አፈርሳታ

Wednesday, 09 July 2014 13:37

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

- ህብረተሰብን መሰረት ያደረገው የአፈርሳታ የወንጀል ምርመራ

- የአፈርሳታ ስርዓትና ሂደት ምን ይመስላል

- ከ200 ዓመታት በላይ ሲሰራበት የቆየው አፈርሳታ ያጋጠሙት ችግሮች ምን ነበሩ?

- አፄ ኃይለስላሴ አፈርሳታን ለማዘመን ያወጡት አዋጅ ምን ነበር?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? ለዛሬ ወደኋላ መለስ ብለን ለረጅም ዘመናት በሀገራችን ሲሰራበት የነበረን የወንጀል ምርመራ ዘዴን እናስታውሳለን። ይህ የምርመራ ዘዴ ወንጀል የፈፀመው ሰው በማይታወቅበት ጊዜ የመረጃ ምንጩን በዋነኝነት ወንጀሉ የተፈፀመበትን አካባቢ ሕብረተሰብ የሚያደርግ ነበር። ሕብረተሰቡን ያላሳተፈን የወንጀል መከላከልም ሆነ ምርመራ ውጤታማ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ቀደምት አባቶቻችንም ይህ የገባቸው ይመስላል። በዘመናዊው አሰራር ሕብረተሰብ አቀፍ የወንጀል ምርመራና መከላከል (Community policing) በሀገራችን ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። ቀድሞስ የተሞከረው ምን ነበር የሚለውን ለማወቅ እንዲረዳን ወደኋላ መለስ እንበል።

1 አፈርሳታ ምንድን ነው?

አፈርሳታ ማለት ባህላዊ የሆነ በመንግሥት ድጋፍ የሚካሄድ ሕብረተሰቡ የሚያካሂደው የወንጀል ምርመራ ዘዴ ነው። አፈርሳታ የሚለው ቃል “አፈርሳ” ከሚለው የኦሮምኛ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙ እህሉን ከገለባው በማነፈስ መለየት ማለት ነው። በአማርኛ ደግሞ “አውጫጭኝ” ተብሎ ይጣራል። ዓላማው በንፁሃን መሀል የተደበቀውን አጥፊ ራሱን ሕብረተሰቡን በመረጃ ምንጭነት በመጠቀም እንዲቀጣ መለየት ወይም ማውጣት ነው።

ያልታወቀውን ወንጀለኛ ማንነት ለመለየት አፈርሳታ በአካባቢው የመንግሥት ኃላፊ ወይም በተበዳይ አመልካችነት ወይም ከባድ ወንጀል በተፈፀመ ጊዜ በመንግሥት አነሳሽነት ሊጠራ ይችላል። የአፈርሳታ ሂደት የሚጀምረው ወንጀሉ የተፈፀመበትን ቦታ ነዋሪዎችና አጎራባቾቻቸውን በመጥራት ነው። ከዚያም የወንጀለኛውን ማንነት ለይተው እስኪያወጡ ድረስ በአንድ አካባቢ አግልሎ በማስቀመጥ እርስ በእርስ እየተጠያየቁ የወንጀለኛውን ማንነት እንዲለዩ የማድረግ ሂደቱ ይቀጥላል። አፈርሳታ ተጠርቶ መቅረት የሚያስቀጣ ሲሆን የስበሰበው ሰውም በአፈርሳታው አጥፊውን ለይቶ ለመጠቆም ካልቻለ ኃላፊነቱን ወስዶ እያንዳንዱ አዋጥቶ በወንጀሉ ጉዳት ለደረሰበት ሰው ካሳ ይከፍላል። አፈርሳታን ውጤታማ ሚያደርገው አጥፊው ተለይቶ ካወጣ በወንጀሉ የደረሰውን ጉዳት የመካስ ኃላፊነቱ የሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል መሆኑ እና አጥፊው ካልተለየ በስተቀር ህብረተሰቡ የመንቀሳቀስ የመስራት ሌላ ጉዳዩን የመፈፀም ነፃነቱ ተገድቦ የሚያሳልፈው ጊዜ ከባድ መሆኑ ተደማምሮ ህብረተሰቡ የሚቻል ከሆነ አጥፊውን ለይቶ እንዲጠቁም ይገፋፋዋል። እንዲያውም አፈርሳታ የተጠራበት ምርመራ እስኪጠናቀቅ “ላሟም አትታለብ ሕፃንም አይጥባ” ተብሎ ነበር የሚታወጀው።

2. አፈርሳታ ከመቼ እስከ መቼ?

አፈርሳታን ያጠኑ አእምሮ ንጉሴ የተባሉት ምሁር አፈርሳታ የተጀመረው በአፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት በ1773 እንደነበርና ንጉሱ “ሌባ አደን” ይባል የነበረውን የፖሊስ ሰራዊታቸውን ለማገዝ ይህን ሕብረተሰቡንም የሚያሳትፍ የምርመራ ዘዴ ጀምረዋል ይላሉ። በተጨማሪም ይህ የአፈርሳታ ስርዓት በአፄ ዘርአያቆብ ዘመነ መንግሥት በ16ኛው ክ/ዘመን ከአረብኛ ወደ ግዕዝ እንደተረጎሙት የሚነገርለት ፍትሃነገስት የተባለው የክርስትና ኃይማኖትና የዓለማዊ ህግጋትን የያዘው መፅሐፍ ውስጥም መሰረት እንዳለው ይህን አንቀፅ በመጥቀስ ፀሐፊው አመሳክረዋል።

“በምድረ በዳ ላይ ተገሎ የተጣለ ሰው አግኝታችሁ ማን እንደገደለው ካልታወቀ፣ ዳኞቻችሁና ሽማግሌዎቻችሁ ይውጡና በሟችና በከተማይቱ መካከል ያለውን እርቀት ይለኩ፡፤ ሟች በተገኘበት ሥፍራ ቅርብ የሆነችውን ከተማ ይመልከቱ የዚያች ከተማ ሽማግሌዎችም “የኛ እጅ በዚህ ደም ውስጥ የለችም አይናችንም ገዳዩን አላየችም” ብለው ይማሉላችሁ። ዳኞች ሆይ የዚህን ሰው ደም አፍሳሽ አጠያይቃችሁ መርምሩና በሀቅ ፍረዱ።

ይሄ የፍትሐ ነገስት አንቀፅ ከአፈርሳታ ጋር የሚቀራረብ የምርመራ ስነስርዓትን ስለሚያስቀምጥ ለአፈርሳታ የመነሻ ምንጭ ሳይሆን እንደማይቀር መገመት ይቻላል።

ዘመናዊው የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት እስከታወጀበት እና የወንጀል ምርመራዎችን የማድረግ ስልጣን የፖሊስ ብቻ እስከሆነበት እስከ 1953 ዓ.ም እንኳን ብንቆጥረው አፈርሳታ በሀገራችን ለ180 ዓመታት እና ከዚያ በላይ ሲሰራበት የነበረ የወንጀል ምርመራ ስርዓት ነው ማለት ይቻላል።

3. የአፈርሳታ ስነስርዓት

የአፈርሳታ ስርዓት የተወሰኑ ምርመራውን የሚያካሂዱ ሽማግሌዎችን በመጠቀም እያንዳንዱን በአፈርሳታ የተጠራውን ሰው ይመረምራል። ጠቋሚው እንዳይታወቅ ለማድረግም መረጃ የሚሰጠው ሰው “ወፍ” ተብሎ ነው የሚጠራው። ነቢዩ ክፍሌ በፃፉት ያልታተመ የሕግ መመረቂያ ፅሁፍ “ወፍ” የሚለው አገላለፅ እንደ በቀል ከሆነው አባባል ጭር ባለ ጫካ ውስጥ እንኳን ብትሆን ወይ ሰይጣን ወይም ወፍ ታይሀለች” እንዳመነጨ ጠቁመዋል። ሶክር የተባሉ ፀሐፊ አፈርሳታ የሚከተለውን ስነስርዓት እንዲህ አስቀምጠውታል።

ተሰብስቦ በአንድ ቦታ ለአፈርሳታ የተዘጋበት ህዝብ ከ7እስከ9 የሚደርሱ ምርጦችን ይመርጡና ምርጦቹ ተነጥለው ከፀሀፊው ጋር ይቀመጣሉ። ትንሽዬ ጉድጓድ ይቆፈርና ውስጡ እሳት ይለኮሳል። እያንዳንዱ ተመራጭ ውሃ ይዘጋጅለትና “ያየሁ የሰማሁትን ሳልደብቅ፣ ወንጀለኛው ወንድሜ አባቴም ቢሆን እናገራለሁ” ብሎ ይምላል። ከዚያም በውሃው እሳቱን እያጠፋ “ሀሰት ብናገር እግዚአብሔር እንደዚህ እሳት ያጥፋኝ ብሎ ይምላል። መሬቱን በአገዳ መጥረጊያ እየጠረጉ “ውሸት ብናገር እግዚአብሔር እንዲህ ዘራችንን ይጥረገው” ብለው ይምላሉ። በተጨማሪ ድፍን እንቁላልና ድፍን ቅል ማጭድ ይቀርብና እያንዳንዳቸው “ያየሁትን እና የሰማሁትን ብደብቅ እንደዚህ ቅል ድፍን ያድርገኝ እንደዚህ በማጭድ ሆዴ ይዘርግፈው” ብለው ሁሉም ይምላሉ።ሁለት ወይም ሶስት የሚሆኑ “ወፎችም” ያዩትን ነገር ለፀሀፊው ብቻ እንጂ ለማንም እንደማይናገሩ ይምላሉ። ምርጦቹም ከአንዱ ቡድን ወደ ሌላው እየተዘዋወሩ እያንዳንዱን ሰው ያየው ወይም የሰማው ነገር እንዳለ ይጠይቃሉ። ከዚያም ወደ ፀሐፊው ተመልሰው “ወፎች ሲናገሩ እንደሰማነው ስርቆቱን የፈፀመው እገሌ ነው” ብለው ይነግሩታል።

ሌባው ሳይገኝ አስራ አምስት ቀናት አፈርሳታው ሊቀጥል ይችላል። ወፍ ስትናገር ወይም አጥፊውን የሚጠቁም ሰው ሲገኝ ካህኑ መስቀልና የቅድስት ማርያምን ምስል ተሸክመው በመምጣት ከምርጦቹ አጠገብ ይቀመጣሉ። ከዚያም ሁሉም የአፈርሳታቸው ተሰብሳቢዎች እየመጡ መስቀሉን እና የድንግል ማርያምን ምስል በመካከል በመምታት “እንደዚህ በመስቀል ላይ ልሰቀል እንደወንጌል አካሌን በመላው አለም ተገነጣጥሎ ይበታተን አላሑም!” እያሉ እየማሉ ይወጣሉ። ሆኖም ግን “ወፍ” የሚለውን አይቼ በሀሰት አልተናገርኩም ብሎ በሚስጥር ለምርጦቹ ነው።

ሁሉም የአፈርሳታው ተሰብሳቢዎች ምለውና ተገዝተው ማንነታቸውን ለማንም ላለመግፅ ለማሉት ለሽማግሌዎቹ የምስክርነት ቃላቸውን ስለወንጀሉ ፈፃሚ ያዩትን የሰሙትን ይናገራሉ። ሁሉም ማስረጃ ተሰብስቦ ከተጠናቀቀ በኋላ ፓሌላ የተባው ፀሐፊ እንደፃፈው ሽማግሌዎቹ በፀሐፊው እየተረዱ የተሰበሰቡትን ማስረጃ በሶስት ዓይነት ማስረጃዎች ከፋፍለው ይጨምቁታል።

 1. መርፌ፡- ወንጀሉ ሲፈፀም የተመለከቱ የአይን እማኞች
 2. ድንጋይ፡- አስፈላጊ የአካባቢ ማስረጃዎችን እና እውነታዎችን የመሰከሩ
 3. ወፍ፡- በሰሚሰሚ ወንጀሉን ማን እንደፈፀመ ከሌሎች ሰዎች ሰምቻለሁ የሚሉ መስክሮች

ከዚያም ሽማግሌዎች ስለ ወንጀሉ አፈፃፀም ምን ያህል መርፌዎች፣ ምን ያህል ድንጋዮች እና ወፎች እንደመሰከሩት ተፅፎ ይመዘገባል።

የተገኘው ማስረጃ “የወፍ” ምስክርነት ወይም የሰሚ ሰሚ ማስረጃ ከሆነ ወንጀሉን ፈፅሟል ተብሎ የተከሰሰው ሰው ይግባኝ መጠየቅ ይችላል። ማስረጃው የመርፌ (የአይን ምስክር) ወይም የድንጋይ (የአካባቢያዊ ማስረጃዎችን የሚያውቅ) ምስክር ከሆነ ግን ይግባኝ መጠየቅ አይችልም። ይህ የማስረጃው አይነት ላይ የሚደረገው ምዘና በምርመራ ሂደቱ ውጤት ላይ የራሱ ተፅዕኖ እንደሚኖው የሚያሳይ ነው። ሆኖም ግን የአፈርሳታው ማስረጃ ጥፋተኛውን ለመቅጣት መቼ በቂ ነው እንደሚባል ግልፅ አይደለም የሚለው ፖሌራ የተባለው ፀሐፊ አንዳንድ ጊዜ እዚያው በዚያው የተጠቆሙት አጥፊዎች ጥፋታቸውን የሚያምኑበት አጋጣሚ እንዳለ ፅፏል። በተጨማሪ በአፈርሳታው የተከሰሱ ሰዎች በመልከኛው (በአካባቢው አስተዳደር) ወደ አጥቢያ ዳኛው ይላካል። ተጠርጣሪው ጥፋቱን ካላመነ የአካባቢው ሰው በድጋሚ ይጠራና የወፎቹን ማንነት እንዲገልፅና ፍ/ቤት ቀርበው እንዲመሰክሩ የሚስማሙ መሆኑን ይጠይቃሉ። አንዳንድ ፀሐፊዎች ደግሞ ከተወሰነ ቁጥር በላይ “ወፎች” ቃላቸውን ከሰጡ ጥፋተኛውን ለመወንጀል በቂ እንደነበር ፅፈዋል።

 1. የአፈርሳታ ስርዓት በሕዝቡም ሆነ በማዕከላዊው መንግሥት ባለስልጣኖች ዘንድ ብዙም ታዋቂና ተቀባይነት ያለው መሆን ባይችልም በየአካባቢው ገዢዎች ግን ጠቀሜታው ከፍተኛ ነበር። በዚህም የጠቀሜታውን ያህል ችግሮች መታየታቸው አልቀረም። አንደኛው የአካባቢው ገዢ (ባላባት) አፈርሳታ መጥራቱ ያለው ተፅዕኖ ደሀዎቹን የአካባቢውን ነዋሪዎች መጨቆኛ መሆኑ ነበር። ለአውጫጭኙ ስራ የሚመጡትን ባለስልጣናትና ወታደሮች አፈርሳታው እስከቆየ ድረስ ምግባቸውንና ቀለባቸውን የሚችሉት ድሆቹ ገበሬዎች ነበሩ። ከእነዚህ መጤ ጥገኞች ለመገላገልና ወደተስተጓጎለው የግብር እና የቤት ስራቸው በፍጥነት ለመመለስ የሀሰት ውንጀላዎችና ጥፋተኛ አለመሆኑን እያወቀ በሀሰት ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ነኝ ወደማለት እንዲየመራ እንዳደረገው ይገመታል። አንዳንድ ወንጀለኞችና ሌሎች ሰዎች የ“ወፍ” ጠቋሚው ማንነት አለመታወቁን በመጠቀም ጠላቶቻቸውን ለማጥቂያነት እና ንፁሀንን ለመወንጀያነት ተጠቅመውበታል። ያለጥፋቱ በሀሰት የተጠቀመበት ሰውም የጠቋሚውን ማንነት ስለማያውቅ ለማስተባበል አስቸጋሪ ይሆንበታል።

እነኚህ የአፈርሳታ ስርዓት ላይ የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በ1925 ዓ.ም አፈርሳታን የመቆጣጠሪያ አዋጅ አውጀው ነበር። በዚህ ሕግ መሰረትም

 1. አፈርሳታ የተጠሩ ሰዎች ሌሎች ሰዎች እስኪመጡ ለመቆየት ሳይገደዱ ሞላው የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተው እንዲሰናበቱ
 2. አፈርሳታ በወር አንዴ ቅዳሜና እሁድ ብቻ እንዲጠሩ እና በስራ ቀን እንዳይደረግ
 3. አፈርሳታ ሲካሄድ ዳኛው በየሶስት ሰዓቱ እየመጣ እንዲቆጣጠር ከሩቅ ስፍራ የተጠሩ ሰዎች ሌሊቱን ከቤታቸው ውጭ በአፈርሳታ እንዲያሳልፉ እንዳይገደዱ ከብቶችን የእርሻ ስራንና ቤት ንብረትን ትቶ ቤተሰቡ ሁሉ በአንዴ እንዲመጣ ከማድረግ አንድ ሰው ምሎ ከተመረመረ በኋላ ሌሎች ቤተሰቦቹን እንዲለቅ እንዲጠየቅ
 4. የአፈርሳታ ስርዓት መራዘምን ለማስወገድ ዳኞች፣ የቤተሰብ አካላት፣ ቅዳሜ ከረፋዱ ሶስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት እንዲምሉና ምርመራው እንዲካሄድ። አባወራዎች ደግሞ እሁድ ከማለዳው አንድ ሰዓት እስከ ሶስት ሰዓት ተሰብስበው ስምንት ሰዓት ላይ ወደ የጉዳያቸው እንዲሰናበቱ። በሁለቱም ቀናት ከፈርሳታ የቀረበ የቤተሰብ አባል ካለ አባወራው አላድ ወይም ሀምሳ ሳንቲም ቅጣት እንዲከፍል። በቀጣዩ ወርም ከቀረ ዳኛው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት መቅረት አለመቅረቱን አጣርቶ በራሱ ጥፋት ከቀረ የመጀመሪያውን ቅጣት ሁለት ወይም ሶስት እጥፍ ገንዘብ እንዲቀጣ። ከአፈርሳታ ቀሪዎች የሚሰበሰብ የመቀጮ ገንዘብ በመንግሥት በተመደበ ሰብሳቢ እንዲሰበሰብ ከአስር ሁለቱ ለፍ/ቤት ዳኝነት እንዲከፈል ከአስር አንዱ ለዳኛው ከአስር ሰባቱ እጅ ለተበዳዩ እንዲከፈል። የአፈርሳታ ዳኛውም ከድሆች በዳኛ እራት ስም ምንም ነገር እንዳይቀበል ተከልክሏል።
 5. እናንተ የአካባቢው ገዢዎች የተከፈላችሁ ዳኛ ስለሆናችሁ ነው። ስለዚህ በስራችሁ ላይ ግዴለሽ በመሆን ሌቦች እንዲበራከቱ አታርጉ። የሚቀርብላችሁን አቤቱታ ተቀብላችሁ አጥፊውን ተከታትላችሁ ካላጠፋችሁ ኃላፊነቱ በእናንተ ላይ ይሆናል።

ንጉሱ የአፈርሳታን ችግሮች በዚህ አዋጅ ለመቀነስና አሰራሩን ለማሻሻል ቢሞክሩም ብዙም ውጤታማ አልሆነም። የተወሰኑ ችግሮች የአፈርሳታ ስርዓት በተወሰነ መልኩ ቀጥሎ እስከነበረበት እስከ 1953 ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ሕግ መውጣት ድረስም ሳይሻሻሉ ቀጥለዋል። የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ሕጉ ማንኛውም ወንጀል የሚመረመረው በፖሊስ ብቻ መሆኑን ቢደነግግም በግልፅ እንደአፈርሳታ ያሉ ባህላዊ ስርዓቶችን ስላልሻረ የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ሕጉ ከወጣም በኋላ ለተወሰነ ጊዜ የአፈርሳታ ስርዓት በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በስራ ላይ ይውል ነበር።

አፈርሳታ አሁን የለም። ተቀራራቢ ባህሪ ያላቸው ሕብረተሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ስራዎችግን በዘመናዊ መልክ እየተተገበሩ ነው። ምንጩ ያልታወቀ ሀብት፣ የሙስና ወንጀል፣ የኮንትሮባንድ ወንጀልን አግባብ ባለው አካል የህብረተሰቡ ክፍሎች የሆኑ ግለሰቦች እንዲጠቁሙ ማንነታቸውን በድብቅ ተይዞ ወንጀሉ ታውቆ ከተመዘበረው ገንዘብ ላይ 25 በመቶ በጉርሻ መልክ እንደሚያገኙ የሚደነግጉ የተለያዩ ሕጎች አሉን። ምስስሎሻቸውን ሳይ ከባህላዊው የአፈርሳታ ስርዓታችን የተቀዱና የተሻሻሉ አሰራሮች ይኖሩባቸው ይሆን ብዬ አስባለሁ።

 •      ይህ ፅሁፍ ለጋዜጣ እንዲመች አድርጌ ከመተርጎምና ጥቂት ማብራሪያዎችን ከመጨመር ውጪ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ የሕግ ፈካልቲ ረዳት ፕሮፌሰር ሆነው ከ1956-1960 ካገለገሉት ስታንፊ ዜድ ፊሸር የኢትዮያ ባህላዊ የወንጀል የፍትህ ሂደት በሚል በአሜሪካን የሕግ መፅሔት ቮልዩም 19 ቁ 4 ላይ ከ1963 ካወጡት የጥናት ፅሁፍ ላይ የተወሰደ በመሆኑ ፀሐፊውን አመሰግናለሁ።
ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
9042 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 925 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us