የወንጀል ሙከራና ማሰናዳት

Wednesday, 30 July 2014 12:35

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? የዛሬ ወጋችን የሚያስቀጡ የወንጀል ሙከራዎችን ይመለከታል። ለመሆኑ አንድ የወንጀል ድርጊት በወንጀል ሕጋችን መሠረት ተሞክሯል ተብሎ የሚያስቀጣው ምን ምን ሕጋዊ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው የሚለውን እናነሳለን። በዋነኛነት ሙሉ በሙሉ የምናጣቅሰው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ፀሐይ ወዳ በጉዳዩ ላይ ሁለት የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን በመተቸት የፃፉትን ፅሁፍ ነው። ረዳት ፕሮፌሰር ፀሐይ ወዳን አመስግነን እንቀጥል።

የአውሮፕላን ጠለፋ ሙከራ

በ1986 ዓ.ም ሁለት ግለሰቦች ከድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ የሀገር ውስጥ በረራ እያደረገ የነበረ አውሮፕላንን በመጥለፍ ሙከራ ተከሰሱ። እነኚህ ተከሳሾች ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ የተጓዙት አይሮፕላኑን ጠልፈው አባል የሆኑበት ወይም የሚደግፉት ታጣቂ የፖለቲካ ቡድን የታሰሩ አባላት እንዲለቀቁ ለመጠየቅ አስበው ነበር። 1ኛው ተከሳሽ በፍተሻ ላይ ተያዘበት እንጂ ቦንብ እና ጩቤ ይዟል። ሁለተኛው ተከሳሽ ደግሞ መሳሪያ ታጥቆ አውሮፕላኑ ውስጥ ገብቶ ፎቶግራፍ በ1ኛ ተከሳሽ ቦርሳ ውስጥ በመገኘቱ ወንጀሉን በአባሪነት ለመፈፀም በማሴራቸው ተከሰሱ።

የመ/ደ/ፍ/ቤት ሁለቱንም ተከሳሾች በነፃ ለቀቃቸው። 1ኛ ተከሳሽ ነው የሙከራ ድርጊቱን የፈፀመው ሆኖም ሙከራው የሚያስቀጣ አይደለም። ሁለተኛ ተከሳሽም በተገቢው ጊዜ አይደለም መሳሪያውን ይዞ የተገኘው የሚል ምክንያት ነበር ፍ/ቤቱ ለውሳኔው መሠረት ያደረገው።

ዐ/ሕግ ይግባኝ ጠየቀ። የተከሳሾች ድርጊት በሙሉ የአውሮፕላን ጠለፋ ሙከራ በመሆኑ የስር ፍ/ቤት በነጻ የለቀቃቸው ከሕግ አግባብ ውጭ ነው አለ። የተከሳሾች ተከላካይ ጠበቃ በበኩሉ ድርጊቱ እንደ ወንጀል ሙከራ ለመቆጠር በአውሮፕላን ውስጥ የሚደረግ ቀጥተኛ እንቅስቃሴ መኖር አለበት። በመሆኑም ከዚያ በፊት የተደረገው ማንኛውም ነገር የማሰናዳት ተግባር እንጂ ሙከራ አይደለም ሲል ተከራከረ።

ይግባኙ የቀረበለት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ.ቁ18/87

-    የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ሻረው። የሰጣቸው ምክንያቶች ሕገ ወጥ መሳሪያ መያዝ በራሱ ወንጀል ነው። ተከሳሾች ወደ አውሮፕላን ይዘው ለመግባት መሞከራቸው ደግሞ ወንጀሉን ለመፈፀም ቁርጠኛ ሃሳብ እንዳላቸው ያሳያል።

-    ድርጊቱ ከቦታና ከጊዜ አንጻር የነበረው ቅርበት ተከሳሾች በፍተሻ ባይደረስባቸው ያሰቡትን ነገር አውሮፕላኑ ላይ ለመፈፀም መዘጋጀታቸውን ያሳያል። ከቦታ ቅርበት አንፃር 2ኛ ተከሳሽ ሕገወጥ መሳሪያ ታጥቆ ወደ አውሮፕላኑ ገብቷል። 1ኛ ተከሳሽም ከአውሮፕላን አቅራቢያ ነበር። ይህ የሆነው ሊታገቱ የነበሩት አብራሪውና መንገደኞች አውሮፕላኑ ላይ ለመሳፈር በሚዘጋጁበት ጊዜ ነው።

-    በመሆኑም የህዝብ ማመላለሻ በሆነው በዚህ አውሮፕላን ላይ ወንጀል ለመፈፀም የተደረገው ዝግጅት ነው ከተባለ ወንጀሎችን አስቀድሞ በእንጭጭነታቸው ለመቅጨት ያሰበውን የሕጉን ዓላማ የሚስት ነው። ተከሳሾች ከፓይለቱ ጋር ወደ አውሮፕላኑ ገብተው ቢሆን ያሰቡትን ማሳካት የሚችሉበት እድል ነበር።

-    ሁለተኛ ተከሳሽም ወንጀሉን ለመፈፀም ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር ማሴራቸውን በማመኑ ለወንጀሉ መፈፀሚያ የሚሆኑ መሳሪያዎችን ከማቅረብ አልረዳም ማለት አይቻልም።

በጀርመን የተሞከረው ግድያ

ይህ ክስ ደግሞ ከሦስት ተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን የገዳይ ቡድን በማቋቋም ሽጉጦችን የድምፅ ማፈኛዎችን እና ተቀጣጣይ ቦምቦችን ከኢትዮጵያ አጓጉዘው በምስራቅ ጀርመን ወደ ምዕራብ ጀርመን በማስገባት በዚያ የሚኖሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ለመግደል በመሞከራቸው የቀረበ ክስ ነው። ተከሳሹ የተከሰሰው በጊዜው የደህንነት ሚኒስቴር ከሚባለው መሥሪያ ቤት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የማስተባበር ሥራ በመስራቱ ነው። ሌሎች በዚህ ክስ ላይ ያልተካተቱት የወንጀሉ ተሳታፊዎች ያጓጓዙትን መሣሪያ ሲሞክሩ በነበሩበት ሆቴል ውስጥ በመፈንዳቱ ተያዙ የንብረት ጉዳት እንጂ ፍንዳታው የሞት አደጋ አላስከተለም።

የቡድኑ ዓላማ ፈንጂዎችን በመፅሐፍ ውስጥ ሊገደሉ የታሰቡት ሰዎች የሚገኙበት ቢሮ እና ቤተመፅሐፍት ውስጥ ማስቀመጥ ነበር። ሌላው ደግሞ በመኪና ላይ ለማጥመድ ነበር የታሰበው።

የሥር ፍ/ቤት ተከሳሹን ጥፋተኛ ሆኖ ስላገኘው በእድሜ ልክ እስር እንዲቀጣ ወሰነበት። ተከሳሹ ይግባኝ አቀረበ። ይግባኙ ተከሳሹና ተባባሪዎቹ ግድያው ሊፈፅምበት ወደ ታቀደው ቤተመፅሐፍት አልሄዱም። ለመገደል የሚፈልገው ሰውም ቤተመፃሕፍቱ ውስ መኖራቸው አልተረጋገጠም። ድርጊቱን እንዲፈፅሙ የተላኩት ሰዎች ገና ሆቴላቸው ውስጥ የፈንጂውን የጊዜ መመጠኛና ማጥመጃ ሲያስተካክሉ ፈንድቷል። የጊዜ መመጠኛውን አስተካክለው ወደ ሆቴሉ ጉዞ ስላልጀመሩ ድርጉቱ መሰናዳት እንጂ ሙከራ አይደለም በመሆኑም የስር ፍ/ቤት ውሳኔ መሻር አለበት የሚል ነው።

ልዩ ዐቃቤ ሕግም ተከሳሹ ከተባባሪዎች ጋር በመሆን የተበዳዮችን ማንነት የት እንደሚገኙ በመለየት አስፈላጊውን መሳሪያ በማጓጓዝ ግድያውን ለመፈፀም ሲዘጋጁ ነው ፈንጂው የፈነዳው።በመሆኑም ድርጊታቸው ከዝግጅት የዘለለ ሙከራ በመሆኑ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ተገቢ ነው የሚል መልስ ሰጠ።

ይግባኙን የሰማው ፍ/ቤት ፈንጂው የፈነዳው በሆቴል ውስጥ ነው እንጂ በቤተመፅሐፍት ውስጥ አይደለም። ተበዳዮችም ድርጊቱ ሊፈፀም በታሰበበት ሰዓት በቤተመፅሐፍቱ መኖራቸው አልተረጋገጠም። በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀፅ 27 አንድ ድርጊት ከዝግጅት ደረጃ አልፎአል ወይም ድርጊቱ ተጀምሯል የሚባለው የመጨረሻው ዝግጅት ሲደረግ ነው። ይህ ማለት ወንጀሉን ለመፈፀም የሚስፈልጉ ነገሮች ሁሉ ዝግጁ ሆነው ፈፃሚው ሁሉን ነገር አዘጋጅቼ ጨርሻለሁ ሲል ነው። በመሆኑም በተያዘው ጉዳይ ዝግጅቱ ተጠናቋል የሚለው የማይሰራው ጊዜ መመጠኛ ተስተካክሎ መሳሪያዎች ወደ ቤተ መፅሐፍቱ ተጓጉዘው ቢሆን ነበር። ሆኖም እነዚህ የመጨረሻ የዝግጅት ተግባራት ሳይጠናቀቁ ፈንጂው በመፈንዳቱ ይግባኝ ላይ የግድያ ሙከራውን አካሂዷል ማለት ስለማያስችል በግድያ ሙከራ ጥፋተኛ አይደለም። ሆኖም ሕገወጥ መሳሪያ ይዞ በመገኘቱ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት ሊቀጣ ይገባል የሚል ውሳኔ ሰጥቷል።

መሠረታዊ መመዘኛዎች

በእነዚህ ሁለት ውሳኔዎች መነሻነት በሀገራችን ሕግ አንድ የወንጀል ተግባር ተሞክሯል ለመባል የሚያስችሉ መሰረታዊ መመዘኛዎችን ፀሐፊው አስቀምጠዋል። ለሀገራችን ሕግ የማሰናዳት ተግባሮች ወንጀሉን ለመፈፀም የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን ማሰባሰብ ወይም ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር በወንጀል ሕግ በአንቀፅ 26 ላይ በራሱ የማያስቀጣ መሆኑ ተደንግጓል። የወንጀል ሙከራን በተመለከተ የተቀመጠው መመዘኛ ሆን ብሎ ወንጀል ለመፈፀም አስቦ በግልፅ ፍጻሜው ላይ ቀጥተኛ ውጤት ያለው ድርጊት መሆኑ ለወ/ሕ/አ 27 ላይ ተደንግጓል። ነጠላ መመዘኛው ድርጊቱ የማያጠራጥርና እርግጠኛ መሆኑ ነው። ማስረጃነቱ ለተመለከተ መሳሪያዎችን ማዘጋጀት ብዙም ማብራሪያ አያስፈልገውም። ሆኖም ሁኔታዎችን ማመቻቸት አሻሚ ቢሆንም በቀላሉ ወንጀሉን ለመፈፀም የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት ያልዘለለ ድርጊቶችን የሚመለከት ነው።

ከላይ ከተነሱት መመዘኛዎች በተጨማሪ የወንጀል ሙከራን የሚመለከቱ የሕግ መፅሐፍት የሚያስቀምጧቸውን ሌሎች መመዘኛዎች እንመልከት።

 1. አጠራጣሪ ወይስ እርግጠኛ?

ብዙውን ጊዜ ወንጀል ለመፈፀም የሚደረጉ የማሰናዳት ተግባሮች አጠራጣሪ ሲሆኑ የሙከራ ተግባራት ግን እርግጠኛ ድርጊቶች ናቸው። እዚህ ጋር ትኩረት የሚሰጣቸው ከድርጊቱ ጀርባ ያሉት ሃሳቦች ናቸው። ሌላኛው ተያያዥነት ያለው መመዘኛ ተጨባጭ ድርጊቶች በራሳቸው ይናገራሉ። በመሆኑም ወደ ምክንያታዊ ድምዳሜ የሚያደርሱ ብቸኛ መንገዶች ናቸው። በመሆኑም በመጀመሪያው መመዘኛ መሰረት የተደረገው ድርጊት ከጀርባው ያለውን የወንጀለኛውን ሃሳብ የሚያሳይ መሆኑ ሲሆን በማሰናዳት ተግባር ግን በመደበኛ ግንዛቤ ድርጊቱ የተፈፀመው አንድን በወንጀል ድርጊት ለመፈፀም ከማሰብ ባልዘዘለ ሁኔታ መሆን አለበት።

 1. ቅርበት

የወንጀል ሙከራ ሕጎች በጋራ የሚግባቡበት ነገር ቢኖር የሙከራ ድርጊት ቅርበት ያለው መሆን ሲኖርበት የማሰናዳት ተግባሮች ግን ከድርጊቱ የራቁ ናቸው። ሆኖም ሕጉ ትክክለኛውን የቅርበት መለኪያ ስለማያስቀምጥ መመዘኛው እንደየሁኔታው የሚወሰን ነው። በመሆኑም አከራካሪ በመሆኑ የሚፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ በቅድሚያ ሌሎቹን መመዘኛዎች ጥቅም ላይ ይውላል። እነሱም፡-

2.1    የመጨረሻው ቅርበት ያለው ድርጊት፡- ይህ መመዘኛ ወንጀል ፈፃሚው የታሰበውን ውጤት ለማስገኘት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ መፈፀም እንዳለበት የሚጠይቅ ነው።

2.2    የማይቀሩ ነገሮች መያዝ፡- ይህ መመዘኛ ድርጊቱን ለመፈፀም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን መያዝን የሚጠይቅ ነው። ለምሳሌ ሕገወጥ ምርጫ ለማድረግ የድምፅ መስጫ ኮሮጆ፣ የአካል ጉዳት ለማድረስ ጉዳት የሚያደርስ መሳሪያ መያዝ ያስፈልጋል።

2.3    አካላዊ ቅርበት፡- በዚህ መለኪያ ላይ ትኩረት ብዙም ምን ተደርጓል፣ ምን ቀርቷል የሚለውና የታሰበው ወንጀል ለመፈፀም የሚያስፈልጉ የጊዜና የቦታ ቅርበቶች ላይ አይደለም። ከዚህ አንፃር ትኩረት መስጠት ያለበት። ለወንጀሉ አስከፊነት የወጤቱ እርግጠኛ አለመሆን፣ ለመከላከል አዳጋች መሆኑ እና ሊያስከትል ከሚችለው ጉዳት ጋር ተዳብሎ መታየት አለበት።

 1. ድርጊቱን የመጣው እድል፡-

በዚህ መመዘኛ የተፈፀመው ድርጊቱ በተለመዱ ሁኔታዎች የሆነ ውጫዊ ጣልቃ ገብነት ካልተከሰተ በስተቀር የታሰበውን ወንጀል ከመፈፀም የሚያስቀሩ መሆን አለባቸው። በአብዛኛው ሰው አስተሳሰብም ድርጊትን ተመሳሳይ ሃሳብ ኖሮአቸው ከመፈፀም ለመቆጠብ ወይም ለመተው ከሚችሉበት ነጥብ ያለፈ መሆን አለበት።

 1. አስፈላጊ እርምጃዎች፡-

ይህ መመዘኛ የወንጀል ሕግ ሞዴል መመዘኛ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ዋና ዋና ይዘቶቹም ድርጊቱ መሰረታዊ እርምጃዎችን አካል የሚባለው ከፈፃሚው የወንጀል ዓላማ ጋር የተሳሰረ ጠንካራ ግንኙነት ሲኖረው ነው። ትኩረት የሚሰጠውም ወንጀሉን ፈፃሚው ያደረገው ድርጊት ላይ እንጂ የሚቀረው ድርጊት ላይ አይደለም። ኃላፊነት የሚጣልበትም የወንጀል ዓላማውን ለማሳካት ያሳየው የተወሰነ ቁርጠኝነት ሳለ ነው። ይህ ድርጊቱም በተከሳሽነት ቃሉ ውስጥ ለመመርመር የሚቻል ነው።

እነዚህንና ሌሎች የወንጀል የሙከራ መመዘኛዎችን ያስቀመጡት ረ/ፕሮፌሰር ፀሐይ ወዳ ለፍተሻው መነሻ ያደረጓቸውን የፍ/ቤት ውሳኔዎች በተለይ የመጀመሪያውን የአውሮፕላን ጠለፋ ጉዳይ በተመለከተ ወንጀሉ የተፈፀመው በ1986 ዓ.ም አዲሱ የወንጀል ሕግ ከመወጣቱ በፊት ሲሆን በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 2 የሕጋዊነት መርህ መሰረት ድርጊቱ ሲፈፀም በሀገራችን ሕግ የአውሮፕላን ጠለፋ የሚባል ወንጀል በሕግ ስላልተደነገገ በወቅቱ ወንጀል ነው ተብሎ በሕግ ባልተደነገገ ጉዳይ ላይ ክስ ተመስርቶ መቀጣታቸው አላግባብ መሆኑን ጠቁመዋል።

    በሙከራና መመዘኛዎቹ መሰረትም በእያንዳንዱ መመዘኛው ሁለቱን የፍ/ቤት ውሳኔዎች የፈተሹት ረ/ፕሮፌሰር ፀሐይ ወዳ ከመመዘኛዎቹ አንጻር ሁለቱም የፍ/ቤት ውሳኔዎች ላይ የስር ፍ/ቤትም ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም የሰጧቸው ውሳኔዎች መመዘኛውን አያሟሉም ሲሉ ትችታቸውን በማብራሪያ አስደግፈው አስፍረዋል።

ይምረጡ
(10 ሰዎች መርጠዋል)
7765 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 933 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us