የአባት ስም

Wednesday, 08 April 2015 12:07

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    ለመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ከትክክለኛ የወላጅ አባት ስም የማይጠሩ ሰዎች ምን የሕግ አማራጭ አላቸው፣

-    የቤተዘመድ ስም በሕጋችን እና በተግባር በስም አጠራራችን ውስጥ ያለው ቦታ ምን ይመስላል?

-    የአባት ስም ለውጥን በማመላከት እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰብር የደረሱ ሁለት አቤቱታዎች በምን ተቋጩ?

-    የአባት ስምን መለወጥ ይቻላል እንዴት?

እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? የዛሬ ወጋችን የሚያተኩረው በስም ላይ ነው። በሕጋችን እውቅና ከተሰጣቸው የማንነታችን መለያዎች ዋነኛው ስም ነው። ለመሆኑ የግል ስምንም ሆነ የአባት ስምን ስለመለወጥ ህጋችን ምን ይላል? የሚለውን እናነሳለን እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርበው አስገዳጅ ውሳኔ የተሰጠባቸውን ሁለት የአባት ስም (የቤተሰብ ስም) ለውጭ ጉዳዮችንም እንመለከታለን። ይመቻችሁ!

1.የሞሚና የአባት ስሞች

ወ/ት ሞሚና አንድ ነገር ችግር ፈጥሮባታል። በተለያዩ ሰነዶች ላይ በአንድ ስም አትጠቀስም። ይህም የሆነው በሁለት የአባት ስሞች ስለምትጠራ ነው የትክክለኛ ወላጅ አባቷ የአቶ ሱልጣን ኮርዋን እና አሳዳጊ አባቷ አቶ ወርቁ ይብሬ ስሞች በተለያዩ ሰነዶች ላይ እየተለያዩ ሞሚና ሱልጣን እና ሞሚና ወርቁ በሚሉ ሰነዶች እንድትታወቅ አድርጓታል። ይሄኔ በሁለት የአባት ስሞች መጠራት አንዷን ሞሚና ሁለት ማንነት እየሰጠ የተለያዩ ችግሮች ስለፈጠረባት የአባቷን ስም ማስተካከል ፈለገች።

ጉዳዩን የማየት ስልጣን ላለው ለአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአሳዳጊዬና በወላጅ አባቴ ስሞች ስጠራ ቆይቻለሁ። በአሳዳጊዬ ስም ሞሚና ወርቁ ይብሬ መባሌ ቀርቶ ሞሚና ሱልጣን ኮርዋላ ተብዬ እንድጠራ ይወሰንልኝ ስትል አመለከተች። ፍ/ቤቱ አቤቱታውን እና የቀረቡትን ማስረጃዎች መርምሮ የሰነድ ማስረጃዎች አመልካቿ አሁንም ቢሆን ሞሚና ሱልጣን ኮርዋላ ተብለው የሚጠሩ መሆኑን ስለሚያሳይ ስም ይቀየርልኝ የሚል ዳኝነት የሚጠይቁበት ምክንያት የለም በሚል መዝገቡን በብይን ዘጋው።

ወ/ት ሞሚና ለከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤትም ሆነ ለከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት የይግባኝ አቤቱታ ቢያቀርቡም ተቀባይነት ባለማግኘቱ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ስህተት በበታች ፍ/ቤቶች ተፈፅሟል። በሁለት የአባት ስሞች መጠራቴ በሰነድ ማስረጃ ቢረጋገጥም የአባት ስሜ እንዲለወጥ ያቀረብኩት ጥያቄ የክስ ምክንያት የለውም መባሉ ያለአግባብ ነው የሚል ነው። ሰበርም በውሳኔው ላይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል፣ አልተፈፀመም የሚለውን ነጥብ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል።

2.የአጎት ስም ወደ አባት ስም፡-

ት/ቤት ለመመዝገብ በአጎቷ ስም የተጠራችው ማህሌት እስከ ዩኒቨርስቲ ድግሪዋ ድረስ በአጎቷ ስም እየተጠራች ተማረች። በወቅቱ ሊሴ ገ/ማርያም መምህር የነበሩት የማህሌት አጎት ልጄ ነች ብለው ትምህርት ለማስመዝገብ ማህሌት ልኡለቃል ገ/ህይወት ተብላ እንድትመዘገብ አደረጉና በዚሁ ስም እስከ ዩኒቨርሲቲ ተምራ ዲግሪ ተቀበለችበት።

እውነተኛው ወላጅ አባቷ አቶ ፈለቀ ደምበል ናቸው፤ እስከ መዋዕለ ህጻናትም ማህሌት ፈለቀ ተብላ ነበር የምትጠራው። ስለዚህ በወላጅ አባቴ ስም እንድጠራ ይወሰንልኝ ስትል ለአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አመለከተች።

ይህ አይነት ጉዳይ በህብረተሰችን ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ነው። በተለያየ ምክንያት ከአባታችን ስም ውጭ በሆነ ሌላ ስም እንጠራለን፤ ማህሌትም ያጋጠማት ይሄው ነበር። ፍ/ቤቱ ምናለ የሚለው እንቀጥል።

የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቱም የቀረቡት የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎችን እንደመረመረበት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 32(2) መሰረት ስልጣን በተሰጠው አካል የተሰጠ ቤተዘመድ ስም የሚገልፅ ማስረጃ አላቀረቡም። ምስክሮችም ልኡለቃል ገብረየሱስ የአጎቷ ስም እንጂ የቤተዘመድ ስም አለመሆኑን ስላላስረዱ አቤቱታው ተቀባይነት የለውም ብሎ የማህሌትን ጥያቄ ውድቅ አደረገው። ማህሌት በየደረጃው ይግባኝ ብታቀርብም የበላይ ፍ/ቤቶች ይግባኙን ባለመቀበል የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ አፀኑ። የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ስትል ማህሌት ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር አቤቱታ አቀረበች።

አቤቱታው ህጋችን አንድ ሰው አንድ ወይም ብዙ የግል ስም የቤተዘመድ ስም እና የአባት ስም እንደሚኖረው ቢጠቅስም የቤተዘመድ ስም በስም አሰጣጥ ባህላችን ስለማንጠቀም የአባት ስምን የቤተዘመድ ስም አድርጎ ይጠቅሳል። በቂ ምክንያት ካለ ፍ/ቤት የቤተዘመድ ስምን እንዲለወጥ መወሰን ይችላል። ስለዚህ ያቀረብኩት ማስረጃ በቂ ሆኖ ሳለ የስር ፍ/ቤቶች ጥያቄዬን ውድቅ ያደረጉት አላግባብ በመሆኑ ውሳኔው ይሻርልኝ የሚል ነበር።

ሰበር አቤቱታውን መርምሮ የሰጠውን ውሳኔ ከማየታችን በፊት ሕጎቻችን በጉዳዩ ላይ የሚሉትን እናንሳ፡-

3.ሕጋችን ስለ ስም

በ1952 የወጣው የፍትህ ብሔር ሕጋችን ስለሰዎችና ስለ መብታቸው በሚለው ክፍሉ የመብት አሰጣጥን የስሞች መብትን ይዘረዝርና በሁለተኛው ምዕራፍ ስለ ስም መዘርዘር ይጀምራል። እንግዲህ ሕጉ መብትና ግዴታ ያለው ሰው እና መብቶቹን ዘርዝሮ በመቀጠል የሰዎች ቀዳሚ መለያ የሆነውን የስም ጉዳይ ያነሳል።

በሕጋችን እውቅና የተሰጣቸው ሶስት የስም አይነቶች ናቸው። የግል ስም፣ የቤተዘመድ ስም እና የአባት ስም። ሕጋችን የተቀዳበት ምእራባውያኑ የስም አጠራር ባህል የቤተዘመድ ስምን እንደ ቋሚ የቤተሰቡ አባላት መለያ የሚጠቀም በመሆኑ የኛ ህግም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 32(2) ላይ ይህንኑ በማንፀባረቅ በአስተዳደር ክፍል ሰነዶች አንድ ግለሰብ የቤተዘመድ ስም የአባት ስም እና የግል ስምን በሚያስቀምጥ ቅደም ተከተል እንደሚጠራ ቢደነገግም በተግባር ግን ይህ ሳይሆን በግል ስም በአባት ስም እና በአያት ስም ነው የምንጠራው።

4.የቤተዘመድ ስም እና የአባት ስም

የፍ/ብሔር ሕጋችን ሕጉ ከመፅናቱ ከመስከረም 1 ቀን 1953 በፊት የተወለደ ሰው የቤተዘመድ ስም እንዲኖረው አይገደድም። ሆኖም ከፈለገ የቤተዘመድ ስም አድርጎ ከአባት በላይ ያሉ የወንድ አያት ቅድመአያቶች ካሉ በእድሜ ታላቅ የሆነውን ሰው ስም የቤተዘመድ ስም አድርጎ እንደሚይዝ በመሻገሪያ ድንጋ አንቀፅ 3358 ላይ ተደንግጓል።

ከመስከረም 1 ቀን 1953 ዓ.ም በኋላ የተወለደ ሰወ ሁሉ ግን አንድ የቤተዘመድ ስም መያዝ ግዴታው እንደሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 335991) ላይ ተደንግጓል። ልጁ ከአባቱ ወደላይ የሚቆጠሩ የቤተዘመድ ስም ከሌለው የአባቱን ስም የቤተዘመድ ስም አድርጎ እንደሚይዝ በንኡስ ቁጥር ሁለት ስር ተደንግጓል።

ህፃኑ ከተካደ ወይም አባቱ ካልታወቀ የቤተዘመድ ስም አድርጎ የሚይዘው የእናቱንየቤተዘመድ ስም ሲሆን እናቱ የቤተዘመድ ስም ከሌላት ደግሞ የአባቱ ስም ለህጻኑ የቤተዘመድ ስም ይሆናል።፡

በእነኚህ ሕጎች መሰረት የተሰጠ የቤተዘመድ ስም በቀጥታ ለዚሁ የቤተዘመድ ተወላጅ ለሆኑ ሁሉ የቤተዘመድ ስም እንደሚሆን የፍ/ብ/ሕ/ቁ 3360 ይደነግጋል

በዚህ መሰረት የቤተዘመድ ስም የሚባለው ሕጋችን ባሰበው መልኩ ከመስከረም 1 ቀን 1953 በኋላ እንዲኖራቸው የሚገደዱበት እና ከዚያ ወዲህ የሚወለዱ የቀጥታ ተወላጆች ሁሉ በቋሚነት የሚይዙት በመስተዳደር ሰነዶች ላይ ቀድሞ የሚጠራና የግል ስምና የአባት ስም የሚከተሉት የአንድ ሰው የመጠሪያ ስም ክፍል ነው በሚል ሊቀመጥ ይችላል።

ሆኖም ሕጉ ከወጣም በኋላ የዘለቀው የስም አጠራር ልምዳችን ሕጉን ለ54 ዓመታት በወረቀት ላይ ብቻ እንዲቀር በማድረግ የግል ስም፣ የአባት ስም፣ የአያት ስም አጠራርን ተከትሏል።

በመሆኑም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 33 (1) መሰረት የልጁ የቤተዘመድ ስም የአባቱ የቤተዘመድ ስም ሲሆን አባቱ የቤተዘመድ ስም ከሌለው ደግሞ የቤተዘመድ ስም የሚሆነው የአባቱ ስም ነው። በመሆኑም ሕጉ ተፈፃሚ ባለመሆኑ በአሁኑ የስም አጠራር ባህላችን አባት ስም እንደ ቤተዘመድ ስም ይቆጠራል ማለት ነው።

የአባት ስም ለውጥ የቤተዘመድ ስም ለውጥ በሚለው በፍ/ብ/ሕጉ አንቀፅ 42 ስር የሚታይ ሲሆን በቂ ምክንያት ካለ እና በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት የማያስከትል ሆኖ ካገኙት በሰውየው ጠያቂነት ዳኞች የአባት ስም እንዲለወጥ መፍቀድ ይችላሉ።

በቂ ምክንያት የሚባሉት በአብዛኛው የሚያጋጥሙት በትክክለኛው ወላጅ አባት ሳይሆን በአሳዳጊ ወይም በሌላ ሰው ስም መጠራት እንዲሁም በጋብቻ ጊዜ ሚስትን በባሏ ቤተሰብ ስም መጥራት እንደምትችልና የራሷን የቤተሰብ ስም መያዝ እንደምትችል የሚደነግገው የፍ/ብ/ሕቁ/40 መሠረት በባሏ የቤተሰብ ወይም በራሷ የቤተሰብ ስም ለመጠራት የምታቀርበው ምክንያት በቂ ሊባል የሚችል ነው።

5.ሰበር ምን አለ?

ስለ ቤተዘመድ ስም ወይም አባት ስም ሕጉ ምን እንደሚል ካየን የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በጉዳዩ ላይ በተሰጡ ክርክሮች የሰጠውን በቅጽ 15 ላይ ታትመው የወጡ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜዎች እንመልከት።

የወ/ት ሞሚናን ጉዳይ በተመለከተ የስር ፍ/ቤት እየተጠራች ያለችው በወላጅ አባቷ ስም መሆኑን ሰነዶች ስለሚያሳዩ ጥያቄው ተቀባይነት የለውም በሚል የሰጠውን ውሳኔ አንድ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች በአባቱ ስም ብቻ ሳይሆን በአሳዳጊውም ስም ሊጠራ የሚችልባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ በትክክለኛ አባቴ ብቻ ልጠራ ብላ ሞሚና ማመልከቷ የክስ ምክንያት የለውም የሚባል ባለመሆኑ ፍ/ቤቱ ጥያቄውን ተቀብሎ መርምሮ መወሰን ሲገባው ውድቅ ማድረጉ አግባብ አይደለም ብሎ የብይን ውሳኔውን በመሻር ጉዳዩን መርምሮ የአባት ስም ለመለወጥ የሚያበቃ በቂ ምክንያት መኖሩን መርምሮ እንዲወስን ለስር ፍ/ቤት መዝገቡን መልሶታል።

የወ/ት ማህሌትን ጉዳይ ደግሞ ማህሌት ለትምህርት ምዝገባ በአጎቷ በአቶ ልኡለቃል ስም መጠራቷንና በሰጡት የምስክርነት ቃል እንዲሁም በሌሎች የሰነድ ማስረጃዎች ተረጋግጦ እያለ የክብር መዝገብ ሹም ባልተደራጀበት አመልካቿ በተወለዱበት በ1979 ቤተዘመድ ስም ልኡለቃል መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ አልቀረበም በሚል ስር ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ የሕግ ስህተተ ያለበት በመሆኑ ተሽሮ አመልካቿ በአጎቷ ስም ማህሌት ልኡለቃል ገብረየስ ተብለው የሚጠሩበት ስም ማህሌት ፈለቀ ደንበል በሚል እንዲቀየር ወስኗል።

    ውሳኔዎቹ በአጭሩ የሚያሳዩት በተለያየ ምክንያት የወላጅ አባታቸው ባልሆነ የአባት ስም የሚጠሩ ሰዎች በቂ ምክንያት አቅርበው በትክክለኛ አባታቸው ስም መጠራት እንደሚችሉ ነው።

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
6972 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 613 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us