የስም ማዛወር ጉዳይ

Wednesday, 13 May 2015 11:40

ከኪዳኔ መካሻ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

-    ከማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብትነት ጋር የሚነሱ የምዝገባ ጉዳዮች

-    ስም ማዛወር የሻጭ ወይስ የገዥ ግዴታ

-    የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነትን መዝገብ ግዴታ ያለበትን የአስተዳደር አካል ስም እንዲያዛውር ማስገደድ ይቻላል።

-    ከማይንቀሳቀስ ንብረት (ከቤት) ሽያጭ ስም ዝውውር ጋር እስከ ሰበር የደረሱ ክርክሮች በምን ተቋጩ

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? የዛሬው ወጋችን የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭን ተከትሎ የሚነሳ የስም ዝውውርን ጉዳይ ይመለከታል። ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ሁለት እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደረሱ ክርክሮችን እና የተሰጠባቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እናነሳለን። መልካም ንባብ።

1.ሻጭ ስም እንዲያዛወር የቀረበበት ክስ

አቶ ደግፌ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 06 የነበራቸውን ሕዳር 20 ቀን 1980 በተፃፈ የብድርና የዋስትና ውል ቤቱን መያዣ አድርገው ከአቶ ሳልህ ሀሴን አስራ ሁለት ሺህ ብር ይበደራሉ። በወቅቱ ቤት መሸጥ መለወጥ አስቸጋሪ ስለነበር እስከ ሕዳር 20 ቀን 1990 ብድሩን ከፍለው ለማጠናቀቅ ይስማማሉ። ቤት መሸጥ ሲፈቀድ አቶ ሳልህ ለአቶ ደግፌ ብር 5 ሺህ ጨምረው በድምሩ በብር 17 ሺህ ቤቱን ለመሸጥ ይስማሙና ከቤቱ የእድሳት ወጪ ጋር በአጠቃላይ 18,787.90 ቤቱን ለመሸጥ ይስማማሉ። ቤት መሸጥ በመንግስት የተፈቀደው በ1982 ዓ.ም ነበር።

ሆኖም አቶ ደግፌ የተበደሩትን ብድር ካለመመለሳቸውም ሌላ በአማራጭ የቤቱን ባለቤትነት በስማቸው እንዲያዛውሩላቸው አቶ ሳልህ ቢጠይቁም ፈቃደኛ አልሆኑም።

በመሆኑም አቶ ሳልህ አቶ ደግፌ ላይ ክስ አቀረቡ። በውላችን መሰረት አቶ ደግፌ ግዴታውን ስላልተወጣ ብር 5ሺ ጨምሬለት የቤቱ ባለቤትነት በስሜ እንዲዛወር ይወሰንልኝ ሲሉ ከሰሷቸው። አቶ ደግፌ ክሱ ቢደርሳቸውም ቀርበው መልስ ባለመስጠታቸው በሌሉበት ጉዳዩ ታየ። ፍ/ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ በአቶ ደግፌና በአቶ ሳልህ መሀል የተደረገው የመያዣ ውል ሳይሆን የወለድ አገድ ውል ነው። ውሉ በተደረገበት ወቅት ተፈፃሚ የነበረው አዋጅ ቁጥር 47/67 ወለድ አገድ ውልን የሚከላከል በመሆኑ ውሉ ሕገወጥና ፈራሽ ነው። ተከራካሪዎቹ ወደነበሩበት ይመለሱ አቶ ሳልህ ቤቱን ይመልሱላቸው አቶ ደግፌ ደግሞ ገንዘቡን ይመልስ ሲል ወሰነ።

አቶ ሳልህ በጉዳዩ ቅር ተሰኝተው ይግባኝ ቢጠይቁም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔውን አፀናው። አቶ ሳልህ የሕግ ስህተት ስለተፈፀመ ይታረምልኝ ብለው ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ።

አቶ ደግፌ ቀርቦ ባልተከራከረበት እና ዳኝነት ባልጠየቀበት ቤቱን ይረከብ ተብሎ መወሰኑ ያለአግባብ በመሆኑ ውሳኔው ተሽሮ በውል ያገኙት መብት እንዲጠበቅላቸው ጠየቁ።

አቶ ደግፌ በሰበር አቤቱታው ላይ መልስ እንዲሰጡ ጥሪ ቀርቦላቸው እንደ ስር ፍርድ ቤት ሳይቀሩ ቀርበው የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ሊፀና ይገባል ሲሉ መልስ ሰጡ። ሰበር ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል። ከውሳኔው በፊት ከጐንደር የተነሳውን ሌላ ክርክር እንመልከት።

2.ማዘጋጃ ቤቱ ስም እንዲያዛውር ተከሰሰ

አቶ ፀዳሉ የጐንደር ከተማ ውስጥ ከወ/ሮ ከበቡሽ ጥር 9 ቀን 1989 በተደረገ የሽያጭ ውል ቤት ይገዛሉ። ከዚያም ቤቱን ከባለቤቷ ላይ ስለገዛሁት የባለቤትነት ስሙን በስሜ አዛውሩልኝ ካርታም በስሜ ተሰርቶ ይሰጠኝ ብሎ የጐንደር ከተማ ማዘጋጃ ቤትን ቢጠይቅም ማዘጋጃ ቤቱ ፍቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም በፍርድ ቤት ታገደ የገዛሁትን ቤት በስሜ ያዙርልኝ ካርታም በስሜ አዘጋጅቶ ይሰጠኝ ሲል ከሰሰ።

ክሱ የቀረበለት የጐንደር ከተማ ነክ ፍ/ቤትም የጐንደር ከተማ አቶ ፀዳሉ የጠየቁትን አስተዳደራዊ ተግባሩን እንዲያከናውንና የቤቱን ስም በስማቸው አዙሮ የባለቤትነት ማረጋገጫ በስማቸው እንዲያዘጋጅላቸው ወሰነ። ቤቱን ለአቶ ፀዳሉ የሸጡት ወ/ሮ ከበቡሽ እና ወ/ሮ መና ውሳኔው መብትና ጥቅማችንን ይጐዳል በሚል መቃወሚያ ቢያቀርቡበትም ፍ/ቤቱ መቃወሚያቸውን ባለመቀበል የሰጠውን ውሳኔ አፀናው። እነ ወ/ሮ ከበቡሽ ለከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤትም ሆነ ለአማራ ብሔራዊ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ ቢያቀርቡም፤ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ የሚነቀፍበት ምክንያት የለም በሚል ውሳኔው ፀና።

ከዚያም እነ ወ/ሮ ከበቡሽ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ብለው የሰበር አቤቱታ አቀረቡ። የሰበር ሰሚው ችሎት የጐንደር ከተማ ነክ ፍ/ቤት ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው ወይ? አቶ ፀዳሉ ለማዘጋጃ ቤቱ በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የተረጋገጠ የሽያጭ ውልን አቀርበው ስም ይዛወርኝ፣ ካርታ ይሰራልኝ ብለው የመጠየቅ መብት አላቸው የሚሉትን ነጥቦች ለመመርመር ጉዳዩ ያስቀርባል ብሎ አቶ ፀዳሉን መልስ እንዲሰጡ አዘዘ። አቶ ፀዳሉም ያቀረብኩት ክስ በይርጋ አልታገደም የጠየኩት ዳኘነትም ውልን መሰረት ያደረገ በመሆኑ የጐንደር ከተማ ነክ ፍ/ቤት ለክልሉ ሕግ መሰረት ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው ሲሉ መልስ ሰጡ።

ሰበር የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ የሰጠውን ውሳኔ ከማየታችን በፊት ጉዳዩን የሚመለከቱ ሕጐችን እንመልከት።

3.የማይንቀሳቀስ ንብረት ማስተላለፍ

የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሚባሉት ቤት እና ህንፃ እንዲሁም ያረፈበት የመሬት ይዞታ ነው። የዚህ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ባለሀብትነትን በሕግ ወይም ባለጉዳዮቹ በሚያደርጉት ሕጋውያን ተግባራት (የሽያጭ ውል፣ የስጦታ ውል ወይም ኑዛዜ) እንደሚተላለፉ የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1184 ይደነግጋል። የእነኚህ ንብረቶች ባለሀብትነት በውል ወይም በኑዛዜ ሲተላለፍም በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ማስመዝገብ አስፈላጊ መሆኑን በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1185 ላይ ተቀምጧል። የተለየ አንዳንድ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ባለቤትነትም ለምሳሌ ተሽከርካሪዎች ግዙፍ ማሽኖች እና የመሳሰሉትም ልክ እንደማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነታቸው ሲተላለፍ መመዝገብ አለበት።

ይሄ የማስመዝገቡ አስፈላጊነት የሚመነጨው እነኚህ ንብረቶች ካላቸው ከፍተኛ ኢኰኖሚያዊ ዋጋ አንፃር የባለሀብቶቹን ፍላጐት የገዥና የሻጭን መብት እንዲሁም በእነዚህ ንብረቶች ላይ አስቀድመው የተደረጉ የተለያዩ መብቶተና ግዴታዎች ካሉ ሦስተኛ ወገኖች እንዲያውቁት በማድረግ ነው ግዙፍ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ግን በእጁ ይዞ የሚገኝ ሰው የራሱ እንደሆኑ ሕግ የሚገምት ሲሆን፤ አይደለም የሚል ሰው ስላለመሆኑ ማስረጃ አቅርቦ ማስረዳት አለበት።

የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ባለሀብትነት ምስክር ወረቀት የሚሰጠው ንብረቱ በሚገኝበት ቦታ ያለው የሚመለከተው የመንግስት የአስተዳደር አካል ሲሆን፤ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1195 መሰረት ይህ ምስክር ወረቀት የተሰጠው ሰው የንብረቱ ባለቤት እንደሆነ ይቆጠራል። በአስተደደር ደንብ የሚወሰን የአስተደደሩ ወጪ እና ለሚደርስበት ኃላፊነት ዋስትና የምስክር ወረቀቱን ሲሰጥ የሚከፈል ክፍያ እንዳለም ሕጉ ደንግጓል። የአስተዳደር መስሪያ ቤቱ የባለሀብትነቱን ምስክር ወረቀት ለሌላ ሰው ከመስጠቱ በፊት ቀድሞ ሰጥቶት የነበረው ምስክር ወረቀት እንዲመለስ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1196 መሰረት ማስገደድ ይችላል።

በዚህ መልኩ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ መብት ያገኘ ሰው የባለቤትነት መብቱ እንዲመዘገብለት ንብረቱ በሚገኝበት የማይንቀሳቀስ ንብረት መዝጋቢ አካል ማስረጃዎቹን በማያያዝ ባለሀብትነቱ እንዲመዘገብለትና የባለቤትነት ማስረጃ እንዲሰጠው መጠየቅ ይቻላል።

በመሆኑም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2876 መሰረት በጽሁፍ እና ከሁለት ምስክሮች በላይ ባሉበት የተደረገ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ በውል አዋዋይ ፊት መደረግ አለበት። በተጨማሪ ለ3ኛ ወገኖች ከሽያጩ በኋላ ለሚያነሱት የመብት ጥያቄ መቃወሚያ ሊሆን የሚችለው በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2878 መሠረት ንብረቱ ባለበት ቦታ ባለው የማይንቀሳቀስ መዝገብ ሲመዘገብ ነው።

ሻጭ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1879 መሠረት ያለበት ግዴታ የማይንቀሳቀሰውን ንብረት በገዥ ስም ለማስመዝገብና የስም ዝውውር ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ማንኛቸውንም ሰነዶች መስጠት ሲሆን፤ ይህ ግዴታም የሽያጭ ውሉ ዋና አካል ተደርጐ ይገመታል።

4.ሰበር ምን አለ?

የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአቶ ሳልህ እና የአቶ ደግፌ ጉዳይ የሰበር ውሳኔዎች ቅጽ 8 ላይ ታትሞ በወጣው በሰ/መ/ቁ. 33945 ጥቅምት 20 ቀን 2001 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል። የስር ፍ/ቤት አቶ ደግፌ ቀርበው ያለልጠየቁትን አቶ ሳልህም በግልጽ ባላመለከቱትና ያልጠየቁትን ዳኝነት በመሆኑ በአቶ ደግፌና አቶ ሳልህ መሀል የነበረው የወለድ አገድ ውል ነው። ውሉ በሚደረግበት ጊዜ በነበረው ሕግ ወለድ አገድ ስለተከለከለ ውሉ ፈራሽ ነው። አቶ ሳልህ ቤቱን አቶ ደግፌ ደግሞ ገንዘቡን ይመላለሱ ብሎ መወሰኑን ተችቶ ከሻረው በኋላ አቶ ደግፌ ስም አዛውር ተብለው ሊከሰሱ መቻል አለመቻላቸውን በተመለከተ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነት ማስተላለፉን መዝግቦ የስም ዝውውር የሚፈፀመው የመንግስት አካል እንጂ ሻጭ ነው የሚል ከሕግም ሆነ ከውል የሚመነጭ ግዴታ የለም። ቤቱን የሚመለከቱ ማስረጃዎችንም አቶ ደግፌ እንዳላስረከቡ አቶ ሳልህ አልጠቀሱም። በመሆኑም ስም ዝውውር ይፈጽምልኝ ብለው አቶ ደግፌን የሚከሱበት የሕግ ምክንያት ስለሌለ አቶ ሳልህ ቤቱን የሸጡላቸውን አቶ ደግፌን ስም አዛውር ብለው መክሰስ አይችሉም ሲል ወስኗል።

የወ/ሮ ከበቡሽን እና የአቶ ፀዳሉን ክርክር ደግሞ ቅጽ 11 ላይ በታተመው በሰ/መ/ቁ.     49428 ሕዳር 28 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ የሰጠበት ሲሆን፤ የጐንደር ከተማ ነክ ፍ/ቤት ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው ካለ በኋላ የጐንደር ማዘጋጃ ቤት በሕግ የተጣለበተን የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነትን የመመዝገብ ግዴታውን ስላልተወጣ የቤቱ ገዥ አቶ ፀዳሉ መብታቸውን ለማስከበር ማዘጋጃ ቤቱ ላይ ክስ መመስረታቸውና ፍ/ቤቱም አስተዳደራዊ ተግባሩን ማዘጋጃ ቤቱ እንዲወጣ መወሰኑ አግባብ ነው በሚል በስር ፍ/ቤት ውሳኔውን አጽንቷል።

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
7358 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 848 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us