ትርፍና ትራፊክ

Wednesday, 19 November 2014 11:35

ኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    ትርፍ መጫን የትራፊክ ቅጣት ብቻ ሳይሆን ሌላም የሚያሳጣው ነገር አለ

-    ትርፍ የጫነው ተሽከርካሪ የተጠየቀለትን የመድን ካሳ አስመልክቶ እስከ ሰበር የደረሰው ክርክር በምን ተቋጨ?

-    የትራፊክ ፖሊስን ክስ አልቀበልም ማለት ይቻላል?

-    እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሰው የትራፊኳና የሹፌሩ ጉዳይ ምን ውሳኔ አገኘ?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? ዛሬ የምናነሳው በሀገራችን አሳሳቢ የሆነውን የመንገድ ደህንነትን በተመለከተ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ የራሳቸውን አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉ በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጡ ሁለት ውሳኔዎችን ነው። ሁለቱም የተለያዩ ተከራካሪዎችን የተለያዩ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ቢሆኑም፤ አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ ነጥብ የመንገድ ደህንነት ቁጥጥሩን የሚያጠናክሩና በስሩ ላይ ካሉት ሕጐች በተጨማሪ አሽከርካሪዎችም ሆኑ የተሽከርካሪ ባለቤቶች መንገድ አጠቃቀማቸው ላይ ተጨማሪ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያስችሉ መሆናቸው ነው። ክርክሮቹንና የመጨረሻ ውሳኔያቸውን እነሆ፡-

ትርፍ የጫነው መኪና ያስነሳው የመድህን ዋስትና ክርክር

1. የክርክሩ መነሻ

ሰኔ 20 ቀን 2004 ዓ.ም የሰ.ቁ3-19516 ኦሮ የሆነ ሚኒባስ መኪና ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ 18 ሰዎችን አሳፍሮ እየተጓዘ ነበር። ሚኒባሱ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ቢሾፍቱ ከተማ መግቢያ ላይ ሲደርስ በነበረው ከፍተኛ ፍጥነት የተነሳ አሽከርካሪው መኪናውን ከመቆጣጠሩ በፊት ያለምንም የማስጠንቀቂያ ምልክት መንገድ ዘግቶ ቆሞ ከነበረ መኪና ጋር ተላተመ። በአደጋው 14 ተሳፋሪዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው አለፈ። አደጋው እጅግ አሳዛኝና ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ የተሽከርካሪ አደጋ የሚያስከትለውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ያሳየ ነበር።

የተሽከርካሪ አደጋዎች ሲደርሱ የሚነሳው ጥያቄ ተሽከርካሪው የመድህን ዋስትና ሽፋን አለው ወይ? የሚለው ነው።

አዎ በርግጥም የሰ.ቁ3-19516 ኦሮ የሆነችው ሚኒባስ የመድህን ሽፋን ነበራት። ግሎባል ኢንሹራንስ ኩባንያ አክስዮን ማኅበር ነበር ለሚኒባስዋ የመድህን ዋስትና ሽፋን የሰጠው። በዚህም ኃላፊነቱ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ የሆነችውን ሚኒባስ የተጐዱ ተሽከርካሪዎች ወደሚጠገኑበት ማከማቻ በማስገባት ሚኒባስዋ ተጠግና መመለስ የማትችልበት መልኩ መጐዳቷን በማረጋገጡ ሚኒባስዋ የአውራሻችን የጋራ ንብረት ነች ብለው ላቀረቡት ለአቶ ፍፁም ላቀውና ለወ/ሮ ብስኩት ላቀው የሚኒባስዋን ዋጋ ብር 350,000 ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ይገልፅላቸዋል።

የተፅናኑት አቶ ፍፁምና ወ/ሮ ብስኩት በአደጋው ሙሉ ለሙሉ ለወደመችው ሚኒባስ የካሳ ክፍያ ሲጠብቁ ከመድህን ሽፋን ሰጪያቸው ከግሎባል ኢንሹራንስ ኩባንያ አንድ ያልጠበቁትን አስደንጋጭ ምላሽ ሰሙ።

ሚኒባስዎ መጫን ከነበረባት 11 ሰው በላይ 7 ትርፍ ሰው ጭና ስትጓዝ በመሆኑ አደጋው የደረሰው። ስለዚህ ካሳ አልከፍልም ሲል ነበር ግሎባል ለደንበኛው ለአቶ ላቀው ወራሾች ያሳወቃቸው።

2. ጉዳዩ ወደ ክስ አመራ

አቶ ፍፁምና ወ/ሮ ብስኩት የግሎባልን ትርፍ ለጫነ ሚኒባስ ካሳ አልከፍልም የሚል መልስ እንደሰሙ በሕግ አስገድደው የመድህን ዋስትና ካሳውን ለማግኘት በአዳማ ልዩ ዞን ከ1 ፍ/ቤት ግሎባልን ከሰሱ።

ክሱ ግሎባል የመድን ሽፋን የሰጣት ሚኒባስ ሙሉ በሙሉ ከቆመ መኪና ጋር ተጋጭታ በመውደሟ ከ350ሺ ካሣ አደጋው ከደረሰበት ከሰኔ 20 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሰብ 9 በመቶ ወለድ ጋር እንዲከፈለን ይወሰንልን የሚል ነበር።

3. የተከሳሽ መልስ

ክስ የቀረበበት የመድን ኩባንያው ግሎባል መከላከያ መልሱን አቀረበ፤

-    ለሚኒባስዋ የመድህን ዋስትና ሽፋን ሰጥቻለሁ። ከአደጋው ሥፍራም ሚኒባስዋን አንስቻለሁ። ይሁን እንጂ ፖሊስን ስለአደጋው ሪፖርት እንዲያቀርብ ጠይቄ ባገኘሁት ምላሽ፤ አደጋው በደረሰበት ወቅት ሚኒባስዋ ሹፌሩን ሳይጨምር የመጫን አቅሟ 11 ሰዎች ሆኖ እያለ፤ 7 ሰዎችን በትርፍነት ጭና ነበር።

-    አደጋው የደረሰው ሚኒባስዋ ከአቅም በላይ በመጫንዋ የፍጥነት መቆጣጠሪያዋ እንዳይታዘዝና መሪዋንም ወደሚፈልግበት አቅጣጫ አሽከርካሪው መምራት ባለመቻሉ ነው።

-    በመድህን ዋስትና ፖሊሲዬ አንቀጽ 6 ላይ የመድህን ዋስትና የተገባለት ተሽከርካሪ ከመጫን አቅሙ በላይ ትርፍ ጭኖ አደጋ ከደረሰበት የመድህን ሰጪው የተሽከርካሪውን ዋጋ የመክፈል ግዴታ የለበትም። በመሆኑም የከሳሾቼ ክስ ውድቅ ይደረግልኝ ሲል ጠየቀ።

4. የፍርድ ቤቱ ውሳኔ

ክሱ የቀረበለት የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ከኢትዮጵያ መድህን ድርጅትና ከግሎባል አንዳንድ የጉዳት ገማች ባለሙያዎች አስቀርቦ ሙያዊ ምስክርነታቸውን ሰማ።

የትራፊክ ፖሊስ ስለአደጋው ያቀረበውንም ሪፖርት አገናዝቦ መረመረና ውሳኔ ሰጠ።

-    ከአቅም በላይ መጫን አደጋ አያስከትልም ማለት ባይቻልም፤ የትራፊክ ፖሊስ ባቀረበው ሪፖርት አደጋው የደረሰው አሽከርካሪው በፍጥነት በማሽከርከርና በማንቀላፋቱ መሆኑን እንጂ ትርፍ በመጫኑ መሆኑን አይጠቅስም፤

-    በመድህን ገቢውና በግሎባል መካከል የተደረገው የመድህን ዋስትና ውል ስምምነትም የመድህን ዋስትና የተገባለት ተሽከርካሪ ትርፍ ሰው ጭኖ ቢገኝ ካሣ አይከፍልም የሚል ባለመሆኑ ለሚደርሰው የሞት፣ የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ጉዳት ካስ ለመክፈል ግሎባል በውሉ ስለተስማማ 350 ሺህ ብር ከነወለዱ ከወጪና ኪሳራቸው ጋር ግሎባል ለከሳሾች ለፍፁምና ለወ/ሮ ብስኩት ይክፈል ሲል ወሰነ።

5. ግሎባል ክርክሩን ቀጠለ

በአዳማ ልዩ ዞን ከ/ፍ/ቤት ውሳኔ ቅር የተሰኘው ግሎባል ለኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ይግባኙን ቢያቀርብም ፍ/ቤቱ የከፍተኛ ፍ/ቤቱን ውሳኔ ትክክል ነው በማለት አፀናው።

ግሎባል የመጨረሻ እድሉን ለመሞከር የሕግ ስህተቶችን የማረም ስልጣን ለተሰጠው ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረበ።

-    አቤቱታው የሚኒባስዋ የመጫን አቅም 11 ሰው መሆኑ በመድህን ፖሊሲው ላይም ሆነ ከሚኒባስዋ የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር (ሊብሬ) ላይ ተገልጿል።

-    በመድህን ፖሊሲዬ ቁጥር 6 ላይ ጠቅላላ ማግለያ በሚለው ስር ውሉ እና ከሚመለከተው አካል በተሰጠው የባለቤትነት ማረጋገጫ ላይ ከተጠቀሰው ሰው ብዛትና ከመቀመጫው ብዛት በላይ ጭኖ አደጋ ለሚደርስበት ተሽከርካሪ ግሎባል ማንኛውንም ክፍያ የመክፈል ኃላፊነት የለበትም ይላል።

-    መድህን ገቢውም ሆነ ግሎባል በን/ሕ/ቁ 657 መሠረት የማግለያ የመድህን ውል ግዴታ ስለተፈራረምን ካሳውን ለመክፈል እንደማልገደድ ያቀረብኩትን ክርክር የስር ፍ/ቤቶች ማለፋቸው አለአግባብ ነው።

ትርፍ መጫን መሪም ሆነ ፍጥነትን አሽከርካሪው መቆጣጠር ስለማይችል ለአደጋ እንደሚያጋልጥ በባለሙያ ምስክር አረጋግጫለሁ። ፍ/ቤቱ ግን ትርፍ በመጫን አደጋው መድረሱ አልተረጋጠም በሚል መወሰኑ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል አለ።

በስር ፍ/ቤት የተወሰነላቸው ከሳሾች ተጠሩና ለሰበር አቤቱታው መልስ እንዲያቀርቡ ታዘዙ

-    እነሱም ትርፍ ከጫነ ተሽከርካሪው ላይ ጉዳት ቢደርስ ካሳ አይከፈልም የሚል የውል ስምምነት የለንም። ግሎባልም ያቀረበው ማስረጃ የለም። የመድህን ፖሊሲ ነው በሚል ያቀረበውም የፖሊሲ ቁጥር የሌለው የማስታወቂያ ብሮሸር ነው፣

-    አደጋው የደረሰው ከመጠን በላይ በፍጥነት በማሽከርከሩና አሽከርካሪው በማንቀላፋቱ መሆኑ በትራፊክ ፖሊስ ማስረጃ ስለተረጋገጠ የግሎባል ክርክር ተቀባይነት የለውም ሲሉ መልስ ሰጡ።

6. የሰበር ውሳኔ

ሰበር የግሎባልንና የእነ ፍፁምን ክርክር መርምሮ አምስት ዳኞች በተሰየሙበት ታህሳስ 4 ቀን 2006 ዓ.ም በሰ/መ ቁ. 90793 አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔው ቅጽ 15 ላይ ታትሞ ወጥተል።

“…. የንብረት የመድህን ዋስትና ከተለዩ የውል አይነቶች አንዱ ሲሆን፤ ውሉም ሕጋዊ ተግባራት በሚከናወኑበት ጊዜ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በዋስትናው ሽፋን መሠረት ለመካስ በማሰብ የሚደረግ ነው።”

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1678(ለ) እንደተመለከተው አንድ ውል በቂ የሆነ እርግጠኛነት ያለውና ሕጋዊ የሆነ ጉዳይ ለማከናወን ሊደረግ ይገባል።

በግሎባል የመድህን ኩባንያና በሚኒባስዋ ባለቤት መካከል የተደረገው የንብረት የመድህን ዋስትና ውልም በሕጉ መሠረት የተደረገ ነው። ሆኖም ሕጋዊ ውል የሚደረገው በሕግ እንዲደረግ ያልተፈቀደውን ድርጊት ወይም የሕግ ክልከላ የተደረገበትን ጉዳይ በማከናወን ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ወይም በሚኖረው ፍላጐት መነሻ ሊሆን አይገባም።

ሚኒባስዋ ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚውል መሆኑ የታመነ ጉዳይ ሲሆን፤ አገልግሎት ሲሰጥም የትራንስፖርት አዋጅ፣ ደንብና መመሪያዎችን መከተል ይኖርበታል። ነገር ግን አደጋው በደረሰበት ወቅት ሚኒባሱ መጫን ከሚገባው 11 ሰዎች በላይ 7 ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ አንደነበረ ተረጋግጧል። ከሳሾችም ትርፍ አልጫነም ነበር ሲሉ ያቀረቡት ክርክር የለም። ተሽከርካሪው ከጫናቸው 18 ሰዎች 14ቱ በአደጋው መሞታቸው በክርክሩ ላይ ተረጋግጧል። ሚኒባስዋ በሕጉ ከተቀመጠው የሰው ቁጥር በላይ መጫኑ የትራንስፖርት ሕጉን የሚጥስ ሲሆን፤ ሕጉ ተጥሶ ከተፈቀደው የሰው ቁጥር በላይ ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ ለደረሰው አደጋ መድህን ሰጪው ግሎባል የዋስትና ሽፋን የመክፈል ኃላፊነት ሊኖርበት አይችልም።

በአጠቃላይ አደጋው የደረሰው የትራንስፖርት ሕግን በመጣስ ሚኒባስዋ 7 ትርፍ ሰዎችን ጭና ስትጓዝ እንደነበር በስር ፍ/ቤቶች የትራፊክ ፖሊስ በላከው ሪፖርት ተረጋግጧል። በመሆኑም የመንገድ ትራንስፖርት ሕግ ከሚፈቅደው ውጭ ትርፍ ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ በመኪናው ላይ የደረሰው ጉዳት የስር ፍ/ቤቶች ግሎባል ይሸፈን በማለታቸው የሕግ ስህተት ፈጽመዋል። በመሆኑም የአዳማ ልዩ ዞን ከ/ፍ/ቤትና የኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍ/ቤት የሰጡትን ውሳኔ በመሻር፤ ግሎባል የመድህን ዋስትና አክሲዮን ማኅበር 350 ሺህ ብር ሙሉ በሙሉ በአደጋው ለወደመችው ሚኒባስ ካሳ የመክፈል ኃላፊነት የለበትም ሲል ወስኗል።

የሰበር ውሳኔ የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ የወጡ ሕጐችን ማክበር የሰው ህይወትና አካል ላይ የሚደርስ ጉዳትና የንብረት ጥፋትን ለማስቀረት ብቻ ሳይሆን ባለንብረቱ በውል የሚያገኘውን የመድህን ዋስትና ሽፋንም በሕግ ፊት ተቀባይነት እንዲያገኝና ጉዳት ለደረሰበት ተሽከርካሪ ካሳ እንዲከፈል አስፈላጊ መሆኑን ያሳየ ነው።

ባነሳነው ክርክር ላይ የሚኒባስዋ ባለቤቶች ካሳ እንዳይከፈላቸው ያደረገው “ትርፍ ሰው” በመጫን የትራንስፖርት መመሪያውን በመተላለፍ ሲሆን፤ ዋነኛ ምክንያቱ በሕግ የተከለከለ ተግባር በመሆኑና ውሉ ሕገወጥ ተግባርን ሕጋዊ ከለላ የሚሰጥ ባለመሆኑ ነው።

ሌሎች ሕገወጥ ተግባራት ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር፣ በመጠጥ ሰክሮ ወይም ጫት ቅሞ ማሽከርከር፣ የሞባይል ስልክ እያናገሩ ማሽከርከር እና ሌሎችም የሚመለከተው አካል ባወጣው መመሪያ የተከለከሉ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ተግባራትን መፈፀም ንብረቱን ለጉዳት ማጋለጥ ብቻ ሳይሆን ለጉዳቱ የተገባውን የመድህን ሽፋን ክፍያም ስለሚያሳጣ አሽከርካሪዎችም ሆኑ ባለንብረቶች ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ ያለባቸውን ግዴታ የሚያከብድ በመሆኑ ልብ ሊሉት ይገባል።

ትርፍ መጫን የመድህን ዋስትና የተሽከርካሪ ጉዳት ካሳን እንደሚያሳጣ አይተናል። አሁን የምናነሳው ደግሞ የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚሰማሩ የትራፊክ ፖሊሶችም ሆኑ ሌሎች የመንግስት ሠራተኞች ስራቸውን በሚያካሂዱበት ጊዜ ተገቢውን ትብብር ማድረግ የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ሆኖም በተቃራኒው በስራ ላይ ያለ የትራፊክ ፖሊስን ስራ ማሰናከል የሚያስከትለው የወንጀል ኃላፊነት ምንድን ነው የሚለውን ቀጥሎ እናያለን።

7. ትራፊኳና ሹፌሩ

መጋቢት 22 ቀን 2003 ዓ.ም ሰሜን ጐንደር ደምቢያ ወረዳ ጫሂት ከተማ ትራፊኳ ም/ሳጅን ሙሉጐጃም ሙሉአለም የዘወትር የማሽከርከርና የመንገድ አጠቃቀም ሕግ የማስከበር ስራዋን እየሰራች ነው። ይህች ኰስታራ ትራፊክ ስህተት አይታ አታልፍም ይሏታል። በዚያ መንገድ የሚመላለሱ አሽከርካሪዎች።

ከፈለ ሰፈነ አይሱዚ የጭነት መኪናውን እያሽከረከረ ብዙ ርቀት ተጉዟል። ነገር ግን መንጃ ፈቃድ አልያዘም። ትራፊክ ሳያጋጥመው ጐንደር ለመድረስ ነበር ሀሳቡ። ጫሂት ከተማ ላይ ቆፍጣናዋ ም/ሳጅን አስቆመችው።

“መንጃ ፈቃድ” አለችው ከሰላምታዋ አስከትላ። ከፈለ የሚለው ጠፋበት። ተንተባተበ። የገዛ ኪሱን እንደ አዲስ ፈተሸ ልቡ እያወቀው።

“አልያዝኩም” አለ እና የዛሬን እለፊኝ ብሎ ተማፀናት።

ም/ሳጅን ቅፁን ጭኗ ላይ አስደግፋ ክሱን ፃፈች እና “ተቀበለኝ” አለችው።

ከፈለ ልመናው አላዋጣ ሲል እምቢታ ሞከረ “አልቀበልም የምታመጪውን አያለሁ”

“በሕግ አምላክ ተቀበለኝ” አለችው ም/ሳጅን ኰስተር እንዳለች። “ልብ አድርጉልኝ የክስ ቻርጅ አልቀበልም ብሏል” አለች ዙሪያዋን ወሬ ለማየት ለተሰበሰቡት።

ከፈለ አይሱዚውን አስነስቶ በመስኰት አንገቱን አውጥቶ “እስቲ ምን እንደምታመጪ እናያለን” አላትና ነዳጅ መስጫውን ረገጠውና መኪናው ተፈተለከ።

ም/ሳጅን ንዴቷን ውጣ ምስክሮች ቆጠረች።

ከ19 ቀናት በኋላ “የለመደች ጦጣ ሁልጊዜ ሸምጣጣ” ሆነና ከፈለ ያንኑ መኪናውን በቆላድባ ከተማ መንጃ ፈቃድ ሳይዝ ሲያሽከረክር ከም/ሳጅን ጋር ተገጣጠሙ። “ባለፈውስ ምን አመጣሽ አለቀበልም” ብሎ መንገዱን ቀጠለ።

አሁን ግን ም/ሳጅን ሙሉጐጃም በዋዛ ልታልፈው አልቻለችም። ሕጉ ተጣሰ። የትራፊክነት ሙያዬም ትርጉም አጣ ስትል ለፖሊስ አመለከተች። የከፈለ ጉዳይ ተጣርቶ ለዐቃቤ ሕግ ተላከ።

ዐቃቤ ሕግ ከፈለ ሰፈነ ላይ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 438 “የመንግስት ሥራን ማሰናከልና የመተባበር ግዴታን መጣስ” በሚል ወንጀል ክስ አቀረበ፤ ደምቢያ ወረዳ ፍ/ቤት።

ከፈለ ክስ ይቀርብብኛል ብሎ አልጠበቀም ነበር፤ ደንግጧል። ክሱ ሲነበብለት ሽምጥጥ አድርጐ ካደ። “እኔ በፍፁም የምትሏትን ትራፊክ ፖሊስ አግኝቻትም አላውቅም፤ ያጠፋሁትም የለም፤ የክስ ቻርጅም አልቀበልም አላልኩም” አለ።

ፍ/ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ሰማ። ከፈለንም የመከላከያ ምስክሮች እንዲያቀርብ አድርጐ ሰማ፤ ሆኖም ምስክሮቹ ክሱን ሊያስተባብሉለት ስላልቻሉ ፍ/ቤቱ ከፈለ የተከሰስክበት አንቀጽ እስከ 5 ዓመት ቢያስቀጣም፤ 1 ዓመት ከስድስት ወራት እስር ይበቃሀል ሲል ወሰነበት።

ከፈለ የሰማውን ማመን ተሳነው። አንድ ወረቀት አልቀበልም ማለት ይሄን ያህል?

ለሰሜን ጐንደር ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቀረበ። ፍ/ቤቱ ይግባኙን ተመልክቶ ጥፋተኛነትህ ትክክል ነው። ቅጣቱ ግን 1 ዓመት ይሁንልህ ሲል አሻሻለለት።

ከፈለ ነገሩ ስላልተዋጠለት ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ስህተት ተፈጸሟል የትራፊክ ፖሊስ ክስ አልቀበልም በማለቴ በዚህ አንቀጽ ልከሰስና ልቀጣ አይገባም አለ።

ሰበር ሰሚው ፍ/ቤትም ከፈለንና ዐቃቤ ሕግን አከራክሮ ጉዳዩን መረመረ። በሰ/መ/ቁ 73953 መጋቢት 13 ቀን 2004 በሰጠው ውሳኔ የወንጀል ሕግ 438 ሌሎች ሰዎች በመንግስት ስራ ላይ በሚፈጽሟቸው ወንጀሎች ውስጥ የሚካተት መሆኑን ከጠቀሰ በኋላ “… የድንጋጌው ይዘት ሲታይ ማንም ሰው ከመንግስት ስራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በሕግ በተፈቀደው ወይም በፍርድ ቤት በተሰጠ ትዕዛዝ መሠረት በመንግስት ሰራተኛ ሲጠየቅ ቀርቦ ለማስረዳት፤ ተገቢውን መልስ ለመስጠት፣ ሰነዶችን ለማቅረብ ወይም ለማስመርመር ወይም ልዩ ልዩ ቤቶች፣ ቦታዎች ወይም ነገሮችን ለማስፈተሽ እምቢተኛ ከሆነ በጠቅላላው ለምርመራ ያልተባበረ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ የመንግስት ስራ ያደናቀፈ እንደሆነ ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን ያሳያል።” ብሎ አንቀፁን አብራራ።

ወደ ከፈለ ሰፈነ ጉዳይ መለስ አለና “በአንቀጽ 438 ውስጥ “በሕግ ከተፈቀደው” እና “በማናቸውም ሌላ መንገድ” የሚሉት ሐረጐች ሲታዩ የከፈለ ድርጊት ይህን ሕግ እንደተላለፈ ያሳያሉ። ምክንያቱም የትራፊክ ፖሊስ የትራፊክ ደንብን የመቆጣጠርና የማስፈፀም ስልጣን በሕግ ተለይቶ የተሰጠው ሲሆን፤ ከዚሁ ስራ ጋር በተያያዘ ኃላፊነቱንና ተግባሩን በመወጣት ሂደት ማንም ሰው ሊያሰናክለው የማይገባ ይልቁንም የመተባበር ግዴታ ያለበት መሆኑ የሚታወቅ ነው” ብሎ ከፈለ ላይ የተወሰነው ቅጣት ላይ የተፈፀመ የሕግ ስህተት የለም በሚል የ1 ዓመት እስራቱን አጽንቶታል።

     ከዚህ የሕግ አንቀጽና የሰበር ውሳኔ የምንረዳው በሕግ ስልጣን የተሰጣቸው ግለሰቦችም ሆኑ አካላት ፖሊስ፣ ትራፊክ፣ ደንብ ማስከበር እና የመሳሰሉት ከመንግስት ስራቸው ጋር በተያያዘ የሚጠይቁንን ነገሮች ሕጋዊነታቸውን አረጋግጠን መቀበል አለብን። ሕጉ የመተባበር ግዴታ ጥሎብናል። በመሆኑም ቅሬታ እንኳን ቢኖረን ያለን አማራጭ አግባብ ላለው የበላይ አካል ወይም ፍ/ቤት ማመልከት ነው። በሕጋዊ መንገድ እንጂ እምቢታን ሕጉ ከልክሏልና አያዋጣም።

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
8427 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 843 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us