ፀጋው መላኩ

ፀጋው መላኩ


የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት መፅሐፍ

 

በቅርቡ በኢትዮጵያ አኮኖሚ ዙሪያ የሚያጠነጥን አንድ መፅሀፍ ለገበያ በቅቷል። መፅሀፉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን ፀሀፊው አቶ ጌታቸው አሰፋ የተባሉ የኢኮኖሚ ባለሙያ ናቸው። መፅሀፉ በ387 ገፆች ተቀናብሮ የተዘጋጀ ሲሆን በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችንም በውስጡ ዳሷል።

ፀሐፊው አቶ ጌታቸው አስፋው በሙያው ረዥም ዓመታትን የሰሩ ሲሆኑ ታሪካቸው እንደሚያመለክተው የብሄራዊ ኢኮኖሚ እቅድ ባለሙያ ሲሆኑ በቀድሞው በኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ወይም በአሁኑ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በሙያቸው አገልግለዋል።

     ቀደም ብሎም በአሥመራ ዩኒቨርስቲ ለሶስት ዓመታት በገጠር ልማትና በታዳጊ ሀገራት የመልማት ችግሮች ዙሪያ በመምህርነት ሙያ ሰርተዋል። ባለፉት ሶስት ዓመታትም በሪፖርተር ጋዜጣና በውይይት መፅሄት ላይ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የዳሰሱ ፅሁፎችን ለአንባቢያን ሲያደርሱ የቆዩ መሆናቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል። አቶ ጌታቸው ይህንን ሙያዊ መፅሃፋቸውን ባሳለፍነው ቅዳሜ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት አስመርቀዋል። በዕለቱም በመፅሀፉ አጠቃላይ ጭብጥና ይዘት ዙሪያ የተለያዩ ምሁራን የየራሳቸውን አስተያየቶች ሰጥተውበታል።

 

በሀገራችን አሁን ካለው የፖለቲካ፣ ልብወለድ፣ ታሪክና የወግ ፅሁፎች ባለፈ በዚህ ደረጃ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ የተፃፈ መፅሀፍ የለም ብሎ መናገር ይቻላል። ቢኖሩም በተቋም ደረጃ የተፃፉ ወይንም ደግሞ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እገዛ ለህትመት የበቁ ናቸው። እነዚህም ጥናቶች ቢሆኑ ታትመው በገበያው ላይ ለህዝብ የሚቀርቡ ሳይሆኑ ይመለከታቸዋል ተብለው ለሚታሰቡ ተቋማት የሚበተኑ በመሆናቸው በማንኛውም አንባቢ እጅ የሚገቡ አይደሉም። በዚህ በኩል ሲታይ አቶ ጌታቸው የተለየ ሥራን ሰርተዋል ያስብላል።

 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት? እንደገፁ ብዛት በይዘቱ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ዳስሷል። ከዳሰሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ በዚህ ወቅት አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው የዋጋ ንረት ይገኝበታል። አቶ ጌታቸው በዚሁ መፅሀፋቸው ለዋጋ ንረት መፈጠር ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች መኖራቸውን በሚከተለው መልኩ በመግለፅ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያዛምዱታል።

 

“የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በዋናነት በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መብዛት እንደሆነ ካወቅን ዘንዳ ይህ የጥሬ ገንዘብ መብዛት ዋጋን እንዴት እንደሚያንር እንመልከት። የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በሁለት መንገድ ነው። አንዱ የሸማቹ የመግዛት አቅሙ አድጎ ለመሸመት ውድድር ውስጥ ሲገባና ወድ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ሲሆን ነው። ሁለተኛው የዋጋ ንረት ምክንያት በአምራቹ ላይ ግብር ወይንም የሰራተኛ ደመወዝ ወይም ጥሬ ዕቃ ዋጋ ጨምሮበት ምርቱን ሲያስወድድ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የዋጋ ንረት የተፈጠረው በሁለቱም መንገድ ነው” ፀሀፊው ከዚሁ የዋጋ ንረት ጋር ምክንያት ጋር በተያያዘ ሀሳባቸውን በሰፊው በማብራራት ለዋጋ ንረት ምክንያት ነው ያሉትን ሃሳብ በሚከተለው መልኩ ትንታኔ ሰጥተውበታል። “በኢትዮጵያ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጨመር የፍላጎት ስበት የዋጋ ንረት ምክንያት እና በውጭ ምንዛሪ ተመን የብር ዋጋ መርከስ፣ በንግድ ትርፍ ግብር መጨመር፣ በጥሬ ዕቃ መወደድ በሚፈጠሩ የማምረቻ ወጪ ግፊት የዋጋ ንረት ምክንያት የሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው እንደሚጨምር ይገመታል።

 

የዋጋ ንረት የመንግሥት ዓላማ ማስፈፀሚያ ነው?

አቶ ጌታቸው በዚሁ መፅሀፋቸው የዋጋ ንረት የኢኮኖሚ መሳሪያ በመሆን አንዳንድ ጊዜ መንግስት የሚጠቀምበት መንገድ መሆኑንም አብራርተዋል።

ባለሙያው “የዋጋ ንረት የመንግስት ዓላማ ማስፈፀሚያ መሳሪያም ነው። የዋጋ ንረት ሀብታሙ ከደሃው ጥሬ ገንዘብ የሚነጥቅበት፤ ከነጠቀውም ውስጥ ለመንግስት የሚገባውን ግብር የሚሰጥበት ስለሆነ መንግስት ከሀብታሙ የሚሰበስበውን ግብር መጠን ከፍ ማድረግ ሲፈልግም ሆን ብሎ ጥሬ ገንዘብ ወደገበያው በመርጨት የዋጋ ንረት ይፈጥራል።

 

አቶ ጌታቸው ከዚህ ባለፈ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመግዛት አቅሙ እያሽቆለቆለ ሥላለው የብር መግዛት አቅም ሁኔታም በበርካታ ዓመታት ድምር ውስጥ ብር ዋጋውን በምን ያህል ደረጃ ዋጋውን እንዳጣ ከህዝቡ በተለይም ከደመወዝተኛው ኑሮ አንፃር በሚገባ ትንታኔ ሰጥተውበታል። ከኤክስፖርቱም ዘርፍ መዳከም ጋር በተያያዘ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎችንና ብዙም ውጤት እያመጡ አለመሆኑ በማስረጃ በተደገፈ መልኩ በሰፊው ተዳሷል። መፅሀፉ በአጠቃላይ ይዘቱ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በስፋት ዳሷል። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ከታሪክና ከዓለም አቀፉ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ጭብት አኳያም አያይዞ ሰፋ ያለ ትንታኔን ሰጥቶበታል።

 

ግብፅ ለወታደርና ለፖሊስ ጡረተኞች የ15 በመቶ የጡረታ ጭማሪ ያደረገች መሆኗን የአህራም ኦን ላይን ዘገባ አመልክቷል። በዚህም ጭማሪ መሠረት ዝቅተኛው የገንዘብ መጠን 125 የግብፅ ፓውንድ መሆኑ ታውቋል።

 

በግብፅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ከሄደው የዋጋ የኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በተለይ የጡረተኞች የኑሮ ሁኔታ እየከፋ መሄዱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ህጉ ተግባራዊ እንዲሆን ከፓርላማው ማፅደቅ በተጨማሪ ፕሬዝዳንቱ ፊርማቸውን ማኖር የሚጠበቅባቸው ይሆናል። ሆኖም አንዳንዶች ጭማሪው ብዙም አይደለም በማለት መንግስት አሁንም የተሻሻለ ማሻሻያ እንዲያደርግ እየጠየቁ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

ባለፈው ግንቦት 23 በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል የተከፈተው ኢድ ኤክስፖ በመካሄድ ላይ ነው። ዝግጅቱም እስከ ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል። በዚህ ኤክስፖ ላይ በርካታ ድርጅቶች ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን ይዘው የቀረቡ ሲሆን ከህንድ ከሶሪያና ከፓኪስታን የመጡ ተሳታፊዎችም የተገኙበት መሆኑ ታውቋል።

 

ይሄው በየዓመቱ በኢድ አልፈጥር ፆም ወቅት የሚካሄደው ኤክስፖ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር በየጊዜው ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሚሰራ ሲሆን በዚህ ዓመትም ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመት ጋር በጋራ በመሆን በትራፊክ አደጋ አስከፊነት ዙሪያ ለጎብኚዎች ግንዛቤ የሚሰጥበትን ሁኔታ ያመቻቸ መሆኑ ታውቋል።

በኤክስፖው ላይ፣አልባሳት የሃይማኖት መፃህፍት፣ የቤት እቃዎች፣ ጌጣጌጦችና የመሳሰሉት ምርቶች በስፋት ቀርበው ተመልክተናል። የዚሁ ዝግጅት አዘጋጅ የሆነው ሀላል ፕሮሞሽን በቀጣይ ኤክስፖውን በዓመት ሁለት ጊዜ ለማድረግ እቅድ ያለው መሆኑ በመክፈቻው ዕለት በተሰጠው ማብራሪያ ተገልጿል።

 

 

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከሰሞኑ የታክሲ ትራንስፖርት ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን ተገልጋዮች የአሁኑ ማሻሻያ የተጋነነ መሆኑን እየተናገሩ ነው፡፡ የታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት በአንፃሩ የታክሲ ታሪፍ ጭማሪው አነስተኛ መሆኑን ነው የገለፁልን፡፡


እስከዛሬ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪው ሲካሄድ የነበረው ከዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ ይሁንና የታክሲ ማህበራቱ ከነዳጅ ዋጋ ባለፈ የአንድ ተሽከርካሪ ግብዓቶች በርካታ በመሆናቸው የእነዚህም ግብዓቶች ዋጋ ታሳቢ ተደርገው የታክሲ ታሪፉ ጭማሪ ማሻሻያ ይደረግ የሚል የቆየ አቋም ነበራቸው፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ጥናቶች ሲደረጉ የቆዩ ቢሆኑም ይህ ነው የሚባል ጭማሪ ሳይደረግ የቆየ መሆኑን የታክሲ ማህበራት ይግፃሉ፡፡


የብሌን ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር አቶ ኑረዲን ዲታሞ እንደገለፁልን የታክሲ ከሰሞኑ አሁን ያለው ጭማሪ ሲታይ በአማካይ በአንድ ኪሎ ሜትር 60 ሳንቲም መሆኑን በመግለፅ ለታክሲ ትራንስፖርት አዋጪ የታሪፍ በአንድ ኪሎ ሜትር በአማካይ አንድ ብር ጭማሪ ቢሆን ነበር ሲሉ አመልክተዋል፡፡ በጭማሪው የጥናት ሂደት ላይም ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ውጪ የታክሲ ማህበራት ያልተሳተፉ መሆኑን በመግለፅ ሂደቱ ፍትሃዊነት ይጎድለዋል ብለዋል፡፡


አቶ ኑሪድን ጨምረውም ከወተት እስከ እንቁላል ብሎም እስከ አልባሳትና የተለያዩ ምርቶች በየዘርፋቸው በብዙ እጥፍ እንዲጨምሩ ሲደረግ የታክሲ ትራንስፖርት ዘርፍ ግን በመንግስት ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት በመሆኑ ይህ ነው የሚባል የታሪፍ ለውጥ ያልታየበት መሆኑን በመግለፅ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ያለውን የጋራዥ ጥገና ዋጋ፣የቅባት፣ የጎማና የመሳሰሉትን ዋጋ መናር ለማሳያነት ተጠቅመዋል፡፡ በአሁኑ የታሪፍ ጭማሪም ቢሆን ከረዥም ጉዞ ውጪ በአጭሩ ጉዞ ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ያልተደረገ መሆኑን በመግለፅ የተወሰነ ለውጥ የሚታየው በረዥም የጉዞ ርቀት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 

 

ማይንድ ሴት ኮንሰልት በመባል የሚታወቀው ድርጅት ባሳለፍነው ቅዳሜ ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ.ም ሰዎችን ለተለያዩ ሥራዎች የሚያነቃቃ ፕሮግራም በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። “እኔ ነኝ አዲሷ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ፕሮግራም በርካታ ታዋቂ ወጣቶችና ታዋቂ ሰዎችን አሳትፏል።

 

ይህ አይነቱ አነቃቂ ኮንፍረንስ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የተለመደ ነው።ዋና አላማውም ሰዎች በነገሮች በጎና የተነቃቃ አዕምሮ ኖሯቸው በማህበራዊና በኢኮኖሚዊ ስራዎች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። በሀገራችን እንደዚህ አይነት ጅምሮች በተለያዩ አቅጣጫዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች የዜጎችን አስተሳሰብ በማነቃቃት ለስራ ፈጠራ ብሎም ለኢንቨስትመንት ሥራ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ እንደሆነ ይታመናል።

 

በዚህ ዙሪያ በሀገራችን ከሚንቀሳቀሱት ባለሙያዎች መካከል አንዱ ዶክተር ምህረት ደበበ ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድም ወደ ሀገር መሪነት ሥልጣን ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ የዚሁ እንቅስቃሴ አካል የነበሩ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

የኮንፍረንሱ ምልከታ

የአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ሰፊ ቢሆንም በወጣቶች ተሞልቷል። የአዳራሹ ስፋት የመድረኩን ክንውን ሰው በሚገባ ስለማያሳይ በርካቶች ፕሮግራሙን የሚታደሙት በዚያው በአዳራሽ ውስጥ በተሰቀሉት ግዙፍ ስክሪኖች ጭምር ነው። በዕለቱ ግጥሞች፣ ወጎችና የተለያዩ የሥነፅሁፍ ሥራዎችም ለታዳሚው ቀርበዋል። ከፕሮግራሙ ግዝፈት አንፃር ሲታይ መድረኩን ይመጥናሉ ተብለው የማይታሰቡ ሥራዎችም ሲቀርቡበት ታይቷል። ለወጣቶች ተሞክሮ ይሆናሉ ተብለው የቀረቡት ስራዎችና ልምድን የማካፈል ንግግሮች እያንዳንዳቸው በይዘታቸው ሰፊ ጊዜን የወሰዱ በመሆናቸው በታዳሚው ዘንድ መሰላቸትን ሲፈጥሩ ታይቷል።

 

በፕሮግራሙ መገባደጃ አካባቢ የማነቃቂያ ስብከት መሰል ንግግር ያደረጉት ዶክተር ምህረት ደበበ በሃሳብ ዙሪያ ሰፋ ያለ ፅንሰ ሀሳብ ለማስጨበጥ ጥረት አድርገዋል። በርካቶችም በጥሞና አድምጠዋቸዋል። ሆኖም ዶክተር ምህረት ብዙዎቹ የንግግር ጭብጦቻቸውን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ያቀረቧቸው በመሆኑ ብዙም አዲስ ነገር አልነበራቸውም ብሎ መናገር ይቻላል።

 

ፕሮግራሙ ዘግይቶ የተጀመረ በመሆኑ እያንዳንዱ የመድረክ ዝግጅት አቅራቢ በመድረክ አስተባባሪ “ይብቃህ” እየተባለ በጆሮው ሹክ ይባለውም ነበር። ዶክተር ምህረትም ቢሆን ይህ እጣ ገጥሟቸዋል። በዚህ በኩል ሲታይ መድረኩ የቅንጅት ችግር የሚታይበትም ይመስላል። በመድረኩ የሙዚቃ ስራዎቸቸውን ያቀረቡት አርቲስቶች በሙያቸው ብቃትም ሆነ የታዳሚውን ጆሮ በመያዝ በኩል የተዋጣላቸው ነበሩ። ሰዓቱ እየገፋ መሄዱን ተከትሎ በከተማዋ ካለው የትራንስፖርት እጥረት ጋር በተያያዘ በርካቶች ፕሮግራሙን አቋርጠው ለመውጣት ተገደዋል። በተለይ በመጨረሻ በነበረው የፕሮግራሙ የሙዚቃ መሸጋገሪያ ወቅት ፕሮግራሙ የተጠናቀቀ እስኪመስል ድረስ በርካታ ታዳሚዎች በጥድፊያ ሲወጡ ታይቷል።

 

ዶክተር ምህረት የማነቃቂያ ንግግራቸውን እያደረጉ እያለ በፍጥነት እንዲያጠናቅቁ ከመድረክ አስተባባሪው በኩል ተነገራቸው። እሳቸውም ንግግራቸውን በፍጥነት አጠናቀው መድረኩን እንደተሰናበቱ፤ ማንም ባልጠበቀው መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አንድ እጃቸውን ከፍ አድርገው ለታዳሚው ሰላምታ እየሰጡ ወደ ንግግር ማድረጊያው ተጠጉ። ታዳሚው ከመቀመጫው በመነሳት በጩኸትና በፉጨት ተቀበላቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ የሚሊኒየሙ ፕሮግራም ከአምስት ወራት በፊት እሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆኑ የተያዘ እንደነበር አስታውሰው የመድረክ ንግግራቸውንም የሚያደርጉት ቀድሞ ፕሮግራሙ ሲያዝ በነበራቸው ማንነት ሳይሆን በአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ማንነታቸው መሆኑን በመግለፅ በቀጥታ ወደ ንግግራቸው ገቡ።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሳቸው በፊት ከነበሩት ተናጋሪዎች በላይ እጅግ በላቀ ሁኔታ የታዳሚዎቸቸውን ቀልብ ገዝተው ንግግራቸውን በስፋት ቀጠሉ። የንግሮቻቸው ጭብጥም በአንድነት፣ በይቅርታ፣ በአብሮነትና በመቻቻል ላይ ያተኮረ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ፕሮግራሙ የገቡት የሳዑዲ አረቢያ ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁ በመሆኑ እግረ መንገዳቸውንም በዚሁ ጉብኝት አላማና ስኬት ዙሪያ ስለነበሩ አንዳንድ ጉዳዮችም ማብራሪያ ሰጥተዋል። በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝታቸው ወቅት ይዘዋቸው ከሄዷቸው አስር ጥያቄዎች ከአንዱ በቀር ዘጠኙ የተመለሱ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

“ሳዑዲ አረቢያ ሄደን ምን ትፈልጋላችሁ ተብለን ስንጠየቅ ገንዘብ ሳይሆን ዜጎቻችንን ፍቱልን ነው ያልናቸው። የሚገርመው ነገር ለዜጎቻችን ክብር መስጠት ስንጀምር ያልጠየቅናው ነገር ሁሉ ይሰጠናል።” በማለት ታዳሚውን በጭብጨባ ግለት ውስጥ ከተቱት።

 

ንግግራቸውንም ቀጠል በማድረግ “ዝርዝሩን ለዲሲፒሊን ብዬ መናገር ቢያስቸግረኝም፤ እጅግ ስኬታማ የሚባል የዲፕሎማቲክ ቆይታ ነበረን። በቆይታችን ከአንድ ጥያቄ በስተቀር የጠየቅናቸው ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ አግኝቷል። አንደኛው ጥያቄ ሺህ ሙሀመድ አሊ አልአሙዲንን ማምጣት ነበር። እሳቸውን በሚመለከት ከክራውን ፕሪንሱ ጋር መቶ በመቶ ተግባብተናል። አንድ ሺህ እስረኞችን ሳዑዲ ለቃለች። መፍታት ብቻ ሳይሆን ዛሬ ምሽት ከፊሉ መግባት ይጀምራል። ሼኽ አልአሙዲንን በሚመለከት እንደ ሀገር ያለንን ፅኑ አቋም አመላክተናል። ለእኛ ሀብታምም ደሃም ዜጋ ነው።

 

ሼህ ሙሐመድ ሄሴን አሊ አልአሙዲ የማንፈልጋቸው ሰዎች ያለን እንደሆነ ሲመጡ እንነግራቸዋለን እንጂ በባይተዋር ሰዎች ሲታሰሩ የሚጨክን ልብ የለንም። ይህ ጠንካራ አቋማችንን የተረዱት ክራውን ፕሪንሱ አሳዛኝ ቢሆንም ማታ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ላይ ተግባብተን ጠዋት ሊለቁ ከወሰኑ በኋላ ቤተሰቦቻቸው ባደረጉባቸው ከፍተኛ ጫና አሁን ከእኛ ጋር ሊመጡ አልቻሉም።

 

ከእሳቸው በሰተቀር አስር ጥያቄ ነበረን? ዘጠኙን መልሰውልን ለአስረኛው ጥያቄ ግን ጥቂት ጊዜ ስጡን ብለዋል። የሼኽ አልአሙዲ መታሰር በዓለም ላይ ያሉ ዲያስፖራዎች ሁሉ አጀንዳ መሆን አለበት። ምክንያቱን ኢትዮጵያ አንተ አንቺ ከሆንሽ፣ አንድ ኢትዮጵያ ታስራለችና ኢትዮጵያ ስትታሰር ዝም ማለት የሚያስችለው ሌላ ኢትዮጵያዊ መኖር የለበትም። የጀመርነውን ዲፕሎማቲክ ጫና በማስቀጠል ጊዜውን መናገር ብቸገርም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ።” በማለት በዚህ ዙሪያ የነበራቸውን ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።

ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ሩስያና ግብፅ ግንኙነቶቻቸውን የበለጠ እያጠናከሩ ሲሆን በቅርቡም ሩስያ የራሷን የሆነ ፓርክ በግብፅ የምትገነባ መሆኗን የአህራም ኦንላይን ዘገባ ያመለክታል። ይሄው በግብፅ ፖርትሰይድ የሚገነባው ግዙፍ የኢንዱስትሪ ዞን በውስጡ የሰባት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ይሄው ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል።

 

ይሄው የኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ በሩስያው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኒስ ማንቱሮቭ እና በግብፅ አቻቸው ታሪክ ካቢል አማካኝነት በሚደረግ የፊርማ ሥነ ስርዓት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ የኢንዱስትሪ ዞን በ 5 ነጥብ 25 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ሥፋት ያለው ቦታ ላይ የሚያርፍ ሲሆን እንደዘገባው ከሆን ይህንን የኢንዱስትሪ ፓርክ እውን ለማድረግ ሁለቱ ሀገራት እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ ተከታታይ ድርድሮችን ሲያደርጉ ነበር። ኢንዱስትሪ ዞኑ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ለ35 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሏል።

 

ሩስያና ግብፅ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግንኙነቶቻቸውን ይበልጥ እያጠናከሩ የሄዱ ሲሆን በቱሪዝም፣ በኮንስትራክሽን፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በልዩ ልዩ ወታደራዊ ዘርፎች ግንኙነቶቻቸውን ይበለጠ እያጠናከሩ ይገኛሉ። እንደዘገባው ከሆነ ሀገራቱ ከዚህም በተጨማሪ በባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ፣እንደዚሁም በግብርናው ዘርፍም በጋራ የሚሰሩበት አካሄድ እየተዘረጋ ነው።

 

ሩስያ ከዚህም ባሻገር ለግብፅ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚያገለግል የኑኩሌር ቴክኖሎጂን ለመገንባት ስምምነት ላይ ደርሳ ወደ ሥራ ከገባች ዋል አደር ብላለች።ይሄው ዳባ በተባለው ቦታ የሚገነባው የኑኩሌር ኃይል ማመንጫ በግብፅ በአሁኑ ሰዓት እየታየ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ችግር ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

“አሰሪው ለኢንዱስትሪ ሠላም እየተጋ፤ ብዙ ሥራ ለብዙ ሰዎች ይፈጥራል” በሚል የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌደሬሽን የተመሰረተበትን 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል የሚያከበር መሆኑን አስታውቋል። በዚሁ በነገው ዕለት በሚካሄደው የምስረታ በዓል ላይም የመንግስት አመራሮች፣የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች እንደዚሁም የአሰሪና ሰራተኛ ማህበራት ተወካዮች ተሳታፊዎች የሚሆኑ መሆኑ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ታደለ ይመር የምስረታ በዓሉን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፌደሬሽኑ በ1945 ዓ.ም የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰው፤ ይሁንና የደርግ መንግስት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ሲከተል ከነበረው ርዕዮተ ዓለም ጋር በተያያዘ ህልውናው እንዲያከትም ያደረገበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፤ ይሁንና ፌደሬሽኑ በ1989 ዓ.ም እንደገና የተመሰረተ መሆኑን ገልፀዋል።

 

ፌደሬሽኑ እስከ ዛሬ ባለው ሂደትም በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አሰሪዎች በየዘርፋቸው እንዲደራጁ በማድረጉ ረገድ ሰፊ ስራን የሰራ መሆኑም ተመልክቷል። በዚህም በአበባ ልማት በኮንስትራክሽን፣በጤና ተቋማት እንደዚሁም በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተሰማሩንትን በማደራጀት ፌደሬሽኑ የራሱን ሚና የተጫወተ መሆኑንም አቶ ታደለ አመልክተዋል።

 

ከዚሁ ጋር በተያያዘም መካከለኛ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች አሰሪዎች ፌደሬሽን በትላንትናው ዕለት ተመስርቷል። እነዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኮከብ የሌላቸው ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች መሆናቸው ታውቋል። መስራች አባላቱ በፌደሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ላይ በመወያየት ካፀደቁ በኋላ የአመራር አባላቱን በመምረጥ የምስረታ ጉባኤው ተጠናቋል።

 

በመተዳደሪያ ደንቡ ውይይት ላይ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ለምን ያህል ጊዜ በጠቅላላ ጉባኤው እየተመረጠ መቀጠል አለበት የሚለው ጉዳይ ብዙ ያነጋገረ ሲሆን ውይይቱ የነበረው የስልጣን ቆይታ ጊዜው ይገድብ ወይንም ጠቅላላ ጉባኤው እስከፈለገው ድረስ ይቀጥል በሚለው ዙሪያ ነበር።

 

ሆኖም በስተመጨረሻ በተሰጠው የህግ ማብራሪያ መሰረት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት የቆይታ ጊዜ ገደብ ሳይጣልበት በጠቅላላ ጉባኤው በሚወሰነው መሰረት ይቀጥል በሚለው በአንድ ድምፀ ተዐቅቦ ፀድቋል። ማህበሩ 11 አባላት በቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉት መርጧል።

 

በዕለቱ በተካሄደውም የፌደሬሽኑ የአመራሮች ምርጫም አቶ ፍርድ አወቅ ስናፍቀው የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት፣ወይዘሮ ኑሪት አባዝናብ ተቀዳሚ ምክት ፕሬዝዳንት እንደዚሁም አቶ ጌታሁን ታደሰ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል።

 

የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያና ሱዳን የሀገሪቱን አማፅያን በማገዝ የኤርትራን ሰላም ለማናጋት እየተንቀሳቀሱ ነው በማለት ላሰማችው ክስ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የማስተባበያ ምላሽ ተሰጥቶበታል።

በዚሁ ዙሪያ ለቻይና ዜና አገልግሎት ዤኑዋ ምላሽ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም የኤርትራ ውንጀላ ሀሰትና መሰረት የለሽ ነው በማለት ክሱን አስተባብለዋል። ቃል አቀባዩ አክለውም ሁለቱ ሀገራት በዝግ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል።

የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያና የሱዳን መንግስታት የኤርትራ አማፅያንን አስታጥቀው ጥቃት እንዲሰነዝሩ ለማድረግ ያሴሩ መሆኑን ገልፆ ነበር።

በሌላ ዜና ሱዳን የአየር ኃይሏን ለማጠናከር ከሰሞኑ FTC2000 በመባል የሚታወቅ የስልጠና እና የጥቃት ማድረሻ ተዋጊ ጀት ግዢ የፈፀመች መሆኑን የሱዳን ትሪብዩን ዘገባ አመልክቷል። የተዋጊ አውሮፕላኖቹም አቀባበል ሥነ ሥርዓት የተከናወነ መሆኑ ታውቋል። እንደዘገባው ከሆነ የሱዳን መንግስት ፊቱን ወደ ቻይና በማዞር ከዚህ ቀደምም የበርካታ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ሸመታ በተለያዩ ዙሮች ያከናወነች ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ የሩስያን ኤስዩ-30 እና ኤስዩ-35 የተባሉ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ከራሷ ከሩስያ ለመግዛት እንቅስቃሴ የጀመረች መሆኑን ይሄው የሱዳን ትሪብዩን ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል።¾

የአፄ ዮሃንስ አራተኛ ማህበር መታሰቢያ ሀውልትና ልዩ ልዩ ተያያዥነት ያላቸው ተቋማት ሊገነቡ ነው።

የአፄ ዮሃንስ አራተኛ ማህበር በመባል የሚታወቀው ማህበር ይሄንኑ ሥራ ለማከናወን ሀላፊነቱን በመውሰድ እየሰራ ሲሆን ይህንኑ ዘርፈ ብዙ መታሰቢያ የልማት ሥራ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው አቢይ አዲ ከተማ ለመስራት እንቅስቃሴ የተጀመረ መሆኑን የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ መክብብ በላይ ባለፈው ዕሁድ በዚሁ ዙሪያ በተጠራው ማብሰሪያ ስብሰባ ላይ አመልክተዋል።

ይሄው የመታሰቢያ የልማት ሥራ ተንቤን አቢይ አዲ ከተማን የትግራይ ክልል የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን የሚያስችላት መሆኑ ተመልክቷል። አቢይ አዲ ከተማ ለዚህ ታሪካዊ ሁነት ተመራጭ ያደረጓት በርካታ ታሪካዊ ሁነቶች መኖራቸው በዕለቱ ተመልክቷል። ይሄው ፕሮጀክት በከተማዋ ሰው ሰራሽ ሀይቅን መገንባት እንደዚሁም ሙዝየምን መገንባት ጭምር የሚያካትት መሆኑ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ በንጉሱ መታሰቢያነት የስነ ታሪክና ቅርስ ምርምር ማዕከል እና የባህልና ቱሪዝም ማዕከልን ለመገንባት ታቅዷል።

በቀጣይም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስብሰባ የሚከሄድ ሲሆን በርካታ ምሁራንና ባለሀብቶችን እንደዚሁም የተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎችንም ለማሳተፍም እቅድ መያዙ ታውቋል።

በዚህም አንድ ራሱን የቻለ ቋሚ ፋውንዴሽን ለማቋቋም የታሰበ መሆኑን የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ መክብብ በላይ ለተሰብሳቢው ጨምረው ገልፀዋል። ከዚሁ የአፄ ዮሃንስ መታሰቢያ ሀውልትና ሙዚየም ጋር በተያያዘ ለሚሰራው ሰፊ መዝናኛ በአቢል አዲ ከተማ 35 ሄክታር መሬት የተፈቀደ መሆኑን አቶ መክብብ ጨምረው አመልክተዋል። ይህንንም ሰፊ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ነሀሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በአቢል አዲ ከተማ የመሰረት ድንጋይ የሚጣል መሆኑ ታውቋል። የመሰረት ድንጋይ መጣሉንም ተከትሎ በ2011 ዓ.ም ሰፊ የገቢ የማሰባሰብ ስራም የሚሰራ መሆኑ ተመልክቷል። ይህም ገቢ የማሰሰባሰብ ሂደት ዓለም አቀፍ የቴሌቶን ቀንንም ጭምር ያካትታል ተብሏል።¾

የውጭ ምንዛሪው ፈተና

Wednesday, 16 May 2018 13:45

 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ድርቅ ከተመታ ቆይቷል። ይህ ሁኔታ እየተባባሰ ሂዶ በአሁኑ ሰዓት ያለው የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ከ 3 ቢሊዮን ዶላር በታች አሽቆልቁሏል። ችግሩ በብዙ መልኩ የተተበተበ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ያሉትን መሰረታዊ ችግሮች በሚከተለው መልኩ ዳሰናቸዋል።

 

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ መልሶ ኤክስፖርቱን ሲጎዳው

 

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ተፅዕኖ እያደረሰ ያለው በኤክስፖርት ገቢውም ጭምር ነው። ወደ ውጪ የሚላኩ የኢትዮጵያ ምርቶች ከማምረቻ ማሽኖች ጀምሮ እስከ ከፊል ያለቀላቸው ምርቶች ድረስ ሀገር ውስጥ የሚገቡት ከውጪ በመሆኑ የውጪ ምንዛሪ እጥረቱ ኤክስፖርትን በማዳከም ሌላ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን የሚፈጥርበት ሁኔታም አለ። በሌላ አነጋጋር የውጭ ምንዛሪ ችግሩ በራሱ ሌላ የውጭ ምንዛሪ ችግርን ይወልዳል ማለት ነው። እየሆነ ያለውም ይህ ነው።


በተለያዩ የኤክስፖርት ምርት ሥራ የተሰማሩ ኩባንያዎች ከተከተሰው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ ምርት አምርተው በኤክስፖርቱ ገበያ መሳተፍ አልቻሉም። በውጪ ገበያ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከተቀባይ ደንበኞቻቸው ጋር በገቡት ውል መሰረት ምርቶቻቸውን በአግባቡና በጊዜ ማቅረብ ካልቻሉ ደግሞ ከገበያ እየወጡ የሚሄዱበት ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው። ይህም በጊዜ ሂደት የሀገሪቱን የኤክስፖርት ገቢ የበለጠ እየጎዳው የሚሄድ ይሆናል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ

 

የውጭ ባለሀብቶች በአንድ ሀገር መዋዕለ ነዋያቸውን ሲያፈሱ ትርፍ ለመሰብሰብ ነው። በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱ የውጭ ባለሀብቶች ኢንቬስት ኢንዲያደርጉ የሚፈቀድላቸው በዶላር ነው። ለዚህም የተቀመጠላቸው ዝቅተኛ የካፒታል መጠን አለ። አንድ የውጭ ባለሀብት በዶላር ኢንቬስት የማድረግ ግዴታ ቢኖርበትም ከምርት በኋላ ትርፉን በውጭ ምንዛሪ መንዝሮ የመውሰድ መብቱ ግን የተጠበቀ ነው።


ሆኖም በኢትዮጵያ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ መዋዕለ ነዋቸውን ያፈሰሱ የውጭ ባለሀብቶች የሚያገኙትን ትርፍ በውጭ ምንዛሪ ቀይረው ወደ ሀገራቸው መውሰድ የቻሉበት ሁኔታ የለም። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የውጭ ባለሀብቶች በተደጋጋሚ ጥያቄዎቻቸውን ሲያቀርቡ የቆዩበት ሁኔታም ነበር።


ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ኢንቬስት ያደረጉ የአውሮፓ ባለሀብቶች ህብረት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት በባለሀብቶቹ በኩል ከተነሱት ጥያቄዎች መካከለም አንዱ ይሄው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጉዳይ ነው። ባለሀብቶቹ ትርፋቸውን በዶላር መንዝረው ለመውሰድ ለብሄራዊ ባንክ ጥያቄ በሚያቀርቡበት ወቅት ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ በተገቢው ሁኔታ እየተስተናገዱ አለመሆኑን የገለፁበት ሁኔታ ነበር። በጊዜው ለባለሀበቶቹ የተሰጣቸው ምላሽ በሁለት አቅጣጫ የተመለከተ ነበር። አንደኛው ባለሀብቶቹ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እስኪቃለል ለጥቂት ጊዜ ትዕግስት እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ሲሆን ሌላኛው የቀረበው አማራጭ ደግሞ ባለሀብቶቹ በኤክስፖርት ሥራም በመሰማርተው የራሳቸውን የውጭ ምንዛሪ የሚያመነጩበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ።


የመጀመሪያውን የውጭ ሀገር ባለሀብቶችን ጥያቄ በአግባቡ ለማሳካት በጊዜው ከነበረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ችግር መሆኑ ተገልፆ ችግሩ በሂደት የሚፈታ በመሆኑ ባለሀብቶቹ እንዲታገሱ የተጠየቀበት ሁኔታ ነበር። ሆኖም ከዚያ በኋላ የውጭ ምንዛሪ ችግሩ መፍትሄ ከማግኘት ይልቅ የበለጠ እየተባባሰ ነበር የሄደው። ሁለተኛው አማራጭ ባለሀብቶቹ ኤክስፖርት በማድረግ የራሳቸውን የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር የሚለው ነው። ይህ ምላሽ በጊዜው በበርካታ የውጭ ባለሀብቶች በኩል ቅሬታን የፈጠረበት ሁኔታ ነበር። አንድ የሀገር ውስጥ ወይም የውጭ ባለሀብት መዋዕለ ነዋዩን ሲያፈስ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ኤክስፖርት እንዲያደርግ የሚገደድባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም ሁሉም ባለሀብት በዚህ ግዳጅ ውስጥ የሚገባባት አሰራር ግን የለም። ባለሀብቶች ገና ከመጀመሪያው ወደ ኢንቬስትመንት ዘርፉ ሲሰማሩ፤ ዘርፉ ለኤክስፖርት ዘርፍ የተለየ በመሆኑ ሙሉ ምርቶቻቸውን ለኤክስፖርት ገበያ እንዲያውሉ የሚገደዱበት ሁኔታ አለ። ይህም የሚሆነው በርካታ ማበረታቻዎች ከተደረገላቸው በኋላ ነው።


የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዋና አላማ የኤክስፖርት ዘርፉን ማሳደግ በመሆኑ፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የገቡ ባለሀብቶች ከሆኑ መቶ ፐርሰንት ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ የመላክ ግዴታ አለባቸው። እነዚህ ባለሀብቶች ወደዚህ ሥራ ሲገቡ ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት ለማድረግ ቃል ገብተውና ፊርማቸውን አኑረው ነው። በመሆኑም እነዚህ ባለሀብቶች ምርቶቻቸውን ልከው የውጭ ምንዛሪ ያስገባሉ፤ከዚህ ገቢ ውስጥም የድርሻቸውን ይወስዳሉ። ሆኖም ከዚህ ውጪ ያሉ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ዘርፉ በተለየ ሁኔታ አስገዳጅ ካላደረገውና፤ ባለሀብቱም በውጭ ገበያ የመሳታፍ ፍላጎት ከሌለው በስተቀር በህጉ መሰረት በዶላር ኢንቬስት አድርጎ ትርፉን በዚያው ምንዛሪ የመጠየቅ መብቱ የተጠበቀ ነው።


ይሁንና ከውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ጋር በተያያዘ ከተገባው ስምምነትና ከህጉ ውጪ ሁሉም የውጭ ባለሀቶችን ኤክስፖርት አድርጉና ትርፋችሁን በውጭ ምንዛሪ ውሰዱ የሚለው አካሄድ ባለሀብቶች ተጨማሪ የኢንቬስትመንት ሥራን እንዳያከናውኑ የሚያደርግ ከመሆኑም ባለፈ ሌሎች የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዳያፈሱ የሚያደርግ ይሆናል። ይህም ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሀገሪቱን ቀጥተኛ የውጭ ኢንቬስመንት ፍስት የሚጎዳውም ይሆናል።

 

የኤክስፖርት ማበረታቻውና የውጭ ምንዛሪው ስንክሳር

 

በግብርናውም ሆነ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተሰማርተው በኤክስፖርቱ ዘርፍ ለመስራት የተስማሙ ባለሀብቶች በህጉ መሰረት በርካታ ማበረታቻ ይደረግላቸዋል። ከማበረታቻዎቹ መካከልም የግብር እፎይታ፣ ከውጭ ለሚያሰገቧቸው ማሽኖችና ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ መብቶች ተጠቃሚነት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው። ባለሀብቶቹ ከሌሎች ባለሀብቶች በተለየ ሁኔታ እነዚህ ማበረታቻዎች ሲደረግላቸው ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት አድርገው ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ ነው።


ሆኖም በርካታ ባለሀብቶች እነዚህን ማበረታቻዎች ከወሰዱ በኋላ ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት አድርጎ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት ይልቅ የሀገር ውስጥ ገበያን የሚጠቀሙበት ሁኔታ አለ። ይህ ጉዳይ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንደዚሁም በንግድ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች በኩል በተደጋጋሚ የሚነሳ ቅሬታ ቢሆንም እስከዛሬም ድረስ ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ተሰጥቶት አይታይም።

 

የዲያስፖራው ፖለቲካና የውጭ የውጭ ምንዛሪው ፈተና

 

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ተደርገው ከሚወሰዱት ምንጮች መካከል አንዱ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚላከው የውጭ ምንዛሪ (remittance) አንዱ ነው። ከንግድ ሚኒስቴርም ሆነ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ከውጭ የሚላከው የውጭ ምንዛሪ መጠን ኢትዮጵያ በኤክስፖርት ምርት ከምታገኘው ገቢ መብለጥ ችሏል። ሆኖም ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ እየጦዘ ከመጣው የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ውጥረት ጋር በተያያዘ የመንግስት የፋይናስ ጉልበት ለማዳከም በሚል የተከፈተ ዘመቻም አለ። ይህ ዘመቻ በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያን ዜጎች የውጭ ምንዛሪ ማዕቀብን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እንዲጥሉ የሚያሳስብ ነው። እንቅስቃሴው በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩትን ገንዘብ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀንሱ ወይንም መንግስት ኪስ እንዳይገባ ከባንክ ሥርዓት ውጪ ያለውን የመላኪያ ዘዴ እንዲጠቀሙ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ ተሰምቷል። ይህ ጥሪ ምን ያህል ግቡን እንደመታ በግልፅ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ይሁንና ምንም አይነት ተፅዕኖን አያመጣም ብሎ መደምደም ግን አይቻልም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ይሄንኑ ጉዳይ አስመለክተው በቅርቡ በአንድ መድረክ የሚከተለውን ምላሽ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።


“መንግስትን ለማስደንገጥ የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት ትክክለኛ መፍትሄ አይደለም። ልጅ ሲያጠፋ የምንቀጣው ራት እየከለከልን አይደለም። እያበላን በድሮው ከሆነ እንቆነጥጣለን በአሁኑ ከሆነ ደግሞ Time out ነው የምንለው። ዲያስፖራ መንግስት ለመቆንጠጥ ዶላር አንልክም ሲሉ። ማነው እየተጎዳ ያለው ሲባል ዝቅተኛ ዶላር የማመንጨት አቅም ያላቸው ነጋዴዎች ናቸው።”

መደበኛ ያልሆነው የንግድ አካሄድና የውጭ ምንዛሬው

 

መንግስት በቂ የውጭ ምንዛሪን ማቅረብ ባልቻለ ቁጥር ነገሮች መደበኛ ያልሆነ አካሄድን መከተላቸው እሙን ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በተለይ የጥቁር ገበያ መጠናከር አንዱ መደበኛ ያልሆነው ገበያ ሥርዓት መጠናከር ማሳያ ነው። ከዚህም ባለፈ ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ ከላኩ በኋላ በመደበኛው የባንክ ሥርዓት የውጭ ምንዛሪን የማያስገቡ ባለሀብቶችም መኖራቸው ይታወቃል።


በብሄራዊ ባንክ ያለው የውጭ ምንዛንረ ወረፋ የሰለቻቸው እንደዚሁም በቂ ከዚህም በኋላ ቢሆን በቂ የውጭ ምንዛሪን ማግኘት ያልቻሉ አስመጪዎች ያላቸው አማራጭ ፊታቸውን ወደ ጥቁር ገበያው በማዞር የዶላር ሸመታን ማካሄድ ነው። ይህም ሁኔታ በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ በኩል ያለውን የምንዛሪ ልዩነት የበለጠ እያሰፋው የሚሄድ ይሆናል። ለዚህ ብቸኛው መፍትሄ መንግስት በቂ የሆነ የውጭ ምንዛሪን ማቅረብ መቻል ብቻ ነው።


ከዚህ ባለፈ በአንድ ሀገር ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገኘ ሀብት በሚኖርበት ወቅት በባለሀብቶቹ በኩል በራስ መተማመን ስለማይኖር በብር የሚገኘውን ገቢ በውጭ ምንዛሪ ቀይሮ በውጭ ባንክ የማስቀመጥ ሁኔታም ይከሰታል። በሙስና ተጎጂ የሆኑ ሀገራት አንዱ የውጭ ምንዛሪ ድርቀት ይህ ነው። ይህ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ሀብት በዘረፋ ከመገኘቱ ባለፈ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ቋሚ ሀብቱ ለሀገር ተጨማሪ ጉዳትን የሚያስከትለው በገንዘብ ማሸሻነት የሚያገለግል መሆኑ ነው። ይህ ጉዳይ መፍትሄ ማግኘት የሚችለው እነዚህ የገንዘብ ማሸሺያ የሆኑ የንግድ ተቋማት አንዳች አይነት እርምጃ ሲወሰድባቸው ብቻ ነው።


በአጠቃላይ ሲታይ በአንድ ሀገር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲከሰት የሚያስከትላቸው ችግሮች ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ናቸው። የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢንቨስትመንትን ይጎዳል፣ የንግድ ሚዛንን ያዛባል፣በውጭ እዳ ክፍያ ላይ የራሱን የሆነ ተፀዕኖን ያሳድራል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ መንግስት ፈተናዎች መካከልም ይሄው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጉዳይ አንዱ ነው። ዶክተር አቢይ በቅርቡ እንደተናገሩት የፈተናው መፍትሄ ዓመታትን የሚፈጅ ነው።

Page 3 of 70

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 254 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us