የሕክምና ሙያዊ ጥናት በሕጋችን

Wednesday, 01 October 2014 14:48

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. '; document.write(''); document.write(addy_text98411); document.write('<\/a>'); //-->\n This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    በህክምና ላይ በሚፈፀም ቸልተኝነት ወይም የሙያ ስህተት ታካሚው ላይ ለሚደርስ ጉዳት የመካስ ኃላፊነቱ የማን ነው?

-    የህክምና ባለሙያውና የጤና ተቋሙ ላደረሱት ጉዳት ያለባቸው ተጠያቂነት

-    የህክምና ሙያው ጥራት መኖሩ እንዴት ይወሰናል?

-    በፍ/ቤቶቻችን ቀርበው የተወሰኑ ሁለት የህክምና ሙያዊ ጥፋት የጉዳት ካሳ ክሶች

እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? የዛሬ ወጋችን ዋናውን ነገር ጤናን የሚመለከት ነው። ዋናው ነገር ጤና' ነውና ጤናችን ሲታወክ ወደ ህክምና እንደሄዳለን። ፍላጎታችን ህክምና ባለሙያዎቹ ባላቸው እውቀት አክመው እንዲያድኑን ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን በጤና ባለሙያው ቸልተኝነት ወይም ስህተት ለመዳን የሄደ ሰው ይብሱኑ ታሞ ወይም ለሌላ ጉዳት ተጋልጦ ይመለሳል። ለመሆኑ በሕክምና ባለሙያው ስህተት ወይም ቸልተኝነት ታካሚው ላይ የሚደርስ ጉዳት በህጎቻችን እንዴት ይታያል? የህክምና ባለሙያው እና የጤና ተቋማቱ ኃላፊነት እስከምን ድረስ ነው የሚለውን ወሳኝ ነጥቦች እንመለከታለን። ዋነኛ ማጣቀሻችን ሀብታሙ ስማቸው በሕግ የማስተርስ ዲግሪ ማሟያ በመስከረም ወር 2004 ዓ.ም የስራው ያልታተመ የጥናት ፅሁፍ በመሆኑ አቶ ሀብታሙ ስማቸውን አመስግነን እንቀጥል።

ሕክምና ጥፋትና ቸልተኝነት

ሕክምና የሚካሄደው ለአዎንታዊ ውጤቶች ቢሆንም ታካሚው ከሕክምናው በኋላ ይጠበቅ ከነበረው የጤና ሁኔታው የባሰበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል። በሌላ አነጋገር ታካሚውን ለማዳን የታሰበው ህክምና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው በህመሙ ላይ ሌላ ችግር ሊያስከትሉበት ይችላል።

በህክምና ጥፋት ወይም ቸልተኝነት ታካሚው ላይ የደረሰ ጉዳትን ለመካስ የተለያዩ ሀገራት ሁለት አይነት የተለመዱ መለኪያዎችን ይጠቀሳሉ። የመጀመሪያው የጥፋተኝነት' መለኪያ ሲሆን የተጎዳውን ህመምተኛ ለመካስ የሀኪሙ ወይም የጤና ተቋሙ ህክምናውን ሲሰጥ የፈፀመው ጥፋት መኖር አለበት የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ያለ ጭነትም ቢሆን በህክምናው ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ታካሚ ሀኪሙ ወይም የጤና ተቋሙ ጥፋት መፈፀሙን ማሳየት ሳይጠበቅበት ተመጣጣኝ ካሳ ማግኘት ይገባዋል የሚል ነው።

ቸልተኝነትና ጥፋት በአጠቃላይ ከውል ውጭ የሚፈጠሩ ግንኙነቶችን ተከትለው አንድ ሰው በሌላው ሰው ላይ ወይም በንብረቱ ላይ ጉዳት በማድረስ የሚፈፀመው የሕግ ስህተት ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። ከሕክምና እና ከማስታመም ውል አንፃር ስናየው ሀኪሙም ሆነ የጤና ተቋሙ ተገቢውን እንክብካቤና ሙያዊ ጥረት እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህ የሕክምና ሙያ ጥፋት ወይም ቸልተኝነት ይህን የውል ግዴታቸውን እንደመጣስ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በመሆኑም የህክምና ሙያው ጥፋት እና ቸልተኝነት በውል ግንኙነት ወይም ከውል ውጪ ከሚያደርስ ጉዳት የሚፈጠሩ ኃላፊነቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ የሚወሰነው እንደየሀገሩ የህግ እና የፖሊሲ የህክምና ጥፋት እና ቸልተኝነት ኃላፊነቱን በየትኛው አግባብ ይከሰታል ብሎ እንዳስቀመጠው ነው። በውልም ሆነ ከውል ውጪ በሚደርስ ጉዳት ቸልተኝነት' እና ጥፋት' ልዩነታቸውን እንመልከት።

የህክምና ሙያ ቸልተኝነት፡- ቸልተኝነት ተገቢውን ጥንቃቄ አለማድረግ ሲሆን አንድን ነገር ለማድረግ ከሚያስፈልገው ተገቢውን ጥንቃቄ ያለምክንያት በመተው የሚፈፀም ድርጊት ነው። የድርጊቱ ምክንያታዊነት የሚመዘነው በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የነበረ ሰው ምን ጥንቃቄ ያደርግ ነበር በሚለው መመዘኛ ነው። ከጤና ባለሙያዎችና ተቋማት አንጻር ስናየው ደግሞ ቸልተኝነት ማለት የጤና ባለሙያው ከትምህርቱ ከእውቀቱ እና ከልምዱ ማወቅ የነበረበትን ነገር በመተው የሰራው ጥሩ ያልሆነ ነገር ሲሆን፤ ሆኖም ግን ሀኪሙ ድርጊቱን የፈፀመው ሆን ብሎ ወይም አውቆ ላይሆን ይችላል ማለት አይደለም።

የህክምና ሙያዊ ጥፋት፡- የሙያ ጥራት በባለሙያው በኩል ቸልተኝነት ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል አንድ ባለሙያ ቅድሚያ ሊያሰጣቸው የሚገቡትን ሙያዊ መመዘኛዎች ባለመከተል ወይም እንደባለሙያ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ነገሮች እንዳለው እውቀትና ክህሎት ባለማስተዋል የሚሰራው ሙያዊ ሥራ ነው።

በመሆኑም ሙያዊ ጥፋት ይባል ሙያዊ የህክምና አገልግሎት መለኪያዎችን እና አገልግሎቱን የሚሰጠውን ሰው የሙያ ደረጃ የሚመለከት ነው። በመሆኑም ድርጊቱ በባለሙያው ወይም ያለባለሙያው ሊፈፀም የሚችል ቢሆንም የህክምና ባለሙያው በሙያ ጥፋት ወይም በቸልተኝነት ድርጊቱን ሲፈፅም ባለሙያው ያልሆነው ሰው ደግሞ ጥፋት ሊፈፅም የሚችለው በቸልተኝነት ብቻ ነው።

የህክምና ሙያዊ ጥፋት በኢትዮጵያ ሕግ

የህክምና ሙያዊ ጥፋት በአጠቃላይ ፍትሃ ብሔራዊ ጉዳይ ነው። በህክምና ሙያዊ ጥፋት ተጠያቂነት በውል ወይም ከውል ውጭ ከሚፈጠር ግንኙነት ሊነሳ ይችላል። የኮመን ሎው ስርዓት የሚከተሉ ሀገራት ጉዳዩ ከውል ውጭ በሚደርስ ኃላፊነት በሚመለከቱ ሕጎች ውስጥ የሚወድቅ ነው።

በኢትዮጵያችን የህክምና ሙያዊ ጥፋት ክስ ከውል ወይም ከውል ውጭ ከሚደርስ ኃላፊነት ሊመነጭ ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ህመምተኛው ከጤና ተቋሙ ጋር ውል ይገባል። ከታካሚውም ከጤና ተቋሙም የሚጠበቀው ተቋሙ የህክምና አገልግሎቱን ለመስጠት መፍቀዱ እና ታካሚው ደግሞ ህክምናውን ለማድረግ መስማማቱ ነው። የጤና ተቋማቱ ለታካሚው ያለባቸው ግዴታ የሚመነጨውም በዋነኝነት ከገቡት የህክምና መስጠት ውል ነው።

ህመምተኛው ህክምናውን ሲወስድ ጉዳት ከደረሰበት የጤና ተቋሙ የገባውን የውል ግዴታ በመጣስ ለፈፀመው ስህተት ክስ ሊያቀርብ ይችላል። በህክምና ውል ውስጥ የውል ግዴታን መጣስ ምን ማለት ነው የሚለው ጥያቄ እዚህ ጋር ይነሳል። በ1960 በወጣው የፍትሃብሔር ሕጋችን የህክምና የማከም ውል በአገልግሎት ውል ውስጥ ተካቷል። በዚህ አይነት ውሎች ውስጥ አንድ የተለየ ውጤትና እንደሚገኝ ማስተማመን ከባድ በመሆኑ በምትኩ ተዋዋዩ በገባው ግዴታ መሰረት ተገቢውን ጥንቃቄና የሙያ ብቃት አገልግሎቱን መስጠት ይጠበቅበታል።

በሌላ በኩል የህክምና ሙያዊ ጥፋት ክስ በጤና ተቋማት ላይ ከውል ውጭ በሚደርስ የጉዳት ካሳም ሊጠየቅ ይችላል ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ የታካሚውና የጤና ተቋሙ ግንኙነት በውል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ከውል ውጭ በሚደርስ ኃላፊነት የሚነሳው ጥያቄ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ነው።

በአጠቃላይ በሀገራችን የህክምና ሙያዊ ጥፋት የሚዳኘው ጥፋቱን የፈፀመውን በመለየት ነው። ሆኖም ለከሳሹም ሆነ ለፍ/ቤቶች ጉዳቱ በማን ጥፋት እንደተከሰተ መለየቱ ቀላል አይደለም። የህክምና ሙያዊ ጥፋት የካሳ ጥያቄም ከተራ የጉዳት ካሳ ጥያቄዎች ብዙም ልዩነት ስለሌለው ዳኛውን ወይም ከሳሹን ምክንያታዊ የሆነ የህክምና ስራ ተሰርቷል ወይ የሚለውን በቅጡ የሚያውቁትን መመዘኛ እንዲጠቀሙ ያስገድዳቸዋል። በተጨማሪ ከፍ/ቤቱም ሆነ ከከሳሹ ይልቅ በጤና ተቋሙ የተሰጠው አንድ የህክምና አገልግሎት ተገቢውን ደረጃ የጠበቀ ነው ወይ የሚለውን መለየት የሚችለው የህክምና ባለሙያው ነው። በመሆኑም የአንድ የህክምና አገልግሎት በቂና ደረጃውን የጠበቀ ነው የሚለው የሕግ እውቀት ባለመሆኑ በተገቢው የሙያ መስክ የባለሙያ ምስክርነት ማስፈለጉ እሙን ነው።

በሀገራችን የባለሙያ ምስክሮች አብዛኛውን ጊዜ ለተከሳሹ ስለሚያደሉ በከሳሽ ወገን ለሚመሰከር ዳኝነት ይታይባቸዋል። ሆኖም በመንግስት የተቋቋሙ ሌሎች የህክምና አሰጣጥ ደረጃን የሚመዝኑና ሙያዊ ጥፋት መኖር አለመኖሩን የሚመሰክሩ ተቋማት አሉ። የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ም/ቤት በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁ 76/1994 የተቋቋመ ሲሆን ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። የሙያዊ ስነምግባር ንኡስ ኮሚቴው የተሰጠው ህክምና ደረጃውን የጠበቀ ነው ወይ የሚለውን ታካሚው አቤቱታ ሲያቀርብ መዝኖ አስያየት ይሰጣል። እስቲ በጥናታዊ ፅሁፍ ላይ የተጠቀሱ ሁለት ክሶችን እናንሳ፡-

ሰናይትና ሜሪስቶፕስ

ሰናይት የወሊድ መቆጣጠሪያ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሜሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ክሊኒክ በማምራት ተገቢው ምርመራ ተደርጎላት ኖርፕላንት የተባለው መከላከያ ክንዷ ውስጥ ይቀበርብላታል። ሆኖም መከላከያው የተቀበረው ቦታ ላይ ህመም ስለፈጠረባት የሜሪስቶፕስ የጤና ባለሙያዎች የወሊድ መከላከያው እንዲወጣላት ይወስናሉ። ሆኖም ኖርፕላንቱ ከወጣላትም በኋላ ህመሙ በመባባሱ የጀርባ ህመምና ጡቷ አካባቢ እብጠት አስከተለ። በመሆኑም ሰናይት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤቶች ህመሙ የተከሰተው የጤና ባለሙያዎቹ ኖርፕላንቱን ሲያወጡ በሰሩት የህክምና ስህተት በመሆኑ የሜሪስቶፕስ ክሊኒክ ካሳ ብር 694,918 (ስድስት መቶ ዘጠና አራት ሺ ዘጠኝ መቶ አስራ ስምንት ብር) ለተጨማሪ ህክምና በማውጣቷ እንዲከፍላት ከሰሰች። ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን አከራክሮ በገቡት የህክምና ውል መሰረት የተከሳሽ (የሜሪስቶፕስ) ሰራተኛ በስራው የህክምና ጥፋት ከሳሿ ላይ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ ነው ስለዚህ በርትዕ (በህሊና ሚዛን) ለጉዳቱ ተመጣጣኝ ነው ያለውን ብር 300ሺህ እንዲከፍላት ወሰነ። የካሳው መጠን አንሷል ስትል ይግባኝ አቅርባ ይገባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ተጨማሪ ብር 394ሺህ918 ብር ይገባታል በማለት የሰር ፍ/ቤትን የካሳ መጠን ውሳኔ ሽሮ በጠየቀችው መሰረት ብር 694ሺህ 918 እንዲከፈላት ወሰነ። ተከሳሽ እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ቢሄድም ውሳኔው ፀናበት።

አብርሃምና አራቱ ዶክተሮች ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር

ከሳሽ አብርሃም በተሽከርካሪ አደጋ የተሰበረውን ግራ እግሩን ለመታከም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ይገባል። የሚያሳዝነው ዶ/ር ቃኘው፣ ዶ/ር ኤልያስ፣ ዶ/ር ሙሉጌታ፣ ዶ/ር ዘላለም የተባሉት አራት ሀኪሞች የግራውን ሳይሆን የቀኝ እግሩን ቀዶ ጥገና ያደርጉለታል።

አብርሃም 65 በመቶ ቋሚ የአካል ጉዳት አላግባብ ቀዶ ጥገና በተደረገለበት የቀኝ እግሩ ምክንያት ስለደረሰበት ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሃምሳ ሺህ ሰባት መቶ ሀምሳ ሁለት ብር ካሳ እንዲከፍሉት አራቱ ዶክተሮችና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ከሰሰ።

አራቱ ዶክተሮች በሰጡት መልስ የከሳሽ ቀኝ እግርን ቀዶ ጥገና ማድረጋቸውን አምነው የቲቢ ህመም ምልክት በምርመራ ስላገኘን ቀዶ ጥገናውን ያደረግነው በቀና ልቦና ለተከሳሹ ስንል ነው ሲሉ ተከራከሩ። ተከሳሽ ግን የተሰበረው ግራ እግሬ ነው፣ ቀኙ ጤነኛና ደህና ነው ብሏል። 5 ተከሳሹ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሰራተኞቼ በሰሩት የግል ጥፋታቸው ልጠየቅ አይገባም፣ ሰራተኛው የግል ጥፋት የመንግስት ተቋማት እንደማይጠየቅ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2126(3) ደንግጓል ሲል ተከራከረ።

ክሱ የቀረበለት የፌ/ከ/ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርር መርምሮ አራቱ ዶክተሮችና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ከሳሽ ላይ ለደረሰው ጉዳት በአንድነትና በነጠላ የመካስ ኃላፊነት አለባቸው ሲል ወስኗል።

     የአቶ ሀብታሙ ስማቸው የጥናት ፅሁፍ ከላይ ያነሳናቸውን ብቻ ሳይሆን በርካታ ነጥቦችን አንስቷል። የፅሁፍ ዋነኛ ነጥብም ራሳቸውን ችለው የጤና ተቋሙ ተቀጣሪ ሳይሆኑ የህክምና ሙያዊ ጥፋት ጉዳት የሚያደርሱ የጤና ባለሙያዎች በተመለከተ በሀገራችን ሕግ የጤና ተቋሙ ያለውን ተጠያቂነት የሚመለከት ሲሆን፤ አሁን ያሉት ሕጎች በውልም ሆነ ከውል ውጭ በሚደርስ ጉዳት የጤና ተቋማቱን ከኃላፊነት ሊያስመልጥ የሚችል ክፍተት ስላለበት ሕግ አውጭው የጤና ተቋማቱን ኃላፊነት የሚያሳትፍ ሕግ ማውጣቱ እንዳለበትና በህክምና ሙያ ጥፋት የሚደርስ ኃላፊነት እንደሌሎች የጉዳት ኃላፊነቶች ሳይሆን በተፈጥሮው መሰብሰብ በመሆኑ ራሱን የቻለ ሕግ ሊወጣለት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
8034 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1003 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us