የወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎች ሥነልቦና

Wednesday, 26 November 2014 13:02

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.    

-    ለመሆኑ ወሲባዊ ጥቃት መነሻው ምንድን ነው?

-    ለወሲባዊ ጥቃት ወንጀል ፈፃሚነት የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

-    የወንጀለኞች ሥነልቦና ጥናት ወሲባዊ ጥቃትን እንዴት ያየዋል?    

 

እንዴት ናችሁ? ሠላም ነው? ሰሞኑን የሰማነው በእህታችን በሃና ኦላንጎ ላይ የተፈፀመውና ለሞት አበቃት የተባለው አሰቃቂና ነውረኛ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ብዙዎቻችንን ያሳዘነ በመሆኑ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኗል። ምንም እንኳን ጉዳዩ በፖሊስ እየተመረመረ የሚገኝ ቢሆንም ሃና ላይ የተፈፀመውን አረመኔያዊ የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን በተመለከተ አጥፊዎቹ እንዴት መቀጣት አለባቸው የሚሉ የተለያዩ ሃሳቦች ይሰነዘራሉ። ውሳኔው ጉዳዩን የሚዳኘው ፍ/ቤት በመሆኑ ወደፊት የምንሰማው ሲሆን እንደው ለግንዛቤ ያህል ምን ያህል ያስቀጣል የሚለውን ስናነሳ በ1996 በወጣው የወንጀል ሕጋችን አንቀፅ 620(2)፣ (3) እና (4) ስር የሚወድቅ ሆኖ እናገኘዋለን። እድሜዋ ከ18 ዓመት በታች መሆኑ፣ በጭካኔ ወይም በማሰቃየት ወይም ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆኑ ወንዶች በህብረት የተፈፀመ መሆኑ ብቻ ከአምስት እስከ ሃያ ዓመት ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን ሆኖም በአንቀፅ 620(3) መሠረት አስገድዶ መድፈሩ ከባድ የአካል ወይም የአእምሮ ጉዳትን ወይም ሞትን ያስከተለ ከሆነ ቅጣቱ የእድሜ ልክ እስራት ይሆናል። ፍ/ቤቱ ባያረጋግጠውም በአስገድዶ መድፈሩ የተነሳ ሃና ህይወቷን በማጣቷ እንዲሁም ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ከሕግ ውጭ ሃናን ይዘው አስቀምጠዋል በመባላቸው አጥፊዎቹ ለተደራቢ ወንጀል የሚጠየቁበት ሲሆን በወንጀል ሕጉ ላይ በተደነገገው መሠረት ፍ/ቤቱ የተሳትፎአቸውን መጠንና የጥፋታቸውን ክብደት መዝኖ አጥፊዎቹ ላይ ሊፈርድባቸው የሚችለው ከፍተኛው ቅጣት የእድሜ ልክ እስራት ነው። ለሃና ቤተሰቦችና ጓደኞች እንዲሁም በደረሰባት ጥቃትና ሞት ሀዘን ለተሰማን ሁሉ መጽናናቱን እየተመኘሁ አጥፊዎች የተፋጠነና ተመጣጣኝ ቅጣት እንደሚያገኙ እጠብቃለሁ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዋነኛነት የምናነሳው ወሲባዊ ጥቃት አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ የሚፈፅሙ አጥፊዎችን ስነልቦና ላይ ተመስርቶ ባህሪያቸውን፣ ለወንጀሉ መንስኤ የሚሆኑ ምክንያቶችን፣ ለጥፋታቸው ሊያገኙ የሚገባቸውን ቅጣትና ከዚያም በኋላ ድጋሚ ይህን ወንጀል እንዳይፈፅሙ ሊወሰድ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች በተመለከተ የወንጀለኞች ስነልቦና የጥናት ዘርፍ የሚጠቁማቸውን ጠቃሚ ነጥቦች ነው። ማጣቀሻዬ በፈረንጆቹ 2006 የታተመ “criminal psychology” የተሰኘው መፅሐፍ ነው። በነገራችን ላይ የወንጀለኞች ስነልቦና ጥናት ማለት ከወንጀል ምርመራ አንስቶ ወንጀል ትንተና፣ ቅጣትና ከቅጣቱ በኋላም ድጋሚ ወንጀል እንዳይፈፀም ማድረግን የሚያጠቃልል የስነ ልቦና እውቀትን ለፍትህ ስርዓቱ ውጤታማነት መጠቀም ማለት ነው። እንቀጥል።

 • ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎች የሚባሉት እነማንናቸው? ምንም እንኳን ሙሉና የተሟላ ትርጓሜ መስጠቱ ቢያስቸግርም ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚ ማለት የወሲባዊ ጥቃት የፈፀመ ሰው፣ በወሲብ ጥቃት ቅጣት የተፈረደበት ወይም ከሌላው ሰው ፍቃድ ውጭ ወሲባዊ ድርጊት የፈፀመ ሰውንም ሊያካትት ይችላል። አንድ ሰው ፈቃዱን በተለያዩ ምክንያቶች ላይገልፅ ይችላል። ተበዳይ ፍላጎቱን መግለፅ ላይፈልግ ይችላል ወይም ለወሲባዊ ድርጊት ፍላጎቷን መግለፅ የማትችልበት ደረጃ ላይ ልትሆን ወይም ሊሆንም ይችላል ( ለምሳሌ በወንጀል ሕጋችን ከ18 ዓመት በታች ወንዱም ሴቷም ለወሲብ ፈቃዳቸውን መስጠት አይችሉም፣ በአእምሮ ችግር፣ በመጠጥ፣ በአደንዛዥ እፅ አእምሮአቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ሰዎችም ፈቃዳቸውን መግለፅ አይችሉም። ተመራማሪዎች እንደሚያስቀምጡት ሁለት አይነት ወሲባዊ ጥቃቶች አሉ። በግብረ ስጋ ነፃነትና ንጽህና ላይ የሚፈፀም ድርጊት ይህ ካለፈቃድ የሚፈፀም ሲሆን በወንጀል ሕጋችን በጋብቻ ውስጥ ያለ ባል ሚስቱ ላይ ካለፈቃዷ ግብረ ስጋ ግንኙነት ቢፈፅምም በአስገድዶ መድፈር ወንጀል አይጠየቅም። ስለዚህ አስገድዶ መድፈር የሚባለው ከጋብቻ ውጭ ሲሆን ነው። ሌላኛው ደግሞ ለመልካም ፀባይና ለተፈጥሮ ባህሪ ተቃራኒ የሆኑ የግብረ ስጋ ግንኙነቶች እንደ ግብረ ሰዶም የመሳሰሉትን የሚመለከት በሕግ የተከለከሉ ፀያፍ ወሲባዊ ድርጊቶችን መፈፀም ሲሆን፤ ፈፃሚዎቹ ተፈቃቅደው ቢሆንም በሕግ የተከለከለ በመሆኑ የሚያስጠይቅ ድፍረት ነው።
 • የወሲባዊ ጥቃት መንስኤ ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ የወሲባዊ ጥቃት ነጠላ የሆነ የመነሻ ምክንያት ስለሌለው የብዙዎቻችን አንድ ሰው ለምን ወሲባዊ ጥቃት ይፈፀምበታል? የሚለውን ለመረዳት አዳጋች ይሆንብናል። ይሁን እንጂ ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚነትን የሚገለፅባቸው የተለያዩ የጥናት መንገዶች አሉ። እነኚህ የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-
 • አስተዳደግን በጥናት፡- በዚህ ላይ የተደረጉ ጥናቶች የወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎችን የልጅነት ጊዜ እና አስተዳደግ የወሲብ ጥቃት ካልፈፀሙት ጋር በማነፃፀር የሚደረጉ ናቸው። በእነኚህ ሰዎች መሀል ያለውን ልዩነት ለማግኘት ጥረት በማድረግ ለወሲባዊ ጥቃት የሚያነሳሳ የህፃንነት ጊዜ ላይ የሚከሰት ነገር መኖሩን ለማሳየት ይሞክራሉ።
 • የጎልማሶችን የህይወት እንቅስቃሴ ማወዳደር፡- ይህም ጥናት የሚያተኩረው ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎችን ካልፈፀሙት ጋር በማነፃፀር ለአካለ መጠን የደረሱ ሰዎች የህይወት መስክ ወሲባዊ ጥቃት ለመፈፀም መንስኤ መሆን አለመሆኑን ለመለየት ይሞክራሉ።
 • የሚያስከትለውን ጉዳት ተገማችነት ማጥናት፡- ይህ ጥናት የወሲብ ጥቃት ፈፃሚዎችን ብቻ የሚያካትት ሲሆን ለአካለ መጠን የደረሱ ሰዎች የወሲብ ጥቃትን ደግመው እንደፊፅሙ የሚያደርጋቸውን ምክንያት ለማየት ይሞክራሉ። ግለሰቡ ለነገሮች ያለው አቀባበል፣ ውስጣዊ ግንዛቤው አስተሳሰብ ሂደቱ ወይም የምክንያታዊነት ችሎታው ለከፍተኛ የወሲባዊ ጥቃት ተደጋጋሚነት ከሌላው ሰው ይልቅ ያጋልጠው ይሆን የሚለውን ያጠናሉ።
 • የጥቃቱን ሂደት የሚገልፅ ጥናት ማካሄድ፡- ይህ የጥናት ዘርፍ ደግሞ የወሲባዊ ጥቃቱን ምን እንዳመጣው ጥቃቱ ሲፈፀምና ከዚያ በኋላ የተከሰቱ ነገሮችን የሚያጠና ነው።
 • የሕጻናት አስተዳደርና ወሲባዊ ጥቃት፡- የወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎችና ጥቃቱን ያልፈፀሙትን ግለሰቦች የህጻንነት ህይወት በማወዳደር የተደረጉ ጥናቶች ከወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚነት ጋር ሊያያዙ የሚችሉ መሰረታዊ ምክንያቶችን ጠቁመዋል። የመጀመሪያው ከወላጆችና በህፃናቱ መካከል የነበረ ግንኙነትን የሚመለከት ነው። ወላጆች ከህፃናት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ለወደፊት ግንኙነቶች እንደ መሰረታዊ ንድፈ ተቀርፆ የሚቀር እንደመሆኑ ይህ ግንኙነት የእንክብካቤ ጉድለትና አመኔታ የሚጣልበት ካልነበረ የህጻናቱ የወደፊት ግንኙነቶችም ተመሳሳይ ይሆናሉ። በዚህ ላይ በመመስረት የተደረጉ የሌሎች ተመራማሪዎ ግኝቶች እንዳሳዩት የወሲብ ጥቃት ፈፃሚ የሆኑት ካልሆኑት ይልቅ ከወላጆቻቸው ጋር የነበራቸው ግንኑነት ደካማ ሆኖ ተገኝቷል። በገዛ ቤተሰባቸው አባል ወሲባዊ ትንኮ የተፈፀመባቸው ህጻናት ከእናቶቻቸው የነበራቸውን ግንኑነት ደካማ እንደነበርና ብዝበዛ የበዛበት፣ ፍቅር አልባ እና እንክብካቤ የጎደለው እንደነበር ለአጥኚዎቹ ገልጸዋል። እንደሌሎች ወንጀለኞች ሁሉ የወሲብ ጥቃት ፈፃሚዎች ሕን የሚጥሱ ወላጆች የነበሯቸው ሲሆን አስገድዶ ደፋሪዎች ደግሞ አባቶቻቸው በህፃንነታቸው ስለነሱ ደንታ ቢስ እንደነበሩ ገልጸዋል። ፀረ ማህበረሰባዊ ባህሪዎችን ያንጸባረቁ በነበሩ ቤተሰቦች ውስጥ ማደግም የህፃኑን ስነምግባራዊ እናማህበራዊ ጤናማ እድገት የሚያደናቅፍና በአመዛኙ የሕፃኑ የወደፊት ሕይወት በወንጀል የተዘፈቀ እንዲሆን የሚያደርግ ነው።

ብዙውን ጊዜ የወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎች ለምን ድርጊቱን እንደሚፈፅሙ ለማወቅ በሚደረግ ጥረት በህፃንነታቸው የተለያዩ ጥቃቶች የደረሱባቸው ሰዎች ሁሉ የወሲብ ጥቃት ወንጀል ይፈፅማሉ ማለት ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ሁሉም ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎች በልጅነታቸው አላግባብ ተበድለዋል ማለት የሚቻል ባይሆንም ጥናቶች እንዳረጋገጡት ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ከአስገድዶ ደፋሪዎች ሩብ ያህል በህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት ከፈፀሙት ሁለት ሶስተኛው ያህሉ በህፃንነታቸው የአስተዳደግ በደል እንደተፈፀመባቸው አንድ ጥናት አረጋግጧል። አስገድዶ ደፋሪዎች ከፍተኛ አካላዊ ጥቃት በአባቶቻቸው የተፈፀመባቸው ሲሆን የቤተሰብ አባል ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ ደግሞ ከሌሎች እኩዮቻቸው የበለጠ በልጅነታቸው ወሲባዊ በደል የደረሰባቸው ናቸው። ይህ መረጃ የተገኘው በራስ በሚሞላ መጠይቅ ሲሆን አብዛኛው የወሲባዊ በደል በጊዜው ለሚመለከተው አካል አልተገለፀም። ይህም የሆነው በቤተሰብ አባላት እጅ የሚፈፀሙ ማንኛውም አይነት ጥቃቶች ይፋ ያለማድረግ ባህሪ ስላላቸው ነው። በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንዳሳየው የውሸት መመርመሪያ መሳሪያ (Lie detector) የተገፀመላቸው ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎች በአፍላ እድሜያቸው የተፈፀመባቸውን ጥቃት የማይገልፁት ከ70 በመቶ ወደ ሃያ በመቶ ወርዷል።

ከላይ ያነሳናቸው የአስተዳደግ ተፅዕኖዎች ለብዙ አይነት ወንጀሎችም ምክንያቶች ናቸው። የወሲብ ጥቃት ፈፃሚዎችን ከሌሎቹ አጠቃላይ ወንጀለኞች የሚለዩአቸው ነገሮች አሉ። ጥናቶች እንደጠቆሙት አንዳንድ አይነት ወሲባዊ ተሞክሮዎች ከሌሎች የአስተዳደግ ተፅእኖዎች ጋር ሲዳበሉ ግለሰቡን ወደ ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚነት ይመሩታል። ጥናት ከተካሄደባቸው ተሞክሮዎች በልጅነት ለወሲባዊ ትዕይንቶች (Pornography) መጋለጥ ነው። አንድ ጥናት እንደጠቆመው 22በመቶ ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎች ከአስር ኣመት እድሜያቸው በፊት ለወሲባዊ ትዕይንቶች የተጋለጡ ሲሆን ለወሲብ ቀስቃሽ ትዕይንቶች ከተጋለጡ መሀል ወሲባዊ ጥቃት ያልፈፀሙት ግን 2 በመቶ ብቻ ናቸው። የወሲባዊ ትዕይንቶች በዋነኝነት ስለወሲብ ያለን እይታ የአንዱ ደስታ ላይ ብቻ ያተኮረ አድርገው የሚያሳዩ በመሆኑ ይህም በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረተ ወሲባዊ ባህሪ እንዲኖር ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ በአስራዎቹ ውስጥ ያሉ ታዳጊ ወጣቶች ወሲብ ቀስቃሽ ትዕይንቶችን ወደፊት ግለ ወሲብ ለማድረግ እንደሚያነሳሱት አርጎ ሊወስዳቸውና በህይወቱ ውስጥ በቀሪ ዘመኑ የሚያጋጥመው አድርጎ ሊረዳው ይችላል። እነኚህ በራሱ ለራሱ ይረካባቸው የነበሩ ድርጊቶች ወደፊት የወሲብ ጥቃትን እንዲፈፅም ሊመሩት ይቻላሉ።

 • የጎልማሳነት ባህሪና ወሲባዊ ጥቃት፡- በደፈናው ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎች አፈንጋጭ የወሲብ ፍላጎት እንዳላቸወ ቢገመትም ዋናው ነጥብ ግን እሱ አይደለም፡፤ አንዳንድ የጥቃት ፈፃሚዎች ለአፈንጋጭ ወሲባዊ ባህሪ ሲያነሳሳቸው ሌሎች ደግሞ ለጥቃቱ የሚያነሷሷቸው አፈንጋጭነት የሌላቸው የወሲብ ባህሪያት ናቸው። በቅርቡ የተካሄደ ጥናት እንዳሳየው አፈንጋጭ ምኞቶች ከወሲባዊ ስሜት ጋር የተቆራኘ ነው። ይህ አይነት ምኞቶች ንዴት፣ ድብርት ወይም ውርደትን ለማስወገድ ይጠቀሙባቸዋል። ይህ ጥቆማ የግብረስጋ ጥቃት ፈፃሚዎች ግብረ ስጋ ግንኙነትን ጥቃቱን ከማይፈፅሙት የበለጠ እንዲህ አይነት መጥፎ ስሜቶችን እንደመቋቋሚያ እንደሚጠቀሙበት ባረጋገጠ ጥናት የተደገፈ ነው።

የወሲብ ጥቃት ፈፃሚዎች በተለይም ህፃናት ላይ ጥቃቱን የሚፈፅሙ የጠበቀ ወዳጅነትን የማቆየትና የማሳደግ ችግር አለባቸው። ፍቅራቸውን መግለፅ፣ ሌሎችን መርዳት ወይም አለመግባባትን መፍታት ከባድ ስለሚሆንባቸው ብዙውን ጊዜ ለሚያጋጥማቸው የወዳጅነት መቋረጥ ወይም በሌላው ሰው መተው በጣም በቀላሉ ስሜታቸው ይጎዳል። ከሌላ ለአካለ መጠን ከደረሰ ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት መመስረት የሚፈልጉ ቢመስሉም ስለሚፈሩና ምናልባትም በዚሁ የመፈለግን የመፍራት መወላወል የተነሳ ብዙውን ግዜ ድንገተኛ የሆነ ስሜታዊ ግንኙነት ከእድሜ አቻቸው ጋር ይመሰርታሉ። ይህ ስሜታዊነት በሌላ የወሲብ ጥቃት ፈፃሚዎች የህይወት ገፅታ ላይም ይንፀባረቃል። በመሆኑም ራሳቸውን መግዛትና ስሜታቸውን መቆጣጠር ስለሚሳናቸው ጥቃቱን ለመፈፀም ያላቸውን ተጋላጭነት ይጠቁማል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጥቃቱ ፈፃሚዎች የህይወት ጫናዎችን መቋቋም የማይችሉ መሆናቸውን ያሳያል። በህይወት የሚያጋጥሟቸውን ትንንሽ ችግሮች በአግባቡ ለመቋቋም ስለሚሳናቸው የችግር መፍቻ አቅማቸው ደካማ ነው። ጥናቶች እንዳሳዩን ግላዊ ጭንቀቶች ቁጣ፣ ድንጋጤ፣ ድባቴ ወይም ድብርት ብዙውን ጊዜ የወሲብ ጥቃት ለመፈፀም ቀስቃሾች ናቸው። የእለት ተዕለት ህይወታቸውን ከመምራት አንጻር የወሲብ ጥቃት ፈፃሚዎች የተወሰኑ ነገሮች ላይ የተዛቡ ወይም ውጤታማ ያልሆኑ አስተሳሰቦች አሏቸው። ለምሳሌ የአስገድዶ ደፋሪው የሴት ጓደኛ ምግብ በሰዓቱ የማታዘጋጅ ከሆነ አስገድዶ ደፋሪው ይህን የሚወስደው የሴት ጓደኛው ከጓደኞቹ ጋር አብሮ እንዳይሆን ለማድረግ ያደረገችው እንደሆነና ልትቆጣጠረው እየሞከረች መሆኑ ለሱ ውርደት እንደሆነ አድርጎ ያስበዋል። እንዲህ አይነት አስተሳሰቦች ወንዳዊ ጥላቻ (hostile masculinity) ሲባሉ ባህላዊ ለሆኑ የወንድ ባህሪዎች የበላይነትና ኃይለኝነት የተጋነነ ግምት በመስጠት የሴቶችን እንደ እርጋታ ያሉ ባህሪዎችን ዋጋ ቢስ የማድረግ አዝማሚያ አላቸው። ህጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚፈጽሙ ሰዎች ያላቸው የተዛቡ አስተሳሰቦች ደግሞ ህጻናት ወሲብ ይፈልጋሉ ወይም ወሲብን ማወቅ ይችላሉ የሚሉ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች አላቸው።

      በአጠቃላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎች ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ ነው፣ ለሌሎች ፍቅር ያንሳቸዋል፣ ሲቸግራቸው ራስን ተጠያቂ ለማድረግ በሌሎች ማላከካቸው፣ በተደጋጋሚ በአሉታዊ ስሜቶች የሚጠቁ መሆናቸው፣ ችግሮችን የመቋቋም ብቃታቸው ደካማ መሆኑና አስተሳሰባቸውን እያወቁ የሚያዛቡ እና ከሌሎች ጋር ግንኙነት የመፍጠር ችሎታቸው ደካማ መሆኑ የስነልቦናቸው መገለጫቸው ሲሆን ወሲባዊ ጥቃትን ለመከላከልም ሆነ አጥፊዎችን ለማረምና ለመቅጣት የሚወስዱ እርምጃዎች እነኚህንና ሌሎችንም ስነልቦናዊ ችግሮች ከግምት ያስገባ ቢሆን የተሻለ ውጤታማ ይሆናል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
8236 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 675 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us