ሕጋዊነትና መብት ማስከበር?

Wednesday, 28 January 2015 13:03

-    ከውል ወይም ከሕግ የሚመነጩ መብቶችን እንዴት ማስከበር አለብን?

-    የውል ግዴታን ባለመወጣት መብትን ለማስከበር የሌላውን ዕቃ መውሰድ ‘እምነት ማጉደል’ ወይስ ‘ሕገወጥ የመብት ማስከበር’?

-    በሕገወጥ መንገድ መብት ማስከበር ምንድን ነው?

-    የሚያስከትለው የወንጀል ኃላፊነትስ?


በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.


 

ሰላም ነው? እንዴት ናችሁ? የዛሬ ወጋችን ከአንድ ሰው ላይ የምንጠይቀውን መብት እንዴት ማስከበር እንችላለን በሚለው ላይ ያተኩራል። የምናነሳው እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሰው ክርክር እምነት ማጉደልን የሚመለከት ስለነበር እግረ መንገዳችንን ለመሆኑ የትኛዎቹ ድርጊቶች ናቸው በእምነት አጉዳይነት ሊያስወነጅሉ የሚችሉት የሚለውንም እናነሳለን። ለማጓጓዝ የተረከቡትን ሲሚንቶ ያልተከፈለኝ ገንዘብ አለ ብለው የሸጡት ሰው ጉዳይ ላይ እስከ ሰበር በተደረገ ክርክር የተሰጠውን ውሳኔም እናያለን።

1.እምነት አጐደሉ ወይስ መብታቸውን አስከበሩ?

አቶ ፅጋቡ የጭነት ማጓጓዣ ሥራ ላይ የተሰማሩ የጭነት መኪና ባለቤት ናቸው። ጭነት የሚያጓጉዙ ሰዎችን ዕቃ እያጓጓዙ ያጓጓዙበትን እያስከፈሉ ኑሮአቸውን ይመራሉ። ሚሊኒየም ዴቨሎፕመንት ፕሮጀክት ከሚባል ድርጅት ጋር ከመቀሌ ወደ ሀውዜን ሲሚንቶ ለማጓጓዝ ይዋዋላሉ። የተወሰነ ክፍያ ተቀብለው ሲሚንቶውን ሀውዜን አድርሰው ቀሪውን ክፍያ ቢጠይቁ ሚሊኒየም ዴቨሎፕመንት ፕሮጀክት ሊከፍላቸው አልቻለም። ስለዚህ አቶ ፅጋቡ ሲሚንቶውን ቸብችበው የሚቀራቸውን ገንዘብ ቀነሱና የሽያጩን ገንዘብ ለአስጫኙ ተቀበለኝ ብለው ጠየቁ። ድርጅቱ አልቀበልም ጭነህ እንድታደርስ የተስማማኸውን ሲሚንቶ ለእኔ ማስረከብ ሲገባህ ሸጠሀልና በእምነት ማጉደል ወንጀል ፍ/ቤት እገትርሃለሁ አለ።

እንዳለውም አደረገውና አቶ ፅጋቡ በትግራይ ክልል ዐ/ሕግ በኩል በክለተ በለሳ ወረዳ ፍ/ቤት እንዲያጓጉዝ የተሰጠውን ስሚንቶ አጓጉዞ በጊዜው ማስረከብ ሲገባው ሽጦ ለግል ጥቅሙ በማዋሉ የወንጀለ ሕግ 675(1)ን በመጣስ የእምነት ማጉደል ወንጀል ፈፅሟል ተብለው ተከሰሱ።

አቶ ፅጋቡ ፍ/ቤት ቀርበው ሲሚንቶውን ተረክቤ የሸጥኩት አስጫኙ ያልከፈለኝ ገንዘብ ስለነበር ገንዘቡን ለማስመለስ መሆኑን እና ይህንኑ ገንዘብ ቀንሼ ቀሪውን ተረከበኝ ብለውም ፈቃደኛ ባለመሆኑ በፍ/ብሔር እንጂ በወንጀል ልጠየቅ አይገባም ብለው መልስ ሰጡ።

ፍ/ቤቱም የዐ/ሕግንና የአቶ ፅጋቡን ክርክር እና ማስረጃ ሰምቶ ጉዳዩ የፍ/ብሔር እንጂ የወንጀል ተጠያቂነት አያስከትልም በማለት አቶ ፅጋቡን በነፃ አሰናበታቸው።

የትግራይ ክልል ዐ/ሕግ አቶ ፅጋቡ በነፃ በመለቀቃቸው ቅር ተሰኝቶ ለክልሉ የምስራቅ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ቢያቀርብም ፍ/ቤቱ የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ አፅንቶ አሰናበተው።

ዐ/ሕግ ለትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ይታረምልኝ ሲል አቤቱታ አቀረበ። የክልሉ ሰበር ሰሚ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ አቶ ፅጋቡ ሲሚንቶውን ሽጠው በውል ግዴታቸው መሰረት ሳያስረክቡ መቅረታቸው ተረጋግጧል። ስለዚህ በወንጀል ሕጉ 675(1) ስር ጥፋተኛ ናቸው ሲል ወሰነ። የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ተቀብሎ አቶ ፅጋቡ በሁለት ዓመት ከሦስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወሰነባቸው።

ይሄኔ ሰበር አቤቱታ ተራው የአቶ ፅጋቡ ሆነና በጠበቃቸው በኩል በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ድርጊቱ ወንጀል ነው ብሎ የወሰነው ከስልጣኑ ውጭ ነው። ድርጊቱ በወንጀል ሕጉ ላይ ስለ እምነት ማጉደል የተቀመጡትን የወንጀሉን ማቋቋሚያዎች አያሟላም ስለዚህ በክልሉ ሰበር ሰሚ የተፈፀመው የሕግ ስህተት ይታረምልኝ ሲሉ አመለከቱ።

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩ እምነት ማጉደል ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመመርመር ጉዳዩን ያስቀርባል ሲል ብይን ሰጠ። ከዚያም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የአቶ ፅጋቡን ድርጊት እምነት ማጉደል ነው ብሎ የስር ፍ/ቤት የቀረቡትን ማስረጃዎች መርምሮ በመወሰኑ የሕግ ስህተት አልተፈፀመም ካለ በኋላ ነገር ግን ድርጊቱ የእምነት ማጉደል ነው ለመባል በወንጀል ሕጋችን 675(1) ስር የተቀመጡትን መመዘኛዎች ማሟላት አለበት። እምነት ማጉደል ለአንድ ለተወሰነ ግልጋሎት ወይም በአደራ የተሰጠውን ዋጋ ያለው ነገር ወይም ጥሬ ገንዘብ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው የማይገባ ብልፅግና ለማስገኘት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለራሱ ወይም ሌላ ሰው ያደረገው የወሰደ፣ የሰወረ ወይም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው አገልግሎት ያዋለ ሰውን የሚመለከት ነው። የአቶ ፅጋቡ ድርጊት ግን በማጓጓዣ ውል መሰረት ለማጓጓዝ የተረከቡትን ሲሚንቶ በተወሰነው ጊዜና ስፍራ አድርሰው ለተቀባዩ የማስረከብ የውል ግዴታቸውን አለመወጣት ነው። ይህ የውል ግዴታን አለመወጣት የእምነት ማጉደል ተግባር መሆኑን 675(1) አይደነግግም። በማጓጓዝ ውል ወይም ልማድ መሠረት የሚገባውን ሙሉ ጥንቃቄ አድርጐ እቃውን በማጓጓዝ በተወሰነው ጊዜና ስፍራ አድርሶ ለተቀባዩ የማስረከብ ግዴታውን ያልተወጣ አጓጓዥ በእምነት ማጉደል ወንጀል እንዲጠየቅ የድንጋጌው ይዘትና መንፈስ የማያሳይ በመሆኑ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሰበት ድምዳሜ ተገቢ አይደለም።

በአቶ ፅጋቡና በሲሚንቶ አስጫኙ መካከል የነበረው የውል ግንኙነት የነበረ መሆኑ ተረጋግጧል። ተከሳሹ ሲሚንቶውን የሸጡት ያልተከፈላቸውን ገንዘብ ለማስመለስ እንጂ ለራሳቸው ወይም ለሌላ ሰው የማይገባቸውን ብልፅግና ለማስገኘት አለመሆኑ ተረጋግጧል። ስለዚህ በእምነት ማጉደል ተጠያቂ የሚሆኑበት አግባብ የለም ብሎ በእምነት ማጉደል ወንጀል መጠየቃቸውን ሰበር ውድቅ አደረገ። ሰበር የአቶ ፅጋቡ ድርጊት እምነት ማጉደለ ባይሆንም ሙሉ በሙሉ ሕጋዊ ተግባር ሆኖ ግን አላገኘውም። አቶ ፅጋቡ በማጓጓዣ ውል ስምምነታቸው መሰረት ይቀረኛል የሚሉት ገንዘብ ካልተከፈላቸው ያለ አስጫኙ ስምምነት ሲሚንቶውን ሸጠው ገንዘቡን ማስመለሳቸው አግባብ አይደለም። የሚጠይቁት መብት ቢኖራቸውም እንኳን መብታቸውን ማስከበር የነበረባቸው በሕግ አግባብ መሆኑን ጠቅሶ አቶ ፅጋቡ ‘በሕገወጥ መንገድ መብትን በማስከበር’ ወንጀል ሊጠየቁ ይገባል አለ። ለመሆኑ ሰበር ይሄን ሲል ምን ማለቱ ነው? የሚለውን ለማየት ሕጉን እናጣቅስ።

2.መብትን በሕጋዊ መንገድ ማስከበር

ከዚህ አባባል ጀርባ ያለው መልዕክት መብቶችና ግዴታዎች የሚፈጠሩት በሕግ እና በውል ነው። ስለዚህ መብቶቹ መጠየቅ ወይም መፈፀም ያለባቸው ለእነዚህ መብቶች እውቅናና ጥበቃ በሰጠው ሕግ በኩል ብቻ ነው። ይሄ ሕጋዊ ሥርዓት ደግሞ ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና፣ ሕግ አስፈፃሚው ተብለው የሚጠሩት ሦስቱ የመንግስት አካላት ሥራ ነው። ሕግ አውጭው ሕጉን ያወጣል፣ ያፀድቃል።

ሕግ ተርጓሚው ደግሞ በነኛ ሕጐች መሰረት አንድ መብት ወይም ግዴታ ተፈጥሯል ወይስ አልተፈጠረም መብቱ ወይም ግዴታው የሚያስከትለው ውጤትስ ምን መሆን አለበት ብሎ ሕጉን ተርጉሞ አከራካሪ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ይሰጣል። ያን ውሳኔ የማስፈፀም ኃላፊነት ላለባቸው የአስፈፃሚው አካላት ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤት፣ የመንግስት የአስተዳደር ተቋማት ውሳኔውን እንዲፈፅሙ ያዛል። መብት በሕጋዊ መንገድ መከበር አለበት ሲባል እንግዲህ አጠቃላይ መሰረቱ ከላይ ያነሳነው በሕግ የተቋቋሙ የሥራ ድርሻ የተከፋፈሉ እና በሕግ የተወሰነ ስልጣን ያላቸው የመንግስት አካላት መኖራቸው ነው።

‘በሕገወጥ መንገድ መብት ማስከበር’ን የሚመለከተው የወንጀል ድንጋጌ በ1996 በወጣው የወንጀል ሕጋችን አራተኛ መጽሐፍ ስር “በሕዝብ ጥቅሞችና በማኅበራዊ ኑሮ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች” የሚለው ታላቅ ክፍል ስር የሚገኝ ንዑስ ርዕስ ስር የሚካተት ነው። በዚህ በአራተኛው መጽሐፍ ላይ በሕዝብ አመኔታ ላይ፣ የሕዝብ ጥቅምን በሚመለከት ሚስጥር ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ በመንግስት ስራ ላይ፣ በፍትህ አስተዳደር ላይ፣ በህዝባዊ ምርጫና ድምፅ አሰጣጥ ላይ፣ በሕዝብ ደህንነት ሰላምና መረጋጋት ላይ፣ በሕዝብ መገናኛዎችና ማጓጓዣዎች ደህንነት ላይ፣ በጤና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ያካተቱ ምዕራፎች ስር በክፍሎች ተለያይተው የወንጀል ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል።

በሕገወጥ የመብት ማስከበር በሦስተኛው ርዕስ “በመንግስት ሥራ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ስር በሦስተኛው ምዕራፍ “ሌሎች ሰዎች በመንግስት ሥራ ላይ የሚፈፅሟቸው ወንጀሎች” በሚለው የምዕራፍ ሁለተኛ ክፍል ስር ይገኛል። ይህ የሚያሳየው የወንጀል ሕጉ የመንግስት ሥራ ብሎ ካስቀመጣቸው አንዱ ሕግንና መብትን ማስከበር መሆኑን መረዳት ይቻላል። ማንኛውም መብት መፈፀም ያለበት መብቱን ለማስጠበቅ በተቋቋሙ መንግስታዊ ተቋማት በኩል ወይም ሕጉ በሚፈቅደው አግባብ መሆን አለበት።

3.ሕገወጥ የመብት ማስከበር

በመብት ሰበብ የሌሎች መብት ያለ ሕጋዊ ስርዓት እንዳይጣስ የሚያደርግ በመሆኑ ነው። በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 436 ላይ ይህ ድንጋጌ የተቀመጠው።

በዚህ ድንጋጌ መሰረት ማንም ሰው መብት ሳይኖረው ወይም ሕግን ተቃራኒ በሆነ መንገድ (ለምሳሌ አንድ ሰው አንድ ዕቃ አከራይቶ ተከራዩን በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ያን ዕቃ እንዲመልስ ካልጠየቀው መውሰድ እንደሚችል በግልፅ የውል ስምምነት ካደረጉና ያ ሰው እስከ ሦስት ወር ዕቃውን እንዲመልስ ካልጠየቀው እቃውን ቢወስደው በውል ያገኘው መብት አለ ማለት ይቻላል) ሆኖም ይህ ከውል ወይም ከሕግ የመነጨ መብት ከሌለ ግለሰቡ ይገባኛል የሚለውን መብት ሕግን ተቃራኒ ካልሆነ መንገድ መጠየቅ አለበት። ሆኖም መብቱ ሳይኖረው ወይም ሕግን ተቃራኒ በሆነ መንገድ፤

-    በመያዣ ወይም ለዋስትና ያስረከበውን ዕቃ ተረካቢው ሳይፈቅድለት ወይም በዚሁ ዕቃ ምክንያት ክስ ቀርቦ በክርክር ላይ እያለ ከወሰደ፣

-    ሊከፈለው የሚገባውን ክፍያ ለማግኘት ሲል የባለዕዳው ንብረት የሆነውን ማንኛውንም ተንቀሳቃሽ ዕቃ የወሰደበት እንደሆነ፣

-    የሌላውን ወይም በሕጉ መሠረት ሊሰራበት የማይችለውን መብት የተጠቀመበት ከሆነ ከአንድ ዓመት የማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል።

4.ሰበር ምን አለ?

በእምነት ማጉደል የተቀጡት አቶ ፅጋቡ በእምነት ማጉደል ሊጠየቁ አይገባም። የፈፀሙት የማጓጓዣ ውል ግዴታን አለመወጣት ነው ብሎ ቢወሰንም በወንጀል ስነስርዓት ሕጉ መሰረት ድርጊቱን በሚሸፍነው የወንጀል ድንጋጌ በሕገወጥ መንገድ መብትን ማስከበር መሆኑን ጠቅሷል። ግለሰቡ ቀሪ ገንዘብ አለኝ ቢሉም እንዲያደርሱ የተሰጣቸውን ሲሚንቶ ያለ አስጫኙ ፍቃድ በመሸጣቸው መብታቸውን ቢያስመልሱም የተጠቀሙት ግን በሕግ የተፈቀደ የመብት ማስከበር ድርጊት ባለመሆኑ በሕገወጥ መንገድ መብትን በማስከበር ወንጀል በአንቀፅ 436(2) ስር ጥፋተኛ ናቸው። ያቀረቡትን የቅጣት አስተያየት በማመዛዘን እስካሁን የታሰሩት በቂ ሆኖ ይፈቱ ሲል በሰ/መ/ቁ. 98647 ሰኔ 2 2006 በዋለው ችሎት ወስኗል።

ለማንኛውም መብትን ማስከበር የሚበረታታ ቢሆንም የምናስከብርበት መንገድ ግን ሕጋዊ መሆን እንዳለበት ልንዘነጋ አይገባም

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
7470 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 787 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us