የተከለከሉ አነጋገዶች

Wednesday, 31 December 2014 13:19

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-          የንግድ ማስታወቂያ ምን መሟላት አለበት?

-          በንግድ ሥራ ውስጥ ነጋዴዎች እንዳይፈፅሟቸው የተከለከሉ ተግባራት፣

-          የገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ላይ ጉድለት ያገኘ ሸማች ምን መብት አለው?

-          የተከለከሉ የንግድ አሰራሮችን መተግበር የሚስከትለው አስተዳደራዊ ቅጣትና የወንጀል ኃላፊነት ምን ይመስላል፣

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? ባለፈው ሁለት ሳምንታት የሸማቾች ጥበቃና የንግድ አሰራር አምድ ቁጥር 813/2006 ላይ ለሸማቾች የተሰጡ ጥበቃዎችና መብቶች እንዲሁም ጤናማ የንግድ ውድድርን ለማጠናከር ነጋዴው ላይ የተጣሉ ግዴታዎችን ተመልክተናል። በዛሬው ፅሐፌ ደግሞ ሌሎች ባለፈው ያላነሳናቸውን በዋነኝነት ነጋዴው እንዳይፈፅማቸው የተከለከሉ የንግድ አሰራሮችን፣ ሸማቾች ጉድለት ያለበት ዕቃ ወይም አገልግሎት ሲያጋጥማቸው ያላቸውን መብትና ሕጉን አለማክበር ነጋዴው ላይ የሚያስከትለውን ኃላፊን እንመለከታለን፡-

 1.  ንግድ ማስታወቂያ፡- “ጥሩ ዕቃ ማስታወቂያ አያሻውም” ይባላል ነበር ድሮ። አሁን ግን የንግድ ሥራው እየተስፋፋ ሲሄድ ነጋዴው ለሥራው ከሚበጅተው በጀት ክፍሎች አንዱ ማስታወቂያ ነው። የንግድ እቃው ወይም አገልግሎቱን ሽያጭ ለማብዛት ማስታወቂያን ይጠቀማል። አጠቃላይ ማስታወቂያ የሚመራበት ራሱን የቻለ አዋጅ አለ። ሸማቾችን ከመጠበቅና ጤናማ የንግድ ውድድርን ከማስፈን አንፃር ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 813/06 አንቀፅ 19 ላይ የንግድ ማስታወቂያዎች ምን አይነት መሆን እንዳለባቸው ተደንግጓል። ሁሉም አይነት የንግድ ማስታወቂያዎች የሚከተሉት ጉዳዮችን በተመለከተ ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መሆን የለባቸውም።

የዕቃውን አይነት፡- ማንኛውም ሸማች ለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት አስፈላጊ የሆነውን ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብቱ ተጠብቋል። ይህን እውን ለማድረግ ነጋዴው ደግሞ በማንኛውም መንገድ እቃውን በሚያስተዋውቅበት ጊዜ የዕቃውን ባህሪ (ተፈጥሮውን) ውህድ ወይም ውስዊ ይዘቱንና መጠኑን በትክክል መግለፅ አለበት። “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” እንደሚባለው በማስታወቂያ የተባለለትን የሚሸጠው እቃ ለየቅል መሆን የለባቸውም። በተጨማሪ የዕቃውን ምንጭ ክብደት፣ መጠን፣ የአመራረት ዘዴ፣ የማምረቻ ቀን፣ አገልግሎቱ የሚያበቃበትን ቀን እና አጠቃቀሙን በተመለከተ የሚገልፁ መረጃዎች እውነትና እውነት ብቻ መሆን አለባቸው።

ከዕቃው ወይም ከአገልግሎቱ ጋር የተያያዙ መረጃዎች፡- ማስታወቂያው የዕቃውን አምራች ወይም የአገልግሎቱን አቅራቢ አገልግሎቱ የሚሰጥበትን ቦታ መሠረታዊ ባህሪ የአገልግሎቱን ጥቅምና አጠቃቀም። የግዢ ሁኔታው (ዱቤ፣ ቅናሽ የመሳሰሉትን፣ ከግዢ በኋላ የሚሰጥ አገልግሎት (ጥገና ፣ መለዋወጫ) ፣ ከዋስትና ዋጋና የክፍያ ሁኔታ ጋር የሀሰት መረጃዎች መስጠት የለበትም።

በተጨማሪ የጥራት ምልክቶች፣ የንግድ ምልክትን እና አርማን እና ዕቃውን ወይም አገልግሎቱን በመጠቀም የሚጠበቅ ውጤትን በተመለከተም ነጋዴው በሚለቀው ማስታወቂያ የተሳሳተ መረጃ መስጠት የለበትም።

 1. ለነጋዴዎች የተከለከሉ ድርጊቶች

አዋጅ ቁጥር 813/06 ለሸማቾች ጥበቃና መብት መስጠትና የገበያውንም ጤናማነትም ሆነ የሸማቾችን ደህንነት ለመጠበቅ የተቀመጡ የነጋዴው ግዴታዎችን ብቻ ሳይሆን ነጋዴው እንዳይፈፅማቸው በግልፅ የተቀመጠ ክልከላዎችን በአንቀፅ 22 ላይ በዝርዝር አስቀምጧል በተወሰኑ ጎራዎች ክፋፍለን ክልከላዎችን እንመልከት።

ትክክለኛ መረጃ፡- ነጋዴው ላይ ከተጣሉበት ግዴታዎች አንዱ ለሸማቹ ስለእቃው ወይም ስለአገልግሎቱ በቂ እና ትክክለኛ መረጃ መስጠት ነው። በንግድ ማስታወቂያ ላይም ይሄው ግዴታ ተጥሎበታል። በተጨማሪ ክልከላዎችን በዘረዘረው የአዋጁ አንቀጽ 22 ስር ከተዘረዘሩት የተከለከሉ የንግድ ድርጊቶች አብዛኛዎቹ ስለንግድ እቃዎችና አገልግሎቶችን የሚመለከቱ መረጃዎች ናቸው።

-          የዕቃውን ወይም የአገልግሎቱን መሠረታዊ መረጃዎች በሚመለከት

-          ጥራትን፣ መጠንን፣ ብዛት፣ ተቀባይነት፣ ምንጭ፣ ባህሪ ውህድ ወይም ጥቅም የተሳሳተ መረጃ መስጠት

-          የንግድ እቃዎችን ሞዴል፣ አዲስ የተሰሩ፣ የተለወጡ እንደገና እንደ አዲስ የተሰሩ ወይም ያገለገሉ ስለመሆናቸው ወይም በአምራቹ እንዲሰበሰቡ የተባሉ ስለመሆናቸው በትክክል አለመግለፅ፣

-          ተገቢ የንግድ ውድድርን ከመጠበቅ አንፃር የሌላውን ነጋዴ እቃ ወይም አገልግሎቶች በአሳሳች ሁኔታ የራስ አስመስሎ ወይም በአሳሳች ሁኔታ መግለፅ፣

-          ስለዋጋ ቅነሽ ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መረጃ ማስተላለፍ፣

-          የንግድ ዕቃው የሚያስፈልገው ጥገና ወይም የሚተኩ ክፍሎቹ እንደሚያስፈልጉት አድርጎ ማቅረብ፣

-          የንግድ እቃዎች የተሰሩበትን ሀገር አሳስቶ መግለፅ ስለንግድ እቃ ወይም አገልግሎት ነጋዴው የሚሰጠው መረጃ ላይ እንዳይፈፅማቸው የተከለከሉ ተግባራት ናቸው።

ሽያጭን በተመለከተ ለነጋዴው የተከለከሉ ተግባራት፡- ነጋዴው ዕቃውን ወይም አገልግሎቶቹን በሚሸጥበት ጊዜ የሚከተሉትን እንዳይፈፅም ተከልክሏል።

-          ማስታወቂያው ሌላ ሽያጩ ሌላ እንዳይሆን ነጋዴው በማስታወቂያ ባስነገረው መልኩ አለመሸጥ አይችልም።

-          ማስታወቂያው የመጠን ውስንነት መኖሩን ካልገለፀ በቀር ሸማቾች በሚፈልጉት መጠን ልክ አለመሸጥ፣

-          ማንኛውደንም አገልግሎት የመስጠት ሥራን በንግድ ሥራው ከሚታወቀው ደረጃ በታች ወይም ባልተሟላ ሁኔታ መስጠት፣

-          የሸማቹን መብት ለመጠበቅ ሲባል ካልሆነ በቀር የንግድ እቃን ወይም አገልግሎትን አልሸጥም ማለት፣

-          የንግድ እቃው ወይም በንግድ መደብሩ ከተለጠፈው ዋጋ አስበልጦ መሸጥ፣

-          አንድን የንግድ እቃ ወይም አገልግሎት ለመሸጥ ሸማቹ ያልፈለገውን ሌላ የንግድ እቃ ወይም አገልግሎት አብሮ እንዲገዛ ማስገደድ።

ሀቀኛ የንግድ አሰራርን መተመለከተ፡- ከንግድ እቃ ወይም ከአገልግሎት ሽያጭ ጋር በተያያዘ የተገባ የዋስትና ግዴታን አለመወጣት፣

-          በንግድ ዕቃ ወይም የአገልግሎት ግብይት ማንኛውንም የማጭበርበር ወይም የማደናገር ተግባር መፈፀም፣

-          በሸማቾች መካከል ተገቢ ያልሆነ አድልዎ መፈፀም የተከለከሉ ተግባራት ናቸው፣

የተጠቃሚዎች ደህንነት የዕቃ ጥራት እና መጠንን በተመለከተ፡-

ሕገወጥ በሆነ ማንኛውም የመለኪያ መሳሪያ መጠቀም ጥራትን በተመለከተ የደረጃዎች ማህተም መጠቀም የሚያስፈልጋቸው የንግድ እቃዎች ወይም አገልግሎቶችን ያለደረጃ ማህተም ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ፣

የሸማቾችን ጤናና ደህንነት በተመለከተ ደግሞ ለሰው ጤናና ደህንነት አደገኛ የሆነ፣ ምንጩ ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃው የወረደ፣ የተመረዘ፣ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈ ወይም ከባእድ ነገሮች ጋር የተደባለቀ የንግድ እቃን ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ ለነጋዴው የተከለከለ ነው።

ፒራሚዳዊ የሽያጭ ስልት፡- ይህ የንግድ ስልት አንድ ሸማች የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት በመግዛቱ ወይም የገንዘብ መዋጮ በማድረጉ እና በሸማቹ አሻሻጭነት የንግድ እቃዎችን ወይም አገልግሎቱን የሚገዙ ወይም የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉ ከሆነ ወይም በሽያጭ ስልቱ ውስጥ የሚገቡ ከሆነ በሸማቾቹ ቁጥር ልክ የገንዘብ ወይም የአይነት ጥቅም እንዳያገኝ የሚገልፅ ስልት ሲሆን በተለያዩ ኩዌስት ማርኬቲንግ ተብሎ የሚታወቀው የአሻሻጭ ዘዴን ጀምሮ ሸማቹን እንደአሻሻጭ የሚጠቀም ስልት ተግባራዊ ማድረግ ወይም ለማድረግ መሞከር ተከልክሏል።

 1. ማከማቸትና መደበቅ

በገበያ ውስጥ በአቅርቦትና ከፍላጎት ጋር አለመመጣጠን ጋር ባልተያያዘ የንግድ እቃዎች እጥረት ከሚፈጠርበት ምክንያቶች አንዱ ዋጋ ለማናር ወይም ጊዜ ጠብቆ በውድ ዋጋ ለመሸጥ በገበያ ላይ የሚፈለጉ እቃዎችን የማከማቸት ተግባር ነው። በአዋጁ አንቀጽ 24 ላይ ነጋዴም ሆነ ነጋዴ ያልሆነ ሰው በገበያ ላይ እጥረት እንዳለ የንግድ ሚኒስቴር በህዝብ ማስታወቂያ የተገለፀ የንግድ እቃን ነጋዴ ከሆነ ከመደበኛ የግብይት አሰራር ውጭ ነጋዴ ካልሆነ ደግሞ ለግል ወይም ለቤተሰብ ፍጆታ ከሚውል መጠን በላይ ማከማቸት ወይም መደበቅ ተከልክሏል፤፤

የንግድ እቃ ከመደበኛ የግብይት አሰራር ውጭ ተደብቋል ወይም ተከማችቷል የሚለው ግምቱ ከነጋዴው ካፒታል 25 በመቶ የሚያንስ ሲሆንና ከውጭ ከመጣ አስመጪው ለቀጣይ ምርት በጥሬ እቃ ወይም በግብአት የሚጠቀምበት ካልሆነ የጉምሩክ ፎርማሊቲን አጠናቆ በ3 ወር ውስጥ ለሽያጭ ካላቀረበው አገር ውስጥ የተመረተ የንግድ ዕቃ ከሆነ አምራቹ ራሱ ለቀጣይ የምርት ሂደት በጥሬ እቃነት ወይም በግብአትነት የሚጠቀምበት እቃ ካልሆነ ከተመረተበት ቀን ጀምሮ በሁለት ወር ውስጥ ለሽያጭ ካልቀረበ በሕገወጥ መልኩ እንደተከማቸ ወይም እንደተደበቀ ይቆጠራል።

የንግድ እቃው በጅምላ ሻጭ ወይም በችርቻሮ ሻጭ የገዛ ከሆነ እቃው ከተገዛበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ ከነጋዴው ካፒታል 25 በመቶ የሚያንስ ከሆነ ለሽያጭ ካልቀረበ እንደተከማቸ ይቆጠራል።

ከላይ የጠቀስናቸው የማከማቸት ወይም የመደበቅ መስፈርቶች ባይሟሉም ከተፈቀደው የስርጭት መስመር ውጭ በማንኛውም ማጓጓዣ ቢጓጓዝ የተገኘ የንግድ እቃ እንደተከማቸ ወይም እንደተደበቀ ይቆጠራል። ከግል ወይም ከቤተሰብ ፍጆታ ውጭ ነጋዴ ያልሆነ ሰው የንግድ እቃ ከተፈቀደው የስርጭት መስመር ውጭ ማጓጓዝም ክልክል ነው።

 1. ከሸማቹ ምን ይጠበቃል?፡- ማንኛውም ሸማች በአዋጅ አንቀፅ 20 መሠረት በገዛው እቃ ወይም አገልግሎት ጉድለት ሲያገኝ ጉድለቱንና ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለንግድ ሚኒስቴሩ ወይም ለሚመለከተው የንግድ ቢሮ ማሳወቅ ይቻላል።

ለሸማቹ የበለጠ የሚጠቅሙ ዋስትናዎች ወይም የሕግ ወይም የውል ግዴታዎች እንደተጠበቀ ሆኖ ሸማቹ ጉድለቱ የተገኘው የንግድ እቃው ላይ ከሆነ እቃው እንዲለወጥለት ወይም ዋጋው እንዲመለስለት ወይም ጉድለቱ አገልግሎት ላይ ከሆነ አገልግሎቱ በድጋሚ ያለክፍያ እንዲሰጠው ወይም የአገልግሎት ክፍያው እንዲመለስለት ግዥው በተፈፀመ በ15 ቀናት ውስጥ ሻጩና መጠየቅ ይችላል።

ሻጩ በጥያቄው መሠረት ጉድለቱን ባለማሟላቱ ሸማቹ ለሚደርስበት ማንኛውም ጉዳት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ካሳ የመጠየቅ መብት አለው። ሸማቹ በአዋጁ የተሰጡትን መብቶች ለመተው ከነጋዴው ጋር የሚያደርገው ውል በሕግ ተቀባይነት የለውም።

 1. ተቆጣጣሪና የዳኝነት አካላት፡- በአዋጅ ቁጥር 813/06 አንቀፅ 27 የፌዴራል የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ለንግድ ሚኒስቴር ተጠሪ ሆኖ ተቋቁሟል። ባለሥልጣኑ የፌዴራል ደረጃ የሸማቾችን ጥበቃና የንግድ ውድድርን በተመለከተ የሚቀርቡ ክሶችን የሚዳኙ አስተዳደራዊ ውሳኔ የሚሰጡ ዳኞችን ክስ የሚመሰርቱ መርማሪዎችና ዐቃቤ ሕጎች አሉት። ክልሎችም የየራሳቸውን የዳኝነት አካልና ይግባኝ ሰሚ አስተዳደራዊ ፍ/ቤት ማቋቋም ይችላሉ።
 1. ሕጉን አለማክበር የሚያስከትለው ኃላፊነት፡-

አስተዳደራዊ ፍ/ቤቶች በዚህ አዋጅ ላይ የተደነገጉትን ሕጎች መጣሳቸውን አጣርተው የተለያዩ የማስተካከያ ትዕዛዞችንና የገንዘብ መቀጮዎችን ሕጉን በጣሱት ላይ የሚወስኑ ሲሆን ነጋዴው የተጣለበትን አስተዳደራዊ እርምጃ ወይም የቅጣት ውሳኔ ካላከበረ በወንጀል ጥፋተኛ በአዋጁ አንቀፅ 43 መሰረት ከአንድ አመት እስከ አምስት ዓመት እስር ይቀጣል።

ነጋዴው የተከለከለው ፒራሚዳዊ የሽያጭ ስልት ከተገቢ ወይም ለሰው አደገኛ የሆኑ እቃዎችን ዓመታዊ ሽያጩ ከ7 -10 በመቶ የገንዘብ ቅጣት እና ከአንድ እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እስራት ይቀጣል።

ሌሎች የተከለከሉ ድርጊቶችን መፈፀም ነጋዴውን ከአመታዊ ሽያጭ ከአምስት እስከ አስር በመቶ የገንዘብ ቅጣት እና ከአንድ እስከ አምስት ዓመት ፅኑ እስር ይቀጣል። ከነጋዴው በተጨማሪ ተሸከርካሪው እና ባለቤቱም የተደበቀ ወይም የተከማቸ መሆኑን እያወቀ አገልግሎቱን ከሰጠ ከገንዘብ ቅጣት አንስቶ ተሽከርካሪውን የመውረስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ሸማቾችም መብታችንን አውቀንና አስከብረን ነጋዴዎችንም ሕጉን አክብረን የምንገበያየው መልካም ግብይት እንዲኖረን እመኛለሁ።

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
7729 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 933 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us