You are here:መነሻ ገፅ»arts»ፀጋው መላኩ - Sendek NewsPaper
ፀጋው መላኩ

ፀጋው መላኩ

 

ከግብር አጣጣልና ክፍያ ጋር በተያያዘ በንግዱ ማህበረሰብና በታክስ አስከፋዩ ኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መካከል አለመግባባቶች ከተፈጠሩ ዋል አደር ብለዋል። የያዝነው ዓመት የግብር ውዝግብ የተነሳው አዲሱን የቀን ገቢ ግምት የተንተራሰ የግብር አጣጣልን ተከትሎ በርካቶች በእጅጉ የተጋነነ ግብር የተጣለባቸው መሆኑን በመግለፃቸው ነው። ያም ሆኖ በርካታ ቅሬታዎች ተሰምተውና ለአቤቱታዎችም ምላሽ ተሰጥቶባቸው የሚበዛው የንግድ ማህበረሰብ የግብር ግዴታውን በአግባቡ የተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ሲገልፁ ይሰማሉ።

 

በግብር አጣጣሉ ዙሪያ ቅሬታ እያሰሙ ካሉት የንግድ ማህበረሰብ አካላት መካከልም የትራንስፖርት አገልግሎት ባለንብረቶች እንደዚሁም የእህል ወፍጮ ሥራ ላይ የተሰማሩ የንግዱ ማህበረሰብ ክፍሎች ይገኙበታል። በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩት የንግዱ ማህበረሰብ ክፍሎች የተጣለባቸው የግብር መጠን ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። በዚሁ ዙሪያም ባሳለፍነው ሰኞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከትራንስፖርት አገልግሎት ባለንብረቶችና ከወፍጮ ቤት ባለቤቶች ጋር ሰፋ ያለ ውይይትን አካሂዷል።

 

 በእለቱም በነጋዴዎቹ በርካታ ቅሬታዎች ተነስተዋል። ከተነሱት ጥያቄዎችና ቅሬታዎች መካከልም የግብር ትመናው ግልፅ አይደለም። በተለያዩ ክፍለ ከተሞችና ክልሎች ያለው የግብር አጣጣል ወጥነት የሌለው ነው። የግብር ደንቡ የወጣው ነጋዴው ሳይመክርበት ነው። በርካታ ተሽከርካሪዎች ያላቸው የአገልግሎት አቅም (Performance) የተለያየ ሆኖ ሳለ፤ የግብር አጣጣሉ ግን አንድ አይነት ነው።ተሽከርካሪዎች የሚሰሩበት ቀን ውስን ቢሆንም የሚጣልባቸው ግብር ግን ዓመቱን ሙሉ እንደሰሩ ተደርጎ በ365 ቀናት በማባዛት ነው፣ ካሽ ሬጂስተር ለነጋዴው ቢሰጥም ግብሩ የሚሰራው ግን የካሽ ሬጂስተርን መረጃ መሰረት ያደረገ አይደለም የሚሉትና ሌሎች በርካታ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ተነስተዋል።

 

ነጋዴዎቹ ከዚህም በተጨማሪ ቀደም ሲል ሲከፍሉት የነበረውን የግብር መጠን በመግለፅ በዘንድሮው ዓመት እንዲከፍሉ የተጠየቁትን ብሎም የከፈሉትን የግብር መጠንም በንፅፅር አሳይተዋል። በዚሁ ዙሪያ አንድ የወፍጮ ቤት ባለቤት ባቀረቡት ቅሬታ ከዚህ ቀደም 645 ብር ዓመታዊ ቁርጥ ግብር ሲከፍሉ የነበረ መሆኑን ገልፀው ሆኖም በአዲሱ የግብር ተመን የተጣለባቸው የግብር መጠን ግን ወደ 11 ሺህ 834 ብር ከፍ ያለ መሆኑን ገልፀዋል።

 

አቶ አረቡ አልየ ይባላሉ። የሁለት ደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ባለንብረት ናቸው። ነዋሪነታቸው በአዳማ ከተማ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ የመጡት በዚሁ የገቢዎችና ጉምሩክ ስብሰባ ለመካፈል መሆኑን ገልፀውልናል። በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ባገኘናቸው ወቅት በሰጡት ማብራሪያ፤ የመጨረሻው የስብሰባው ውጤት ከተስፋ የዘለለ ሆኖ እንዳላገኙት ገልፀውልናል። በግብር አጣጣሉ በኩል በተለይ ወጥነት የሚታይበት ሆኖ አለመገኘቱ አንዱ የቅሬታቸው ምንጭ ነው። እሳቸው ግብር የሚከፍሉት በሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎቻቸው ነው። ሁለቱም ተሽከርካሪዎቻቸው አንድ አይነት ሞዴል፣ የመጫን አቅምና የስሪት ዘመናቸውም ተመሳሳይ ቢሆንም፤ የሁለቱ ተሽከርካሪዎች ፋይል በተለያየ ክፍለ ከተሞች በመገኘቱ ብቻ የተለያየ ግብርን የሚከፍሉበት ሁኔታ መፈጠሩን በመግለፅ፤ ይህም የግብር አጣጣሉ ምን ያህል ወጥነት የሌለውና በአጣጣሉ ሂደትም ታሳቢ ተደርጎ የሚወሰደው ግብዓት ምን እንደሆነ ያልገባቸው መሆኑን ገልፀውልናል።

 

አንድ ተሳታፊም ባለፈው በጀት ዓመት 18 ሺህ ብር ግብር ከፍለው በያዝነው ዓመት ግን 98 ሺህ ብር የተጠየቁ መሆኑን አመልክተዋል። የግብሩን መብዛት አቤቱታ ባቀረቡበት ወቅትም መጠኑ ብዙም ዝቅ ሳይል 81 ሺህ ብር እንዲከፍሉ የተደረገ መሆኑን ባለንብረቱ አመልክተዋል። ተወያዮቹ ከዚህም በተጨማሪ የሚመለከተው አካል ቀድሞውኑ ጠርቶ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት እንዲካሄድ አለማድረጉንም ጭምር በማንሳት ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል። የተሽከርካሪዎቹ ግብር አጣጣል በሚጭኑት አቅም መጠን ሲሆን በጭነት ልክ ግብራቸው የማይወሰን እንደዚሁም ለኪራይ አገልግሎት የሚውሉ ሞተር የሌላቸው ተሳቢዎች ጉዳይም ተነስቷል። በዚህ ዙሪያ የታየውን ችግር ለመፍታት በየቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ሰርኩላር የሚተላለፍ መሆኑን ከመድረኩ በኃላፊዎች በተሰጠው ገለፃ ተመልክቷል።

 

በሌላ በኩል ከመድረኩ በተሰጠው ምላሽ በተሽከርካሪዎቹም  አገልግሎት ላይ የተጣለው የግብር ማሻሻያ መነሻ በ1997 ዓ.ም የነበረውን የግሽበት መጠን ታሳቢ በማድረግ መሆኑ ተመልክቷል። በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች የታየው ወጥነት የሌለው የግብር አወሳሰን አሰራርም በስህተትነት ተወስዶ በቀጣይ ማስተካከያ የሚደረግበት መሆኑን ከመድረኩ በተሰጠው ማብራሪያ ተገልጿል። ግብሩን ለመወሰን ለጊዜው ስራ ላይ የዋለው የግሽበት ማስተካከያ (Inflation Adjustment) ለአጭር ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚሆን የተመለከተ ሲሆን በቀጣይ የሚለወጥበት አሰራርም ይኖራል ተብሏል። ተወያይ ነጋዴዎቹ በበኩላቸው ግሽበት ታሳቢ ተደርጎ ግብሩ ከተጣለ በዚሁ ግሽበት እንደ ነዳጅ፣ ጎማ፣ ቅባትና የመሳሰሉት የተሽከርካሪዎቻቸው ግብዓቶችም ዋጋ ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ እየናረ በመሄዱ ይህም ጉዳይ አብሮ ሊታይ ይገባው የነበረ መሆኑን አመልክተዋል።

 

በኢትዮጵያ ግዙፉ ጫማ አምራች ኩባንያ የሆነው ሁጁያን ኩባንያ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለአንድ መቶ ሺህ ኢትዮጵያዊያን የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን ኩባንያውን ጠቅሶ የቻይና የዜና ወኪል ዤንዋ ባሰራጨው ዘገባ አመልክቷል።

 

 በድርጅቱ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚሰተር ሻሪ ዛንግ ጋር ቆይታ ያደረገው ይሄው የዜና ወኪል፤ ኩባንያው በአሁኑ ሰዓት ለ 4 ሺህ 2 መቶ ኢትዮጵያዊያን ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን አመልክቷል።

 

 በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመትም ይህንን የሰራተኛ ቁጥር ወደ 6 ሺህ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው አመልክተዋል። በሂደት ግን የኩባንያውን የማምረት አቅም በከፍተኛ ደረጃ በማስፋት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለአንድ መቶ ሺህ ኢትዮጵያዊያን የስራ እድልን የሚፈጥርበትን ሁኔታ መኖሩን ኃላፊው ጨምረው አመልክተዋል። ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር ካለባቸው በርካታ ሀገራት መካከል  ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ያመለከቱት ኃላፊው፤ ሀገሪቱ  የስራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ በምታደርገው ጥረት ኩባንያው የራሱን ድርሻ የሚወጣ መሆኑን ጨምረው አመልክተዋል። ሁጁዋን ኩባንያ ሠራተኞችን ከመቅጠር ባለፈተቀጣሪዎች በስልጠና ክህሎትን እንዲያዳብሩ ብሎም ከአሰሪዎቻቸው ጋር መግባባት እንዲችሉ መሰረታዊ የቻይንኛ ቋንቋ እንዲማሩ የሚያደርግ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።

 

 ከዚህም በተጨማሪ ሠራተኞች የዘመኑን የጫማ አመራረት ቴክኖሎጂ ልምድን በመቅሰም በራሳቸው የስራ ፈጠራ በግላቸው እንዲሰሩ ጥረት እያደረገም ነው ተብሏል። በቻይና አፍሪካ ልማት ፈንድ ትብብር የፋይናስ እገዛ የሚደረግለት ይህ ግዙፍ ኩባንያ በቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም አማካኝነት እውን እንዲሆን የተደረገ ነው። የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም የቻይና ኩባንያዎች በአፍሪካ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ልዩ ልዩ ድጋፎችን የሚያደርግ ፎረም ነው።

በትራንስፖርት አገልግሎትና በእህል ወፍጮ ሥራ የተሰማሩ ባለንብረቶች በረቂቅ መመሪያ ግብር እንድንከፍል ተደርገናል በማለት ምሬታቸውን ገለፁ። ባለፈው ሰኞ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊዎች ጋር ባለንብረቶቹ ባደረጉት ውይይት የግብር አከፋፈሉን ሁኔታ የሚመለከተው መመሪያ ባልፀደቀበት ሁኔታ ግብር እንድንከፍል በመደረጉ ከመመሪያ መፅደቅ በኋላ በመመሪያው ከተቀመጠው ግብር መጠን በላይ እንድንከፍል ተደርገናል በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

 

በዚሁ ዙሪያ ያነጋገርናቸው በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዲስ አበባ ግብር አወሳሰንና አሰባሰብ ፕሮግራም ልማትና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ፈቃደ ችግሩ የተፈጠረ መሆኑን አምነው፤ የችግሩ መንስኤም ከጊዜ እጥረት ጋር የተያያዘ መሆኑን አመልክተዋል። የፌደራል የገቢ ግብር ደንብ የወጣው ሰኔ 27 ቀን 2009 ዓ.ም መሆኑን ያስታወሱት አቶ ያሬድ፤ ግብር ማስከፈል የተጀመረው ግን ከሀምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ስለነበር መመሪያውን ለማውጣት በቂ ጊዜ ሳይገኝ በመቅረቱ ነጋዴዎቹ በረቂቁ መመሪያ ግብራቸውን እንዲከፍሉ የተደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።

 

“የደረጃ ሐ ደንቡ ሲፀድቅ ከረቂቁ ጋር ልዩነት አልነበረውም። በዚህ በኩል ችግር አላጋጠመም፣ የደረጃ ሀ እና ለ ግን መመሪያው ከደንቡ በኋላ ስለሚዘጋጅ መመሪያው ተዘጋጅቶ ያለቀው ሀምሌ መጨረሻ በመሆኑ ነው ችግሩ ያጋጠመው ያሉት አቶ ያሬድ”፤ መመሪያው ከፀደቀ በኋላ ነጋዴዎቹ በረቂቅ መመሪያው ከከፈሉት ገንዘብ በላይ ከፍለው ከተገኙ በሁለት አማራጭ ሂሳባቸውን ማወራረድ የሚቻል መሆኑም አመልክተዋል። በዚህም በአንድ መልኩ ገንዘቡን ተመላሽ ማድረግ ሲሆን ያ ካልሆነ ደግሞ ትርፉን ገንዘብ ወደ። ሚቀጥለው የግብር ዓመት ማዘዋወር መሆኑ በአማራጭነት ተቀምጧል።¾

 

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር አማካኝነት በየዓመቱ የሚካሄደው ኤግዚብሽን በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል ተካሄደ። ኤግዚብሽኑ የኮንስትራክሽን ግብዓት አምራቾችን፣ አቅራቢዎችን፣ ዲይዛይንና ስፔስፍኬሽን አዘጋጆችን፣ ሥራ ተቋራጮችን፣ የሪል ስቴት አልሚዎችንና ሌሎች በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ባካተተ መልኩ የተካሄደ ነው።

 

 በዚሁ ካለፈው ረቡዕ መስከረም 10 ቀን ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በተካሄደው ዓለም አቀፍ ኤግዚብሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ26 ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች የታደሙ መሆኑን የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማህበር የቦርድ ሊቀመንበር ኢንጂነር አበራ በቀለ አስታውቀዋል። ተሳታፊ ኩባንያዎች ከመጡባቸው ሀገራት መካከልም ቻይና፣ ህንድ፣ ቱርክና ደቡብ ኮሪያ የሚገኙበት መሆኑ ታውቋል።

 

 የዚሁ ኤግዚብሽን አካል የሆነና በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ ወይይትም በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተካሂዷል። የቢዝነስ ለቢዝነስ ግንኙነትና ትስስር የመፍጠር ሥራም በዚሁ ኤግዚብሽን ላይ ተካሂዷል። የእለቱ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ባደረጉት ንግግር የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ  በ2003 ከነበረበት 19 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ የምርት ድርሻ በ2008 ዓ.ም ወደ 224 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ያደገ መሆኑን አመልክተዋል።

 

 እንደ ኃላፊው ገለፃ ከሆነ  ዘርፉ በእነዚህ ጊዜያት ብቻ ከ50 በመቶ በላይ አማካይ ዓመታዊ እድገትን ሲያስመዘግብ ቆይቷል። በዚህም በ2008 ዓ.ም ብቻ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለኢኮኖሚው 14 ነጥብ 71 በመቶ የምርት እድገት በማስመዝገብ ቀዳሚ መሆኑን ኢንጂነር ኃይለ መስቀል ጨምረው አመልክተዋል።

 

የኬኒያ መንግስት ሰሞኑን ቢኤንቲ ኮንስትራክሽን ኤንድ ኢንጂነሪግ ከተባለ ኩባንያ ጋር ባደረገው የግንባታ የውል ስምምነት መሰረት ናይሮቢን ከወደብ ከተማዋ ሞምባሳ ጋር የሚያገናኝ የፍጥነት መንገድ(Express Highway) ለመገንባት እንቅስቃሴ የጀመረ መሆኑን አስታውቋል። የመንገድ ግንባታው 3 ቢሊዮን የኬኒያ ሽልንግ ወጪን የሚጠይቅ ሲሆን ይህ ወጪም በአንዳንድ ኬኒያዊያን ትችት እየደረሰበት ይገኛል። የትችቱ መነሻ የሆነው ሀገሪቱ ናይሮቢን ከሞምባሳ የሚያገናኘው ቻይና ሰራሹ የባቡር መስመር በቅርቡ ከተመረቀ በኋላ በዚያው መስመር አዲስ የፍጥነት መንገድ መገንባቱ ለምን አስፈለገ በሚል ነው?

 

 እንደ ስታንዳርድ ዲጂታል ዘገባ ከሆነ የዚህ የፍጥነት መንገድ ግንባታ በታሰበው መሰረት ከተጠናቀቀ ናይሮቢን ከሞምባሳ ለማገናኘት አራት አማራጮች ይኖራሉ። የመጀመሪያው በቅኝ ገዢዎች የተሰራው መንገድ፣ ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ በነፃነት ማግስት የተገነባው መንገድ ነው። ይህ መንገድ በአሁኑ ሰዓት በጥገና ተደግፎ አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆን በቅርቡ የተመረቀው ቻይና ሰራሹ ባቡር ደግሞ ሶስተኛው የትራንስፖርት አማራጭ ተደርጎ ተወስዷል። አራተኛው ገና ወደ ግንባታ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የፍጥነት መንገዱ ነው።

 

 የበርካታ ኬኒያዊያን ተቃውሞም እዚህ ጋር ነው። በበርካታ የኬኒያ አካባቢዎች ደካማ የመንገድ ኔትወርክ ባለበት ሁኔታ ከናይሮቢ ሞምባሳ አራተኛ አማራጭ የትራንስፖርት መንገድ፤ ያውም የፍጥነት መንገድ መገንባቱ ለምን አስፈለገ በማለት የሚጠይቁ በርካታ ኬኒያዊያን ቢኖሩም ለጥያቄያቸው በቂ ምላሽ ሳያገኙ ግንባታውን ወደ መሬት ለማውረድ የፊርማ ስነስርዓቱ ተከናውኗል።  

 

ሌላው ከዚሁ ግንባታ ጋር በተያያዘ የሀገሪቱን መንግስት እያስተቸው ያለው ጉዳይ የግንባታው መስመር በርካታ የዱር እንስሳት የሚገኙበት በመሆኑ በግንባታ ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ የእንስሳቱን ህልውና አደጋ ላያ ይጥላል በሚል ነው። ከናይሮቢ ሞምባሳ ያለው መስመርና አቅጣጫ ከፍተኛ የሆነ የዱር እንስሳት ክምችት ያለበትና ሰፋፊ ጥብቅ ፓርኮችንም የያዘ አካባቢ ሲሆን ያለፈው ቻይና ሰራሹ የባቡር ፕሮጀክት ሲደርስበት ከነበሩበት ትችቶች መካከል አንዱ የዱር እንስሳቱን ቀጣይ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነው በሚል ነው።

 

 ይህ አሁን የሚገነባው የፍጥነት መንገድም ሰፊ የዱር እንስሳት መኖሪያ አካባቢያዎችን በግንባታው አጠቃሎ የሚይዝ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የዱር እንስሳቱን ለተሽከርካሪ አደጋ የሚያጋልጥ መሆኑም ብቻ ሳይሆን በተሽከርካሪ ድምፅ ረብሻም ጭምር አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ የሚያደርግ መሆኑም እየተነገረለት ነው። ይህም የኬኒያን የቱሪዝም ዘርፍ ጉዳት ሊያደርስበት ይችላል የሚል አስተያየት እየተሰጠበት ቢሆንም በመንግስት በኩል ግን ተቀባይነትን ሊያገኝ አልቻለም። እንደ ስታንዳርድ ዲጂታል ዘገባ ከሆነ የግንባታውን ሥራ ለማከናወን የአሜሪካው ቢኤንቲ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የስምምነት ፊርማውን አኑሯል።

 

Economyየኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት የኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ በተለያዩ ጊዜያት በሀገሪቱ ለተነሱ ችግሮች የራሱን ድጋፎች ሲያደርግ ቆይቷል። ሆኖም ይህ ድጋፍ ወጥነት በሌለው መልኩና ለጊዜያዊ ችግሮች መፍትሄ ከመስጠት ባለፈ በዘለቄታዊነትና ቀጣይነት ባለው አሰራር የተደገፈ አልነበረም። የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ባለፉት ጊዚያት የንግዱን ማህበረሰብ በማስተባበር ለድርቅ ተጎጂዎች እንደዚሁም ከሳዑዲ ተመላሽ ለሆኑ ዜጎች ድጋፍ እንዲደረግ የራሱን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

 

 ይሁንና ለመሰል ችግሮች ቋሚ የሆነ ድጋፍ ለማድረግና ዘለቄታዊነት እንዲኖረው በማሰብ “የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድን” ለማቋቋም ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው።  ከዚሁ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ተወካዮችና ኃለፊዎች  በያዝነው ሳምንት አንድ ስብሰባ በማካሄድ በማህበራዊ ኃላፊነት ፈንዱ ማቋቋማያ ቻርተር ላይ ገለፃና አጠር ያለ ውይይት ተካሂዷል። በዚሁ ረቂቅ ቻርተር መሰረት የግሉ ዘርፍ ማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት የሚኖራቸው ሙሉ በሙሉ ፈቃደኝነቱ ባላቸው  የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ወይንም ተቋማት መሆኑን ተመልክቷል።

 

ማህበራዊ ኃላፊነት ፈንዱ የሚኖሩት ተግባራትም በዚሁ ረቂቅ ቻርተር ላይ በዝርዝር ተቀምጧል። በዚህም ቻርተር መሰረት የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንዱ፤ በተፈጥሮ ችግሮች ምክንያት ከሥራና ከመኖሪያ ቀያቸው የሚፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እገዛ ያደርጋል ተብሏል። ለሀገሪቱና ለህዝቡ የሚጠቅሙ የሚችሉ የምርምር ሥራዎችን መደገፍም አንዱ የዚሁ ፈንድ እገዛ አካል ተደርጎ ተወስዷል። አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች እንደዚሁም ዘመናዊ የግብርና ሥራዎች በሀገሪቱ እንዲስፋፉም በማህበራዊ ኃላፊነት ልማት ፈንዱ ድጋፍ ከሚሰጣቸው ዘርፎች ተደርጎ ተወስዷል። ይህ በቀጣይ የሚቋቋመው የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ የሆነ የራሱ ቢሮ የሚኖረው መሆኑ የተመለከተ ሲሆን ተቋሙን የሚመራና የሚያስተዳደር ቦርድ የሚኖረው መሆኑም ተመልክቷል። የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንዱ የበላይ አካል ጠቅላላ ጉባኤው እንደሚሆን በዚሁ ገለፃ የተመለከተ ሲሆን ጉባኤውም ከተሰጡት ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንዱን ዓመታዊ በጀትና የሥራ መርሃ ግብር ማፅደቅ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የሂሳብ መዛግብትንና ገንዘብ ነክ ጉዳዮችንም የሚመረምር የውጭ ኦዲተርን የመሾም ስልጣንም የተሰጠው ለጠቅላላ ጉባኤው ነው። ጉባኤው እንደ ሁኔታውና አግባቡም ሥልጣኑን በውክልና ለቦርዱ ሊሰጥ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩም በዚሁ ረቂቅ ቻርተር ላይ ተመልክቷል። የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ በዚሁ ዙሪያ በሰጡን ማብራሪያ የግሉ የንግድ ማህበረሰብ ይህንን ፈንድ በማገዙ ረገድ በቀጣይ ከሚኖረው ድርሻና ኃላፊነት ባሻገር የመንግስት የልማት ድርጅቶችም ተሳታፊ የሚሆንበት አሰራርም ይኖራል። እንደሳቸው ገለፃ በቀጣይም ከ2 መቶ ያላነሱ የመስራች ጉባኤ አባል ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

 በእርግጥ በኢትዮጵያ በቁጥር በርካታ የንግድ ማህበረሰብ ክፍሎች ቢኖሩም የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላት የሆኑት ግን ውስን ናቸው። ከዚህ አንፃር ምክር ቤቱ ምን ያህል ሰፊውን የንግድ ማህበረሰብ ሊያንቀሳቅስ ይችላል የሚል ጥያቄም ተነሰቶ ነበር።

 

አቶ ሰለሞን በዚህ በኩል አንድ ዜጋ ወገኑን ለማገዝ ሰብአዊነትንና ቁርጠኝነትን ብቻ የሚጠይቅ በመሆኑ ምክርቤቱ ከአባላቱ ውጪ የሆኑትን የንግድ ማህበረሰብ አካላት የማንቀሳቀስ ብሎም የማስተባበር አቅሙ ያለው መሆኑን አመልክተዋል። እያንዳንዱ ነጋዴ ለዚህ ማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ለሚያደርገው አስተዋፅኦ የሚሰጠው የገንዘብ መጠን ብዙም በወጪ ደረጃ ሊታይ የማይችል መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሰለሞን፤ሆኖም ብዙዎች ከተሳተፉበት የሚኖረው ድጋፍ በቀላሉ የማይታይ መሆኑን አመልክተዋል። “አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች ቀድሞውኑ የራሳቸው የማህበራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት አሰራር የዘረጉ በመሆኑ፤አሁን በምክር ቤቱ ሊቋቋም የታሰበው የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ከሌሎች ጋር የስራ መደራረብን የሚፈጥርበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም ወይ?”  የሚል ጥያቄም ለአቶ ሰለሞን ተነስቶላቸው ነበር።

 

 እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ፤ ሌሎች ቀደም ሲል በተናጠል የሚሰሯቸውን የማህበራዊ ኃላፊነቶች እንደተጠበቁ ባለበት ሁኔታ በዚህኛው አዲሱ የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ላይ መሳተፍ የሚችሉበት እድሉም ክፍት ነው። አዲሱ የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ የንግዱን ማህበረሰብ ኪስ በማይጎዳና ሀብትን በማቀናጀት የሚሰራ በመሆኑ ከሌሎቹ የቀደሙ አሰራሮች የተለየ ነው። ሌላው ለአቶ ሰለሞን የተነሳላቸው ጥያቄ “የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክርቤት የግሉን ዘርፍ ማህበራዊ ኃላፊነት ፈንድ ለማቋቋም አልዘገየም ወይ?” የሚል ነው። እንደሳቸው ገለፃ የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ የእድሜ ቆይታ ከደርግ መንግስት ለውጥ ጋር ተያይዞ አጭር በመሆኑና የግሉም ዘርፍ የራሱን አቅም ለመገንባት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሲሰራቸው ከነበሩት ሥራዎች አንፃር የማህበራዊ ኃላፊነት ፈንዱን የማቋቋሙ ሥራ ዘገየ ሊባል የሚችል አይደለም።

 

 

 

Economy3በጤና እና በቢዝነስ ዘርፎች በስፋት በመስራት ላይ የሚገኘው አዲስ አበባ ሜዲካል እና ቢዝነስ ኮሌጅ ባሳለፍነው ቅዳሜ መስከረም 6 ቀን 2010 ዓ.ም በብሄራዊ ቴአትር አዳራሽ በደረጃ አራት ነርስ፣ በአዋላጅ  ነርስ፣ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በዲግሪ ፕሮግራም በነርሲንግና በጤና መኮንንነት ዘርፍ በአጠቃላይ 504 ተማሪዎችን አስመረቀ። የኮሌጁ ባቤትና ፕሬዝዳንት አቶ አንተነህ ገቢሳ በምረቃ ፕሮራሙ ላይ እንደተናገሩት፤ አዲስ አበባ ሜዲካልና ቢዝነስ ኮሌጅ የተመሰረተው በ1997 ዓ.ም መሆኑን አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት በተለይም ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በዲግሪ ፕሮግራም ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እውቅና አግኝቶ በነርሲንግና በጤና መኮንን ዘርፎች ለሶስተኛ ዙር ያስመረቃቸው ተማሪዎች እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

 

ኮሌጁ በደረጃ አራት የቢዝነስ መስኮች በአካውንቲንግ በሴክሬተሪያል ሳይንስ፣ በሰው ኃይል አስተዳደር፣ በማርኬቲንግ፣ በፐርቼዚንግና በሌጋል ሰርቪስ መስኮች ትምህርት መስጠት የጀመረበት ወቅት መሆኑም ተነግሯል። በዕለቱ በነርሲንግ ደረጃ አራት 143 ተማሪዎች፣ በአዋላጅ ነርስነት 18 ተማሪዎችን እንዲሁም በዝዋይ ካምፓስ በቴክኒክና ሙያ ደረጃ አራት በአካውንቲንግ ዘርፍ 61 ተማሪዎችን እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ 47 ተማሪዎችን አስመርቋል። ከእነዚህም ውስጥ 50 ለሚደርሱና ትምህርታቸውን ከፍለው መማር ለማይችሉ ዜጎች፤ ኮሌጅ የነፃ ትምህርት ዕድልን በመፍጠር እንዲመረቁ በማስቻል የማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ሲሉም አቶ አንተነህ ተናግረዋል።

 

ከኮሌጁ ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች በተሰማሩበት መስክ ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንደሚወጡ ተስፋ አለኝ ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ልዩ አማካሪ የሆኑት አቶ አንተነህ ምትኩ ናቸው። በተለይም በጤናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ምሩቃን የእናቶችና ህጻናትን ጤና ከማሻሻል አንፃር ብዙ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል። አያይዘውም የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና የቲቪ ህመምን ስርጭትን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡን በማስተማር ጭምር የተሻለና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል ይኖርባችኋል ብለዋል።

 

ኮሌጁ ባለፉት ተከታታይ አስራ አንድ ዓመታት በአጠቃላይ ከ50ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስተምሮ ያስመረቀ ሲሆን፤ እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ በኮሌጁ ተምረው የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል 85 በመቶ የሚሆኑት ብቁ ሆነው በመገኘታቸው፤ በተለያዩ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተቀጥረው በማገልገል ላይ እንደሚገኙም ሰምተናል። አዲስ አበባ ሜዲካልና ቢዝነስ ኮሌጅ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ በዝዋይ፣ በድሬዳዋ፣ በመተሃራ እንዲሁም ወደጎረቤት ሀገር በመዝለቅ በሀርጌሳ ሶማሌ ላንድ በደረጃና በዲግሪ ፕሮራሞች በማሰልጠንና በማስመረቅ ላይም ይገኛል ተብሏል።

 

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት ከተገኙት መካከል የመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን ማዕከል መስራች አቶ ቢኒያም በለጠ እና የኩላሊት ህሙማን እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ፤ ለተመራቂዎቹ አበረታችና አነቃቂ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ ምሩቃን በሰብዓዊ እንቅስቃሴም ላይ ተሳትፏቸው እንዳይጓደል ጠይቀዋል።  

 

Economy2ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛውን ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንባት የቻለችው ቻይና በአውሮፓ ህብረትና በሌሎች ንግድ አጋሮቿ ኢኮኖሚዋን ክፍት እንድታደርግ ጫና እየተደረገባት ነው። ቻይና በዋነኝነት በመንግስት የበላይነትና ቁጥጥር የሚመራን የኢኮኖሚ ስርዓትን መገንባት የቻለች ሲሆን፤በአንፃሩ ግዙፍ የንግድ አጋሮቿ የሆኑት አውስትራሊያ፣የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካና እንግሊዝ ግን ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነፃ ኢኮኖሚ ስርዓት እንዲገነባ ፅኑ አቋም ያላቸው መንግስታት ናቸው።

 

ቻይና ከዚህም በተጨማሪ ያልተገባና ፍትሃዊነት የጎደለው የንግድ ውድድር እንዲኖር ኩባንያዎቿን በሰፊው ትደጉማለች፣ የንግድ አሰራር ግልፅነት አይታይባትም፣ አዕምሯዊ የፈጠራ ውጤቶች ያለአግባብ ታባዛለች በሚል በተደጋሚ ክስ ሲቀርብባት የቆየች ሀገር ናት። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቻይና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት እያሽቆለቆለ መሄዱን ዘ አይሪሽ ታይምስ ከሰሞኑ ያሰራጨው ዘገባ ያመለክታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ጠንከር ያለ አቋሙን የገለፀው የአውሮፓ ህብረት የንግድ ማህበራት ምክር ቤት ይሄንኑ ጉዳይ በዋና አጀንዳነት ይዞ የቻይና ከፍተኛ ባለስልጣናትን የሚያግባባ አንድ ቡድን አቋቁሟል።

 

 ይሄው ቡድን በቀጣይ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በሚኖረው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ይሄው የንግድ ጉዳይ በዋና አጀንዳነት ተነስቶ አቋም እንዲያዝበት ፍላጎት ያለው መሆኑን አመልክቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዢ ቺፒግ ብዙ ይጠበቃል ተብሏል። ቻይና ኢኮኖሚዋ ግልፅነት የማይታይበትና በነፃ ገበያ ስርዓት ለሚመሩ ሀገራት የማይመች ነው የሚለውን ወቀሳ የሚያጠናክርም ሪፖርት ከሰሞኑ ወጥቶባታል።

 

 ዘ ኦርጋናይዜሽን ፎር ኢኮኖሚክ ኮኦፖሬሽን ኤንድ ዲቨሎፕመንት በሚል ስያሜ የሚታወቀውና በተለያዩ አለም ዓቀፍ ኢኮኖሚያዊ ጥናቶች ላይ ከመሳተፍ ባሻገር የራሱን ሪፖርት ጭምር የሚለቀው ድርጅት፤ለውጭ ቀጥተኛ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ክፍት የሆኑ ሀገራትን ደረጃ ሲያወጣ ከዘረዘራቸው 62 ሀገራት መካከል ቻይና የ59ኛ ደረጃ በመያዝ እጅግ ዝቅተኛ የሚባልን ውጤት አስመዝግባለች። 

 

ሰሞኑን  ራንድ ሜርቻንት ባንክስ ለውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ተመራጭ ያላቸውን ሀገራት በዝርዝር ያሰቀመጠ ሲሆን ኢትዮጵያም ከአፍሪካ ሀገራት የ4ኛ ደረጃን ይዛለች። የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘችው ግብፅ ናት። ከዚህ ቀደም በነበረው የድርጅቱ ሪፖርት በአፍሪካ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ቁንጮ አድርጎ ያስቀመጣት ደቡብ አፍሪካን ነበር። Where to Invest in Africa 2018 በሚለው በዚሁ ጥናቱ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ሰፊ ሚና ያላትን ናይጄሪያን ከምርጥ ተመራጭ አስሩ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገራት ውጪ አድርጓታል። ግብፅ የመጀመሪያውን ደረጃ ለመያዝ የበቃቸው የአልሲሲ መንግሰት ባደረገው ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ነው ተብሏል። ሞሮኮ የሶስተኝነትን ደረጃ ያገኘች ሲሆን በህዝባዊ አመፅ በተደጋጋሚ ስላሟን እንዳጣች የሚገልፀው ይሄው ሪፖርት ቀደም ብሎ አራተኛ የነበረችውን ጋናን በልጣ የአራተኝነት ደረጃን እንድትቆናጠጥ አድርጓታል።

 

 ኢትዮጵያ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የሚታይባት አለመረጋጋት የኢንቨስትመንት ፍሰቱንና የሀገሪቱን አመቺነት ይጎዳዋል ቢባልም፤ በሌላ መልኩ መንግስት ለኢንዱስትሪ ዞኖች የሰጠው ልዩ ትኩረት፣ የኤሌክትሪክ ሀይል ርካሽነትና፣ ለባቡር መሰረተ ልማት ግንባታው ላይ የተካሄደው ኢንቨስትመንት ሀገሪቱ የተሻለ ተወዳዳሪ እያደረጋት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

በ2009 ዓ.ም ተጀምሮ ተስፋፍቶ የቀጠለውን ግጭት ተከትሎ በመንግስት በኩል ተደርሶባቸዋል ከተባሉት የችግሩ ምንጮች መካከል አንደኛው በሀገሪቱ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች መኖራቸው ነው። ይህንንም ድምዳሜ ተከትሎ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት በ2009 የሁለቱ ምክርቤቶች መክፋቻ ስበሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር መንግስት ወጣቶችን ወደ ሥራ ሊያስገባ የሚያስችል የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ዝግጁ ያደረገ መሆኑን በመግለፅ ይህም የገንዘብ በየክልሉ በድርሻ የሚከፋፈል መሆኑን አመለከቱ። የፕሬዝዳንቱ የመስከረም ወር መጨረሻ 2009 ንግግርን ተከትሎ ይህንን የወጣቶች የስራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድን የሚመለከተው አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ  በዚያው ዓመት አጋማሽ ላይ ነበር። በዚህ አዋጅ መሰረትም በሀገሪቱ የሚገኙና እድሚያቸው ከ18 እስከ 34 ያሉ ወጣቶች የፈንዱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተደንግጓል።

 

ይህንንም የፈንድ አዋጅ መፅደቁን ተከትሎ በየክልሉ የሚገኙ በአዋጁ የተመለከቱትን መስፈርቶች የሚያሟሉ ወጣቶች እንዲመዘገቡ ተደርጓል። በዚህም ከሶስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የተዘዋዋሪ ፈንዱ ተጠቃሚ ለመሆን በየክልሉ በገጠርና በከተሞች የተመዘገቡ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በወቅቱ ይህ ገንዘብ ከፌደራሉ መንግስት የሚለቀቅ መሆኑ ሲገለፅ ከወራት በፊት ለፓርላማው በቀረበቀው በጀት ውስጥ ተካቶ የፀደቀ ግን አልነበረም።

 

 ይህም በመሆኑ በመጨረሻ ወደ አፈፃፀም ሲገባ ለክልሎች የሚለቀቀው የገንዘብ መጠን በተመደበላቸው የክፍፍል መጠን ሆኖ አልተገኘም። ለምሳሌ የቤኒሻንጉል ክልል የተመደበለትና የተለቀቀለት የገንዘብ መጠን ሊመጣጠን ባለመቻሉ ለስራ ፈጠራ የመዘገባቸውን ወጣቶች ለማስተናገድ የተገደደው  ከመደበኛ በጀቱ በመቀነስ ነበር። ለአዲስ አበባ ከተማ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የተመደበው የገንዘብ መጠን ወደ 419 ሚሊዮን ብር ሲሆን በዚህም ወጣቶች እንዲጠቀሙ የተደረገው 17 ሚሊዮን ብሩን ብቻ ነበር። በአጠቃላይ ሲታይ በመንግስት የተገባው ቃልና በመጨረሻ ወደ አፈፃፀም ሲወረድ የታየው እወነታ ፈፅሞ የሚገናኝ ሆኖ አልታየም።

 

የመንግስት የፋይናስ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ከማደጉ ባሻገር የገቢው መጠን ደግሞ በዚያው መጠን አሽቆልቁሏል። በዚህ በኩል በተለይ በውጭ ምንዛሪ የታየው ማሽቆልቆል ከዓመት ዓመት እየከፋ ሄዷል። ከዚህም በተጨማሪ ሀገሪቱ በተደጋጋሚ ያለፈችብት ህዝባዊ ዓመፅም ኢኮኖሚውን ክፉኛ ጎድቶታል። ይህ ብቻ ሳይሆን የደመወዝተኛው የደመወዝ ግብር ዝቅ እንዲል መደረጉ ለመንግስት ገቢ መውረድ አንዱ ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀስ ነው። መንግስት የደመወዝ ግብርን ሲቀንስ ይሄንኑ ያጣውን ገቢ የሚያተካኩ የተለያዩ የገቢ ምንጮችን ታሳቢ በማድረግ ነበር። ከእነዚህም ታሳቢ የገቢ ምንጮች መካከል አንዱ ተደርጎ የተወሰደው በአዲስ መልኩ የተሻሻለውን የገቢ ግብር አዋጅ ተከትሎ በንግዱ ማህበረሰብ ላይ የታክስ ጭማሪ ማድረግን ነበር።

 

 መንግስት የቀን ገቢ ግምቶችን ማሻሻያ የሚያደርገው በየስድስት ዓመቱ ሲሆን በተሻሻለው አዋጅ መሰረት የቀን ገቢ ግምት በየሶስት ዓመቱ እንዲሆን ተደንግጓል።  በሳላፍነው ዓመት የመንግስት የቀን ገቢ ግምት ማሻሻያ ወቅት ስለነበር የተደረገውን ማሻሻያ ተከትሎ የተካሄደው ግምት የማወጣት ስራ በርካታ የንግዱን ማህበረሰብ አስቆጥቷል። ይህም ጉዳይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲያወዛግብ ከመቆየቱም ባሻገር በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልል የንግድ ስራን እስከማቆም የዘለቀ አድማ እንዲካሄድ አድርጓል። የመንግስት የገቢ ፍላጎት ንረት ገቢውን ለመሻሻል ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር የወጪ መጠኑንም ለመቀነስ ጥረት በማድረግ ላይ ነው።

 

 በዚህም አላስፈላጊ ወጪዎችን ለመቀነስ የሚያስችል መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን ይህም መመሪያ ተግባራዊ የሚሆን ከሆን የመንግስትን ወጪ በመቀነስ በገቢውና በወጪው መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ አይነቱ አካሄድ ከኢህአዴግ መንግስት ቀደም ካለ ታሪክ አንፃር ሲታይ ከወጪ አኳያ የመጀመሪያው እርምጃ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው። መንግስት ገቢውን ከፍ እንዲያደርግ የሚያስገድዱ በርካታ ነባራዊ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።

 

የኢትዮጵያ መንግስት ወጪው በከፍተኛ ደረጃ እየናረ መሄዱን ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት ገቢውን ለማሳደግና ወጪውን ለመቀነስ ጥረት እያደረገ ነው። ከውጪ አንፃር ባለፉት ጊዜያት ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቀላል የማይባል ጉዳት የደረሰበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን የድርቁ ሁኔታ ቀላል የማይባል ገንዘብን መጠየቁም አንዱ ፈተና ነበር። እነዚህና ሌሎች የኢኮኖሚው ተግዳሮቶች መንግስት ለወጣቶች የስራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድ ያፀደቀውን የ10 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንኳን በተፈለገው መጠን እንዳይለቅ አድርጎታል።

Page 10 of 67

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us