ጣልቃ ገብነት

Friday, 24 April 2015 12:46

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    በሌሎች ሰዎች ክርክር ሶስተኛ ወገኖች ጣልቃ የሚገቡበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

-    ጣልቃ የመግባት መብት ከምን ይገኛል?

-    እስከ ሰበር የደረሰው የጣልቃ ገብነት ክርክር በምን ተቋጨ?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? አንዳንዴ በሆነ ጉዳይ ላይ “አያገባችሁም” ተብላችሁ አታውቁም። ለምሳሌ የሁለት ሰዎች ክርክር ፀብ ወይም ስምምነት ሊሆን ይችላል። ምን ብላችሁ መለሳችሁ? “በዚህ በዚህ ምክንያት ያገባኛል!” ነው እንዴ ሌላ ምን ይባላል። “ጣልቃ መግባት” ብዙም አዎንታዊ ስሜት የሚሰጥ አይደለም። ነገር ግን አንዳንዴ የራስን መብት ወይም ጥቅም ለማስጠበቅ በሌሎች ጉዳይ መካከል መግባት ግድ ይላል። ለመሆኑ በፍ/ብሔር ክርክሮች ላይ በስነስርዓት ሕጉ መሰረት ጣልቃ እንዴት ይገባል? ጣልቃ የመግባት መብትስ ያለው ማነው የሚለው የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ነው። እስከ ሰበር የደረሰ የጣልቃ ገብነት ክርክር እናነሳለን። በጉዳዩ ላይ ሕጉ ያስቀመጣቸውን አንቀጾችም እናነሳና ስለ ጣልቃ ገብነት መሠረታዊ የሕግ እውቀት ይኖረናል ማለት ነው። መልካም ንባብ፡-

1.ሻጭ ተከሳሽ ገዥ ጣልቃ መግባት ይችላሉ

ወ/ሮ እየሩሳሌም አቶ መከተ ላይ ክስ ያቀርባሉ። ክሱ አቶ መከተ የቤት ቁጥር 3936 የሆነው ቤት ላይ ያለኝን መብት ከልክለውኛል ቤቱ የኔ ነው ያስረከቡኝ የሚል ነበር። ቤቱን ደግሞ አቶ መከተ ለአቶ አስፋው ሸጠውታል። አቶ አስፋውም ቤቱን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። የይዞታ ማረጋገጫም አውጥተውበታል። በተጨማሪ ተከሳሽ አቶ መከተ በሰጧቸው ውክልና ጠበቃ ቀጥረው የወይዘሮ እየሩሳሌምን ክስ እየተከራከሩ ይገኛሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የወ/ሮ እየሩስን እና የወኪል ተደራጊያቸው የአቶ መከተን ክስ እያየ ለነበረው ለፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አቶ አስፋው እና ወ/ሮ ፀሐይ ቸከሩ የተባሉ ግለሰብ ወደ ክርክሩ ጣልቃ እንግባ ብለው ያመለክታሉ።

ፍ/ቤቱም የጣልቃ ገብነት ማመልከቻቸው ለዋናዎቹ ከሳሽና ተከሳሽ ለወ/ሮ እየሩሳሌም እና ለአቶ መከተ ምን ትላላችሁ ወደ ክርክራቸው ይግቡ ወይስ አይግቡ አስተያየታችሁን አቅርቡልኝ ሲል ጠየቃቸው።

ወ/ሮ እየሩስ በሰጡት አስተያየት አቶ አስፋው እኔ የከሰስኩት የአቶ መከተ ወኪል ሆኖ ጠበቃ ቀጥሮ እየተከራከረኝ ከቆየ በኋላ በክርክሩ የኔም ጥቅም ነካህ ብሎ ጣልቃ ልግባ የሚልበት የሕግ አግባብ የለም። ወ/ሮ ፀሐይም ጣልቃ ልግባ ያለበት ምክንያት በማስረጃ የተደገፈ ባለመሆኑ ውድቅ መደረግ አለበት ሲሉ ለፍ/ቤቱ አስተያየታቸውን አቀረቡ።

ተከሳሹ አቶ መከተ በበኩላቸው አቶ አስፋውም ሆነ ወ/ሮ ፀሐይ ጣልቃ ቢገቡ አልተወውም ሲሉ ገለፁ።

ፍ/ቤቱም የጣልቃ አስገቡኝ ጥያቄውንና ዋናዎቹ ተከራካሪዎች የሰጡትን አስተያየት ከሕጉ ጋር አገናዝቦ መረመረ። ጣልቃ አስገቡኝ ያሉት አቶ አስፋው የተከሳሹ ወኪል ሆነው በቀጠሯቸው ጠበቃ በኩል ክርክር የተነሳበት የቤት ቁጥር 3936 የሆነው ቤት የአቶ መከተ የግል ቤት ባልሆኑ ለአቶ አስፋው ሸጠውላቸው በእጃቸው እንደሚገኝና አቶ አስፋው (ጣልቃ ልግባ ባዩ) በስማቸው ስለተመዘገበ የወ/ሮ እየሩስ ክስ ውድቅ ይደረግ ብለው በመከራከራቸው ጣልቃ ልግባበት የሚሉት ክርክር መብትና ጥቅማቸውን የሚነካበትን የሕግ አግባብ አያሳይም። በተጨማሪ በተከሳሽነትም በጣልቃ ገብነትም የሚከራከሩበት አግባብ የለም በሚል የጣልቃ ልግባ አቤቱታቸውን ውድቅ አደረገው። ወ/ሮ ፀሐይም ጣልቃ መግባት የሚያስችል ማስረጃ አላቀረቡም በሚል ሳይቀበለው ቀረ።

አቶ አስፋው ጣልቃ እንዳልገባ መከልከሌ አላግባብ ነው ሲሉ ለከፍተኛው ፍ/ቤት ይግባኝ ቢያቀርቡም ፍ/ቤቱ ይግባኙን ስላልተቀበላቸው የሕግ ስህተት ተፈፅሟል፣ ጣልቃ አትገባም የተባልኩት ከሕግ ውጭ በመሆኑ ይታረምልኝ ሲሉ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ። ፍ/ቤቱም የሰበር አቤቱታው ላይ የከሳሽ የወ/ሮ እየሩስ አቶ አስፋው በወከላቸውና በራሳቸው ስም በአንድ ጊዜ መከራከር አይችሉም አለኝ የሚሉት የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተርም በሚመለከተው አካል መክኗል። ስለዚህ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ሊፀና ይገባል ሲሉ አቶ መከተ (ተከሳሹ) ደግሞ አቶ አስፋው ጣልቃ ሊገቡ ይገባል ሲሉ መልስ ሰጡ። የሰበር ፍ/ቤቱ አቤቱታውን ከሕጉ አንጻር መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔውን ከማየታችን በፊት ጉዳዩን የሚመለከተው ሕግ ምን ይላል የሚለውን እናንሳ።

2.ሶስተኛ ወገኖች እንዴት ወደ ክርክር ይገባሉ

በሌሎች ተከራካሪዎች በሚደረግ ክርክር መካከል ተከራካሪ ወገን ያልሆኑ 3ኛ ወገኖች ጣልቃ የሚገቡት ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 41-43 በተደነገጉት ሶስት መንገዶች ነው።

2.1.    ጠይቀው የሚገቡ ሰዎች፡- እነኚህ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 41 መሠረት ክርክሩ እኔንም ያገባኛል የሚለውን ምክንያት ለፍ/ቤቱ አቅርበው ጣልቃ ለመግባት ፈቃድ መጠየቅ የሚችሉ ናቸው።

2.2.    የዐ/ሕግ ጣልቃ ገብነት፡- በተወሰኑ ፍ/ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ሕጉ ዐ/ሕግ መንግሥትን በመወከል ተከራካሪ መሆን እንደሚችል ይፈቅዳል። በመሆኑም ይህ ሕግ በፈቀዳቸው የሰዎች መብት፣ ችሎታ ማጣት፣ ጋብቻ እና ስለኪሳራ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ዐ/ሕግ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 42 መሠረት ጣልቃ ገብቶ የመከራከር ስልጣን ተሰጥቶታል።

2.3.    በፍ/ቤት ታዞ ጣልቃ መግባት፡- አንድ ሰው ለቀረበበት ክስ ሌላ ያልተከሰሰ ሰው እኔ የተከሰስኩበትን የክሱ ኃላፊነት ላይ ይህን ያህል ድርሻ አለው፤ ስለዚህ በተከሳሽ ጣልቃ ገብነት ወደ ክርክሩ እንዲገባ ይታዘዝልኝ ብሎ ፍ/ቤቱን ሲጠይቅ ፍ/ቤቱ ጥያቄውን ከተቀበለው በወሰነው ቀጠሮ ቀርቦ ወደ ክርክሩ ጣልቃ እንዲገባ ያዛል። ጣልቃ ግባ ተብሎ የታዘዘው ሰው በቀጠሮው ቀን ካልቀረበ ፍ/ቤቱ ክሱ እንዲቀርብበትና በክሱ ውስጥ እንዳለ አድርጎ በመቁጠር ውሳኔ ይሰጣል።

እንግዲህ በስነስርዓት ሕጉ በሌሎች ሰዎች ክርክር ጣልቃ የሚገባባቸው ከላይ ያነሳናቸው ሶስቱ አግባቦች ሲሆኑ ጣልቃ መግባት ዓላማው በክርክሩ ተካፋይ መሆኑ ጥያቄው ሊቀርብ የሚችለው በሂደት ላይ ባለ ክርክር ሲሆን ክርክሩ ውሳኔ ካገኘ በኋላ ጣልቃ ልግባ ማለት አይቻልም።

በተጨማሪ ክርክሩ የሌሎች ነውና ጣልቃ ይግባ ባዩ በጉዳዩ ላይ ይገባኛል የሚል መሆን አለበት። በስነስርዓት ሕጉ ቁ 41(2) መሰረትም ያገባኛል የሚልበትን ምክንያት በተለይም በክርክሩ ላይ ያለውን መብት ወይም ጥቅም የሚገልጽ ማመልከቻ ለፍ/ቤቱ ማቅረብ አለበት። ሰው ሳይሆን በሌሎች ሰዎች በሚያደርጉት ክርክር ላይ ለሚያገባቸውና ለምን ጉዳዩ እንደሚያገባቸው ማስረዳት ለሚችሉ ሰዎች የተቀመጠ መብት ነው።

ይህን መብት ለመጠቀም ግን ለፍ/ቤቱ ጥያቄ መቅረብና በሥነሥርዓት ሕጉ ቁጥር 41(3) መሠረት ጣልቃ ገቡ በክርክሩ እንዲገቡ ያቀረብ ምክንያትና ማስረጃ መዝኖ ፍ/ቤቱ መፍቀድ አለበት። ብዙ ጊዜ ፍ/ቤቶች ዋናዎቹ ተከራካሪዎች እንዲሰጡ ያደርጋሉ። ሕጉ ግን የመፍቀድ ያለመፍቀዱን ጉዳይ ለፍ/ቤቶች ስልጣን የተተወ ይመስላል።

የጣልቃ ገብነቱ ጥያቄ ከተፈቀደ ፍ/ቤቱ ጣልቃ ገቡ የሚያቀርበው መከራከሪያ ለዋናዎቹ ተከራካሪዎች እስኪደርሳቸው ክርክሩን ለጊዜው አግዶ ያቆየዋል።

ጣልቃ ገቡ ከተፈቀደለት በኋላ ክርክሩን ለዋናዎቹ ተከራካሪዎች በራሱ ምክንያት ሳያደርሳቸው ከቀረ በራሱ ፍላጎት ጣልቃ መግባቱን እንደተወው ተቆጥሮ መብቱ እንደሚሰረዝ የሥነሥርዓት ሕጉ በቁ 41(4) ላይ ደንግጓል።

ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታና ስርዓት ከላይ የጠቀስኩት ሲሆን በመግቢያችን ላይ ባነሳሁት ክርክር ሰበር ወደ ሰጠው ውሳኔ ልመለስ።

3.ሰበር ምን አለ?

አቶ አስፋው በከሳሽ ወ/ሮ እየሩሳሌም በተከሳሽ አቶ መከተ ጉዳይ ጣልቃ ልግባ በሚል ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ በሰ/መ/ቁ 95934 ግንቦት 18 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቶበት በቅፅ 16 የሰበር ውሳኔዎች ላይ ታትሟል።

    ውሳኔው አቶ አስፋው አቶ መከተ በሰጧቸው ውክልና ጠበቃ ቀጥረው ስለአቶ መከተ ተከራክረዋል። ክርክሩ የአቶ መከተን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ቢወሰን የአቶ አስፋውን መብት የሚነካበት ሁኔታ የለም። የራሳቸውንም መብት እና ጥቅም አንፃር የገዙትን ቤት በራሳቸው ስም ጣልቃ መግባታቸው ክርክሩን ከማጓተት ውጭ ሌላ ጥቅም የለውም። ስለዚህ በስር ፍ/ቤቶች አቶ አስፋው ጣልቃ ሊገቡ አይገባም በሚል የተሰጠው ውሳኔ አግባብ ነው ብሎ የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ አፅንቶታል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
6540 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 715 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us