የተሽከርካሪ አደጋ እና ቸልተኝነት

Thursday, 05 February 2015 10:55

-  በተሽከርካሪ አደጋ ለሚደርስ ጉዳት አሽከርካሪው ቸልተኛ ነበር ወይስ አልነበረም የሚለው እንዴት ይመዘን፣

-  ቸልተኛነት ምንድን ነው?

-  ድንገተኛ አደጋ ለጉዳቱ መንስኤ ነው የሚባለው በምን ሁኔታ ነው?

-  በሬውና እረኛውን ለማዳን ሁለት ሰዎች የገደለው አሽከርካሪ የወንጀል ክስ በምን ተቋጨ? 

 

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? የዛሬው ጽሁፍ የሚያተኩረው በተሽከርካሪ አደጋ በአሽከርካሪው ቸልተኝነት ላይ ነው? ለመሆኑ አንድ የተሽከርካሪ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ በሰውና በንብረት ላይ ለሚደርሰው ጉዳት አሽከርካሪው በቸልተኝነት ጥፋት ፈጽሟል ወይስ አልፈፀመም የሚለው ነጥብ መመዘን ያለበት በምን አግባብ ነው? አደጋና ጉዳት መድረሱ ብቻ አሽከርካሪውን ተጠያቂ ሊያደርገው ይችላል? የሚሉትን ነጥቦች ሊመልሱልን የሚችሉ እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሱ ክርክሮችን እናያለን። እንቀጥል….

1. እረኛውንና በሬውን ለማዳን…

አቶ ፋሲል ብርሃኑ የካቲት 8 ቀን 2000 ዓ.ም ከጅማ አዲስ አበባ የሚጓዙ መንገደኞችን የሰ.ቁ. 3-42361 በሆነው አይሱዙ መለስተኛ አውቶብስ ጭነው ጉዞአቸውን ጀመሩ። ሶኰሩ አካባቢ ሲደርሱ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ሆኖ ነበር። ቲሮ ቁምቢ ቀበሌ ውስጥ ኪላ ጐሼ የሚባል ቦታ ላይ አንድ ኩርባ (መታጠፊያ) ጋር ሲደርሱ አንድ በሬ አስፋልቱ መሀል ላይ ገብቷል። በሬው ብቻ ሳይሆን እረኛውም በሬውን ለመመለስ ወደ መንገድ ገብቷል። ከመንገዱ በስተቀኝ ጭልጥ ያለ ገደል ነው። መኪናው በሬውና እረኛው በቅርብ እርቀት ላይ ናቸው። ሹፌሩ አቶ ፋሲል የሆነ ነገር ማድረግ ነበረበት። ፈታኝ ቅፅበት ነው። የጫናቸው ከሱ ጭምር 45 ሰዎች ናቸው። በዚህ ቅርበት ፍጥነቱን ቢቆጣጠርም ብዙም ለውጥ አያመጣም። አንድ አማራጭ ወሰደ። በስተቀኝ ገደል ስለሆነ በሬውና እረኛውን ላለመግጨት ወደ ግራ ተጠመዘዘ እረኛውንና በሬው ቢተርፉም አይሱዙዋ ተገለበጠች መኪናው ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩት 45 ሰዎች ሁለቱ ወዲያውኑ ሞቱ።

የኦሮሚያ ክልል ዐቃቤ ሕግ በጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ፋሲል ላይ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543(3) ስር ያለ ጥንቃቄ ሲያሽከረክር መኪናው በመገልበጡ ሁለት ተሳፋሪዎችን በቸልተኝነት በመግደል ወንጀል ክስ መሠረተበት። የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሹ ፋሲል ጥፋተኛ አይደለሁም በማለቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን የትራፊክ ፕላንና የተሽከርካሪውን የቴክኒክ ምርመራ ውጤት ተቀብሎ አቶ ፋሲልን ተከላከል ሲል ብይን ሰጠ።

የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ተሽከርካሪው ከጅማ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ ሰኮሮ ኩርባ ቦታ ሲደርሱ መገልበጡን አረጋገጡ። አንደኛው ምስክር ተሽከርካሪው በመካከለኛ ፍጥነት ይጓዝ ነበር ሲል ሁለተኛው ምስክር ፍጥነቱን መገመት አልቻልኩም አለ። ሦስተኛው የዐቃቤ ሕግ ምስክር ተከሳሹ ተሽከርካሪውን በፍጥነት ሲያሽከረክር ስለነበር ፍጥነቱን ሳይቀንስ ኩርባው ላይ በመድረስ መኪናው መገልበጡን መሰከረ።

የአቶ ፋሲል የመከላከያ ምስክሮች ተሳፋሪዎች የነበሩ ሲሆን፤ የተሽከርካሪውን ፍጥነት አንደኛው በጥሩ ሁኔታ ላይ ነበር ሲል ሌላኛው ምስክር አደጋው በደረሰ ወቅት በግምት በሰዓት ከ50 እስከ 60 ኪሎ ሜትር ይጓዝ እንደነበር መሰከረ።

የጅማ ዞን ከ/ፍ/ቤት የዐቃቤ ሕግንና የተከሳሽን ማስረጃዎች መርምሮ አቶ ፋሲል ኩርባ ላይ ከ50 እስከ 60 ኪሎ ሜትር በሰዓት በመጓዙ ድንገት የገቡበትን በሬና እረኛ ለማዳን ወደጐን ሲጠመዘዝ መኪናው ተንሸራቶ አደጋው ደርሷል። ሰዎቹ የሞቱትም አቶ ፋሲል ቀስ ብሎ መንዳት በነበረበት ቦታ ላይ በፍጥነት በማሽከርከሩ ነው በማለት የወ/ሕ/አ 543(3) በመተላለፍ ጥፋተኛ ነው ብሎ የቅጣት አስተያየት ተቀብሎ አቶ ፋሲል በአምስት ዓመት ጽኑ እስርና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወሰነበት።

አቶ ፋሲል ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ቢያቀርብም ፍ/ቤቱ ቅጣቱን ወደ ሦስት ዓመትና 5ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ቀነሰለት እንጂ አልሻረውም። ወደ ኦሮሚያ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ ቢያቀርብም የስር ፍ/ቤት ውሳኔን በድምፅ ብልጫ አፀናው።

አቶ ፋሲል ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት “የስር ፍ/ቤቶች የሕግ ስህተት ፈፅመዋል መኪናው የተገለበጠው ድንገት ኩርባ (መታጠፊያ) ላይ የገቡትን እረኛና በሬ ለማዳን በማሰብ መኪውን ወደ ግራ አቅጣጫ ስለጠመዘዝኩት ነው። በዚህ ሂደት የሞቱት ሁለት ተሳፋሪዎች በአደጋ ምክንያት ሞቱ ከሚባል በስተቀር በእኔ ቸልተኝነት ሞቱ ተብሎ ጥፋተኛ ልባል አይገባም። ጥፋተኛ የተባልኩበት የወ/ሕ/አ 543(3) እግረኛን ገጭቶ ለገደለ እንጂ መኪና ተገልብጦ ሰው ለሞተበት አሽከርካሪ ተፈፃሚ ሊሆን አይገባውም። ስለዚህ የሕግ ስህተቱ ታርሞ ውሳኔው ይሻርልኝ” የሚል የሰበር አቤቱታ አቀረበ። የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም ሁለቱ ተሳፋሪዎች የሞቱት በአሽከርካሪው (በአቶ ፋሲል) ቸልተኝነት ነው ሊባል ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን የሕግ ነጥብ ለመመርመር ግራ ቀኙን አከራክሮ ሐምሌ 22 ቀን 2001 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔውን ከማየታችን በፊት አንድ እንጨምር

2. ወንድሙን የገደለው ሹፌር

እዛው ጅማ ነው። ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም አቶ አብነት ዋቆ እንደ እረዳት አብሯቸው የሚሰራውን አብዲ ዋቆን እና ተሳፋሪዎችን ጭኖ የሰ.ቁ.3-28157 ኦሮ በሆነ የሚኒባስ መኪና ከጅማ ከተማ ወደ አጋሮ ከተማ ሲያሽከረክር ከማለዳው 12፡30 ሰዓት ላይ ድንገት ሚኒባስዋ መንገድ ለቃ በመውጣት ከእንጨት ጋር ተጋጭታ ተገለበጠች። ሌሎች ተሳፋሪዎችና አሽከርካሪው አቶ አብነት ሲተርፉ የአሽከርካሪው ወንድም አብዲ ዋቆ በአደጋው ህይወቱ አለፈ።

የኦሮሚያ ክልል ዐቃቤ ሕግ አቶ አብነት ዋቆ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 543(2)ን በመተላለፍ በሹፌርነት ሙያው የሌለውን ህይወትና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ እያለበት በፈፀመው ቸልተኛነት በደረሰ አደጋ አብዲ ዋቆ በመሞቱ ክስ መሰረተበት።

አቶ አብነት ጥፋተኛ አይደለሁም ብሎ ክሱን በመካዱ ዐቃቤ ሕግ የባለሙያ ምስክር በአደጋው ቦታ የተነሳውን ፕላን አቅርቦ አቶ አብነት ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርጉ ሲያሽከረክሩ በደረሰ አደጋ ሟች መሞቱን ስላስረዳ እንዲከላከሉ ተበየነ። አቶ አብነት አደጋው የደረሰው በድንገተኛ አደጋ አጋጣሚ መሆኑን ያስረዱልኛል ያሏቸውን ምስክሮች አቀረቡ። የጅማ ዞን ከ/ፍ/ቤት የአቶ አብነት ማስረጃ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ ባለማስተባበሉ ጥፋተኛ በማድረግ ግራ ቀኙ ባቀረቡት የቅጣት አስተያየት በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ቀላል እስርና በብር ሦስት ሺ የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወሰነ።

አቶ አብነት በውሳኔው ቅር ተሰኝተው ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት እና ለሰበር ሰሚ ችሎት በቅደም ተከተል ይግባኝ ቢያቀርቡም፤ ይግባኛቸው ተቀባይነት አላገኘም።

አቶ አብነት መስከረም 16 ቀን 2006 ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት “የሞት ጉዳቱ የደረሰው የገዛ ወንድሜ ላይ ሆኖ ከአቅም በላይ በሆነ አጋጣሚ ሆኖ እያለ በስር ፍ/ቤቶች መታለፍ ያለአግባብ ነው። ቅጣቱም ተገቢ አይደለም መገደብ ሲገባው በመታለፉም መሰረታዊ የሕግ ስህተት ነው።” የሚል አቤቱታ አቀረቡ። በአቶ ፋሲል ብርሃኑ ጉዳይ በሰ/መ/ቁ. 42703 ከተሰጠው ውሣኔ አንፃርም ተገቢ አይደለም? የሚለውን ለመመርመር የሰበር ችሎቱ ግራ ቀኙ በጽሁፍ እንዲከራከሩ በማድረግ ውሳኔ ሰጥቷል። ወደ ሰበር ውሳኔዎች ከማለፋችን በፊት ወንጀሉን የሚደነግገውን አንቀጽ እንመልከት።

3. በቸልተኝነት ሰውን መግደል

የወንጀል ሕጋችን በአንቀጽ 543 ላይ በቸልተኝነት ሰውን መግደል የሚያስከትለውን ቅጣት ደንግጓል። ድንጋጌው በዋነኝነት የሚመለከተው የሌላውን ሰው ህይወት ጤንነት ወይም ደህንነት የመጣበቅ የሙያ ግዴታ ያለባቸውን እንደ የህክምና ባለሙያዎች፣ አሽከርካሪዎች እና የመሳሰሉትን እንዲሁም ሙያዊ ባልሆንም ሌሎች ከሕግ ወይም ከውለ የሚመነጩ ግዴታዎች ያለባቸው ሰዎች በቸልተኝነት ሰውከገደሉ ሲሆን ቅጣቱ ከአንድ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስር እና ከ3 እስከ 6 ሺህ ብር የሚደርስ መቀጮ ነው።

ጥፋቱን የሚያባብሰውና ኃላፊነቱን የሚያከብደው የሌላውን ህይወት ደህንነት የመጠበቅ የሙያ ወይም ሌላ ግዴታ ያለባቸው ሰዎች፡-

 1. ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሰዎችን ከገደሉ ወይም
 2. ወንጀሉን የፈፀሙት ግልፅ የሆነ ደንብ ወይም መመሪያ በመተላለፍ ከሆነ (ለምሳሌ የትራፊክ ሕጐችን) ወይም
 3. የሚያፈዙ ንጥረ ነገሮችን ወይም መጠጥ በመውሰድ እራሳቸውን ከኃላፊነት የሚያወጣ ሁኔታ ውስጥ ከተው ከሆነ የሚጠብቃቸው ቅጣት ከ5 እስከ 15 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከብር 10ሺህ እስከ 15ሺህ መቀጮ ነው።

ከላይ ከጠቀስኳቸው የሙያ ወይም ሌላ ግዴታ ካለባቸው ሰዎች ውጪ ያሉ ሰዎች ደግሞ በቸልተኝነት ሰውን ከገደሉ የሚጠብቃቸው ከ6 ወር እስከ ሦስት ዓመት ሊደርስ በሚችል ቀላል እስር ወይም ከ2 እስከ 4 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ነው።

4. ሰበር ምን አለ?

እረኛውንና በሬውን ለማዳን መኪናውን ወደ ግራ በማዞሩ ተገልብጦ ሁለት ሰዎች በመሞታቸው ጥፋተኛ የተባለውን የአቶ ፋሲልን ጉዳይ ሰበር ሰሚ ችሎቱ አቶ ፋሲል ለአደጋው መነሻ የሆነውን ድርጊት የፈፀመው በቸልተኝነት ነው አይደለም የሚለውን ለመወሰን የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 59 ለቸልተኝነት የሰጠውን ትርጓሜ አጣቅሷል። በድንጋጌው መሰረት “… አንድ ሰው በቸልተኝነት ወንጀል ፈጽሟል የሚባለው ውጤቱን እያወቀ ውጤቱ አይደርስም ከሚል መነሻ ድርጊቱን የፈፀመ እንደሆነ ወይም ደግሞ የወንጀል ውጤት የሚያስከትል መሆኑን ባያውቅም ውጤቱን ማወቅ ነበረበት ወይም ጥረት ቢያደርግ ውጤቱን ማወቅ ይችል ነበር ማለት ሲቻል ነው።”

በመሆኑም ቸልተኝነት አለ ለማለት ሕጉ የሚጠቀምበት ዋነኛ መስፈርት የተከሰሰው ሰው በድርጊቱና በውጤቱ መሀል ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ ያለው ወይም ሊኖረው የሚገባው ግንዛቤ ነው። ድርጊቱን የፈፀመው ሰው የነበረው እውቀትና ግንዛቤ ወይም ሊኖረው የሚገባው እውቀትና ግንዛቤ የሚመዘነው ከሰውዬው እድሜ ያለው የኑሮ ልምድ፣ የትምህርት ደረጃው፣ ሥራውና የማኅበራዊ ኑሮ ደረጃውን ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 54(1) ይደነግጋል።

በአቶ ፋሲል ላይ የቀረቡት የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችና የመከላከያ ማስረጃዎች የተሽከርካሪው ፍጥነት ከ50 እስከ 60 ኪሎ ሜትር በሰዓት እንደነበር አደጋው የደረሰው መታጠፊያ መንገድ ላይ ድንገት የገቡትን በሬና እረኛ ለማዳን ወደ ግራ በመጠምዘዙ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህ ፍጥነት ከጅማ እስከ አዲስ አበባ ባለው መንገድ መጓዝ ክልክል መሆኑን ስፍራው ላይ የፍጥነት ገደብ መኖሩን የሚያስረዳ ማስረጃ አልቀረበም። የመኪናው የቴክኒክ ብቃትም አሽከርካሪው በዚያ ፍጥነት ማሽከርከር እንዳልነበረበት የማያሳይ በመሆኑ አቶ ፋሲል መኪናው ከመገልበጡ በፊት ተገቢውን ሙያዊ ጥንቃቄ አለማድረጉን የሚያሳይ ነገር የለም።

እረኛው ሲገባ ማድረግ የነበረበት ጥንቃቄም ሲታይ ጨፍልቆ ቢያልፍ ከፍ ያለ ወንጀል ይሆናል ወደቀኝ ገደል ነው ወደ ግራ መጠምዘዙም መኪናወን እንደሚገለብጠው ተሳፋሪዎች እንደሚሞቱም ያውቅ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ በዐቃቤ ሕግ አልቀረበም። በመሆኑም አደጋው የደረሰው በድንገተኛ አጋጣሚ እንጂ በአሽከርካሪው ቸልተኝነት ባለመሆኑ የስር ፍ/ቤቶች አቶ ፋሲልን ጥፋተኛ አድርገው በመቅጣታቸው መሰረታዊ የሕግ ስህተት ስለፈፀመ ውሳኔዎቹ ተሽረው አቶ ፋሲል ነፃ እንዲወጣ ቅፅ 9 ላይ በወጣው በሰ/ወ/ቁ. 42703 ሐምሌ 22 ቀን 2001 ዓ.ም በሞላው ችሎት ወስኗል።

አቶ አብነት ጉዳይም ይህንንኑ ቀድሞ የተሰጠ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም አንፃር በሰበር ችሎቱ መርምሮታል። አቶ አብነት ዋቆ ላይ የቀረበው የባለሙያ ምስክርና የአደጋው ቦታ ፕላን ተገቢ ጥንቃቄ ሳያደርግ በወቅቱ አደጋው መድረሱን በስር ፍ/ቤት ተረጋግጧል። በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 57 ስር ከአቅም በላይ በሆነ ኃይል ወይም ምክንያት አንድ ሰው ምንም ጥፋት ሳይፈፀም ጉዳት ቢያደርስ በወንጀል አይጠየቅም።

ሆኖም አቶ አብነት ተገቢውን ጥንቃቄ በአደጋው ወቅት መድረሱንና ከአቅም በላይ የሆነ አደጋ መከሰቱን የሚያስረዳ ማስረጃ ስላላቀረበ በስር ፍ/ቤቶች ጥፋተኛ በመባሉ የተፈፀመ የሕግ ስህተት የለም።

ሆኖም ቅጣቱን በተመለከተ በግራ ቀኙ የቅጣት አስተያየትና በቅጣት አወሳሰን መመሪያው መሰረት ፍ/ቤቱ መወሰኑን ቡገልፅም ሟቹ አብዲ ዋቆ የተከሳሹ ወንድም መሆኑን እንደ ቅጣት ማክበጀ ምክንያት የሚወስድበት የሕግ አግባብ ስለሌለ አንድ ዓመት ከ6 ወር የነበረውን የስር ፍ/ቤትን ቅጣት ወደ አንድ ዓመት በመቀነስ እንዲቀጡ በሰ/ወ/ቁ. 93741 ታህሳስ 14 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት ወስኗል ውሳኔው የሰበር ውሳኔዎች ቅጽ 15 ላይ ታትሞ ወጥቷል።


ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
6913 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 729 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us