” በተባሉት ክፍሎች የተሰጡት ተጨማሪ መረጃዎች መጽሐፏን ትምህርታዊ አድርገዋታል ማለት ይቻላል። መጽሐፏን ያነበብነውንም ስለሩስያ እንዳገር፣ ስለሕዝቧ ታሪክ፣ ባህል፣ ወግና አኗኗር መጠነኛ ዕውቀት ሳናገኝ አልቀረንም።

በመፅሐፏ ጥሩነት ሳልዘናጋ አንድ ያልተቀበልኩትን ነጥብ በማንሳት አስተያየቱን እደመድማለሁ። በየገጹ ራስጌ ላይ ከደራሲው አንቶን ፓቪሎቪቶ ቼኮብ ስም ቀጥሎ “በትዕግሥት ፀዳለ-ኀሩይ” ይላል። ይህም ራሱ ጥሩ ትሩፋት ቢሆንም ከፊቱ “ትርጉም” በትዕግሥት ፀዳለ-ኅሩይ ባለማለቱ የደራሲውን የፈጠራ ችሎታና ተደናቂነት የሚሻማ ይመስላል። በተረፈ ቅብጥብጧ የተሳካ የረጅም ሥራ መቅድም ሆና ስለምትታየኝ የቼኮቭም ሆኑ የሌሎች ተደናቂ የሩስያ ድርሰቶች ትርጉም እንዲቀጥል ያለኝን ምኞት እገልጻለሁ።

   

ንባብ ለሕይወት

Wednesday, 26 July 2017 13:22

 

በጥበቡ በለጠ

 

ስለ ንባብ ምን ተባለ

-    “የኔ ምርጥ ጓደኛ ብዬ የምቀርበው ሰው ያላነበብኩትን መፀሐፍ “እንካ አንብብ” ብሎ የሚሰጠኝ ነው።” አብርሃም ሊንከን።

-    “ዘወትር ባነበብኩኝ ቁጥር ውስጤ የነበረውና ያለው ትልቁ የመቻል አቅም ይቀሰቀሳል።” ማልኮም ኤክሥ።

-    “ለአንድ ሰው መፅሐፍ ስትሸጥ የሸጥከው ብዙ ወረቀቶችን፣ የተፃፈበትን ቀለምና ጥራዙን አይደለም። ለርሱ የሸጥክለት ዋናው ነገር ሙሉ የሆነ አዲስ ህይወትን ነው።” ክርስቶፈር ሞርሌይ

-    “በዚህ ዘመን በየትኛውም ሁኔታ በጣም ግዜ የለኝም፣ እረፍት የለኝም ብለህ የምታስብ ቢሆን እንኳን ለማንበብ የግድ ግዜ መስጠት አለብህ። ይህን አላደረክም ማለት ግን በገዛ ፍላጎትህ ራስህን አላዋቂ እያደረከው ነው ማለት ነው።” ኮንፊሽየሥ

-    “መፅሐፍትን በሚገባ ማንበብ ማለት በድሮ ዘመን ይኖር ከነበረ በጣም አስተዋይ ሰው ጋር መወያየት ማለት ነው።” ሬኔ ዴካርቴሥ

-    “ማስቲካ ለማምረት ከምናወጣው ወጪ በላይ ለመፅሐፍቶች ብዙ ወጪን ባናወጣ ኖሮ ይህች ሀገራችን እንዲህ የሠለጠነችና የዘመነች አትሆንም ነበር።” አልበርት ሀባርድ (አሜሪካዊ)

-    “ከየትኛውም ነገር በላይ ትልቁንና ከፍተኛውን ደስታ የማገኘው ሳነብ ነው።” የፋሽን ዲዛይነሯ ቢልብላሥ

-    “መፅሐፍን ከማቃጠል የባሰ በርካታ ወንጀሎች አሉ። ከነዚህ መሃል መፅሐፍትን አለማንበብ አንዱ ትልቁ ወንጀል ነው።” ጆሴፍ ብሮድስኪ

-    “አላዋቂነትንና ችኩልነትን የምንዋጋበት ብቸኛው ወሳኝ መሣሪያ ማንበብ ነው።” ሌኖርድ ቤይንሥ ጆንሰን

-    “ዛሬ ያነበበ ነገ መሪ ይሆናል።” ማርጋሪት ፉለር

-    “መፅሐፍን የማያነብ ሠው ማንበብን ከነጭርሱ ከማይችል ሠው በምንም አይሻልም።” ማርክትዌይን

-    “አንድ መፅሐፍ ባነበብን ቁጥር እዚህ ምድር ላይ በሆነ ቦታ ለኛ አንድ በር እየተከፈተልን ነው።” ቬራናዛሪያን

-    “ማንበብ ከምንገምተው በላይ ዘላቂ የሆነ ደስታን ነው የሚሰጠን።” ላውራቡሽ

-    “አንድ ሠው ምን አይነት ማንነት እንዳለው ያነበባቸውን መፀሀፎች አይቶ መናገር ይቻላል።” ራልፍ ዋልዶ ኤመርሠን

-    “አንድ ባህል ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዳይተላለፍ ከተፈለገ መፀሀፎችን ማቃጠል አያስፈልግም። ይልቅ ሠዎቹ መፅሐፍ ማንበብን እንዲያቆሙ ማድረግ በቂ  ነው።” ራይ ብራድበሪ

-    “ለማንበብ ግዜ የለኝም ካልን ለማውራትና ለመፃፍ እንዴት ግዜ እናገኛለን?” ስቴቨን ኪንግ

-    “ህፃናት እንደሚያደርጉት ለመገረም ብለው መፅሐፍን አያንብቡ። ለመማርም ሆነ ህልመኛ ለመሆንም ፈልገው አያንብቡ። ይልቅ ለመኖር ሲሉ ነው ማንበብ ያለብዎት።” ጉስታቮ ፍላውበርት

-    “ከመናገርህ በፊት አስብ። ከማሠብህ በፊት አንብብ።” ፍራን ሌቦውትዝ

-    “አንተ ያላነበብከውን መፅሐፍ አንብብ ብለህ ለልጅህ አትስጠው።” ጆርጅ በርናንድ ሾው

-    “በአሁኑ ሰአት እየተቃጠሉ ካሉ መፅሐፍት በላይ የሚያሳስበኝ በአሁኑ ሰዓት እያልተነበቡ ያሉ መፀሀፎች ናቸው።” ጁዲ ብሉሜ

-    “ልጆቼ ወደፊት ሲያድጉ ማንበብ የሚወዱና ለእናታችን ትልቅ መፅሐፍ መደርደሬ እንስራላት ብለው የሚጨነቁ ቢሆኑ ደስታዬ ወደር አይኖረውም።” አና ክዊድሰን (የኒዮርክ ታይምስ ፀሃፊ)

-    “ከውሻ ውጪ የሠው ልጅ ታማኝ ወዳጅ መፅሐፍት ናቸው። ከውሻ ጋር ወዳጅ ስንሆን ግን የማንበብ እድላችን በጣም ያነሠ ነው።” ጉርቾ ማርክሥ

-    “መፅሐፍ ማለት በኪሳችን ይዘነው የምንዞረው በመልካም ፍሬዎች የተሞላ እርሻ ነው።” ቻይናውያን

-    “መፅሐፍ የሚያነቡ ሠዎች ብቸኝነት አያጠቃቸውም።” አጋታ ክርስቲ

-    “መፅሐፍ ማንበብ ነፍስን ያክማል።” በቴክሳስ ላይብረሪ መግቢያ ላይ የተፃፈ

-    “መፅሐፍ የሌለበት መምሪያ ቤት ማለት መስኮት የሌለበት ቤት ማለት ነው።” ሎነሬች ማን

-    “ከየትኛውም መዝናኛ በላይ እንደማንበብ ዋጋው ርካሽ ሆኖ በቀላሉ የሚያዝናና ነገር የለም። ደግሞም በማንበብ እንደሚገኘው ዘለቄታዊ ደስታ ሌሎች መዝናኛዎች ዘላቂ ደስታን አይሠጡም።” ሌዲ ሞንታኑ

-    “እኔ ዘወትር የማስበው በቀጣይ ስለማነበው መፅሐፍ ብቻ ነው።” ሮኦልድ ዳህል

 

 

የሀገር ውስጥ ሰዎች አባባል ስለንባብ

-    “ማንበብ የአአምሮ ምግብ ነው፤ ዋናው የአእምሮ ምግብ!”  ደራሲ ስዩም ገ/ህይወት

-    “ማንበብ ህይወትን የምንቀይርበት ትልቅ መሳሪያ ነው። ያለ ንባብ ህይወትን በአግባቡ መምራት አይቻልም።” አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው

-    “ማንበብ የእውቀት ብርሃን ነው። ስለዚህ ባነበብን ቁጥር ውስጣችንም ሆነ በዙሪያችን ያለው ውጫዊ ነገር በሙሉ በብርሃን የተሞላ ይሆናል።” ሰአሊ አንዷለም ሞገስ

-    “ሰው ምግብ ሳይበላ እንደማይውለው እኔም ሳላነብ አልውልም። ምክንያቱም ማንበቤ እኔን ከምንም ነገር በላይ ተጠቃሚ አድርጎኛል።” ሀይለልዑል ካሳ (የባንክ ባለሙያ)

-    “ንባብ ያልታከለበት ግንዛቤ ግልብ ያደርጋል።” ደራሲ በአሉ ግርማ

-    “መፅሐፍትን ማንበብ ታሪክህን በሚገባ እንድታውቅ ያደርግሀል። ታሪክህን ስታውቅ ደግሞ ራስህን ታውቃለህ።” አምባሳደር ዘውዴ ረታ

-    “በዚህች ጥንታዊ ሀገር መፅሐፍትን መፃፍ ብቻ ሳይሆን ማንበብ፣ ማስነበብ፣ ማስፃፍ፣ ሲነበቡ መስማት ጭምር የተከበረ ነገር ነበር።” ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

-    “ማንበብ በሁሉም ነገር ምልዑ ሆነን እንድንንቀሳቀስና ከግዜው ጋር አብረን እንድንራመድ ያስችለናል።” ፍቅር ተገኑ (የፀጉር ውበት ባለሙያ)

-    “ማንበብ እኮ ሁሉን ነገሮች ያንተ እንዲሆኑ ያደርጋል። ስታነብ ትዝናናለህ። ማንበብህን ተከትሎ ደግሞ ስለሁሉም ነገር ማወቅና መረዳት ትጀምራለህ።” ድምፃዊ ፀሃዬ ዮሀንስ

-    “ማንበብ ያልኖርነውን ትላንት ዛሬ ላይ መኖር እንድንችል ያደርጋል። ከዛ ካልኖርንበት ዘመን እንኳን ጓደኞች እንዲኖሩን፤ የነርሱንም ያህል ዘመኑን የኖርነው ያህል እንዲሰማን ያስችላል።”  ገጣሚናጋዜጠኛ ዳዊት አለሙ

-    “መፅሐፍ ያጣ አእምሮ፤ ውሃ ያጣ ተክል ማለት ነው። ሰው ራሱን አውቆና ችሎ እንዲኖር መፅሐፍ ማንበብ በእጅጉ ይጠቅማል።” መምህርንጉሴ ታደሰ መምህር

-    “ማንበብ ከባይተዋርነት ያድናል። ባነበብን ቁጥር በአለም ላይ ስላሉ ነገሮች ስንሰማም ሆነ ስናይ አዲስ አይሆንብንም። ወዳጆችን ለማፍራትም አንቸገርም። ማንበብ የሙሉነት መስፈርት ነውና።” ገጣሚና ጋዜጠኛ ፍርድያውቃል ንጉሴ

-    “ማንበብ አእምሮን አያስርብም። የሚያነብ ሰው ዘወትር ንቁና በአስተሳሰቡ የበለፀገ ነው።” ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)

-    “እውቀቴን ሁሉ ያገኘሁት በማንበብ ነው። በአጭሩ ማንበብ አዋቂ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ሰው ያደርጋል።” ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ

-    “ማንበብ ፍፁም ደስተኛ ያደርጋል። እስከዛሬ ባላነብ ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር? እያልኩ ዘወትር አስባለሁ።” ህዝቅያዝ ተፈራ (የህግ ባለሙያ)

-    “ማንበብ በጣም ያዝናናል። በየትኛውም ግዜ የሚወጡ መፅሐፍትን ማንበብ የሃሳብ ሀብታም ያደርጋል።” ተዋናይ ዋስይሁን በላይ

-    “እኔ ማታ ማታ አነባለሁ። ሁሌ አንብቤ ሳድር በጣም ደስተኛ ከመሆኔም በላይ የደንበኞቼን ባህርይ እንድረዳ ረድቶኛል።” ካሳሁን ፈየራ (የታክሲ ረዳት)

-    “ማንበብ በየትኛውም ነገር ላይ ተፈላጊውን ተፅዕኖ መፍጠር እንድትችል ያደርግሃል። ከሰዎች ጋርም በቀላሉ እንድትግባባ መንገዱን ይጠርግልሃል።” እድሉ ደረጀ (የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች)¾

እኔና ሃያሲው

Wednesday, 26 July 2017 13:19

 

በበኃይሉ ገ/እግዚአብሔር

 

ከዚህ በታች የቀረበው ግጥም ርዕስ ከንፈር መጠጣ ነው፤ በኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ውስጥ የመጀመሪያው አጭር እና የማይጻፍ ርዕስ ያለው ግጥም ይህ ይመስለኛል።

እምጭ (ከንፈር መጠጣ)

እመጫቷ

እጆቿን ዘርግታ፣

ልጆቿን አስጥታ፣

ከጠዋት እስከ ማታ፣

ትላለች፤

‹‹ወገኖቼ ስለ ልደታ!››

(ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም፤ ጠዋት 2፡00 ሰዓት ላይ አንዲት መንገድ ዳር ከልጆቿ ጋር ቁጭ ብላ የምትለምን ሴት አይቼ የጻፍኩት ግጥም)

ግጥም መጻፍ እወዳለሁ። ‹‹ግጥም ሙያ አይደለም፤ እጣ ፈንታ እንጂ!›› እንዲል ፈረንጅ ከልጅነቴ ጀምሮ አብሮኝ ያደገ ጥበብ ነው ግጥም። በተለይ ሲርበኝ ግጥም መጻፍ ደስ ይለኛል። እንደውም ከምግብ ይልቅ ሰውነት የሚሆነኝ እንጀራ ሳይሆን ግጥም መጻፍ ነው ብል ማጋነን አይሆንም።

በቅርቡ እናቴን እንዲህ አልኳት፤ ‹‹አንቺ እናቴ! እንጀራ በበርበሬ አማረኝ!›› እናቴም እንደ ማፈርም፣ እንደ መሳቀቅም ብላ፣ ‹‹ልጄ ሆይ! ዘንድሮ ተረት የሆነው ድኅነት ሳይሆን በርበሬ አይደለምን?›› አለችኝ፤ አዘንኩ። እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ ገጣሚ በጣም አዘንኩ። ወዲያው፣

‹‹ዋ! በርበሬ፤

አንተ በርበሬ፤

የእኛ ወዳጅ እስከ ዛሬ፤

ለምን ሆንክብን በሬ!?›› ብዬ ስንኞችን ከአእምሮዬ ጓዳ አውጥቼ ግጥም አሰናኘሁ። …በጥቅሉ ድህነት ወይም ረሃብ የኔ የግጥም ምንጮቼ ናቸው።

ከቀናት መካከል ባንዱ፤ ለአንዱ ሃያሲ የግጥም ሥራዎቼን ሰጠሁት፡ ‹‹አደከምከኝ!›› አለ መጀመሪያውኑ በደከመ ድምፅ። ‹‹ምን አደከመህ?›› አልኩት ውስጥን በሚመረምር የገጣሚ ዐይን እያየሁት። ‹‹ካንተ ጋር ግጥማቸውን እንዳይላቸው የጎበኙኝ ሰዎች በዙና ደከምኩ›› አለ በመታከት። ይባስ ብሎ፣ ‹‹ገጣሚያን በጣም በዙ። ይህ ከሆነ ገጣሚነት የተሰጥኦ ጉዳይ መሆኑ ቀረ ማለት ነው›› ብሎ ታላቅ ትካዜ ውስጥ ገባ። ተበሳጨሁ። ‹‹አንተ ሃያሲ ስለምን ትሆናለህ ከይሲ? ምድር በገጣሚያን ብትሞላ ጉዳቱ ምንድር ነው?›› ስልም ጠየቅኩት፤ መልስ ግን አልነበረውምና ዝም  አለ።

በሌላኛው ዕለት ደግሞ ወደ ሌላኛው ሃያሲ ዘንድ አቀናሁና ግጥሞቼን ሰጠሁት። ሃያሲው በጥሞና እንዳነበበው ሲነግረኝ ደስ አለኝ። ‹‹ርዕስ አወጣጥ ትችልበታለህ!›› አለኝ። በሆዴ፣ ‹‹ኧረ መግጠምም እችላለሁ›› እያልኩ ደስታዬን ተደሰትኩ።

ከግጥሞቼ መካከል ከፍተኛ ምናባዊነት የሚስተዋልበትን አንድ ግጥም አነሳና፣ ‹‹እዚህ ጋር ‹ልክ እንደ በረሸሽ ከውስጥ እንደሚሸሽ› ብለሃል፤ ለመሆኑ ‹በረሸሽ› የሚለው ቃል ትርጉም ምንድር ነው?›› አለኝ። ሳቄ መጣ። እውነቴን ነው የምለው ሳቄ መጣ። ከሃያሲ የማልጠብቀው ጥያቄ ነውና ከውስጠቴ የሚመጣውን ሳቅ መገደብ አልተቻለኝም። እንደገጣሚ የአስተውሎት ሳቅ ስቄ ስጨርስ፣ ‹‹ግጥሙ የሚለው ልክ እንደበረሸሽ ከውስጥ እንደሚሸሽ ነው አይደል?›› ስል ጠየቅኩት ሃያሲውን፤ ‹‹አዎን!›› አለ። ‹‹በቃ በረሸሽ ማለት በግጥሙ ውስጥ እንደተጠቀሰው ከውስጥ የሚሸሽ ነገር ማለት ነው›› ብዬ መለስኩ እየሳቅኩ። ወዲያው ይህን ከማለቴ አንድ ግጥም መጣልኝ።

‹‹ሳቄ መጣ

ከውስጠት የወጣ፤

ሳቄን ሳቅ ቢጠራው

ሳቄን ሳቅ አነቀው›› አልኩ።

የሃያሲው ትችት በዚህ አላቆመም፤ አንድ ወደ ጎን ባለብዙ ሐረግ ስንኝ፣ ወደታች በጣም ረዥም ግጥሜን አነሳና፣ ‹‹አሁን ይሄ ግጥም ፀጋዬ ቤት ነው ወይስ ፀጋዬ ኮንዶሚኒየም!?›› ብሎ ወረፈኝ። ተናደድኩ፤ በጣም ተናደድኩ ‹‹ቆይ የራሴን ቤት መፍጠር አልችልም!›› አልኩ እንባ እያነቀኝ። 

‹‹የሰቡ የአማርኛ ቃላትን መጠቀም ትወዳለህ። እሺ መጉነጥነጥ ምንድነው?›› አለኝ። አሁንም ተበሳጨሁ። ‹‹ደራሲ ቃላት ይመርጣል፤ ገጣሚ ቃላት ይፈጥራል ሲባል አልሰማህም!›› አልኩ ተቆጥቼ። ሃያሲው እየተበሳጨ ጥያቄውን ወደ ሌላ  አደረገ።

‹‹ውዴ ሆይ እስኪ እንንሸራሸር›› በሚል ርዕስ በጻፍከው ግጥም ውስጥ፣ ‹በቀለበት መንገድ እንጓዝ ተቃቅፈን› የሚል ስንኝ አንብቤያለሁ፤ ከግርጌው ላይ ደግሞ ‹1982› የሚል ዓመተ ምህረት ተጽፏል።››

‹‹አዎ! ግጥሙን የጻፍኩበት ዓ.ም ነው›› አልኩት አንድም ሳያስቀር በማንበቡ እየተደነቅኩ።

‹‹የቀለበት መንገዱ ግን ያን ጊዜ አልነበረም። ታዲያ አንተ ዓመተ ምሕረቱን ከየት አመጣኸው?›› አለኝ።

‹‹ምንድነው የሚለው ይኼ ሰውዬ?›› የሚያወራው ሁሉ ግጥሜ ሳይገባው ነውና በጣም ተናደድኩ። ‹‹ያልከው ሁሉ ትክክል ነው። የገጣሚ አገር ግን አዲስ አበባ ብቻ አይደለችም። ገጣሚ የትም ነው አገሩ። በግጥሙ ውስጥ የተጠቀሰው የቀለበት መንገድ በምናብ የፈጠርኩት እንጂ ይሄ ዲዛይኑ ላይ ቀለበት፤ ካለቀ በኋላ ማጭድ የሚመስለውን የአዲስ አበባ መንገድ አይደለም።›› ሃያሲው ይህ ንግግሬ የገባው አልመሰለኝም። በቸልታ እራሱን ነቅንቆ ወደ ሌላ ጥያቄ አመራ።

ከግጥሞቼ መካከል ‹‹እቃዬ ወደቀ›› በሚል ርዕስ የጻፍኩትን ቅኔ ለበስ ባለአራት ስንኝ ግጥም በሃያሲ ዐይኑ ትክ ብሎ እያየ፤ ‹‹እና ምን ይሁን?›› አለኝ። ‹‹ምኑ?›› አልኩት። ‹‹እቃው ስለወደቀ ምን ይፈጠር ብለኽ ነው ይህን የጻፍከው?›› አለኝ። በዚህ ጊዜ ፈገግ አልኩ እንደ ገጣሚ። ግጥሙን እስኪ አንብበው አለኝ። እንደሚከተለው አነበብኩለት። ያውም በቃሌ፤

እቃዬ ወደቀ

እጄ ላይ የነበረው እቃ፣

ተዘናግቼ ወሬዬን ስደቃ፤

ላንቃዬን ሳንቃቃ፣

ወደቀ በቃ።

‹‹ሰው የሰጠኝ ያማረ ብዕር ነበር። በጣም የምወደው። አንድ ቀን በእጄ ይዤው ከጓደኛዬ ጋር ሳወራ ወድቆ ተሰበረብኝ። ከዚያ ወዲያው ይህቺን ልብ የምትነካ ግጥም ጻፍ አደረግኳት!›› አልኩት ፈገግታዬን ሳልቀንስ። ከዚያም ሃያሲው በመርማሪው ዐይኑ እያየኝ፣ ‹‹ግጥም የቀውሶች ቋንቋ አይደለም!›› አለና ግጥሞቼን አፍንጫዬ ላይ ወርውሮልኝ ሄደ። በወቅቱ እንደ ሰው ተከፋሁ፤ እንደገጣሚ ግን በሃያሲው ድርጊት ደስ ተሰኘሁ። ሃያሲው ግጥሞቼ ገብተውት አስተያየት ቢሰጠኝ ኖሮ መልካም ቢሆንም ሂስ መቀበል የእንደኔ ዓይነቱ በሳል ገጣሚ ግዴታ ነውና ተቀበልኩ። አዎ! ሂስ ያሳድጋልና።

አለቃ ባሳዝነው፣ ‹‹አንዳንድ ቃላትና ፍቺዎቻቸው›› በሚለው አዲሱ መጽሐፋቸው ‹‹ሂስ›› የሚለውን ቃል እንዲህ ይፈቱታል። ‹‹ሂስስ… ሂ…ስስ፤ ሂድስ፤ ሄዛ፣ ሂድ ወደዛ፤ ሂ…ስ!››

 

Page 10 of 180

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us