ውልና አተረጓጎሙ

Wednesday, 15 April 2015 14:28

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. '; document.write(''); document.write(addy_text21567); document.write('<\/a>'); //-->\n This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    ውል መተርጎም ምንድን ነው?

-    ውል መተርጎም የሚያስፈልገው መቼ ነው?

-    ፍ/ቤት ውሎችን ሲተረጉሙ በምን መልኩ መሆን አለበት?

-    እስከ ሰበር ደርሰው የውል አተረጓጎም ክርክር በምን ተቋጨ?

 

እንዴት ናችሁ ለክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ እንዴት ነበር? መጪው የዳግም ትንሳኤ በዓልም እንደ ፋሲካው ያማረ እንዲሆን ተመኝቼ ወደዛሬው ርዕስ ልግባ።

ዛሬ የምናወጋው ከውል በመነጨ መብትና ግዴታ ላይ አለመግባባት ተከስቶ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሲያመራ ፍ/ቤቶች አከራካሪውን ጉዳይ ለመፍታት ውሉን በምን መልኩ መተርጎም አለባቸው ፍ/ቤቶችስ ውልን በሚተረጉሙ ጊዜ ስልጣናቸው እስከምን ድረስ ነው የሚሉትን ነጥቦች እናነሳለን። በጉዳዩ ላይ እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት የደረሱና አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተሰጠባቸውን ክርክሮችንም እናያለን። መልካም ንባብ።

1.የወፍጮው ብድር ያስነሳው ክርክር፣

ሀጂ አብዱራሃማን በአላባ ልዩ ወረዳ ነጋዴ ናቸው። የወፍጮ ቤት ስራ አዋጭነቱን ስለሚያውቁ ወፍጮ መትከል የሚያስፈልገውን 40ሺ ብር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለመበደር ሃሳብ አቅርበው ባንኩ ተቀበላቸው። ሐምሌ 16 ቀን 1988 ሀጂ እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የ40ሺ ብር የወፍጮ መግዣ የብድር ውል ተዋዋሉ። ገንዘቡን በቀጥታ ለወፍጮ አስመጪው ድርጅት ለመክፈል ባንክ ተስማማ። በዚህም መሰረት ባንኩ ለሰላም የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል 40 ሺ ብር ከፈለና ሀጂ ወፍጮውን ተቀበሉ።

ሀጂ ለስንት ያሰቡት ወፍጮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተበላሸ። ለባንኩ ኧረ ምን አይነት ወፍጮ ነው የገዛችሁት? አንድ ነገር አድርጉልኝ ወይ በሌላ በሚሰሩ ወፍጮ ተኩልኝ ሲሉ ጠየቁ። ሆኖም መፍትሄ ስላላገኙ በአላባ ወረዳ ፍ/ቤት ክስ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ላይ አቀረቡ።

ክሱ ባንኩ ያስፈረመኝ ውሉን ተግባራዊ አላደረገም፤ ውሉ ለህሊና ተቃራኒ እና ተንኮል ባለው ሁኔታ ያስፈረመኝ በመሆኑ ውሉ ይፍረስና ብድሩ ቀሪ ተደርጎልኝ ባንኩም የማይሰራ ወፍጮውን ይውሰድ የሚል ነው።

ባንኩ በሰጠው መልስ ሀጂ የተበደሩኝ ወፍጮ ሳይሆን 40ሺ ብር ነው። ይህንንም የብድር ገንዘብ ለአስመጪው ኩባንያ ስለከፈልኩ ወፍጮው ካልሰራ የብድሩ ስምምነት ይፈርሳል የሚል ግዴታም አልገባሁም። ተፈፀመብኝ ያሉትን ተንኮልም ሀጂ አላብራሩም፤ በመጋቢት 12 ቀን 1993 ዓ.ም የተፃፈው ደብዳቤም ሀጂ በጠየቁት መሰረት ሌላ የወፍጮ መግዣ ብድር ፈቀድኩ እንጂ የተበላሸውን እተካለሁ አላልኩም። ስለዚህ ውሉ ሊፈርስ አይገባም አለ።

የአላባ ልዩ ዞን ወረዳ ፍ/ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የሀጂን ግልፅ የሆነ የኑሮ ልማድ እውቀት ማጣትን በመጠቀም እንዲሁም ባንኩ የመንግስት የልማት ድርጅት በመሆኑ በውል የገባውን ቃል እንደማያጥፍ በማመን የብድር ውል አስፈርሟቸዋል። ወፍጮው ብልሽት ያለበት መሆኑን ቢያውቅ የማይቀበሉትን የብድር ግዴታ እንዲቀበሉ መደረጉ ሆን ተብሎ በማታለል ወይም ሀሰተኛ የማግባቢያ ዘዴ በመጠቀም በተንኮል የተደረገ መሆኑን ካላረጋገጥኩ ውሉ መፍረስ አለበት። ሀጂና ባንኩ ቀጥተኛ የወፍጮ ሽያጭ ውል ባያደርጉም በተዘዋዋሪ መንገድ ውሉ የወፍጮ ብድር መሆኑን ስለሚያመለክት በብድር የተሰጠው ወፍጮም ጉድለት ስላለበት ውሉ ፈርሶ ሀጂም ባንኩም ከብድሩ በፊት ወደ ነበሩበት ሁኔታ ይመለሱ ሲል ወሰነ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በውሳኔው ቅር ተሰኝቶ ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ይግባኝ አቀረበ። ፍ/ቤቱም መዝገቡን መርምሮ የብድር ውሉ የወፍጮ መግዣ ብድር መሆኑን እንጂ የወፍጮው ግዢ በማን እንደተፈፀመ አይገልፅም። ይህ ቢሆን የተዋዋዮቹ ሃሳብ ምን ነበር የሚለው መታየት አለበት። በወፍጮው ርክክብ ሰነድ ላይ ባንኩ ገዥ መሆኑን ያሳያል። ከርክክብ በኋላም ባንኩ ወፍጮው ባለመስራቱ ሻጭ ላይ ክስ መስርቷል። ሀጂ ተገዝቶ የሚቀርብላቸው ወፍጮ የተበላሸ መሆኑን ቢያውቁ የብድር ውሉን አይፈርሙም ነበር። ስለዚህ የስር ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ ጉድለት የለበትም በማለት ውሳኔውን አፀናው።

ባንኩ በፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ውሉ የብድር ሆኖ እያለ የስር ፍ/ቤቶች ውል በመተርጎም ሰበብ ከውል በኋላ ያለውን ሁኔታ ማመዛዘን ያስፈልጋል በማለት የወፍጮ ሽያጩን ባንኩ እንደፈፀመ አርገው በመቁጠር የሰጡት ውሳኔ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል። ሽያጭ እንኳን ተፈፅሟል ቢባል በአንድ ዓመት ውስጥ መቅረብ ስላለበት በይርጋ መታገድ ሲገባው ባንኩ አጭበርብሯል በሚል ማስረጃ ሳይቀርብ መወሰኑ የሕግ ስህተት ስለሆነ ይታረምልኝ ውሳኔው ይሻርልኝ ሲል አመለከተ።

ሰበር ሰሚ ችሎት ባንኩ ባቀረበው አቤቱታ ላይ ሀጂ መልስ እንዲሰጡ አዞ ሀጂም የስር ፍ/ቤት ያቀረቡትን ክርክር የሚያጠናክር መልስ አቅርበው ውሉ ይፍረስ በሚል ስር ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሳኔ የሕግ ስህተት ስለሌለበት ሊፀና ይገባል ሲሉ ተከራከሩ።

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሀጂንና የባንኩን ክርክር መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል ውሳኔውን ከማየታችን በፊት ሕጉ ስለውል አተረጓጎም ያስቀመጣቸው አንቀፆች ምን ይላሉ የሚለውን ላስቀድም።

ውሎች እንዴት ይተረጎማሉ?

ውል ማለት ከሁለት በላይ የሆኑ ሰዎች አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ባላቸው ግንኙነት ንብረት ወይም በገንዘብ ሊገመት የሚችል ግዴታ የሚገቡበት ግንኙነት መሆኑ ከፍ/ብ/ሕ/ቁ 1675 ድንጋጌ መረዳት ይቻላል።

በመሆኑም በሕጉ መሰረት ግዴታና መብቶቹን የሚፈጥሩ ውሎች በተዋዋዮች መሀል የተፈጠሩ እና አስገዳጅነት ወይም ተፈፃሚነት ያላቸው ሕጎች ናቸው። በውሉ ከማይለወጡ አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌዎች በስተቀርም ውሉ ውስጥ የሚሰፍረው ቃል ተዋዋዮቹ የተስማሙበት ነው። ተዋዋዮቹ በውል እንዲለወጥ የማይከለከሉ ሁኔታዎችን በእነሱ ላይ ተፈፃሚ እንዳይሆን በማድረግ በውል ሕጉ ላይ የተቀመጡትን ግዴታዎችን መብቶች ማስፋት ወይም ማጥበብ ሕጉ እስከሚፈቅደው መጠን እንደሚችሉ የውሎችን ውጤት የሚደነግገው የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1731 ያስቀምጣል። በተዋዋዮች መሀል አለመግባባት በሚነሳ ጊዜ ክርክሩ የሚዳኘው በውሉ መሰረት ነው።

በመሆኑም የሚያከራክራቸው ነጥብ ላይ ትርጉም ፍ/ቤቶች መስጠት የሚችሉት ውሉ የተዋዋዮቹን ስምምነት ለመረዳት ግልጽ ካልሆነ ብቻ መሆኑን የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1733 ድንጋጌ ያስረዳል። በመሆኑም የውል ክርክሮችን በሚወስኑበት ጊዜ ስልጣኑ የተሰጣቸው ፍ/ቤቶች በግልፅ በውሉ ላይ ከተቀመጠው በመራቅ የተዋዋዮቹ ሀሳብ ምን ነበር የሚለውን ወስደው መተርጎም አይችሉም።

ሆኖም የውሉ ቃል የሚያሻማና የስምምነቱን ወሰን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል በሚሆንበት ጊዜ ፍ/ቤቶች ውሉን መተርጎም ይችላሉ። ማለትም ውሉ ላይ የሰፈረው ቃል የተዋዋዮቹን ስምምነት ለመግለፅ በቂ በማይሆን ጊዜ የተዋዋዮቹ ውሉን ሲገቡ ሃሳባቸው ምን ነበር? የሚለውን ለማግኘት ግልጽነት የጎደለውን ወይም አሻሚውን ስምምነት የፈጠረውን ክፍተት የሚከተሉትን የውል አተረጓጎም ድንጋጌዎች በመከተል ይሞሉታል።

  1. የቅን ልቦና ትርጓሜ፡- በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1732 ውሎች የሚተረጉሙት በተዋዋዮች መሀል ሊኖረው የሚገባውን የቅንነትና የመተማመን ግንኙነት መሠረት በማድረግና ያለውን ልማዳዊ ስርዓት በመከተል መሆን አለበት የሚለው ቀዳሚ የውል አተረጓጎም መርህ ቢሆን ፍ/ቤቶች የተዋዋዮቹ ቃል በቅንነት እና በታማኝነት የሰፈረ ነው በሚለው መርህ ላይ ሊመሰረቱ ይገባል።
  2. የተዋዋዮች የጋራ ሃሳብ፡-ውል ስምምነት እንደመሆኑ መጠን ተዋዋዮች ሀሳብ የሚያገናኝ ነው። ሆኖምይህ ግልፅ ያልሆነና አሻሚ ሲሆን ሃሳባቸው የተገናኘበት ምን እንደነበር መታወቅ አለበት። ይህንም ለማወቅ ከውል በፊት ወይም በኋላ ተዋዋዮቹ የነበሩበትን ሁኔታ ማመዛዘን እንደሚያስፈልግ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1732 ላይ ተደንግጓል። ውሉ ላይ የተገለፀው ጠቅላላ ሃሳብ ከሆነ ደግሞ መተርጎም ያለበት ሊዋዋሉ የፈለጉበት መስሎ በሚታየው ነገር ብቻ ነው።
  3. የርስ በርስ አተረጓጎም፡- ውሎች ውስጥ የተለያዩ ክፍሎች ይኖራሉ። ከላይ በጠቀስህ መልኩ እያንዳንዱ ይተረጉምና በዚሁ ላይ ተመስርቶ (ይህንኑ ትርጓሜ) በመከተል ሌላኛው ይተረጎማል። በዚህ ጊዜ ሁለት ትርጉም የሚሰጡ ስምምነቶች ካሉ ለውሉ ይበልጥ ተስማሚ የሚሆነውን ትርጓሜ መያዝ እንደሚያስፈልግ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1736 ይገልጻል።
  4. ውጤት የሚሰጥ አተረጓጎም፡-አሻሚ ወይም ግልጽ ያልሆነው ስምምነት ሁለት ትርጉሞች ሲኖሩት ውሉን ትርጉም አልባ ከሚያደርገው ይልቅ ተጨባጭ ውጤት እንዲኖረው በሚያደርገው መልኩ እንዲተረጉም የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1737 ያዛል።
  5. ለባለዕዳው ምቹ የሆነ አተረጓጎም፡-የውል ሁኔታ አጠራጣሪ ከሆነ በውሉ አስገዳጅ ለሆነው ሰው ሳይሆን ለሚገደደው ሰው በሚጠቅም መልኩ ሲሆን ውሉ በውል ሰጪው ብቻ ተዘጋጅቶ የቀረበ ከሆነ ደግሞ ለውል ተቀባዩ በሚጠቅም መልኩ መተርጎም አለበት።
  6. ያለዋጋ የተደረገ ውል፡-አንድ ሰው የገባው ግዴታ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለነፃ የተደረገ ከሆነ ደግሞ ግዴታውን የሚያቀል ትርጓሜ ይሰጠዋል።

ሰበር ምን አለ?

     ከላይ ያነሳነውን በሀጂ አብድራህማን እና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ መሀል የነበረው ክርክር የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/ወ/ቁ 15667 መጋቢት 13/1999 በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ ቅጽ 4 ላ ታትሞ ወጥቷል።

     በውሳኔው በሀጂና በባንኩ መካከል የተደረገው ውል የገንዘብ ብድር ነው። ብድሩም በቀጥታ ለወፍጮ አስመጪው እንደሚከፈል ስለሚገልፅ ግልፅ በመሆኑ ለትርጉም በር አይከፍትም። የባንክ አበዳሪነት ግልጽ ሆኖ እያለ ወፍጮን ማን ገዛው የሚለውን በማንሳት ውሉ ግልፅ እንዳልሆነ አደርገው መተርጎማቸው የስር ፍ/ቤቶች በሕግ ከተሰጣቸው የውል መተርጎም ስልጣን ወሰን ውጭ ነው።

     ባንኩ የመንግስት ተቋም በመሆኑና በሀጂ የእውቀት ማነስ የተነሳ ተንኮል መፈፀሙን የሚያሳይ ማስረጃዎች አልቀረበም። ወፍጮውን ሀጂ ከተረከበ በኋላ የሚገኝበትን ጉድለት ክስ የሚያቀርቡበት ጊዜ በሻጭ የሚነሳ በመሆኑ ባንኩ ሻጭ ስላልሆነ ተቀባይነት የለውም።

     በአጠቃላይ ሰበር ሀጂና ባንኩ ያደረጉት የብድርውል ግልፅ በመሆኑ ትርጉም ስለማያስፈልገው ስር ፍ/ቤቶች በትርጉም ስም የብድር ውሉ እንዲፈርስ የሰጡት ውሳኔ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔን በመሻር የብድር ውሉን አፅንቷል። 

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
6979 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 816 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us