ሳምንታዊ የሥራና የእረፍት ጊዜ

Wednesday, 14 January 2015 12:42

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. '; document.write(''); document.write(addy_text52856); document.write('<\/a>'); //-->\n This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-          በቀን ውስጥ በሥራ ማሳለፍ ያለብን ከፍተኛው የሥራ ሰዓሰት ምን ያህል ነው?

-          የሳምንቱ የሥራ ቀናት የሥራ ሰዓት ድልድል ምን መሆን አለበት?

-          የሳምንት እረፍትና የትርፍ ሰዓት ሥራ በምን መልኩ እንዲሆኑ ሕግ ያስገድዳል

-          በትርፍ ሰዓት ክፍያና በሳምንት እረፍት መስራትን የሚመለከቱ እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት የደረሰ ክርክሮች ላይ ምን ተወሰነ?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው። ስለሥራ ሰዓትና ስለእረፍት ነው የምናጣቅሰው በመንግስት ሰራተኞች አዋጅ የማይተዳደሩና ራሱን በቻለ ሕግ የማይታቀፉ ሠራተኞችን የሚመለከተውን በአዋጅ ቁጥር 377/96 የሚታቀፉትን በግለሰብ፣ በግል ወይም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ በሥራ ውል ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞን ነው። በቅድሚያ ከስራ ሰዓትና ከእረፍት ጋር በተያያዘ እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የደረሰ ክርክሮችን እናንሳ።

 1. በቀን 16 ሰዓት ማሰራት፡-

ሳሙኤል ተፈራ እና ሶስት የሥራ ባልደረቦቹ በሜታ አቦ ቢራ አክስዮን ማህበር በህክምና ሙያ ተቀጥረው ይሰሩ ነበር። ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መስሪያ ቤታቸውን ከፅሁፍ ስራ ጋር የተቋረጠባቸው ክፍያ፣ በሽፍት (በፈረቃ) ላሰሩን ሥራ የሚገባቸውን ክፍያ የአልጋ ክፍያ እንዲከፈላቸውና የፅዳት ሰራተኛ እንዲመደብላቸው እንዲወሰንላቸው ክስ አቀረቡ።

ሜታ ለቀረበበት ክስ በሰጠው ቢራ አምርቶ የሚሸጥ መሆኑን ገለፀ። ከሳሾች ስራቸው የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ መስጠት ነው። በስራ ድልድሉ መሠረት እሁድ የስራ ሰራተኛ በቀጣዩ ቀን 24 ሰዓት እረፍት ይሰጠዋል። በሳምንት 48 ሰዓት ነው የሚሰሩት። ስለዚህ የትርፍ ሰዓት ክፍያ አይገባቸውም። በፈረቃ ለሚሰራ ሰራተኛ የአልጋም ሆነ የእራት ክፍያ የሚፈፀምበት የሕግ አግባብ የለም። የህክምና መሳሪያቸውን የማፅዳት ኃላፊነት ስላለባቸው የፅዳት ሠራተኛ ልመድብ አይገባም።

ፍ/ቤት በሰጠው ውሳኔ በሳምንት 48 ሰዓት እየሰሩና እሁድ ከሰሩ በቀጣዩ ቀን 24 ሰዓት ካረፋችሁ በሽፍት በመስራታቸው ብቻ ክፍያ መጠየቃቸውና የፅዳት ሰራተኛ ይመደብልን የሚሉበት የሕግ መሰረት የለም በሚል ክሳቸውን ውድቅ አደረገው። እነ ሳሙኤል በፍ/ቤቱ ውሳኔ ቅር ተሰኝተው ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔው እንዲሻር ይግባኝ አቀረቡ። ፍ/ቤቱም የይግባኝ ክርክሩን ሰምቶ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 61(1) የማንኛውም ሰራተኛ የሥራ ሰዓት በቀን ከስምንት ወይም በሳምንት ከ48 ሰዓት አይበልጥም ስለሚል እነ ሳሙኤል ቅሬታ ያቀረቡት በሳምንት ከ48 ሰዓት በላይ ሰራን ብለው ሳይሆን በቀን 16 ሰዓት ሰራን ነው። ስለዚህ ለሰራተኛው በቀን ከ8 ሰዓት በላይ መስራት ግዴታ ባለመሆኑ በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ እንዲሰሩ ሜታ አቦ ጊዜውን ማመቻቸት አለበት ሲል ወሰነ።

ሜታ አቦ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ሲል ለሰበር አቤቱታ አቀረበ። ሰበርም ክርክሩንና የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል። ከውሳኔው በፊት አንድ ሌላ ክርክር ልጨምር።

 1. በሰንበት ማሰራት ይፈቀዳል?

አቶ አብዮት አለማየሁ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ በሚባል ድርጅት ውስጥ ሲሰሩ ነበር። እንደለመዱት ማረፊያዬ ሃይማኖታዊ ማህበራዊ ጉዳዬን የምፈፅምበት እሁድ መጣልኝ እያሉ ሲጠብቁ አለቃቸው እሁድ አስቸኳይ ስራ ስላለ ወደ ሥራ እንድትገባ ይላቸዋል። አቶ አብዮት እሁድ የመስራት ግዴታማ የለብኝም ብለው ከስራ ይቀራሉ። በዚህ ምክንያት መስሪያ ቤታቸው ከስራ አባረራቸው። ከሥራ የተሰናበትኩት ያለአግባብ ነው፤ በሕጉ ላይ የተቀመጡ የተለያዩ ክፍያዎች ይከፈሉኝ ሲሉ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አሰሪያቸውን ከሰሱ።

አለማየሁ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ለክስ ለሰጠው መልስ አስቸኳይ ስራ አለ እሁድ ግባ ብንለው እምቢ ብሎ በመቅረቱ ስራ ላይ ጉዳት ስላደረሰ ነው ያባረርኩት ሲል መልስ ሰጠ። ፍ/ቤቱም እንዲያማ ከሆነ በእሁድ ካልሰራው ብለህ ማባረረህ ከሕግ ወጭ ነው ስላመንክ ሌላ ማስረጃም መስማት አያስፈልግም ብሎ የተለያዩ ክፍያዎች ለአቶ አብዮት እንዲከፍል ወሰነ።

አሰሪው ይግባኝ ለከፍተኛው ፍ/ቤት ቢያቀርብም የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ስላፀናበት የሕግ ስህተት ተፈፅሟል፣ ውሳኔው ስህተት ነው በሚል ለሰበር አቤቱታ አቀረበ። ሰበርም አስፈላጊ በሚሆን ጊዜ ሰራተኛውን በሳምንት የእረፍት ጊዜው ማሰራት ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለውን ነጥብ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል። እስቲ ጉዳዩን የሚመለከቱ የሕግ አንቀጾችን እንይ፡-

 1. የሥራ ሰዓት፡-

“እኔ እስካልደከመኝ ወይም በቃኝ እስካላልኩ የፈለኩትን ያህል ብሰራስ? የሚል ይኖራል። ዝቅተኛው የቀንና የሳምንት የሥራ ሰዓት ለሰራተኞች የተደነገገው ግን ያለ ምክንያት አልነበረም። በተለይ በአውሮፓ ሀገራት የኢንዱስትሪው አብዮት ጊዜ የተለያዩ ፋብሪካዎችና የምርት ተቋማት በባለሀብቶች እየተቋቋሙ ስራው ጠፋ። ይሄኔ የባለሀብት ዋናው መገለጫ ወጪውን መቀነስ ትርፉን ማብዛት ነውና። ሰራተኞች በየቀኑ ያለ በቂ እረፍት እንዲሰሩና ምርታቸው እንዲያድግ ማድረግ ጀመሩ። ሰራተኛውም በሰዓት የምትከፈለውን አነስተኛ ገቢ ለማግኘት እየተስማማ መስራት ቀጠለ። ይሄ ግን የሰራተኞች ጤና ምርታማነት እና ያገልግሎት ዘመን ላይ የራሱን ጫና ማሳደር ጀመረ። ይህን ለመከላከል የዓለም የስራ ድርጅት አባል ሀገራት አሰሪውና ሰራተኛውንም የማይጎዳ ዝቅተኛ መሟላት ያለባቸው የሥራ ሁኔታዎች እንዲኖሩ ለተለያዩ ስምምነቶች ተደረጉ። ሀገራትም በገቧቸው አለማቀፋዊ ግዴታዎች መሠረት ሕጎቻቸው ከነዚህ ስምምነቶች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ አደረጉ። አዋጅ ቁጥር 377/96 በመግቢያው ላይ የአሰሪና ሰረተኛ ጉዳይ አዋጁ ሀገራችን ከፈረመቻቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖች ጋር የተጣጣመ ሕግ መሆኑን ይጠቅሳል።

የስራ ሰዓት እና የእረፍት ጊዜ በአዋጁ አንቀፅ 2(5እና6) የሥራ ደንብ (አሰሪውና ሰራተኛው የሚመሩበት የውስጥ ደምብ) እና የሥራ ሁነታ አሰሪና ሰራተኛውን መካከል ያለጠቅላላ ግንኙነት) ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።

የሥራ ሰዓት በአዋጁ አንቀፅ 61 ላይ የቀንና የሳምንት ጣሪያው ተደንግጓል። በመሆኑም መደበኛው የሥራ ሰዓት በቀን ከስምንት ሰዓት ወይም በሳምንት ከአርባ ስምንት ሰዓት አይበልጥም። መደበኛ የሥራ ሰዓት የሚባለው በሕግ በሕብረት ስምምነት (የሠራተኞች ማህበር ከአሰሪው ጋር የሚያደርገው ስምምነት) ወይም ከስራ ደንብ (አሰሪውና ሰራተኛው የሚመሩበት የመስሪያ ቤቱ የውስጥ መመሪያ) ላይ ሰራተኛው ስራውን የሚያከናውንበት ወይም በስራ የሚገኝበት ጊዜ ነው።

እነኚህን አንድ ሰራተኛ በቀን ወይም በሳምንት እንዲሰራ ከሚፈቀድለት መደበኛ የስራ ሰዓት ጣሪያ በላይ ሰራተኛው ቢፈቅድም እንኳን ማሰራት አይቻልም። በውስጥ የስራ ደምብም ሆነ በህብረት ስምምነት በሕግ ከተቀመጠው ጣሪያ በላይ መደበኛ የቀን ወይም የሳምንት የስራ ሰዓት ማሰራት አይፈቀድም።

ሆኖም ግን በአዋጅ አንቀፅ 63 እና 64 ላይ እንደተቀመጠው የቀኑንም ሆነ የሳምንቱን መደበኛ የስራ ሰዓት ማደላደል ይቻላል። የየቀኑን መደበኛ የስራ ሰዓት በተመለከተ ለሳምንቱ የድርጅቱ የሥራ ቀኖች እኩል ይደለደላሉ። ይህ እንደ ስራው ጠባይ እየታየ የሚደረግ ሲሆን የስራው ባህሪ አስገዳጅ ከሆነ ሁሉም የስራ ቀናት እኩል መደበኛ የሥራ ሰዓት ባይኖቸውም ሳምንቱን የስራ ቀናተ በማሳጠር ልዩነቱን ለተቀሩት ቀኖች ማደላደል ይቻላል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የሌሎች ባንኮች የሰራተኞች የስራ ሰዓት ከሰኞ እስከ አርብ ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ቀኑ 10፡30 ሲሆን ቅዳሜ ደግሞ ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ቀኑ 6 ሰዓት ነው። በቀን 7፡30 ሰዓት ቅዳሜ 4 ሰዓት ይሰራሉ። ሌሎች አብዛኞቹ የግል ድርጅቶች ደግሞ ከጠዋቱ 2፡30 እስከ 11፡30 ከሰኞ እስከ አርብ ይሰሩና ቅዳሜና እሁድ ያርፋሉ። ይሄ እንግዲህ ድርጅቶች እንደየስራቸው ባህሪ ያደላደሉት የስራ ሰዓት ነው። ይህ ድልድል በሚደረግበት ጊዜ ግን የቀኑን መደበኛ የስራ ሰዓት በቀን ከ10 ሰዓት በላይ ማራዘም እንደማይቻል የአዋጁ አንቀፅ 63 ገደብ አሰቀምጧል።

የሳምንቱን የስራ ሰዓት ለእያንዳንዱ ሳምንት እኩል ማደላደል በስራው ሁኔታ የተነሳ ካልተቻለ የሳምንቱን የስራ ሰዓት ከ48 ሰዓት የበለጠ አድርጎ ማደላደል የሚቻል ሲሆን ዝቅተኛውን እና የከፍተኛውን የሥራ ሰዓት አማካይ በመውሰድ መደረግ ስላለበት ሰራተኛው የሰራበት አማካይ የስራ ሰዓት ግን በሕግ ከተቀመጠው የቀንና የሳምንት የስራ ሰዓት መብለጥ የለበትም። ይህ የቀንና የሳምንት መደበኛ የሥራ ሰዓት ጣሪያ የንግድ መልክተኞችና የንግድ ወኪሎችን አይመለከትም።

 1. የሳምንት እረፍት፡-

በቀን ውስጥ ካሉት 24 ሰዓታት በመደበኛ ሁኔታ በስራ እንድናካፍል የተፈቀደው 8 ሰዓቱን ሲሆን በሳምንት ካሉት 168 ሰዓታት ደግሞ በአጠቃላይ ስራ ላይ የምናሳልፈው ከፍተኛው መደበኛ የስራ ሰዓት 48 ሰዓት ነው። በአዋጁ አንቀጽ 69 መሠረት በሰባት ቀናት ጊዜ ውስጥ ያልተቆራረጠ የ24 ሰዓት የሳምንት እረፍት ለማንኛውም ሰራተኛ የተፈቀደ ሲሆን በህብረት ስምምነት በሌላ ሁኔታ እንዲሆን በአሰሪውና በሰራተኛ ማህበሩ መካከል ስምምነት ከሌለ በቀር የሳምንት እረፍት እሁድ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሰኞ ከንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ የሚቆይ መሆን አለበት። በተጨማሪም ለድርጅቱ ሰራተኞች በሙሉ በአንድ ላይና በአንድ ጊዜ የሚሰጥ ነው።

በመርህ ደረጃ በሳምንት የእረፍት ጊዜ ስራ የማይፈቀድ ሲሆን ሆኖም በአንቀፅ 71 መሰረት የድርጅቱን መደበኛ ተግባር የሚያደናቅፍ ሁኔታዎችን ለማስወገድ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ

-                      አደጋ ሲደርስ ወይም የሚደርስ መሆኑ ሲያሰጋ፣

-                      ከአቅም በላይ ሁኔታ ሲያጋጥም፣

-                      አስቸኳይ የሚሰራ ሥራ ሲያጋጥም፣ ሰራተኛውን በሳምንት የእረፍት ጊዜው ማሰራት ይቻላል። በሳምንት እረፍት የሚሰጠው ሲሆን፤ ሰራተኛው የእረፍት ጊዜውን ሳይወስድ የሥራ ውሉ ቢቋረጥ በሰራው ሰዓት መጠን ማካካሻ ክፍያ ያገኛል።

 1. የትርፍ ሰዓት ስራ፡-

ከቀኑ መደበኛ ስምንት የስራ ሰዓት በላይ የስራ ሰራተኛ የትርፍ ሰዓት ሥራ እንዲሰራ በአዋጁ አንቀፅ 66 መሠረት የሚቆጠርለት ሲሆን ሆኖም ሰራተኛው የትርፍ ሰዓት ስራ እንዲሰራ አይገደድም። አሰሪውም የትርፍ ሰዓት ስራ ማሰራት የሚችለው አደጋ ሲደርስ ወይም የሚደርስ መሆኑ ሲያሰጋ፣ ከአቅም በላይ ሁኔታ ሲያጋጥም፣ በአስቸኳይ ስራ ሲያጋጥም፣ እና ወይም በሚያቋርጥና በተከታታይ ከስራ የቀሩ ሰራተኞችን ለመተካት ሌላ አማራጭ መንገድ ሊኖረው አይችልም ተብሎ ሲገመት ነው።

ሆኖም ለአስቸኳይ ስራ የሚሰራ የትርፍ ሰዓት ስራ በቀን ከ2 ሰዓት በወር ከ20 እና በዓመት ከ100 ሰዓታት መብለጥ የለበትም። የትርፍ ሰዓት ክፍያ ከመደበኛው ክፍያ የሚበልጥ ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 68 መሠረት በመደበኛ የስራ ቀን ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት የስራ መደበኛ የሰዓት ደሞዙ በአንድ ከሩብ (በአንድ ከሩብ)ተባዝቶ ከምሽቱ 4 ሰዓትእስከ ንጋቱ 12 ሰዓት የትርፍ ሰዓት የስራ መደበኛ በሰዓት ደምወዙ በአንድ ተኩል ተባዝቶ፣

በሳምንት የእረፍት ቀን የሚሰራ መደበኛ የሰዓት ደምወዙ በሀለት ተባዝቶ

-                      በህዝብ በዓላት የትርፍ ሰዓት የሚሰራ መደበኛ የሰዓት ደምወዙ በሁለት ተኩል ለሰራበት ሰዓት ተባዝቶ ደምወዝ መክፈያ ቀን በተወሰነው ቀን ይከፈለዋል።

የሳምንት የሥራ ቀናትና እረፍትን የሚመለከቱት የአዋጅ ቁጥር 377/96 ከላይ ያሳናቸው ሲሆኑ ሁለቱ ክርክሮች ላይ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እንመልከት፡-

 1. ሰበር ምን አለ፡-

በቀን 16 ሰዓት አሰርቶናል የሚል የትርፍ ሰዓት እና ሌሎች ጥያቄዎችን ያነሱትና ሜታ አቦን የከሰሱት የእነ ሳሙኤል ጉዳይ በሰ/ወ/ቀ 365/8 ጥቅምት 4 ቀን 2001 ውሳኔ አግኝቶ በቅፅ 8 የሰበር ውሳኔዎች ሰብስብ ላይ ወጥቷል።

ከላይ ያነሳነውን የግራ ቀኙን ክርክር ከሕጉ ጋር ያገናዘበው ሰበር ችሎቱ እነ ሳሙኤል ድርጅቱ ባወጣው የሥራ ፈረቃ ድልድል ተስማርተው ሲሰሩ መቆየታቸውንና እሁድ ከሰሩ በሚቀጥለው 24 ሰዓት እንደሚያርፉ መገንዘቡን ጠቅሶ አንድ ድርጅት እንደስራው ፀባይ በሕግ ከተቀመጠው ማዕቀፍ (ገደብ) ሳይጥስ የስራ ሰዓቱን ከማሻሻል የሚከለክለው ሕግ የለም። በሳምንት ከ48 ሰዓት ሳይበልጥ በሰዓት ተስማምተው ሲሰሩ ቆይተው ያልሰሩበትን የትርፍ ሰዓት ክፍያ የሚጠይቁበት የሕግ አግባብ የለም። የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከአዋጁ አንቀፅ 61(1) ከሚባለው አላማ ጋር ሳያገናዝብ የድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ በሚገድብ መልኩ ለ8 ሰዓት ብቻ በቀን እንዲሰሩ መገደቡ አላግባብ ነው በሚል ውሳኔውን ሽሮ የመ/ደረጃ ፍ/ቤቱን ውሳኔ አፅንቷል። እዚህ ጋር የቀን የስራ ሰዓት ሲደላደል ከ10 ሰዓት በላይ በቀን መሆን የለበትም የሚለውን የአንቀፅ 63 ድንጋጌ ከግምት ውስጥ የገባ አይመስልም። ምክንያቱም ሰበር የሰጠው ትርጉም በሳምንት ከ48 ሰዓት በላይ ማሰራት ይቻላል የሚል ትርጉም ይሰጣል። ሆኖም ህጉ የቀን የስራ ሰዓት ሲደለድለው ከ10 ሰዓት መብለጥ የለበትም ይላል።

    በሳምንት እረፍት የመስራት ግዴታን በተመለከተ በሰ/መ/ቁ 378/5 ህዳር 2 ቀን 2001 በሰጠው ውሳኔ አቶ አብዮት አስቸኳይ ስራ አለ እሁድ ግባ ሲባል እምቢ ማለቱ በአዋጁ አንቀፅ 13(7) አሰሪው የሚሰጠውን ሕጋዊ ትዕዛዝ ባለማክበሩ አሰሪው የማሰናበት መብት አለው። የስር ፍ/ቤቱ አስቸኳይ ስራ አጋጥሞ ነው በሳምንት የእረፍት ቀን ስራ የተባለው ወይስ አይደለም የሚለውን ሳያጣራ በሳምንት እረፍት ስራ የተባለው ወይስ አይደለም የሚለውን ሳያጣራ በሳምንት እረፍት ሰራተኛው ስራ በመባሉ ብቻ ስንብቱን ሕገወጥ ማለቱ ስህተት ነው ብሎ አስቸኳይ ስራ አለ የለም የሚለውን አጣርቶ እንዲወስን ለስር ፍ/ቤቱ መልሶለታል።

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
8391 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 842 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us