የመቃብር ቤቱ ክርክር

Thursday, 16 October 2014 14:26

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.    

-    ሃይማኖት በመቀየራቸው በሰሩት የመቃብር ቤት እንዳይቀበሩ የተከራከሩት ግለሰብ ያቀረቡት ክስ

-    በጉዳዩ ላይ የተሰጠ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም፣

-    ሃይማኖት የቀየረ ሰው በቀድሞ ሃይማኖቱ ያገኛቸውን መብቶች በሙሉ ያጣል?

-    ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ሥራዎች በዓለማዊው ሕግ ሊዳኙ ይችላሉ?  

እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? የዛሬው ወጋችን ከሃይማኖትና ከእምነት ነፃነት ጋር በተያያዘ አንድ አማኝ ከሚከተለው እምነት የሚያገኘውን መንፈሳዊ አገልግሎት አንዱ የሆነውን የመቃብር ሥፍራን ግለሰቡ እምነቱን ሲቀይር መጠቀም ካለመቻሉ ጋር የተነሳና እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ የሕግ ትርጉም የተሰጠበትን ጉዳይ ይመለከታል። የአማኙንና የእምነት ተቋሙን መብትና ግዴታዎች በዓለማዊ ሕጎቻችን ይታያሉ የሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

  1. የክርክሩ መነሻ

ሐረር

ወ/ሮ ማንያህልሻል አበራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ ነበሩ። በሐረር ከተማ በሚገኘው የደብረሳህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን በሳቸውና በቤተሰቦቻቸው የመቃብር ቤት ለማሰራት እንዲፈቀድላቸው ቤተክርስቲያኒቱን ጠይቀው ተፈቅዶላቸው የመቃብር ቤት ያሰራሉ። በዚህ የመቃብር ቤት ቤተዘመዶቻቸው ሲሞቱ ሲቀበሩበት ይቆያሉ። ወ/ሮ ማንያህልሻል ከደ/ሳ/ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን አንድ ደብዳቤ ደረሳቸው። ደብዳቤው “ሃይማኖትሽን የቀየርሽ በመሆኑ ስትሞቺ በመቃብር ቤቱ መጠቀም አትችይም” የሚል ነበር።

ግለሰቧ ሃይማኖቴን አልቀየርኩም የሚለውን ክርክር ከማንሳት ይልቅ ወደ ሐረር ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሄድ ቤተክርስቲን ላይ ክስ መሰረቱ። ክሱ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ እያለሁ በቤተክርስቲያኑ የሰራሁትን የመቃብር ቤት ያለምንም ካሳና ግምት ለመልቀቅ የውል ግዴታ ባለመግባቴ ለመቃብር ቤቱ ያወጣሁትን ሁለት መቶ ሺ ብር ቤተክርስቲያኑ ይክፈለኝ የሚል ነበር። ክስ የቀረበበት የደ/ሳ/ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን ለክሱ በሰጠው መልስ ወ/ሮ ማንያህልሻል ባሰሩት መቃብር የዘመዶቻቸው ስርዓተ ቀብር ተፈፅሞ አፅማቸው አርፎበታል። እሳቸው ግን ሃይማኖታቸውን በመቀየራቸው በመቃብር ቤቱ የመጠቀም መብት የላቸውም። ቤተክርስቲያኗ የመቃብር ቤት ግምት ለመክፈል የገባቸው ውል የለም። ጥያቄው የእምነቱን መሠረታዊ ቀኖናና አሰራር የሚፃረር ነው። የመቃብር ቤቱ ግምትም ከብር 13ሺ አይበልጥም የሚል መልስ በመስጠት ተከራከረ።

ክሱ የቀረበለት የሐረር ክልል ከፍተኛ ፍ/ቤት የመቃብር ቤቱ ዋጋ በባለሙያ ተገምቶ እንዲቀርብ በማድረግ ተከሳሽ ቤተክርስቲያኑ በግምቱ መሰረት ብር 50,153.40 (ሃምሳ ሺህ አንድ መቶ ሃምሳ ሶስት ብር ከአርባ ሳንቲም) ለከሳሽ ለወ/ሮ ማንያህልሻል እንዲከፈል ወሰነ።

ቤተክርስቲያኗ በውሳኔው ቅር በመሰኘት ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ቢያቀርብም ፍ/ቤቱ ይግባኟን ውድቅ አደረገ። ቤ/ክርስቲኗ በውሳኔው ቅር በመሰኘት የሕግ ስህተት ተፈፅሟል። ፍ/ቤቱ ቦታው የመቃብር ቦታና ከእምነቱ ጋር የተያያዘ መሆኑን ሳያገናዝብ ለጉዳዩ አግባብነት የሌለውን የፍ/ብ/ሕ/ቁ1179 በመጥቀስ ለመቃብር ቤቱ ግምት ለከሳሿ እንዲከፈል የሰው ውሳኔ የሕግ ስህተት ስላለበት ይታረምልኝ ሲል ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር አቤቱታ አቀረበ።

ከሳሽ ወ/ሮ ማንያህልሻል በሰበር አቤቱታቸው ላይ በስነስርዓት ሕጉ መሠረት የቀረበ አይደለም የሚል መከራከሪያ ቢያነሱም ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሕግ መሰረት ያለው ሆኖ ስላላገኘው መቃወሚያውን ውድቅ በማድረግ ዋነኛው ጭብጥ ወ/ሮ ማንያህልሸል በመቃብር ቤቱ ግምት እንዲከፈላቸው መወሰኑ አግባብ ነው፣ አይደለም የሚለውን ጭብጥ መርምሮ መጋቢት 13 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰ/ወ/ቁ 85979 ውሳኔ ሰጥቷል። የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ትንታኔ የሰጠባቸውን ነጥቦች እንመልስ፡-

2. የሃይማኖት ነፃነት

ማንኛውም ሰው የማሰብ የሕሊና የሃይማኖት ነፃነት ያለው መሆኑንና ይህም መብት የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ የመቀበል ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል የመተግበር የማስተማር ወይም የመግለፅ መብትን እንደሚያካትት በሕገመንግስታችን አንቀፅ 27(1) ላይ ተደንግጓል።

በተጨማሪም ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን እምነት መያዝ የነበረውን እምነት ለመቀየር ያለውን ነፃነት በሃይል ወይም በሌላ ሁኔታ በማስገደድም መገደብ ወይም መከልከል የማይቻል መሆኑ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 27(3) ላይ የእምነትና የሃይማኖት ነፃነት ማናቸውም ሰው በሚያምንበት እምነትና በሚከተለው ሃይማኖት ቀኖና ስርዓት መሰረት በዚህ ዓለም በሚኖርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ መንፈሳዊ ፀጋ አግኝቼባቸዋለሁ የሚላቸውን የበጎ አድራጎት ተግባራቶችንና ሌሎች ስራዎችን የማከናወን ነፃነትን ጭምር የሚመለከት ነው።

3. የወ/ሮ ማንያህልሻል ሃይማኖት መቀየርና ባስገነቡት መቃብር ቤት የመጠቀም መብት

በግራ ቀኙ ክርክር እንደተረጋገጠው ወ/ሮ ማንያህሉሽ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ በነበሩበት ወቅት በደ/ሳ/ቅ/ሚካኤል ግቢ ውስጥ የመቃብር ቤት እንድትገነባ ልዩ ፈቃድ ተሰጧቸው በግል ወጪያቸው የመቃብር ቤቱን ያስገነቡት ሃይማኖቱ ቀኖናና ስርዓት በማመንና ተገዥ በመሆን ነበር። ግለሰቧ ይከተሉት የነበረውን ሃይማኖት የመለወጥና የመረጡትን ሃይማኖት የመከተል የማምለክ የመተግበር ሕገ መንግስታዊ መብታቸው በአንቀፅ 27(1) በአንቀፅ 13 (2) እና ሀገራችን ፈርማ ያፀደቀቻቸው በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሁለንተናዊ መግለጫ (Universal declaration of human rights) በአንቀፅ 18 እና በዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት አንቀፅ 18(1) ድንጋጌዎች የተረጋገጠላቸው ሲሆን ቤ/ክርስቲያንም ይህን መብታቸውን የሚገድብ ደብዳቤ ያልፃፈና ሌሎች የከሳሽ (የወ/ሮ ማንያህሉሽን) መብቶች የሚገድቡ ተግባራትን አልፈፀመም።

ግለሰቧም ሃይማኖቴን አልቀየርኩም የሚል ክርክር አላቀረቡም። በመሆኑም ቤ/ክርስቲያኗ የሚያራምደውን እምነትና አስተምሮት በመተው የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ከሆኑ የእምነቱ ተከታይ በመሆናቸው ተሰጥቷቸው የነበረው ክብር መብትና ጥቅም በነበረው ሁኔታ እንዲቀጥል መጠየቅ አይችሉም። ወ/ሮ ማንያህሉሻል የሌላ እምነትና ሃይማኖት ተከታይ መሆን ሲጀምሩ ከቤተክርስቲያኑ ጋር የነበራቸው ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ትሰስርና ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል። ከሳሿ በቤ/ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ የመቃብር ቤት እንድትስራ የተፈቀደላት የነበራትን የሃይማኖትና የእምነት ትስስር መሰረት በማድረግ ነው እንጂ በከሳሿና በቤ/ክርስቲያኑ መካከል በገንዘብ የሚተመን የኢኮኖሚያዊ ውልና ስምምነት መሰረት በማድረግ አይደለም። ስለዚህ በመቃብር ቤቱ ላይ የተሰጣት ልዩ ፈቃድ ከእምነቱ ተለይቶ የሚፈፀምና የሚተገበር ተራ የውል ወይም የንብረት ግንኙነት ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም።

በመሆኑም ወ/ሮ ማንያህልሻል የእምነቱ ተከታይ ናቸው በሚል የተሰጣቸውን ልዩ ፈቃድ በመጠቀም በሰሩት መቃብር ቤት ላይ ያላቸው መብትና ጥቅም ግለሰቧ ሃይማታቸውን ከለወጡና የሌላ እምነት ተከታይ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል። ከዚህ አንጻር ሲመዘን ቤ/ክርስቲያኑ ግለሰቧን ስትከተለው የነበረውን ሃይማኖት በመለወጥ የሌላ ሃይማኖት ተከታይ በመሆንሽ በቤ/ክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ በሰራሽው የመቃብር ቤት የመጠቀምና ስትሞቺም በመቃብር ቤቱ የመቀበር መብት የለሽም በማለት ለወ/ሮ ማንያህልሻል የፃፈው ደብዳቤ በሕገመንግስቱን አንቀፅ 11፣27(1-3) መሠረት ያደረገና ተገቢነት ያለው ነው።

4. ሃይማኖቱን የለወጠ ሰው ሃይማኖቱን ሲከተል ለሰራቸው ተግባሮች 

ግምት እንዲከፈለው መጠየቅ ይችላል?

የሃይማኖትና የእምነት ነፃነትና የሃይማኖትና እምነትን የመለወጥ መብት አንድ ሰው በፊት ይከተለው የነበረውን ሃይማኖትና እምነት መሰረት በማድረግ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ግዴታውን ለመወጣትና መንፈሳዊ ፀጋና ቡራኬ ለመጎናፀፍ በማሰብ የሰጣቸው ስጦታዎች ወይም ወጪያቸውን ለመሸፈን የሰራቸው የሃይማኖትና የእምነት ማምለኪያው ሃይማኖታዊ ትምህርት ማስተማሪያ ቤቶች ወይም በእምነቱ መሰረት የቀብር ስርዓት መፈፀሚያ እንዲሆን በማሰብ የሰራው ቤት እንዲመለስለት ወይም እንዲፈርስ ወይም ግምታቸው እንዲከፈላቸው የመጠየቅ መብትን የሚያስከትል አይደለም። በመሆኑም ወ/ሮ ማንያልሻል የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በነበሩበት ወቅት ለራሳቸውና ለዘመዶቻቸው ስርዓተ ቀብር ማስፈፀሚያ ይሆናል በሚል እምነት ያሰሩትን የመቃብር ቤት ግምት ቤ/ክርስቲያኑ እንዲከፈላቸው ለመጠየቅ የሚያስችላቸው ሕጋዊ መሠረት የለም።

ቤተክርስቲያኑም ለግለሰቧ የእምነት ተከታይ በነበሩበት ጊዜ ከሀይማኖቱን መሰረታዊ ቀኖና ስርዓት ለስርዓተ ቀብራቸው ማስፈፀሚያ ለሰሩት የመቃብር ቤት ሃይማኖት በመቀየራቸው መቀበር እንደማይችሉ ለመከልከሉ የመቃብር ቤቱን ዋጋና ግምት የመክፈል ኃላፊነት የለባቸውም።

የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1179 በግለሰቦች መካከል በሰብዓዊ ሕግጋት መሠረት በሚደረግ ስምምነት ባለመሬቱ ሳይቃወመው ሕንፃ የሰራ ሰው ባለመሬቱ ህንጻውን ሲያስለቅቀው የሕንጻውን ግምት እንዲከፈለው የሚደነግግ ነው። ከሃይማኖትና ከእምነት ነፃነትና መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ከመሆናቸው የመንግስት (አስፈፃሚው ሕግ አውጪው ሕግ ተርጓሚው) በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 11 (3) ከተቀመጠው ድንጋጌ አንጻር የተጠቀሰው የፍ/ብ/ሕግ በአንድ ሃይማኖታዊ ተቋም ቅጥር ግቢ ለተገነባ የመቃብር ቤት ተጠቃሽም ተፈፃሚም የሚሆን አይደለም።

      ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች ላይ ትንታኔ ከሰጠ በኋላ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሐረር ክልል ከ/ፍ/ቤት ጠ/ፍ/ቤት የሰጡትን ውሳኔ በመሻር የደ/ሳ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን ለወ/ሮ ማንያህልሻል የመቃብር ቤቱን ግምት የመክፈል ኃላፊነት እንደሌለበት ወስኗል። ይህ አስገዳጅ የህግ ትርጉም የተሰጠበት ውሳኔ በፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር ችሎት ውሳኔዎች ቅፅ 15 ላይ ታትሞ ወጥቷል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
8804 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 769 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us