ፍትሕን በፍልስፍና

Wednesday, 12 November 2014 15:26

ኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-          ለመሆኑ ፍትሕ ማለት ምን ማለት ነው?

-          አንድን ነገር ፍትሐዊ ነው ብለን ለማለት እንዴት እንችላለን?

-          ፍትሕ መመዘን ያለበት ከሚያስገኘው ጥቅም አንፃር ነው ወይስ ከራሱ ከነገሩ ሕጋዊነት አንፃር?

-          ሁሉም ሕግ ፍትሕን ይወክላል?

 

ሠላም ናችሁ? እንዴት ነው? ዛሬ አንቀጽ እያጣቀስን ስለ ሕግ አይደለም የምናወራው። ይልቁንስ ታላላቆቹን ፈላስፎች እየጠቀስን ፍልስፍናቸውን እያነሳን ስለ ፍትሕ እናወራለን። ለመሆኑ ሁላችን የምንሻት ይህቺ ፍትሕ ምንድን ናት? እያልን ፅንሰ ሀሳቧን እንፈትሻለን። ማጣቀሻችን “Philosophy of Law a very short introduction” የተባለው በራይሞንድ ዋክ ተጽፎ እ.ኤ.አ በ1998 ዓ.ም የታተመ መጽሐፍ ነው።

ሕግ እና ፍትሕ አንድ ናቸው?

ብዙውን ጊዜ ሕግና ፍትህ እኩል ተደርገው ይወሰዳሉ። ፍ/ቤቶች የፍትሕ አደባባዮች ወይም የፍትሕ አምሳያዎች ተብለው ይጠራሉ። ህንፃዎቻቸው ‘ፍትሕ’ የሚለው ቃል ጐልቶ የሚታይበትና እኩልነትና ተገቢነትን የሚወክሉ መልዕክቶች የሞሉባቸው ናቸው። መንግስታት የሕግ አስተዳደር ስራውን የሚሰሩላቸው የፍትሕ ሚኒስቴሮችን አቋቁመዋል። ጥፋተኛ የተባሉ ወንጀለኞችም ተከሰሱ ወይም ተቀጡ ብቻ ሳይሆን የሚባለው “ለፍትሕ ቀረቡ” ይባላሉ። ሆኖም ጥንቃቄ መወሰድ አለበት። ሕግ አንዳንዴ ከፍትሕ ያፈነግጣል። ሁኔታዎች ሲከፉ እንዲያውም የኢ-ፍትሐዊነት መሳሪያም ይሆናል። የጀርመን ናዚ እና የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓትን በሕግ ፍትሕን ካጠፉት መሀል መጥቀስ ይቻላል። በርግጥ እድለኛ በሆነ ህዝብ ውስጥ ሕግ የፍትሕ መፈለጊያ መሣሪያ ቢሆንም፤ ሁለቱንም ግን ሁልጊዜ አንዱ ሌላኛውን እንደሆነ አድርጐ በቅንፍ ማስቀመጡ ትክክል አይደለም።

የፍትሕ ምንነት፡- መቼም ቢሆን ፍትሕ የሚለው ቃል ከቀላል ሀሳብነት የራቀ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ስለፍትሕ የሚነሱ ሀሳቦች በአሪስቶትል አባባል ነው የሚነሱት። ‘ፍትሕ’ እኩሎችን በእኩል ዓይን፤ እኩል ያልሆኑትን ደግሞ እንደሚበላለጡበት መጠን እኩል ባልሆነ መጠን ማስተናገድ ነው።

አሪስቶትል የማረሚያ ፍትሕን (ፍ/ቤቶች አንዱ ሌላው ላይ የሰራውን ስህተት የሚያርሙበት) እና የማከፋፈል ፍትሕ (ለእያንዱንዱ ሰው የሚገባውን ድርሻ ለመስጠት የሚጥር) በሚል ለይቶ ያስቀምጣቸዋል። እንደ አሪስቶትል አባባል የማከፋፈል ፍትሕ በዋናነት የሕግ አውጭው ስራ ነው። አሪስቶትል ይህን ይበለን እንጂ በተጨባጭ የፍትሕን ምንነት አልነገረንም።

በጥቂቱ የጠራ ፍንጭ የምናገኘው ከጥንታውያኑ ሮማውያን ነው። የፍትሐብሔር ሕጐችን ያካተቱ ድንጋጌዎችን ለሮማውያን ያወጣው (ከ482-565) የኖረው አፄ ጃስቲንያን ያወጣቸው ሕግ ውስጥ ስለፍትሕ ምንነት ጠቅሷል። በዚህ የጀስቲኒያ ሕግ ፍትሕ ማለት “ቋሚና ዘላቂ የሆነ ለእያንዳንዱ የሚገባውን የመስጠት ምኞት ነው።” ‘ሕግን በደምብ መረዳት’ ማለት “በሀቀኝነት መኖር፣ ሌሎችን አለመጉዳት እና ለሁሉም ሰው የሚገባውን ድርሻ መስጠት” ማለት መሆኑም ተገልጿል። እነኚህ አባባሎች ምንም እንኳን በተወሰነ መልኩ ጥቅል ቢሆኑም፤ ቢያንስ ሦስት ጠቃሚ አንዱ በአንዱ ላይ የተደራረቡ የፍትሕ ጽንሰ ሀሳብ መገለጫዎችን ይዘዋል። የመጀመሪያው የግለሰብን አስፈላጊነት ይዘዋል። በሁለተኛ ደረጃ ግለሰቦች በቋሚነት እና ያለ አድልዎ መስተናገድ እንዳለባቸውና በሦስተኛነት ደግሞ እኩልነት አቅፈዋል።

አድሎአዊ ያለመሆን ጉዳይ የፍትሕ ቁልፍ አካል በመሆኑ በቁሳዊ መልኩ በቴሚስ በፍትሕ ወይም በሕግ አማልክት ምስል ወይም ቅርፅ ላይ ይገለፃል። የፍትሕ አማልክት በአንድ እጇ ሰይፍ በሌላኛው ደግሞ ሚዛን ይዛ ተቀርፃለች። ሰይፍ የዳኝነት ስልጣንን የሚይዙ ሰዎች ያላቸውን ጉልበት ሲገልፅ ሚዛኑ ደግሞ ገለልተኛነትና አድሏዊ ባልሆነ መልኩ ፍትሕን መስጠትን ይወክላል። በ16ኛው ክፍለ ዘመን የስነ ጥበብ ባለሙያዎች የፍትሕን አማልክት ዓይን በመሸፈን ሳሏት። ይህ እውር መሆኗንና ማንኛውንም ግፊት ወይም ተፅዕኖ እንደምትቋቋም የሚያሳይ ነው።  

ስለፍትሕ ጽንሰ ሀሳብ አመርቂ ምላሽ ለማግኘት በምናደርገው ፍተሻ ‘እኩልነት’ ጠቀሜታ አለው። እኩሎችን በእኩልነት፣ እኩል ያልሆኑትን እኩል ባልሆነ መልኩ ማስተናገድ በግለሰቦች መካከል ልዩነት የምናደርግበትን መመዘኛ እርግጠኛ የሆነና በአስፈላጊ ነጥቦች ላይ የተመሰረተ ነው ብለን ከወሰድነው የተወሰነ አትኩሮትን የሚስብ ነጥብ አለው። አንደኛው መለኪያ የተለያየ ፍላጐታቸው ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ ኤልሳቤት ሀብታም ነች። ከበደ ደግሞ ደሃ ነው እንበል። ማንኛውም ምክንያታዊ የሆነ ሰው ከኤልሳቤት ይልቅ ለከበደ ሀብት መስጠቱን ይቃወማል። አንዳንዱ ምናልባት የከበደ የድህነቱ ምንጭ ስንፍናውና አባካኝነቱ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ፍላጐትን መሰረት ያደረገው መለኪያ ከችግር የፀዳ አይደለም።

ተገቢው ዋጋስ ምንድን ነው? ለግለሰብ የሚገባውን በመስጠት ፍትሕ ሊሰጥስ ይችላል። ብዙውን ጊዜ የሆነ ሰው የሚገባውን ዋጋ ነው ያገኘው ሲባል እንሰማለን። ለምሳሌ ቤተልሄም ጠንክራ ስለሰራች ከበላይ የተሻለ እድገት ማግኘት ይገባታል ልንል እንችላለን። ሆኖም ግን ምናልባት በላይ የቤቲን ዓይነት የስራ ተነሳሽነቱ ሊኖረው ያልቻለበት ምክንያት የሚረዳቸው ብዙ ጥገኞች ስላሉበትና ድካሙና መሰላቸቱ በስራው ላይ ቁርጠኝነት እንዳያሳይ እንቅፋት ስለሆነበት ነው። የበላይ ዳተኝነት የመነጨው ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠረው በማይችለው በቤተሰቡ የቀደመ ሁኔታ በሚያሳድርበት ጫና ከሆነ ፍትሕን ‘የሚገባውን ዋጋ’ በመስጠት ላይ ከመሰረትነው በርግጥም ኢ-ፍትሐዊነት ሊያስከትል ይችላል።

በግለሰቦች መካከል ያለው ፍትሕ ላይ ያለው ችግር የማኅበራዊ ፍትሕ ካለበት ፈተና የሚያንስ አይደለም። ለዚህም ነው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተቋማት ሀብትን በአግባቡ ለመቋደስ የተቋቋሙት። የፍትሕ ዘመነኛ እሳቤዎች የሚያዘነብሉት አንድ ማኅበረሰብ እጅግ አግባብ በሆነ መልኩ የማኅበራዊ ህይወትን ጫናዎችና ጥቅሞች እንዴት ማከፋፈል ይችላል በሚለው ላይ ነው። አንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ ንድፈ ኀሳብ የፍትሕ ተግባራዊ ጠቀሜታ ሲሆን፤ ሌላኛው ዘመናዊው አማራጭ የፍትሕ ንድፈ ኀሳብ ነው። እስቲ በመጠኑ እነኚህን የፍትሕ ንድፈ ኅሳቦች እንመልከት።

የፍትሕ የአስፈላጊ ተግባር ንድፈ ኀሳብ

ፍትሕ እንደአስፈላጊ ተግባራዊ ንድፈ-ኀሳብ አቀንቃኞች (Utilitarians) መሰረቱ ደስታን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ማድረስ ነው። በዚህ የታወቀው ጀርሚ ቤንታም የተባለው ሊቅ እንደሚለው በእለት ተዕለት ህይወታችን ደስተኛ ለመሆንና ስቃይን ለማስወገድ ስለምንታትር ማኅበረሰቡም ቢሆን የተዋቀረው እነኚህኑ ዓላማዎች እውን ለማድረግ ነው።

….. ተፈጥሮ ሰውን በሁለት የማይደፈሩ ጌቶች እጅ ላይ ነው ያለችው፤ እነሱም ስቃይና ደስታ ናቸው። እነኚህ ጌቶች ናቸው ምን ማድረግ እንደነበረብን የሚጠቁሙን። እንዲሁም ምን ማድረግ እንዳለብን የሚወስኑልን። በአንድ በኩል የትክክልና የስህተት ተግባር መለኪያ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመንስኤ እና የውጤት ሰንሰለት ከዙፋናቸው ጋር የታሰረ ነው ….. የአስፈላጊ ተግባር መርህ እነኚህን ጌታዎች መሪነት እውቅና ይሰጣል። በተጨማሪም ለስርዓቱ መሰረት አድርገው የወስዷቸዋል። የዚህም ዓላማ የምክንያታዊነትና የሕግን እጆች በመጠቀም የደስታ መናርን ውጤቶች እንዲበዙ ማድረግ ነው። ይህ እውነታ ላይ ጥያቄ ለማንሳት የሚሞክር ስርዓት የሚመራው ከስሜት ይልቅ በድምፅ፣ ከምክንያት ይልቅ በምክንያት አልቦነት፣ ከብርሀን ይልቅ በጭለማ ነው።

በመሆኑም ወሳኙ መመዘኛ የምናደርገው ነገር የሚያስከትለው ውጤት ነው። ውጤቱ አስደስቶናል ወይስ አስከፍቶናል? የሚለው ነው የሚወሰነው። ‘ደስታን የሚጨምር ስሌትን’ በመጠቀም ቤንታም እንደሚለው ለማንኛውም ድርጊት ወይም ትዕዛዝ የደስተኝነት ምክንያቶችን መገምግም እንችላለን። በመሆኑም የተግባራዊ ጠቀሜታ ንድፈ ኀሳብ ድርጊቱ ያስከተለውን ውጤት ነው የሚመለከተው። ለዚህም ነው ‘ውጤታዊነት’ ቅርፅ አለው ተብሎ የሚገለፀው፤ ሆኖም ትክክል ወይም ስህተት መስራት ከውጤቱ ተነጥሎ የሚታይ ነው ብለው የሚያምኑት። የስነምግባር ስርዓቶች “ፍትሕ እስከተደረገ ድረስ ሰማይ ይገለባበጥ!” ከሚለው መፈክራቸው ተነጥሎ መታየት አለበት።

የአስፈላጊ ጥቅም ጽንሰ-ኀሳብ ሁለት ልዩነቶች አሉት። በድርጊት አስፈላጊ ጥቅም (የድርጊቱ ትክክለኛ እና በስህተት መሆን የሚወሰነው የሚያስከትለው ውጤት ጥሩ ወይስ መጥፎ በመሆኑ ላይ ነው። ሌላኛው ደግሞ የሕግ የአስፈላጊነት ጥቅም ሲሆን በዚህ መለኪያ የአንድ ድርጊት ስህተትነት ወይም ትክክለኛነትን የሚወስነው ሕጉ በሚያስከትለው ጥሩ ወይም መጥፎ ነገር በመሆኑ ሁሉም ሰው በተመሳሳይ ሁኔታዎች ሕጉ የሚለውን ነገር መተግበር አለበት። የሕግ የአስፈላጊ ጥቅም መመዘኛ ዳኞች ከሳሽ በተከሳሽ ላይ ካሳ እንዲወስኑ መዝገብ ሲቀርብላቸው ጠቃሚ ይሆናል። ዳኛው የፍርዱን ውጤት ተከሳሹ ላይ የሚያስከትለውን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ ውሳኔ እንዲሰጥ ያስችለዋል።

ዘመናዊው የአስፈላጊ ጠቀሜታ ጽንሰ ኀሳብ አቀንቃኞች የሚሉት ፍትህ መመዘን ያለበት ሰዎች የሚፈልጉትን ማሳካት እስከሚችሉበት ገደብ ድረስ በመሆኑ ምርጫቸውን መጠበቅ አለብን ይላሉ። በመሆኑም ‘ጥሩ’ የሚባለው ነገር መተው አለበት የሚለውን ነጥብ የሚቀበሉ መሆናቸው ዘመናዊው የፍትሕ የጠቀሜታ መለኪያ አቀንቃኞች ኀሳብ አንዱ ጠቀሜታ ነው።

የፍትሕ አስፈላጊ ጠቀሜታ ንድፈ ኀሳብ ሞራላዊ ኀሳብ የነበረውን የፍትሕን ትርጉም በአእምሮ ምርጫ ላይ የተመሰረተና ፍትሕን ወደታች ወርዶ የሰዎችን ደስታ መለኪያ አድርገውታል። ሆኖም የተለያዩ ትችቶችን ማስተናገዳቸው አልቀረም። ንድፈ-ኀሳቡ ‘የሰዎችን የተለያዩ’ መሆን አላጤነም። ግለሰቦችን ሁሉ እኩል አድርጐ በማየቱ ዋጋቸው ደስታና ሀሴትን ለማጣጣም ብቻ አድርጐታል። በተጨማሪም ዋነኛው የሞራል ግብ የደስታን መጠን መጨመር ብቻ በመሆኑ ደስታ ደስታን ከማከፋፈል ደህንነትን ከማስፈን እና ከመሳሰሉት ተነጥሎ መታየቱ አለአግባብ ነው ይላሉ።

ጆን ራውል የጠቀሜታ መመዘኛውን ትክክል የሆነውን ነገር መተርጐም ያለበት ‘ጥሩ’ የሚባለው ምንድን ነው የሚለውን በመጠቀም ነው። ይህ ማለት ንድፈ ኀሳቡ የሚጀምረው ‘ጥሩ’ (ለምሳሌ ደስታ) ምንድነው ከሚል መነሻ ሲሆን፤ ድርጊቱ ትክክል የሚሆነው ያን ጥሩነት የሚያሳድግ እስከሆነ ድረስ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሳል።

በፍትሕና የምጣኔ ሀብታዊ የሕግ ትንታኔ፡- በአስፈላጊ ጠቀሜታ ላይ እንደተመሰረተው የፍትሕ ትርጓሜ ሁሉ የሕግን የምጣኔ ሀብታዊ ትንታኔ የተካኑ ምሁራን ምክንያታዊ የሆነው የእለት ተዕለት ምርጫችን በማኅበረሰቡ ውስጥ ትክክል የሆነው ምንድንነው የሚለው ላይ መመስረት አለበት ይላሉ። እያንዳንዳችን እንደተባለው እርካታችንን ለመጨመር የምንጥር ከሆነና ይህ ማለትም ይህን ዓላማ ለሚያሳካልን ነገር የሆነ ነገር መክፈል ከሆነ በአጠቃላይ የምንጠየቀውን ለመክፈል ፈቃደኛ ነን ማለት ይቻላል። በሌላ አባባል ውድ መኪና ለመግዛት እጅግ ከፍተኛ የሆነ ፍላጐት ካደረብኝ የመግዣውን ገንዘብ ለማግኘት እዘጋጃለሁ ማለት ነው።

የዚህ እሳቤ ፊት አውራሪ የሕግ ሊቁ እና ዳኛው ሪቻርድ ፓስነር ነው። ፓስነር የአስፈላጊ ጥቅም እሳቤ አራማጆችን አቋም አይቀበልም። ይልቁንስ ባልተፃፈ ሕግ በሚመሩ ስርዓቶች ዳኞች የምጣኔ ሀብታዊ ደህንነትን ለመጨመር እንደሚጥሩ ሊታዩ ይገባል። በሌላ አባባል በርካታ የሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ያደረጉት ብዙውን ጊዜ ሳይታሰብበት ቢሆንም፤ የሕግ ተርጓሚው እጅግ የተሻለ የሆነውን ውጤት ለማግኘት በማለም ላይ ነው። ዳኞች ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ክርክሮችን በማኅበረሰቡ ሀብት ላይ የሚያወጣውን ከፍተኛ እድገት መርጠው ታሳቢ በማድረግ ይወስናሉ።

በቀላል ምሳሌ ለማየት ይህን ጋዜጣ በብር 6 ገዛህ እንበል። ከፍተኛ ለመክፈል ፈቃደኛ የነበረን የገንዘብ መጠን 10 ብር ነበር። ስለዚህ ሀብትህ በአራት ብር ጨምሯል ማለት ነው። በተመሳሳይ ፓስነር እንደሚለው ማኅበረሰቡም የሀብቱን መጠን ከፍተኛ ደረጃ ማድረስ የሚችለው እምቅ የሀብት ምንጮቹ የእያንዳንዱ ግብይት በአጠቃላይ የተቻለውን ያህል ከፍተኛ ደረጃ በሚደርስበት መልኩ ሲከፋፈል ነው። እንደ እሱ (ፓስነር) አባባል በትክክል መሆን ያለበትም ይሄ ነው።

የፓስነር ንድፈ-ኀሳብ የተመሰረተው የምጣኔ ሀብታዊ ንድፈ-ኀሳቦችን በሚከተሉ ለውጦች ላይ ነው። አንዳንድ ለውጥ ውጤታማ ነው የሚባለው ያገኘው ነገር፣ የጨመረለት ዋጋ፣ ያጣው ነገር ከቀነሰበት በታች ሲሆን ነው። ሌላው ደግሞ አንድ ሁኔታ ቢያንስ አንድ ሰው ከለውጡ በፊት ከነበረበት ሁኔታ የከፋ ሁኔታ ውስጥ ሳይካተት ሊለወጥ አይችልም የሚለው ነው። ሁለቱም ለማውጣት ወይም ለመክፈል ባለን ዝግጁነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በተጨማሪም የሚያስከትለውን ልመና የመቀነስ ጽንሰ ሀሳብንም ተጠቅሟል። ተስፋ የቆረጠ ለማኝ አንድ ብር ትልቅ ለውጥ በሀብቱ ላይ ያመጣል። ለአንድ ሚሊየነር ደግሞ አንድ ብር ቢመጣም ቢሄድም ምንም ለውጥ አያመጣለትም።

ገሀዳዊው ህይወት ያለህ ቀላል የስሌት ምሳሌ ከሚጠቀመው በላይ የተወሳሰበ ነው። የተወሰኑ ወጭዎች በሂደቱ መከሰታቸው አይቀርም። ምንም የግብይት ወጪ በሌለበት አመርቂ ውጤት የሕጉን ምርጫ ከግምት ሳያስገባ ይገኛል። ይህን ከፍትሕ አንፃር ስናየው በመጀመሪያ የነበረው የሀብት ክፍፍል ፍትሕዊ እንዳልነበር ይገመታል። “አመርቂ ወይም አጥጋቢ” ማለት የነበረውን እኩል አለመሆን የምንጠብቅበት መሳሪያ ነው። በሌላ አነጋገር የሕግ የምጣኔ ሀብት ትንታኔ ከርዕዮተ-ዓለማዊዎቹ ከካፒታሊዝም ከነፃ ገበያ ስርዓት የተለየ ነው ማለት ነው? ሀብትን ማካበትስ እውን ከፍትሕ ጋር ይስተካከላል? ሀብት ማካበት በራሱ እሴት ይሁን ወይስ እንደ መሳሪያ ሆኖ ነው? ማኅበረሰቡ ፍትሕን ለመገበያያ በቂ ነው ብሎ ነው፤ የሚያስበው። አብዛኞች የማኅበረሰቡን ሀብት መጨመር እውን ማኅበረሰቡን ያሻሽላል ወይስ ፍላጐታችን ፓስነር ከሚለው ይብስ የተወሳሰበ ነው? ሲሉ የፓስነርን ንድፈ ሀሳብ ይሞግታሉ።

ፍትሕ እንደ ተገቢነት

ጆን ራውል የፃፈው የፍትሕ ንድፈ ኀሳብ ፍትሕን እንደ ተገቢ ድርሻ ስለሚወወስደው የአስፈላጊ ጠቀሜታ አቀንቃኞችን እኩል ያለመሆን ሀሳብ ባይቀበልም ከፍተኛ ደህነትን ማስተማመን በሚለው ግቡ ይስማማል። ድህነትን ማስተማመን የጥቅም ጉዳይ እንዳልሆነና “ቀዳሚው የማኅበረሰቡ ጥሩነገር” መሆኑን የሚሞግት ሲሆን፤ ራስን ማክበርንም እንደሚያጠቃልል ይገልፃል። በተለይም የፍትሕ ጥያቄ ከደስታ ጥያቄ እንደሚቀድም ይከራከራል። አንድን አስደሳች ነገር ብቻ ስናይ ነው ጥቅም ወይም ዋጋ አለው ብለን የምንፈርደው። ሰውን ከማሰቃየት ደስታን ለሚያገኝ ሰው ድርጊቱ ዋጋ እንዳለው መጀመሪያ ማሰቃየት ራሱ ትክክለኛ ወይም ፍትሐዊ ነው ወይ የሚለውን ስንወስን እንደምን ማወቅ እንችለለን? የአስፈላጊ ጥቅም አቀንቃኞች ትክክለኛ ማለት ጥሩ የሆነው ነው ብለው ሲተረጉሙት። ራውል ደግሞ ትክክለኛ ከጥሩም ይቀድማል። ማኅበራዊ ውል አላማው መንግስት ማቋቋም ሳይሆን የመሰረታዊ መነሻው ራሱ የፍትሕ መርህ ነው። በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አብሮነት ቀጣይ ሂደቶችንም ይቆጣጠራል። በዚህ መልኩ የፍትሕን መርሆዎች መተግበር ነው፤ ፍትሕን እንደ ተገቢነት መተርጐም የሚቻለው።   

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
7394 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 820 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us