ፕሮፌሰር እንድርያስ ስለጠበቆች

Wednesday, 25 February 2015 12:40

ክፍል-3

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

በክፍል አንድ እና ሁለት ጠበቆችን ተቀባይነት ለሌለው ላልተፈለገ ባህሪ የሚያጋልጡ ምክንያቶችና ተግባሮችን አቅርቤያለሁ። ጽሁፉ ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ በ1984 (እ.ኤ.አ.) በእንግሊዘኛ ቋንቋ በአንድ የፍልስፍናና የሕግ የጥናት መጽሔት ስብስብ ላይ ያሳተሙት የጥናት ሥራቸው ሲሆን፤ ለጋዜጣ እንዲመች አድርጌ ከፋፍዬ ከማቅረብ ውጭ የእኔ ሚና ወደ አማርኛ መመለስ ብቻ መሆኑን እገልፃለሁ።

1.የጥብቅና ሙያ ዓላማ በአሪስቶትል ማነፃፀሪያ

ጠበቆች ከከፍተኛ የፍትህ ዓላማ ይልቅ ዝቅተኛ ለሆነው ሌላውን ተከራካሪ የመርታት ግብ ላይ ያተኩራሉ። ለዚህም ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልጋቸውም። ምክንያቱም የፍትህ ዓላማ ከተከራካሪዎቹ ጋር ሲያዛምዱት ዝቅተኛ መሆኑ የማይቀር ነው። እዚህ ጋር የፍትህ ዓላማ የእያንዳንዱን ዕጣ ፈንታ የማሻሻል ወይም የበለጠ እኩልነት ያለበት ማኅበራዊ መዋቅር መመስረትም አይደለም። እዚህ ጋር ፍትህ በግርድፉ የሚያዘው ግለሰቦች አንዱ በሌላኛው መንገድ ላይ እንዳይገቡ ሲሆን አንዱ በሌላኛው መንገድ ላይ አቋርጦ ከገባ ደግሞ በመንገዱ ላይ ማን መብት እንዳለው ይወስናል። የፍትህ ጥያቄ የሕግ ክርክሮችን በዚህ መልኩ መፍታት ከሆነ ደግሞ ጠበቃው አስተውሎቱ በመውረዱ አቅሙን በትክክል መቆጣጠሩ ብቻ ሳይሆን በትክክለኛው አቅጣጫም አስኪዶታል ሊያስብል ይችላል።

ምንም እንኳን የዘመኑ የጠበቆች ገጽታ ለአሪስቶትል የጥሩ ወታደር ምሳሌ ታማኝ ቢሆንም፤ ጠበቆችን በአሳማኝ መልኩ የሚገለፅ አይደለም። ምክንያቱም የአሪስቶትል የመልካም ወታደር እሳቤ በራሱ እኔ እንደማስበው ከፍተኛ ግድፈት ስላለበት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ከምሉዕ ያነሰ መልካምነት ያላቸው ሰዎች የተዋጣለት ወታደር ይወጣቸዋል የሚለው ድምዳሜው በጣም በጠባብ የዓላማ ትርጉም ላይ የተመሰረተ ነው። እንደ የጦርነት ስልት መንደፍ፣ ጦርነት ማሸነፍ፣ የዘመቻ ጉዞ መጓዝ ያሉ በርካታ ድርጊቶች ውስጣዊ ትስስር ያላቸውን ዓላማዎች ያካተቱ ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ውስብስብ ድርጊቶች ስንፈፅም በወቅቱ የቅርብ ዓላማችን የነበረውን የጦርነት ስልቱን መተግበር፣ ይሄን ድልድይ መያዝ፣ ያን ድልድይ ማቋረጡን ሁሌም በትክክልም ዋነኛው ጥረታችን ነው ብለን አንገልፀውም። እነኚህ የቅርብ ዓላማዎች የሚፈለጉት የትልቁና የሩቁ ዓላማ አካል ስለሆኑ ሲሆን፤ ሆኖም ግን ለአድራጊው ተወካይ ወይም ከእሱ በፊት፣ በሂደቱ ላይ ወይም ከስራው በኋላ ለሚመጡት እንዴት ለመጨረሻው ግብ እንደሚውሉ ግልፅ ላይሆንላቸው ይችላል። ይህ ከሆነ ታዲያ አንድ የላቀ እይታ ያለው ሰው እነኚህ ወታደሮች እንደ ድልድይ ወይም ኰረብታ ለመያዝ ሲሉ ብቻ ለዚያ ሁሉ አደጋ መጋለጣቸው እንዴት መልካም ነገር ነው ብሎ አይልም። ምክንያቱም ሀሳባቸው ያን ድርጊት መፈፀም ብቻ አይደለም። ከጨካኞችና ኃላፊነት ከማይሰማቸው በስተቀር የወረራውን ዓላማ አንዳችም ትኩረት ሳይሰጥ ማንም ሰው በፈቃደኝነት ዴን ቤን ፑን ለመማረክ ከእሳት ጋር አይጋፈጥም።

ዓላማዎችን ለቀቅ ባለ መልኩ ከተረዳናቸው ማለትም የጦርነቱን ግብ እንዲሸፍኑ ተደርገው ሲታሰቡም አሪስቶትል ያልበዛ መልካምነት ጥሩ ወታደር ያስገኛል የሚለው አባባሉ አሁንም ግልፅ አያደርገውም። የዚህ መነሻ ጦርነቶች እንዴት ፋይዳ ቢስ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመጠቆም ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ድምዳሜውም በውጤቱ ጠቀሜታ አለአግባብ ተፅዕኖ ያረፈበት ነው። ሰዎች በውጊያ ላይ ትልልቅ አደጋዎችን የሚጋፈጡት ግጥሚያውን ማሸነፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ሲያምኑ ብቻ ሳይሆን ጓዶቻቸውንም ለመርዳት ሲሉ እራሳቸውንም ሊሰው ይችላሉ። በይበልጥ ደግሞ እኛ ቀላል ግብ ነው ብለን የወሰድነውን ነገር በማካሄድ ላይ እያለን ካልጠበቅነው አስፈሪ ተግዳሮቶች ጋር ሊያጋጥሙንና እነሱን ስንጋፈጥ ትልቅ ወኔ ልናሳይም እንችላለን። ይሄኔ ግን የበለጠ ካላቸው ይልቅ አነስተኛ መልካምነት ያላቸው ሰዎች የተዋጣላቸው ወታደሮች ይሆናሉ ብለን ለማሰብ የሚኖረን ምክንያት አነስተኛ ይሆናል። በአጠቃላይ አነስተኛ መልካምነት ያላቸው ሰዎች ሁሌም በተሻለ መልኩ ሊያከናውኑት የሚችሉት ነው የሚባል መልካም ተግባር የለም።

የአሪስቶትላውያኑን ስናጤነው ክብደቱ የሚመነጨው የወታደራዊ ወኔ እሳቤ ጠበቃውን እንደተዋጊ አድርጐ ከማሰብ ነው። የጠበቃው ዓላማ ደንበኛው ቀዳሚ ሆኖ በማየት የቅርብ ግብ ላይ ብቻ ሊገደብ የሚችል አይደለም። በተለይም ይህ አይነት ግብ ፋይዳ ቢስ ወይም የተሳሳተ መሆኑን ለማጤን የሚያስችለው ጥሩ ደረጃ ላይ እንደመገኘቱ ነገሩን የሰፊው ስርዓት ዓላማ አካል አድርጐ ማየት ግዴታው ነው። ጠበቆችን ሁሌም የደንበኛቸውን ማሸነፍ ብቻ የሚሹ አንድ ዓላማ ያላቸው አድርጐ ለማሰብ ከአብዛኛው ሰው በባሰ ሁኔታ የደኸየ ስነልቦና መስጠት ይኖርብናል። የጠበቃው ዓላማዎች አመኔታ በማይጣልበት መልኩ የዘቀጡ ቢሆኑም እንኳን እነሱም ላይ ለመድረስ አስፈሪ አደጋዎች እና ፈተናዎችን ማስወገድን ሊጠይቀው ይችላል። ለምሳሌ የደንበኛውን ዓላማ ለማሳካት አለቅጥ መሯሯጡ ጠበቃው ላይ አስከፊ ጉዳት ሊያደርስበት ይችላል። ስለዚህ የወረዱ ዓላማዎችንም እንኳን ለማሳካት በሚያደርገው ተገቢ ጥረት ውስጥ ጠበቃው በስራው ላይ የተለያዩ ዓይነት የላቁ ብቃቶች ሊያስፈልጉት ይችላል።

2.ጥብቅና እንደ ውድድር ወይም ግጥሚያ ሲታይ

ጠበቃውን እንደ ተዋጊ በማሰብ ውስጥ ያለው ችግር የሕግ ሥርዓቱን ወይም እንደሚባለው የሕግ ሙግቱን (የክርክር ውድድሩን) እንደ ጨዋታ ግጥሚያ ከማየት ጋር የተያያዘ ነው። አብዛኛዎቹ ጨዋታዎች በጥንቃቄ ከሞራል (ከምግባሩ) ዓለም የተገለሉ ናቸው። በጨዋታ ውስጥ የእንቅስቃሴው ዓላማዎች እንዲሁም ውጤታማ ለመሆን የሚደረጉ የተገቡና ያልተገቡ አካሄዶች የሚተረጐሙት በጨዋታው ሕጐች ነው። በእነዚህ ሕጐች ውስጥ ሆነው ተጫዋቾቹ ለተሰጥኦዋቸው፣ ለክህሎታቸው እና ለልዩ ብቃታቸው ነፃ መድረክ የሚሰጧቸው ለግባቸው ፋይዳ ወይም ዓላማቸውን ለማሳካት ለሚያልፉበት ሂደት ሞራላዊ አግባብነት በትኩረት በማጤን አይደለም። ምንም እንኳን ምንም ያህል ሞራላዊነት (ተገቢ ምግባር) እና በየትኛው ገፅታው በሕግ ውስጥ ይታያል የሚለው ምክንያታዊ የሆነ አለመስማማትን ሊያስነሳ የሚችል ቢሆንም፤ ሕግ በተራ ሁኔታዎቹ ላይ እንኳን እንደ ስፖርት ወይም እንደ አሪስቶትላውያኑ ውጊያ ከመካከለኛ ምግባር (የሞራል) ህይወት ተለይቶ የተዘጋበት አለመሆኑ ላይ ብዙ አጠራጣሪ አይደለም። በመሆኑም ጠበቆች በስራቸው የተፈቀዱ ክህሎቶችን በመጠቀም ስህተት ሳይፈጽሙ ለደንበኛቸው አሸናፊነት ሲሉ ያለአንዳች ርህራሄ በቁርጠኝነት ሊሰሩበት አይችሉም።

በማንኛውም ደረጃ ላይ ጠበቆች የአሪስቶትላውያኑን ወታደር የማይመስል አሰራር ለራሳቸው በመከተል የሚሳካላቸው ከሆነ በሙያዊ ስራቸው ተፅዕኖ ሚናቸውን ስለሚያግዙት በስራቸው የሚዋጡት ከፍተኛ ዋጋ ከከፈሉ ነው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ የጠበቃው ግላዊ ባህሪ በሙያዊ ስራው ሊደርስበት አይችልም ምክንያቱም በተጨባጭ ግላዊ ባህሪ ስለማይኖረው ነው። በነቀዘ ባህሪ ላይ ከመፈናጠጥ ካለ ግላዊ ባህሪ መቅረቱ የከፋም ሆነ አልሆነ ባህሪን መንሳቱ (ማሳጣቱ) የሚናቅ የሙያው ጠባይ ሊሆን አይችልም።

ምናልባትም የጠበቃው ግላዊ ህይወትና ባህሪ ከጠቃሚው የሙያዊ ሥራው ጐጂ ተፅዕኖዎች የማይደፈር ወይም የማይነካ አለመሆኑን መግለፁ አስደንጋጭ ላይሆን ይችላል። ለነገሩ አንድ ሰው ሊኖርበትና ሊከበርበት የሚችለውን ሥራው ውስጥ እጅግ ምክንያታዊ እንዲሆን ወይም መተዳደሪያው ሁልጊዜም ህይወትና ምክንያታዊ ባህሪ እንዲኖረው መጠበቁ በጣም የሚበዛ አይደለም።

3.ጥብቅና ሞራላዊ ፀፀት ሲያስከትል

ጆን ራውልም የሰነዘረው ሀሳብ አንድ ሰው ስለራሱና ስለ አካባቢያዊ ሁኔታው ባገኘው እጅግ ትክክለኛ መረጃ መሰረት በምክንያታዊነት መርጦት የነበረውን የተሻለ ህይወት በመምራቱ ጥልቅ የሆነ መከፋት ሊያድርበት አይችልም የሚል ነው። ራውል በአፅንኦት እንዳስቀመጠው በምክንያታዊነት የተሻለ የተባለው ህይወት የሚያሰቃይ መሆኑ ቢገለጥለትም እንኳን ግለሰቡ ስቃዩን እሱ ያመጣው እንዳልሆነ በሚኖረው እውነተኛ እምነቱ ውስጥ መፅናናትን ያገኛል። እራሱንም በምክንያታዊ እሳቤ በጥፋተኝነት ሊወቀስ አይችልም። ምክንያቱም ከዚህ የተሻለ ማድረግ የሚችለውም ነገር ስላልነበረው ነው። ይህን ቢልም ራውል ተቀባይነት ያለውን ህይወት በመኖሩ የሞራል ወይም የምክንያታዊ አስተሳሰብ ፀፀት ሊያድርበት የማይችልም ሰው ቢሆን ሙሉ በሙሉ ያን ህይወት በመኖሩ የተፈጥሮአዊ የሆነ ፀፀት ሊሰማውም እንደሚችል ያምናል።

ሆኖም ግን ይህ መከራከሪያው የተሽመደመደ ነው። ምክንያቱም ከዚህ መሰረታዊ የሆነ ተፈጥሮአዊ ቁጭት ከሞራል ፀፀት ነፃ መሆን ጋር ሲተያይ ብዙም ሊጣጣም የሚችል ባለመሆኑ ነው። የመጪው ጊዜ ሁኔታው ሲታይም የሚኖርበት ህይወት ውስጥ የነበረውን ተነሳሽነቱን ያጣ ሰው በምክንያታዊነት የተሻለ የሚለውን ህይወት ለመምራት ተነሳሽነቱን ከየት እንደሚያመጣውም ግልፅ አይደለም። ታዲያ ይህ አይነቱ ሰው የራውልን የራስ ክብር መሰረታዊ ጥሩነቶች ወይም አንድ ሰው ህይወቱን ለመምራት የሚሰሙት የሚችሉና ዋጋ ያላቸው ነገሮችን አጠሩትም? እስከ ተቃራኒያዊ ሙግቱ መዳረሻ ድረስ ብቻ የሚኖር ጠበቃ ደግሞ በተመሳሳይ አካሄድ ሲታይ የከፋ አደጋ ውስጥ የሚገኝ ነው። የሚጠየቀውን ነገር ሲፈፅም ሞራላዊ አግባብነታቸው አጠያያቂ የሆኑ ድርጊቶች ላይ ሊሰማራና በዚህም የማይፈለግ ባህሪ ሊይዝ ይችላል። ይህ ሁኔታም ተፈጥሮአዊ ፀፀት (ቁጭት) ብቻ ሳይሆን ምግባራዊ (ሞራላዊ) ፀፀት ውስጥም ለመካተት በቂ ምክንያት ይሆንበታል።

ተሟጋቹ ጠበቃ በሙያዊ ሚናው ላይ ጉዳትን ማስወገድ እንዳይችል ብሎም ይህን ብርቱ ጉዳይም እንዳይቀበል መፍቀድ ይቻላል። ማንኛውም የዚህች ዓለም የተወሰኑ እውነታዎች ያልተጨበጡለት ሰው እንኳን የተወሰኑ ጠቃሚ ማኅበራዊ ግቦች ግላዊ መስዋዕትነትን እንደሚጠይቁ አያጣውም።

ጠበቆችም ሙያቸው ምርጫቸው እንደመሆኑ ለሌሎች መልካም ለመሥራት ወይም ለአጠቃላዩ ህዝብ የጋራ ጥቅም የራሳቸውን ጥቅም መስዋዕት እንዲያደርጉ የተወሰኑ ነገሮችን ለመጠየቅ ያላሰብንበት ደረጃ ላይ አይደለንም። የጠበቆች መልካም ባህሪን (መገለጫን) ማጣትም በራስ የሚከፈል መስዋዕትነት ጉዳይ ነው።

    ፕሮፌሰር እንድርያስ ጠበቆች የሚጋለጡባቸውን የሥራ ባህሪ ችግሮችና መነሻዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን የተነተኑት ለአጠቃላዩ ኅብረተሰብ ጥቅምስ ምን ማድረግ አለባቸው የሚሉትንም ነጥቦች አንስተዋል። ሳምንት በክፍል አራት እንቀጥለዋለሁ። በነገራችን ላይ የፕሮፌሰር ጽሁፍ በዋነኝነት (Adversarial lawyer) የሚባለው ከኰመን ሎው የሕግ ስርዓት ውስጥ ባለጉዳዮቻቸውን ወክለው የሚከራከሩ ጠበቆችን የሚመለከት ነው። በዚህ የሕግ ስርዓት ውስጥ የዳኞች ሚና ውስን ሲሆን፤ የማሳመኛ ነጥቦችን፣ ማስረጃዎችን ምስክሮችን የሚያቀርቡትም ሆነ የሚያውጣጡት ጠበቆቹ ናቸው። ዋነኛ ጥረታቸውም ለጁሪው (ከኅብረተሰቡ ለተውጣጡ ጥፋተኛነት ፈራጆች) የደንበኛቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ማሳመን ነው። በሀገራችን የምትከተለው የሲቪል ሎው ሥርዓት ግን የሚከተለው ከዚህ የተለየውን ሲሆን፤ እውነታውን ለማጣራት ከተከራካሪ ወገኖች በተጨማሪ ዳኞችም የራሳቸው ተሳትፎና ሚና አላቸው። በመሆኑም የፕሮፌሰር ጽሁፍ ሙሉ በሙሉ የሀገራችንን ጠበቆች አሰራር የሚመለከት ባይሆንም፤ የጥብቅና ሙያ መሠረታዊ ባህሪያት ግን በሁለቱም የሕግ ስርዓቶች ተመሳሳይ በመሆኑ ለእኛም ሀገር የጥብቅና ሙያ ውስጥ ጽሁፉ ጥሩ ግንዛቤ ያስጨብጣል ብዬ ስላመንኩ ተርጉሜ ማቅረቤን ማስታወስ እወዳለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
5843 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 860 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us