You are here:መነሻ ገፅ»arts»ፀጋው መላኩ - Sendek NewsPaper
ፀጋው መላኩ

ፀጋው መላኩ

 

የዓለም አቀፉ የገንዘብ (IMF) ማኔጂግ ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋርድ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ጉብኝት አድርገዋል። ይህ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የቤኒንና የጂቡቲ የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝታው አካል መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

 

 በዚሁ ጉብኝታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደዚሁም ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር ቆይታም አደርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ የኢስት ኢንዱስትሪ ዞንንም የጉብኝታቸው አካል አድርገዋል። ላጋርድ ከጉብኝታቸው መልስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አወድሰው በተለይ በማምረቻው ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተመለከቷቸው የቻይና እና የኔዘርላንድስ ኢንቨስትመንቶች ያስደሰቷቸው መሆኑን አመልክተዋል። ይህም እሰቴን በመጨመር የዓለም አቀፉን የጥራት ደረጃ በሟላ መልኩ ምርቶቹን የማምረቱ ሂደት የኢትዮጵያን የኤክስፖርት ገበያ በማጠናከሩ በኩልም ሰፊ ሚና የሚኖረው መሆኑንም ማኔጂግ ዳይሬክተሯ ጨምረው አመልክተዋል።

 

 ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ገንዘብ ድርጅት አባል የሆነችው ድርጅቱ ከተመሰረተበት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ ነው። ሆኖም ሀገሪቱ የድርጅቱ መስራች አባል ሀገር ከሚባሉት ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም ሌሎች ሀገራት ከተቋሙ የሚያገኙትን ጥቅም ያህል ተጠቃሚ ናት ብሎ መናገር ያስቸግራል። በተለይ የደርግ መንግስት በነበረው የፀና ኮሚኒስታዊ አቋም የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት ጨምሮ ከበርካታ መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የነበረው ግንኙነት በእጅጉ የተበላሸ ነበር። ሆኖም አገዛዙ የማክተሚያ ጊዜው እየተቃረበ በነበረበት ወቅት በነበረው የለውጥ ሂደት የአለም ባንክን እና የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት ምክረ ሀሳቦች የመቀበል አዝማሚያን ያሳየበት ሁኔታ ነበር።

 

በዘመነ ኢህአዴግ ያለው አካሄድ ዥንጉርጉር የሆነ ግንኙነት የሚታይበት ነው። ኢህአዴግ የስልጣን መንበሩን እንደተቆጣጠረ ሀገሪቱ ከዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ በብዙው ኢኮኖሚያዊ ማገገም ውስጥ መግባት ስለነበረባት መንግስት ከእነዚህ አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ ከመስራት ባሻገር በብዙ መልኩ ታዛዥነቱን ማንሳትም ጭምር ነበረበት። በዚህም በተለይ ብር ከዶላር አንፃር ያለው የምንዛሪ ዋጋ በተከታታይ እንዲወርድ በማድረጉ ረገድ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሰፊ ምክረ ሀሳባዊና የተፅዕኖ ሚና ነበረው።

 

ገዢው ፓርቲ  ከነበረው ኮሚኒስታዊ ተፈጥሮ አንፃር ከድርጅቶቹ ጋር አብሮ ለመስራት ያሳየው መለሳለስ ከነበረው መሰረታዊ ችግር አንፃርም ነበር። ሆኖም በሂደት በስልጣን የመጠናከር፤ ብሎም ኢኮኖሚያዊ ማገገሞች ሲታዩ ሁኔታዎች በሂደት እየተለወጡ መሄድ ጀመሩ። በተለይ ከ1997 ሀገራዊ ምርጫ ቀውስ በኋላ የወጡ በርካታ አነጋጋሪ ህጎች የገዢውን ፓርቲና የምዕራባዊያኑን ግንኙነቶች ይበልጥ ከማሻከር ባሻገር ኢህአዴግ የመንግስት ቁጥጥር ያየለበትን የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚከተል መሆኑን በግልፅ ማሳየት ጀመረ። የገንዘብ ተቋማት ከምዕራቡ ዓለም የሊብራል የፖለቲካ ፍልስፍና ጋር በተያያዘ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ያለምንም መንግስት ጣልቃ ገብነት በራሱ ህግጋቶች እንዲመሩ የሚፈልጉ በመሆናቸው ልዩነቶቹ ይበልጥ በግልፅ መንፀባረቅ ጀመሩ።

 

 ገዢው ፓርቲ የነፃ የኢኮኖሚ ሥርዓት (Free Market)  አካሄድን የሚቀበል መሆኑን ከገለፀ በኋላ፤ ገበያው ያለምንም መንግስት ጣልቃ ገብነት በራሱ የጨዋታ ህጎች ብቻ ይመራ የሚለውን አሰራር ግን የማይቀበል መሆኑን በሊቀመንበሩ በአቶ መለስ በኩል በተደጋጋሚ መግለፁን በስፋት ተያያዘው። የዚህ አስተምህሮ ጠንሳሽና አቀንቃኝ የነበሩት አቶ መለስ የቀደመውን የምዕራቡን አለም የሊብራል አስተሳሰብና አካሄድ በኒኦሊብራል የገበያ አክራሪነት ስም የበለጠ በማውገዝ በየመድረኩ ጎልተው መታየት የጀመሩት ከዚህ በኋላ ነበር።

 

 መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ የማረጋጋትን ሥርዓት ማስያዝን ብሎም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ደግሞ የግሉ ዘርፍ ሊገባባቸው በማይችሉ የተመረጡ ኢኮኖሚ ዘርፎች መዋዕለ ነዋይን በማፍሰስ በኢኮኖሚው ውስጥ የራሱን የሆነ ጉልህ ተሳትፎ ሊኖረው እንደሚገባ በገዢው ፓርቲ በኩል የተያዘ ጥብቅ የፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ አቋም ሆኖ በግልፅ የታየውም ከዚህ በኋላ ነበር። ባለሁለት አሀዝ የተባለው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገትም በምሳሌነት እየተጠቀሰ ማሳያ እንዲሆንም ተደርጓል።

 

 አቶ መለስ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ የውይይት መድረኮች ለመሳተፍ ባገኙባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ይሄንኑ ፍፁም ገበያ መር የሆነውን የምዕራቡን ዓለም ፖለቲካዊ የኢኮኖሚ ፍልስፍና ብዙም የማስኬድ መሆኑን በተደጋጋሚ ሞግተዋል።

 

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጊዜው ከኢትዮጵያ ባለፈ መላው ታዳጊ ሀገራት በተለይም አፍሪካዊያን ከምዕራቡ ዓለም ኢኮኖሚያዊ አካሄድ በተለየ መልኩ የራሳቸውን አዲስ የኢኮኖሚ ዕቅድና ሥልትን ነድፈው በነፃ ገበያና በግሉ ዘርፍ ከሚመራ የኢኮኖሚ አካሄድ ይልቅ፤ የግሉን ዘረፍ በስፋት ባሳተፈ መልኩ በመንግስት ቁጥጥር ባልራቀና በእሱም የበላይነት የሚመራ የኢኮኖሚ ሥርዓትን እንዲከተሉ የራሳቸውን ምክረ ሀሳብ በአፅንዖት ይሰጡ ነበር።

 

በተለይም እ.ኤ.አ በ2008 የተከሰተው ዓለም አቀፉን የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የምዕራቡ ዓለም መንግስታት ግዙፍ የፋይናስ ተቋማቶቻቸውን ከለየለት ክስረት ለመታደግ በጊዜው በመንግስት ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጋቸው አቶ መለስ ሀሳባቸውን በተጨባጭ ምሳሌ እያስደገፉ እንዲያስረዱም አስችሏቸው ነበር። ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ የሚለውን የፓርቲውን የፖለቲካ መስመርና ባህሪ ከቀደሙት የልማታዊ መንግስታት አስተምህሮ ጋር አዳቅሎ “ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ”  የሚል የራሱን የፖለቲካ ኢኮኖሚ አካሄድ ቀይሶ ሀገሪቱን መምራት ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።

 

አሁንም ቢሆን ይህ አይነቱ ጥብቅ የኢህአዴግ ፖለቲካዊ የኢኮኖሚ ዶግማ በምዕራቡ ዓለም ሊብራል አስተሳሰብ ተቀባይነት ያለው አይደለም። የዚህ የምዕራቡ ዓለም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተፅዕኖ መፍጠሪያ ዋነኛ መሳሪያዎች የሆኑት ደግሞ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና ዓለም ባንክ ናቸው። መንግስታት ከእነዚህ ተቋማት ጋር ለመስራት ግዴታ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች መካከል የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው በብድር መልኩ የሚለቁት ጠቀም ያለ የብድር ገንዘብ ነው።

 

ይህ የሚለቀቀው የብድር ገንዘብ አንድ ሀገር ስላስፈለገው ወይንም የመበደር አቅም ስላለው ብቻ የሚበደረው ገንዘብ ሳይሆን በብዙ ቅድመ ሁኔታዎች የሚፈቀድና የሚለቀቅ ነው። ከአቶ መለስ ህልፈተ ህይወት በኋላ በኢትዮጵያ በርካታ ነበራዊ ለውጦች ተከስተዋል። ባለፉት ዓመታ የተከሰቱት ተከታታይ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ኢኮኖሚው በነበረበት አካሄድ እንዳይቀጥል አድርጎታል። ባለሁለት አሃዝ የተባለው እድገት ወደ ነጠላ አሀዝ መውረዱ ተመልክቷል። እንደ ቻይና ያሉ አበዳሪ ሀገራት ቀደም ሲል ለኢትዮጵያ በስፋት የሚለቁትን ብድር ማቀዘቀቀዝን መርጠዋል። የሀገሪቱ የኤክስፖርት ገቢ ክፉኛ በማሽቆልቆሉ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመስፋት ላይ ነው።

 

እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች የገዢው መንግስት ባለስልጣናት በአቶ መለስ አስተምህሮ ፀንተው የግዙፎቹን የዓለም ባንክና የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት እጅ ጥምዘዛ የሚቋቁበት አቅም እንዳይኖራቸው አድርጓል። ይህም በመሆኑ መንግስ የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት ምክረ ሀሳብ በመተግበር በቅርቡ ብር ከዶላር አንፃር ያለው የምንዛሪ መጠን እንዲወርድ ማድረግ ግድ ሆኖበታል። በቀጣይም ከኢትዮጵያ መንግስት ባህሪ ውጪ የሆኑ በተፅዕኖ የሚታዩ ለውጦች ይኖራሉ ተብሎ ይታሰባል። በተለይም የፋይናሱንና የቴሌኮም ዘርፉን ከመንግስት መዳፍ የሚወጣበት አካሄድ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 እነዚህ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከመንግስታት ጋር አብረው ለመስራት በበርካታ ቅድመ የታጠሩ ናቸው። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ደግሞ የምዕራቡን ዓለም የኢኮኖሚ ፍልስና መሰረት ባደረገ መልኩ የተቃኙ በመሆናቸው በመንግስታት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

 

እነዚህ ሁኔታዎች ዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅትንም ሆነ ዓለም ባንክን በሰፊው ሲያስወቅሷቸው ቆይተዋል። እነዚህ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ታዳጊ ሀገራትን ሳይቀር በአባል ድርጅትነት ሳይቀር አቅፈው ይዘዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በአጠቃላይ እስከ 189 የሚደርሱ አባል ሀገራትን በውስጡ አቅፎ የያዘ ሲሆን በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም የዚሁ ተቋም አባላት ናቸው።

 

ሀገራቱ በአባልነታቸው ከባንኩ ቀጥተኛ ገንዘብ ብድር ከማግኘት ባለፈ የፖሊሲ ምክርና ደጋፍም ጭምር የሚያገኙበት ሁኔታ አለ። ሀገራት በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብተው የክፍያ ሚዛን ችግር ሲገጥማቸው የመታደጊያ ገንዘብ የሚለቅበት አሰራርም አለ።

 

የብድሩም ሁኔታ በተመለከተ ለታዳጊ ሀገራት በልዩ ሁኔታ በረዥም ጊዜ የሚፈቀድና  በአነስተኛ ወለድ የሚታሰብ የብድር አይነትን የሚፈቅድበት አሰራር አለ። ሆኖም ቅድመ ብድር መመዘኛውና የፖሊሲ ተፅዕኖው ፈተኛው የሆነው ይህ ድርጅት በተለይ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ያመጣው ተጨባጭ አዎንታዊ ተፅዕኖ ሲፈተሽ ግን ብዙም አመርቂ ሆነው አልታዩም።

 

በተለይ ከሰሃራ በታች ያሉት የአፍሪካ ሀገራት በዚህ ረገድ ውጤታማ ተጠቃሚነት አልታየባቸውም። በክርሲቲያን ላጋርድ የአዲስ አበባ ቆይታ የተንፀባረቀውም ይህ እውነታ ነው። ማኔጂግ ዳይሬክተሯ በዚሁ አዲስ አበባ ቆይታቸው ከሰሃራ በታች ያሉ 17 የአፍሪካ ሀገራት አጠቃላይ ኢኮኖሚ ክፉኛ እያሽቆለቀለ መሆኑን ገልፀው፤ ለዚህም ጉዳይ መፍትሄ ማፈላለጉ ግድ መሆኑን አመልክተዋል።

 

 የተባበሩት መንግስታት አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር በመሆን በጋራ በሰጡት መግለጫ በአፍሪካ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ አድገትን ለማምጣት በአህጉሪቱ አዲስ የልማት ሞዴል የሚያስፈልግ መሆኑን አመልክተዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በዚህ ደረጃ አፍሪካን በተመለከተ የመለሳለስ ሁኔታን በማሳየት በይፋ መግለጫ ሲሰጥበት ይሄው የአዲስ አበባው መረጃ የመጀመሪያው ነው ማለት ያስችላል። በቀጣይ ድርጅቱና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዲስ በጥናት የተደገፈ የመፍትሄ ሀሳብን ይዘው የሚመጡ መሆኑን አስታውቀዋል። ምን አይነት መፍትሄና መቼ? የሚለው ጉዳይ ግን ጊዜው ሲደርስ የሚመልሰው ይሆናል።

 

ኢትዮቴሌኮም  international Diamond prize for Excellence in Quality 2017 አሸናፊ መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አስታውቋል። ሽልማቱን ያዘጋጀው መቀመጫውን ሲውዘርላንድ ያደረገው Eurpean Society for Quality Research መሆኑን ይሄው መግለጫ ጨምሮ ያመለክታል።

 

ሽልማቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አንዷለም አድማሴ ህዳር 30 ቀን 2010 ዓ.ም በቦታው በመገኘት መቀበላቸው ታውቋል። እንድ ኩባንያው መረጃ ከሆነ የሽልማቱ አሸናፊ ተቋማት ምርጫ የተደረገው በደንበኞች አስተያየትና የገበያ ጥናት፣ ከተጠቃሚዎች በተገኘ መረጃ እንደዚሁም ይህንኑ ሽልማት ከዚህ በፊት በወሰዱ ተቋማት የሚሰበሰቡ ውጤቶችን መሰረት ያደረገ ነው።

በተያያዘ ዜና ኢትዮ ቴሌኮም የአፍሪካ የ2017 ምርጥ ቀጣሪ ኩባንያ ሽልማትን ያሸነፈ መሆኑንም አመልክቷል፡፡ በዚህም የአፍሪካ ምርጥ የገፅታ ብራንድ በተሰኘ መድረክ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ይሄንኑ ሽልማት የተቀበለ መሆኑን መረጃው ጨምሮ ገልጿል፡፡

 

እንደ ኩባንያው መረጃ ከሆነ ኩባንያው ከቀጠራቸው ከ17 ሺህ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች ባለፈ በ2 ሺህ የገጠር ቴሌኮም ማስፋፊያ ሥራ አስር ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ በመቻሉ ለሽልማቱ አብቅቶታል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የሰራተኞች ሥራ የመልቀቅ መጠንም ከ አንድ በመቶ በታች መሆኑ ሌላው ለዚሁ ሽልማት አሸናፊነት ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀስ መሆኑን ድርጅቱ የላከልን መረጃ ጨምሮ ያመለክታል፡፡ 

 

ሞጆ ከተማ ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች በተለየ ሁኔታ በርካታ እምቅ የእድገት ዕድሎች ያሏት ከተማ ናት። ከተማዋ ሰፊ የእድገት እድሎች እንዲኖሯት ያደረጓት ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ፣ በሀገሪቱ ትልቁ የሆነው ደረቅ ወደበን የያዘች መሆኗ፣ ከአዲስ አበባ አዳማ የተዘረጋው የፍጥነት መንገድ አካል መሆኗ፣ በአሁኑ ሰዓት በግንባታ ላይ ያለው የሞጆ-ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት መነሻ ሆኗ ማገልገሏ በዋነኝነት የሚጠቀሱ የከተማዋ የእድገት ዕድሎች ናቸው።

 

 ከዚህም በተጨማሪ ከአዲስ አበባ አዳማ ከተገነባው የፍጥነት መንገድ ጎን ለጎን እያገለገለ ያለው መሃል አገርን ከጅቡቲ ወደብ ጋር የሚያገናኘው ነባሩ መንገድም ሞጆ ከተማን አቋርጦ የሚያልፍ ነው። ሞጆ ይህ ብቻ ሳይሆን አራት የመግቢያ በሮችን የያዘች ከተማም ጭምር ናት።

 

 ከኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ከአዲስ አበባ አዳማ ከተገነባው የፍጥነት መንገድ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የሞጆ የፍጥነት መንገድ ነው። ይህ መንገድ 202 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። መንገዱ ከአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ሞጆ 52 ኪሎ ሜትር በመነሳት በደቡብ አቅጣጫ የመቂ፣ የዝዋይ (ንባቱ) አርሲ ነገሌ ከተሞችን በማገናኘት ሀዋሳ የሚገባ ነው።

 

 የሞጆ ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ከደቡብ አፍሪካ-ኬፕታውን እሰከ ግብፅ -ካይሮ የሚዘረጋው አህጉራዊ ሰፊ የመንገድ ኔትወርክ አካል እንዲሆን ታሳቢ ተደርጎ እየተገነባ ያለ መንገድ ሲሆን በሀዋሳ በኩል ኢትዮጵያን ከኬኒያ ጋር በማገናኘት የሞምባሳን ወደብ ለመጠቀም የሚያስችል ነው።

 

ሞጆ ከተማ ካላት ዘርፈ ብዙ እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም አንፃር የሚገባትን ያህል የኢንቨስትመንት ፍሰት አግኝታለች ባይባልም ከተማዋ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩና ከ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታልን ያስመዘገቡ 199 ባለሀብቶችን እያስተናገደች መሆኗን ከከተመዋ አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ይህም የኢንቨስትመንት ፍሰት ከ9 ሺህ ላላነሱ ዜጎች  ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ይሄው መረጃ ጨምሮ ያመለክታል።

 

ከተማዋ ራሷን የበለጠ በማስተዋወቅ ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ በቅርቡ አንድ የንግድ ባዛርና ኤግዚብሽን የምታካሂድ መሆኑ ታውቋል። ይህም “ሞጆ የትራንዚትና ሎጅስቲክስ የልማት አገናኝ የንግድ ባዛር እና ኤግዚብሽን በሎጂስቲክስ ከተማ” በሚል የሚካሄደው ኤግዚብሽን ከታህሳስ 15 እስከ 28 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

 

 ይህም ባዛርና ኤግዚብሽን የከተማዋን እምቅ የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት አቅም የበለጠ ለማስተዋወቅ እገዛ ያደርጋል ተብሏል። 16 የሚደርሱ የቆዳ ፋብሪካዎች አሉ። በሞጆ ከተማ በህብረተሰቡ ከሚነሱት ችግሮች መካከል አንዱ ከቆዳ ፋብሪካዎች የሚለቀቀው የተበከለ ኬሚካል ፍሳሽ ነው።

 

 በከተማዋ 16 የሚሆኑ የቆዳ ፋብሪካዎች ያሉ ሲሆን ከፋብሪካዎቹ የሚወጣው ፍሳሽ ኬሚካል በነዋሪው ብሎም በአርሶ አደሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያሳደረ መሆኑን በቅሬታ መልክ ይነሳል።

 የሞጆ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እልፍነሽ ቤቻ  ከፋብሪካዎቹ የሚለቀቀው ኬሚካል በአካባቢ ብሎም በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ መቆየታቸውን ገልፀው፤ይሁንና ችግሩን በመፍታቱ ረገድ በአሁኑ ሰዓት ጅምሮች መኖራቸውን አመልክተዋል።

 

ሌላው በእነዚሁ ቆዳ ፋብሪካዎች ላይ የሚነሳው  ቅሬታ ከሰራተኞች ደህንነት ብሎም ተገቢውን ክፍያ ካለመክፈል ጋር በተያያዘ ነው። ወይዘሮ እልፍነሽ ችግሩ መኖሩን ገልፀው ይሁንና የሚታየው ችግር በሁሉም ድርጅቶች ሳይሆን በተወሰኑ ድርጅቶች መሆኑን ገልፀውልናል። ይህም ችግር ከቅጥር ጀምሮ እስከ ሰራተኛ ደህንነት (Safety) የሚዘልቅ መሆኑንም አመልክተዋል።

 

 አንድ የቆዳ ፋብሪካ ከሀገሪቱ የአሰሪና ሰራተኛ ህግ ውጪ ሰራተኞቹን በሙሉ በቀን ስራ ብቻ ቀጥሮ ሲያሰራ የነበረ መሆኑን በዋቢነት ያመለከቱት ከንቲባዋ፤ በዚህም ፋብሪካው “ሰራ የለኝም” ካለ ሰራተኞቹ እዚያው ውለው ምንም አይነት የክፍያ ሂሳብ ሳይታሰብላቸው እንዲሁ ወደቤታቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንደነበር ገልፀውልናል።

 

 መስተዳድሩ የእነዚህን አንድ ሺህ ሰባት መቶ የሚሆኑ ሰራተኞች  ቅሬታንም በመስማት የከተማ መስተዳድሩ ከባለሀብቱ ጋር ባደረገው ውይይት 60 በመቶ የሚሆኑት ሰራተኞች በቋሚነት፤ እንደዚሁም 40 በመቶ የሚሆኑትን ደግሞ በጊዜያዊነት የቅጥር ውል እንዲፈፅሙ የተደረገ መሆኑን ወይዘሮ እልፍነሽ ጨምረው አመልክተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሰራተኞች በሥራ ላይ ሳሉ ተገቢው ደህንነትን እንዲያገኙ ብሎም በምሽት ሥራ ወቅትም ተገቢው የመኝታ ቦታ እንዲኖርም ከባለሀብቶቹ ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ተግባር የተገባ መሆኑን በከንቲባዋ ተገልጿል።

 

 የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ካለመጠቀም ጋር በተያያዘ ከፋብሪካዎቹ የሚወጡት የተበከሉ ኬሚካሎች በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱበት ያለበት ሁኔታ መኖሩን በጥናት የተረጋገጠ መሆኑን ወይዘሮ እልፍነሽ አመልክተዋል። ችግሩንም በዘላቂነት ለመፍታት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች መኖራቸውን ገልፀውልናል። እነዚህም ሥራዎች ፋብሪካዎቹ የራሳቸው የሆነ የፍሳሽ ኬሚካል ማጣሪያ (Treatement Plant) እንደኖራቸው ማድረግ ነው ተብሏል።

 

ግብፅ ያለባትን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ፍላጎት ለማጣጣም ጥረት በማድረግ ላይ ስትሆን ከሰሞኑም የዚሁ አካል የሆነውን የኑሉሌር የአሌክትሪክ ኃይል ለመገንባት የሚያስችላትን ሥምምነት ከሩስያ ጋር ተፈራርማለች። የስምምነቱ ፊርማ ሥነስርዓት የተካሄደው በካይሮ ሲሆን በዚሁ ስምምነት ላይም የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ እና የሩስያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ተገኝተዋል።

 

 ይሄው ዳባ በሚል የሚታወቀው ግዙፍፕሮጀክት 21 ቢሊዮን ዶላር ወጪን የሚጠይቅ መሆኑ ሮይተርስ በዘገባው ያመለከተ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀውም እ.ኤ.አ በ2027/2028 መሆኑን ዘገባው ጨምሮ ያመለክታል።

 

በተደረሰው ስምምነት መሰረትም ሩስያ የግንባታውን ወጪ 85 በመቶ የምትሸፍን ይሆናል። በ2015 በተደረሰው የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት ሩስያ እያንዳንዳቸው 1 ሺህ 2 መቶ ሜጋ ዋት ለማመንጨት የሚያስችሉ 4 የኑኩሌር ማብላያዎችን በግብፅ ምድር መገንባት ይጠበቅባታል። በዚህም ግብፅ ከዚህ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቅ በኋላ አሁን ካላት አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ተጨማሪ 4 ሺህ 8 መቶ ሜጋ ዋት የኑኩሌር ኃይልን የምታገኝ ይሆናል።

 

ሁለቱ ሀገራት ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ያላቸውን የንግድ ግንኙነት እያጠናከሩ ሲሆን ግንኙነቱም በአካባቢው ጆኦፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በወታደራዊ ግንኙነት ዘርፎች ላይ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን የአህራም ኦንላይን ዘገባ ያመለክታል። ሁለቱ ሀገራት ከኢኮኖሚ ግንኙነቱ ባሻገር በአካባቢው ላለው የሰላም እጦት መፍትሄ ለማፈላለግ በጋራ እየሰሩ መሆኑን መረጃዎቹ ያመለክታሉ።

 

 በዚህም በእስራኤል ፍልስጤም የሰላም ጉዳይ እንደዚሁም በሶርያና በሊቢያ ጉዳይም ሁለቱ ሀገራት በጋራ ለመስራት በፑቲን የካይሮ ቆይታ ወቅት ሰፊ ውይይት የተደረጋበቸው መሆኑ ታውቋል። ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን  ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በማጠናከር በአሁኑ ሰዓት ያላቸው ዓመታዊ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት መጠን 4 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ መሆኑን የአህራም ኦንላይን ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል።

 

ወደ ማምረት ሥራ ከገባ ከሁለት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ዋን ውሃ በሀገር ውስጥ ላለው ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት እንደዚሁም ዓለም አቀፉን ገበያ ለመቀላቀል አሁን ያለውን የማምረት አቅም በእጥፍ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ድርጅቱ እስከዛሬ ድረስ ያስመዘገበውን የሥራ ዓመራር ውጤት  እንደዚሁም የምርጥ ጥራቱን ውጤታማነት አስመልክቶ ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 30  ቀን 2010 ዓ.ም ለሰራተኞቹ የማበረታቻ ሽልማትን አበርክቷል።

ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በሰዓት 14 ሺህ ሊትር ውሃን አጣርቶ በማሸግ ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን በቀጣይ በሚኖረው ማስፋፊያም በሰዓት 32 ሺህ ሊትር ውሃን አጣርቶ ለገበያ ለማቅረብ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን የድርጅቱ የጥራት ማረጋገገጫ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙና ሁሴን ገልፀዋል።  በሁለት ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ሥራ የጀመረው “ዋን ውሃ” ሰበታ አካባቢ ከሚገኘው ሞጎሌ ተራራ ሥር ከሚፈልቅ ውሃ የሚመረት ነው።

ኩባንያው በአሁኑ ሰዓት 365 ቋሚ ሰራተኞች ያሉት መሆኑ የታወቀ ሲሆን በቀጣይ በዕቅድ ከተያዘው የማስፋፊያ ሥራ ጋር በተያያዘም ለተጨማሪ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ድርጅቱ በአመራረቱ ሂደት የአይ ኤስ ኦ (ISO) ጥራት የምስክር ወረቀትን አግኝቷል።

 

የናይጄሪ መንግስት ናይጄሪያ በቅርቡ በኢትዮጵያ የተካሄደውን የሞባይል ምዝገባ ተከትሎ ልምድ ለመቅሰም ልዑካን ቡድን የላከች መሆኗን ኢትዮ ቴሌኮም ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የልዑካን ቡድኑ አባላት በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በኢትዮ ቴሌኮም መስሪያቤቶች በመገኘት ለዚሁ ሥራ የሚውሉትን መሳሪያዎች የጎበኙ መሆኑን መግለጫው ያመለክታል። በልዑካን ቡድኑ ጉብኝት ወቅትም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አንዱአለም አድማሴና በመገናኛ ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር የስታንደርዳይዜሽንና ሬጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባልቻ ሬባ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ መሆኑ ታውቋል።

በዚሁ ገለፃ ወቅትም ምዝገባው በህገ ወጥ መንገድ ሀገር ውስጥ የገቡ የሞባይል ቀፎዎችን ለመለየት ብሎም በቴሌኮም ማጭበርበር የተሰማሩ አካላትንም ለመቆጣጠር ያስቻለ መሆኑን አቶ ባልቻ መገለፁን ይሄው መግለጫ ያመለክታል።

ለምዝገባ ሥርዓቱ ማከናወኛ የሚውለውን መሳሪያ ለኢትዮጵያ ያቀረበው ኢንቪጎ የተባለ ኩባንያ ሲሆን፤ የዚሁ ኩባንያ ሥራ  አስፈፃሚ ሚስተር ፉአድጎራኢቭ ለናይጄሪያው ልዑካን ቡድን ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡ መሆኑ   ታውቋል።

 

ዳሸን ባንክ ህዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው የባለአክስዮኖች 23ኛ መደበኛና 21ኛው መደበኛ ዓመታዊ ስብሰባ በ2016/17 በጀት ዓመት 980 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ። ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ሲታይ የ29 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ያሳየ መሆኑ ተመልክቷል።

 

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት በዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተካ አስፋው አማካኝነት የቀረበ ሲሆን በዕለቱም በቀረበው ሪፖርት እንደተመለከተው በ2016/17 በጀት ዓመት የባንኩ ዓመታዊ የሃብት መጠን በ 6 ቢሊዮን ብር እድገት በማሳየት 34 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል። ዓመታዊ የተቀማጭ ገንዘቡ መጠንንም በ22 በመቶ በማሳደግ 27 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ማድረሱ ተገልጿል።

 

 በሪፖርቱ አጠቃላይ ዳሰሳ በዓመቱ በዓለም አቀፍ፣ በሀገር አቀፍና በባንኩ ሴክተር ያለው አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አጠር ባለ ምልከታ ለተሰብሳቢው ቀርቧል። በዚህም አጠቃላይ የአለም አቀፉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ቀደም ካሉት ዓመታት የተሻለ መሆኑ ተመልክቷል። ይሁንና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት አጠቃላይ እድገት ከታሰበው በታች እንደነበር በዚሁ ሪፖርት ላይ ተካቶ ቀርቧል። የኢትዮጵየን የኢኮኖሚ እድገት በተመለከተም ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የታየውን ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠል አለመቻሉ የተመለከተ ሲሆን፤ በተለይ የወጪ ንግድ መቀዛቀዝና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር በኢኮኖሚው ላይ የራሱን የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረ መሆኑን በዚሁ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል።

 

ሪፖርቱ የዳሰሳ አድማሱን በማጥበብ የባንኩ ዘርፍ አጠቃላይ ሁኔታም ተመልክቷል። እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ በሀገሪቱ ዘርፉን የተቀላቀለ አዲስ ባንክ ባይኖርም በሀገሪቱ ያሉት ባንኮች ግን በከፍተኛ ሁኔታ ቅርንጫፎቻቸውን የማስፋትና ተደራሽነታቸው ላይም በሰፊው ሰርተዋል። ዳሸን ባንክም የዚሁ ቅርንጫፍን የማስፋት ሥራ አንዱ አካል መሆኑን ያመለከቱት አቶ ተካ፤በዚህም ባንኩ ባለፈው ዓመት ብቻ 83 ቅርንጫፎችን  የከፈተ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

ይህም የባንኮች ቅርንጫፍ መስፋፋት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውንም የተቀማጭ (ቁጠባ) መጠንንም ከፍ እያደረገው የሄደ መሆኑ ተመልክቷል። የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አስፋው አለሙ በበኩላቸው ከባንኩ አጠቃላይ ሀብት ውስጥ 51 በመቶ የሚሆነው በብድር መልክ ወጪ የተደረገ መሆኑን ለጉባኤተኛው ገልፀዋል።  ባንኩ የተቀማጭ ገንዘቡን ከፍ በማድረጉ ረገድ የቅርንጫፎቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ፤ ብሎም ሀብትን ለማሰባሰብ በተሰራው ሥራ (Deposit Mobilisation) ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው በፕሬዝዳንቱ ገለፃ ተመልክቷል።

 

ይህ ብቻ ሳይሆን ባንኮች የሚለቁት የብድር መጠንም ከፍ እንዲል ያደረገ መሆኑንም ሪፖርቱ ጨምሮ ያመለክታል። ዳሸን ባንክ ከዚህ አንፃርም ሂሳብ ከተዘጋበት ባለፈው ዓመት የሥራ ዘመን ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ያሰራጨ መሆኑን ይኸው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት ይገልፃል። ይሁንና ከወጪ ንግድ መቀዛቀዝ ጋር በተያያዘ በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ ባንኩ ደንበኞቹ የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሪ፤ በመጠንም ሆነ ጊዜውን በጠበቀ መልኩ ማቅረብ አለመቻሉን አቶ ተካ አመልክተዋል።

 

 ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር አሁንም ድረስ በተባባሰ ሁኔታ ቀጥሏል ተብሏል። እንደ አቶ ተካ ገለፃ በእነዚህ ተግዳሮቶች ውስጥም ቢሆን ባንኩ 980 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍን አግኝቷል። ባንኩ ካለፉት ዓመታት በተለየ ሁኔታ ለሰራተኞቹ 70 ሚሊዮን ብር የሁለት ወር ተኩል የማበረታቻ ቦነስ የሰጠ መሆኑን ያመለከቱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፤ ይህም የገንዘብ መጠን ከባንኩ ገቢ ላይ ባይቀነስ ኖሮ የባንኩ የትርፍ መጠን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ይሆን ነበር።

 

ይህም የተመዘገበው የትርፍ መጠን እ.ኤ.አ በ2015/16 ዓ.ም ከተመዘገበው የትርፍ መጠን ጋር ሲነፃፀር የ 3 በመቶ ወይንም በብር በ29 ነጥብ 1 ሚሊዮን እድገት ማሳየቱን ሪፖርቱ ጨምሮ ያመለክታል። ባንኩ ካገኘው አጠቃላይ ትርፍ ውስጥም 212 ሚሊዮን ብር በታክስ መልኩ ወደ መንግስት ካዝና ገቢ ማድረጉንም ተገልጿል።

 

 እንደ አቶ አስፋው ገለፃ የተቀማጭ ሂሳብ ደንበኞች ቁጥር 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ደርሷል። ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር በንፅፅር ሲታይ የ23 በመቶ  እድገት የታየበት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጨምረው አመልክተዋል። የባንኩ ተበዳሪ ደንበኞች ቁጥርም የ19 በመቶ እድገትን በማሳየት 12 ሺህ 8 መቶ 48 የደረሰ መሆኑን የፕሬዝዳንቱ ገለፃ ጨምሮ ይገልፃል።

 

 የባንኩ የክፍያ ካርድ ተጠቃሚዎችም ቁጥር በ 29 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑ በፕሬዝዳንቱ ሪፖርት የተጠቀሰ ሲሆን በቁጥር ደረጃም 557 ሺህ የደረሰ መሆኑን ነው ፕሬዝዳንቱ የጠቀሱት። የኤቲኤም ማሽኖችንም በተመለከተ ከተገዙ የተወሰኑ ዓመታትን ያሳለፉና የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት ማሽኖችን በአዲስ ኤቲኤም ማሽኖች የመተካቱ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የቀረበው ሪፖርት ያመለክታል።

 

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረ ማሪያም ወረዳ በክልሉ የመጀመሪያው የሆነ የመድሃኒት ፋብሪካ ተገንብቶ ወደ ሥራ ገብቷል። ፋብሪካው ተገንብቶ ወደ ሥራ የገባው ሂውማን ዌል በተባለ የቻይና ኩባንያ ሲሆን በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አማካኝነት ባለፈው ዕሁድ ህዳር 24 ቀን 2010 ዓ.ም ተመርቋል። የመድሃኒት ፋብሪካው የተገነባው ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ ከተማ 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቱለፋ በተባለች ከተማ ነው።

 

የመድሃኒት ፋብሪካው ባለቤት የሆነው ሂውማን ዌል ፋርሲማዩቲካል ኢትዮጵያ የአለም አቀፉ ሂውማን ዌል ሄልዝ ኬር ግሩፕ አካል ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ለገነባው የመድሃኒት ፋብሪካ ወጪ ያደረገው አጠቃላይ የኢንቨስትመንት መጠን 20 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ታውቋል። ኩባንያው በቀጣይ በሶስት ዙር በሚያካሂደው የማስፋፊያ ሥራ የኢንቨስትመንቱን መጠን ወደ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑ ተመልክቷል። ኩባንያው ወደ ምርት የገባው የፋብሪካውን መሰረት ድንጋይ በጣለ ከአንድ ዓመት ብዙም ባልራቀ ጊዜ ወስጥ ሲሆን፤ በዚህም ፋብሪካው ከ30 በላይ መድሃኒቶችን የሚያመርት መሆኑ ታውቋል።

 

 ከእነዚህም የመድሃኒት አይነቶች መካከል በታብሌት መልኩ የሚዋጡ፣በመርፌ የሚሰጡና በሽሮፕ መልኩ የሚጠጡ መኖራቸውን የኩባንያው መረጃ ያመለክታል። ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሥራ ሲገባ እስከ 3 መቶ ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሏል።

 

ፋብሪካው በምርቶቹ ከኢትዮጵያ ባለፈ የምስራቅ አፍሪካ ገበያንም ለማስፋት እቅድ ይዟል። ኩባንያው ከቻይና ባለፈ በበርካታ በአውስትራሊያና እስያ ሀገራት እንደዚሁም በሰሜን አሜሪካ አድማሱን እያሰፋ ሲሆን በአፍሪካም ኢትዮጵያን ጨምሮ በማሊ እና ቡርኪናፋሶ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል። ሂውማን ዌል ኩባንያ በጥቂት ኮሌጅ ተማሪዎች እ.ኤ.አ በ1939 የተመሰረተ መሆኑን የኩባንያው ታሪክ ያመለክታል። ከዚያም ራሱን በማሳደግ ዛሬ በዓለማችን አሉ ከሚባሉት መድሃኒት አምራች ኩባንያዎች መካከል አንዱ ለመሆን የበቃ መሆኑን ከራሱ ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ ይገልፃል።

 

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር የሰሜን ሸዋ ዞን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ካለው የኢንቨስትመንት ፍስት አኳያ የነበረው ተጠቃሚነት ያን ያህል የነበረ መሆኑን አስታውሰው፤ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግን የዞኑ የግል ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው እየጨመረ መሄዱን አመልክተዋል። እንደ አቶ የሺጥላ ገለፃ በዞኑ ከአጠቃላይ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ ውስጥ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ብቻ ከ34 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው 646 ፕሮጀክቶች ፈቃድ ወጥቶባቸዋል። 301 ያህል ፕሮጀክቶች ደግሞ 526 ሄክታር የለማ መሬት የወሰዱ መሆኑን ያመለከቱት ዋና አስተዳዳሪው፤ከእነዚህም ውስጥ ሃያ ስምንቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት የገቡ መሆናቸውን ገልፀዋል። 84 የሚሆኑት ፕሮጀክቶች ደግሞ በግንባታ ላይ መሆናቸውን ዋና አስተዳዳሪው ጨምረው አመልክተዋል።

 

ከእነዚህም በግንባታ ላይ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከልም ብዙዎቹ በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ምርት ሥራ ይገባሉ ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ 112 አዳዲስ ፕሮጀክቶች የመሬት ጥያቄ አቅርበው ውሳኔ እየተጠባበቁ መሆኑን አቶ የሺጥላ ገልፀዋል።

 

በኢትዮጵያ የቻይና ኢምባሲ የኢኮኖሚና ንግድ አማካሪ የሆኑት ሚስስ ሊዩ ባደረጉት ንግግር የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረ መሆኑን ገልፀው፤ በኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትም ቻይና ቁጥር አንድ ሀገር መሆኗን አመልክተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቻይና የኢትዮጵያ ዋነኛ አለም አቀፍ የንግድ ሸሪክ (Trade Partner) መሆኗን በመግለፅ፤ ኢትዮጵያና ቻይና ካላቸው የሁለትዮሽ  ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ባሻገር በጤናው ዘርፍም የቆየ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆኑን አስታውሰዋል።

 

 በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ቻይናዊያን የጤና ባለሙያዎች ወደ  ኢትዮጵያ በመመጣት የተለያዩ ሙያዊ እገዛዎች ያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል። ቻይና ለኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ እያደረገችው ካለው እገዛ ጋር በተያያዘ የጥሩነሽ ቤጂግ ሆስፒታል አንዱ ማሳያ ተደርጎ የሚታይ መሆኑን ሚስስ ሊዩ ጨምረው አመልክተዋል።

 

እ.ኤ.አ በ2015 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው አስረኛው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ቻይና ከአፍሪካ ጋር ካላት ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ባሻገር በጤናውም ዘርፍ ከአፍሪካዊያን ጋር በጋራ ለመስራት ሰፊ እቅድ ያላት መሆኑን በቻይና ፕሬዝዳንት በኩል ተገልፆ እንደነበር ሚስ ሊዩ ጨምረው በማስታወስ፤ በኢትዮጵያ ያለው የዘርፉ ኢንቨስትመንትም የዚሁ አቅጣጫ አካል መሆኑን አመልክተዋል።

 

ቻይና በቀጣይም በኢትዮጵያ ያለውን የጤናውን ዘርፍ ኢንቨስትመንትም ለማበረታታት በብዙ መልኩ በስፋት የምትሰራ መሆኗን በአማካሪዋ በኩል  ተገልጿል። የመድሃኒት ማምረቻና ማቀነባባሪያ ኢንዱስትሪያቸውን ያላዳበሩ ታዳጊ ሀገራት የውጭ መድሃኒት አቅርቦት ጥገኛነታቸው ለበርካታ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እያጋለጧቸው መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከእነዚህም ችግሮች መካከል ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችና ፈዋሽነት የሌላቸው የውሸት መድሐኒት ምርቶች ማራገፊያ መሆን ተጠቃሽ ነው። እነዚህን ችግሮች ለመከላከልም ሀገራት ሰፊ የሆነውን የመድሃኒት አቅርቦት ድርሻ በራሳቸው የምርት አቅርቦት እንዲሸፍኑ ይመከራል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው መድሃኒትን በሀገር ውስጥ ማምረቱ ምርቱን በቅርበት ለማግኘት ከማስቻሉም ባሻገር ፋብሪካው ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚኖረውንም የላቀ ጠቀሜታ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል። ከዚህም በተጨማሪ የመድሃኒት ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ብሎም ሀገሪቱ ለመድሃኒት ግዢ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማዳንም በኩል መሰል ፋብሪካዎች የሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በቀላሉ የማይታይ መሆኑን አመልክተዋል።

 

በአፋር ክልል ኤርታሌ አንድ የጀርመን ቱሪስት የተገደለ መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል። እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ ከቱሪስቱ በተጨማሪ አንድ ኢትዮጵያዊ አስጎብኚም የመቁሰል አደጋ ደርሶበታል። በቱሪስቱ ላይ ጥቃቱ የተሰነዘረው በኢትዮ ኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ላይ ሲሆን ከኤርትራ አካባቢ የተነሱ ታጣቂ ኃይሎች የተሰነዘረ ጥቃት ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬን አሳድሯል። ጥቃቱን ተከትሎም የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ወደ አካባባቢው በሂሊኮፕተር የደረሱ መሆኑን ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። በአካባቢው ካለው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ  ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ወደ ቦታው የሚጎርፈው የቱሪስት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።  በኤርታሌ አካባቢ በቱሪስቶች ላይ መሰል ጥቃት ሲደርስ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ በ2012 በተመሳሳይ መልኩ ከኤርትራ አካባቢ ሰርገው የገቡ ታጣቂ ኃይሎች በቱሪስቶች በአካባቢው ጉብኝት ሲያደርጉ ቱሪስቶች ላይ ጥቃትን ከመሰንዘር ባለፈ  አንዳንዶቹን አፍነው የወሰዱበት ሁኔታ እንደነበርም ይታወሳል።

ኤርታሌ አካባቢ ከሚታየው ከፍተኛ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ ቦታው የበርካታ የውጭ ቱሪስቶች መስህብ ቢሆንም ከኢትዮ ኤርትራ ያልተፈታ የድንበር ችግር ጋር በተያያዘና የፀጥታው ሁኔታም አስጊነት አንዳንድ ሀገራት ተጓዥ ቱሪስቶቻቸው ወደ ቦታው እንዳይሄዱ ምክር የሚለግሱበት ሁኔታ ቢኖርም የአካባቢው የቱሪስት ፍሰት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የመጨመር ሁኔታ የሚታይበት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።¾

 

አንድ የኢንሹራንስ ዋስትና የተገባለት ተሽከርካሪን አደጋ ከደረሰበት በኋላ በውሉ መሠረት ኢንሹራንሶች ጉዳት የደረሰበትን ተሽከርካሪ ለማስጠገን ወይንም ምትክ ተሽከርካሪን ለባለቤቱ ለመስጠት የሚወስደውን ረዥም ጊዜ ተከትሎ በባለቤቶቹ ላይ የሚፈጠረውን የተሽከርካሪ እጦት ለመቅረፍ ብሎም ጊዜውን ለማሳጠር የሚያስችል ሥርዓትን የተዘረጋ መሆኑን ዘ አልትሜት ኢንሹራንስ ብሮከር ከሰሞኑ ገልጿል።

ድርጅቱ በሰጠው መግለጫ አንድ ተሸከርካሪ አደጋ ከደረሰበት በኋላ ተሸከርካሪው ጋራጅ ገብቶ፤ ተጠግኖ ለመውጣት ወራት ሊፈጅ የሚችል መሆኑን አመልክቶ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የኢንሹራንስ ደንበኞች ጉዳዩ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ ተሽከርካሪ አልባ የሚሆኑበትን ሁኔታ መኖሩን አመልክቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ደንበኞቹ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ለማከናወን ሲሉ ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ለመከራየት ተጨማሪ ወጪን ለማውጣት የሚገደዱ መሆኑን ኃላፊዎቹ አመልክተዋል።

ይህንንም ችግር ለመፍታት ድርጅቱ ምትክ በሚል የሚጠራ አገልግሎት መጀመሩ የተመለከተ ሲሆን ይህም አገልግሎት ደንበኞች ተሽከርካሪያቸው በአደጋ ምክንያት ጋራጅ በጥገና ላይ ሲሆን ተሽከርካሪው ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት እስከሚጀምር ድረስ ባለቤቶቹ ምትክ ተሽከርካሪ የሚያገኙበት አሰራር መሆኑ ተመልክቷል። አንድ የተሽከርካሪ ባለቤትም የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ካስፈለገም ባለቤቱ የኢንሹራንስ ውሉን በአልትሜት ኢንሹራንስ ብሮከር በኩል መግዛት የሚጠበቅበት መሆኑ ተገልጿል። ይህ የምትክ አገልግሎት ለጊዜው በአውቶሞቢሎች የሚጀመር መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊዎቹ፤ በሂደትም አድማሱን ወደ ሌሎች ተሽከርካሪዎች ያሰፋል ብለዋል።

ድርጅቱ  ከዚህም በተጨማሪ “ሎሌ” የሚል ስያሜ የተሰጠው አገልግሎትንም የሚጀምር መሆኑንም አስታውቋል። ይህም አገልግሎት አንድ ደንበኛ ኢንሹራንስ ከገባ በኋላ በኢንሹራንስ ውሉ መሰረት ተገቢውን ካሳ እንዲከፈለው ለማድረግ እገዛ የሚያደርግ ነው ተብሏል። በዚህም አገልግሎት ድርጅቱ ለደንበኞቹ በኢንሹራንስ ውል መሠረት የካሳ ክፍያቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያገኙ፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘም  የደንበኞቹን ጥያቄ ለማቅረብ፣ ለመከታተል፣ ለመደራደርና ለማስፈፀም የሚሰራ መሆኑ ታውቋል። ድርጅቱ በዚህ ዙሪያ በሚሰጠው አገልግሎት ራሱን እንደ “አገልጋይ” እንደዚሁም ደንበኞቹን እንደ “ጌታ” በመቁጠር “ሎሌ” የሚለውን ስያሜ የጠቀመ መሆኑ ተመልክቷል።

Page 7 of 67

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us