Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 392

የወንጀል ምስክርት

Wednesday, 13 November 2013 13:02

(የሕግ ባለሙያ)  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

 

በወንጀል ጉዳይ በምስክርነት የተጠሩ ምስክሮች መብትና ግዴታ

የወንጀል ምስክርነቶች

-         በፖሊስ

-         በቀዳሚ ምርመራ ፍ/ቤት

-         በመደበኛው ፍ/ቤት እንዴት ይሰጣሉ?

-         ለምስክሮች የሚቀርቡ የተለያዩ የጥያቄ አይነቶች

-         እውነቱን አለመመስከር የሚያስከትለው የወንጀል ኃላፊነት

 

 

ሰላም ነው? እንዴት ናችሁ?

 

ባለፈው ሳምንት በተለያዩ አጋጣሚዎች ፍርድ ቤት ስትቀርብ እንዳትሳቀቅና እንዳትደናገር ምን ማድረግና ማለት እንዳለብህ የስነስርዓት ሕጉን እያጣቀስን አውግተናል። በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ተከሳሽ ከጊዜ ቀጠሮ ችሎት አንስቶ በመደበኛው ችሎት ቀርቦ የእምነት ወይም ክህደት ቃሉን እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ሕጉ በሚደነግገው መሰረት ምን ማድረግ ወይም ምን ማለት እንዳለበት ለመጠቆም ሞክሬያለሁ። ብዙ ሰዎች ግድ ካልሆነባቸው በስተቀር ችሎት ላይ ቆመው በከሳሽ በተከሳሽነት መከራከር ብቻ ሳይሆን በምስክርነት መቅረብ እንኳን አይመቻቸውም። ይሳቀቃሉ ዳኝነት የመስጠቱ ስነስርዓት የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በቅጡ ስለማይረዱት ይፈሩታል። በችሎት ታዳሚነት ሲገኙ እንኳን የሆነች ጥናት ሰርተው ችሎት ተዳፍረው የሚቀጡ እየመሰላቸው ስለሚፈሩ ነፃ አይሆኑም። ሆኖም ግን የፍ/ቤት የችሎት ስነስርዓት ላይ ከማንኛውም ሰው የሚጠበቁ ግዴታዎችና መብቶች ያን ያህል ውስብስብና የሚያስፈሩ አይደሉም። ዛሬም የተወሰኑትን አንስተን እንመለከታለን በቅድሚያ


አስቂኝ የችሎት ላይ ገጠመኞች

ባለፈው አንድ መፅሀፍ ሳነብ ነበር። LAW AND LAUGHTER ይሰኛል። እርእሱ ሕግና ሳቅ እንደማለት ነው። መፅሀፉ ቆየት ብሏል ከታተመ 100ኛ ዓመቱን ይዟል መፅሐፉ። የመፅሐፉ ዓላማ የሕግን ቀላል ዘና ያለ ጎኑን ለማሳየት በታላቋ ብሪታንያ፣ በአየርላንድና በአሜሪካ ችሎቶች ላይ ያጋጠሙ አስቂኝ አስገራሚና አስተማሪ ገጠመኞን አካቷል። ጥቂቶቹን እነሆ. . .


ሞቅ ያለው ምስክር

እንግሊዛዊው ዳኛ ሎርድ ማንስፊልድ የሁለት መርከቦችን ግጭት ተከትሎ የተነሳውን ሙግት እያስቻሉ ነው። ስለግጭቱ እንዲስረዳ የቀረበው አንድ መርከበኛ “ከመመልከቻ ማማው ላይ ቆሜ እያለሁ. . .” ሲል ዳኛው ማንስፊልድ ቀበል አርገው “የመመልከቻ ማማው የትነው የሚገኘው?” ሲሉ ጠየቁት።

 

ታዳሚ ሁሉ እንዲሰማው “ይሄ ደግሞ ምን አይነቱ ነው የርቀት መመልከቻ የት እንዳለ ሳያውቅ ነው እንዴ ዳኛ የሆነው” በማለት ጮክ ብሎ ይዘልፋቸዋል።

 

ይሄኔ ዳኛ ማንሰፊልድ ምስክሩን ችሎት በመደፈር ለመቅጣት ማማ የት እንደሚገኝ ብትነግረኝም ከገደቡ አልፎ የሞላ ባህር ግን ምን ማለት እንደሆነ አሳይተኸኛል ሲሉ በአሽሙር ምስክሩ አቅሉን እስኪስት መቀምቀሙን ጠቆሙት።


 

ሁሌም ባይሆን አንዳንድ ጊዜ ዳኞች ለሙያቸው አክብሮት ከሌላቸው የሕግ ባለሙያዎችና የፍትህ ስርዓቱ አካላት ጋር ግጭቱስ ይገባሉ። አንዳንዶቹ በችሎት መዳፈር ተዳፋሪዎችን በመቅጣት የሙያውን ክብር ያስጠብቃሉ። በርግጥ ይህ ሕጉ በሚያዘው መሰረት ችሎቱን ማስከበር አስፈላጊ ቢሆንም አንዳንዴ ግን ተመጣጣኝ ሆነ አስገራሚ ምላሽ መስጠቱ የበለጠ ውጤታማ ሲሆን ይታያል በሚል LAW and LAUGHTER (ሕግና ሳቅ የተሰኘው መፅሀፍ ይሄን ገጠመኝ ተርኳል. . .

 

አንድ ነገር ፈጅ ኤለን ብር ከተባሉት ዳኛ ፊት በነበረው ሙግት በተከታታይ በሚያነሳቸው የማይጨበጡ ነጥቦች የተነሳ አቤቱታዎቹ በዳኛው ፊት ተቀባይነት በማጣታቸው ብስጭት ይልና “ክቡር ዳኛ አሁን በርግጥ የተከበሩ ዳኛ ቢሆኑም እኔ የእርስዎን ፍቃድ አበምስት ሽልንግ ከፍዬ አገኝ የነበረበት ጊዜ ትዝ ይለኛል” ይለል።

 

ይሄኔ ዳኛው ከቁጣ ወይም ከብስጭት ይልቅ በሚያስገርም ፈገግታ ተሞልተው “ጌታዬ እኔም እኮ ያልኩት ሀሳብህ ያን ያህል እንኳን ዋጋ (አምስት ሽልንግ) አያወጣም ነው” ሲሉ መለሱለት።

 

 

አንድ አንደበተ ርተዑነቱን ለማሳየት የሚፈልግ ጠበቃ ከዳኛ ኤለንብሮ ፊት ቀርቦ ይህን ንግግር አሰማ “ክቡር ዳኛ፣ ከፊትም ከቀረብኩት በሌላ ሳይሆን በለንደን ከተማ ተሟጋችነት ነው። ክቡር ዳኛ የለንደን ከተማ እራሷም ፍትህን ለማገዝ ከክቡርነትዎ ፊት ቀርባለች። ክቡርነትዎ በተፈጥሮ መፅሀፍ ላይም ተጽፏል። “ምን መፅሃፍ ላይ?” ብለው ጠየቁ ዳኛ ኤለንብሮ የጠበቃውን ዲስኩር አቋርጠው።

 

“የተፈጥሮ መፅሃፍ ላይ” ሲል መለሰ አፈጮሌው ጠበቃ

 

“እንግዲያውስ ገፅ ስንት ላይ እንደሆነ ንገረኝ?” ብለው ልክ ገፁን እንደሚመዘግቡ ብእራቸውን ወድረው ሲጠብቁት ጠበቃው ምን ብሎ ይናገር የሌለ መፅኀፍ ጠቅሶ. . .


 

 

ምስክርነት በወንጀል ጉዳይ

በየትኛውም አይነት የፍትሕ ስርዓት ውስጥ ከውሳኔ ላይ ለመድረስ ማስረጃ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። አንድ ነገር ተደርጓል ወይም ሆኗል ብሎ ለመደምደምና ያንን ድርጊት የፈፀመው ወይም መፈፀም እያለበት ግዴታውን ሳይወጣ የቀረው ማንነው? ድርጊቱስ ያስከተለው ውጤት ምንድን ነው? መጠኑስ ምን ያህል ነው የሚሉት ነጥቦች ሳይጣሩ ፍትሕን መስጠት አይቻልም። እነኚህንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለመመለስ ደግሞ ከሚያስፈልጉ የተለያዩ የማስረጃ አይነቶች አንድ ደግሞ ምስክርነት ነው። ምስክርነት ማለት ስለአንድ አከራካሪ ጉዳይ ላይ ግራ ቀኙ (ከሳሽ ተከሳሽ) ዳኝነት የሚጠይቁበትን ነገር የሚያስረዳ ወይም ደግሞ የተከሰሱበትን ነገር እንደክሱ አለመሆኑን ለመከላከል ያቀረቡትን መከላከያ እውነትነቱን የሚያረጋግጥ ሰው በአካል በመገኘት በቃል ወይም ፍ/ቤቱ በልዩ ሁኔታ ሲፈቅድ ለፅሁፍ የሚሰጡት ማረጋገጫ ነው። ምስክሮች ስለአከራካሪው ጉዳይ በአይናቸው አይተው በጆሮአቸው ሰምተው በአካል ተገኝተው ያገኙትን ከድርጊቱ ፈፃሚ ወይም ከተበዳይ የሰሙትን ወይም ከሌላ ሶስተኛ ወገን ስለጉዳዩ ያገኙትን መረጃ ወይም እውቀት በመግለፅ ነው። በተለይ ደግሞ በወንጀል ጉዳይ ላይ ፍርድ ወይም ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት በማያጠራጥር መልኩ ተከሳሽ ወንጀሉን መፈፀሙ መረጋገጥ ስላለበት የወንጀል ምስክሮች በፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ከዚሁ አንጻርም ኃላፊነታቸው የጎላ ነው።

 

ከፖሊስ ይጀምራል፡- አንድን ወንጀል የአፈፃፀሙን ሁኔታ ማን፣ መቼ፣ የት፣ እንዴት እና ለምን? እንደፈፀመው ማስረጃዎችን መርምሮ ማግኘትና ክስ እንዲመሰረት ለዐቃቤ ሕግ ማስተላለፍ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 22 ለፖሊስ ከተሰጡት ኃላፊነት አንዱ ነው። በመሆኑም መርማሪው ፖሊስ አስፈላጊ ሆኖ ያገኘውን ተገቢነት ያለውን ማስረጃ መስጠት የሚችል ማንኛውንም ሰው ጠርቶ የመመርመር ስልጣን በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 30(1) ላይ ለፖሊስ ተሰጥቶታል። እናም በወንጀል ጉዳይ ምስክር የመሆን ግዴታዎች ከፖሊስ ጣቢያ ሊጀምሩ ይችላሉ። ፖሊስ ምስክሮች የሚሰጡት ማንኛውንም ቃል በማስረጃነት የመመዝገብ ግዴታ አለበት። በተጨማሪ ፖሊስ ምስክሩን መደለል ወይም እንዲደለል ማድረግ የተስፋ ቃል ወይም የሃይል ስራ ሌሎች ከሕግ ውጭ የሆነ ማስረጃ የማግኛ ዘዴዎችን እንዳይጠቀም በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ31 ላይ ተደንግጓል። በተጨባጭ ግን ፖሊሶቻችን ይህን ግዴታቸውን ከመወጣት ይልቅ ማስረጃቸውን አጠናቅረው ለማስቀጣቱ ትኩረት ሲሰጡ ይታያል።

 

እውነቱን ብቻ መናገር፡- ምስክርነት ትልቅ ኃላፊነት ነው። በመሆኑም ይህን ኃላፊነት በአግበቡ ለመወጣት በወንጀል ጉዳይ ለምስክርነት ፖሊስ ዘንድ የተጠሩ ምስክሮች ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ሁሉ እውነተኛውን መልስ የመስጠት ግዴታ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ በቁ 30(2) ላይ ተጥሎባቸዋል።

 

የዝምታ መብት፡- ይህ መብት ያላቸው ምስክሮችም ሁሉም ፖሊስ ዘንድ የቀረቡ ምስክሮች ሳይሆኑ የሚሰጡት መልስ በወንጀል ሊያስከስሳቸው የሚችሉት ምስክሮች ብቻ ናቸው። የዝምታ መብታቸውን እየተተቀሙ መሆኑን በዝምታ ከመግለፅ ይልቅ “ምላሽ አልሰጥም” ብለው እምቢታቸውን መግለፅ ይችላሉ።

 

የመመስከር መብት፡- ሌላው ደግሞ ፖሊስ በምስክርነት የጠራቸው ሰዎች በምርመራ ላይ ስላለው ጉዳይ በራሳቸው ፍቃድ መልስ አልሰጥም ካሉ በኋላም ቢሆንለ መናገር ዝግጁ መሆናቸውን ከገለፁና ቃላቸውም እንዲመዘገብላቸው ከጠየቁ ፖሊስም ሆነ ማንኛውም ሰው ሊከራከራቸው እንደማይችል በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 31(2) ላይ ተደንግጓል።

 

ምስክርነት በፍ/ቤት፡- ምስክሮች በሁለት አይነት ሁኔታዎች በፍ/ቤት ሊቀርቡ ይችላሉ። በቀዳሚ ምርመራ ፍ/ቤት እና በመደበኛው ጉዳዩን በሚያስችለው ፍ/ቤት ነው።

 

የቀዳሚ ምርመራ፡- ቀዳሚ ምርመራ የሚባለው በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 80 እና ተከታዮቹ መሰረት በከፍተኛው ፍ/ቤት ቀርበው የሚታዩ ከባድ የግፍ አገዳደል እና የከባድ ውንብድና ወንጀሎች እንዲሁም ዐቃቤ ሕግ ቀዳሚ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ የሰጠባቸው በከፍተኛው ፍ/ቤት የሚታይ ጉዳዮች ወንጀሉ በተፈፀመበት አካባቢ በሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሚታይበት ስነሥርዓት ነው። ምስክሮች በዚህ ሂደት ውስጥም በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 84 መሰረት እንዲቀርቡ ሊዝዙ ይችላሉ። ምስክሮቹ በዐቃቤ ሕግ የማስረጃ ዝርዝር ውስጥ ባይካተቱም ፍ/ቤቱ አስፈላጊ መስሎ ከታየው በማንኛውም ጊዜ ማንኛውንም ምስክር ጠርቶ እንዲመሰክር የማዘዝ ስልጣን አለው። ምስክሮች በቀዳሚ ምርመራ ፍ/ቤት በሚቀርቡበት ጊዜ የሚሰጡት እያንዳዱ ቃል ለየብቻው በወረቀት ላይ ተመዝግቦ የሚቀመጥ ነው። በተጨማሪም ፍ/ቤቱ የተከሳሽን ስለክሱ የሚሰጠውን ቃል ከሰማ በኋላ የሚያቀርባቸውን የመከራከሪያ ምስክሮች ዝርዝር ከነአድራሻቸው እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ይሰማል።

 

ምስክሮች በየትኛውም ደረጃ እውነተኛውን ቃል ብቻ የመመስከር ግዴታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በቀዳሚ ፍ/ቤት የቀረቡ ምስክሮች የሚከተለው ግዴታ አለባቸው።

 

ሲጠሩ ለመቅረብ ዋስ መጥራት፡- በቀዳሚ ምርመራ ፍ/ቤት የቀረቡ ምስክሮች ድጋሚ ሲጠሩ የመቅረብ ግዴታ አለባቸው። ይህንም በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 90(1) መሰረት የራስ ዋስትና ወረቀት በመፈረም ለፍ/ቤቱ ማረጋገጥ አለባቸው።

 

የራስ ዋስትና ለመፈረም ፍቃደኛ ያልሆነ ምስክር ደግሞ ፈቃደኛ እስከሚሆን ድረስ ወይም ክሱ በመደበኛው ፍ/ቤት እስከሚታይበት ጊዜ ድረስ የቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍ/ቤት በቁ 90(2) መሰረት በማረፊያ ቤት እንዲቆይ የማዘዝ ስልጣን ስላለው ምስክሮች ፍ/ቤቱ በሚጠይቀው መልኩ በቀጣይ ቀጠሮ ለመቅረብ ፍቃደኛነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው።


 

በመደበኛ ችሎት

የክሱ መስማት ከተጀመረ በኋላ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ124 መሰረት ምሰክሮች ክሱ በሚሰማበት ቀነ ቀጠሮ እንዲቀርቡ መጥሪያ ይደርሳቸዋል። የመጀመሪያው የምስክሮች ግዴታ የመጥሪያውን ትዕዛዝ አክብረው መቅረብ ነው። ሆኖም መጥሪያ መድረሱ ተረጋግጦ ምስክሩ ሳይቀርብ ከቀረ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 125 መሰረት በፖሊስ ታስረው እንዲቀርቡ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ይሰማል። በመሆኑም ምስክሮች ከአቅም በላይ ካልሆነባቸው በስተቀር ከማንኛውም ጉዳይ ቅድሚያ የፍ/ቤቱን ጥሪ አክብረው በቀኑና በሰዓቱ በአካል ከችሎት መቅረብ አለባቸው።

 

ከዚያም ክሱ ከተሰማ በኋላ ፍ/ቤቱ ምሰክሮች እንዲቀርቡ ሲጠሩ ምስክሮች የተጠሩት በማን ጉዳይ መሆኑን በዐቃቤ ሕግ ምሰክርነት ይሁን በተከሳሽ የመከላከያ ምስክርነት አጣርተው በማረጋገጥ ፍ/ቤቱ ስለማንነታቸው ለሚያቀርብላቸው ጥቄ ትክክለኛውን ምላሽ መስጠት አለባቸው።

 

መሃላ፡- የምስክሮቹ ማንነት ከተጣራ በኋላ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 136(2) መሰረት መሃላ መፈፀም አለባቸው። የመሃላ አላማ እውነቱን እንደሚናገሩ ማረጋገጫ ሲሆን መሃላ መማል የማይችሉበት ምክንያት ካላቸው ደግሞ እውነቱን እንደሚናገሩ በመግለፅ ለፍ/ቤቱ ማረጋገጥ አለባቸው።

 

ዋና ጥያቄ፡- በመጀመሪያ በዐቃቤ ሕግ በኩል ለቀረቡት ምስክሮች የሚቀርብ የጥያቄ አይነት ሲሆን በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ ውሳኔ ስለሚሰጥበት ፍሬ ነገር ምስክሩ በቀጥታ ወይም ቀጥታ ባልሆነ መንገድ የሚያውቃቸውን ነገሮች እንዲገልፅ የሚጠየቅበት ሲሆን በዚህ ጥያቄ ላይ መሪ ጥያቄ የሚባሉት እንዲህ እንዲህ ሆኗል ወይስ አልሆነም? የሚሉ ጥያቄዎችን እንዲጠይቅ አይፈቅድም።

 

ሆኖም ተከራካሪው ወገን ዐቃቤ ሕግ ወይም ተከሳሽ ወይም ጠበቃው ከፈቀደ መጠየቅ ይችላል።

 

መስቀለኛ ጥያቄ፡- መስቀለኛ ጥያቄ ዋና ጥያቄ ካበቃ በኋላ ምስክሩ የሰጠው ቃል የሚያጠራጥር ወይም ስህተት መሆኑን ለፍ/ቤቱ በመግለፅ ለማስተባበል የሚደረግ ቀደም ብሎ በዋና ጥያቄ ምሰክሩ የሰጠውን መልስ ለማውጣጣት የሚደረግ የአውጫጭኝ ጥያቄ ነው። በዚህ የጥያቄ ሂደት ላይ ምስክሩን መሪ ጥያቄ መጠየቅ ይችላል።

 

ድጋሚ ጥያቄ፡- ደግሞ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ ወይም ጠበቃው በመስቀለኛ ጥያቄ የተነሳውን ነገር ለማጣላት የሚያቀርቡት ጥያቄ ነው።

 

ምስክሮች በመጥሪያው መሰረት ችሎት ላይ ከቀረቡ በኋላ ቀጠሮ ሊለወጥ ይችላል። ወይም ደግሞ ፍ/ቤቱ የምስክርነት ቃላቸውን በድጋሚ ለመስማት በተለያዩ ሁኔታዎች በድጋሚ ሊጠሩ ይችላሉ። በመሆኑም ድጋሚ ቢጠሩም ቀርበው ተገቢውንና እውነተኛውን የምስክርነት ቃላቸውን መስጠት ግዴታ አለባቸው።

 

የሀሰት ምስክርነት፡- የምስክሮች ዋነና ግዴታ እውነቱን መናገር ነው። በመሆኑም ይህን አላማ ለማሳካት የሀሰት ምስክርነት በወንጀል የሚያስቀጣ መሆኑ ተደንግጓል። በወንጀል ሕግ አንቀፅ 453 መሰረት በምስክርነት የዳኝነት ወይም የዳኝነት ነክ ሥርዓት በሚካሄድበት ጊዜ ቀርቦ አንዱን ተከራካሪ ለመጉዳት ወይም ለመጥቀም አስቦ ሀሰተኛ ምስክርነት የሰጠ፣ ሀሰተኛ የልዩ የሙያ አዋቂነት አስተያየት የሰጠ ወይም እውነቱን ደበቆ ሰው ሃሳቡ ባይሳካም እንኳን በቀላል እስራት ወይም ነገሩ ከባድ ሲሆን በአምስት ዓመት ፅኑ እስራት ያስቀጣል።

 

ሆኖም ምስክሩ የሀሰት ምስክርነት የሰጠው ምሎ ወይም ማረጋገጫ ሰጥቶ ሃሳቡም በከፊል ተሳክቶ ከሆነ ቅጣቱ ከአስር አመት የማይበልጥ ፅኑ እስራት ነው። የሀሰት ምስክርነቱ ከአስር አመት በላይ ጥፋተኛ ያልሆነው ሰው እንዲቀጣ ካደረገ ቅጣቱ የሀሰት ምስክርነቱ ያስከተለውን ቅጣት ያህል ነው።

 

ምስክሩ በወንጀል ሕግ 454 መሰረት የሀሰት ምስክርነቱን ከሰጠ በኋላ ጉዳዩ የመጨረሻ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት በነፃ ፍቃድ ቃሉን አቃንቶ ወይም ለውጦ ከሆነ ፍ/ቤቱ በመሰለው መንገድ ቅጣቱን ሊያቀልለት ይችላል።

                        ለዛሬ በዚህ ይብቃን

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
10777 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 975 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us