ፕሮፌሰር እንድርያስ ስለጠበቆች

Wednesday, 11 March 2015 12:49

ክፍል 4

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ


ከክልል 1-3 ጠበቆች ላልተገባ ባህሪ የሚጋለጡባቸውን ውጪያዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ከፍትህ ይልቅ ለደንበኛ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥቶ መሟገት በጠበቆችና በአጠቃላይ ኅብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ አይተናል።

በዚህ በመጨረሻው የፕሮፌሰሩ ፅሁፍ ጠበቆች ግላዊ ከሆነ ውክልና ባሻገር የሚወክሏቸውን ፍላጐቶች በምን መስፈርት መምረጥ አለባቸው እነማንንስ ሊወክሉ ይገባል? ተቋማዊ ለውጥን በማምጣት ያላቸው ሚናስ ምንድን ነው? የሚሉት እና ሌሎችንም ጠቃሚ ነጥቦች ተዳሰዋል። መልካም ንባብ።

ጠበቆች መልካም ባህሪያቸውን የሚያጡት ራሳቸውን ለመስዋዕት ስለሚያቀርቡት ነው። ለገዛ እራሱ መልካም ነገሩን ለመስዋዕትነት የሚያቀርብ ጠበቃ አመለካከት ሌኒን የቤትሆቨንን አፓሽኔታ ሙዚቃ ሲሰማ ከገለፀው ጋር ተመሳሳይ ነው፡-

“እጅግ የሚያስደምም የልዕለ ሰብ ሙዚቃ… ሰዎች እንዲህ ያለ ተአምርም ይሰራሉ… እኔ ግን አዘውትሬ ሙዚቃ ማድመጥ አልችልም። ስሜቴን ስለሚነካው የማይረቡ የደግነት ቃላትን መናገር እንድፈልግና ተነስቼ በቆሻሻ የምድር ሲኦል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ትንንሽ ጭንቅላቶችን አይዟችሁ በሚል ስሜት እንድደባብሳቸው የሚያደርግ ውበት የሚፈጥር ነው። አሁን ግን ማንም ሰው የማንንም ትንሽ ጭንቅላት መዳበስ የለበትም… እጁን ሊመቱት ይችላሉ። ማድረግ ያለበት ትንሽ ጭንቅላታቸውን መምታት ነው። ያለርህራሄ መኰርኰም። ምንም እንኳን በሀሳብ ደረጃ ማንኛውንም አይነት ኃይል በሰዎች ላይ መጠቀምን ባንደግፍም ነገሩ ግን እጅግ ከባድ ሥራ ነው።”

በእንዲህ አይነቱ ምርጫው የማይደሰቱ ሌሎችን በተመለከተ ደግሞ ከጠቃሚና አስቸኳይ ማኅበራዊ ሚናዎች ጋር ለሚጋፈጡትና የነፍሳቸውን ንፅህና ለሚጠብቁት ሰዎች አንዳንዶች የሚሰማቸው የንቀት ስሜት ይሰማዋል።

እኔ ይህን ተቃውሞ የሚያሰምሩበትን ተግባራዊ እይታዎችና አመለካከቶችን ለመከራከር ወይም መሰረታዊ የሆኑ ማኅበራዊ እሴቶች አደጋ ውስጥ ሲወድቁ ያላቸውን ጉልበት ማናናቅ አልፈልግም። ከዚህ ይልቅ ጠበቆች በተለይም መልካም ባህሪያቸውን መተዋቸው ለምን መጥፎ እንደሚሆንባቸው ጥቂት ምክንያቶችን እጠቁማለሁ። የጠበቃው የተሟጋችነት አቋም ያልተገባ የሚሆንባቸውና የተዋጊነት ባህሪና ክህሎት በዚያ ሚናው ውስጥ ሲካተቱ ሙያዊ አገልግሎቱን በደምብ ለመወጣት እንቅፋት የሚሆኑባቸው ወሳኝ የሆኑ የሕግ ሁኔታዎች አሉ። በመሆኑም የጠበቃው መልካም ባህሪውን በራሱ የመሰዋቱ ሁኔታ የግል ጥሩነትን ብቻ ማጣት ሳይሆን የአጠቃላዩን ኅብረተሰብ ጥቅሞች ማሳጣትም ጭምር ነው።

1.ጠበቃውና ግላዊ ባህሪው ከአጠቃላይ ህዝብ ጥቅም አንፃር

የጠበቃው ባህሪ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ለማየት የሕግ ሥራን ዓላማ በጠባቡ ከሚያይ አተረጓጐምን አለመያዙ ጠቃሚ ነው። የሕግ ክሶች ዓላማ ሁልጊዜም ግልፅ በመሆኑና በተቀመጡ ሕጐች ላይ የሚነሱ የግል ክርክሮችን መፍታት አይደለም። በፍትሐብሔርም ሆነ በወንጀል ክርክሮች ውስጥ በሰፊው ሲታይ አንዳንድ ጊዜ ሕጉ ላይ ለውጥ የማምጣት ዓላማ ያለው ይሆናል። የሕግ ለውጥን የሚያስከትሉ ውሳኔዎች ቀጥተኛ ውጤታቸው በተከራካሪ ወገኖች ላይ ብቻ ሳይገደብ እርቆ የሚሻገር ተፅዕኖ አላቸው። ለእንዲህ አይነት ክርክሮች የሚያሳዩ ምሳሌዎች አንድ በት/ቤት ውስጥ የሚፈፀም የዘር መድሎን በፖሊስ ዲፓርትመንት ውስጥ ያለውን ይፋ የሆነ ማንአለብኝነትና ጭካኔ የሚፈፀምባቸውን ተቋማዊ ስህተቶች ለማረም የተነሱ ክርክሮች ይጠቀሳሉ።

ተቋማዊ ስህተት ላይ ያነጣጠረ ክርክር ውስጥ ተከሳሾቹ የት/ቤቱ ኃላፊ ወይም የፖሊስ አዛዡ ላይከሰሱ ወይም አስቦ ወንጀል በመስራት ጥፋተኛ ላይባሉ ይችላሉ። እውነታኛው የክሱ ኢላማም መዋቅራዊ ኢ ፍትሐዊነትን የፈጠረው ተቋም ላይ ያነጣጠረ ነው። ተከሳሾቹም ማኅበራዊ ጥናት ያመጣውን ተቋም ለማቋቋም ወይም ህልውናውን ለማስጠበቅ ያለባቸው ኃላፊነት ጥቂት ነው ወይም ኃላፊነት ላይኖርባቸውም ይችላል። በመሆኑም የሚፈለገው ውጤት በሕግ ውሳኔ ተቀባይነት ካገኙት ማኅበራዊ እሴቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ ተቋሙ እንዲሄድ የሚያስችሉ የተወሰኑ ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ማስገኘት በመሆኑ መፍትሄውን ተከሳሾቹ የሚሰጡት አይደለም። በተመሳሳይ ክሱን የመሰረተው ግለሰብም የተቋማዊ ጥፋቱ ተጠቂ ላይሆን ይችላል። ከሳሹ በተቋሙ የተበደለ ከሆነም በርካታ ቁጥር ያላቸው ተበዳዮች የክሱ አካል ላይሆኑ ይችላሉ። በተለይም እንደ ዘር መድልዎ ባሉ ክርክሮች በመንግስት ተቋማት ባልተገባ መልኩ የተሰተናገዱ ተበዳዮችን መለየቱ በጣም ከባድ ነው። በመጨረሻም ከሳሽም ሆነ ተበዳዮች ተቋማዊ ለውጥን ማስገኘት በሚፈለገው ዳኝነት ላይ እውነተኛ ተጠቃሚዎች ላይሆኑም ይችላሉ። ብቸኛው የሚቻልና ተገቢ የሆነው የማስተካከያ እርምጃው የወደፊቱን ሁኔታ ያካተተና ጥያቄ ባስነሳው ኢ-ፍትሐዊ ተግባር በቀጣዩ ጊዜ ሰለባ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ለመጠበቅ የሚያስችል ተደርጐ የሚቀረፅ ነው።

  1. ጠበቆችና የተቋማዊ የለውጥ ክርክሮች

በተቋማዊ ጥፋቶች ላይ በሚነሱ የሕግ ክርክሮች ውስጥ ጠበቆች የተሟጋችነት (ባላንጣዊ) ሚናዎችን መጠበቅ አይችሉም። የመጀመሪያውን ችግሩን አብርሃም ቻይስ ባነሳው ጥያቄ ላይ አመላክቶታል።

“የተለየና ፍላጐቱን አስረግጦ ማስቀመጥ የሚችል ደንበኛ በሌለበት በሙግት ክርክር ስርዓቱ በሚካሄድበት አግባብ ጠበቆች የሚኖራቸው ግዴታና ስራ ይኖራል ብለን ልንተማመንበት እንችላለን?”

(The adversarial Lawyer) ተሟጋቹ ጠበቃ የደንበኛውን ፍላጐትና ጥቅም አንግቦ ሕግ በሚፈቅደው መንገድ እንዲያስኬደው ይጠበቅበታል። ሆኖም ጠበቃው ተቋማዊ ጥፋትን ለማስተካከል የሚፈልጉትን በሚወክልበት ጊዜ መከተል ያለበትን ስነ-ስርዓት በግልፅ ወይም ስሜት በሚሰጥ መልኩ የሚያሳዩ ነገሮች ያሉ አይመስልም። የተከራካሪዎቹ ማንነት እና የፍላጐታቸውን አይነት ለመወሰንም ሊከብድ ከመቻሉ በተጨማሪ እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን ለመወሰን ጠበቃው የተለየ ምቹ ሁኔታ ላይ መሆኑም ግልፅ አይደለም። ጠበቃው እነኚህን ችግሮች መፍታቱ ቢሳካለትም እንኳን በተቋማዊ ጥፋቱ በተቃራኒ ያሉ ተከራካሪ ወገኖች በፍላጐታቸው ላይ በተቋሙ የደረሰው ጉዳት የተለያየ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል። በመሆኑም ጠበቃው የትኞቹ የተበዳዮች የሚጋጩ ጥቅሞች በፍ/ቤቱ እንደሚያቀርብ መወሰን ቢኖርበትም ይህ ውሳኔ ቀላል ወይም የሚያጨቃጭቅ ሊሆን አይችልም። በቁጥር የሚበዙትን፣ የተሻለ ተሰሚነት ያላቸውን ወይም የተሻለ ኃይል ያላቸውን አካላት ፍላጐት መወከሉ ደግሞ ምክንያታዊ አሳማኝነት የለውም። በእነዚህ ማዕቀፎች ውስጥ ያሉ ተወዳዳሪ ጥቀሞችን መወሰኑ ደግሞ ለምሳሌ ከመጪው ጊዜ ሰዎች ጥቅም አንፃር ለመወሰን ወይም ተአማኒነት ለማግኘት የሚችል አይሆንም። እነኚህ ችግሮች ሲጋረጡበት እሱ ለማረም የሚፈልገው አንዳች አይነት ተቋማዊ ስህተት ውስጥ ለአደጋ የተጋለጡ ጥቅሞችን ፋይዳ በህሊናው ማብሰልሰሉን ገሸሽ ሊያደርገው አይችልም። ይህ ማሰላሰል ደግሞ አግባብ ባለው ከጥቅም ወይም ከፍላጐት በነፃ መርህ በመሳብ ካልሆነ በስተቀር ብዙም ርቆ ሊጓዝ አይችልም።

3.ጠበቆች ማንን መወከል አለባቸው?

የወገንተኝነት አቋም ላይ ለማደም የሚሞክር ጠበቃም ተመሳሳይ ችግሮች ይገጥሙታል። በተቋማዊ ጥፋት ላይ ባነጣጠሩ የፍ/ቤት ክርክሮች ውስጥ በሚፈለገው ማሻሻያ ላይ ስር የሰደዱ ልዩነቶች ሊኖሩም ይችላሉ።

ለምሳሌ በትምህርት ቤት የዘር መድሎ እንዲቀር የሚፈልጉ ወገኖች ትምህርት ቤቶች እኩል ተደራሽነት ይኑራቸው ወይስ ዝቅተኛው አማካይ ትምህርት እኩል ተደራሽነት ይኑረው የሚለው ትክክለኛው የችግሩ ማስተካከያ በሚለው ላይ ላይስማሙ ይችላሉ። የአናሳ ቁጥር ያለው ህዝብ ወላጆች ለልጆቻቸው ሁሉም ተቀላቅሎ በሚማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ አማካይ ትምህርት እንዲያገኙ መምረጣቸው ተረጋግጧል ቢባል ጠበቃው የወደፊቱ ተማሪ ህፃናት እና መጪው ትውልድ በጠቅላላ በዘር በተከፋፈሉ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ጥቅማቸው በደህና ሁኔታ የሚጠበቅ ከሆነስ የሚለውን ማጤን ይኖርበታል። ምክንያቱም ለምን አይነት ተቋማዊ ተሀድሶ ነው የምሟገተው የሚለውን ለመወሰን ጠበቃው አሸናፊ የሚያደርገው የተዘጋጁ ጥቅሞች ስለማይኖሩት ነው። በመሆኑም ኃላፊነት የተሞላበት ውሳኔ ከሚጋጩ ጥቅሞች ባሻገር ያሉትን የፍትህ ስርዓቱን የሚያተኩርባቸው ህዝባዊ እሴቶችን የሚያስተውል መሆን አለበት።

በርግጥ በተቋማዊ ጥፋት ክስ ላይ የተሰማራውን ጠበቃ ቀዳሚ የሙያው ዓላማ የሕግ ፍትህን ማስገኘት እንደሆነ የፍ/ቤቱ ሠራተኛ አድርጐ ማሰቡ ሊያሳስት የሚችል ነው። ልክ እንደ ዳኛው ጠበቃውም ከመንግስት ነፃ (ገለልተኛ) ነው። እዚህ ጋር ይህ ያነሳነውን ገለልተኝነት በተለይም ጠቃሚ የሚያደርገው ክሱ የሚቀርበው በመንግስት ተቋም ላይ ሲቀርብ ነው። ነገር ግን ዳኛው እንጂ ጠበቃው የተወሰኑ ጥቅሞችን ከመወከል ኃላፊነት ነፃ የወጣ አይደለም። ነገሩን የሚያካብደው ደግሞ ጠበቃው የተሟጋችነት ባላንጣዊ ሚናውን በመከተል ከዚህ የተወካይነት ግዴታው ሙሉ በሙሉ ሊላቀቅ አለመቻሉ ነው።

4.ጠበቆችና ፖለቲካዊ ውክልና

ምናልባት ተቋማዊ እና ፍትሐዊነትን የሚሟገት ጠበቃን ሥራ እና ኃላፊነት ለመረዳት የተሻለው መንገድ ልማዳዊ በሆነው ተመጣጣኝ (ተገቢ) የፖለቲካዊ ውክልና እሳቤ ውስጥ ማየቱ ነው። ተገቢ ፖለቲካዊ ውክልና ቢያንስ ሦስት የተለያዩ ተቀባይ የሚያደርጉት ዓላማዎች አሉት።

የመጀመሪያው መንግስታዊ ውሳኔዎች የተወሰኑ ሰዎችን የሚደግፍና የሌሎችን ደግሞ የሚያደናቅፉ በመሆናቸው ያልተካተቱት ሰዎች ጥቅም ቸል አለመባሉን ለማረጋገጥ በውሳኔው ተፅዕኖ የሚያርፍባቸው ሁሉ ተገቢነት ያለው ውክልና ሊኖራቸው ስለሚገባ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ መንግስታዊ ውሳኔዎች የሚከበሩና ቅቡልና ያላቸው በመሆናቸው ሰዎች እነሱ የሚመርጡትን መርህ እውን የሚያደርጉ ውሳኔዎችን መፈለጋቸው ነው። በቂና ሁሉን አቀፍ ውክልና የሚያስፈልገው የጋራ የሆኑ መርሆዎችን የተሻለ የሚያሟሉ እሳቤዎች በውሳኔ መስጠቱ ውስጥ የመሰማት እድል እንዳያጡ ነው። ሦስተኛው መንግስታዊ ውሳኔዎች ተግባራዊ ሊሆኑ በሚችሉ መልኩ መቀመጥና የሚሳተፉባቸው ሊወጧቸው የሚችሏቸው መሆን ስላለባቸው ነው። በቂ እና ሁሉን ያማከለ ውክልና የሚያስፈልጋቸው በውሳኔው የሚገደዱ ግለሰባዊ ወይም ማኅበራዊ ሁኔታዎች የሚያስከትሉት ከፍተኛ የሆነ ጫና ካለ ሳይታወቅ እንዳያልፉ ለማስቻል ነው።

አይነተኛ የሆነ ምሉዕ ውክልና ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት ዓላማዎች የሚያሟላ መሆን ይገባዋል። የመጀመሪያውን ብቻ ነጥሎ ትኩረት መስጠቱ የበለጠ ቅቡልነት ያላቸው እያሉ ለጠንካሮቹ ፍላጐት ወይም ጥቅም ማዘንበል ይሆናል። ሁለተኛውን ዓላማ ለብቻው መከተል ደግሞ በህዝቡ ላይ የሚፀኑት ውሳኔዎች ከተወከሉት ጋር የሚዛመዱ ጥቅሞችን ብቻ የሚያስተጋቡ ይሆናሉ። ሦስተኛው ዓላማ ካልተካተተ ግን አደጋ አለው። የተወሰነውን ውሳኔ የሚመለከታቸው ሰዎች በቀላሉ ሊገዙለት ወይም ሊከተሉት አይችሉም። ለምሳሌ ወገንተኛ ያልሆነና በመርህ ላይ የተመሰረተ መሬትን የህዝብ ያደረገ የመሬት ስሪት ማሻሻያ ፖሊሲ ወይም ልዩነትን ወይም ማግለልን የከለከለ የትምህርት ቤት አውቶብስ አጠቃቀም ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ ይሆናሉ። ሆኖም ሦስተኛው የውክልና አይነት በራሱ ተጨባጨና እንዲያውም ከፍተኛ ስህተት የነበሩ ነገሮች ላይ በተግባቦት ላይ የተመሰረተ የሰመረ ማኅበራዊ አተገባበር ሊያስገኝባቸው የሚችል ነው።

ተቋማዊ መሻሻልን ለማስገኘት በታሰበ የፍ/ቤት ክርክር ውስጥ ጠበቃውም በእነኚህን በበቂና ሁሉን ያማከለ ውክልና ውስጥ ያሉ ሦስት አለማዎችን ማገናዘብ አለበት። በውሳኔው የሚነካ እንዳችም ጉልህ የሆነ ጥቅም ሰይጣን እንዳልተተወ ማየት ይገባዋል የሚያቀርበውን ትክክለኛ የዳኝነት ጥያቄ ቢወሰንም ጠበቃው የሚወክላቸውን ሰዎች አስተያየት ማገናዘብና በጥንቃቄ መመዘን አለበት። በተጨማሪ በጉዳዩ ላይ ፍላጐት ወይም ጥቅም ያላቸውን ወገኖች ምክርና የተደራጀ ተሳትፎ በመጠየቅ ጠበቃው የታቀደው ተቋማዊ ማሻሻያ አላስፈላጊ ስነ-ልቦናዊና ስነ-ማኅበረሰባዊ ውጥረቶችን በተጠቃሚዎቹ ላይ እና በሌሎች ላይ እንደማያስከትል ማረጋገጥም አለበት። ምንም እንኳን የተወሰኑት የውክልና ኃላፊነቶችን የመንግስት ተሟጋች ነገረፈጅም የሚጋራቸው ቢሆኑም የተወሰኑ ልዩ ጥቅሞችን በሚወሰኑ ጠበቆችና በይበልጥ ደግሞ በዳኞቹ የተነሳ ጠበቆቻችን ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። እነኚህን በብቃት ለመወጣት ምን ማድረግ አለባቸው የሚለውን ለይቶ ቢያንስ እንደ አንድ የአሰራር መመሪያ ማስቀመጡ ሊከብድ ይችላል። ሆኖም ግን ዝርዝሩ ውስጥ ሳንገባ (Adversarial Lawyer) ተሟጋች ጠበቃ በቂና ሁሉን ያካተተ ፖለቲካዊ ውክልና እሳቤዎች ሙሉ በሙሉ እየተገበረ ለመኖር በደምብ የሚስማማ አለመሆኑን ለማየት ከባድ አይደለም። ለሌሎች ደግነትና እርህራሄ የሌለው፣ ባላንጣውን የሚረታበት ጠንካራ የተፋላሚነት ባህሪ የታጠቀ፤ ምናልባትም በውስጡ የገዛ ራሱን በመናቅ ስሜት የሚሰቃይ ሰው። የሌሎችን ጥቅም (ፍላጐት) እና ሀሳብ በቅንነት የርህራሄ ስሜት ትኩረት እንዲሰጥም ሆነ ወይም መርሁ የሚለውን ነገር በጥንቃቄ እንዲከተል ሊጠበቅ የሚችል አይደለም። ህዝባዊ እሴቶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ጥሩ አድርጐ የሚወክለን የሆነ ሰው ከፈለግን የተለያዩ ግላዊ ባህሪያት እና ተሰጥኦዎችን ያሟላ ጠበቃ ነው ማፈላለግ ያለብን።

ጠበቆች እንደ ፖለቲካዊ ወኪል በሚኖራቸው ማና ላይ ባሉት እሳቤዎች ሲመሩ በህዝቡ ህይወት የዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን ተቋማዊ ተደራሽነት በማስፋት እጅግ ዋጋው የላቀ አገልግሎት ይሰጣሉ። የጠበቆች ስራ እንደ ፖለቲካዊ ውክልና ያለውን ጠቀሜታ እና ጠበቆችን ከስራቸው ጋር የሚተሳሰሩ ባህሪያትና ችሎታዎችን የማሰልጠኑ ተግባር አንገብጋቢነት ሁለት አስተማማኝ መሠረት ያላቸው የዘመናዊ ማኅበረሰብ የሚታሰብባቸውን አጠቃላይ እምነቶችን በማስቀመጥ መገንዘብ ይቻላል።

    ህይወት መሰረታዊ ግብአቶች ጤና፣ ትምህርት፣ መጓግዣ፣ ከውጭ ከሚሰነዘር ጥቃት በቂ መከላከያ፣ የአካለ ጉዳት፣ የስራ አጥነትና የእድሜ መግፋት መተዳደሪያ ማግኘት ላልቻሉ ሰዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች በመንግስት ተቋማት መቅረባቸው እየጨመረ በመምጣቱ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሕግ አውጭው በዘመናዊ ማኅበረሰብ ውስጥ እነኚህ መሰረታዊ ህዝባዊ እሴቶች ከፍተኛ ጉልበት ባላቸው የመንግስት ተቋሞች ሲጣሱ ስልታዊ ወይም ሁሉን በበቂ ሁኔታ ያቀፈ ጥበቃ መስጠት አለመቻሉ ነው።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
6119 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 995 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us