ሕገ ወጥ የሥራ ስንብት

Wednesday, 29 October 2014 14:26

በኪዳኔ መካሻ

Email This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    በሕገ ወጥ መንገድ ከሥራ ከተባረሩ ወደ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የ3 ወር ጊዜ ሳያልፍዎት ሄደው በነፃ መዝገብ ከፍተው አሰሪዎን መክሰስ ይችላሉ።

-    ፍ/ቤቱ እስከ 6 ወር ከሚደርስ የውዝፍ ደመወዝዎ ጋር ወደ ስራ እንዲመለሱ ሊወስን ይችላል።

-    እርስዎ ወደ ስራ መመለስ ካልፈለጉ እስከ የ180 ቀን ደመወዝ እና ያለ ማስጠንቀቂያ ከተባረሩ እስከ 3 ወር የሚርስ ደመወዝዎን በካሳ መልክ ይከፈልዎታል።

-    ከካሳው በተጨማሪ ከ1 ወር እስከ 12 ወር የሚደርስ ደመወዝና የስንብት ክፍያም ሊያገኙ ይችላሉ።

-    በተጨማሪ አሰሪዎ ከ7 ቀን በላይ ያለ አግባብ ያዘገየብዎ ክፍያ ካለ እስከ 3 ወር የሚደርስ ደመወዝ ሊከፈልዎ ይገባል።

-    ያልወሰዱት የዓመት እረፍት፤ የሳምንት ወይም የህዝብ በዓል እረፍት ስራ፣ ያልተከፈለዎት የትርፍ ሰዓት ክፍያ ወይም ሌላ ክፍያ ካለ ተሰልቶ ይሰጥዎታል።

ሰላም ነው? ለዛሬ ሠራተኞች ከሥራ በሕጋዊ ወይም በሕገወጥ መንገድ የሚሰናበቱባቸውን ምክንያቶች እናነሳለን።

ቅነሳ፡- አሰሪው ሠራተኞችን ማስጠንቀቂያ በመስጠት ከሥራ ማሰናበት የሚችልበት አንደኛው ምክንያት የሠራተኞች ቅነሳ ሲኖር ነው። ሠራተኞችን መቀነስ የሚቻለው በአ/ሰ/ሕ/አ28/(2) መሠረት የሠራተኛውን ስራ በከፊልም ሆነ ለዘለቄታው የሚያስቆም ምክንያት ሲኖር ስራ እና የምርት ወይም የአገልግሎት ተፈላጊነት በመቀነሱ እና በመቀዝቀዙ፤ አዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ወይም የድርጅቱን ምርታማነት ለማሳደግ ሲባል ሠራተኞችን ለመቀነስ ሲወሰን ብቻ ነው። ይህ ምክንያት መኖሩ ብቻ ቅነሳውን ቅነሳ አያሰኘውም ቢያንስ ከቅነሳው ቀን በፊት በነበረው 12 ወራት በድርጅቱ ከሚሰሩት ሠራተኞች 10 በመቶ ወይም የድርጅቱ ሠራተኞች ቁጥር ከሃያ-ሃምሳ ከሆነ ቢያንስ አምስት ሠራተኞችን የሚመለከት ለአስር ተከታታይ ቀናት ላላነሰ ጊዜ የሚቆይ መሆን አለበት። በአ/ሰ/ሕ/አ 29 ስር የተጠቀሰውን ከላይ ያነሳነውን መስፈርት ካሟላ አሰሪው የወሰደው እርምጃ የሠራተኞች ቅነሳ ሊባል ይችላል።

የሠራተኞች ቅነሳ ለማድረግ አሰሪው በሕግ የተቀመጠውን መስፈርት ካሟላ በኋላም ቢሆን በዘፈቀደ የሚያደርገው አይደለም። የሥራ ችሎታ እና ከፍተኛ የምርት ውጤት የሚያስመዘግቡ ሠራተኞች በስራው ላይ የመቆየት የቅድሚያ እድል ይሰጣቸዋል። በስራ ችሎታም በውጤትም ተመሳሳይ የሆኑት ደግሞ በሚከተለው ቅደም ተከተል መሠረት ነው የሚቀነሱት። የመጀመሪያ የቅነሳ ሰለባ የሆኑትን በድርጅቱ ከሌሎች አንፃር ለአጭር ጊዜ ያገለገሉ ሠራተኞች፤ ቅነሳው በነሱ ካላበቃ በመቀጠል አነስተኛ ጥገኞች ያላቸው (ሰርተው ራሳቸውን ማስተዳደር የማይችሉ ልጆች ባል/ሚስት፤ እናት አባት ያሉባቸው)፤ ከዛም በኋላ ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ የማይካተቱ ሌሎች ሠራተኞች እነሱም ተቀንሰው ካልበቃ በደርጅቱ በስራ ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሠራተኞች ፤ የሠራተኞች ተጧሪዎች በመጨረሻ እረድፍ ነፍሰ ጡር ሴቶች የቅነሳው ዙር ሊደርሳቸው ይችላል። በኮንስትራክሽን ስራ ላይ የተሰማሩና የሚሰሩት የግንባታ ስራ በማለቅ ላይ ከሚገኙ አሰሪዎች በስተቀር ሌሎች በአዋጅ ቁ.377/96 ስር የሚታቀፉ አሰሪዎች ሁሉ በአ/ሰ/ሕ/አ 293 ላይ የተቀመጠውን የቅነሳ ቅደም ተከተል ካልጠበቁና የቅነሳ መስፈርቶችን ካላሟሉ በስተቀር ሕጋዊ የሠራተኞች ቅነሳ ማካሄድ አይችሉም። ከሰራተኛው ችሎታ ማጣትና ከቅነሳ ጋር የተያያዙ የሠራተኞች ስንብቶች በአሰሪው ተነሳሽነት የሚወሰድ ሲሆኑ ቅድሚያ ለሰራተኛው ማስጠንቀቂያ መስጠት አሰሪውን ግድ ይለዋል። ስለዚህ እስቲ የማስጠንቀቂያን ምንነት እና የአሰጣጥ ሥነ ስርዓቱን እንመልከት።

ማስጠንቀቂያ ምንድንነው? ማስጠንቀቂያ ማለት አሰሪው በሕግ ያለ ማስጠንቀቂያ ሰራተኛውን ለማባረር ከተፈቀዱለት ምክንያቶች ውጭ ሰራተኛውን ሲያሰናብት ወይም ሰራተኛው በሕግ ያለማስጠንቀቂያ ስራውን መልቀቅ ከተፈቀደለት ምክንያት ሌላ በራሱ ምክንያት ስራውን ሲለቅ፣ ሰራተኛው ስራ ላይ እያለ በሕግ ለተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የስራ ውሉ የሚቋረጥ መሆኑን እና የስራ ውሉ የሚቋረጥበትን ቀን እና ምክንያቱን በመግለፅ በፅሁፍ ስራን የሚያቋርጠው አሰሪው በራሱ ተነሳሽነት ከሆነ ለሰራተኛው ደግሞ ስራውን የሚለቀው ሰራተኛው በራሱ ተነሳሽነት ከሆነ ለአሰሪው የሚያሳውቅበት የስራ ውሉ ከመቋረጡ በፊት ተዋዋይ ወገኖች የስራ ውሉን ለማቋረጥ ያላቸውን ሀሳብ አስቀድመው የሚገልፁበት ሥነ ሥርዓት ነው።

ማስጠንቀቂያ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት፡- በአ/ሰ/ሕ/አ 34 መሰረት የስራ ውል መቋረጡን አስመልክቶ የሚሰጥ ማስጠንቀቂያ በፅሁፍ ሆኖ በተቻለ መጠን ማስጠንቀቂያ ለሚሰጠው ወገን ለራሱ መድረስ አለበት።

በአሰሪው የሚሰጥ ማስጠንቀቂያ፡- አሰሪው በሕግ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ ለሚገደድባቸው የስራ ውል መቋረጫ ምክንያቶች በወኪሉ ወይም በአሰሪው ተፈርሞ ለሰራተኛው ለራሱ መሰጠት አለበት። ሰራተኛው ካልተገኘ ወይም ማስጠንቀቂያውን ለመቀበል እምቢ ካለ ሰራተኛው በሚገኝበት የስራ ቦታ ቢያንስ ለ10 ቀናት ግልፅ በሆነ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ መለጠፍ አለበት። አሰሪው ሰራተኛው ከሥራ ታግዶ ባለበት ጊዜ ማስጠንቀቂያ መስጠት አይችልም። አሰሪው ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ማሟላት ያለበት ዋናው ነገር በሕግ የተቀመጠውን የማስጠንቀቂያ ጊዜ ማሟላቱን ነው። በአ/ሰ/ሕ/አ 35 መሠረት ከሥራ ውል የሚመነጩ የአሰሪና ሰራተኛ ግዴታዎች ማስጠንቀቂያው ለተሰጠበት ጊዜ ፀንተው ይቆያሉ። በመሆኑም ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም የማስጠንቀቂያ ጊዜው እስኪያልቅ አሰሪውም እንደ አሰሪ ሰራተኛውም እንደ ሰራተኛ ይቀጥላሉ። የማስጠንቀቂያ ጊዜው መቆጠር የሚጀምረው ማስጠንቀቂያው ለአሰሪው ወይም ለሰራተኛው ከደረሰው ቀን ቀጥሎ ካለው ቀን ጀምሮ ነው። ስራው በተወሰነ ጊዜ የሚያልቅ ወይም በተለምዶ ጊዜያዊ ስራ የሚባለው ከሆነ አሰሪውና ሰራተኛው በስራ ውላቸው ላይ የማስጠንቀቂያ ጊዜውን በተመለከተ ስምምነት ማድረግ የሚችል ሲሆን ላልተወሰነ ጊዜ ለተደረጉ የስራ ውሎች ግን እንደ ሰራተኛው የአገልግሎት ዘመን እና እንደ ቅነሳው ምክንያት የማስጠንቀቂያ ጊዜው እርዝመት ይለያያል። በዚህም መሠረት አሰሪው፡-

-    የሙከራ ጊዜውን ለጨረሰና እስከ አንድ ዓመት ላገለገለ ሰራተኛ የአንድ ወር ጊዜ፣

-    ከአንድ ዓመት - ዘጠኝ ዓመት ላገለገለ ሰራተኛ የሁለት ወር የማስጠንቀቂያ ጊዜ፣

-    ከዘጠኝ ዓመት በላይ ለሰራ የሦስት ወር የማስጠንቀቂያ ጊዜ፣

-    የሙከራ ጊዜ የጨረሱና በቅነሳ ምክንያት ለሚሰናበቱ ሠራተኞች የሁለት ወር የማስጠንቀቂያ ጊዜ መሰጠት አለበት።

ማለትም የስራ ውሉ ከሚቋረጥበት ቀን በፊት እንደየምክንያቱና እንደ ሰራተኛው የአገልግሎት ጊዜ ከአንድ ወር፣ ከሁለት ወር፣ ከሦስት ወር በፊት አስቀድሞ በፅሁፍ የስራ ውሉን የሚያቋርጥበትን ቀን እና ምክንያቱን በመግለፅ ማሳወቅ አለበት። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሰራተኛው ሌሎች አማራጮችን ለመፈለግ እና የስራ ውሉ ሲቋረጥ በቀጣይነት ምን ማድረግ እንዳበት ለማሰላሰል የስንብቱ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት የተደወለለት የማስጠንቀቂያ ደወል ሊረዳው ይችላል ተብሎ በሕግ አውጭው ተገምቷል። ሆኖም ግን የማስጠንቀቂያው ጊዜ አልቆ የስንብቱ ቀን እስኪመጣ ሰራተኛውም አሰሪውም ያለባቸው ግዴታ እንደነበረ ይቀጥላል።

በሰራተኛው የሚሰጥ ማስጠንቀቂያ፡-ስራ ውል ለማቋረጥ ማስጠንቀቂያ መስጠት የአሰሪው ግዴታ ብቻ አይደለም። ሰራተኛውም ያለ ማስጠንቀቂያ ስራ ከሚለቅባቸው የተወሰኑ ምክንያቶች ውጭ በማንኛውም ምክንያት ስራ መልቀቅ ቢችልም ለአሰሪው ስራ ለመልቀቅ ማሰቡን የሚለቅበትን ምክንያት እና የሚለቅበትን ቀን ማሳወቅ አለበት። ማስጠንቀቂያው” ሰራተኛው በፅሁፍ ለአሰሪው ለራሱ ወይም ለወኪሉ ወይም ለድርጅቱ ጽ/ቤት ገቢ በማድረግ ማሳወቅ ሲኖርበት በሰራተኛ የሚሰጥ ማንኛውም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ከሰላሳ ቀን በፊት መሰጠት አለበት።

ማስጠንቀቂያ አለመስጠት፡- አሰሪውም ሆነ ሰራተኛው ማስጠንቀቂያ መስጠት እያለባቸው ያለ ማስጠንቀቂያ የስራ ውላቸውን ካቋረጡ ሰራተኛው ከሆነ ያለ ማስጠንቀቂያ ስራን የለቀቀው በአ/ሰ/ሕ/አ 45 መሠረት እስከ 30 ቀን የሚደርስ አሰሪው ላይ የሚቀረውን ክፍያ ያሳጣዋል።

ማስጠንቀቂያ መስጠት እያለበት ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ሰራተኛውን ያባረረው አሰሪው ከሆነ ደግሞ አሰሪው በሕግ አግባብ ውጭ የስራ ውሉን እንዳቋረጠ ተቆጥሮ ለሰራተኛው የስራ ስንብት ክፍያ፤ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ እና የካሳ ክፍያ እንዲከፈለው በሕግ ይገደዳል።

በሰራተኛው አነሳሽነት የሚደረግ የስራ ውል መቋረጥ፡- (ስራ መተው ወይም ስራ መልቀቅ)

ልክ እንደ አሰሪው ሰራተኛውም ያለማስጠንቀቂያ ወይም በማስጠንቀቂያ ከአሰሪው ጋር የሚያገናኘውን የእንጀራ ገመዱን መበጠስ ይችላል።

ያለ ማስጠንቀቂያ ሰራተኛው ስራ መልቀቅ የሚችልባቸው ምክንያቶች

ሰራተኛው ስራን መልቀቁን የሚለቅበትን ምክንያት እና የሚለቅበትን ቀን ለአሰሪው በፅሁፍ በማሳወቅ ብቻ ስራ በሕጋዊ መንገድ መልቀቅ የሚችልባቸው ምክንያቶች በአ/ሰ/ሕ/አ 321 ስር ተቀምጠዋል፤ እነሱም፡-

1ኛ/ አሰሪው የሰራተኛውን ሰብአዊ ክብርና ሞራሉን የሚነካ ወይም በወንጀል ሕግ መሰረት የሚያስቀጣ ሌላ አድራጐት የፈፀመበት ከሆነ። መቼም እንጀራ ሆነና ተብሎ ሰራተኛው የሰውነት ክብሩንና ሞራሉ ተጐድቶ እንዲሰራ በሕግም ሆነ በአሰሪው አይገደድም። ወይም ደግሞ የወንጀል ድርጊት በአሰሪው እየተፈፀመበት እያለ እንጀራዬ ነው ብሎ ወይም ቆይ ማስጠንቀቂያ ልስጥ እያለ ለእንጀራው ብሎ መብቶቹን አሳልፎ መስጠት ስለሌለበት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ስራውን መልቀቁን በማሳወቅ ብቻ የመብት ጥሰቱ እንዳይባባስ ማስቆም እና ለተፈፀመበት የወንጀል ድርጊትም ሆነ ሌላ የመብት ጥሰት በሚመለከተው የሕግ አካል አሰሪውን በኃላፊነት መጠየቅ ይችላል።

2ኛ/ አሰሪው ለሰራተኛው ለደህንነቱ ወይም ለጤንነቱ የሚያሰጋ እና ሊደርስ የተቃረበ አደጋ መኖሩን እያወቀ መውሰድ ያለበትን እርምጃ ሰራተኛው ከሰራተኛ ማኅበር ወይም ከሚመለከተው የመንግስት አካል በተሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት በተወሰነው የጊዜ ገደብ አስፈላጊውን እርምጃ ካልወሰደ ሰራተኛው ዓይኑ እያየ ለአደጋ ሲጋለጥና ጉዳት ሲደርስበት እጁን አጣምሮ መጠበቅ ስለሌለበት ያለ ማስጠንቀቂያ ዋናው ነገር ጤና፣ ዋናው እኛ ደህና ብሎ ስራውን መልቀቅ ይችላል።

3ኛ/ አሰሪው በህብረት ስምምነት በስራ ደንብ ወይም አግባብ ባላቸው ሌሎች ሕጐች በተወሰነው መሰረት ግዴታዎቹ በተደጋጋሚ ካልተወጣ ለምሳሌ ደመወዝ አለመክፈል፣ የስራ ሰዓት፣ የዓመት ፍቃድ፣ የሳምንት እረፍት፣ የህመም እና የወሊድ ፈቃድ የመሳሰሉትን ለሰራተኛው ማሟላት ያለበትን መብትና ግዴታዎቹን ካልተወጣ ሰራተኛው ምንም ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ስራውን እንዲለቅ ተፈቅዶለታል።

ሰራተኛው ያለማስጠንቀቂያ ስራ መልቀቅ የሚችልባቸው ምክንያቶች በተከሰቱ ወይም ድርጊቱ በተፈፀመ በ15 ቀናት ጊዜ ውስጥ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤውን ካላስገባ ወይም ስራ ያለማስጠንቀቂያ ለመልቀቅ ምክንያት ሆነኝ የሚለው ድርጊት በተወገደ በ15 ቀናት ጊዜ ውስጥ ስራውን መልቀቁን ካላሳወቀ ምክንያት ነው ባለው ድርጊት ያለ ማስጠንቀቂያ ስራ የመልቀቅ መብቱ በይርጋ ቀሪ ይሆናል። ወይም በሌላ አገላለፅ ሰራተኛው ያለ ማስጠንቀቂያ ስራ የለቀቀበት ድርጊት ከተፈፀመ ወይም ድርጊቱ መፈፀም ካቆመ 15 ቀናት ካለፉት በኋላ በዚያ ድርጊት ሰበብ ያለ ማስጠንቀቂያ ስራ የመልቀቅ መብት የለውም። ስለዚህ ሠራተኞች ስራ ያለማስጠንቀቂያ የሚያስለቅቅ ድርጊት ከተፈፀመባቸው ወይም ድርጊቱ ካቆመ በኋላ ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ብቻ ስራቸውን የመልቀቅ መብት እንዳላቸው ሊዘነጉት አይገባም። አምና ታቻምና ሐምሌ ላይ የሰራኸኝ ስራ ብለው የቆየ ቂም አንስተው ያለ ማስጠንቀቂያ አሰሪውን የኔና ያንተ ነገርማ አበቃለት ካሉ ሕጉ አይፈቅድም።

በማስጠንቀቂያ ስራን መልቀቅ፡- በአ/ሰ/ሕ/አ 31 መሠረት ሰራተኛው የ30 ቀናት ማስጠንቀቂያ አስቀድሞ ለአሰሪው በመስጠት በማናቸውም ምክንያት ስራ መልቀቅ እንደሚችል ይገልፃል። አሰሪው በማስጠንቀቂያም ሆነ ያለማስጠንቀቂያ ሰራተኛውን ማባረር ወይም ማሰናበት የሚችልባቸው በሕግ የተቀመጡት ውስን ምክንያቶች ብቻ ሲሆኑ ሰራተኛው ግን ማስጠንቀቂያ ከሰጠ እና ስራውን መልቀቅ እስከ ፈለገ ድረስ የሚገድበው ነገር የለም። አሰሪው ሰራተኛውን ደበርከኝ ብሎ በማስጠንቀቂያም ሆነ ያለ ማስጠንቀቂያም ሊያባርረው አይችልም። ሰራተኛው ግን መስራት ደበረኝ ስንፍና አማረኝ የእርሶ የዓይን ቀለም ደስ አላለኝም ቢል ይችላል። እሱ በተሰማው ምክንያት ስራውን መልቀቅ መብቱ ነው። የ30 ቀን ማስጠንቀቂያው” በአግባቡ ለአሰሪው እስከሰጠ ድረስ።

በሕገወጥ መንገድ ከሥራ ከተሰናበቱስ?

ላስታውስዎት የስራ ውልዎ የተቋረጠው በሕግ፤ በስምምነት አሰሪው በማስጠንቀቂያ እና ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ ከተፈቀደልዎት ምክንያቶችና ከማስጠንቀቂያ አሰጣጥ ስነ ሥርዓት ውጭ ወይም ከሠራተኞች ቅነሳ አግባብ ውጭ ከሆነ ወይም እርስዎ በራስ ተነሳሽነት የስራ ውልዎን ካላቋረጡ በአ/ሰ/ሕ/አ/ቁ 42 መሠረት ሕገ ወጥ የስራ ስንብት ተፈጽሞቦዎታል ወይም በሕገወጥ መቀስ የእንጀራ ገመድዎ ስለተበጠሰ ለደረሰብዎት ጉዳት ሕግ ካሳ እና ሌሎች መፍትሄዎችን ሰጥቷል። በአ/ሰ/ሕ/አ 43-44 ስር በተዘረዘሩት አንቀፆች መሰረት መብትዎን ለማስከበር የሚሄዱት ወደ ፍ/ቤት ነው። አዲስ አበባ ከሆነ ወደ ፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የስራ ክርክር ችሎት። የሚኖሩበት መስሪያ ቤት አድራሻ በክልል ከሆነ ወደ ክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሄደው ክስ መመስረት ይችላሉ።

የሥራ ውሌ በሕገወጥ መንገድ ተቋርጦብኛል የሚሉ ከሆነ ክስዎን ማቅረብ የሚችሉት ውሉ በተቋረጠ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ነው። ከዚያ ካለፈ ክስ የማቅረብ መብትዎ ይርጋ በሚባለው መብት ማገጃ የጊዜ ገደብ ይቋረጣል። በአ/ሰ/ሕ/አ/ቁ 1622 መሰረት የዳኝነት ክፍያው ቸግርዎት መብትዎን እንዳይተው በአ/ሰ/ሕ/አ/ቁ 1652 መሰረት ፍ/ቤት የሚያቀርቡት የስራ ክርክር ጉዳይ ሁሉ ከክፍያ ነፃ መሆኑ ተደንግጓል።

ፍ/ቤትስ ሄደው ምን ያገኛሉ?

ፍ/ቤት የሚያስተናግድዎት እንደጠየቁት የዳኝነት ዓይነት ሲሆን በሕገወጥ መንገድ ከሥራ ተባርሬያለሁ የሚሉ ከሆነ ወደ ስራ እንዲመለሱ እንዲታዘዝልዎት ወይም ለሕገወጥ የስራ ስንብት ካሳ፤ ማስጠንቀቂያ ካልተሰጥዎት በማስጠንቀቂያ ጊዜ ሊከፈልዎት የሚገባውን ደመወዝ አሰሪዎ ከሰባት ቀን በላይ አለአግባብ ያዘገየብዎት ክፍያ ካሳ እስከ ሦስት ወር የሚደርስ ደመወዝዎን፤ የስራ ውሉ ሲቋረጥ ያልወሰዱት የዓመት ፍቃድ ካለ በገንዘብ ተለውጦ እንዲሰጥዎት፤ ያልወሰዱት የህዝብ በዓላት ወይም የሳምንት እረፍት ካለ እሱም ወደ ክፍያ ተለውጦ እንዲከፈልዎት፤ የትርፍ ሰዓት ክፍያ እና ሌሎችም ያልተከፈሉኝ ክፍያዎች ወይም ጥቅማ ጥቅሞች አሉ የሚሉ ከሆነ ፍ/ቤቱን እንዲያስከፍልዎት ዳኝነት መጠየቅ ይችላሉ።

ወደ ስራ ገበታዎ የመመለስ እድል

የእንጀራ ገመድዎ የተበጠሰው በአሰሪዎ በመባረርዎ ከሆነ እና የተባረሩት በሕግ ሰራተኛ እንዳይባረርባቸው በተከላከሉት የሰራተኛ ማኅበር መሪ ወይም ተጠሪ በመሆንዎ አሰሪው ላይ ወይ ሌላ የፍ/ቤት ክስ ላይ ተካፋይ በመሆንዎ በብሄረሰብም፣ በፆታ፣ ሐይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት፤ የጋብቻ ሁኔታ፣ ዘር፤ ቀለም፤ የቤተሰብ ኃላፊነት የዘር ሐረግ እርግዝና ወይም በማኅበራዊ አቋሞች ምክንያት መሆኑን ፍ/ቤቱ ካረጋገጠ አሰሪዎን ወደ ስራዎ እንዲመልስዎ ያስገድደዋል። እርሶም አልመለስም በቃኝ ካሉ ግን ካሳ እንዲከፈልዎት መጠየቅ መብትዎ ነው። የተባረሩት በሕገወጥ መንገድ ቢሆንም በሌሎች ምክንያቶች ከሆነ ደግሞ እርስዎ ወደ ስራ መመለስ ቢፈልጉም ፍ/ቤቱ ወደ ስራ ቢመለሱ በቀጣይነት ለሚኖረው የስራ ግንኙነት ችግር ይፈጥራል ብሎ ካሰበ በካሳ እንዲሰናበቱ የመወሰን ስልጣን ተሰጥቷል። ወደ ስራ እንዲመለሱ ተወስኖልዎት እርሶ ለመመለስ ፍቃደኛ ካልሆኑ ፍ/ቤቱ ሁኔታዎችን አመዛዝኖ ሙሉ ካሳ ወይም ተገቢ ነው ያለውን ተመጣጣኝ ካሳ ወስኖልዎት ስንብትዎን ሊያፀናው እንደሚችል በአ/ሰ/ሕ/አ/ቁ 43 (ከ1-3) ላይ ደንግጓል።

ወደ ስራዎ እንዲመለሱ በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቱ ተከራክረው ከረቱ እና ከተወሰነልዎት የሚያገኙት ስራዎን ብቻ ሳይሆን እስከ 6 ወር የሚደርስ ውዝፍ ደመወዝ ጋር ነው። አሰሪዎ ወደ ስራ እንዲመለሱ በተሰጠው ውሳኔ ቅር ተሰኝቶ ይግባኝ ካለ እና እርስዎ በይግባኝ ላይም ከረቱ እና ወደ ስራ የመመለስዎ ነገር ከፀና እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ ደመወዝዎ በፍ/ቤት በተቀጠለው የእንጀራ ገመድዎ (ሥራዎ) ላይ እንደሚመረቅልዎ የአ/ሰ/ሕ/አ/ቁ 435 ያበስራል።

ወደ ስራ ገበታዎ ካልተመለሱስ?

በሕገወጥ መንገድ ከሥራ ተባረው ወደ ስራ እንዲመለሱ ካልተወሰነልዎት ደግሞ ያልዎት አማራጭ በሕግ የተቀመጡትን የተለያዩ ዓይነት ክፍያዎች እንዲያገኙ በአማራጭ ይወስንልዎታል። የክፍያዎቹን ዓይነትና መጠናቸውን እስቲ እንመልከት።

1ኛ/ የካሳ ክፍያ፡- በሕገወጥ መንገድ ከሥራ የተሰናበተ ሰራተኛ ወደ ስራው የማይመለስ ከሆነ በአ/ሰ/ሕ/አ/ቁ 434 መሠረት የሰራተኛው የ180 ቀን ደመወዝ ይከፈለዋል። ይህን የካሳ ክፍያ በሁለት መልኩ ከፍሎ ማየት ይቻላል።

2ኛ/ ላልተወሰነ ጊዜ የተቀጠረ ሰራተኛ፡- አማካይ የቀን ደመወዙ በ180 ተባዝቶ ይከፈለዋል። በተጨማሪም ሰራተኛው የተባረረው ማስጠንቀቂያ ሊሰጠው ሲገባ ያለ ማስጠንቀቂያ ከሆነ ወይም ማስጠንቀቂያው በሕጉ አግባብ ካልደረሰው ሊሰጠው ይገባ የነበረውን የማስጠንቀቂያ ጊዜ የሚከፈለው ደመወዝ ይከፈለዋል።

3ኛ/ ለተወሰነ ጊዜ የተቀጠረ ሰራተኛ፡- የሚያገኘው ካሳ የውሉ ጊዜ እስኪያልቅ በስራ ላይ ቢቆይ ኖሮ ሰራተኛው ያገኝ የነበረውን ደመወዝ የሚያህል ክፍያ ነው። ክፍያው ግን የሰራተኛው አማካይ ደመወዝ በ180 ተባዝቶ ከሚገኘው ክፍያ መብለጥ የለበትም።

ምሳሌ እጠቅሳለሁ፡- አቶ ተፈራ እና አቶ በላይ የአንድ የግል ሆቴል ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ አስተናጋጅ እና ካሸር ናቸው። አቶ ተፈራ ለ10 ዓመት በአስተናጋጅነት አገልግለዋል። የቅጥር ውላቸውም ላልተወሰነ ጊዜ ነው። አቶ በላይ ደግሞ ለስልጠና የተላከ ሰራተኛን ለመተካት በካሸርነት ለ1 ዓመት በጊዜያዊነት የተቀጠረ ሰራተኛ ነው። አቶ ተፈራ አሰሪያቸውን የሚገባኝን የዓመት እረፍት ከልክሎኛል ብለው ስራ ላይ እያሉ ከሰሱ። አቶ በላይንም በምስክርነት ቆጠሩት። በዚህ የተበሳጨው የሆቴሉ ባለቤት ሁለቱንም ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ እኔ እያስተዳደርኳችሁማ የአይጥ ምስክር ድንቢጥ እንደሚባለው ከሳሼና ምስክር አትሆኑብኝም ብሎ ያባርራቸዋል። ሁለቱም በሕገወጥ መንገድ ከሥራ ተሰናብተናል ብለው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ክስ አቀረቡ። ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን አከራከረ። ጉዳዩን መርምሮ የአቶ ተፈራ እና የአቶ በላይ የእንጀራ ገመድ የተቋረጠው በሕገወጥ መንገድ ነው በአ/ሰ/ሕ/አ/ቁ 26(2)(ሐ) መሰረት አሰሪው ሰራተኛው ከሳሽ ወይም የፍ/ቤት ምስክር በመሆን ሊያባርረው ስለማይችል በዚህ ምክንያት የተባረረ ሰራተኛን አሰሪው ወደ ስራው የመመለስ ግዴታ ስላለበት ወደ ስራቸው ይመለሱ ሲል ወሰነ። አቶ ተፈራ ደመወዛቸው በወር ብር 1ሺ 500፤ አቶ በላይ ደግሞ 900 ብር ነበር። የፍ/ቤቱ ውሳኔ ቢኖርም አቶ ተፈራ እና አቶ በላይ ሁለት አማራጮች አላቸው። የመጀመሪያው ወደ ስራ መመለስ ከፈቀዱ በአ/ሰ/ሕ/አ/ቁ 435 መሰረት ፍ/ቤቱ ለእያንዳንዳቸው እስከ ስድስት ወር የሚደርስ ደመወዝ ለአቶ ተፈራ እስከ 9,000 ብር ለአቶ በላይ ደግሞ እስከ ብር 5,400 የሚደርስ ደመወዝ ይከፈላቸዋል። አሰሪያቸው ይግባኝ ብሎ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም ወደ ስራ መመለሳቸውን ካፀናው ለአቶ ተፈራ እስከ 10ሺ ብር የዓመት ውዝፍ ደመወዝ ለአቶ በላይ እስከ 10ሺ 800 ብር ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፈላቸውና ስራቸውን እንዲቀጥሉ ያዛል። የምሳሌያችን ግለሰቦች ወደ ስራ መመለስ ካልፈለጉ ደግሞ ካሳ መጠየቅ ስለሚችሉ ለአቶ ተፈራ የአቶ ተፈራ አማካይ የቀን ደመወዝ የሆነው 50C180 9ሺ ብር ካሳ በተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ስላልተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ በአንቀፅ 35(1)(ሐ) ሊሰጣቸው ይገባቸው የነበረው ከዘጠኝ ዓመት በላይ ስለሰሩ የሶስት ወር ጊዜ ስለሆነ የሶስት ወር ደመወዛቸው ብር 4ሺ 500 ይከፈላቸዋል። ለአቶ በላይ ደግሞ የሰራው ሶስት ወር ነው የተቀጠረው ለአንድ ዓመት ጊዜ ስለሆነ ስራ ላይ ቢቆይ የዘጠኝ ወር ደመወዝ ያገኝ ነበር በአ/ሰ/ሕ/አ/ቁ 43(4)(ለ) መሰረት 9C900 8ሺ 100 ብር ነው። ሆኖም ይህ ገንዘብ ከሰራተኛው የ180 ቀን ደመወዝ ወይም ከ6 ወር ደመወዙ መብለጥ ስለሌለበት የሚያገኘው ብር 5ሺ 400 ብቻ ይሆናል።

የስራ ስንብት ክፍያ፡- በአ/ሰ/ሕ/አ 39 መሰረት ሰራተኛው የተሰናበተው ድርጅቱ በመክሰሩ፤ ከሕግ ውጭ የስራ ውሉ በመቋረጡ፤ በሕግ አግባብ ሰራተኛው በመቀነሱ፤ አሰሪው የሰራተኛውን ሰብአዊ ክብርና ሞራሉን በመንካቱ በወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊት ስለፈፀመበት አሰሪው የሰራተኛውን ደህንነት እና ጤንነት የሚያሰጋ አደጋ እያለ አደጋውን እያወቀ መከላከያ እርምጃ ባለመውሰዱ ሰራተኛው የአካል ጉዳት ደርሶበት ስራስራት አለመቻሉ በመረጋገጡ፤ የጡረታ ወይም የፕሮቪደንት ፈንድ የሌለው ሰራተኛ በጡረታ ከሥራ ሲገለል ቢያንስ አምስት ዓመት የሰራ ሰራተኛ በህመም ወይም በሞት የስራ ውሉ ሲቋረጥ ለአሰሪው ይገባ ስልጠና ጋር የተያያዘ የውል ግዴታ ሳይኖርበት በፈቃዱ ስራውን ሲለቅ በኤች አይ ቪ ኤድስ ህመም ምክንያት ሰራተኛው የስራ ውሉን በራሱ ጥያቄ ካቋረጠ የአ/ሰ/ሕግን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁ.494/98 መሰረት የሥራ ስንብት ክፍያ የማግኘት መብት አለው። በነገራችን ላይ ለሕገወጥ የስራ ስንብት ክፍያ ከካሳው በተጨማሪ የሚከፈል ነው። የክፍያውን መጠን በተመለከተ በአ/ሰ/ፈሕ/አ/ቁ 40 ላይ እንደተመለከተው አንድ ዓመት ያገለገለ ሰራተኛ የመጨረሻ ሳምንት የቀን ደመወዙ በ30 ተባዝቶ ይከፈለዋል። ከ1 ዓመት በታች ያገለገለም እንደ አገልግሎት ጊዜው ተመጣጣኝ ክፍያ አለው።

ከአንድ ዓመት በላይ ያገለገለ ሰራተኛ በአንድ ዓመት የአገልግሎት ክፍያው ላይ በየተጨማሪው ዓመት አንድ ሶስተኛው እየታከለ ይከፈለዋል። ሆኖም አጠቃላይ የክፍያው መጠን ከ12 ወር የሰራተኛው ደመወዝ አይበልጥም።

ሰራተኛው የተሰናበተው በቅነሳ ወይም ድርጅቱ ከስሮ በመዘጋቱ ከሆነ ከስንብት ክፍያው በተጨማሪ የመጨረሻ ሳምንት የቀን ደመወዙ በ60 ተባዝቶ ይከፈለዋል።

ሰራተኛው በራስ አነሳሽነት ያለ ማስጠንቀቂያ ስራ መልቀቅ የሚያስችለው በደል ደርሶበት ስራውን ከለቀቀ ከሥራ ስንብት ክፍያው በተጨማሪ የመጨረሻ ሳምንት አማካይ የቀን ደመወዙ በሰላሳ ተባዝቶ እንደሚከፈለው የአ/ሰ/ሕ/አ ቁ.41 ይገልፃል።

      ሌሎች ክፍያዎች በሕገወጥ መንገዱ የተሰናበተ ሰራተኛ ከካሳ ክፍያ እና ከሥራ ስንብት ክፍያ በተጨማሪ ያልወሰደው የዓመት ፍቃድ በገንዘብ ተቀይሮ እንዲከፈለው፤ ያልወሰደው የሳምንት ወይም የህዝብ በዓል እረፍት በገንዘብ ተቀይሮ እንዲከፈለው አሰሪው የዘገየበት ክፍያ ካለ ክፍያው ለዘገየበት ካሣ እንዲከፍለው የትርፍ ሰዓት ክፍያ እና ሌሎች አሰሪው ጋር ቀሩኝ የሚላቸውንም ክፍያዎች ከጠየቀና ፍ/ቤቱ የሰራተኛው ጥያቄ በአግባቡ የቀረበ መሆኑን ካረጋገጠ በሕግ ላይ በተጠቀሰው መጠን መሠረት ተሰልተው ለሰራተኛው እንዲከፈል ይወስናል።

ይምረጡ
(50 ሰዎች መርጠዋል)
12680 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 810 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us