ሊፍትና ካሣ

Wednesday, 18 March 2015 13:57

በኪዳኔ መካሻ (የሕግ ባለሙያ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.    

 

  • ያለጥቅም (በነፃ) በሚሰጥ የማጓጓዣ አገልግሎት ጉዳት ቢደርስ ካሣ የሚከፍለው ማነው?
  • ሊፍት ተሰጥቷቸው ሲጓዝ ጉዳት የደረሰበት ተከሳሽ ባለንብረቱ ላይ ያቀረበው የካሳ ክስ በምን ተቋጨ፣
  • ህፃናትን በተመለከተ አሽከርካሪዎች ከሌላው ተሳፋሪ የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ለምን? 

 

1.የሊፍት ነገር

እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? በከተማችን ካለው የትራንስፖርት ችግር አንፃር አሁን አሁን ሊፍት መጠየቅ የሚያሳቅቅ ነገር አልሆነም። በተለይ ማታ እና ጠዋት ሊፍት የሚሰጥ ተገኝቶ ነው? ከግፊያው፣ ከሰልፍ፣ ከመዘግየቱ ይገላግላል። አንዳንዴ ሰው እንደ ጤፍ በፈሰሰበት አይተው እንዳላዩ ለብቻቸው አራት ሰው እግረ መንገዳቸውን ማሳፈር የሚችሉ የግልም ሆነ የመንግስት መኪኖች ሽው ብለው ሲያልፉ፤ “ምን አለበት እግረ መንገዱን የተወሰነ ሰው ቢወስድ ሰው ተቸግሮ እያዩ እንዳላዩ ማለፍ ባህላችን ነው? ምን አይነት ጊዜ ላይ ደረስን ?” የሚል ተሰልፎ ታክሲ ወይም አውቶብስ የሚጠብቅ ሰው አታጡም። “ትራፊኰችስ ትርፍ ብቻ ከሚያሳድዱ ምን አለ ትራንስፖርት ያጣን አይቶ እንዳላየ ከማለፍ በሚል ማታ እና ጠዋት ሊፍት ለመስጠት ከአቅም በላይ ችግር ካላጋጠማቸው በቀር የማይተባበሩትን ቢቀጡ?!” የሚል በትራንስፖርት እጦት የተማረረ ድምፅ ትሰማላችሁ። ይሄ ሁሉ አስተያየት ቢነሳም፤ ዝም ብለው የሚያልፉ አሸከርካሪዎች እንዳሉ ሁሉ የአካባቢያቸውን ችግር ለማቃለል የግላቸውን አስተዋፅኦ በቀናነት ለማበርከት ሊፍት የሚሰጡም ብዙዎች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም።

ለማንኛውም ዛሬ የምናነሳው አያድርስና ሊፍት ተሰጥቶት በነፃ የሚጓዝ ሰውን የጫነው ተሽከርካሪ አደጋ ቢደርስበትና ሊፍት የተሰጠው ሰው ቢጐዳ ኃላፊነቱ የማን ነው? የተሽከርካሪው ባለቤት ወይስ አሽከርካሪው የሚለውን የሚመለከቱ ሁለት እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሱ ጉዳዮችን እናነሳለን።

 

2.በነፃ ተሳፍሮ ካሣ መጠየቅ

ተሽከርካሪው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ንብረት የሆነ ለሥራ ጉዳይ ወደ ሸካ ዞን ሄዶ በነበረበት ጊዜ ውሳኔው ላይ ከየት እስከ የት እንደሆነ ባይጠቀስም አቶ ተመኘሁ እንዳሻውን ሹፌሩ ያሳፍራቸዋል። ሊፍት ሰጥቷቸው ይሁን አንዳንድ ሹፌሮች እንደሚታሙበት ያለመስሪያ ቤታቸው እውቅና በሚያሽከረክሩት መኪና ላይ ገንዘብ ለግላቸው አስከፍለው እንደሚያጓጉዙት አልታወቀም። ብቻ አቶ ተመኘሁ ተሳፈሩና በጉዞ ላይ እያሉ የተሳፈሩበት ተሽከርካሪ በመገልበጡ በእግራቸው ላይ ጉዳት ደረሰ።

ትንሽ ከጉዳታቸው ካገገሙ በኋላ አቶ ተመኘሁ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን በሸካ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ንብረትነቱ የኢ.መ.ባ በሆነውና የኢ.መ.ባ. ሰራተኛ በሆነ ሹፌር ይሽከረከር በነበረው መኪና ተሳፍሬ ስጓዝ መኪናው ተገልብጦ ጉዳት እግሬ ላይ ስለደረሰ ካሣ ይከፈለኝ ሲሉ ከሰሱ።

ተከሳሹ የኢ.መ.ባ በነገረ ፈጁ በኩል ለክሱ በሰጠው መልስ አቶ ተመኘሁ የተሳፈሩበት መኪና ለመንግስት ሥራ የተሰማራ እንጂ ሰዎችን ለማጓጓዝ የተዘጋጀ የንግድ ተሽከርካሪ አይደለም። አቶ ተመኘሁ በመኪናው ላይ የተሳፈሩት ያለአግባብና ለእኔ ለባለንብረቱ ጥቅም በማይሰጥ ሁኔታ ስለሆነ ካሣ የምከፍልበት የሕግ ኃላፊነት የለብኝም አለ።

የሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን መርምሮ የኢ.መ.ባ. ንብረት በሆነውና በሰራተኛው ሲሽከረከር በነበረው ተሽከርካሪ አቶ ተመኘሁ የደረሰባቸውን ጉዳት ኢ.መ.ባ. ካሣ የመክፈል ኃላፊነት አለበት ሲል ወሰነ።

ኢ.መ.ባ. ጉዳዩን በይግባኝ ለማየት ስልጣን ባለው ፍ/ቤት ይግባኝ ቢጠይቅም ፍ/ቤቱ ይግባኙን ሳይቀበለው ስለቀረ ሰኔ 9 ቀን 2000 ዓ.ም የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ይታረምልኝ ሲል ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረበ። ሰበር ሰሚ ችሎቱም ኢ.መ.ባ. በሕግ ካሣ የመክፈል ኃላፊነት አለበት ተብሎ መወሰኑ አግባብ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል። ከውሳኔው በፊት አንድ ሌላ ተመሳሳይ ጉዳይ እንጨምር፤

  

3.የሕፃኑ የሊፍት ጥያቄ

ደረጄ ማሞ የ13 ዓመት ህፃን ነው። እንደ ህፃናት ጊዜውን በትምህርት ብቻ አይደለም የሚያሳልፈው። ጫማ ይጠርጋል። በቀን ቢያንስ 8 ብር ሸቅሎ አባቱን ቄስ ማሞን ይረዳል። አንድ ቀን ይህ ሆነ። ቀኑ ግንቦት 8 ቀን 2002 ዓ.ም ነበር፤ ንብረትነቷ የኢ.ፌ.ድ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሆነችውን ፒካፕ መኪና አቶ ተስፋዬ የተባሉ የምክር ቤቱ ሹፌር እያሽከረከሯት የካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 03/04 የሚገኘው በተለምዶ ብረት ድልድይ ጋር ደረሰች። ደረጄ ለአቶ ተስፋዬ ምልክት ሰጣቸው “ጋሼ ወደ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ከሆኑ ያሳፍሩኝ” ደረጄ ጠየቀ።

አቶ ተስፋዬ “በል እሺ ከኋላ ውጣ” አሉትና ደረጄ የፒካፕዋ ዕቃ መጫኛ ላይ ተሳፈረ። ወደ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አቅጣጫ መኪናዋ መብረሯን ቀጠለች።

ትንሽ እንደተጓዙ አቶ ተስፋዬ የሆነ ነገር ከመኪናቸው ላይ ሲወድቅ ተሰማቸው። መኪናዋን አቁመው ሲያዩ ሊፍት የሰጡት ደረጄ ነበር። መውደቁ ባደረሰበት ጉዳት ብዙም ሳይቆይ ደረጄ በ13 ዓመቱ ከዚህ ዓለም ተሰናበተ።

ቄስ ማሞ የልጃቸው የደጋፊያቸው የደረጄን ሞት ሲሰሙ ዓለም ተደፋባቸው። ልጅ ብቻ አልነበረም ያጡት እርጅና ላደከመው ጉልበታቸው በስተርጅና ያገኙት ምርኩዝ ነበር። አልባሻቸው፣ አጉራሻቸው ደረጄ ነበር። እርማቸውን አውጥተው እንዳበቁ ክስ መሰረቱ።

ቄስ ማሞ ለፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ያቀረቡት ክስ የፒካፕዋን ባለቤት የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ሹፌሩን 1ኛና 2ኛ ተከሳሽ ያደረገ ነበር። ክሱ በምክር ቤቱ መኪና እና በሹፌሩ ምክንያት ልጄ አስተዳዳሪዬ ወድቆ በመሞቱ በቀን 8 ብር ያገኝ ስለነበር እስከ 50 ዓመቱ ለ37 ዓመታት ይሄው በየቀኑ የሚያስገኝልኝ ገቢ ታስቦ ለህክምና ለቀብር ማስፈፀሚያ ካወጣሁት ወጪ ጋር 119ሺህ 870.00 (መቶ አስራ ዘጠኝ ሺህ ስምንት መቶ ሰባ ብር) ካሣ ሁለቱም ተከሳሾች ለጋራ ወይም በነጠላ ይክፈሉኝ የሚል ነበር።

የፌዴሬሽን ምክር በት እኔ በተሽከርካሪው ላይ ሹፌሩ ሰው እንዲጭን አልፈቀድኩም። መኪናም የተሰማራው ለመንግስት ሥራ ጥቅም ነው እንጂ እቃ መጫኛው ላይ ሰው እንዲጭን አይደለም። ህፃን ደረጄ በንብረቴ ላይ መሳፈሩን አላውቅም። ያገኘሁትም ጥቅም የለም ስለዚህ ኃላፊነት የለብኝም ሲል መልስ ሰጠ። 2ኛ ተከሳሽ አቶ ተስፋዬም ጠየቀኝ፣ አሳፈርኩት ወደቀ እኔ ያጠፋሁት ነገር ስለሌለ ልጠየቅ አይገባም የሚል ማስተባበያ መልስ አቀረቡ። የፌ/የመ/ደረጃ ፍ/ቤት ክርክሩን መርምሮ የፌ/ም/ቤትም ሆነ ሹፌሩ አቶ ተስፋዬ ካሣ የመክፈል ኃላፊነት አለባቸው። የካሣው መጠን ግን ስለበዛ በርትዕ ብር 31ሺህ 300 (ሰላሳ አንድ ሺህ ሦስት መቶ ብር) ለቄስ ማሞ ካሣ እንዲከፍሉ ወሰነ።

የፌ/ም/ቤትና አቶ ተስፋዬ ይግባኝ ለከፍተኛው ፍ/ቤት አቅርበው ውሳኔው የሚለወጥበት ምክንያት የለም ስለተባሉ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ። ሰበርም ም/ቤቱና ሹፌሩ ካሣ እንዲከፍሉ መወሰኑ አግባብ ነው አይደለም የሚለውን መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል። የሰበርን ውሳኔዎች ከማየታችን በፊት ለውሳኔው መሰረት የሆነውን የሕግ ድንጋጌ እናንሳ።

 

4.የጥቅም አለመኖር እና ኃላፊነት

ሰዎች በውል ወይም ከውል ውጭ በሚኖራቸው ግንኙነት አንዱ ሌላኛው ላይ በሚፈፅመው ጥፋት ወይም ኃላፊ በሚሆንበት ጉዳይ ጉዳት ሊደርስ ይችላሉ። በውል ግንኙነት ውስጥ ለሚደርስ ጉዳት ተዋዋዮች በውላቸውና በሕግ መሰረት ያደረሱትን ጉዳት የሚክሱበት አግባብ አለ። ከውል ውጭ ባለ ግንኙነት የሚደርስ ጉዳት በፍ/ብ/ሕጉ ከቁጥር 2026 ጀምሮ በዝርዝር ተቀምጧል።

የመጀመሪያው ግለሰቡ በውል ወይም በሕግ ግዴታ ባይኖርበትም በፈፀመው ጥፋት ሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካደረሰ ኃላፊነት እንዳለበት የሚደነግግ ነው።

ሁለተኛው ጥፋት ባይፈፀምም አንድ ሰው በሌላው ሰው ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ስራ በመስራቱ ወይም በይዞታው ስር ያለ ወይም በእጁ የያዘው ንብረት ወይም ሌላ ነገር ጉዳት ካደረሰ ጉዳት ለደረሰበት ሰው ኃላፊ የሚሆንበት ሲሆን፤ ሦስተኛው ደግሞ አንድ ሰው በጥፋቱ ወይም የያዘው ንብረት ወይም የሰራው ስራ ጉዳት ሲያደርስ ለዚህ ሰው ስራ በሕግ ወይም በውል ተጠያቂነት ያለበት አሰሪዎች ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናትን ሞግዚቶች ኃላፊ የሚሆኑበት አግባብ ነው። እነዚህ ከውል ውጭ የሚመነጭ ኃላፊነቶች መሰረታዊ መርሆዎች ሲሆኑ፤ ኃላፊነቱ ተግባራዊ የሚሆንበትን ግንኙነት ከሚወስኑ ሌሎች ድንጋጌዎች መካከል ጥቅም የሌለው ግንኙነትን የሚመለከተው የፍ/ብ/ሕጉ ቁ.2089 ድንጋጌ አንዱ ነው።

የውል ግንኙነቱ ባይኖርም የአንድ ንብረት ባለቤት ወይም ጠባቂ (ንብረቱን በእጁ ይዞ የሚጠቀም ሰው) ባለቤቱ ወይም ጠባቂው ጥቅም በሚያገኙበት ግንኙነት በእንስሳው በህንፃው ወይም በሌላ ንብረቱ ለሚደርሰው ጉዳት የተጐዳው ሰው ሁለቱንም መጠየቅ እንደማይችል የሚደነግግ ሲሆን፤ በዚህ ዓይነት ጥቅም አልባ ግንኙነት ባለንብረትም ሆነ በንብረቱ የሚጠቀም ሰው የሚጠየቀው የፈፀመው ጥፋት ካለ ብቻ መሆኑን የ2089 ድንጋጌ አስቀምጧል።

 

5.ሰበር ምን አለ

የኢ.መ.ባ.ን እና የአቶ ተመኘሁን ክርክር በሰ/መ/ቁ.36 457 ሰኔ 2 ቀን 2001 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል። በውሳኔውም አቶ ተመኘሁ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለማጓጓዝ ባልተመደበው የኢ.መ.ባ. መኪና ተሳፍረው ሲጓዙ ቢሆንም ኢ.መ.ባ. አቶ ተመኘሁ በመኪናው በመሳፈራቸው ያገኙት ጥቅምም የለም። ስለመሳፈራቸውም አያውቅም። በመሆኑም ይህ የጥቅም ግንኙነትና የባለንብረቱ ፍቃድ ወይም እውቅና በሌለበት ኢ.መ.ባ. አቶ ተመኘሁ ላይ ለደረሰው ጉዳት ካሣ መክፈል የለበትም በሚል የሸካ ዞን እና የፌ/ከ/ፍ/ቤት የሰጡትን ውሳኔ ሽሮታል።

የህፃን ደረጄን ጉዳይ ደግሞ ቅጽ 15 ላይ በታተመው በሰ/መ/ቁ. 92020 ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም ውሣኔ ሰጥቶበታል።

አቶ ተስፋዬ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግለት ለሚገባው ሀገራችን በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ሆነ በሕገ መንግስታችን አንቀጽ 36(2) ለህፃናቱ በህይወት የመኖር መብትና የአካል ደህንነት ጥበቃን ሰጥቷል። ይሄን ባለመወጣት አቶ ተስፋዬ ያለጥንቃቄ ህፃን ደረጄን በመጫናቸው ጥፋተኛ ናቸው። እነዚህን ሕጐች ግምት ውስጥ በማስገባት አቶ ተስፋዬም ሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ካሣ የማይከፍሉበት ምክንያት ስለሌለ የስር ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሳኔ በውጤት ደረጃ ትክክል ነው፤ በመሆኑም የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ፀንቷል። ምክር ቤቱና ሹፌሩ በአንድነትና በነጠላ ለቄስ ማሞ ብር 31ሺህ 300 ይክፈሉ ሲል ወስኗል።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
6072 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 851 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us