ስለዋስትና

Wednesday, 17 September 2014 14:13

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. '; document.write(''); document.write(addy_text47748); document.write('<\/a>'); //-->\n This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.


-    ዋስ ሆነዋል ሊያውቋቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉ፣

-    የአንድን ዋስ ኃላፊነት ቀሪ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎች ምን ምን ናቸው?

-    የዋስትና አይነቶችና ልዩነታቸው፣

-    የዋስነቱ ገንዘብ የከፈለ ሰው ገንዘቡን ለማስመለስ ያሉት አማራጮች፣

-    በሥራ ዋስትና ግዴታ ላይ እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት የደረሰ ክርክርና የተሰጠ ውሳኔ


እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? የዛሬ ወጋችን ስለ ዋስነት ነው። ለሥራ ቅጥር ወይም ለሌላ የወል ግዴታ ዋስ በምንሆንበት ጊዜ የሚኖሩብን ግዴታዎች ምንድን ናቸው? ከዋስነት ጋር በተያያዘ የሚመጡብን ኃላፊነቶችን ሊያስቀሩልን የሚችሉ ሁኔታዎችስ በሕጋችን ላይ ምን ይመስላሉ? የሚሉትን ነጥቦች እናያለን።

መቼም በአንድ አጋጣሚ ለሌሎች ሰዎች የወል ግዴታ መፈፀም ወይም ለሚያደርሱት ኃላፊነት ዋስ መሆን አይቀርም። እኔ ለምሳሌ ሌሎች ሰዎች ሥራ ስቀጠር ዋስ ሆነውኛል እኔም በተለይ ለሌሎች ዋስ ሆኛለሁ። ዋስ ሁነኝ መባባል አንዱ የማህበራዊ ግዴታ መገለጫ ሆኗል። ዋስ አምጣ ስትባሉ ወደሚያውቃችሁ ወደምትቀርቡት ሰው ነው የምትሄዱት አብዛኛውን ጊዜም ዋስ ሁነኝ ብሎ ለሚጠይቅ የቅርብ ሰው አሻፈረኝ ማለቱ ትንሽ ከበድ ስለሚል ብዙ ሰዎች ሕጋዊ ኃላፊነቱን ብዙም ሳያጤኑት በማህበራዊ ግዴታነቱ (በይሉኝታ) ዋስ ይሆናሉ።

በአብዛኛው የታወቁትና የተለመዱት የዋስትና አይነቶች ለስራ ቅጥር፣ ለብድር ውል፣ እና በወንጀል የተጠረጠረና ዋስትና የተፈቀደለት ሰው በቀጠሮው ቀን ፍ/ቤት መቅረቡን ለማረጋገጥ የሚሰጡ ዋስትናዎች ናቸው። የዛሬው ትኩረታችን በሁለት ሰዎች መካከል ለሚደረግ ውል ለሚመነጩ ግዴታዎች የሥራ ውል፣ የብድር ውል ሌሎች አይነት ውሎች ላይ የሚገባ የዋስነት ግዴታን የሚመለከት በመሆኑ አንድ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሰ ክርክርን ተመልክተን እንቀጥል።

ፖስታ ቤት እና ፖስተኛው

ስሙን መጥቀሱ አስፈላጊ ሆኖ ያልታየኝ አንድ ፖስተኛ በኢትዮጵያ ፓስታ አገልግሎት ድርጅት (ኢ.ፓ.አ.ድ) ተቀጥሮ ሲሰራ 54፣150 የሻወቸር ካርድና ብር 6,338 የቴምብር ቀረጥ ገንዘብ በድምሩ ብር 61,088 ያጎድላል። ፖስታ ቤቱ ፖስተኛውን ብቻ በመክሰሱ አልተመለሰም። አቶ ንብረትና አቶ መላኩ ፖስተኛው ሲቀጠር እያንዳንዳቸው የብር 30ሺህ ዋስ ስለሆኑ በ2ኛና በ3ኛ ተከሳሽነት የጎደለውን ገንዘብ ከነወለዱ ሁሉም በጋራ ወይም አንደኛቸው እንዲከፍሉት እንዲወሰንለት በቄለም ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ አቀረበ።

1ኛ ተከሳሽ የሆነው ፖስተኛ ለክሱ በሰጠው መልስ የስራ ድርሻዬ ፖስተኛ ስለሆነ ጎደለ የተባለው ገንዘብ አይመለከተኝም። የተሰራው የሂሳብ ማጣሪያም በሌለሁበት በመሆኑ ልጠየቅ አይገባም አለ። ሁለቱ ዋሶች ደግሞ እኛ ዋስ የሆንነው ፖስተኛው ለ6 ወራት በጊዜያዊነት በፖስተኛነት ለተቀጠረበት ስራ ነው እንጂ ከዚያ በኋላ በፖስተኛውና በፖስታ ቤቱ መካከል በአዲስ መልክ ለታደሰው የቅጥር ውል ባለመሆኑ በኃላፊነት ልንጠየቅ አይገባም ሲሉ ተከራከሩ።

ፍ/ቤቱም የግራቀኙን ክርክር መዝኖ 1ኛ ተከሳሽ የሆነው ፖስተኛ 61,088 ማጉደሉን አረጋግጫለሁ። ስለዚህ ለዳኝነትና ለሌሎች ወጪዎች ብር 1,500 ጨምሮ ይከፈል። ዋሶቹን በተመለከተ ግን ሁለቱ ዋሶች ዋስትና የገቡበት የፖስተኛው ጊዜያዊ የቅጥር ውል ጊዜው አልቆ ውሉ በአዲስ መልክ በሌላ ሥራ መደብ ላይ በ1ኛ ተጠሪና በአመልካች መካከል ሲደረግ የዋስትና ውሉ አብሮ ያልታደሰ በመሆኑ ኃላፊነት የለባቸውም በማለት በነፃ አሰናበታቸው።

ከሳሽ የነበረው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት (ኢ.ፓ.አ.ድ) ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ቢያቀርብም ይግባኙ ተቀባይነት ስላላገኘ ውሳኔው የሕግ ስህተት ተፈፅሞበታል። የዋስትና ውሉ በጊዜ ያልተገደበ እንዲሁም የ1ኛ ተከሳሽ (የፖስተኛው) ጊዜያዊ የስራ ቅጥር ውል መታደስ በራሱ 2ኛና 3ኛ ተከሳሾች የ(ዋሶቹን) በመጀመሪያው ቅጥር የገቡትን የዋስትና ግዴታ ቀሪ ሊያደርገው ስለማይችል የበታች ፍርድ ቤቶች ዋሶቹን ነፃ በማድረጋቸው የሕግ ስህተት ስለፈፀሙ ውሳኔያቸው ተሽሮ ዋሶቹም ከተከሳሹ (ፖስተኛው) ጋር ለእዳው ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረግልኝ ሲል ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረበ። ዋሶቹ በፅሁፍ ለሰበር አቤቱታው መልሳቸውን አቀረቡ። 1ኛው ተከሳሽ የሆነው ፖስተኛው መልስ እንዲሰጥ መጥሪያ ቢደረሰውም ስላልቀረበ መልስ የመስጠት መልሱ ታለፈ።

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ ፖስተኛው በፖስተኝነት በጊዜያዊነት ሲቀጠር ዋስ የሆኑት ሁለቱ ዋሶች ጊዜያዊው የስራ ቅጥር ውል አልቆ የስራ መደቡ ወደ ክለርክነት ሲለወጥ የዋስትና ውሉም አብሮ አለመታደሱ የዋሶቹን ኃላፊነት ቀሪ ያደርጋል ወይስ አያደርግም የሚለውን ነጥብ በመመርመር ውሳኔ ሰጥቷል። ከውሳኔው በፊት እስቲ ዋስትናን የደነገጉ አንቀፆቻችንን እናንሳ።

ዋስትና ምንድን ነው? የውል ወይም የሕግ ግዴታ መኖርን ተከትሎ አንድን ግዴታውን ለመፈፀም ውል የገባው ሰው አነድ ውሉ ሳይፈፀም ቢቀር ከውሉ ግዴታ በማይዘል መጠን ሌላ ሰው ያን ግዴታ በክፍል ወይም በሙሉ ለመፈፀም የሚገባው ሌላ ውል ነው። ዋስትና እንዲኖር ሁለት ውሎች ያስፈልጋ። የመጀመሪያው መሰረታዊውን ግዴታ ተዋዋዩ ላይ የሚፈጥረው ውል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ያን ውል ተዋዋዩ ሳይፈፅም ቢቀር ለመፈፀም ዋሱ የሚገባው ውል ነው።

ከፍ/ብሔር ሕጋችን አንቀፅ 1920 እና 22 እንደምንረዳው ዋስትና የሚፈጠረው በገንዘብ ሊተመን የሚችል የአንድ ግዴታ መኖርን ተከትሎ ነው። በ1921 ላይ ደግሞ ዋስ ለመሆን የዋነኛው ተዋዋይ (ባለዕዳ) ፍቃድ ወይም እውቅና አያስፈልግም፤ ዋናው ባለዕዳ ሳያውቅም ዋሱ ዋስ ሊሆነው ከፈለገ ዋስ መሆን ይችላል።

የዋስትና የውል ባህሪያት፡- የዋስትና ውል በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1725 (ሀ) ላይ በፅሁፍ መደረግ እና ዋሶቹ እና ዋስትና የሚገባበት ዋናው ተዋዋይ (ባለገንዘቡ) መፈረም አለባቸው ሁሉ በ1727 (2) መሠረት ለሁለት ምስክሮች ፊት መደረግ አለበት። ስለዚህ በህሊና ግምት ወይም በቃል በተደረገ ውል ወይም ምስክሮችና ተዋዋዮች ላልፈረሙበት የፅሁፍ ውል ዋስትና ቢደረግም በፍ/ጠ/ሕ/ቁ 1922(1) መሰረት ዋስትናው እንዳለ አይቆጠርም።

በተጨማሪ የዋስትና ውል በግልፅ ለምን አይነት ግዴታ አለመፈፀም እንደተደረገ በውሉ ላይ መጠቀስ አለበት። ከዋናው ግዴታ ላይ ከተጠቀሰው ወሰንም ሊያልፍ አይችልም። በተጨማሪ የዋሱ ግዴታ በዋስትና ውሉ ላይ በገንዘብ መጠን ካልተጠቀሰም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1922(3) የዋስትና ውሉ ፈራሽ ነው።

የዋስትና ውሉ ከዋናው እዳ በላይ ለሆነ ግዴታ ከተገባ የግዴታው መጠን በዋናው እዳ ላይ የሚቀነስ ሲኖር ዋናው ባለዕዳ ላይ የነበረው ግዴታ ቀሪ ከሆነ የዋሱ ግዴታም አብሮ ቀሪ ይሆናል።

ዋስትና ላልተወሰነ ወይም ለተወሰነ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1925 ይህን የሚወስኑት ዋሱና ባለገንዘቡ ናቸው። ዋስነቱ ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ በውሉ ላይ ካልተወሰነ ዋሱ የዋናው እዳ ተጠያቂነት ካልደረሰ ዋስትናውን የማውረድ መብት አለው።

ለምሳሌ አቶ አ ከአቶ በ ከ1 ዓመት በኋላ የሚመለስ ገንዘብ ቢበደር አቶ ተ ደግሞ አቶ አ የተበደረውን ብር ባይመልስ የ10ሺ ብር ዋስ ለመሆን ዋስነቱ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ሳይጠይቅ የዋስትና ውል ቢገባ ከ1 ዓመት ጊዜ እስካልደረሰና አቶ አ ተጠያቂ እስካልሆነ ድረስ ዋሱ አቶ ተ የዋስትና ግዴታውን ለአቶ በ በፅሁፍ ማውረዱን በማሳወቅ ማስቀረት ይችላል።

ዋሱ ዋናው ባለዕዳ በገንዘቡ ላይ የሚያነሳቸውን መከራከሪያዎች አንስቶ መከራከር የሚችል ሲሆን ዋናው ባለዕዳ የፍቃድ ወይም ውል የመግባት ችሎታ ጉድለት እንዳለበት እያወቀ የተዋሰ ሰው ግን የፍቃድ እና የችሎት ጉዳይን አንስቶ መከራከር እንደማይችል በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1926 ላይ ተደንግጓል።

በተጨማሪ በዋናው ባለዕዳ እና በባለገንዘቡ መካከል ከዋስነት ውሉ በኋላ የሚደረግ ሌላ ውል የዋሱን ግዴታ ሊያብስበት የማይችል ሲሆን የእዳ መክፈያ ጊዜውን ዋሱ ሳይፈቅድ ባለገንዘቡ ለባለ እዳው ካራዘመበት ዋሱ ከግዴታው ነፃ እንደሚሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1928 ላይ ተቀምጧል።

ዋሱ ክስ ቀርቦበት የባለዕዳውን ግዴታ ከፈፀመ ባለዕዳውን የከፈለውን ገንዘብ ከነወለዱና ከነወጪው እንዲከፈለው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1930 መሠረት ዋናውን ባለዕዳ ከሶ መጠየቅ ይችላል። በሌላ በኩል ዋሱ ግደታውን ከተወጣ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1934 መሠረት በባለ ገንዘቡ መብቶች ተተክቶ የባለዕዳውን ንብረቶች መሸጥ ወይም በባለገንዘቡ በውሉ ከባለዕዳው በሚያገኛቸው ጥቅሞች ከፍሎበታልና ተተክቶ የመጠየቅ መብት አለው።

የዋስትና አይነቶች፡- በፍ/ብ/ሕጋችን የሚታወቁ 3 አይነት የዋስትና ግዴታዎች አሉ።

 1.      የአንድነትና የነጠላ ዋስትና፡- በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1933 መሠረት ከባለዕዳው ጋር በአንድነት ለመገደድ የጋራ ባለዕዳ የሆነ ወይም በሌላ ማናቸውም ተመሳሳይ ስም ለባለእዳው እኩል ለመገደድ የተስማማ ዋስን የሚመለከት ሲሆን ባለገንዘቡ ለዋናው ባለዕዳው ሳያስታውቅ ዋሶቹን ብቻ መጠየቅ ወይም አንድ ላይ ከባለዕዳው ጋር መጠየቅ ይችላል።
 2.      ተራ ዋስትና፡- ይህ የዋስትና አይነት ዋሱ ዋናው ባለዕዳ ግዴታውን መፈፀም የማይችል መሆኑን ሳያረጋግ ባለገንዘቡ ዋሱን ማስገደድ የማይችልበት የዋስትና አይነት ሲሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1934(2) መሠረት ተራ ዋስትና የገባ ሰው ባለገንዘቡን በቅድሚያ በዋናው ባለዕዳ ሀብቶች ላይ እንዲከራር እዳውን ሀብቱን አሽጦ እንዲያስከፍል መጠየቅና የባዕዳውን ንብረቶች መጠቆም ይችላል። የባለዕዳው እዳውን መክፈል አለመቻሉ በፍ/ቤት ቢረጋገጥ ግን ዋናውን ባለዕዳ በቅድሚ አስከፍል ብሎ መጠየቅ አይችልም።
 3.      የጠለፋ ዋስ፡-ይህ ደግሞ ለአንድ ግዴታ ዋስ ለሆነ ሰው እንደዋስትናው ግዴታውን መፈፀሙን ለማረጋገጥ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1949 መሰረት የሚሰጥ ተጨማሪ ዋስትና ሲሆን ዋናው ዋስ የዋስትና ግዴታውን መወጣት አለመቻሉ ልክ እንደ ተራ ዋስትና አካሄድ ከተረጋገጠ በኋላ የጠለፋ ዋሱ የዋናው ዋስ ግዴታ ለመፈፀም የሚገደድበት የዋስትና አይነት ነው።

ሰበር ምን ወሰነ?

በፍ/ብ/ሕጋችን ሶስትና የሚመለከቱ መሠረታዊ ድንጋጌዎችን ቃኘት አድርገን ተመልክተናል። የፖስታ ቤቱና የፖስተኛው ዋሶች ሙግት እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መድረሱ አይተን ውሳኔው ብቻ ነበር የቀረን። የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቀ 86813 መስከረም 22 ቀን 2006 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን በሰበር ውሳኔዎች ቅፅ 15 ላይ ውሳኔው ታትሞ ወጥቷል።

ለዚህ ውሳኔ መነሻ የሆነው የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1827(1) ድንጋጌ ነው። ፖስተኛው የጊዜያዊ የፖስተኝት የስራ ውሉ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ አብቅቶ ወደ ክለርክነት የሥራ መደብ የመጀመሪያው ውል ተለውጧል ይሄ በስር ፍ/ቤቶች ተረጋግጧል። ሕጉ ደግሞ “አንድ ውል በሌላ ውል ሲተካ ከመጀመሪያው ግዴታ ጋር የሚገኙት ዋስትናዎች፣ ቅድሚያዎች፣ መያዣዎች እንዳሉ እንዲቀጥሉ በግልፅ የተጠበቀ ካልሆነ በቀር ምትክ ወደሚሆነው የገንዘብ መብት አይተላለፍም ይላል። በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1927(1) ላይ ይህ ማለት ዋሶቹ ተጠያቂ እንደሆኑ ፖስተኛው ጊዜያዊ የቅጥር ውሉ ተጠናቆ በክለርክነት የቅጥር ውል ሲተካ በአዲሱ ውል ላይም ቀርበው ዋስ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነበረባቸው። ሆኖም ይህ ባለመደረጉ ዋስ የሆኑበት የጊዜያዊ ፖስተኝነት የስራ ውል አብቅቶ በአዲስ የሥራ ውል ስለተተካ ለአዲስ የክለርክነት የሥራ ውል ላይ ፖስተኛ የነበረው ተከሳሽ ለሚያደርሰው ኃላፊነት ግዴታ የለባቸው። ስለዚህ በቄለም ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና በክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሁለቱ ዋሶች ነፃ እንዲሆኑ የተሰጠውን ፍርድ የሕግ ስህተት አልተፈፀመበትም ብሎ ሰበር አፅንቶታል።

     ለማንኛውም በተለይ ዋስ ስንሆን ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች ማስተዋሉ ሊያስከትልብን የሚችለውን ኃላፊነት አውቀነው እንድንገባበት ኃላፊነቱ ሲመጣም በቂ መከላከያ እንድናቀርብ ይረዳናልና ቅድሚያ ህጎቹን ልብ እንበል።

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
8990 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 935 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us