የተፋጠነ ፍትሕ በሕጋችን

Wednesday, 27 August 2014 11:18

ኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    የወንጀልም ሆነ የፍ/ብሔር ጉዳዮች የፍትህ መዘግየት ምን ያስከትላል?

-    ፍትህ የሚዘገይባቸው ምክንያቶች

-    የተፋጠነ የወንጀል ፍትሕ የማግኘት መብት በሕገመንግስታችንና በሌሎች ሕጐች

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? አለን። ዛሬ የምናወጋው ስለ ተፋጠነ ፍትህ ነው። በተለይም በወንጀል ጉዳይ ላይ የተንዛዛና የዘገየ ፍትህ የሚያስከትለው ተፅእኖ ምንድን ነው? በሀገራችን ሕጐች የተፋጠነ ፍትሕን የማግኘት መብታችን ተረጋግጧል? በየትኞቹ ሕጐች ላይ? የፍትህ ተቋማቶቻችንስ በተጨባጭ በተገቢው ጊዜ ፍትህን እየሰጡ ነው? በጉዳዩ ላይ የደተረጉ ጥናቶች ምን ይላሉ? የሚሉትን ነጥቦች እናነሳለን። በዚህ ጽሁፍ ላይ የእኔ ሚና ለጋዜጣ እንደሚመች አድርጐ ማቅረብ እንጂ ሙሉ ኀሳቡን የወሰድኩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር የሆነት ተባባሪ ፕሮፌሰር ፀሐይ ወዳ “የወንጀል ጉዳዮችን በተገቢው ጊዜ (ሳይዘገይ) መዳኘት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ካቀረቡት ጥናት ነው። ተባባሪ ፕሮፌሰር ፀሐይ ወዳን ላበረከቱልን ጥናት እጅ ነስቼ ላመስግንና ልቀጥል።

ተከናንቦ የተኛ መዝገብ

“ዓለም ወረተኛ ክፉ ባል አግብታ

ውሽማዋ ጉቦን ከቤቷ አስተኝታ

ከሳሽ ሐዘንተኛ ተከሳሽ ሰርገኛ

እንግዲህ ዶሴዬ ተከናንበህ ተኛ”

ድምፃዊ ፍሬው ኃይሉ

“ተከናንቦ የተኛ ዶሴ” (መዝገብ) ታውቃላችሁ? ነፍሱን ይማረውና ፍሬው ኃይሉ በዘመኑ የታዘበውን የፍትህ መዘግየት እና የሥርዓቱ በሙስና መዘፈቅ የገለፀባቸው ውብ ስንኞች መዝጊያ ሐረግ ነው። እህህ… እያለ በአኰርዲዮኑ አጅቦ ብሶቱን ሲያንቆረቁረው፤ የፍትህ መዛባትና፣ መነፈግና መዘግየት በባለጉዳዮች ላይ የሚያሳድረውን ህመምና መከፋት ዘልቆ እንዲሰማን ያደርገናል። ፍሬው ኃይሉ በሙዚቃው ውስጥ ዓለም በጉቦ እንደተዘፈቀች ከሳሽ በተገቢው ጊዜ ጉዳዩ ውሳኔ ባለማግኘቱ ሲጉላላና ሲያዝን ተከሳሽ በሰጠው ጉቦ የተከሰሰበት ጉዳይ ሳያሳስበው እንደሰርገኛ እየተደሰተ እንዳለና በዚህም ከሳሹ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ተስፋ ቆርጦ የከፈተውን መዝገብ ዳኞቹ ውሳኔ አያሳርፍብህም። “ተከናንቦ ተኛ” ሲለው ይሰማናል። በአጭሩ ለዳኝነት ያቀረብነው ጉዳይ ቢቻል በፍጥነት ካልተቻለም በተገቢው ጊዜ ውሳኔ ካልተሰጠበት እና ከተጓተተ መዝገብ ቤት ተከናንቦ ተኝቷል ለማለት ነው። መብታችንን ልናስከብርበት ወይም መብት የለንም ብለን ቁርጣችንን አውቀን ልንቀመጥ አንችልም። ከዛሬ ነገ ይወሰናል ስንል ወራት፣ ዓመታት ያልፋሉ። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ነው ፍሬው በግጥምና በዜማ የገለፀው።

ወደ ተባባሪ ፕሮፌሰር ፀሐይ ወዳ ጥናት ስንመልሰው ደግሞ የፍሬው ኃይሉን ኀሳብ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲህ ተብራርቷል።

የወንጀል ጉዳይን በተገቢው ጊዜ እልባት መስጠቱ ሕግ የጣሱ ሁሉ በልባቸው የሚመላለስ ጉዳይ ነው። የቆየው ብሒልም ቢሆን “የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል” እንደሚለው በተገቢው ጊዜ የፍርድ ውሳኔ ማግኘት ወይም የተፋጠነ ፍትህ በአብዛኛው የምናነሳው በወንጀል ከተከሰሰ ተከሳሽ አንፃር ቢሆንም፤ በፍ/ብሔር ጉዳይ ተሟጋቾ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ተመጣጣኝ ነው። ዋነኛው ችግሩ ብዙ የሰነበተ ሙግት የተከራካሪዎቹ መብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ነው። የሕግ ጉዳይ ውሳኔ ለማግኘት በጣም የረዘመ ጊዜ ከወሰደ አንደኛው ተከራካሪ ወገን ተጐጂ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ምስክሮች ሊሞቱ ወይም ሊጠፉ ይችላሉ፤ ቁሳዊ ማስረጃዎች የማስረዳት አቅማቸው ሊላሽቅ ወይም ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሊጐዱ ይችላሉ። የማስታወስ አቅምም ይዳከማል። በተለይም ደግሞ በወንጀል ጉዳዮች በቀዳሚነት መብቱን የሚነፈገው ተከሳሹ ነው። ምክንያቱም እንደ ዐቃቤ ሕጉ ለፍርድ ቤት የሚያቀርበውን ማስረጃ ለማሰባሰብ የሚያስችለው ነፃነትና የገንዘብ፣ የሰው ኃይልና ሌሎችም ምንጮች የሉትም። የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብትን መነፈግ ዐቃቤ ሕጉ ክርክሩ የሚፈጀውን ጊዜ እንዲወስን በር ስለሚከፍትለት በመጨረሻም ተከሳሹን ያለ ምንም ዋስትና ዳኝነት ከማግኘቱ በፊት በቁጥጥር ስር እንዲውልና የከሳሽነት ስልጣኑን አለአግባብ እንዲጠቀምበት ሊያደርገው ይችላል። የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ባሳተመው ሰነድ ላይ የፍትህ መዘግየት ተፅዕኖ በዚህ መልኩ ተገልጿል።

“በፍትህ አስተዳደር ውስጥ የሚከሰት አለቅጥ መዘግየት ሁነኛ አደጋዎችን ያስከትላል። በተለይም የሕግ የበላይነትን ከማክበር አንፃር የሙግት ስነስርዓቶች የተፋጠኑ መሆናቸው በሕጉ ላይ እንዲኖር ለሚፈለገው እርግጠኝነት ምላሽ የሚሰጥ ነው። ምክንያቱም ለዜጐችም ሆነ ለመንግስት እንዲሁም ለሌሎች ዘርፈ ብዙ ፍላጐቶቻቸውን በተቻለ መጠን ምላሽ በመስጠት ግለሰቦች ሰላማዊ ሕይወትን እንዲመሩ ያስችላቸዋል። … የኢኮኖሚው እንቅስቃሴም ለረጅም ጊዜ እልባት ሳያገኙ በሚቆዩ ሙግቶች ጉዳት ይደርስበታለ። ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ክርክሮች እንዲህ አይነት ሰላማዊ ኑሮን ይረብሻሉ። የፍ/ቤት የሙግት ስነስርዓቶች ለዘላለም የሚቀጥሉ ባይሆኑም፤ የፈጁትን ያህል ጊዜ ፈጅተውም ሐቀኛ ትህን ላያስገኙም ይችላሉ። ውሳኔዎች በተወሰኑ መጠን አስቀድመው ሊገመቱ በሚችሉበት ሁኔታ መወሰን አለባቸው።

የፍትህ መዘግየት ፍትህን ለማስከበር፣ ሙግቶችን ለመወሰን እና በተለይም ደግሞ ወንጀለኞችን ለመቅጣትና ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን ለመግታትና ለመከላከል መንግሥት ያለው አቅም ላይ ሕዝቡ የሚያሳድረው አመኔታ ይሸረሸራል። ይህ ደግሞ ግለሰቦች አማራጭ የግጭት መፍቻ ደግሞ ግለሰቦች አማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶችን እንዲከተሉ ወይም በራሳቸው መንገድ በደሉን የሚሉትን ወገን እንዲቀጡ ሊያደርጋቸው ብሎም ሊያነሳሳቸው ይችላል።”

የወንጀል ሂደቶች በሕዝብ ገንዘብ ወጪያቸው የሚሸፍን እንደመሆኑ የሚወስዱትን ጊዜ ማሳጠር የህዝቡን ገንዘብ መቆጠብም ነው። በመሆኑም ተከሳሹም ሆነ ማኅበረሰቡ በተፋጠነ የፍትህ ሂደት መብት ላይ የማያጋጭ ፍላጐት እንዳላቸው መገንዘብ ያስፈልጋል። የተከሳሹ ፍላጐት፤ መንግስት ያቀረበበት ክስ የሚያሳድርበትን መረበሽ፣ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብቱ ላይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን፣ ከስራ መፈናቀሉን፣ በህዝቡ የሚደርስበትን ነቀፌታ መቀነስና በተጨማሪ ከፍርድ በፊት የሚደርስበትን ያልተገባ የእሰር ጫና ማስወገድ ነው የማኅበረሰቡ በተፋጠነ ፍትህ ላይ ያለው ፍላጐት ደግሞ ለዐቃቤ ሕጉ የማያዳላ ውጤታማ የወንጀል ክስ ዳኝነት፣ በይፋ የሚፈፀሙ የወንጀል ክስ ሂደት አለአግባብ መጠቀምንና የባለስልጣናትን ሕገወጥ ድርጊቶችን መቅጣት፣ በእስር ላይ ያልዋለ ተከሳሽ ፍርዱን በመጠበቅ ላይ እያለ ተጨማሪ ወንጀል እንዳይሰራ መከላከልና መጨረሻ ላይ በነፃ የሚለቀቁ ተከሳሾች የፍርድ ውሳኔ በእስር ላይ ሲቆዩ የሚባክነውን ወጪ መቀነስ ናቸው።

ከላይ የተነሱት እውነታዎች ቢኖሩም የፍርድ ሂደቶች በበርካታ አገሮች ውስጥ አዝጋሚ ናቸው። የዚያኑ ያህል ለውሳኔ ዓመታተን የፈጁ ጉዳዮች ለእያንዳንዱ ሰው ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል። ለአዝጋሚ የፍርድ ሂደቶች በርካታ ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል። ከእነኚህ ምክንያቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።

-    በወንጀል ፍትህ ስርዓቱ የተለያዩ አካሎች ማለትም ፖሊስ፣ ዐ/ሕግ፣ ፍ/ቤቶች ላይ የጉዳዮች መደራረብ፣

-    በተለያዩ ምክንያቶች የምስክሮች መታጣት፣

-    ከእስር ለማምለጥ የተጠርጣሪዎች መሸሽ፣

-    ከፍርድ በፊት የሚኖሩ መለዋወጦችና ጉዳዩን በጊዜው ለመወሰን የሚያስችል እንዲሁም ሕጉ ያስቀመጠው ጊዜ ሲያልፍ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ሕጉ የሚጠይቀው አስፈላጊ ነገር መጉደል ነው።

ይህ ችግር ዓለም አቀፍ እንደመሆኑ የተለያዩ የዓለማችን የፍትህ ስርዓቶች የተፃፉ ጽሁፎች እንደሚያሳዩት በርካታ ሀገሮች የፍትህ መዘግየት የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማሉ። አንዳንድ የፍትህ ስርዓቶች ልዩ ልዩ የፍትህ አካላቶች ክሶችን የሚከታተሉበት አስገዳጅ የጊዜ ገደብ ያስቀምጣሉ። ይህን የጊዜ ገደብ አለመጠበቅም አድሎ በሚያስከትል መልኩ ወይም በማያስከትል መልኩ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ያደርገዋል። ከፍትህ መዘግየት ጋር በተያያዘ ቅርበት ያለው መፍትሄ የይርጋ ሕግ ሲሆን፤ የሚዘገዩ ክሶች በተወሰነ ጊዜ እልባት እንዲያገኙ ያስችላል።

የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት በኢትዮጵያ ሕጐች

በሀገራችን የተፋጠነ ፍትህ ማግኘት ሕገመንግሥታዊ መብት ከመሆኑም ባሻገር የተለያዩ ዝርዝር የበታች ሕጐችም ይህ መብት ተግባራዊ የሚሆንባቸውን ድንጋጌዎች በሚጠበቀው መልኩ ባይሆንም አካተዋል። ሆኖም ግን በተግባር የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት ከመከበር ይልቅ ሲጣስ ይስተዋላል።

ሕገ መንግስት፡- ሕገ መንግስታችን በአንቀጽ 17 ማንም ሰው ክስ ሳይመሰረትበት ወይም ሳይፈረድበት እንደማይታሰር ይደነግጋል። የተያዙ ሰዎችን መብት የሚዘረዝረው አንቀጽ 19 የተያዙበትን ምክንያት እና የቀረበባቸውን ክስ የማወቅና ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ በ48 ሰዓታት ፍ/ቤት የመቅረብ መብት እንዳላቸውና በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ፍ/ቤት ካልቀረቡ የያዛቸው ፖሊስ ወይም ሕግ አስከባሪ አካላዊ ነፃነታቸውን እንዲያከብር (ከእስር እንዲለቃቸው) ፍ/ቤቱን የመጠየቅ መብትና በዋስ የመለቀቅ መብታቸውን ደንግጓል። አንቀጽ 20 ደግሞ የተከሰሱ ሰዎች በሕግ የመዳኘት ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት በግልፅ ችሎት በተገቢው ጊዜ የመዳኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

እነኚህ ሕገ መንግስታዊ አንቀጾች በዝርዝር ያልተቀመጡና ግልፅ ያልሆኑ በመሆናቸው ለትርጉም የተጋለጡ ናቸው። ለምሳሌ በአንቀጽ 19 የተጠቀሰው የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት በአንቀጽ 20(1) ግልጽ ባልሆነው ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ በሚለው ሐረግም አሻሚ ነው። በግልፅ በጊዜ የተገደበው በአንቀጽ 19(3) ስር ያለው በ48 ሰዓታት ፍ/ቤት የመቅረብ መብት ሲሆን፤ በዋስትና የመለቀቅ መብት ግን ተግባራዊ የሚሆነው በሕጉ የተቀመጡ ልዩ ሁኔታዎች የማይከለክሉት ከሆነ ብቻ በመሆኑ ግልፅና ቁርጥ ያለ መብት ነው ለማለት ያዳግታል።

የወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ሕግ፡- ሕገ መንግሥቱ ጠቅላላ መብቶችን የደነገገ ሲሆን፤ የበታች ሕጐች እነኚህን መብቶች ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ አንፃር የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉ ጠቃሚ ድንጋጌዎችን አካቷል። የተፋጠነ ፍትህ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ በርካታ ምክንያቶች ከፖሊስ፣ ከዐ/ሕግ፣ ከፍ/ቤት ብሎም ከተበዳዩ ሊነሱ ይችላሉ። እስቲ እንመልከታቸው።

የምርመራ ጊዜ፡- የወንጀል ክስ ምርመራ የሚካሄደው ፖሊስ ተጠርጣሪውን ከጠራ ወይም ካሰረ በኋላ ነው። በትክክል ለመናገር ለዚህ ምርመራ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ የለም። “ካላስፈላጊ መዘግየት” ፖሊስ ምርመራውን ማጠናቀቅ አለበት በሚል ድፍን እና አለአግባብ ለመጠቀም በተመቻቸ ሐረግ ነው የተገለፀው። የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉ ለዚህ ያስቀመጠው መፍትሄ ተጠርጣሪው ዋስ በመጥራት ፖሊሱ በሚወስነው ጊዜ እና ቦታ ለመቅረብ ቃል ገብቶ እንዲለቀቅ ሲሆን፤ ይህም የሚሆነው የተጠረጠረበት ወንጀል በፅኑ እስር የሚያስቀጣ ሲሆን፤ ወይም ወንጀሉን መፈፀሙ አጠራጣሪ ከሆነ አሊያም ተጠርጣሪው ወንጀሉን መፈፀሙ ከተረጋገጠ ነው። ተከሳሹ እነኚህን መስፈርቶች አሟልቶ ካልተለቀቀ በዋስትና እንዲለቀቅ በፍ/ቤት ማመልከት ይችላል።

ተከሳሹ ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች ሊለቁት ካልቻሉ ምርመራው ላልተወሰነ ጊዜ ሊቀጥል ስለማይችል፤ ምርመራውን ካላጠናቀቀ ፖሊሱ ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ይጠይቃል። በእያንዳንዱ ጥያቄ የሚፈቀድለት ጊዜ ከ14 ቀናት አይበልጥም። የተከሰሰበት ወንጀል በሞት ወይም በፅኑ እስር በሚያስቀጣ ከባድ ወንጀል ካልሆነ ወይም ተበዳዩ በደረሰበት ጉዳት የሚሞት ካልመሰለ ፍ/ቤቱ ዋስትና ሊፈቅድለት ይችላል። በሽብር ወንጀል ከ19 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች የዋስትና መብት በሕግ ተከልክሏል። በተጨማሪ ተከሳሹ የዋስትናው ሁኔታዎችን የሚያስከብር ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል የሚፈጽም ወይም ምስክሮችን እና ማስረጃዎችን የሚያጠፋ መስሎ ከታየው የዋስትና መብት ላያከብርለት ይችላል።

እነኚህ ገደቦች ቢኖሩም ፖሊስ ለምን ያህል ጊዜ “ጊዜ ቀጠሮ” ተከሳሹ ላይ እንደሚጠየቅ የተቀመጠ ገደብ ባለመኖሩ ተከሳሹ ላልተወሰነ ጊዜ ሳይፈረድበት በፍ/ቤት ይሁንታ በፖሊስ ሊታሰር ይችላል። ተከሳሹ ፍ/ቤቱ ዋስትና ሲከለክለው ይግባኝ የማለት መብት ያለው መሆኑ በግልፅ አልተቀመጠም። ሕጉ የምርመራ ጊዜን ካለመገደቡም በላይ አላስፈላጊ መዘግየት ሲከሰት መዝገቡን የመዝጋት መብት እንዳለውም አይገልጽም።

ቀዳሚ ምርመራ፡- በሕጉ ቀዳሚ ምርመራ የሚደረገው በነፍስ ማጥፋት እና በከባድ ውንብድና ለተከሰሰ ተከሳሽና በወ/መ/ሥ/ሥ/መ/ሕ/አ 80 መሠረት ወዲያውኑ ክሱ መሰማት ካልቻለ ነው። በመሆኑም ለቀዳሚ ምርመራ ቀጠሮ መሰጠት የለበትም። አላማውም የምስክሮችን ቃል መቀበል ነው። ተከሳሹም የሚቀርቡለትን ምስክሮች ስም ማስመዝገብ ይችላል። በተጨማሪ ፍ/ቤት ተከሳሹ የሚሰጠውን ቃል በማንኛውም ጊዜ ክሱ ከመመስረቱ በፊት መቀበል ይችላል። ይህ እንደ ቀዳሚ ምርመራ የፍትህ መዘግየት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም።

ክስ መመስረቻ ጊዜ፡- በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/አ 109(1) ዐቃቤ ሕግ የፖሊስ ምርመራ ወይም የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ በደረሰው በ15 ቀናት ውስጥ ክሱን እንዲያዘጋጅ ይደረጋል። ሆኖም በተቀመጠው ጊዜ ባያዘጋጅስ የሚለውን አልመለሰም። ተከሳሹ ወይም ተበዳይ ክሱ እንዲቀርብ መጠየቅ መቻሉን በተመለከተ ያስቀመጠው ድንጋጌ የለም።

ክስ ከተመሰረተ በኋላ፡- ፍ/ቤቱ ክሱ የሚሰማበትን ጊዜ እንደሚወስን የሥነሥርዓት ሕጉ በአንቀጽ 94 ላይ ያስቀምጣል። ምን ያህል ጊዜ የሚለው ግን አልተገደበም። ቀጠሮን በተመለከተ ፍ/ቤቱ ቀጠሮ የሚሰጥባቸው ምክንያቶች ተዘርዝረዋል። ሆኖም ፍትህ እንዳይዘገይ ቁርጥ ያለ ጊዜ አላስቀመጠም። ሆኖም በተዘዋዋሪ መንገድ የወንጀል ፍትህ መዘግየትን ለማስቀረት የሚሞክሩ ድንጋጌዎችን አካቷል። ለፍትህ መጓተት አስተዋፅኦ የሚያበረክቱት የሚከተሉት ነጥቦች ናቸው።

-    “ለፍትህ አስፈላጊ ከሆነ” ላልተወሰነ ጊዜ የክስ ሂደቱ ሊቋረጠ መቻሉ ለፍትህ አስፈላጊ የሚለው ቃል አሻሚ በመሆኑ ተገቢው መመሪያ ካልተበጀለት ለፍትህ መዘግየት መንስኤ ይሆናል።

-    በአንቀጽ 94(2) ስር የተዘረዘሩት ያልተወሰኑ የቀጠሮ መስጫዎች የበዙ ሲሆኑ፤ በአንቀጽ 95 ስር የተሰጠው ተደጋጋሚ ቀጠሮዎችን የማጣሪያ ድንጋጌም በቂ አይደለም።

-    ሕጉ ቀጠሮ በየሳምንቱ እንዲሆን ቢያስቀምጥም በተደጋጋሚ መቅጠር የሚቻል መሆን፣ አለመሆኑን አላስቀመጠም።

ዋነኛው ነጥብ የተራዘመ ወንጀል ክስ ሂደትን ወይም ተደጋጋሚ ቀጠሮን በተመለከተ የይግባኝ መብት አለመፈቀዱ ነው።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
7208 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1155 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us