እነማን ፍ/ቤት ሊቆሙልን ይችላሉ?

Wednesday, 21 January 2015 15:25

 

-  ከፍ/ብሔር ክርክር ከሳሽ ወይ ተከሳሽ ሆነው መቅረብ ካልተመቸዎ ወይም ካልቻሉ ምን  አማራጭ አለዎ?

-   ከዘመዶችዎ መካከል እነማን እርስዎን ወክለው መሟገት ይችላሉ?

-   ፍ/ቤት ቆሞ ለመከራከር የሚያስችል ውክልና ምን ማሟላት አለበት

-  እስከ ፌደራል ሰበር የደረሱ ፍ/ቤት ቆሞ የመከራከርን ውክልና የተመለከቱ ክርክሮች በምን ተቋጩ?

 

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

እንዴት ናችሁ፤ ሰላም ነው የጥምቀት በዓል እንዴት ነበር? እንዲህ በወጉ ሰላምታ ከተለዋወጥን ወደዛሬው ወጋችን እንለፍ። ለመሆኑ በፍ/ብሔር ከሰው ወይም ተከሰው እርስዎ መቅረብ ካልቻሉ ስለርስዎ ቀርበው ለመከራከር የሚችሉት እነማን ናቸው? በፍ/ቤት ክርክር ሌላውን ሰው ወክሎ ለመከራከር ተወካዩ ምን ማሟላት አለበት የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እሞክራለሁ። የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎች በ2006 ዓ.ም ቀርበው አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ የተሰጠባቸውን ሁለት የፍርድ ቤት መከራከር የሚያስችል ውክልናን የሚመለከቱ ሙግቶችንና የተሰጡትን ውሳኔዎች እንዲሁም ጉዳዩን የሚመለከቱ ሕጐችን እናነሳለን። እንቀጥል፡-

 

1. የአክስት ልጅ ፍ/ቤት ቆሞ መከራከር ይችላል?

ወንዶ ገነት ወረዳ ፍ/ቤት ነው። አቶ አየለ ሚናም፣ አቶ አሰፋ ባዩ ላይ የንብረት ግምት ክስ አቅርበው አቶ አሰፋ በሌሉበት 95 ሺህ 067 ብር እንዲከፈላቸው አስወስነው ይዞታቸውንም በስማቸው ያዛውራሉ። የአቶ አሰፋ ባዩ ወኪል አቶ ዘሪሁን ሞገስ ውሳኔው እንዲፈፅሙ የቀረቡባቸውን ክስ ሲያዩ እንዴት ይሆናል ሲሉ በማስረጃነት የቀረበውን ውሳኔ ሲያዩ “እኔ ተወካያቸው እያለሁ አቶ አሰፋ ባዩ በሌሉበት ውሳኔው መሰጠቱ አለአግባብ ነው። አቶ አሰፋን ወክዬ ወደ ክርክሩ ልግባ” ሲሉ ለፍ/ቤቱ አመለከቱ።

አቶ አየለ በሰጡት መልስ አቶ አሰፋ ለአቶ ዘሪሁን የሰጡት ውክልና በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2205 ንብረት የማስተዳደር እንጂ ስለ አቶ አሰፋ ፍ/ቤት ቆመው መከራከር አያስችላቸውም። ስለዚህ ውክልናው ተቀባይነት ስለሌለው በእኔና በአቶ አሰፋ ጉዳይ አቶ ዘሪሁን አያገባቸውምና መከራከር አይችሉም ሲሉ መልስ ሰጡ።

ወኪል ዘሪሁን ቀደም ሲል እስከ ክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ድረስ በዚሁ የውክልና ስልጣን ማስረጃዬ ከአቶ አየለ ጋር ስንከራከር ስለነበር አሁን መከራከር አይችልም ማለት አይችሉም አሉ። የወንዶገነት ወረዳ ፍ/ቤት አቶ አየለ ክሱን ሲያቀርቡ በጠቀሱት አድራሻ መጥሪያውን ለአቶ አሰፋ ባልሆነ አድራሻ እንዲላክ ስላደረጉ ውሳኔውን አንስቻለሁ። የአቶ አሰፋ ወኪል አቶ ዘሪሁን ክርክሩን ይቀጥሉ ሲል ብይን ሰጠ።

አቶ አየለ ሚናም ከብይኑ በኋላ ባቀረቡት አቤቱታ አቶ አሰፋ ለአቶ ዘሪሁን ውክልና የሰጡት በ1996 ዓ.ም ነው። ክርክሩ በ2004 ዓ.ም ነው። አቶ አሰፋ እንዲቀርቡ በጋዜጣ ተጠርተው ስላልቀረቡ በህይወት መኖራቸውንም እጠራጠራለሁ ካሉ እራሳቸው ይቅረቡልኝ አሉ። አቶ ዘሪሁን አቶ አሰፋን ወክዬ ለመከራከር የሚያስችለኝ ውክልና እያለኝ አቶ አሰፋ መቅረባቸው አስፈላጊ አይደለም ብለው መልስ ሰጡ። ፍ/ቤቱም አንዴ ወኪሉ ወደ ክርክሩ እንዲገቡ ተፈቅዷልና ድጋሚ መቃወሚያ መቅረቡ አለአግባብ ነው ሲል ብይን ሰጠ።

አቶ አየለ፣ አቶ ዘሪሁን አቶ አሰፋን ወክሎ መከራከር ይችላል የሚለው ብይን ስላልተዋጠላቸው ይግባኝ ለሲዳማ ዞን ከ/ፍ/ቤት አቀረቡ። ፍ/ቤቱ የሰር ፍ/ቤትን ውሳኔ አፀናው። ወደ ደቡብ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር አቤቱታ ቢያቀረቡም የደቡብ ሰበርም ብይኑን አፀና።

ይሄኔ አቶ አየለ ወደ ፌዴራሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ። አቤቱታው በአቶ ዘሪሁን እና በአቶ አሰፋ መካከል የዝምድና ትስስር ሳይኖር ፍ/ቤት ቆሞ መከራከር የሚያስችል ውክልና ነው ብዬ ብከራከርም የሥር ፍ/ቤቶችም ክርክሬን ባለመቀበል ብይን በመስጠታቸው የሕግ ስህተት ፈጽመዋል ይታረም የሚል ነበር።

አቶ ዘሪሁን አቶ አሰፋ የሰጡኝ ውክልና ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ንብረታቸውን በተመለከተ ክስ እንዳቀርብ መልስ እንድሰጥና እንድከራከር በግልፅ ስልጣን ሰጥቶኛል። በቀድሞ ክርክራችንም በዚሁ ውክልና አቶ አየለን ስሞግታቸው ይህን መቃወሚያ ስላላነሱ የሰበር አቤቱታው ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም አሉ።

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቶ አየለ አቶ ዘሪሁን አቶ አሰፋን ወክለው ለመከራከር የሚያስችል ስልጣን የላቸውም በሚል ያቀረቡት መቃወሚያ በሰር ፍ/ቤቶች ተቀባይነት ማጣቱ ትክክል ነው? የሚለውን ነጥብ መረመረ። በቃል ክርክር ወቅት አቶ ዘሪሁን አንደኛው የሰበር ዳኛ ጠየቋቸው ወኪል አድራጊም አቶ አሰፋ ጋር ዝምድና አላችሁ ምንዎ ናቸው? አቶ ዘሪሁን መለሱ “የአክስቴ ልጅ” ሰበር ክርክሩን መርምሮ ውሳኔ ሰጠ። ከውሳኔው በፊት አንድ ክርክር እንጨምር።

 

2. የባለቤቱ ወይስ የድርጅቱ ወኪል

ብርሃኑ አማረ ይባላሉ ሰውዬው። በስማቸው የሚጠራ ብርሃኑ አማረ ጠ/ሕንፃ ስራ ተቋራጭ የሚባል ድርጅት አላቸው። ፍርማ ብርብር ከአቶ ብርሃኑ አማረ ላይ ክስ መስርቶ ተጠርተው ስላልቀረቡ በሌሉበት ክሱ ተሰማና አቶ ብርሃኑ አማረ ላይ ውሳኔ ተሰጠ። ይሄኔ በሌለሁበት የተሰማው ውሳኔ ይነሳልኝ የሚል አቤቱታ ለብርሃኑ አማረ ጠ/ሕ/ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ነገረፈጅ ቀረበ።

ፍርማ ብርብር ኃ/የተ/የግ/ማኅበር አቤቱታው አስተያየት እንዲሰጥ ሲቀርብለት እኔ የከሰስኩትና ያስፈረድኩት ግለሰቡ ብርሃኑ አማረ ላይ እንጂ ድርጅታቸው ብርሃኑ አማረ የሕ/ሥራ/ተቋራጭ ላይ አይደለም። ከድርጅቱ ጋር የውል ግንኙነት የለኝም። ውሳኔም አልተሰጠበትም። ስለዚህ በድርጅቱ ነገረ ፈጅ በኩል የቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት የለውም አለ።

ክርክሩን የሚያየው የፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት በአቶ ብርሃኑ አማረ ስም የተቋቋመው ብርሃኑ አማረ ጠ/የሕ/ሥራ ተቋራጭ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት መሆኑን ሳይሆን የግለሰብ ነጋዴው የንግድ ስም ነው። አቤቱታውን ያቀረበው የዚህ ድርጅት ነገረ ፈጅ በመሆኑ ነገረ ፈጅ ደግሞ በሕግ ለተቋቋመ ድርጅት እንጂ ግለሰብን (የተፈጥሮ ሰውን) ወክሎ መከራከር ስለማይችል የሕጉን መመዘኛ ሳያሟሉ ያቀረቡትን አቤቱታ አልቀበለውም ብሎ መዝገቡን ዘጋው።

የብርሃኑ አማረ ድርጅት ነገረ ፈጅ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርበው ተቀባይነት ስላላገኙ፤ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ። ሰበር የድርጅቱ ነገረ ፈጅ ለባለቤቱ አቶ ብርሃኑ አማረን ወክሎ መከራከር አይችልም መባሉ አግባብ ነው? አግባብ አይደለም ከተባለስ ፍ/ቤቱ ምን ማድረግ አለበት የሚሉትን ነጥቦች ግራ ቀኙን አከራክሮና መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔውን እናቆየውና ሕጉ ምን እንደሚል እንመልከት።

 

3. ስለሌላው ፍ/ቤት መቆም

በተለያዩ ምክንያቶች ከሳሽ ወይም ተከሳሽ በምንሆንበት የፍ/ቤት ክርክር ላይ መቅረብ ላንችል ወይም ላንፈልግ እንችላለን። በዚህ ሁኔታ ላይ ፍ/ቤቱ ዋናው ባለጉዳይ ቀርቦ እንዲከራከር ካላዘዘ ወይም እራሱ ተከራካሪው እንዲቀርብ የሚያስገድድ ሕግ ከሌለ ነገሩን ለማስረዳት ለመከራከር ለሚጠየቀው ሁሉ በቂ መልስ ለመስጠት የሚችል ሰው ባለጉዳዩን ወክሎ በነገረ ፈጅነት፣ በወኪልነት፣ በጠበቃነት መከራከር እንደሚችል የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 57 ይፈቅዳል።

3.1  ውክልና፡- ስለሌላው ፍ/ቤት ቆመው መሟገት የሚፈቀድላቸው ሰዎች በቅድሚያ የሚሟገቱለት ሰው ለተወሰነ ጊዜ ወይም ለተወሰነ ጉዳይ ወይም ማንኛውንም ከሳሽ ወይም ተከሳሽ የሚሆኑበት ጉዳይ ላይ ቀርቦ እንዲከራከር በጽሁፍ ፈርመው ውክልና መስጠት አለባቸው። ይህ ተሟጋች ማቆምን የሚመለከተው የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 63 ድንጋጌ ሌላ ሰው በፍ/ቤት እንዲከራከርለት ውክልና የሚሰጥ ሰው ስልጣኑን ነገረ ፈጅ ወይም ጠበቃ ወይም ወኪል ለመሾም ብቻ እንዲሆን ካደረገ ውክልናው የተሰጠው ተወካይ በውክልናው ላይ በተጠቀሰው መሰረት ጠበቃ ወይም ወኪል መቅጠር አለበት እንጂ በራሱ መሟገት እንደማይችል ይደነግጋል። ይህ ድንጋጌ ወካዩ ክርክሩን በተባለው የሕግ ባለሙያ ለማድረግ ከፈለገ ወኪሉም ይህን የወካዩን ፍላጐት ተግባራዊ እንዲያደርግ የተቀመጠ ይመስላል። ሁሉም ፍ/ቤት ቀርበው መከራከር የሚችሉ ሰዎች ከላይ ያነሳነው ፍ/ቤት ቀርቦ ለመከራከር የሚያስችል የጽሁፍ ውክልና ማቅረብ አለባቸው። እነማንን ፍ/ቤት ቆመው እንዲከራከሩል መወከል እንደምንችል እንመልከት።

3.2  ተሟጋች ዘመዶች፡- በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 58(ሀ) የዋናው ባለጉዳይ ባለቤት ወንድም፣ እህት፣ ልጅ፣ አባት፣ እናት፣ አያት የሕግ ባለሙያ ወይም ጠበቃ ካልሆኑም ለውክልናው ወይም ለነገረ ፈጅነቱ አበል ሳይሰጣቸው ቀርበው መከራከር ይችላሉ። በተጠቀሱት የዝምድና ትስስር ውስጥ የማይወድቁ ሰዎች ግን ይህ ውክልና ሊሰጣቸው አይችልም፤ ቢሰጣቸውም ፍ/ቤት ቀርቦ መከራከር አያስችላቸውም።

3.3  ድርጅቶችና ተቋማት፡- ጉዳዩ በሚታይበት ፍ/ቤት የግዛት ክልል ውስጥ በማይገኙ ሰዎች ስም የንግድ ወይም የሌላ ስራ የሚያካሂዱ ወኪሎች ለምሳሌ ስራ አስኪያጆች፣ የንግድ ወኪሎች የመሳሰሉት ክስ ወይም አቤቱታ ለማቅረብ ስልጣን ከተሰጣቸው ድርጅቱን መወከልና መከራከር ይችላሉ። ሆኖም ይህን ማድረግ የሚችሉት ዋናው ባለጉዳይ ድርጅቱ ነገረፈጅ ወይም ወኪል ካልወከለ ነው።

መንግስትም ሆነ የግል ድርጅቶች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 59 መሰረት ፍ/ቤት ቆሞ እንዲከራከርላቸው ነገረፈጅ ወይም ሌላ ጠበቃ ወይም ወኪል መወከል ይችላሉ። አሁን በተግባር ነገረ ፈጅ የሚባለው ለመንግስት ወይም ለግል ድርጅት ተቀጥሮ የሚሰራና የፍ/ቤት ክርክር ለማድረግ ውክልና የተሰጠው የሕግ ባለሙያ ነው። በግሉ ፍቃድ አውጥቶ ለተቋማትም ሆነ ለግል ድርጅቶች ውክልና እየተቀበለ የሚከራከረው ባለሙያ ደግሞ ጠበቃ ይባላል። ሆኖም በስነስርዓት ሕጉ ላይ ነገረ ፈጅ እያለ ነው የሚጠቅሳቸው።

3.4  በማረሚያ ቤት ያሉ ሰዎች፡- በእስር ቤት የሚገኙ ሰዎች የፍ/ብሔር ክርክራቸውን ለጠበቃ ወይም ፍ/ቤት መቆም ለሚፈቀድላቸው የቅርብ ዘመዶች በወህኒ ቤቱ ስም የተረጋገጠ የጽሁፍ ውክልና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 62 መሠረት መስጠት ይችላሉ።

በአጠቃላይ ፍ/ቤት ቀርቦ በተወካዩ ስም ለመከራከር በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2205 መሠረት ውክልናው የተሰጠበትን ጉዳይ በግልፅ የሚጠቅስ ልዩ የጽሁፍ ውክልና መቅረብ አለበት። ውክልናው በውልና ማስረጃ መዝጋቢው የተመዘገበና የተረጋገጠ መሆንም አለበት።

 

 4. ሰበር ምን አለ?

ከላይ ያነሳናቸው ሁለት ክርክሮች እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርበው የሕግ ትርጉም ተሰጥቶባቸዋል ቅጽ 16 ላይ በቅርቡ ታትመው ወጥተዋል።

አቶ አሰፋ የአክስቴ ልጅ ናቸው ውክልና ሰጥተውኛል ብሎ ውክልናውን አቅርቦ በስር ፍ/ቤቶች እንዲከራከር የተፈቀደለት አቶ ዘሪሁን ጉዳዩ ሰበር ሲደርስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 58(ሀ) መሰረት የተዘረዘረው የዝምድና ደረጃ እንዳላቸው አላረጋገጡም። ውክልናው ፍ/ቤት ቆመው ይከራከሩልኝ ቢልም አቶ ዘሪሁን ጠበቃም ስላይደሉ ፍ/ቤት መቆም የሚያስችል ዝምድናም ስለሌላቸው ፍ/ቤት አቶአሰፋን ወክለው መቆም አይችሉም። ቀደም ብሎ በተደረገ ክርክር አቶ አየለ በዝምታ ሲከራከሩ ቆይተው አሁን ውክልናውን መቃወም አይችሉም የሚለውን በተመለከተ አቶ ዘሪሁን በስር ፍ/ቤት በጭብጥነት አሲዘውት በተወካይነት እንዲከራከሩ የጠየቁ በመሆናቸው አቶ አየለ የውክልናው ሥልጣን ፍ/ቤት መቆም አያስችልም የሚለውን መቃወሚያ ከማንሳት የሚያግዳቸው ነገር የለም።

ስለዚህ የስር ፍ/ቤቶች መቃወሚያውን ተቀብለው ዋናው ባለጉዳይ ወይም ትክክለኛው ተወካይ እንዲቀርብ ማድረግ ሲገባቸው ውክልናው ሕጋዊ መሆኑን ሳይመረምሩ ማለፋቸው መሰረታዊ የሕግ ስህተት ነው ብሎ ከወንዶ ገነት እስከ ደቡብ ክልል ሰበር ችሎት የሰጡትን ውሳኔ ሽሮታል።

ለአቶ ብርሃኑ አማረ ጉዳይ ቀርቦ ለመከራከር የጠየቀው የብርሃኑ አማረ ጠ/ሕ/ሥ/ተ ነገረ ፈጅ ጉዳይን በተመለከተ በሰ/መ/ቁ 94302 ሚያዝያ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ውሳኔ ተሰጥቷል።

ብርሃኑ አማረ ጠ/ሕ/ሥራ ተቋራጭ የድርጅቱን የንግድ ስራ ዘርፍ ወይም የንግድ ስም የሚያሳይ ነው። ፍርማ ክስ አቅርቦ ያስወሰነው አቶ ብርሃኑ አማረ ገብረአብ ላይ ነው። ለመከራከር የቀረቡት የተቋራጩ ነገረ ፈጅ ከአቶ ብርሃኑ አማረ ጋር ፍ/ቤት ቀርቦ ለመከራከር የሚያስችል ዝምድና ያላቸው መሆኑን ያቀረቡት ክርክር የለም። ያቀረቡት ውክልናም ይሄን ዝምድናቸውን አይጠቅስም። የዋናው ባለጉዳይ የአቶ ብርሃኑ አማረ ወኪል ወይም ነገረ ፈጅ መሆኑን በተመለከተ ያቀረበው ክርክር የለም። የውክልና ሰነድም ይህን አያሟላም። የስር ፍ/ቤቶች ይህን በተመለከተ የሰጡት ውሳኔ ትክክል ሲሆን፤ የቀረቡት ውክልና ፍ/ቤት ለመቆም የሚያስችል ውክልና ባይሆንም፤ በተገቢው ባለስልጣን ተረጋግጦ የቀረበ በመሆኑ ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ተገቢው ውክልና ወይም ዋናው ባለጉዳይ እንዲቀርቡ ማዘዝ ሲገባው መዝገቡን ዘግቶ ማሰናበቱ አግባብ ባለመሆኑ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ተሻሽሏል። ፍ/ቤቱ ትክክለኛው ውክልና እንዲቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ተገቢውን እንዲወስን መዝገቡ ይመለስለት ሲል ወስኗል።

በመጨረሻም ፍ/ቤት በፍ/ብሔር ጉዳይ ከሳሽ ወይም ተከሳሽ ሆነን መቅረብ ካልፈለግን ወይም ካልቻልን ለጠበቃ ጉዳዩን መስጠቱ ይመረጣል። ይህ ካልተቻለ ደግሞ እንዲከራከሩልን መወከል ያለብን ሕጉ የሚፈቅዳቸውን ዘመዶቻችንን ነው። ይህ ካልተቻለ ጠበቃ እንዲወክሉልን ሌሎች ሰዎችን መወከል እንችላለን። ስለዚህ ፍ/ቤት እንዲቆሙልን ውክልና ስንሰጥ ቅድሚያ ወኪሎቹ በስነስርዓት ሕጉ መሰረት ፍ/ቤት ቀርበው ሊከራከሩልን የሚችሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል። 

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
7538 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 862 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us