You are here:መነሻ ገፅ»arts»ፀጋው መላኩ - Sendek NewsPaper
ፀጋው መላኩ

ፀጋው መላኩ

ከራስ ያለፈ በጎ ተግባር

Wednesday, 18 April 2018 12:50

 

በኢትዮጵያ ትምህርትን ለማዳረስ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎች መሰራታቸው ቢታወቅም ከትምህርት ጥራት አኳያ ግን አሁንም በርካታ ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን የሚያመላክቱ ብዙ ማሳያዎች አሉ። የትምህርት ጥራት ለመማር ማስተማር ከሚያስፈልጉ ቁሳዊ ግብዓቶች ጀምሮ እስከ መሰረተ ልማቶችና ሰብዓዊ ሀብትን ጭምር አጠቃሎ የያዘ ነው። ከሶስቱ የአንዱ መጓደል በትምህርት ጥራት ላይ የሚያመጣው ጉዳት ከፍተኛ ነው።

 

እኛም ከሰሞኑ በአዲስ አበባና በዱከም መካከል በምትገኝና አቃቂ ወረዳ ተብላ በምትጠራ የሚገኝን ኦዳ ነቤ የተባለ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በጎበኘንበት ወቅት የተመለከትነው ይህንን እውነታ ነው። የትምህርት ቤቱ ግንባታ የተከናወነው በ1997 ዓ.ም መሆኑን ከመምህራኑ ገለፃ መረዳት ችለናል።

 

አሁን ባለው ሁኔታ ትምህርት ቤቱ በቂ መማሪያ ክፍሎች የሉትም። የተገነባው በእንጨትና በጭቃ ሲሆን አንዳንዶቹ ክፍሎች የቆይታ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ይመስላል። የጭቃ ምርጊታቸው እየረገፈ ነው። የመዝመምና የመውደቅ አዝማሚያም ይታይባቸዋል። አንዳንዶቹ ክፍሎች እንደውም መጪውን ክረምት የሚሻገሩ አይመስሉም። በአካባቢው መብራትና ውሃ የማይታሰብ ነው። በቂ አጥርም የለውም።

 

ከትምህርት ቤቱ ግንባታ ከደረጃ በታች መሆን ባሻገር በውስጡም ቢሆን በቂ የማስተማሪያ ቁሳቁሶችንና ሌሎች ተጓዳኝ ግብዓቶችን ያሟላ አይደለም። የተማሪዎች ቤተመፃህፍት የለውም። ቤተሙከራ የማይታሰብ ነው። እንኳን ሌላ የተማሪዎች መቀመጫና ወንበር እንኳን በበቂ ሁኔታ የተሟላበት ሁኔታ የለም። የመምህራን ማረፊያ ክፍልንም በበቂ ሁኔታ ያሟላ አይደለም።

 

ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ሰዓት በሁለት ፈረቃ በጠቅላላው 360 ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑን ከመምህራኑ ገለፃ መረዳት ችለናል። ተማሪዎቹ የትምህርት አገልግሎቱን የሚያገኙት ከአንደኛ እስከ አራተኛ በመጀመሪያ ፈረቃ፤ ከዚያም ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ በሁለተኛው ፈረቃ ነው። ይህ እንዲሆን የተደረገው በቂ መማሪያ ክፍል እንደዚሁም መምህራን ባለመኖራቸው ነው። ተማሪዎቹ ከቀያቸው ወደ ትምህርት ቤቱ ለመድረስ በቀን እስከ ሁለት ሰዓት በእግራቸው መጓዝ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ከተደረገልን ገለፃ መረዳት ችለናል።

 

ይህ ትምህርት ቤቱ አሁን ያለበትን ደረጃ ለመለወጥ አንድ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ምሁር ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተመልክተናል። ምሁሩ ዶክተር ገዛኸኝ ሆርዶፋ ይባላሉ። ተውልደው ያደጉትና የልጅነት የትምህርት ጊዜያቸውን ያሳለፉት በዚያው ትምህር ቤቱ በሚገኝበት ኦዳ ነቤ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ሲሆን በጊዜው ከቀበሌው እስከ ዱከም ብሎም እስከ ደብረ ዘይት በእግራቸው በመጓዝ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩ መሆኑን ነግራውናል። ዶክተር ገዛኸኝ በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ስኮላርሺፕ አግኝተውተምረዋል። ከዚያም በሥራው ዓለም በተባበሩት መንግስታት የበጎ ፈቃደኛ ሰራተኛ ሆነው ስደተኞችን በልዩ ልዩ ድጋፎች ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ይህም አጋጣሚ በርካታ ሀገራትን የመመልከት እድሉን ፈጥሮላቸዋል። በአሁኑ ሰዓትም ነዋሪነታቸው በካናዳ ነው።

 

ዶክተር ገዛኸኝ በሥራቸው መሃል ወደ ሀገራቸው ሲመለሱም ለቤተሰባቸው ብሎም ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ እገዛዎችን ያደርጉ ነበር። ከእገዛዎቹም መካከል የታመሙ ሰዎችን ማሳከምና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በተለያዩ ጊዜያትም በርከት ያሉ የአካባቢው ሰዎች በራሳቸው ወጪ ህክምና እንዲያገኙ ያደረጉ መሆኑን ከእሳቸው ገለፃ መረዳት ችለናል።

 

በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ጉዳት ላይ የሚገኘውን የኦዳ ነቤ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትንም በራሳቸው ወጪ በማገዝ ላይ ናቸው። ቀደም ባሉት ጊዜያት ትምህርት ቤቱ የብረት መቀመጫ ዴስኮች እንዲኖረው አድርገዋል። ባሳለፍነው ቅዳሜም በቦታው በመገኘት ማልያና ታኬታ ጫማዎችን ባካተተ መልኩ የስፖርት ትጥቆችን፣ ኳሶችን፣ እንደዚሁም አጋዥ መፃህፍትን በልገሳ መልክ አበርክተዋል። በቀጣይም ለትምህርት ቤቱ የቤተ መፅሐፍት ህንፃን፣ ጤና ጣቢያን እና የውሃ ጉድጓድን ለማስቆፈር ከአካባቢው የስራ ኃላፊዎች ጋር በጋራ በመሆን የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል። በተቀመጠውም የፕሮጀክት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንባታዎቹ በሶስት ዓመታት ጊዜያት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል። ዶክተር ገዛኸኝ እንደ አካባቢው ተወላጅነታቸው የበጎ አድራጎት ሥራውን እያከናወኑ ያሉት በግላቸው ወጪ መሆኑን ገልፀው፤ ዋና አላማውም ለመሰል የልማት እገዛ በሌሎች አስተሳሰብ ውስጥ ተነሳሽነት እንዲፈጠር ማድረግ ነው። ዶክተር ገዛኸኝ ሌሎች በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በቻሉት ሁሉ መሰል እገዛን ቢያደርጉ ለሀገር ልማት በተለይም ለትምህርት ጥራት የራሳቸውን አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ መሆኑን በመግለፅ ጥሪያቸውንም አስተላለፈዋል።

 

በወረዳው ባሉ ትምህርት ቤቶች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡን የወረዳው የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጫላ ዳዲ በአቃቂ ወረዳ በአጠቃላይ 53 ትምህርት ቤቶች ያሉ መሆኑን ነግረውናል። ትምህርትን በማዳረሱ ረገድ አሁን ያሉት 53 ትምህርት ቤቶች የተደረሰውም ከሰባት ትምህርት ቤቶች በመነሳት ነው። ሆኖም ትምህርት ከማዳረስ ባሻገር በትምህርት ጥራት ደረጃ በአካባቢው ብዙ የሚቀር ነገር መኖሩን አቶ ጫላ አመልክተዋል። እንደሳቸው ገለፃ በወረዳው ካሉት 53 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተገቢውን የጥራት ደረጃ የሚያሟሉት አራቱ ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው። ኦዳ ነቤ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ ቀሪዎቹ 49 ትምህርት ቤቶች ከጥራት አኳያ ሲታዩ ከደረጃ በታች ናቸው።

 

የህዝብ ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው፤ በዚህ ረገድ ወረዳው ሊሰራቸው ካሰባቸው ስራዎች መካከልም አንዱ ዲያስፖራውን ጨምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ የድጋፍ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥረት ማድረግ ነው።¾

 

በአበበ ድንቁ የውሃ እና ከአልኮል ነፃ የመጠጥ ኢንዱስትሪ  የሚመረተው ቶፕ የታሸገ ውሃ ገበያውን የተቀላቀለ መሆኑን ሚያዚያ 4 ቀን 2010 ዓ.ም በኢሊሌ  ኢንተርናሸናል ሆቴል በተካሄደው የምርት ማብሰሪያ ሥነ ሥርዓት ይፋ ሆኗል። የማምረቻ ድርጅቱም ከአዲስ አበባ ምዕራብ አቅጣጫ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ታጠቅ ገፈርሳ ቡራዩ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል። በሰዓት 18 ሺህ የታሸገ ውሃ የሚያመርት ሲሆን በምርቱም ባለ ሀያ ሊትርን ጨምሮ በአራት አይነት የይዘት መጠን ተመርቶ የታሸገ ውሃን የሚያቀርብ መሆኑን ጋዜጣዊ መግለጫው ያመለክታል።

 

ቶፕ ውሃ ከሌሎች የውሃ ማምረቻ ፋብሪካዎች በተለየ ሁኔታ የውሃ ማሸጊያ ላስቲኩን መልሶ ለመጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂን ስራ ላይ ያዋለ መሆኑን በዕለቱ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ተመልክቷል። ይህም ጥቅም ላይ በዋሉ የታሸገ ውሃ ፕላስቲኮች አማካኝነት የሚደርሰውን አካባቢያዊ ብክለት ለመቀነስ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል ተብሏል። ኩባንያው አሁን ካለው የታሸገ ውሃ ማምረቻ በተጨማሪ በሰዓት 24 ሺህ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ማሸግ የሚያስችለውን ተጨማሪ የማሽን ተከላንም እያከናወነም ነው ተብሏል። በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ያለውን የታሸገ ውሃ ገበያ ለመቀላቀል ሰባት ኩባንያዎች በዝግጅት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

 

ድርጅቱ 740 ሺህ የፕላስቲክ ጠርሙስ ውሃን አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ያቀደ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከእያንዳንዱ የታሸገ ውሃ ሽያጭ ሁለት ሳንቲም በመሰብሰብ ውሃ ባለደረሰባቸው የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጉድጓድን አስቆፍሮ ንፁህ የመጠጥ ውሃን ለማዳረስ በዕቅድ እየሰራ መሆኑን የሥራ ኃላፊዎች አመልክተዋል። በዚህም ኩባንያው በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ሶስት መቶ ሰላሳ አራት ሺህ ብር በላይ ለዚሁ ተግባር ለማዋል ያሰበ መሆኑ ታውቋል።

 

ኢትዮጵያ የ1 ነጥብ 66 ቢሊዮን ዶላር የዕርዳታ ጥያቄ አቀረበች፡፡ የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ አጠቃላይ የሰብአዊ እርዳታ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከሆነ ይህ የዕርዳታ ገንዘብ የሚያስፈለገው 7 ነጥብ 9 የሚሆኑ ዜጎችን በምግብ አቅርቦት ለመደገፍ ነው፡፡ ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው ከሆነ የእርዳታ እገዛ ከሚያስፈልጋቸው ዜጎች መካከል በተለያዩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ይገኙበታል፡፡


በሞያሌ በተፈጠረው ግድያ አስር ሺ የሚሆኑ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ወደ ኬኒያ የተሰደዱ ሲሆን የኬኒያ ቀይ መስቀልም እርዳታ እያቀረበላቸው መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የኢትዮጵያን መንግስት ዋቢ ያደረገው ይሄው መረጃ ወደ ኬኒያ የተሰደዱት ዜጎች በመመለስ ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም እነዚህን ዜጎች ለማቋቋም እገዛን ይጠይቃል ተብሏል፡፡


የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን የዕርዳታ ጥሪ ያቀረበው ለግብርና ሥራ፣ ለከብት እርባታ፣ ለትምህርት፣ ለአስቸኳይ መጠለያዎች ግንባታ፣ ለጤና አገልግሎት የሚውል መሆኑ ታውቋል፡፡ እድርዳታና እገዛ ከሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካልም ግማሽ ያህሉ ህፃናት መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የህፃናት ፈንድ መረጃ ያመለክታል፡፡


እገዛ የሚያስፈልጋቸው በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ከተነሱት ግጭቶች ጋር ለተፈናቀሉ ወገኖች ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ከጎረቤቶቿ ለተቀበለቻቸው ስደተኞችም ጭምር መሆኑ ታውቋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ከተለያዩ የጎረቤት ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ገብተው የተጠለሉ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች መኖራቸውንና ስደተኞቹም በዋነኝነት ከደቡብ ሱዳን እና ከኤርትራ የሚገቡ መሆናቸውን የሪሊፍ ድረ ገጽ መረጃ ያመለክታል፡፡● ሌላ የድርድር ቀነ ቀጠሮ ተይዟል

 

በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ከሰሞኑ በካርቱም ሲያደርጉት የነበረው ስብሰባ ያለውጤት የተበተነ መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ሲደረግ የነበረው ይኸው ውይይት በመጨረሻ ያለውጤት መበተኑን የሱዳኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋቢ ያደረገው የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ያመለክታል፡፡ የውይይቱ ዋነኛ ጭብጥ ግድቡ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ሊኖረው በሚችለው ተፅዕኖ፤ እንደዚሁም በግድቡ ውሃ አሞላል ዙሪያ መሆኑን ከዚያው ከካርቱም የወጣው ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል፡፡ እንድ ግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሹክሪ ገለፃ ከሆነ አሁን ያለስምምነት የተበተነው ውይይት፤ ድርድሩ ባበቃበት በሰላሳ ቀናት ውስጥ በድጋሜ ይጀመራል፡፡ ይህ የአሁኑ የሶስትዮሽ ድርድር ሊካሄድ የነበረው በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ የነበረ ሲሆን፤ ይሁንና በኢትዮጵያ የተከሰተውን የፖለቲካ አለመረጋት ተከትሎ በኢትዮጵያ ጠያቂነት ጊዜው ሊራዘም ችሏል፡፡


የድርድሩ ተሳታፊዎች ከሆኑት መካከል የውሃና የመስኖ ሚኒስትሮች የሚገኙበት ሲሆን ከድርድሩ አለመሳካት በኋላ ስምምነት ያልተደረሰባቸው ዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮች በጥልቀት ለመመልከትና ቀጣዩን ድርድር ለማቅለል የሶስቱም ሀገራት አቻ የውሃና የመስኖ ሚኒስትሮች የሶስትዮሽ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ በዚህ ውይይት ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንደዚሁም ከውሃና መስኖ ሚኒስትሮች ባሻገር የየሀገራቱ የደህንነትና የፀጥታ ኃይሎች የተገኙ መሆኑን ዘገባዎች ጨምረው ያመለክታሉ፡፡ የግድቡን የውሃ አሞላል ሂደት በተመለከተ ኢትዮጵያ ጠንካራ አቋም ይዛ የቀረበች መሆኗን የአልሞኒተር ዘገባ ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያን ተደራዳሪ ቡድን የመሩት አቶ ጌዲዮን አስፋውን ዋቢ በማድረግ የግድቡን የውሃ አሞላል ሂደት በተመለከተ ኢትዮጵያ ለግብፅ ግልፅ ደብዳቤ ቀደም ብላ የላከች መሆኗን ያመለከተው አልሞኒተር፤ በዚህም ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ የምታከናውነው ሥራ የማታቆም መሆኗን ኃላፊውን በመጥቀስ አመልክቷል፡፡


ግብፅ ህዳሴውን ግድብ በተመለከተ የዛሬ ሶስት ዓመት በሶስቱ ሀገራት መሪዎች በተፈረመው “የመርሆ መግለጫ” አተገባበር ላይ ቁርጠኛ አቋም ያላት መሆኑን በመግለፅ፤ ድርድሩም በዚሁ መንፈስ ይመራል የሚል አቋም ያላት መሆኑን ገልፃለች፡፡ አንዳንድ የግብፅ ምሁራን በህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ዙሪያ ሊፈጠር በሚችለው የውሃ እጥረት ግብፅ ጉዳት የሚደርስባት ከሆነ ኢትዮጵያ ካሳ የምትከፍልበት ሁኔታ እንዲኖር በመወትወት ላይ መሆናቸውን ዘገባዎች እያመለከቱ ነው፡፡


ቻይና እና አሜሪካ የገቡበትን የንግድ እሰጣ ገባ ተከትሎ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ፒ ግ ውጥረቱን ሊያረግብ የሚችል ንግግር አደረጉ፡፡ ፕሬዝዳንቱ በዚያው በቻይና እየተካሄደ ባለው የቢዝነስ ኮንፍረንስ ላይ እንደገለፁት፤ ቻይና ኢኮኖሚዋን የበለጠ ክፍት በማድረግ ከቀሪው ዓለም ጋር በጋራ የምትሰራ መሆኗን አሰታውቀዋል፡፡ “ቻይና ለበርካታ ዓለም አቀፍ የንግድ ህጎች አትገዛም፣ቴክኖሎጂዎችን የባለቤትነት መብትን ሳታከብር አባዝታ ለገበያ ታውላለች፣ ገበያዋን በተገቢው መንገድ ክፍት አታደርግም” በሚልና በመሳሰሉት በአሜሪካ በኩል ክስ ሲቀርብባት ቆይቷል፡፡ ይህ ውዝግብ ተካሮ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በወሰዱት እርምጃ በበርካታ የቻይና ምርቶች ላይ የገቢ ምርት ታሪፍ እስከመጣል መድረሳቸው የሚታወስ ነው፡፡

 

ቻይናም በአሜሪካ ገቢ ምርቶች ላይ ተመሳሳይ እርምጃዎችን በመውሰድ ውጥረቱ የበለጠ እንዲባባስ እስከማድረግ ደርሳ ነበር፡፡ ሆኖም ከሰሞኑ ፕሬዝዳንቱ ያደረጉት ንግግር ቻይና በያዘችው አቋም እንደማጥቀጥል የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡ እንደ ኤቢሲ ኒውስ ዘገባ ከሆነ፤ ፕሬዝዳንቱ “ቻይና በሯን አትዘጋም እንደውም የበለጠ እያሰፋች ትሄዳለች” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የቻይና እና የአሜሪካ የንግድ ውዝግብ የበለጠ ውጥረት ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ ቻይና በውጭ ተሽከርካሪዎች ላይ የያዘችው ጠንካራ አቋም ነው፡፡


ሀገሪቱ የውጭ ባለሀብቶች ከቻይና መኪና አምራች ኩባንያዎች ጋር በሽርክና እንዳይሰሩ ብዙም ፍላጎት የሌላት ከመሆኑም ባሻገር በገቢ ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለችው ታሪፍም ቢሆን ሌላኛው የአለመግባባቱ መንስኤ ነው፡፡ በዚህም የቻይና መንግስት በሁለቱም አቅጣጫዎች ይዟቸው የነበሩትን አቋሞች የቀየረ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡ ትራምፕ ከቀደሙት አስተዳደሮች በተለየ ሁኔታ በቻይና የንግድ ግንኙነት ላይ በወሰዱት እርምጃ እስከ 50 ቢሊዮን በሚደርሱ የቻይና ልዩ ልዩ ሸቀጦች ላይ ታሪፍ እንዲጣል ማድረጋቸውን ተከትሎ ቻይናም አፀፋዊ እርምጃን ውስዳለች፡፡


ሆኖም ይህ የሁለቱ ግዙፍ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሀገራት እርምጃ በሁለቱንም ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖን እንደሚያሳድር የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም ቻይና ውዝግቡን የበለጠ ከማጦዝ ይልቅ ነገሩን እያቀለሉ መሄዱን የመረጠች መሆኑን የኤቢሲ ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል፡፡ የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ውዝግብ በአለም አቀፉ የንግድ እንቅስቃሴም ላይ የራሱን የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖን በማሳደር ላይ ነው፡፡ ውዝግቡ እየተካረረ መሄዱን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ የመጨመር አዝማሚያ እንደዚሁም የአክስዮን ገበያዎች የመቀነስ ሁኔታ ታይቶባቸው ነበር፡፡ ሆኖም ከፕሬዝዳንቱ ንግግር በኋላ በተፈጠሩት ተስፋዎች በሁለቱም ገበያዎች የመረጋጋት አዝማሚያ መታየቱን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ዶክተር አቢይ አህመድ ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያደረጉትን ጉዞ በተመለከተ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሰፋ ያለ ሽፋን ሰጥተውታል።

 

አልጀዚራ የዶክተር አቢይን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መሾም አስመልክቶ ባሰራጨው ዘገባ ጠ/ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ 16ኛው ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን አመልክቷል። በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሳውን ህዝባዊ አመፅ ተከትሎ በርካቶች ለህልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን ያመለከተው ይኸው ዘገባ፤ ከዚሁ ህዝባዊ አመፅ ጋር በተያያዘም አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን የለቀቁበት ሁኔታ መፈጠሩን አስታውሷል። ህዝባዊ አመፁም በመጀመሪያ በመሬት መብት ጉዳይ ተጀምሮ በሂደት አድማሱን በማስፋት በብሄራዊ ደረጃ ሰፊ የፖለቲካ ውክልና ጥያቄን ያነሳ ቢሆንም በመንግስት በኩል የተሰጠው ምላሽ ግን የከፋ እንደነበር ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል።


አልጀዚራ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በውትድርናው ዘርፍ እስከ ሌተናንት ኮሎኔልነት ደረጃ የደረሱ መሆኑን ገልፆ፤ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሏቸውንም ልምዶች በመጠኑም ቢሆን ለመዘርዘር ሞክሯል። አልጀዚራ ዘገባውን ሰፋ በማድረግ የአስተያየት ሰጪዎችንም ሀሳብ አካቷል። ከእነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች መካከል በዩኒቨርስቲ ኦፍ ለንደን ስኩል ኦፍ ኦሪየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲሰ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አህመድ አደም ይገኙበታል።


ተባባሪ ፕሮፌሰሩ የዶ/ር አቢይን መመረጥ በተስፋ የሚያዩት መሆኑን ገልፀዋል። ንግግራቸውን በመቀጠልም “ ይህ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ብሎም ለገዢው ግንባር ታሪካዊ አጋጣሚ ነው። አቢይ የመጀመሪያው የኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው። የእሱ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መምጣት ለሀገሪቱ መረጋጋትና አንድነት መንገድ ጠራጊ ነው።” በማለት ከተናገሩ በኋላ በመቀጠልም “አቢይ ከክርስቲያን እናት፣ ከሙስሊም አባት የተገኘ የለውጥ አቀንቃኝ ነው” ነው ብለውታል።


ዶክተር መረራ ጉዲና በዚሁ የአልጀዚራ ዘገባ አስተያየታቸውን የሰጡ ሰው ናቸው። እሳቸው በአስተያየታቸው የዶክተር አቢይን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መምጣት በጥርጣሬ የሚያዩት መሆኑን ገልፀዋል። ዶክተር መረራ ሲናገሩም “ አቢይ እኮ የተመረጠው በገዢው ፓርቲ እንጂ በቀጥታ በኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም። የሚያከናውነውም ሥራም ፓርቲው ባስቀመጠለት መስመር የሚወሰን እንጂ በራሱ የሚያደርገው ነገር የለም” ብለዋል


ሌላኛው የዶክተር አቢይን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መምጣት አስመልክቶ ሽፋን የሰጠው ሲኤንኤን ነው። ሲኤን ኤን በዚሁ ዘገባው ዶክተር አቢይ አንድ መቶ ሚሊዮን ከሚጠጋው የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ አንድ ሶስተኛን ክፍል ከሚይዘው የኦሮሞ ብሄረሰብ የተገኙ መሆኑን አመልክቷል። የአቢይ ወደ ሥልጣን መምጣትም በሀገሪቱ የሚታየውን መከፋፈል ለማርገብ የሚደረግ ሙከራ አድርጎ ዘግቦታል።


ፍራንሰ 24 ወጣትና አንደበተ ርቱው በማለት በማለት ዶክተር አቢይን አሞካሽቷል።


ዶክተር አቢይ በኢህአዴግ ምክርቤት የግንባሩ ሊቀመንበር መሆናቸው ከታወቀ ጀምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን አግኝተዋል። የአብዛኞቹ ዘገባም የእሳቸው ወደ ሥልጣን መምጣት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየደፈረሰ የመጣውን የሀገሪቱን ሰላም ለመመለስ የሚረዳ መሆኑን የሚገልፅ ነው።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአባላት ጥያቄ መሠረት አምስት የመደበኛ አባልነት መቀመጫዎችን ለመሸጥ ለአራተኛ ጊዜ በምርት ገበያው ዋና መስሪያ ቤት ባካሄደው ጨረታ እስከ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የጨረታ ዋጋ ላቀረቡ ተጫራቾች የአባልነት መቀመጫዎች የተሸጡ መሆኑን ድርጅቱ የላከልን ጋዜጣዊ መግለጫ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የአባልነት መቀመጫዎችን እንዲሸጥላቸው ለሚጠይቁ አባላት በየሩብ ዓመቱ ጨረታ በማውጣት የሚሸጥ ሲሆን ይህ ሽያጭም በዚህ መሰረት የተከናወነ መሆኑ ታውቋል። በዚህ ጨረታ ላይ አምስት ተጫራቾች የምርት ገበያውን የአባልነት ወንበር ለመግዛት ዋጋ ያቀረቡ ሲሆን ለጨረታ የቀረበው ከፍተኛው ዋጋ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፤ ዝቅተኛው ደግሞ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል። ምርት ገበያው ሥራውን በጀመረበት ወቅት አንድ የአባልነት መቀመጫ በ50,000 ብር ይሸጥ ነበር። ለአባልነት ወንበር ለጨረታ የቀረበው ከፍተኛ ገንዘብ ካለፈው ጋር ሲነፃፀር የ787 ሺህ ብር ብልጫ እንዳሳየ ይሄው መረጃ ያመለክታል።


የኢትዮጵያ ምርት ገበያው 347 አባላት አሉት። የአባልነት መቀመጫ ማንኛውም ህጋዊ ሰው ወይም ድርጅት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመገበያየት መብት የሚሰጥ ሲሆን ይህም የመገበያያ መቀመጫ ሁለት አይነት የአባልነት መደቦች አሉት። እነዚህም ተገበያይና አገናኝ አባል በመባል ይታወቃሉ። ተገበያይ አባል የሚገበያየው በራሱ ስም ብቻ ሲሆን አገናኝ አባል ደግሞ በራሱ ወይም በደንበኞች ስም መገበያየት የሚያስችል የአባልነት አይነት ነው። ደንበኛ ማለት ማንኛውም ህጋዊ ሰው ወይም ድርጅት በአገናኝ አባላት በኩል በምርት ገበያው የሚገበያይ ማለት ነው።


መደበኛ ተገበያይ አባላት እና አገናኝ አባላት የአባልነት መቀመጫቸውን በምርት ገበያው ተቀባይነት ላገኘ ሰው ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ ይሄው መረጃ ጨምሮ ያመለክታል። የአባልነት መቀመጫውን የሚያስተላልፍ አባል አስፈላጊውን እውቅና ካገኘ በኋላ ቢያንስ ለሶስት ዓመታት በምርት ገበያው አባልነት የመቆየትና በምርት ገበያው ደንብ የተቀመጡ ሌሎች መስፈርቶችን ማሟላት ይጠበቅበታል። ምርት ገበያው አምስተኛውን የአባልነት መቀመጫ የጨረታ ሽያጭ በቅርቡ የሚያካሂድ መሆኑ ታውቋል።

ግብፅ በውሃ እጥረት ሥጋት ዙሪያ በርካታ ምሁራንን ጠርታ አወያየች፡፡

በዚሁ በግብፅ መንግስት በተጠራው ሀገር አቀፍ የምሁራን ኮንፍረንስ ግብፅ አሁን ያላትን የውሃ ፍላጎት መጠን በምን መልኩ ማሳደግ እንዳለባት ሰፊ ውይይት የተደረገ መሆኑን የአልሞኒተር ዘገባ ያመለክታል፡፡


እንደዘገባው ከሆነ በዚሁ መፍተሄ አፈላላጊ አገር አቀፍ ኮንፍረንስ ላይ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ግብፃዊያን ሳይንሲስቶች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በዚሁ ኮንፍረንስ ግብፅ ሊኖራት በሚችለው የውሃ አማራጮች ዙሪያ፣በሀገሪቱ የውሃ ደህንነትና ውሃን መልሶ መጠቀም በሚቻልባቸው ዘዴዎች ዙሪያ በሰፊው የተመከረበት መሆኑ ታውቋል፡፡ በሰፊው የኮንፍረንሱ ውይይት ላይ ሀገሪቱ ካላት የውሃ ሀብት ውስጥ 97 በመቶ የሚሆነው ከግዛቷ ውጪ ከሌሎች ሀገራት የሚገባ መሆኑም በስጋትነት ተነስቷል፡፡


ሀገሪቱ አለባት የተባለው የውሃ እጥረትና ቀጣይ ፈተና በሰፊው በዚሁ ውይይት ከተዳሰሰ በኋላ መፍትሄዎችም ጭምር የተቀመጡ መሆኑን ይሄው የአልሞኒተር ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል፡፡ በዚሁ የመፍትሄ ሀሳብም ችግሩን ለመቅረፍ የግብፅ ህዝብ ውሃን በቁጠባ እንዲጠቀም ግንዛቤን መፍጠር፣ የባህር ውሃን በቴክኖሎጂ አጣርቶ መጠቀምና ውሃ ነክ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች ይበልጥ ማዳበር በዋነኝነት ተቀምጠዋል፡፡


ግብፅ እ.ኤ.አ በ1959 ኢትዮጵያን ባገለለ መልኩ ከአባይ ውሃ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን የውሃ ድርሻን ለመጠቀም የደረሰችበት ሥምምነት የሀገሪቱ ህዝብ 25 ሚሊዮን በነበረበት ወቅት መሆኑን በመግለፅ ዛሬ የህዘቡ ቁጥር በብዙ እጥፍ የጨመረ በመሆኑ ተጨማሪ የውሃ ሀብት የሚያስፈልግ መሆኑ በዚሁ ኮንፍረንስ ላይ የተመለከተ መሆኑ ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡


ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልጋት ዓመታዊ የውሃ መጠን 76 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ መሆኑ ያመለከተው ይሄው ዘገባ፤ በዚህ ሥሌት ከተሄደም የውሃ ፍላጎትና አቅርቦት ልዩነቱ 21 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መሆኑ ጨምሮ አትቷል፡፡ አንዳንዶች ግብፅ ከፍተኛ የሆነ የከርሰ ምድር ያላት መሆኑን በመግለፅ መንግስት የውሃ እጥረት እንዳለና ችግሩ ወደፊትም እንደሚባባስ የሚገልፅበት መንገድ የራሱ ፖለቲካ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

 

የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በቅርቡ በሩዋንዳ ኪጋሊ ባደረጉት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ 44 ሀገራት የነፃ ገበያ ቀጠናን ለማቋቋም ስምምነት ፈርመዋል። በአህጉሪቱ 54 ሀገራት የሚገኙ ሲሆን በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚን ያንቀሳቅሳሉ ተብለው ከሚጠቀሱት ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችውን ናይጄሪያን ጨምሮ አስር ሀገራት ስምምነቱን አልፈረሙም።


ኢትዮጵያም ስምምነቱን በመቀበል ፊርማዋን አኑራለች። ይሄው የአፍሪካ አህጉር ነፃ የንግድ ቀጠና (African Continental Free Trade Area) ተብሎ የሚጠቀሰው አህጉር አቀፍ ነፃ የንግድ ሥርዓት በዋነኝነት በሀገራት መካከል የተሳለጠ የንግድ ግንኙነት እንዳይኖር የሚያደርጉትን መሰናክሎች ያስወግዳል ተብሏል። በዚህም የፊርማው አካል የሆኑ ሀገራት በስምምነቱ መሰረት በገቢ በአፍሪካዊያኑ ሀገራት ገቢ ሸቀጦች ላይ የሚጥሏቸው ምንም አይነት የጉምሩክ ታሪፎች አይኖርም ማለት ነው። እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ የአፍሪካ ሀገራት እርስ በእርስ የሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ከአስር በመቶ አይበልጥም።


የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ በአንፃሩ 25 በመቶ የደረሰ መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል። እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ ይህ ሰፊ የንግድ ቀጠና እውን የሚሆን ከሆነ ለ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን አፍሪካዊያን የተሻለ ህይወትና ብልፅግናን ያመጣል። ይህ የአሁኑ የአፈሪካዊያን የነፃ ገበያ ቀጠና በቀጣይ ህብረቱ ለመሄድ ያሰበባቸውን በርካታ መንገዶች አመላካች ነው ተብሏል። ከእነዚህም ቀጣይ ተግባራት መካከል አንዱ የህብረቱ አባል ሀገራት አንድ አይነት መገበያያ ገንዘብን እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው።


የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጠናን ለማቋቋም 44 ሀገራት ፊርማቸውን ቢያኖሩም ስምምነቱን እውን በማድረጉ ረገድ ግን ከባድ ፈተናዎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከእነዚህም ፈተናዎች መካከል አንዱ ሀገራቱን እርስ በእርስ የሚያገናኝ እንደ መንገድና ባቡር ያሉ መሰረተ ልማት አለመኖራቸው ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሀገራት ያላቸው የምርት አይነት ተመሳሳይነት የሚታይበት መሆኑ፣ እንደዚሁም ሀገራቱ ምርቶችን የሚያመርቱበት ሂደት ኋላቀር መሆኑ ሌላኛው ምክንያት የንግድ እንቅፋት ተደርጎ ይጠቀሳል። ምርቶቹ ከሌሎች ከአህጉሪቱ ውጪ ካሉ ሀገራት አንፃር ሲታይ በውድ የአመራረት ዘዴ መመረታቸው የአፍሪካ ሀገራት እርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ ከማድረግ ይልቅ እንደ ቻይና እና ሌሎች መሰል ሀገራት ጋር የበለጠ የንግድ ትስስር እንዲኖራቸው ያደርጋል። ይህም ሁኔታ አፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናን ከመመስረቷ ቀደም ብሎ የአመራረት ቴክኖሎጂዋን ማሻሻል ይገባት ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ።


የጋራ ገበያን ለመፍጠር አህጉራዊ ትስስርን ለማምጣት የሚያስችሉ በርካታ የጋራ መሰረተ ልማቶች መገንባት ግድ ይላቸዋል። ሆኖም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ይህ የልማት ትስስር በአፍሪካ የለም። ይህንን ሁኔታ የተመለከቱ የኢኮኖሚ ተንታኞች የአሁኑ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችን የጋራ የንግድ ቀጠና ሥምምነት “ከፈረሱ ጋሪው” የሚል ትችትን እንዲያቀርቡ እያደረጋቸው ነው።

ኢትዮጵያና የንግድ ሥምምነቱ ሁኔታ


ይህንን ግዙፍ ኢኮኖሚን የሚፈጥር ነፃ የአፍሪካ የንግድ ቀጠናን ለማቋቋም ፊርማቸውን ካስቀመጡት ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ ይህንን ፊርማዋን ስታስቀመጥ በእድልም በስጋትም የሚታይበት ሁኔታ አለ። እንደ መልካም እድል ተደርገው ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ነፃውን ገበያ መቀላቀል በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሀብቶች ሰፊ የገበያ መዳረሻ እድልን የሚፈጥር መሆኑ ነው። እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ ይህ ከግብፅ ካይሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን የሚዘረጋው ሰፊና ግዙፍ ነፃ የንግድ ቀጠና 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ሰዎችን በስሩ የሚያቀፍ በመሆኑ እጅግ ሰፊ የገበያ መዳረሻ የሚሆን ነው።


የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ዋና ፀሃፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ ይሄንን ሀሳብ ይጋራሉ። ሰፊ ገበያን መፍጠሩ ያንን ገበያ ለመጠቀም የሚፈልጉ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያበረታታ መሆኑን ይገልፃሉ። በዚህም በአፍሪካ ግዙፍ ገበያ መኖሩን ይጠቅሳሉ። ኢትዮጵያን በተመለከተም አቶ እንዳልካቸው የአምራች ኢንዱስትሪዋ ካለው ውስን አቅም አንፃር በተወዳዳሪነቱ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። ኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪውን የበለጠ ለማጠናከርና ተወዳዳሪ ለማድረግ ኢንዱስትሪ ፓርኮችንና መሰረተ ልማቶች እየገነባች መሆኑን የገለፁት አቶ እንዳልካቸው፤ በነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ግን በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በርካታ ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎች መኖራቸውን ገልፀውልናል። ከዚህ አንፃርም አሁን በአፍሪካ ሀገራት መካከል የተደረሰውን ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት እንደ መልካም አጋጣሚም እንደዚሁም እንደ ስጋትም የሚያዩት መሆኑን ገልፀዋል። ሆኖም ሀገሪቱ እድሉን በአግባቡ መጠቀም የምትችልበትን አሰራር መፍጠር ከቻለች ግን ከስጋቱ ይልቅ መልካም አጋጣሚው የሚያመዝን መሆኑን አቶ እንዳልካቸው ጨምረው አመልክተዋል። የንግድ ሚኒስትሩ ዶክተር በቀለ ቡላዶ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የዚህ ነፃ የንግድ ቀጠና አባል ለመሆን የሚያስችሏት ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች መኖራቸውን ገልፀዋል።


አንደኛው ኢኮኖሚያዊ ሲሆን ሌላኛው ፖለቲካዊ ነው። ኢኮኖሚያው አቅጣጫ የገበያ እድሉ ማስፋት መቻሉና አፍሪካም የተሻለ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ ሲሆን ፖለቲካዊ አቅጣጫው ደግሞ ኢትዮጵያ በህብረቱ ውስጥ ካላት ሚና አንፃር የሚታይ ነው። ዶክተር በቀለ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መስራችና ፣የህብረቱ ዋና ፅህፈት ቤት መቀመጫ በመሆኗ አርባ አራት ሀገራት ፊርማቸውን ካስቀመጡበት ስምምነት ውጪ መሆን እንደሌለባት ያለውን ፖለቲካዊ አንድምታ በማሳየት የመንግስትን ውሳኔ ትክክለኛነት አመላክተዋል። ሆኖም ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖውን በተመለከተም ኢትዮጵያ በፊርማው ማግስት ገበያዋን ክፍት ለማድረግ የማጥሯሯጥ በመሆኑ ሥጋት ሊኖር የማይገባ መሆኑን ነው የገለፁት።


ሚኒስትሩ “እኛ ስምምነቱን ስለፈረምን በቀጣዩ ዓመት ገበያውን ከፈትን ማለት አይደለም። እኛ በየዓመቱ እንከፍታለን ብለን አልፈረምንም። ሌሎች ሀገራት ግን በየዓመቱ አስር በመቶ ገበያቸውን ለመክፈት ተስማምተዋል። እኛ ግን በፈለግን ጊዜ ነው ገበያችንን የምንከፍተው።” በማለት እየተነሳ ያለውን ቀለል አድርገውታል።


ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ለዚሁ ነፃ የንግድ ገበያ የሚከፈቱ፣ በሂደት እየተከፈቱ የሚሄዱና ጭራሽኑ ሊከፈቱ የማይችሉ በማለት ሊይታ አስቀመጣለች። ሆኖም እነዚህ በሶስት የተከፈሉ የገበያ ዘርፎች በዝርዝር ተቀምጠው ግልፅ የተደረጉበት ሁኔታ የለም።


አዲስ የተመረጠው የዳሸን ባንክ አ.ማ የዳይሬክተሮች ቦርድ አቶ ነዋይ በየነ ሙላቱን አዲሱ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር እንዲሆኑ ያካሄደውን ምርጫ ብሔራዊ ባንክ አጸደቀ። አቶ ነዋይ በየነ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ባንኩን በቦርድ ሊቀመንበርነት ያገለገሉትን አቶ ተካ አስፋውን ይተካሉ።

 

የባንኩ ባለአክሲዮኖች 23ኛ መደበኛ ዓመታዊው ጉባኤ ኅዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም በተከናወነው ወቅት አቶ ነዋይ በየነን ጨምሮ ዘጠኝ አባላት ያሉት የቦርድ ዳይሬክተሮች ምርጫ መከናወኑ ይታወሳል።


ብሔራዊ ባንክም የካቲት 30 ቀን 2010 ዓ.ም የአዳዲሶቹን የቦርድ አባላት ምርጫ አጽድቋል።


አቶ ነዋይ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኤሌክትሪካል ኢንጂኒየሪንግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ፋካልቲ እ.ኤ.አ በ1984 ዓ.ም እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪያቸውን ደግሞ በቢዝነስ ሊደርሺፕ ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ (ዩኒሳ) የቢዝነስ አመራር ድህረ-ምረቃ ትምህርት ቤት እ.ኤ.አ በ2013 ዓ.ም አግኝተዋል።


አቶ ነዋይ የሥራ ሕይወታቸውን የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1984 ዓ.ም በኤንሲአር ኢትዮጵያ ሰልጣኝ የመስክ መሐንዲስ በመሆን ነበር። በበርካታ ዓለም አቀፍ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተቋማትም በከፍተኛ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል። በአሁኑ ሰዓት የአይቢኤም የቢዝነስ አጋር የሆነው አፍኮር ኃ/የተ/ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።


አቶ ነዋይ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት መሆናቸውን ከባንኩ የደረሰን ዜና ያስረዳል።

Page 1 of 66

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us