የመጨረሻው ፍትሕ

Wednesday, 22 October 2014 12:22

አጭር ልበወለድ ደራሲ ሊዎ ቶልስቶይ

ትርጉም ኪዳኔ መካሻ

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    ከስመጥሩ ሩሲያዊ ፀሐፊ ሊዎ ቶልስቶይ በ1880 ዓ.ም የፃፈው (God Sees the Truth, but waits) የሚለው አጭር ልብወለዱ ከታዋቂ ድርሰቶቹ አንዱ ነው። ቶልስቶይ በዚህ ዘመን አይሽሬ ስራው የፍትህን ምንነት በሀሰት መወንጀልና ንጹህነትን ማስረዳት አለመቻልምን አይነት መራር ስሜትንና ጉዳት እንዳለው ያሳየናል። ከዘመናት በኋላ እውነተኛው አጥፊ ሰገለጥ ያለጥፋቱ የተወነጀለ ሰውስ በምን ሊካስ ይችላል የሚለውን ጥያቄም ያነሳል። እነሆ ወደ ታሪኩ፡-

በቭላድሚር ከተማ ኢቫን ዲሚትሪች አክሲኖፍ የተባለ ወጣት ነጋዴ ነበር። ሁለት ሱቆችና የራሱ ቤት አለው። አክሲኖፍ መልከመልካም፣ ፀጉረ ዞማ፣ ጨዋታ አዋቂና መዝፈን የሚወድ ሰው ነበር። ካገባ በኋላ ግን አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር መጠጣት አቆመ።

በአንድ የክረምት ወቅት አክሲኖፍ ወደ ኒዘኒ ገበያ ለመሄድ ተነሳ። ቤተሰቡን ሲሰናበት ሚስቱ “ኢቫን ዲሚትሪች ዛሬ አትሂድ መጥፎ ህልም አይቻለሁ” አለችው።

አክሲኖፍ ሳቀና “ገበያ ስደርስ ወደመሸታ ቤት እንዳልሄድ ነው የፈራሽው” አላት።

ሚስቱ “ምን እንዳስፈራኝ አለውቅም፤ እኔ የማውቀው መጥፎ ህልም ማየቴን ነው። በህልሜ ከከተማ ተመልሰህ ባርኔጣህን ስታወልቅ ፀጉርህ ገብስማ ሆኖ አይቻለሁ” አለችው።

አክሲኖፍ ሳቀ “ይህማ ጥሩ ምልኢ ነው” አላት። “እቃዬን ሁሉ ሸጬ ጨርሼ ጥሩ ስጦታ ይዜልሽ ካልመጣሁ ምን አለ በይኝ” ከዛም ቤተሰቡን ተሰናብቶ ጉዞውን በሰረገላው ጀመረ።

ግማሽ መንገድ ያህል እንደተጓዘ የሚያውቀው ነጋዴ አገኘና ምሽቱን በአንድ መሸታ ቤት አረፉ። ሻይ አብረው ጠጥተው ጎን ለጎን ወደያዙት መኝታ ቤት ገቡ።

አክሲኖፍ አርፍዶ መነሳት ልማዱ ስላልሆነና በቅዝቃዜው ለመጓዝ ከመንጋቱ በፊት ነጂውን ቀሰቀሰና ፈረሶቹን ለጉዞ እንዲያዘጋጅ ነገረው።

ወደ ማረፊያ ቤቱ ባለቤት (ከጀርባ ባለው ጎጆ ይኖራል) ሄዶ ሂሳብ ከፈለና መንገዱን ቀጠለ።

ሃያ አምስት ማይሎች ያህል ተጉዞ ፈረሶቹን ለማብላት ቆመ። መንገድ ላይ ካለ ቡና ቤት አረፍ አለና በረንዳው ላይ ሆኖ የሻይ ማፍያ ምድጃው እንዲለኮስ አዘዘና ጊታሩን አውጥቶ መጫወት ጀመረ።

ድንገት የፈረስ የቃጭል ድምፅ ተከትሎ አንድ የፖሊስ ሹም ሁለት ወታደሮችን አስከትሎ ብቅ አለ። ወደአክሲኖፍ ቀረበ፤ ማንነቱንና መቼ እንደመጣ ጠየቀው። አክሲኖፍ ጥያቄውን በሙሉ መለሰና “አባክህ ሻይ አብረን እንጠጣ” አለው።

የፖሊስ ሹሙ ግን የአውጫጭኝ ጥያቄውን ቀጠለ “ባለፈው ምሽት የት ነው ያደርከው? ብቻህን ነበርክ ወይስ ከሌላ ነጋዴ ጋር? ነጋዴውን ዛሬ ማለዳ አይተኸዋል? ለምን ያረፍክበትን ቤት ከመንጋቱ በፊት ለቀቅክ?

አክሲኖፍ ለምን ይህን ሁሉ ጥያቄ እንደሚጠየቅ ቢገርመውም የሆነውን ሁሉ አብራርቶ ገለፀለትና “እኔ ሌባ ወይ ዘራፊ የሆንኩ ይመስል ለምን ለምን በመስቀለኛ ጥያቄ ታጣድፈኛለህ? እኔ ለንግድ ስራዬ የምጓዝ ሰው ስለሆንኩ እኔን መጠየቁ አስፈላጊ አይደለም።

የፖሊስ ሹሙ ወታደሮቹን ጠራና “እኔ የዚህ አውራጃ የፖሊስ ኃላፊ ነኝ፤ የምጠይቅህም ባለፈው ምሽት አብረኸው የነበርከው ነጋዴ ታርዶ ስለተገኘ ነው። አንተ ላይ ፍተሻ ማድረግ አለብን።

ወደ ቤት ገቡ። ፖሊሱና ወታደሮቹ የአክሲኖፍን ሻንጣዎች ከፍተው ፈተሸ። ድንገት ፖሊሱ ጩቤ ከቦርሳው አወጣና “ይሄ የማን ጩቤ ነው?” ሲል ጮኸ።

አክሲኖፍ በደም የተለወሰ ጩቤ ከቦርሳው ሲወጣ በአይኑ በብረቱ ስላየ ፍርሃት ያዘው።

“እንዴት ጩቤው ላይ ደም ሊገኝ ቻለ?” አክሲኖፍ ለመመለስ ቢሞክርም ቃላት ማውጣት ተሳነው።

“እኔ. . . እኔ አላውቅም . . . የኔ አይደለም” ሲል ተንተባተበ።

የፖሊስ ኃላፊው “ዛሬ ጠዋት ነጋዴው አልጋው ላይ ጉሮሮው ታርዶ ተገኝቷል። ይህን ማድረግ የምትችለው አንተ ብቻ ነህ። ቤቱ ከውስጥ ተቆልፎ ስለነበር ሌላ ማንም ሰው አልነበረም። ይኸም በደም የተለወሰ ጩቤም ቦርሳህ ውስጥ ተገኘብህ። ፊትህና አካኋንህም ያሳብቅብሃል። እንዴት እንደገደልከውና ምን ያህል ገንዘብ እንደወሰድክ ንገረኝ?

አክሲኖፍ ድርጊቱን አለመፈፀሙንና ነጋዴውን ሻይ ከጠጡ በኋላ እንዳላየው ከራሱ ስምንት ሺህ ሩብል በቀር ሌላ ገንዘብ እንደሌለው ጩቤውም፤ የሱ እንዳልሆነ በመሃላ ተናገረ። ሆኖም በተሰበረ ድምፅ ፊቱ ገርጥቶ ወንጀለኛ ይመስል እየተንቀጠቀጠ ነበር የሚናገረው።

የፖሊስ ኃላፊው ወታደሮቹን አክሲኖፍን እንዲያስሩትና ሰረገላው ላይ እንዲጭኑት አዘዘ። እግሮቹን በአንድ አስረው ጋሪው ላይ ሲወረውሩት አክሲኖፍ አማተበና አለቀሰ። ገንዘቡና ንብረቱን ወስደው በአቅራቢያው ባለ ከተማ ወስደው አሰሩት። ስለባህሪው ምርመራ የተካሄደው በቮላድሜር ከተማ ነበር። ነጋዴዎችና ሌሎች የከተማው ነዋሪዎች በድሮ ጊዜ ይጠጣና ጊዜውን በከንቱ ያባክን የነበረ ቢሆንም ጥሩ ሰው መሆኑን ተናገሩ። የፍርድ ሂደቱ ቀጠለና ከራይዘን የመጣውን ነጋዴ በመግደል እና ሃያ ሺህ ሩብል በመዝረፍ ተከሰሰ።

ሚስቱ ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ስለወደቀች የትኛውን ማመን እንዳለባት አላወቀችም። ልጆችም ገና ትንንሾች ናቸው። አንደኛው ገና ጡት ያልጣለ ጨቅላ ነው። ሁሉንም ይዛ ባሏ ወደተያዘበት ከተማ አመራች። መጀመሪያ ላይ እንድታየው እንኳን አልተፈቀደላትም ነበር። ከብዙ ልመና በኋላ የፖሊስ ኃላፊዎቹ ፈቀዱላትና ወደ እሱ ወሰዷት። ባሏን የእስረኛ ልብስ ለብሶና ሰንሰለት አጥልቆ ከሌቦችና ከወንጀለኞች ጋር ተዘግቶበት ስታየው ራሷን ስታ ወደቀችና ለረጅም ጊዜ ሳትነቃ ቆየች። ከዚያም ልጆችዋ ወደሷ ሰብስባ ከአጠገቡ ተቀመጠች። እቤት ውስጥ ስላለመችው ነገር ነገረችውና ምን እንዳጋጠመው ጠየቀቸው። ሁሉንም ነገር ነገራትና “ታዲያ ምን ይሻላል?” ስትል ጠየቀችው።

“ለንጉሱ ንጹህ ሰው እንዳይጎዱ አቤት ማለት አለብን”ሲላት ሚስቱ ለንጉሱ (ለዛሩ)አቤቱታ ማቅረቧንና እንዳልተቀበሏት ነገረችው። አክሲኖፍ መልስ ሳይሰጣት አንገቱን አቀረቀረ።

ያለነገር አልነበረም ፀጉርህ በከፊል ሸበቶ በህልሜ ያየሁት። ታስታውሳለህ? በዚያን ቀን መንገድ መጀመር አልነበረብህም”። በእጆቿ ፀጉሮቹን እየዳበሰች “የኔ ውድ ሻንያ ለሚስትህ እውነቱን ንገራት አንተ አይደለህም ያደረከው? ስትል ጠየቀችው።

“አንቺም ጠረጠርሽኝ” አለና አክሲኖፍ ፊቱን በእጆቹ ሸፍኖ ማንባት ጀመረ። ይሄኔ ወታደሩ ሚስቱና ልጆቹ ከዚያ እንዲሄዱ ለመናገር መጡ። አክሲኖፍም ቤተሰቡን ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናበተ።

እነሱ ከሄዱ በኋላ አክሲኖፍ ያለችውን ሲያስታውስ ሚስቱም እንደጠረጠረችው ታወሰውና “እውነቱን የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ይመስላል ለሱ ብቻ ነው ይግባኝ መጠየቅ ያለብኝ። ከእሱ በስተቀር ምህረት የሚሰጥ የለም” አለ ለራሱ።

እናም አክሲኖፍ ከዚያ በኋላ ይግባኝ መፃፉን ትቶ ተስፋ ቆረጠና ለእግዚያብሔር ብቻ ፀለየ።

አክሲኖፍ በግርፋት ተቀጥቶ ወደ ማእድን ማውጫ እንዲላክ ተፈረደበት። ጫፉ በተቋጠረ ጅራፍ ከተገረፈ በኋላ ቁስሉ ሲጠግግ ከሌሎች ወንጀለኞች ጋር ወደሳይቤሪያ ተጓዘ።

ለሃያ ስድስት ዓመታትም አስኬኖፍ በሳይቤሪያ በረሃ በእስር ቅጣት ቆየ። ፀጉሩ እንደበረዶ ነጣ፤ ግራጫማ ጢሙ በቀጭኑ ተንዠረገገ። ሳቁ ሁሉ ጠፋ። ይቆማል፣ በዝግታ ይራመዳል፣ የሚናገረው ጥቂት ነው። አብዝቶ ከመፀለይ በቀር ለአፍታ እንኳን ስቆ አያውቅም።

በእስር ቤት አክሲኖፍ ቦት ጫማ መስራት ስለተማረ ጥቂት ገንዘብ አገኘ። ባገኘው ገንዘብም የቅዱሳን ህይወት የሚል መፅሐፍ ገዛ። በእስር ቤቱ በቂ ብርሃን ካለ ይህን መፅሐፍ ያነባል። በሰንበት በወህኒ ቤቱ ቤተክርስቲያን ወንጌል ያነባል። ድምፁ መልካም ስለነበር የህብረ ዝማሬ አካል ሆኖ ይዘምራል።

የእስር ቤቱ ኃላፊዎች አክሲኖፍን በለሰለሰ ጸባዩ ወደዱት። የወህኒ ባልደረቦቹም አከበሩት። “አያታችን” እና “ቅዱሱ” እያሉ ይጠሩታል። ለወህኒ ባለስልጣናቱ አቤቱታ ማቅረብ ሲፈልጉ አክሲኖፍን እንዲናገርላቸው ያደርጉታል። በእስረኞቹ መሀል ፀብ ከተነሳም ወደእሱ በመምጣት ትክክለኛውን ነገር እንዲያስቀምጥላቸውና እንዲዳኛቸው ያደርጋሉ።

አክሲኖፍ ከቤቱ የሚመጣለት ወሬ ስላልነበር ሚስቱና ልጆቹ በህይወት እንዳሉ እንኳን አያውቅም ነበር። አንድ ቀን አዲስ እስር የተፈረደባቸው ወንበዴዎች ወደ ወህኒው መጡ። ማታ ላይ የከረሙት እስረኞች በአዲሶቹ ዙሪያ ተሰብስበው ከየት ከተማ ወይም መንደር እንደመጡና በምን ጥፋት እንደተቀጡ ይጠየቋቸው ጀመር። እንደሌሎቹ ሁሉ አክሲኖፍም ከአዲሶቹ እስረኞች አጠገብ ተቀምጦ የሚያወሩትን አንገቱን ደፍቶ ያዳምጣል።

ከአዲሶቹ እስረኞች አንዱ እረጅም ደልደላ ሰውነት ያለውና ችምችም ብሎ የበቀለ ግራጫማ ጢም ያለው ሲሆን ለሌሎቹ ለምን እንደታሰረ እየነገራቸው ነበር። “ወዳጆቼ እንግዲህ” አላቸውና “እኔ የወሰድኩት ለግጦሽ የታሰረ ፈረስ ነው፤ በስርቆት ተከስሼ ያሳሰረኝ። ካደረሰኝ በኋላም ለቅቄዋለሁ አልኳቸው። በዚያ ላይ ደግሞ የፈረሱ ነጂ የቅርብ ጓደኛዬ ነበር። ስለዚህ ችግር የለውም” አልኳቸው። እነሱ ግን አይሆንም አሉና “ሰርቀኸዋል” አሉኝ። ሆኖም የትና እንዴት እንደሰረኩት መናገር አልቻሉም። በአንድ ወቅት እውነተኛ ጥፋት አጥፍቼ ነበር። ከረጅም ጊዜ በፊት ያኔ ነበር ወዲህ መምጣት የነበረብኝ፤ ያን ጊዜ ግን አልተደረሰብኝም ነበር። አሁን ግን ወዲህ ያመጡኝ ዝም ብለው ነው. . . ኧረ ግን ዋሽቼያችኋለሁ። ከዚህ በፊትም ሳይቤሪያ ነበርኩ። ግን ብዙም አልቆየሁም።

“ከየት ነው የመጣኸው?” አንደኛው ነበር የጠየቀው። “ከቭላድሚር ቤተሰቦቼ እዚያ ከተማ ውስጥ ናቸው። ስሜ ማካር ይባላል ሴሚኒዮችም ብለው ይጠሩኛል።

አክሲኖፍ ካቀረቀረበት ቀና አለና “ሴሚኒዮች እስቲ ንገረኝ ስለቭላድሚሩ ነጋዴ አክሲኖፍ ቤተሰብ የምታውቀው ነገር አለ አሁንም በህይወት አሉ? ሲል ጠየቀው።

ታውቃቸዋለህ? አሳምሬ ነዋ። የአክሲኖፍ ቤተሰብ ሀብታም ቢሆኑም አባታቸው ሳይቤሪያ ነው። አንደኛው ሃጥያተኛ ይመስላል። አንተስ አያታችን እንዴት ወዲህ መጣህ?

አክሲኖፍ ክፉ አጋጣሚውን መናገር አይወድም “አዬየየ” አለና “እኔማ ለሀጥያቴ ከታሰርኩኝ ሃያ ስድስት አመት ሆነኝ” ሲል መለሰለት።

“ምን አጥፍተህ ነው?” ማክር ሴሚዮኒች ጠየቀ

አክሲኖፍ ግን የመለሰለት “ደህና ደህና እኔ የሚገባኝ ቢሆን ነው የታሰርኩት” የሚል ብቻ ነበር። ሌላ ተጨማሪ ነገር አልተናገረም ነበር። ሆኖም ጓደኛው ለአዲስ መጪው አክሲኖፍ እንዴት ወደሳይቤሪያ እንዳመጣ ነገረው። እንዴት አንድ ሰው ነጋዴውን እንደገደለና የገደለበትን ጩቤ አክሲኖፍ እቃ ውስጥ እንዳስቀመጠበትና አክሲኖፍ በስህተት እንደተፈረደበት ነገረው።

ማካር ሲሞኒች ይህን ሲሰማ ወደ አክሲኖፍ ተመለሰና ጉልበቱን በእጆቹ እየተመተመ “በጣም የሚደንቅ ነው! እውነት እጅግ ያስገርማል! እንደው አያታችን ግን በጣም አረጀህብኝ” ሲል በአግራሞት ተናገረ።

ሌሎቹ ምን እንዳስደነቀውና አክሲኖፍን ከዚህ ቀደም የት እንደሚያውቀው ጠየቁት። ሆኖም ማካር ሲሞኒች መልስ አልሰጣቸውም። እዚህ መገናኘታችን በጣም አስገራሚ ነው ወንድሞቼ የሚል መልስ ብቻ ነበር የሰጠው። የተናገራቸው ቃላቶች አክሲኖፍን ይሄ ሰው ገዳዩን ያውቀው ይሆን የሚል ጥያቄ ስለጫረበት “ሲሞኒች ምናልባት ስለጉዳዩ ሰምተህ ይሆን ወይም እኔን ከዚህ በፊት ታውቀኝ ነበር?” ሲል ጠየቀው።

እንዴት ላልሰማ እችላለሁ። አለም እንዲሁ የተሞላችሁ በወሬ ነው። ሆኖም ጊዜው እሩቅ ነውና የሰማሁትንም ዘንግቼዋለሁ። “ምናልባት ነጋዴውን ማን እንደገደለውስ ሰምተህ ይሆን?” አክሲኖፍ ጠየቀ።

ማካር ሲሞኒች ሳቀና “ጩቤው ቦርሳው ውስጥ የተገኘበት ሰው መሆን አለበት! ጩቤውን የደበቀው የሆነ ሰው ከሆነም “እስካልተያዘ ድረስ ሌላ አይደለም” እንደሚባለው ነው። እንዴት ተንተርሰኸው ተኝተህ ሌላ ሰው ጩቤውን ቦርሳህ ውስጥ ሊያስቀምጥ ይችላል። በርግጥም ይህን ሲያደርግ ከእንቅልፍህ መባነን ነበረብህ?

አክሲኖፍ ይህን ንግግሩን ሲሰማ ነጋዴውን የገደለው ሰው እሱ መሆኑ ተሰማው። ከተቀመጠበት ተነስቶ ሄዶ ያን ሌሊት ሙሉ እንቅልፍ ባይኑ አልዞረም። እጅግ የመከፋት ስሜት ተሰማው። ሁሉም አይነት ምስሎች በአእምሮው ተመላለሱ። የሚስቱ ምስል ወደ ገበያ ተለይቷት ሲሄድ የነበረችበት ሁኔታ ታየው። ልክ አብራው እንዳለች ፊቱንና አይኖችዋን አቅንታ ከፊት ለፊቱ ታየችው። ፊቷንና ንግግሯም ተሰማው። ልጆቹም በዛ በነበሩበት ሁኔታ ትንንሾች ሆነው ታዩት። አንዱ ትንሽ ከፍ ያለ ሌላኛው የናቱን ጡት የሚጠባ ነበር። ከዛም ራሱምድር እንደነበረው ወጣትና ደስተኛ ሆኖ እየመጣ የመጠጥ ቤቱ በረንዳ ላይ ቁጭ ብሎ ጊታሩን እየተጫወተ እያለ ሲያስሩት ምን ያህል ነፃነት ይሰማው እንደነበር ታወሰው። የታጎረበት ቦታ ገራፊው ዙሪያውን ከበው የነበሩት ሰዎች፣ ሰንሰለቶቹ የወንጀል እስረኞቹ የሃያ ስድስት ዓመት የእስር ህይወቱ፤ ያለእድሜው ማርጀቱ በአይነ ህሊናው ታየው። ይህን ወደ እኔ ማሰቡ መከራውን ስለበዛበት እራሱን ለመግደል ተዘጋጅቶ ነበር።

“ይሄ ሁሉ የዛ የክፉ ሰው ስራ ነው!” ሲል አስቦ አክሲኖፍ ቁጣው ከመጠን ስላለፈ ማካር ሲሞኒችን እራሱንም ቢሆን ጎድቶ ቢበቀለው ናፈቀ። ሌሊቱን ሙሉ ፀሎቱን ቢደግምም ሰላሙን ሊያገኝ አልቻለም። ቀን ላይም ወደ ማካር ሲሞኒች አቅራቢያ አልሄደም፤ ቀና ብሎ እንኳን አላየውም።

በዚህ ሁኔታ አስራ አምስት ቀናት አለፈ። አክሲኖፍ ማታ መተኛት አልቻለም ምን ማድረግ እንዳለበት ባለማወቁም ሲሰቃይ ከረመ።

አንድ ምሽት ወደ እስር ክፍሉ ሲያመራ የሆነ እስረኞች ከሚተኙበት ጥላ ስር አፈር እንደተቆፈረ ተመለከተ። ምንነቱን ለማየት ቆም አለ። ድንገት ማካር ሲሞኖች ከአጥሩ ግድግዳው ስር ተንፏቆ ብቅ አለና አክሲኖፍን ሲያልፍ በአይኑ ተመለከተው። አክሲኖፍ ወደሱ ሳይመለከት ሊያልፍ ቢሞክርም ማካር ግን እጁን በመያዝ በግርግዳው ስር ሲቆፍር እንደነበርና አፈሩን በቦት ጫማው እያደረገ በየቀኑ እስረኞች ወደስራ ሲሰማሩ መንገድ ላይ በመበተን ያስወግደው እንደነበር ነገረው።

ሽሜው ያየኸውን ለማንም ትንፍሽ እንዳትል ከኔ ጋር አብረህ ታመልጣህ። ከነገርካቸው ግን ነፍሴ እስክትወጣ ይገርፉኛል። ከዛ ቀድሜ ግን እኔ እገልሃለሁ” አለው።

አክሲኖፍ ጠላቱን ፊት ለፊት እያየ በቁጣ ነደደ። እጁን አሽቀንጥሮ ገፈተረውና “እኔ ለማምለጥ አልሻም፤ አንተም እኔን መግደል አያስፈልግህም። ገና ድሮ አስቀድመህ ገድለኸኛል። አንተ ያደረከውን ለመናገር ግን ላረገውም ላላረገውም እችላለሁ። እግዚያብሔር እንዳዘዘኝ ነው የማደርገው” አለው።

በነጋታው እስረኞቹ ወደ ስራ ሲጓዙ አጃቢ ወታደሮቹ አንደኛቸው በቦት ጫማው አፈር ሲያጓጉዙ እንደነበር አወቁ። እስር ቤቱ ተፈተሸና የተቆፈረው ጉድጓድ ተገኘ። የወህኒው አዛዥ መጥቶ ሁሉንም እስረኞች ጉድጓዱን ማን እንደቆፈረው ጠየቀ። ሁሉም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ካዱ። የሚያውቁት እስኪሞት ድረስ እንደሚገርፉት ስላወቁ ማካር ሲሞኒችን አሳልፈው መስጠት አልፈለጉም። በመጨረሻም አዛዡ ሀቀኛ ሰው መሆኑን ወደሚያው ወደ አክሲኖፍ በመዞር “አንተ እውነተኛ ሽማግሌ ነህ በእግዚአብሔር ስም እውነቱን ንገረኝ ጉድጓዱን የቆፈረው ማን ነው?” ሲል ጠየቀው

ማካር ሲሞኒች ነገሩ የማይመለከተው መስሎ እንደቆመ አዛዡን ብቻ እንጂ አክሲኖፍን በሙሉ አይኑ አይመለከትም ነበር። የአክሲኖፍ ከንፈሮቹና እጆቹ ተንቀጠቀጡ። ለረጅም ጊዜ ቃላት ካንደበቱ ማውጣትም ተሳነው። ለምንድን ነው ህይወቴን ያበላሸውን ሰው የማልጠቁምበት። እኔ ለተሰቃየሁት ስቃይ በዚህ ዋጋውን ያግኝ” ማን ደግሞ ብናገርበት በግርፋት ነፍሱን ከስጋው መንጥቀው ያወጧታል። በዛ ላይ የጠረጠርኩትም ተሳስቼ ሊሆን ይችላል። ደግሞስ የእሱ መጎዳት እኔ ምን ጥቅም አለው?

“ደህና ሽማግሌው” አለና የወህኒ አዛዡ “እውነቱን ንገረን ማነው ከአጥሩ ግድግዳ ስር ጉድጓዱን የቆፈረው?

አክሲኖፍና ማካር ሲሞኒችን ለአፍታ ተመለከተና “ጌታዬ እኔ እከሌ ነው ማለት አልችልም። እንድናገር እግዚያብሔር አልፈቀደውም። እንደፈለጋችሁ ማድረግ ትችላላችሁ በእጃችሁ ውስጥ ነኝ” ሲል መለሰ።

የወህኒ አስተዳዳሪው የተቻለውን ያህል ቢጥርም አክሲኖፍ ተጨማሪ ነገር ሊናገር ስላልቻለ ነገሩን ሳይጋለጥ በዛው ተተው።

የዛን ለሊት ምሽት አክሲኖፍ አልጋው ላይ ተንጋሎ ሽልብታ እንደጀመረው አንድ ሰው ኮቴውን ሳያሰማ መጥቶ ካጠገቡ ተቀመጠ። በጭለማው ውስጥ እንደምንም አጮልቆ ሰውየው ማካር መሆኑን አየ።

“ደሞ ከኔ ምን ቀረህና መጣህ?” አክሲኖፍ እኮ ለምን መጣህ? አለው። ማካር ሲሞኒች ዝም እንዳለ ነው። አክሲኖፍ ብድግ ብሎ አልጋው ላይ ተቀመጠና “ምን ፈልገህ ነው? ሂድልኝ አሊያ ጥበቃዎቹን እጠራለሁ” አለው።

ማካር ሲሞኒኝ እንዳለ ነው። አክሲኖፍ ላይ ተጎንብሶ ኢሻን ዲሚትሪች ይቅር በለኝ” አለው።

“ምን ስላረከኝ?” አክሲኖፍ ጠየቀ።

“ነጋዴውን የገደልኩትና ጩቤውን አንተ እቃ ውስጥ የደበኩት እኔ ነኝ። አንተንም ልገልህ አስቤ ነበር። ሆኖም ከውጭ ድምጽ ስለሰማሁ ጩቤው ቦርሳህ ውስጥ ደብቄው በመስኮት ዘልዬ አመለጥኩ።

አክሲኖፍ ዝም እንዳለ ነበር። ምን መናገር እንዳለበትም አላወቀም።

ማካር ሲሞነኝ ከአልጋው ተንሸራቶ ወረደና ወለሉ ላይ ተንበረከከ “ኢቫን ዲሚትሪች” አለው። ይቅርታ አድርግልኝ፤ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለህ ይቅር በለኝ። ነጋዴውን የገደልኩት እኔ እንደነበርኩ አምኜ ቃሌን እሰጥና አንተ ተለቀህ ወደ ቤትህ ትሄዳለህ።

“ላንተ ለመናገር ሊቀልህ ይችላል” አለው አክሲኖፍ “ለኔ ግን እነኚሀን ሃያ ስድስት ዓመታት በአንተ ፈንታ ተሰቃቼያለሁ። ታዲያ ወዴት ብዬ ነው አሁን የምሄደው?. . . ሚስቴ ሞታለች ልጆቼም ቢሆን እረስተውኛል። የትም መሄጃ ስፍራ የለኝም. . .”

ማካር ሲሞኒች ከተንበረከከበት አልተነሳም ጭራሽ ከጭንቅላቱ ወለሉ ላይ ተደፋ “ኢቫን ዲሚትሪች ይቅር በለኝ “እያለ አለቀሰ”። “ጫፉ በተቋጠረ ጅራፍ ሲገርፈኝ እንኳን አሁን አንተን እንደማየቱ ያህል አላመመኝም. . . አንተ ግን አሁንም አዝነህልኝ የምታውቀውን ጥፋቴን አልተናገርክብኝ። ስለ ክርስቶስ ብለህ ይቅር በለኝ፤ እኔ እርጉም በደለኛ ሰው ነኝ” አለው ሳግ እየተናነቀው።

አክሲኖፍ የሲቃ ድምጹን ሲሰማ አብሮ ማንባት ጀመረ። “እግዚያብሔር ይቅር ይልሃል” አለው። “እኔ ምናልባትም ከአንተ መቶ እጥፍ የባስኩ ልሆን እችላለሁ” አለው ይህን ሲናገር ልቡ በብርሃን ተሞላና። ለቤቱ የነበረው ናፍቆት ለቀቀው። ከእስር ቤቱ ለመውጣትም ቅንጣትም ፍላጎት ስላልነበረው የመጨረሻው ሰዓቱ እስኪደርስ ብቻ ነበር በተስፋ የሚጠብቀው።

     አክሲኖፍ ይህን ከሌላ በኋላ ማካር ሲሞኒች የግድያ ወንጀሉን መፈፀሙን አምኖ ቃሉን ሰጠ። ሆኖም ከእስር የመፈቻ ትዕዛዙ ሲመጣ አክሲኖፍ ነፍሱ ከስጋው ተለይታ ነበር።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
9036 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 819 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us