የሽልማት ማስታወቂያ የሕግ አስገዳጅነቱ

Wednesday, 10 September 2014 10:55

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. '; document.write(''); document.write(addy_text53630); document.write('<\/a>'); //-->\n This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.


-    አንድንድድር ላሸነፈ ወይም ድርጊት ለፈፀመ ሰው ሽልማት ለመስጠት ቃል የገባ ሰው ያለበት ግዴታ፣

-    ሸልማለሁ ብሎ ሳይሸልሙ መቅረት ይቻላል?

-    የስጦታ የተስፋ ቃል እና ሽልማት ልዩነታቸው ምንድነው?

-    እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ የደረሰው የቁንጅና ውድድር አሸናፊዋና የውድድሩ አዘጋጅ የሽልማት ክርክር በምን ተቋጨ፣

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? እንኳን ለ2007 ዓ.ም በሰላም አደረሰን። አዲሱ ዓመት የሰላም ፍቅር፣ የጤናና የብልፅግና እንዲሆንልን እመኛለሁ። ከበዓላት ጋር ተያይዞ የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶች ይኖራሉ። እነኚህ ዝግጅቶች እና ሌሎች የማስታወቂያ የገቢ ማሳሰቢያ ዝግጅቶች ላይ ብዙውን ጊዜ አንድ ነገር ቃል ይገባል። ሽልማት ይህን ውድድር ባሸነፈ፣ ይሄ እጣ ለወጣለት፣ ይሄን ምልክት ላገኘ ይህን ያህል ገንዘብ ወይም ንብረት፣ የጉዞ የመዝናኛ፣ የትምህርት እድሎች በሽልማት መልክ እንደሚሰጡ ቃል ይገባሉ ማን? አዘጋጆች ወይም ስፖንሰሮች። አንዳንዴ ታዲያ ቃል የተገባው ሽልማት የውሃ ሽታ የሚሆንበት አጋጣሚ ይከሰታል።

ለመሆኑ ሕግ እንደዚህ አይነት የተስፋ ቃሎችን እንዴት ያያቸዋል? ሽልማቱን ቃል የገባው ሰው ቃሉን ቢያጥፍ የሚገደድበት አግባብ አለ? እስቲ ሕጋችንን እና በዚሁ ጉዳይ ላይ እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት የደረሰ አንድ ክርክር ላይ የተሰጠ ውሳኔን እንመልከት።

መስከረም 9 /2001 ዓ.ም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች፣ ክልላዊ መንግስት በኮንሶ ልዩ ወረዳ ካራት ከተማ የደቡብ ሚስ ቱሪዝም የቁንጅና ውድድር ተካሂዶ ነበር። በዚህ ውድድር ከክልሉ ልዩ ልዩ ዞኖች የተውጣጡ በርካታ ቆነጃጅት ተሳትፈዋል። ውድድሩን ያዘጋጀው ተርካንፌ ፕሮሞሽንና ማስታወቂያ ስራ ድርጅት ሲሆን በውድድሩ ላይ 1ኛ ለምትወጣው ቆንጆ በሀዋሳ ከተማ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ፣ በክልሉ በሚገኙ ኮሌጆች የነፃ ትምህርት እድልና ፣ የብር 5ሺህ ሽልማት እንደሚሰጥ ማስታወቂያ ላይ ተገልጿል። በማስታወቂያው መሰረት ቆነጃጅቱ ሊወዳደሩ ተመዘገቡና ውድድሩ ተካሄደ። በውድድሩ አሸንፋ የደቡብ ሚስ ቱሪዝም የተባለቸው ወ/ት ፍሬወይኒ ቴዎድሮስ ስትሆን ቃል ከተገቡት ሽልማቶች መካከል የነፃ ትምህርት እድሉና የብር 5ሺህ ገንዘብ ስጦታው ተሰጣት የቤት መስሪያ ቦታው ግን በተገባላት ቃል መሰረት አልተሰጣትም።

ይሄኔ የቁንጅና ውድድሩ አሸናፊ ወ/ት ፍሬወይኒ የውድድሩን አዘጋጅ ተርካንፌ ፕሮሞሽንና ማስታወቂያ ስራ ድርጅትን በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት ከሰሰችው። ክሱ የውድድሩ አዘጋጅ ለአሸናፊዋ ለመስጠት ቃል የገባውን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣት ቦታውን መስጠት ካልቻለ ደግሞ በወቅቱ የሀዋሳ ከተማ የ200 ካሬሜትር የቤት መስሪያ የሊዝ ዋጋ ተመን ብር 360,000 እንዲከፍላት የሚጠይቅ ነበር።

የውድድሩ አዘጋጅ ተርካንፌ ፕሮሞሽን ለክሱ በሰጠው መልስ በውድድሩ ማስታወቂያ ላይ የተገለፀው እድል የሚለው ቃል የስጦታ የተስፋ ቃል እንጂ ሽልማት ባለመሆኑ ግዴታ አይጥልብኝም። የስጦታ የተስፋ ቃል በሕግ ፊት ተቀባይነት የለውም። የውሉ ጉዳይም የሚቻል ባለመሆኑና መሬት የመንግስትና የሕዝብ ንብረት በመሆኑ ልገደድበት አይገባም። ስለዚህ የአሸናፊዋ ቆንጆ ክስ ውድቅ ይደረግልኝ አለ።

የሀዋሳ ከፍተኛ ፍ/ቤትም ቆንጆዋን እና የቁንጅና ውድድር አዘጋጁን ድርጅት አከራክሮ የውድድሩ ማስታወቂያ የሚያሳየው የስጦታ የተስፋ ቃል በመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 243 መሰረት አዘጋጁ ላይ ግዴታ አይጥልበትም። የሽልማቱ ጉዳይም የሕዝብና የመንግስትን መሬት የሚመለከት በመሆኑ አዘጋጁ በራሱ ለአሸናፊዋ ሊሰጣት የሚችለው ነገር ባለመሆኑ የደቡብ ሚስ ቱሪዝም ወ/ት ፍሬወይኒ ክስ ተቀባይነት የለውም ሲል ወሰነ።

ወ/ት ፍሬወይኒ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበችው የይግባኝ አቤቱታም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። በመሆኑም በስር ፍ/ቤቶች የሕግ ስህተት ተፈፅሟል የውድድሩ አዘጋጅ በግልፅ በማስታወቂያ ከገለፃቸው ሽልማቶች መካከል ሁለቱን ሰጥቶ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ለመሸለም ቃል አልገባሁም በማለት ያቀረበውን ክርክር በበታች ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት ማግኘቱ ሕጉ ስለውል አፈፃፀም ያስቀመጣቸውን ድንጋጌዎች መሰረት ያላደረገ በመሆኑ ይታረምልኝ ስትል አመለከተች። የውድድሩ አዘጋጅም የሰበር አቤቱታ ደርሶት በሀዋሳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያደረገውን ክርክር የሚያጠናክሩ ነጥቦችን አንስቶ ተከራክሯል።

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቁንጅና የውድድሩ አዘጋጅ ለአሸናፊዋ ቃል የገባውን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት ይገደዳል ወይስ አይገደድም የሚለውን ነጥብ ላይ ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔውን ከማየታችን በፊት እስቲ ሕጎቻችን በተነሳው ጉዳይ ላይ የሚሉትን እንመልከት።

ሽልማት የመስጠት ውል

ስለውል ግንኙነቶች መብቶችና ግዴታዎች የሚደነግገው የፍ/ብሔር ሕጋችን በአንቀፅ 1689 ላይ ሽልማት ለመስጠት በግልፅ የሚሰጥ የተስፋ ቃል በሕግ ፊት ተፈፃሚነት ያለው ውል መሆኑን ይደነግጋል። አንድ ሰው የጠፋ እቃን ላገኘ ወይም አንድን ሌላ ነገር ለፈፀመ ሰው ሽልማት ይሰጠዋል ብሎ በማስታወቂያ ከለጠፈ ወይም በአደባባይ ሊታወቅ በሚችል የመገናኛ ዘዴ ቃል ከገባ ቃሉን እንዲፈፅም ይገደዳል።

ይህ ሽልማት የመስጠት ግዴታው ተፈፃሚ የሚሆነው ለሽልማት የሚያበቃውን ነገር መፈፀም ወይም ማግኘት ለቻለ ሰው ሲሆን ይህ ሰው በሽልማቱ ላይ በሽልማት ያበቃል ተብሎ የተገለፀውን ነገር ያደረገ ወይም የጠፋ ነገር ያገኘው እንደሚያሸልም ሳያውቅ ወይም ሽልማት እንደሚሰጥ የወጣውን ማስታወቂያ ሳያይ ወይም ሳይሰማ እንኳን ቢሆንም ለሽልማት የሚያበቃውን ድርጊት የፈፀመው እሸልማለሁ ባዩ የሰጠውን የተስፋ ቃል ተቀብሎ እንደሆነ ይቆጠርለታል። በመሆኑም ሽልማት ለመስጠት በግልፅ ቃል የገባ ሰው ለሽልማት የሚያበቃውን ድርጊት ለፈፀመ ሰው ቃል የገባውን ሽልማት የመስጠት የውል ግዴታ አለበት።

ስጦታና ሽልማት ይለያያሉ። በፍ/ብ/ሕጋችን ስጦታን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ከአንቀፅ 2427 ጀምሮ በዝርዝር የተቀመጡ ሲሆን ስጦታ ሰጪው ችሮታ በማድረግ ሃሳብ ከንብረቶቹ አንዱን የሚለቅበት ወይም ግዴታ የሚገባበት ውል ሲሆን ሽልማት ግን አንድን ድርጊት ለሚፈጽም ሰው ሽልማት ሰጪው የሚሰጠውን ሽልማት በመግለፅ በሚያወጣው ማስታወቂያ መሰረት ያን በማስታወቂያው ላይ የተፈፀመውን ድርጊት ለሚፈፅም ሰው በገባው ግዴታ መሰረት ለመፈፀም የሚገደድበት ነው። ስለዚህ በቀላሉ ስጦታ በችሮታ ላይ ሲመሰረት ሽልማት ግን አንድን በግልጽ የተነገረ ተግባር በመፈፀም ላይ የተመሰረተ ነው።

ስጦታ እሰጣለሁ ብሎ ቃል መግባት የስጦታ ውል ከሌለ በስተቀር ቃል ገቢው ላይ በፍ/ብ/ሕ በ2435 መሰረት ግዴታ እንደማይጥልበት የተደነገገ ሲሆን ሆኖም የስጦታ ቃል የተገባለት ሰው የተሰጠውን ቃል በመተማመን በቅን ልቦና ያወጣው ገንዘብ ካለ እንዲመለስለት መጠየቅ ይችላል።

ሰበር ምን አለ?

ወ/ት ፍሬወይኒን እና የተርካንፌ ፕሮሞሽን ክርክር ላይ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 62146 ሐምሌ 12 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቷል።

ሰበር ጉዳዩ የስጦታ የተስፋ ቃል ሳይሆን የውድድሩ አዘጋጅ ሽልማት የመስጠት በግልፅ ቃሉን የሰጠበት ውል ነው በሚል የሰበር ፍ/ቤቶች ጉዳዩን እንደ ስጦታ ተስፋ ቃል ማየታቸው አግባብ አለመሆኑን ጠቅሶ ከታች በኋላ ወደ ዋናው ነጥብ አልፏል። ለክርክሩ መሰረት የሆነው የቁንጅና ውድድር አዘጋጅ ድርጅት የፃፈው ደብዳቤ “. . . በውድድሩ አሸናፊ የሆነች ወጣት በክልሉ ርዕሰ ከተማ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እና በክልሉ በሚገኙ ታላላቅ ኮሌጆች ውስጥ ነፃ የትምህርት እድል ሲኖራት የብር 5000.00 (አምስት ሺህ) ገንዘብ ሽልማትም ታገኛለች” በሚል የተቀመጠ ሲሆን ወ/ት ፍሬወይኒ ውድድሩን በማሸነፍ ሁለቱን ሽልማቶች አዘጋጅ ድርጅቱ ሰጥቷታል። “እድል ሲኖራት . . .” የሚለውን ቃል የስር ፍ/ቤት የተስፋ ቃል እንጂ ግልፅ የሆነ ሽልማት እንደሚሰጥ የሚያሳይ መሆኑን የሚያረጋግጥ አይደለም ብሎ የሰጠው ትርጓሜ የወል ቃላቶች ግልፅ ባልሆኑ ጊዜ ፍ/ቤቶች ምን አይነት አተረጓጎም መከተል እንደሚገባቸው ሕጉ የደነገጋቸውን ድንጋጌዎች ያልተከተለ አተረጓጎም ነው። በመሆኑም የውድድሩ አዘጋጅ ተርካንፌ ፕሮሞሽን በአሸናፊዋ በሀዋሳ ከተማ የመኖሪያ ቤት ለመስጠት ግዴታ ገብቷል።

መሬት የመንግስትና የሊዝ ስለሆነ ግዴታው ሊፈፀም አይችልም የሚለውን መከራከሪያ በተመለከተ መሬት የመንግስትና የሕዝብ ቢሆንም አዘጋጁ በገባው ቃል መሰረት የሊዝ ሕጉን ተከትሎ እሰጣለሁ ብሎ የገባውን የቤት መስሪያ ቦታ ሊያገኝ አይችልም የሚያስብል አይደለም። በመሆኑም የሀዋሳ ከተማ ከ/ፍ/ቤትና የክልሉ ጠ/ፍ ቤት የሰጡት ውሳኔ የሕግ ስህተት ስለተፈፀመበት ተሸሮ ተርካንፌ ፕሮሞሽን ለመሸለም ቃል በገባው መሰረት ለቁንጅና ውድድሩ አሸናፊ ለወ/ት ፍሬወይኒ ቴዎድሮስ በሀዋሳ ከተማ 200 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ በሊዝ ገዝቶ እንዲሰጣት ይህን ካልቻለ በከተማው የሊዝ ዋጋ መሰረት ተተምኖ የሚመጣውን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ዋጋውን እንዲከፍላት ተወስኗል።

ስለዚህ በተለያዩ አጋጣሚዎች አንድን ድርጊት ለፈፀመ ሰው ሽልማት እንደሚሰጡ ቃል የሚገቡ ሰዎች ቃል ከመግባታቸው በፊት በደምብ ቢያስቡበትና ቃላቸውን ለመሸለም የሚያበቃውን ነገር ቃላቸውን ጠብቀው መሸለም ግዴታ እንዳለባቸው ልብ ሊሉ ይገባል። ውድድሩን አሸንፈው ያሸልማል የተባለውን ድርጊት ፈፅመው ሽልማቱ ያልተሰጣቸውም በሕግ መብታቸውን ማስከበር እንደሚችሉ ጠቁሜ ላብቃ።                          

                              መልካም አዲስ ዓመት

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
6611 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 937 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us